የዚህ ስያሜ ትርጓሜ
- ኦርቶዶክስ (Orthodox)
“ኦርቶዶክስ” የሚለው ቃል የግሪክ ቃል ሲሆን የተቀናበረው “ኦርቶ” እና “ዶክስ” ከሚሉት ሁለት ቃላት ነው፡፡ትርጉማቸውም ኦርቶ ማለት ቀጥተኛ: ትክክለኛ ማለት ሲሆን ዶክስ ማለት ደግሞ እምነት/ሃይማኖት ማለት ነው፡፡ በአንድነት ሲሆኑ ኦርቶዶክስ ማለት ቀጥተኛ፡ ትክክለኛ እምነት/ሃይማኖት ማለት ነው፡፡
ኦርቶዶክስ የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት ላይ የዋለው በ325 ዓ.ም በኒቅያ ጉባዔ ነው፡፡ በኒቅያ “ወልድ ፍጡር ነው” የሚለውን የአርዮስን የክህደት ትምህርት ለማውገዝና ሃይማኖታቸውን ለማፅናት የተሰበሰቡ ሃይማኖታቸው የቀና 318ቱ ሊቃውንት ይህን ቃል የተጠቀሙት ሐዋርያት ያስተማሯት ሃይማኖት ቀጥተኛና ትክክለኛ ናት ለማለት ነው፡፡ ሌሎች እንደ አርዮስ ክህደት ያሉት በየዘመኑ የሚነሱት ልዩ ልዩ አዳዲስ ትምህርቶች የምንፍቅና መሆናቸውን ለማረጋገጥ ይህችን ሃይማኖት ኦርቶዶክስ ብለዋታል፡፡
በዘመናችን የቋንቋ አጠቃቀምም ኦርቶዶክሳዊ መንገድ (orthodox) ማለት ቀጥተኛ (የተለመደ የታወቀ) የችግር አፈታት ሲሆን ኢ-ኦርቶዶክሳዊ (unorthodox) ማለት ደግሞ ከተለመደው ከታወቀው ወጣ ያለ የችግር አፈታት ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ይህን ቃል አንዳንዶች ግትርነትን ወይም ለለውጥ ያልተዘጋጀ የሚለውን ለመግለፅም ሲጠቀሙበት ይታያል፡፡ ይህ ግን በሂደት የመጣ የትርጉም መዛባት ተደርጎ ሊወስድ ይችላል፡፡
- ተዋሕዶ (Miaphysite)
ተዋሕዶ የሚለው ቃል ከልሣነ ግእዝ የመነጨ ቃል ነው፡፡ ትርጒሙም “አንድ ሆኖ” ማለት ነው። በዚህ ትርጉም ውስጥ አንድ የሆኑት መለኮታዊና ሰብዓዊ ባሕርይ (መለኮትና ትስብዕት) ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የተዋሕዶ ትርጓሜ በአጭሩ “ወልድ ዋሕድ” የሚለው ነው፡፡ ክርስቶስ ሰው የሆነው ያለሚጠት (ያለመመለስ)፣ ያለ ውላጤ (ያለ መለወጥ)፣ ያለ ቱሳኤ (ያለ መቀላቀል)፣ ያለትድምርት (ያለ መደመር)፣ ያለ ቡዓዴ (ያለመለያየት)፣ ያለ ኅድረት (ያለ ማደር) ነው፡፡ ክርስቶስ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ፣ ከሁለት አካል አንድ አካል የሆነው በተዋህዶ ነው፡፡ ስለዚህ ተዋሕዶ የሚለው ቃል ክርስቶስ ሰው የሆነበትን ምስጢር የሚገልፅ ታላቅ ቃል ነው፡፡ ክርስቶስ ሰው የሆነው በ ተ ዋ ሕ ዶ ነው!
- ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ (Orthodox Miaphysite)
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋህዶ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ፣ ከሁለት አካል አንድ አካል ሆነ (ሥግው ቃል ነው) ብላ የምታምን ቀጥተኛና ትክክለኛ እምነት/ሃይማኖት ማለት ነው፡፡ ይህም ነቢያት የተናገሩትን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ያስተማረውን፣ ሐዋርያት የሰበኩትን፣ ሊቃውንት ያመሠጠሩትን አስተምህሮ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ከሐዋርያት (ከመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች) በቀጥታ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈች ከእኛ ትውልድ ስለደረሰች ቀጥተኛ ናት፡፡ ያልተበረዘች ያልተለወጠች ያልተከለሰች ስለሆነችም ትክክለኛዋ እርሷ ናት፡፡
በማቴ 16፡16-18 ላይ “ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፡- ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ። እነርሱም፡- አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት። እርሱም፡- እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፡- አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።” ይላል፡፡
ተዋሕዶ (ወልድ ዋሕድ) የሚለው ይህንን የጴጥሮስን እምነት የሚያመለክት ነው፡፡ ጌታችን እንዳረጋገጠው ይህች የጴጥሮስ እምነት ዓለት ናት፡፡ ቤተክርስቲያናችንም በቀጥታ በዚህ እምነት/ዓለት ላይ የተመሠረተች ስለሆነች ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ትባለለች፡፡ ይህች ዓለት የምትለወጥ/የምትታደስ አይደለችም፡፡ ቤት ሲታደስ እንኳን መሠረቱ አይታደስም፡፡ ሃይማኖት መሠረት ነው፡፡ ምግባር ደግሞ ግድግዳና ጣሪያ ነው፡፡ ቤት ቢያረጅ ጣሪያና ግድግዳው እንጂ መሠረቱ አይታደስም፡፡ መሠረቱን ለማደስ መሞከር ቤቱን ሙሉ በሙሉ አፍርሶ እንደገና መሥራት ነው፡፡ ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ “ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (1ኛ ቆሮ 3:11)።” ይላል፡፡ በዚህ መሠረትነት ላይ የጸናች ሃይማኖት ሰውን ታድሳለች እንጂ እርሷ አትታደስም፡፡
- የተዋሕዶ ምሳሌዎች (Examples of Miaphysite)
የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ፡- ነፍስና ሥጋ ተዋሕደው አንድ ሰው ይባላል እንጂ ሁለት አይባልም፡፡
የብረትና የእሳት ተዋህዶ፡- ብረት በእሳት ሲግል የጋለ ብረት እንጂ ይህ ብረት ነው፣ ይህ ደግሞ እሳት ነው ተብሎ አይለይም፡፡
የሲና ሐመልማል፡- እሳቱ ሐመልማሉን ሳያቃጥለው፣ ሐመልማሉም እሳቱን ሳያጠፋው በአንድነት (በተዐቅቦ) መታየታቸው የተዋህዶ ምሳሌ ነው (ዘፀ 3፡2)፡፡
- ይህንን አስተምህሮ የተቀበሉት (Miaphysite churches)
የተዋሕዶን (Miaphysite) አስተምህሮ የተቀበሉት ኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት ይባለሉ፡፡ እነዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን (Ethiopian Orthodox Tewahedo Church)፡ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን (Eritrean Orthodox Tewahedo Church)፡ የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን (Coptic Orthodox church)፡ የአርመንያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን (Armenian Orthodox Church)፡ የሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና (Syrian Orthodox Church) የህንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን (Indian Orthodox church) ናቸው፡፡ እነዚህ ጉባዔ ኬልቄዶንን የማይቀበሉ የምሥራቅ ኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት በዶግማቸው አንድ ናቸው፡፡
አንዳንድ ወገኖች “ኦርቶዶክስ የሚል ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም::” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ነገር ግን በትንቢት “በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች እወቁ፥ በእርስዋም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ እነርሱ ግን። አንሄድባትም አሉ (ኤር 6፡16)።” ይላል፡፡ በሐዲስ ኪዳንም “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው (ዕብ 13፡8)።” ይህ የሚያሳየው አንዲት ቀጥተኛ መንገድ/ሃይማኖት እንዳለች ነው፡፡ እርሷም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ናት፡፡ ይህን ስንልም በመረጃና በማስረጃ ነው፡፡ አስተምህሮ በቀጣይ እነዚህን መረጃዎችና ማስረጃዎች በቀጣይ ለአንባቢያን ታቀርባለች፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
በጣም አሪፊ ነው
LikeLike
በጣም አሪፍ ነው!
LikeLike