ጌታችን በዚህ በስምንተኛው አንቀጸ ብፁዓን “ብፁዓን እለ ይሰደዱ በእንተ ጽድቅ፡ እስመ ሎሙ ይእቲ መንግሥተ ሰማያት/ስለጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።” (ማቴ 5:10) በማለት አስተምሯል። ጽድቅ ማለት እውነት፣ እርግጠኛ ነገር፣ ቅንነት ማለት ሲሆን ሰው በእግዚአብሔር ታምኖ በፊቱም ክብርና ሞገስ የሚያስገኝለት በጎ ሥራ ጽድቅ ይባላል፡፡ በግዕዙ “እለ ይሰደዱ” (የሚሰደዱ) የሚለው ቃል በዕብራይስጥ הנרדפים ፣ በግሪክ δεδιωγμένοι ሲሆን ቀጥታ ትርጉሙ መከራ የሚቀበሉ፣ የሚሳደዱ (the persecuted) የሚል ነው። ከዚህ አንጻር ‘ስለጽድቅ የሚሰደዱ’ የሚለው እውነትን በመያዛቸው፣ እውነትን በመናገራቸው፣ ለእውነትና ለፍትሕ በመቆማቸው፣ ወይም በጎ ምግባርን በማድረጋቸው ምክንያት ወይም እውነትን ፍለጋ (ለማግኘት) መከራ የሚቀበሉትን ሁሉ ያመለክታል።
አንድም ጽድቅ የሚባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ እርሱ ጸሐየ ጽድቅ ነውና (ኤር 23:6 2ኛ ቆሮ 5:21)። ከዚህም አንጻር ስለጽድቅ የሚሰደዱ ማለት ክርስቶስን በማመናቸውና በመከተላቸው፣ ትዕዛዛቱን በመፈጸማቸው፣ ክርስቶስን በመስበካቸው ወይም እርሱን የበለጠ ለማገልገል ብለው መከራ የሚቀበሉትን ያመለክታል። የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲያስተምር “በአንጾኪያና በኢቆንዮን በልስጥራንም የሆነብኝን የታገሥሁትንም ስደት ታውቃለህ፤ ጌታም ከሁሉ አዳነኝ። በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።” (2ኛ ጢሞ 3:11-12) ብሏል። ስለዚህም እውነት ስለሆነው ክርስቶስ መከራ የሚቀበሉ ንዑዳን፣ ክቡራን ፣ የተመሰገኑ ናቸው፥ መንግስተ ሰማያት የእርሱ ናትና። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንዳብራራው ጌታችን “ስለጽድቅ የሚሰደዱ” ብቻ ብሎ መከራ የሚያደርሱትን ወይም የሚያሳድዱትን አካላት አለመግለጹ የተጋድሎ ዋናው ጉዳይ ዓላማው (“ስለጽድቅ መሆኑ”) እንጂ የአሳዳጆቹ ማንነት ስላልሆነ ነው። በአሕዛብም፣ በመናፍቃንም፣ በሚያምኑትም፣ በማያምኑትም መሳደድ ዓላማው ጽድቅ እስከሆነ ድረስ ዋጋው መንግሥተ ሰማያት ናት። ይልቁንም የሚያምኑትን ወገኖች በኃጢአታቸው ምክንያት ገስፆ መከራን የሚቀበል የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን በረከት ያገኛል።
“ስለጽድቅ” የምትለው የጌታችን ቃል ሰማዕትን ከወንበዴ የምትለይ እጅግ ታላቅ ቃል ናት። የሰማዕትና የወንበዴ ስቅላት ቅጣቱ አንድ አይነት ሊሆን ይችላል። ዓላማው ግን የተለያየ ነው። የሰማዕቱ ለጽድቅ ነው። የወንበዴው ግን ለበደለው በደል ቅጣት ነው። ሰማዕቱ ሽልማት ይጠብቀዋል። ወንበዴው ግን ንስሐ ካልገባ ይህ ዕድል የለውም። ጌታችን በመስቀል የተሰቀለው ስለእውነት ነው። የሁለቱ ወንበዴዎች ግን ለቅጣት ነበር። የሦስቱም ፍርድ ግን ስቅላት ነበር። የጌታችን ስቅላት ዓላማው ሰውን ለማዳን ነው። በመስቀሉም ሰውን ከራሱ ጋር አስታርቆበታል። ስለዚህም መስቀሉ የፍርድ ዙፋን ሆናው “ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ (እስከዚያ ድረስ ስለበደሌ ስሰቀል ልኑር ማለቱ ነው)” ላለው ፊያታዊ ዘየማን “ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ” አለው።
የክርስትና ሕይወት የፈተና፣ የመከራና የተጋድሎ ሕይወት እንጂ ዛሬ የምድራዊ ሀብትና የዕውቅና ምንጭ እንደሆነው የተድላና የደስታ የመወዳደስ ሕይወት አይደለም። ጌታችን ስለዚህ የክርስትና መንገድ ሲያስተምር “ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።” (ማቴ 7:14) በማለት ነው የገለጸው። እንዲሁም የክርስትና ሕይወት መከራ የበዛበት መሆኑን ሲያስተምረን “ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።” (ማቴ 5:10) በማለት ነው የተናገረው። እውነተኛው መንፈሳዊ ሕይወት የክርስቶስን መከራ መስቀል መሸከም እንጂ የተደላደለን ኑሮ በምድር ላይ መኖር አይደለም። ለዚህም ነው ጌታችን “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” (ማቴ 16:24) በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማራቸው። ከእርሱ የተማሩትና እርሱን በእግርም በግብርም የተከተሉት ሐዋርያት ደግሞ “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል።” (ሐዋ 14:22) ብለው አስተምረውናል፣ በሕይወታቸውም መከራን በመቀበል አርአያ ሆነውናል።
ሁሉን ትተው መስቀሉን ተሸክመው ክርስቶስን ያገለገሉ ቅዱሳን ስምዐ ጽድቅ (የጽድቅ ምስክር) ተብለዋል። ጻድቁ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ከእነዚህ የጽድቅ ምስክሮች መካከል አንዱ ናቸው። ኢትዮጵያን በወንጌል በማብራታቸው ‘ሐዲስ ሐዋርያ’ ተብለዋል። ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ለማመልከት “ወንጌለ መለኮት ሰበከ፣ ስምዐ ጽድቅ ኮንከ፣ ወበእንተዝ ተክለ ሐይማኖት ተሰመይከ /የመለኮትን ወንጌል አስተማርክ የጽድቅ ምስክርም ሆንክ ስለዚህ ተክለ ሃይማኖት ወይም የሃይማኖት ተክል ተብለህ ተጠራህ/” እያሉ በዝማሬ የጽድቅ ምስክርነታቸውን ይመሰክሩላቸዋል።
ጽድቅ የሚገኘው እውነተኛ እምነትን ከበጎ ምግባር አስተባብሮ በመያዝ ነው።
ጽድቅ የሚገኘው በርትዕት እምነትና በበጎ ምግባር ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ “ወንድሞቼ ሆይ፥ እምነት አለኝ የሚል፥ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው። አንተ ከንቱ ሰው፥ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፥ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን?መጽሐፍ፥ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅ ሆኖም ተቈጠረለት የሚለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ፤ ሰው በሥራ እንደሚጸድቅ በእምነት ብቻም እንዳይደለ ታያለህን? እንዲሁ ዘማይቱ ረአብ ደግሞ ጕበኞችን ተቀብላ፥ በሌላ መንገድ ባወጣቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ፥ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።” (ያዕ 2:14-26) በማለት ጽድቅ በእምነትና በበጎ ሥራ እንደሚገኝ ተነግሯል።
ጌታችንም በወንጌሉ ከሁሉ አስቀድመን መንግሥቱንና ጽድቁን መፈለግ እንደሚገባን ሲያስተምር “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።” (ማቴ 6፥33) በማለት ነበር። እንዲሁም “ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም።”(ማቴ 5:20) በማለት በተራራው ስብከቱ አስተምሯል። ስለመጥምቁ ዮሐንስ መንገድም ሲናገር “ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ መጥቶላችሁ ነበርና፥ አላመናችሁበትም፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ግን አመኑበት፤ እናንተም ይህን አይታችሁ ታምኑበት ዘንድ በኋላ ንስሐ አልገባችሁም” (ማቴ 21:32) ብሏል። ስለመንፈስ ቅዱስም “እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም፥ ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው።” (ዮሐ 16:8-10) በማለት አስተምሯል።
ብርሃነ ዓላም ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ “የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፥ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው።” (1ኛ ጴጥ 3: 12) በማለት ጻድቃን በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደዱ እንደሆኑ አስተምሯል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ስለጽድቅ ሲያስተምር “ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና። አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥ እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ። እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥ ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው።” (ሮሜ 3:20-26) ብሏል። “እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ” ማለት ግን ለአንዳንዶች እንደሚመስላቸው ምግባር አያስፈልግም ማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል። አይሁድም አሕዛብም ለጽድቅ የሚያበቃ ሥራ ስላልነበራቸው ሁለቱም ያለልዩነት የሚድኑት እንደ አይሁድ በምግባር በመመካት ሳይሆን በክርስቶስ ቤዛነት በማመን መሆኑን ለማሳየት ነው እንጂ።
“በመጨረሻው የፍርድ ቀን የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፥ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል። ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና። ጻድቃንም መልሰው ይሉታል፦ ጌታ ሆይ፥ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ?” (ማቴ 25፣ 31-36)። ይህም ጽድቅ የሚገኘው በእምነት ብቻ ሳይሆን በእምነት ሆኖ በሚፈፀም ምግባርም ጭምር መሆኑን ያረጋግጥልናል።
ይህ አንቀጸ ብፁዓን በስደትም ይተረጎማል።
ይህ ስምንተኛው አንቀጸ ብፁዓን በዋናነት ስለጽድቅ መከራን መቀበልን (Persecution) የሚመለከት ቢሆንም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከስደት ጋር አያይዘውም ይተረጉሙታል። ስደት መከራ ነውና። ስደት አንዱ የሰማዕትነት ዓይነት ሲሆን በሁለት ዓይነት ተከፍሎ ሊታይ ይችላል። እነዚህም የአካል ስደት እና የልቡና (የመንፈስ) ስደት ናቸው። የአካል ስደት በአካል ከሚኖሩበት ቦታ ወደሌላ ቦታ መሸሽን/መሄድን ያመለክታል። የልቡና (የመንፈስ) ስደት ደግሞ ከነበሩበት የልቦና አቋም ተነቅሎ ወደሌላ አመለካከት መሄድን ያሳያል። የአካል ስደት በተለያየ ምክንያት ከሚኖሩበት ቦታ ወደ ሌላ ቦታ፣ ሀገር ወይም አህጉር መሄድ ነው። የልቡና ስደት ግን በአካል ቦታ ሳይቀይሩ ጭምር ከያዙት እምነት፣ ዓላማ ወይም የሕይወት መንገድ ተነቅሎ ወደ ሌላ መሄድ ነው። አንዳንድ ስደት ደግሞ የአካልም የልቡናም ሊሆን ይችላል።
ከጽድቅ አንጻር ስደትን በአራት መደብ ከፍሎ ማየት ይቻላል። የመጀመሪያው ስደት ወደ ጽድቅ መሰደድ ሲሆን ከዓለም ወደ እግዚአብሔር (ወደ ጽድቅ) በልቦና (በመንፈስ) መሰደድ ነው። ይህም የክርስትና መሠረት ነው። ሁለተኛው በጽድቅ መሰደድ ሲሆን በጽድቅ (የጽድቅን መንገድ በመከተል) ምክንያት የሚመጣ ስደት ሲሆን ቅዱሳን ሐዋርያት ክርስቶስን በማመናቸውና በመስበካቸው የተሰደዱት ስደት ነው። በቤተ ክርስቲያን የብዙ ዘመናት ታሪክም ብዙ ክርስቲያኖች በሃይማኖታቸው ምክንያት ተሰደዋል። ሦስተኛው ስደት ጽድቅን ፍለጋ (ጽድቅን ለማግኘት ወይም የጽድቅን አገልግሎት ለመፈጸም) የሚደረግ ስደት ነው። ይህም ጽድቅን ለማግኘት መሰደድ (ምናኔን)፣ ጽድቅን ለመስበክ (ለማስተማር) መሰደድና ጽድቅን ለመማር (ለማወቅ) መሰደድን ያጠቃልላል። በዚህም ብዙ ቅዱሳን ለመማር፣ በማስተማር ክርስቶስን ለማገልገል፣ በምናኔም በጾም በጸሎት ለመጽናት ተሰደዋል። ይህም ጌታችን በትምህርቱ “ስለስሜም ቤቱን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል።” (ማቴ 19:29) በማለት ያስተማረው ነው። አራተኛው ከጽድቅ መሰደድ ሲሆን ከጽድቅ ወደ ኃጢአት/ሞት የሚደረግ ስደት ነው። ይህም የይሁዳና የዴማስ ዓይነት ስደት ነው።
በፍጥረት ታሪክ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ስደቶች ከጽድቅ መሰደድ ነበሩ። የመጀመሪያው ስደት ሳጥናኤል ከዓለመ መላእክት ወደ ሲኦል መባረሩ (መሰደዱ ነው)። ሁለተኛው ስደት ደግሞ በሰይጣን ምክንያት የሰው ልጅ ሕገ እግዚአብሔርን ተላልፎ ከገነት ወደ ምድር የተሰደደው ስደት ነው። ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም “አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት /ከገነት በተሰደደ ጊዜ የአዳም ተስፋው አንቺ ነሽ” በማለት የተናገረው የአዳምን ከገነት ወደ ምድረ ፋይድ የተሰደደውን ስደት የሚመለከት ነው። አባታችን አብርሃም ጽድቅን ለማግኘት እግዚአብሔር ወዳሳየው ወደ ከነዓን ተሰዷል (ዘፍ 12:1)። ኋላም ወደ ጌራራ ምድር ተጉዟል (ዘፍ 20:1)። አብርሃም ከከለዳውያን ዑር ከሀገሩ ወጥቶ በባዕድ ሀገር ሲንከራተት የኖረው ተጠብቆ የሚቆየው ተስፋ ጸንቶ ነበር፡፡ የተስፋውም ባለቤት እግዚአብሔር የተስፋውን ዋጋ እንዲያገኝ አደረገው (ዘፍ.15፡6)፡፡ ሕዝበ እስራኤልም በረሀብ ምክንያት ወደ ግብፅ ተሰደው ለባርነት ተዳርገዋል (ዘፍ 46)። ወደ ባቢሎንም በምርኮ ተወስደው ተሰደው ነበር (2ኛ ነገሥት 24-25)።
ጌታችን ራሱ ወደምድረ ግብፅ ተሰዶ ስደትን ባርኮልናል። አባ ጽጌ ድንግል በሰቆቃወ ድንግል ላይ “ኢየሱስ ስዱድ ተስፋሆሙ ለስዱዳን፥ ኢየሱስ ግፉእ ተስፋሆሙ ለግፉአን” በማለት የተናገሩት የክርስቶስን ከቤተልሔም ወደ ግብፅ የተሰደደው ስደት በእርሱ አምነው ለሚሰደዱ ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋቸው፣ አርአያቸው መሆኑን ይመለከታል። ቅዱስ ማቴዎስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእናቱ እቅፍ ስለተሰደደው ስደት ሲጽፍ “እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ። ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ። ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሄደ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ። ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ ተሣለቁበት ባየ ጊዜ እጅግ ተቆጣና ልኮ ከሰብአ ሰገል እንደ ተረዳው ዘመን በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን፥ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ። ያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ፥ ድምፅ በራማ ተሰማ፥ ልቅሶና ብዙ ዋይታ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፥ መጽናናትም አልወደደችም፥ የሉምና የተባለው ተፈጸመ።” (ማቴ 2:13-18) ብሏል።
ቤተ ክርስቲያን መከራ መስቀልን ተሸክማ ትኖራለች።
መከራና ቤተ ክርስቲያን ተለያይተው አያውቁም። ቤተ ክርስቲያን ከምስረታዋ ጀምሮ ስደት ላይ ነበረች፣ ዛሬም ናት፣ ወደፊትም እንዲሁ። ጽድቅ የሚገኝበት መንገድ በመከራ ውስጥ ማለፍ ነውና። የመጀመሪያ ክርስቲያኖች የነበሩትን ሐዋርያትንም ዓላውያን ነገሥታት አሳደዋቸዋል። ቅዱስ ሉቃስ ይህንን ስደት “በዚያን ቀንም በኢየሩሳሌም ባለች ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ሆነ፤ ሁሉም ከሐዋርያትም በቀር ወደ ይሁዳና ወደ ሰማርያ አገሮች ተበተኑ። በጸሎትም የተጉ ሰዎች እስጢፋኖስን ቀበሩት ታላቅ ልቅሶም አለቀሱለት። ሳውል ግን ቤተ ክርስቲያንን ያፈርስ ነበር፤ ወደ ሁሉም ቤት እየገባ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጐተተ ወደ ወኅኒ አሳልፎ ይሰጥ ነበር። የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ።” (ሐዋ 8:1-4) በማለት ገልጾታል። ዘመነ ሰማዕታትንም ቤተ ክርስቲያን በስደትና በመከራ አሳልፋለች።
አብነት የሚሆኑን በእግዚአብሔር ያመኑ ቅዱሳን በምድር ላይ መከራን ታግሰዋል። ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና። እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ። ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ።” (ዕብ.11፡32-38) ብሎ የተናገራቸው ስለ ጽድቅ ብለው የተሰደዱትን ነው፡፡
ሐዋርያትም መልካሙን ገድል ተጋድለው እኛም እንድንጋደል አስተምረዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስ በጻፈው መልእክቱ “መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ። ሁሉን በሕይወት በሚጠብቅ በእግዚአብሔር ፊት፥ በጴንጤናዊውም በጲላጦስ ዘንድ መልካሙን መታመን በመሰከረ በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት አዝሃለሁ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ያለ እድፍና ያለ ነቀፋ ሆነህ ትእዛዙን ጠብቅ፤ ያንም መገለጡን በራሱ ጊዜ ብፁዕና ብቻውን የሆነ ገዥ፥ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ፥ ያሳያል።” (1ኛ ጢሞ 6:12-15) በማለት በእምነት እንዲጋደል አስተምሮታል።
ጌታችን መስቀል ተሸክሞ ወደ ቀራንዮ ሲወጣ ሲያለቅሱለት ለነበሩት ሴቶች “በእርጥብ እንጨት እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ፥ በደረቀውስ እንዴት ይሆን?” (ሉቃ 23:31) ነበር ያላቸው። ይህን ማለቱ ጽድቅን ባደረገው፣ ምንም ኃጢአት በሌለበትና ሰውን ለማዳን በፈቃዱ በመጣው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ይህን ሁሉ መከራ የሚያደርሱ ከሆነ ኃጢአትን በሚያደርጉ በሰው ልጆች ላይ ምን ያህል መከራ ያደርሱ ይሆን ማለቱ ነው። ስለዚህም ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ አላቸው። በዚህም ለክርስቲያኖች መከራ መቀበል እንግዳ ነገር ሳይሆን ክርስትናቸው ተፈትኖ ወደ ክብር የሚደርሱበት መሆኑን አስተምሯል።
በፈተናና በመከራ ማለፍ ክርስቶስን መምሰል ነው።
የሰውን ልጅ አርአያና ቤዛ ሆኖ ለማዳን የመጣው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አይሁድ ሊገድሉት ያሳድዱት ነበር። የሚያሳድዱትም የሚያስነቅፍ በደል ተገኞቶበት ሳይሆን በጎ ምግባሩ ክፋታቸውን ስላጎላባቸው፣ የናቋቸውን ስላከበረ፣ በሰንበት ድውይ ስላዳነ ነበር። ወንጌላዊ ዮሐንስ ይህንን “ስለዚህም በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር።” (ዮሐ 5:16) በማለት ጽፎታል። የዓለም መድኃኒት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ባቀና ጊዜ አልተቀበሉትም ነበር። ወንጌላዊ ሉቃስ “የሚወጣበትም ወራት በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና፥በፊቱም መልክተኞችን ሰደደ። ሄደውም ሊያሰናዱለት ወደ አንድ ወደ ሳምራውያን መንደር ገቡ፤ፊቱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ስለነበረ አልተቀበሉትም።” (ሉቃ 9:51-53) በማለት እንዳልተቀበሉት ተናግሯል።
የክርስቶስን ወንጌል የሚሰብኩ እውነተኞች ሐዋርያት ዓለም ሲጠላቸውና ሲያሳድዳቸው ነበር። ይህም ጌታችን አስቀድሞ “በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁና፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም።” (ማቴ 10:22-23) በማለት እንደተገራቸው ነው። እንዲሁም “ስለዚህ ደግሞ የእግዚአብሔር ጥበብ እንዲህ አለች። ወደ እነርሱ ነቢያትንና ሐዋርያትን እልካለሁ፥ ከእነርሱም ይገድላሉ ያሳድዱማል።” (ሉቃ 11:49) በማለት እንደተናገረው ነው።
ጌታችን በጊዜው አሳዳጆች ለነበሩት ጻፎችና ፈሪሳውያን “ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ።” (ማቴ 23:34) በማለት ሲገስጻቸው ነበር። ለደቀ መዛሙርቱ ግን “ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ ያሳድዱአችሁማል፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል።” (ሉቃ 21:12) በማለት ነበር ለአገልግሎት ያዘጋጃቸው የነበረው።
ጠቢቡ ሰሎሞን “ክፉ የሚያደርጉ ይስታሉ፤ ምሕረትና እውነት ግን መልካምን ለሚያደርጉ ናቸው።” (ምሳ 14:22) እንዳለው በክርስቲያኖች፣ በቤተ ክርስቲያን እና በክርስትና ላይ ክፉ የሚያስቡ፣ የሚያቅዱና የሚያደርጉ ይስታሉ። ለእነዚህም ንስሐ ገብተው ከዘላለም ቅጣት ይድኑ ዘንድ ልንጸልይላቸው ይገባል። ምሕረትና እውነት ግን መልካምን ለሚያደርጉ፣ መልካምን በማድረጋቸውም መከራን ለሚቀበሉ ነው። ክርስቲያኖችን የሚሳድዱ በእውነትም ያሳዝናሉ። ራሳቸው ጽድቅን አጥተው ጽድቅን የሚያደርጉትን ያሳድዳሉ፣ በዚህም በራሳቸው ላይ ኃጢአትን ለሚያሳድዷቸው ግን ጽድቅን ይጨምራሉ።
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “በግፍ መከራን የሚቀበል ሰው እግዚአብሔርን እያሰበ ኃዘንን ቢታገሥ ምስጋና ይገባዋልና። ኃጢአት አድርጋችሁ ስትጎሰሙ ብትታገሡ፥ ምን ክብር አለበት? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፥ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል። የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።” (1ኛ ጴጥ 2:19-23) በማለት ክርስቲያኖች መከራን እንዲታገሱ አስተምሯል።
እንዲሁም “ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጒዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤ ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር።” (1ኛ ጴጥ 4:15-16) በማለት ሰው በክርስትናው መከራን በመቀበሉ ማፈር እንደሌለበት አስተምሯል። መከራን መፍራት እንደማይገባም ሲናገር “ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም።” (1ኛ ጴጥ 3:14) ብሏል።
መከራን መታገስ ለጽድቅ አክሊል ታበቃለች።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን?” (ሮሜ 8:35) በማለት እንደተናገረው ስደት ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን አይገባም። ይልቁንም የክርስቶስን ፍቅር፣ ለእኛም ብሎ የተቀበለውን መከራ እንድናስብ ያደርገናል እንጂ። ይህ የተወደደ ሐዋርያ በቆሮንቶስ መልእክቱም “እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና በሥጋ ስናድር ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የምናውቅ ከሆንን፥ ታምነናል ይልቁንም ከሥጋ ተለይተን በስደት መኖር በጌታም ዘንድ ማደር ደስ ይለናል።” (2ኛ ቆሮ 5:6-7) በማለት ከሥጋ ተለይተን በስደት (በመከራ) እንድንኖር አስተምሯል።
እንዲሁም “ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና።” (2ኛ ቆሮ 12:10) በማለት በክርስቶስ መከራን መቀበል ለእምነታችን ኃይል እንደሆነ አስተምሯል። ለመንፈስ ልጁ ለጢሞቴዎስም በጻፈው መልእክቱ “በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል። መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።” (2ኛ ጢሞ 4:6-8) በማለት ስለክርስቶስ መከራ መቀበል የሚያስገኘውን ዋጋ ተናግሯል።
ቅዱሳን በመከራቸው ሁሉ የሚያሳስባቸው የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ነው። ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ “በድካም አብዝቼ፥ በመገረፍ አብዝቼ፥ በመታሰር አትርፌ፥ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ። አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ። ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ። ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ ፍርሃት፥ በወንበዴዎች ፍርሃት፥ በወገኔ በኩል ፍርሃት፥ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፥ በከተማ ፍርሃት፥ በምድረ በዳ ፍርሃት፥ በባሕር ፍርሃት፥ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፤ በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ። የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።” (2ኛ ቆሮ 11:23-28) በማለት ከደረሰበት መከራ ይልቅ የአብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ እንደሚያሳስበው ተናግሯል።
የቤተ ክርስቲያንና የክርስቲያኖች አሳዳጅ ማነው?
ቅዱስ አትናቴዎስ “ጠላታችን አርዮስ ሳይሆን ዲያብሎስ ነው” እንዳለው ለክርስቲያኖች ዋናው ጠላት ዲያቢሎስ ነው። ብርሃነ ዓላም ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚህ ሲናገር “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ። ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ። እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤ በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።” (ኤፌ 6:11-17) ብሏል። አንድ ቅዱስ አባት እንዳሉት “ያልተጋደለ አያሸንፍም፣ ያላሸነፈም የድል አክሊል አያገኝም።”
ክርስቲያኖችን የሚያሳድዱ ሰዎች የዲያቢሎስ ሰለባዎች (ተጠቂዎች) ናቸው። ከተጠቂነት ቢድኑ እነርሱም እንደ እኛ ክርስቲያን ሊሆኑ የሚችሉ ሰለሆኑ ልንጸልይላቸው ይገባል። በቅዱሳት መጻሕፍት እንደምናነበውም ክርስቲያኖችን ሲያሳድዱ የነበሩ ተመልሰው ለቅድስና በቅተዋል። ለዚህም ሳውል ይባል የነበረው ቅዱስ ጳውሎስ ታላቅ ምስክር ነው። ስለዚህ ነው ጌታችን በትምህርቱ “በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን (የሚጠሏች ሁን ሰዎች) ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ።” (ማቴ 5:44) በማለት ያስተማረው። ዓለም ስታሳድደን ጌታን እናገኘዋለን። ጌታችን ያዳነው ከመወለዱ ጀምሮ ዓይነ ስውር የነበረውን አይሁድ “አንተ ሁለንተናህ በኃጢአት ተወለድህ፥ አንተም እኛን ታስተምረናለህን?” ብለው ወደ ውጭም ባወጡት ጊዜ “ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ አገኘውም።” (ዮሐ 9: 34-35) ይህ ሰው እግዚአብሔር ያደረገለትን ተአምር በመመስከሩ አይሁድ ወደ ውጭ አስወጡት። ነገር ግን ወደ ውጭ ሲያስወጡት ጌታን አገኘው፣ ተከተለውም።
ብፁዓን ናቸው: እግዚአብሔር ስለጽድቅ የሚሳደዱትን አይተዋቸውም።
በነቢዩ ኢሳይያስ “ጽዮን ግን:- እግዚአብሔር ትቶኛል ጌታም ረስቶኛል አለች። በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን? አዎን፥ እርስዋ ትረሳ ይሆናል፥ እኔ ግን አልረሳሽም። እነሆ፥ እኔ በእጄ መጻፍ ቀርጬሻለሁ፥ ቅጥሮችሽም ሁልጊዜ በፊቴ አሉ።” (ኢሳ 49:14-16) እንዳለው እግዚአብሔር በስሙ መከራ የሚቀበሉትን አይተዋቸውም። ጌታችንም ለደቀመዛሙርቱ “ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ። ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም። የእናንተስ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ ተቈጥሮአል። እንግዲህ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ። ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ።” (ማቴ 10:28-33) በማለት ስለስሙ መከራን ሲቀበሉ እንደማይለያቸው ተስፋን ሰጥቷቸዋል።
ልበ አምላክ የተባለ ዳዊትም “ጻድቃን እጃቸውን ወደ ክፋት እንዳይዘረጉ የኃጥኣን በትር በጻድቃን ዕጣ ላይ አይኖርም። አቤቱ፥ ለቸሮች ልባቸውም ለቀና መልካምን አድርግ። ወደ ጠማማነት የሚመለሱትን ግን ዓመፃን ከሚሠሩት ጋር እግዚአብሔር ይወስዳቸዋል።” (መዝ 125:3-5) ብሏል። እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና (ዕብ 2:18)። መከራን የሚቀበል ክርስቲያን ሁሉንም ለክርስቶስ ይሰጣል እንጂ ክፉን በክፉ አይመልስም። ለዚህም ምሳሌ የሆነን ክርስቶስ “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ” (1ኛ ጴጥ 2:23)። ስለዚህ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።” (ኢሳ 53:7) በማለት ነበር የተናገረው። የእርሱ ስለእኛ መከራን መቀበሉ በራሱ ፈቃድ፣ እርሱ በፈቀደላቸው ጊዜ ነበር። ስለዚህም ሲናገር “በመቅደስ ዕለት ዕለት ከእናንተ ጋር ስሆን እጆቻችሁን አልዘረጋችሁብኝም፤ ይህ ግን ጊዜያችሁና የጨለማው ሥልጣን ነው አላቸው።” (ሉቃ 22:53) ብሏል።
መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና
በመጀመሪያው አንቀጸ ብፁዓን ያነሳትን መንግሥተ ሰማያት ውስጥ ለውስጥ ሲናገራት ቆይቶ በስምንተኛው አንቀጸ ብፁዓን ላይ ድጋሜ አመጣት። ወልደ እግዚአብሔር ወልደ ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስ “መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” ማለቱ መንግሥተ ሰማያት የተዘጋጀችው ለእነርሱ ነው፣ እነርሱም ይወርሷታል፣ የራሳቸው ያደርጓታል ማለቱ ነው። በአንደኛውና በስምንተኛው ማንሳቱ በመጀመሪያው ቃል ኪዳን ሲሰጥ ነው። ሰባቱ አንቀጸ ብፁዓን ወደ ፍጹምነት መድረሻ ናቸው። ስምንተኛው ደግሞ የፍጹምነት ማሳያና ማረጋገጫ ነው። እነዚህ ወደ ፍጹምነት የሚያደርሱ አንቀጸ ብፁዓን በነቢዩ ኢሳይያስ “የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ” ተብለው የተገለፁት ሰባት የመንፈስ ቅዱስ ሀብታት ናቸው (ኢሳ 11:2)።
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል” (2ኛ ቆሮ 4:8-16) እንዳለው ስለጽድቅ መከራን የሚቀበሉ አይጠፉም። ቅዱስ ጴጥሮስም “ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ።” (1ኛ ጴጥ 4:12-13) በማለት በክርስቶስ መከራ መካፈል የሚያስደስት መሆኑን ተናግሯል።
ቅዱስ ጳውሎስም ክርስቶስን በሞቱ ሊመስለው እንደሚመኝ ሲናገር “እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ።” (ፊልጵ 3:11) በማለት ነበር። ክርስቶስንም በመከራው እንደመሰለው ሲናገር “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው።” (ገላ 2:20) ብሏል።
ነገር ግን “ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን። እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፥ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ አለ።” (ማቴ 13:30) እንደተባለ ፍርዱ በመከር ጊዜ ይሆናል። ያ ፍርድ መከራን ለተቀበሉ የጽድቅ አክሊል የሚታደልበት፣ የክርስቶስን ስም የተሸከሙትን ያሳደዱት ደግሞ ወደዘላለም ፍርድ የሚሄዱበት ነው። ሐዋርያው ያዕቆብም በመልእክቱ “ በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።” (ያዕ 1:12) በማለት በፈተና የሚጸና የክብርን አክሊል እንደሚቀበል ጽፏል። በዚህም ብዙ ቅዱሳን፣ ጻድቃንና ሰማዕታት በፈተና ጸንተው የጽድቅ አክሊልን ተቀብለዋል።
ሥጋዊ (ዓለማዊ) ስደት
ሰው በዚህች ምድር ላይ ሲኖር በተለያየ ምክንያት ከሚኖርበት አካባቢ በተለያየ ምክንያት ሊሰደድ ይችላል። እነዚህም የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች፣ እንዲሁም ሥጋዊ/ዓለማዊ ፍላጎቶች ሊሆኑ ይችላሉ። የተፈጥሮ ችግሮች ለምሳሌ ድርቅ፣ ረሃብ፣ የተፈጥሮ አደጋዎች ሲሆኑ ሰው ሠራሽ ችግሮች ደግሞ እንደ ጦርነት፣ ግጭት እና የመሳሰሉት ናቸው። በእነዚህ ምክንያት ብዙ ሰው ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር ይሰደዳል። የሥጋ ፍላጎቶች ደግሞ የተሻለ ኑሮ ወይም ትምህርት ወይም ሥራ ፍለጋ ሰው ይሰደዳል። ከዚህ በተጨማሪ ሰው በኃጢአት ምክንያትም ሊሰደድ ይችላል። ባደረገው ኃጢአት ምክንያት ሰውን ፈርቶ ሊሰደድ ይችላል። ጌታችን “ስለጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው” ብሎ ያስተማረው ከእነዚህ የስደት ምክንያቶች ጋር መምታታት የለበትም። ሰው በምድር ላይ በየትኛውም ቦታ ሊንቀሳቀስ ይችላልና።
በሌላ በኩልም ቀማኞችና ነፍሰ ገዳዮችም በኃጢአታቸው ምክንያት ሊከሰሱ፣ ሊታሠሩ፣ ሊሰደዱ ይችላሉና ጌታችን ይህንን አንቀጸ ብፁዓን “ስለጽድቅ የሚሰደዱ” በማለት ዓላማውን በግልጽ ለይቶ አስቀመጠልን። በተያያዘም ተግተን ባለመሥራታችን፣ ወይም በስንፍናችን ወይም በራሳችን የክፋት ሥራዎች ምክንያት የሚመጡብንን ሥጋዊ ችግሮችና መከራዎች ከዚህ ትምህርት ጋር መምታታት የለባቸውም። ሳንሠራ ቀርተን ብንራብ፣ በመጥፎ ጠባያችን ምክንያት ሰዎች ቢ(ያ)ርቁን፣ በሐሰተኛ ትምህርት፣ በአድሏዊነትና በከፋፋይ ሥራችን ብንከሰስ ወይም ብንታሠር፣ ተጣልተን ፍርድ ቤት ብንቀርብ ወዘተ እነዚህ የእኛው ምድራዊ ችግሮች ናቸው። በዚህም ምክንያት የሚደርስብን ቅጣት የሚገባን እንጂ ስለጽድቅ ሊባል አይገባም። እነዚህ ሥራችንን በሚገባ በመሥራት፣ ኃላፊነታችንን በሚገባ በመወጣት የሚቀረፉ ናቸውና።
ስለ ጽድቅ መከራን የተቀበሉ ምሳሌዎቻችን
የክርስትና ሕይወት በፈተና፣ በመከራ፣ በስደት፣ በመገፋት፣ በመታሠር፣ በሰማዕትነት የተሞላ ነው። ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም “አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዛ ዐለም፤ ወከዓው ደሞሙ በእንተ እግዚአብሔር፤ ወተዐገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት /ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፤ ስለ እግዚአብሔር ብለው ደማቸውን አፈሰሱ፤ ስለ መንግሥተ ሰማያትም ሲሉ መራራ ሞትን ታገሡ” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) በማለት እንደተናገረው ብዙ ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም ንቀው ስለመንግሥተ ሰማያት ደማቸውን አፍስሰዋል። በተለይም በስንክሳርና በቅዱሳን ገድላት እንደምናነበው በአጸደ ሥጋ የነበሩበት ሕይወት የመከራ እንጂ የተድላና ደስታ አልነበረም። በመከራና በስደት በሰማዕትነት ብዙዎች ለዘላላማዊ ክብር በቅተውበታል። ለማሳያ ያህል ከብሉይና ከሐዲስ ጥቂት ምሳሌዎችን እንደሚከተለው አቅርበናል።
ጻድቁ አቤል: የጻድቃን ሕይወት የመከራ ሕይወት ነው። ለዚህም በዘመናት ብዙ ምሳሌዎች አሉን። ጻድቁ አቤል የዋህና ጻድቅ ስለነበር የመጀመሪያው ሰማዕት ሆኗል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለአቤል ሲናገር “አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፥ በዚህም፥ እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር፥ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል።” (ዕብ 11:4) ብሏል።
ጻድቁ ዮሴፍ: ወንድሞቹ በግፍ ወደ ግብፅ የሸጡት ጻድቁ ዮሴፍም የወንድሞቹን በደል በመተው “አሁንም እናንተ ወደዚህ የላካችሁኝ አይደላችሁም፥ እግዚአብሔር ላከኝ እንጂ፤ ለፈርዖንም እንደ አባት አደረገኝ፥ በቤቱም ሁሉ ላይ ጌታ፥ በግብፅ ምድርም ሁሉ ላይ አለቃ አደረገኝ።” (ዘፍ 45:8) ነበር ያላቸው። ምንም እንኳን እነርሱ ቢሸጡትም እርሱ ግን እግዚአብሔር ላከኝ አላቸው።
ንጉስ ዳዊት: ንጉሥ ዳዊት ምንም ባልበደለበት ከእርሱ ቀድሞ የነገሠው ሳኦል ሊገድለው ያሳድደው ነበር። መጽሐፍ ስለዚህ “ዳዊትም ከአርማቴም አገር ከነዋትዘራማ ሸሸ፥ ወደ ዮናታንም መጥቶ። ምን አደረግሁ? እኔንስ ለመግደል የሚፈልግ በአባትህ ፊት ጠማምነቴና ኃጢአቴ ምንድር ነው? ብሎ ተናገረው።” (1ኛ ሳሙ 20:1) ይላል። ሌሎች የቀደሙት ነቢያትም እንዲሁ ብዙ መከራና መሳደድ ይደርስባቸው ነበር። ነቢዩ ኤርምያስ ስለእውነት በጉድጓድ ተጣለ፣ በግዞትም ተቀመጠ (ኤር 38:6)። ነቢዩ ሚክያስንም በግዞት አኑሩት፥ የመከራም እንጀራ መግቡት፥ የመከራም ውኃ አጠጡት (1ኛ ነገ 22:27)።
ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ: ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ ስለእውነት ሰማዕትነትን የተቀበለ ጻድቅ ሰው ነው። ለኢይዝራኤላዊውም ለናቡቴ በሰማርያ ንጉሥ በአክዓብ ቤት አጠገብ የወይን ቦታ ነበረው። አክዓብም ናቡቴን በቤቴ አቅራቢያ ነውና የአትክልት ቦታ አደርገው ዘንድ የወይን ቦታህን ስጠኝ፤ ስለ እርሱም ከእርሱ የተሻለ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ፤ ወይም ብትወድድ ግምቱን ገንዘብ እሰጥሃለሁ ብሎ ተናገረው። ናቡቴም አክዓብን “የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር ያርቅልኝ” አለው። ኢይዝራኤላዊውም ናቡቴ የአባቶቼን ርስት አልሰጥህም ብሎ ስለ ተናገረው አክዓብ ተቈጥቶና ተናድዶ ወደ ቤቱ ገባ። በአልጋውም ላይ ተጋድሞ ፊቱን ተሸፋፈነ፥ እንጀራም አልበላም። ሚስቱም ኤልዛቤል ወደ እርሱ መጥታ ልብህ የሚያዝን እንጀራስ የማትበላ ስለምንድር ነው? አለችው። እርሱም ኢይዝራኤላዊውን ናቡቴን። የወይንህን ቦታ በገንዘብ ስጠኝ፤ ወይም ብትወድድ በፋንታው ሌላ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ ብዬ ተናገርሁት፤ እርሱ ግን የወይን ቦታዬን አልሰጥህም ብሎ ስለ መለሰልኝ ነው አላት። በዚህም ምክንያት በናቡቴ ላይ የሐሰት ምስክር ተዘጋጅቶበት ተወግሮ እንዲገደል ሆኗል። እግዚአብሔር ግን የናቡቴን ደም አልረሳም። (1ኛ ነገሥ 21:1-29)
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ: የጌታ መንገድ ጠራጊ የተባለው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እውነትን በመመስከሩ መከራን ተቀብሏል። ሄሮድስ በወንድሙ በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ዮሐንስን አስይዞ አሳስሮት በወህኒ አኑሮት ነበርና፤ ዮሐንስ እርስዋ ለአንተ ትሆን ዘንድ አልተፈቀደም ይለው ነበርና። ሊገድለውም ወዶ ሳለ፥ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስለ አዩት ፈራቸው።ነገር ግን ሄሮድስ የተወለደበት ቀን በሆነ ጊዜ፥ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ዘፈነች ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤ ስለዚህም የምትለምነውን ሁሉ እንዲሰጣት በመሐላ ተስፋ አደረገላት። እርስዋም በእናትዋ ተመክራ። የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ በወጭት ስጠኝ አለችው። ንጉሡም አዘነ፥ ነገር ግን ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ተቀምጠው ስላሉት ሰዎች እንዲሰጡአት አዘዘ፤ ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ አስቆረጠው። (ማቴ 14:1-10)
ቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስ: አይሁድ የእስጢፋኖስን ምስክርነት “በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቈጡ ጥርሳቸውንም አፋጩበት። መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና “ እነሆ፥ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፈኑ፥ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ ሮጡ፥ ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት። ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ። እስጢፋኖስም:- ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር። ተንበርክኮም። ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ። ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር።” (ሐዋ 7: 54-60)
ቅዱስ ጴጥሮስ (በስብከት) “በዚያም ዘመን ንጉሡ ሄሮድስ መከራ ያጸናባቸው ዘንድ ከቤተ ክርስቲያኑ በአንዳንዶቹ ላይ እጁን ጫነባቸው። የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው። አይሁድንም ደስ እንዳሰኛቸው አይቶ ጨምሮ ጴጥሮስን ደግሞ ያዘው። የቂጣ በዓልም ወራት ነበረ። በያዘውም ጊዜ ወደ ወኅኒ አገባው ከፋሲካም በኋላ ወደ ሕዝብ ያወጣው ዘንድ አስቦ እያንዳንዱ አራት ወታደሮች ሆነው እንዲጠብቁት ለአራት ጭፍራ ክፍል አሳልፎ ሰጠው። ጴጥሮስም በወኅኒ ይጠበቅ ነበር፤ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር ጸሎት አጥብቆ ይደረግ ነበር። ሄሮድስም ሊያወጣው ባሰበ ጊዜ፥ በዚያች ሌሊት ጴጥሮስ በሁለት ሰንሰለት ታስሮ ከሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ሆነው ወኅኒውን ይጠብቁ ነበር። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ቀረበ በቤትም ውስጥ ብርሃን በራ፤ ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና። ፈጥነህ ተነሣ አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ። መልአኩም። ታጠቅና ጫማህን አግባ አለው፥ እንዲሁም አደረገ። ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ አለው። ወጥቶም ተከተለው፤ ራእይንም የሚያይ ይመስለው ነበር እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደ ሆነ አላወቀም። የመጀመሪያውንና የሁለተኛውንም ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚያወጣው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ እርሱም አውቆ ተከፈተላቸው፤ ወጥተውም አንዲት ስላች አለፉ ወዲያውም መልአኩ ከእርሱ ተለየ። ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ። ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ አለ።” (ሐዋ 12:1-11)
ቅዱስ ጳውሎስ: (በስብከት) ቅዱስ ጳውሎስ በሚያስተምርበት ዘመንም የአርጤምስን ቤተ መቅደስ የሚያመልኩ ሰዎች ብዙ ሁከትን በመፍጠር በደቀ መዛሙርቱ ላይ መከራን ያጸኑባቸው ነበር። ወደ አደባባይም አውጥተው ለፍርድ ያቀርቧቸው ነበር። ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ላይ ስለዚህ ሲናገር “በዚያም ጊዜ ስለዚህ መንገድ ብዙ ሁከት ሆነ። ብር ሠሪ የሆነ ድሜጥሮስ የሚሉት አንድ ሰው የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች በብር እየሠራ ለአንጥረኞች እጅግ ትርፍ ያገኝ ነበርና፤እነዚህንም ይህንም የሚመስለውን ሥራ የሠሩትን ሰብስቦ እንዲህ አላቸው። ሰዎች ሆይ፥ ትርፋችን በዚህ ሥራ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ።ይህም ጳውሎስ በእጅ የተሠሩቱ አማልክት አይደሉም ብሎ፥ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት ክፍል በቀር በእስያ ሁሉ ብዙ ሕዝብን እንደ አስረዳና እንደ አሳተ አይታችኋል ሰምታችሁማል። ሥራችንም እንዲናቅ ብቻ አይደለም፥ እስያ ሁሉ ዓለሙም የሚያመልካት የታላቂቱ አምላክ የአርጤምስ መቅደስ ምናምን ሆኖ እንዲቆጠር እንጂ፥ ታላቅነትዋም ደግሞ እንዳይሻር ያስፈራል። ይህንም በሰሙ ጊዜ ቍጣ ሞላባቸው። የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት እያሉም ጮኹ። ከተማውም በሙሉው ተደባለቀ፥ የመቄዶንያም ሰዎች የጳውሎስን ጓደኞች ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ከእነርሱ ጋር ነጥቀው በአንድ ልብ ሆነው ወደ ጨዋታ ስፍራ ሮጡ።” (ሐዋ 19:23-41) ብሏል።
ቅዱስ ጴጥሮስ (በሰማዕትነት): በኔሮን ቄሳር ዘመን እነዚህ ሁለት ሐዋርያት ሰማዕትነትን ተቀብለዋል። ቅዱስ ጴጥሮስ ዓለምን ዞሮ ካስተማረ በኋላ በእርጅና ዘመኑ የክርስቲያኖች ጠላት በሆነው ዓላዊው ንጉሥ በኔሮን ዘመነ መንግሥት የሞት ፍርድ ስለታወጀበት ወንጌልን ሲያስተምር ቆይቶ የሮም መኳንንቱ እንዳይገድሉት ልብሱን ቀይሮ ከሮም ከተማ ሲወጣ ጌታችን መስቀል ተሸክሞ ከፊቱ ሲመጣ አየው። በዚህ ጊዜም ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን “ጌታ ሆይ ወዴት ትሄዳለህ?” ብሎ ጠየቀው። ጌታችንም “በሮም የሚሰቀልልኝ ስላጣሁ ልሰቀል መሄዴ ነው” አለው። ቅዱስ ጴጥሮስም “አይሆንም” በማለት መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ሮም ተመለሰ። ሮማውያንም እንደ ሥርዓታቸው ቅዱስ ጴጥሮስን ከገረፉት በኋላ ሊሰቅሉት ወደ ሮም አደባባይ ይዘውት ሲሄዱ “እንደ ጌታዬ ወደ ላይ ሳይሆን ቁልቁል ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ” በማለቱ የሮም ወታደሮች እርሱ እንደነገራቸው ዘቅዝቀው በመስቀል ሰማእትነትን ተቀብሏል።
ቅዱስ ጳውሎስ (በሰማዕትነት): የሮም ንጉሥ ኔሮን ቄሣር ቅዱስ ጳውሎስን ወደ ፍርድ ሸንጎ አስቀርቦ እንዲሞት ፈረደበት። ወታደሮች ሊገድሉት ሲወስዱትም ከንጉሥ ኔሮን ወገን የኾነችውን የአንዲት ብላቴና መጐናጸፊያ “ዛሬ እመልስልሻለሁ” ብሎ ከተቀበላት በኋላ ፊቱን በብላቴናዋ መጐናጸፊያ ተሸፍኖ አንገቱን በሰይፍ ተቀልቶ በሰማዕትነት አርፏል። ደቀ መዛሙርቱም ራሱን ከአንገቱ ጋር ቢያደርጉት እንደ ቀድሞው ደኅና ኾኖላቸው በክብር ገንዘው ቀብረውታል። ሰያፊው ቅዱስ ጳውሎስን እንደ ገደለው ለመናገር ወደ ንጉሡ ሲመለስም ያቺ መጐናጸፊያዋን የሰጠችው ብላቴና “ጳውሎስ ወዴት አለ?” አለችው። እርሱም “ራሱን ተቈርጦ በመጐናጸፊያሽ ተሸፍኖ ወድቋል” ሲላት “ዋሽተሃል፤ እነሆ ጴጥሮስና ጳውሎስ በእኔ በኩል አልፈው ሔዱ። እነርሱም የመንግሥት ልብስ ለብሰዋል። በራሳቸውም በዕንቍ ያጌጡ አክሊላትን አድርገዋል። መጐናጸፊያዬንም ሰጡኝ። ይህችውም እነኋት፤ ተመልከታት” ብላ ሰጠቸው። ከእርሱ ጋር ለነበሩትም አሳየቻቸው። አይተውም አደነቁ፤ ስለዚህም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ።
ቤተ ክርስቲያን ሁል ጊዜ ለተሰደዱት ትጸልያለች።
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አምላኳን ኢየሱስ ክርስቶስን ተስፋሆሙ ለስዱዳን (ለተሰደዱ ተስፋቸው) ብላ ትጠራዋለች (ቅዳሴ እግዚእ)። አዎን እርሱ መከራን ለሚቀበሉት፣ በሃይማኖት፣ በመማር/በማስተማር፣ በምናኔ ለሚሰደዱት ሁሉ ተስፋቸው ነው። እርሱ ስለሰው ልጅ መዳን ነፍሱን አሳልፎ እስከመስጠት ድረስ መከራን የተቀበለ በእርሱ አምነው መከራን የሚቀበሉትን በመንግሥቱ ያከብራቸዋልና። በእንተ ቅድሳት በሚባለው የቅዳሴ ክፍልም “እግዚአብሔር ትዕግስትን በጎ ትምህርትንም ይሰጣቸው ዘንድ የድካማቸውንም ፍጹም ዋጋ ይሰጣቸው ዘንድ ስለተሰደዱ ሰዎች እንማልዳለን” በማለት በመከራ፣ በስደት ላይ ላሉት ሁሉ ትጸልያለች። እንዲሁም በጸሎተ ቡራኬ “የተጨነቀችዪቱን ነፍስ ሁሉ አሳርፍ፤ በሰንሰለት የታሠሩትን፤ በስደትና በምርኮ ያሉትንም፤ መሪር በሆነ አገዛዝ የተያዙትንም አምላካችን ሆይ በቸርነትህ አድናቸው” እያለች በመከራ ላሉት ትለምናለች።
መደምደሚያ
በስምንተኛዋ የአንቀጸ ብፁዓን ትምህርቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ስለጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።” (ማቴ 5:10) በማለት በቃል ያስተማረውን በመዋዕለ ሥጋዌው በገቢር አሳይቶናል። በህፃንነት መሰደዱም፣ በሚያስተምርበት ጊዜ በሀሰት መከሰሱም፣ በመጨረሻም በሀሰት ክስና ምስክር መከራ መስቀሉን መቀበሉ፣ ሕማምና ሞቱ በጽድቅ፣ ስለ ጽድቅ የተደረጉ ናቸው። የመንግስተ ሰማያት ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ጽድቅ መሰደዱ ጥቅሙ በስሙ ለምናምን ለእኛ ነው። በቤዛነቱ የመንግስተ ሰማያትን በር ከፍቶልናል። ከእኛ የሚጠበቀው በቸርነቱ ላዘጋጀልን ርስት (መንግስተ ሰማያት) የተገባን ሆነን መገኘት ነው። ለዚህም ገድላቸውን፣ ታሪካቸውን በዚህች ጦማር የተጠቀሱትንም ያልተጠቀሱትንም እግዚአብሔር ያከበራቸው የሰይጣንን ማሰናከያ ድል ያደረጉ ቅዱሳን አብነት አድርገን ስለ ጽድቅ ብንገፋ፣ ብንሰደድ የመንግሥተ ሰማያት ባለቤት አምላካችን እግዚአብሔር መንግሥቱን ሊያወርሰን የታመነ ነው። ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የቅዱሳን ሁሉ ጸሎትና አማላጅነት ይርዳን። አሜን።