ሕግጋተ ወንጌል (ክፍል ፮): ውስንነት፣ ጉድለትና መስፈርት በሌለባት ፍጽምት ፍቅር ተዋደዱ

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስድስተኛዋና የመጨረሻዋ በሆነችው ሕገ ወንጌሉ “ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ (ማቴ 5:43-48)” በማለት አስተምሯል። ሕግ ሁሉ በፍቅር ይጠቃለላልና (ገላ 5:14)፣ ፍቅርም የሕግ ፍጻሜ ነውና (ሮሜ 13:10) ይህችን ሕገ ወንጌል ስለፍጽምት ፍቅር አደረጋት። አንድም ፍቅር ሁሉንም ነገር አንድ ላይ ያስተሳስራልና (ቆላ 3:14) ይህችን ሕግ የሕገ ወንጌል ማሠሪያ አደረጋት። አንድም ፍጽምት ፍቅር የፍጹምነት መገለጫ ናትና የሕገ ወንጌሉ መፈጸሚያ አደረጋት።

የፍጽምት ፍቅር ባህርያት

ፍጽምት ፍቅር ወሰን(ገደብ/Limit) ወይም ድንበር (Boundary) የላትም። የሚወዱንንም፣ የሚጠሉንንም፣ የሚያሳድዱንንም እንድንወድ የምታደርግ ናትና። ፍጽምት ፍቅር በሰዎች ማንነት የማትወሰን፣ በጊዜ፣ በቦታና በሁኔታዎች መለዋወጥ የማትቀየር ናት። ፍጽምት ፍቅር ጉድለት (እንከን ወይም ሕጸጽ/Limitations) አልባ ናት። ባልተከፈለ ልብ፣ ባለማበላለጥ በምሉዕነት የምትደረግ ናትና። ፍጽምት ፍቅር መስፈርት የላትም። ቅድመ ሁኔታ የላትም፣ ጊዜ ሁኔታ የላትም፣ ድኅረ ሁኔታም የላትም። ፍጽምት ፍቅር ለወደዱን ወይም ለወደፊት እንዲወዱን ለምንጠብቃቸው ብቻ የምትደረግ አይደለችም። ፍጽምት ፍቅር እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን የወደደባት ፍቅር ናት (ዮሐ 3:16)። ፍጽምት ፍቅር እግዚአብሔር ጠላቶቹ ሳለን እኛን የወደደባት ፍቅር ናት (ሮሜ 5:8)። ይህች ፍጽምት ፍቅሩም ለዘላለም ጸንታ የምትኖር ጽንዕት ናት (መዝ 136:1)።

ፍጽምት ፍቅር እግዚአብሔርን የምንመስልባት ናት (1ኛ ዮሐ 4:8)። ፍጽምት ፍቅር ጌታችን “እኔ እንደወደድኋችሁ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ” ብሎ የሰጠን አዲሲቷ ትዕዛዝ ናት (ዮሐ 13:34-35 15:12)። ፍጽምት የሆነች ፍቅር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መገለጫዋን በዝርዝር ያስተማረላት ናት (1ኛ ቆሮ 13:4–7)። ይህች ፍቅር ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳስተማረን ኃጢአትን የምትሸፍን ናት (1ኛ ጴጥ 4:8)። ፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስም እንዳስተማረን በቃል ብቻ ሳይሆን በሥራና በእውነት የምትገለጥ ናት (1ኛ ዮሐ 3:18)። ፍጽምት ፍቅር ለዘላለም ጸንተው ከሚኖሩት ሦስቱ (እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር) አንዷና የምትበልጠው ናት (1ኛ ቆሮ 13:13)። ፍጽምት ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናት፣ ብዙ ውኃ ያጠፋት ዘንድ አይችልም፣ ፈሳሾችም አያሰጥሙአትም (መኃ 8:6–7)። ፍጽምት ፍቅር የምናየውን ወንድማችንን በመውደድ የማናየውን እግዚአብሔርን የምንወድባት ታላቅ ምስጢር ናት (1ኛ ዮሐ 4:20–21)።

ፍጽምት ፍቅር ስሜታዊ ሳትሆን መንፈሳዊ ናት። ጌታችን በዚህች ሕገ ወንጌል “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ” በማለት እንዳስተማረው ፍጽምት ፍቅር መውደድን፣ መመረቅ (መባረክን)፣ መልካም ማድረግን እና መጸልይን የምታካትት ናት። ይህንንም የምታደርገው ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ይመለሱ ዘንድ ነው። ፍጽምት ፍቅር ምድራዊ ሳትሆን ሰማያዊ ናት። ምድራዊ ፍቅር ሰው የሚወዱትን ብቻ የሚወድባት፣ ወንድሞቹን ብቻ የሚወድባት፣ ቀራጮችና አሕዛብም የሚያደርጓት ናት። ሰማያዊት ፍቅር ግን ክርስቶስ ጠላቶቹ ሳለን እስከሞት ድረስ እንደወደደን እኛም የሚያሳድዱንን ጭምር የምንወድባት ፍጽምት ናት። ጌታችን በዚህች ሕገ ወንጌል አስቀድሞ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ በማለት መሠረትን አነፀ። ከዚያም ጠላቶቻችሁን ውደዱ በማለት ፍጽምት ሕግን ሠራ። በመጨረሻም እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ በማለት የዚህች ሕገ ወንጌል ዓላማ የሰውን ልጅ ፍጹም ማድረግ መሆኑን አስተማረን።

ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ

የዚህ ቃል መነሻው በሕገ ኦሪት “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ (ዘሌ 19:18)” ተብሎ የተገለጸው ነው። ይህ ሕግ ባልንጀራን እንደራስ ስለመውደድ ቢናገርም በአይሁድ ዘንድ በዘመኑ በነበረው ባህልና አስተሳሰብ “ባልንጀራህን (ወዳጅህን) ውደድ፣ ጠላትህን ጥላ” የሚል ትርጓሜ ተሰጥቶት ነበር። ነገር ግን በብሉይ ኪዳን “ጠላትህን ጥላ” የሚል ሕግ ተጽፎ አይገኝም። ይልቁንም “የጠላትህን በሬ ወይም አህያውን ጠፍቶ ብታገኘው በፍጹም መልስለት (ዘጸ 23:4)” ተብሎ ተጽፏል እንጂ። እንዲሁም “ጠላትህ ቢራብ እንጀራ አብላው፥ ቢጠማም ውኃ አጠጣው፤ ፍም በራሱ ላይ ትሰበስባለህና፥ እግዚአብሔርም ዋጋህን ይመልስልሃልና (ምሳሌ 25:21-22)” ተብሎ ተነግሯል እንጂ። ጌታችን “ጠላትህን ጥላ እንደተባለ ሰምታችኋል” ያለው በዘመኑ የነበሩ የአይሁድ መምህራንን ትርጓሜ ጠቅሶ እንጂ በሕገ ኦሪት እንደዚያ ተብሎ አልተጻፈም። ሕግንና ነቢያትን ሊፈጽማቸው መጥቷልና ጠላቶቻችሁን ውደዱ በማለት ይህንንም ሕግ ፍጹም አደረገው።

ጠላቶቻችሁን ውደዱ

ጌታችን “ባልንጀራህን (ወዳጅህን) ውደድ” የሚለውን ሕገ ኦሪት ፍጹም ሲያደርገው “በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን (የሚጠሏችሁን) ውደዱ” በማለት አስተማረ። ይህ የእግዚአብሔር ልጆች የሚያደርገን ሕግ እንደሆነ ሲያረጋግጥልን ነው “በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ” ያለው። እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ቅድመ ሁኔታ የሌለው ፍጹም ነው። እርሱ ለማንም ሳያዳላ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ያለ አንዳች ልዩነት ዝናቡን ያዘንባልና። እኛም እርሱን እንድንመስል፣ የእርሱም ልጆች እንሆን ዘንድ ባልጀራህን ወደድ የምትለውን ሕግ ፍጹም አድርጓት “ጠላቶቻችሁን ወደዱ” በማለት አስተማረን። ወዳጆቻችንን ብንወድ ስለወደዱን ወይም ስለሚወዱን ነው። ታዲያ ዋጋችን ምንድነው? ለወዳጆቻችን መልካም ብናደርግ መልካም ስላደረጉልን ወይም ስለሚያደርጉልን ነው። ታዲያ ዋጋችን ምንድን ነው? ወዳጆቻችንን ብናመሰግን መልሰው ያመሰግኑናል። ታዲያ ዋጋችን ምንድን ነው? ይህንን ሁሉ ለሚጠሉን ብናደርግ ግን በእውነት ዋጋችን በሰማይ ነው።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዘጠኝ የፍቅር ደረጃዎችን አስተምሯል። እነርሱም ክፉ አለማድረግ፣ ክፉ ላደረገብን ተመጣጣኝ መልስ ከመስጠት መቆጠብ፣ ክፉን በክፉ መመለስን መተው፣ ክፉውን መቀበል (መታገስ)፣ ከዚህም የክፋውን መቀበል (መታገስ)፣ ክፉ አድራጊውን አለመጥላት፣ ክፉ አድራጊውን መውደድ፣ ለክፉ አድራጊው መልካም ማድረግ፣ ለክፉ አድራጊው መጸለይ ናቸው። ይህ ሊቅ ስለዚህች ስለስድስተኛዋ ሕገ ወንጌልም ሲናገር “የስነምግባርን ደረጃ ምን ያህል ከፍ እንዳደረገው ተመልከቱ። ጠላቶቻችሁን አትጥሉ ብቻ አላለም። ጠላቶቻችሁን ወደዱ አለን እንጂ” ብሏል። እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና የሚለውንም ሲያብራራ “እንመስለው ዘንድ እርሱ መልካምነቱን የሚያሳይበትን መንገድ አስተዋላችሁን? የሚወዷችሁን ብቻ ብትወዱ ምንም ታላቅ ነገር እያደረጋችሁ አይደለም። ጠላቶቻችሁን ብትወዱ ግን እግዚአብሔር ትመስሉታላችሁ። ለጠላቶቻችን መልካም ከማድረግ በላይ እግዚአብሔርን እንድንመስል የሚያደርገን ነገር የለም” ብሏል።

የሚረግሙአችሁንም መርቁ

አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን “ፈራጆችን አትስደብ፥ የሕዝብህንም አለቃ አትርገመው (ዘጸ 22:28)” በማለት እስራኤል ጠላቶቻቸውን እንዳይረግሙ የተሰጣቸው ሕግ ነበር። ጌታችን ይህንን ሕግ “የሚረግሙአችሁንም መርቁ” በማለት ፍጹም አደረገው። እግዚአብሔር ክፉዎችንና በጎዎችን በበረከቱ ይጎበኛልና እኛም የእርሱ ልጆች እንሆን ዘንድ የሚረግሙንን አለመርገም ብቻ ሳይሆን እንድንመርቅ አስተማረን። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚህ ሲናገር “የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፥ መርቁ እንጂ አትርገሙ (ሮሜ 12:14)” ብሏል። እንዲሁም “በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን፤ ሲሰድቡን እንመርቃለን፥ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፥ ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን (1ኛ ቆሮ 4:12)” በማለት ጌታችን ያስተማረውን በተግባር ፈጽሞታል። ቅዱስ ጴጥሮስም “ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና (1ኛ ጴጥ 3:9)” በማለት የሚሰድቡንን እንድንባርክ (እንድንመርቅ) አስተምሯል። ይህ ማለት ክፉ ለሚናገሯችሁ መልካም ቃልን እንጂ ክፉን አትመልሱ ማለት ነው። ክፉ የተናገሩንን በሌሉበትም ቢሆን ስለእነርሱ መልካም እንጂ ክፉ መናገር የለብንም። ፍቅር ከልብ እንጂ ለዓይነ ሰብእ ብቻ ተብላ የምትደረግ አይደለችምና።

ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ

ጌታችን በዚህች ፍጽምት በሆነችው ስድስተኛዋ ሕገ ወንጌል ለሚጠሉን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም መልካምን እንድናደርግ አስተምሮናል። መልካም ማድረግ መልካም ከመናገር በላይ ፍቅርን ይገልጻል። እርሱ ለክፉዎችም ለደጎችም መልካሙን ሁሉ እንደሚያደርግ እኛም የእርሱ ልጆች ለሚጠሉን ጭምር መልካምን በማድረግ እንድንመስለው አስተምሮናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላቲያ ሰዎች “እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ (ገላ 6:10)” በማለት እንደጻፈላቸው ለሰው ሁሉ (ለሚወዱንም ለሚጠሉንም) መልካምን ልናደርግ ይገባናል። እንዲሁም ለዕብራውያን ሰዎች “ነገር ግን መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና (ዕብ 13:16)” እንዳለው መልካምን በማድረግ እግዚአብሔርን ደስ ልናሰኘው ይገባናል። ጠቢቡ ሰሎሞንም ስለዚህ “ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ማድረግ አትከልክል፥ ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን (ምሳ 3:27)” በማለት ለማንኛውም ለተቸገረ ሰው መልካምን ማድረግ እንደሚገባ ጽፏል።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ጠላትህ ቢራብ አብላው (ሮሜ 12:20)” የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት ሲያብራራ “በቀልን መተው ብቻ ሳይሆን ለሚጠሉት መልካምን ማድረግ የክርስቲያን ምልክቱ ነው። ክፉውን በመልካም በማሸነፍ የእግዚአብሔር ልጆች እንሆናለንና” በማለት አስተምሯል። እንዲህ በማድረግን በራሱ ላይ የእሳት ፍሕም ትከምራለህ የሚለውንም ሲተነትነው “ጠላትህን ስታበላው ራስህን የምትጠቅመውን ያህል እየጠቀምከው አይደለም። በራሱ ላይ የእሳት ፍሕም እየከመርክ ነው እንጂ። ይህም ፍሕም የሚያቃጥለው ሳይሆን ልቡን የሚያቀልጥ (የሚያራራ) ነው” ብሏል። እንዲሁም ጠላትን የመውደድ ደረጃዎችንም ሲያብራራ “ጠላትን መውደድ አራት ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው ማንንም ለመጉዳት አለመነሳት ነው። ሁለተኛው ጉዳት ሲደርስብን አለመበቀል ነው። ሦስተኛው ለሚጎዱን ሰዎች መልካምን ማድረግ ነው። አራተኛውና ክፍተኛው ደረጃ የሚያደርሱብንን ጉዳት በደስታ መቀበል ነው” ብሏል።

ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ

ጌታችን በዚህችው ፍጽምት በሆነችው ሕገ ወንጌል “ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ” በማለት አስተምሯል። እርሱም ለሚሰቅሉት አይሁድና የካህናት አለቆች “አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው (ሉቃ 23:34)” በማለት ፍጹም አብነት ሆኖናል። ጌታችንን አብነት ያደረገው ቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስም ለሚወግሩት አይሁድ “ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው” ብሎ በታላቅ ድምፅ በመጸለይ ምህረትን ለምኖላቸዋል (ሐዋ 7:59-60)። በእውነት ከዚህ በላይ ለጠላት መጸለይስ ምን አይነት ምሳሌ ይገኛል? በብሉይ ኪዳንም የነበረው ጻድቁ ኢዮብ ላሳዘኑት ወዳጆቹ ቢጸልይ እግዚአብሔርን የነበረውን እጥፍ አድርጎ መልሶለታል (ኢዮብ 42:10)። ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስም አስቀድሞ “ለነፍሴ ጕድጓድ ቈፍረዋልና በውኑ በመልካም ፋንታ ክፉ ይመለሳልን? ስለ እነርሱ በመልካም እናገር ዘንድ ቍጣህንም ከእነርሱ እመልስ ዘንድ በፊትህ እንደ ቆምሁ አስብ (ኤር 18:20)” በማለት የተናገረው ይህንኑ የሚያጠናክርልን ነው።

ለእኛ ለክርስቲያኖች ዋናው ጠላታችን ዲያብሎስ እንጂ የሚጠሉን ሰዎች አይደሉም። የሚጠሉን ሰዎችማ እንደ እኛ ሰዎች ስለሆኑ እውነትን ቢያውቁና ወደ ልባቸው ቢመለሱ እንደ እኛ ክርስቲያኖች ሆነው፣ ምናልባትም ከእኛ በተሻለ እግዚአብሔርን ሊያስደስቱ የሚችሉ ናቸው። ሐኪም ሕመምተኛን ለማከም ሕመምተኛውን ሳይጎዳ በሽታውን ያመጣውን ተዋስያን ለይቶ የሚያጠፋ መድኃኒት እንደሚሰጠው ሁሉ እኛም የክፉ ነገር ሁሉ አመንጪ ከሆነው ከዲያብሎስ ይድኑ ዘንድ ለጠላቶቻችን ልንጸልይላቸው ይገባል። ስለዚህ የበደሉንን ይቅር ማለት ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔርም ጋር ይታረቁ ዘንድ፣ እንደ ሳውልም ከአሳዳጅነት ተመልሰው ያገለግሉት ዘንድ እንድናማልዳቸው ነው ጌታችን ለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ ያለው። እርሱ ማንም እንዲጠፋ አይሻምና።

የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ

ጌታችን “የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን?” በማለት ያስተማረው የሚወዱንን መውደድ ተፈጥሯዊና ማንኛውም ሰው የሚያደርገው ስለሆነ እኛ ክርስቲያኖች ከዚያ በላይ ሄደን የሚጠሉንንም እንድንወድ ነው። በወቅቱ ቀራጮች ኃጢአተኞች ተደርገው ይወሰዱ ስለነበር “ ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን?” በማለት ከቀራጮች የተሻልን እንድንሆን አስተምሮናል። እንዲሁም “ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን?” በማለት ፍቅራችን ከአሕዛብ ፍቅር የተሻለች መሆን እንዳለባት አስተምሯል። ሰውን እጅ መንሳት (ሰላም ማለት) የአክብሮት፣ የመውደድና የሰላማዊ ግንኙነት መገለጫ ነውና ሰዎች ሲጣሉ ሰላም መባባል ያቆማሉ። ጌታችን ግን ይህንን ልማድ ወደ ፍጽምት ፍቅር ሲቀይረው የሚጠላችሁን ሰውም ሰላም በሉት ብሏል። 

በመጨረሻም “እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ” በማለት ፍጽምት ፍቅርን ገንዘብ እንድናደርግ ሕገ ወንጌልን ሠራልን። ይህች ፍጹም ፍቅር ወንጌላዊው ዮሐንስ በመልእክቱ “ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል (1ኛ ዮሐ 4:10-11)” በማለት የገለጻት ናት። ፍጹም ፍቅር ጌታችን “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም (ዮሐ 15:13)” በማለት የገለጻት፣ በመስቀልም ላይ ቤዛ ሆኖ ሰውን ያዳነባት ናት። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት (ቆላ 3:14)” እንዳለው ፍርሃት የሌለባትን ፍጽምት ፍቅር ገንዘብ አድርገን የሰማዩ አባታችን ልጆች ልንሆን ይገባናል።

ማጠቃለያ

በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች የሚጠሉንን (ጠላቶቻችንን) ይቅርና የሚወዱንን (ወዳጆቻችንን) እንኳን ከልባችን እንወዳለን ወይ? እንኳን ከጠላቶቻችን ጋር ሰላም ልንመሠርት ይቅርና ከወዳጆቻችን ጋር ያለንን ሰላም ለማስቀጠል ተቸግረናል። አሕዛብ (የማያምኑ ሰዎች) ያደርጉታል የተባለውን የሚወዱንን መውደድ እንኳን ካቃተን፣ ይህንንማ ቀራጮችስ ያደርጉት የለምን የተባለውን ማድረግ ከተሳነን፣ በእውነት ግብራችን ክርስትናችን ያለበትን ደረጃ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየን ነው።

ጌታችን የእግዚአብሔር ልጆች ትሆኑ ዘንድ ወዳጆቻችሁን ብቻ ሳይሆን ጠላቶቻችሁንም ውደዱ ብሎ አስተምሮናል። ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ደግሞ በተቃራኒው ጠላቶቻችንን ብቻ ሳይሆን ወዳጆቻችንንም ጭምር እንድንጠላ ይጎተጉተናል። ክርስቶስ በደሙ የዋጀን እኛ ክርስቲያኖች ግን ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ “ዲያብሎስን ግን ተቃወሙት ከእናንተም ይሸሻል፤ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል (ያዕ 4:7-8)” በማለት እንዳስተማረን በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረን፣ ክርስቶስም የሞተለትን የሰው ልጅ ሁሉ ከልባችን በመውደድ ዲያብሎስንም ልንቃወመው፣ ወደ እግዚአብሔር ልንቀርብ ይገባናል።

ፍጽምት ፍቅር ከዓለም ለይታ የእግዚአብሔር ልጆች የምታደርገን ናት። ፍጽምት ፍቅር እግዚአብሔር ፍጹም እንደሆነ እኛም ፍጹማን ሆነን እርሱን የምንመስልባት ናት። ይህች ሕገ ወንጌል ጽድቃችን ከፈሪሳዊያን፣ ከአሕዛብ እንዲበልጥ ታደርጋለች። ይህችን ሕገ ወንጌል በመፈጸም ጌታችን ጽድቃችሁ ከፈሪሳዊያን ጽድቅ ካልበለጠ ወደ መንግሥተ ሰማያት አትገቡም ያለውን አልፈን ለመንግሥተ እግዚአብሔር እንበቃለን። ይህችን ሕገ ወንጌል በመፈጸም የእግዚአብሔር ልጆች እንሆናለን። ልጆቹ ከሆንን ደግሞ የመንግሥቱ ወራሾች ነን። ይህችን ሕገ ወንጌል በመፈጸም ፍጹማን እንሆናለን። የሕግ ፍጻሜ የሆነችውን ይህችን ሕገ ወንጌል ፈጽመን የመንግሥቱ ወራሾች ለመሆን ያብቃን። አሜን።

Leave a Reply