አንዲት እምነት/ሃይማኖት

እምነት ምንድን ነው? ሃይማኖትስ?

እምነት ማለት “ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው፡፡ ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደተዘጋጁ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን (ዕብ 11፡1-3)፡፡” ለምሳሌ መንግስተ ሰማያትን (የዘላለም ሕይወትን) ተስፋ እናደርጋለን፡፡እምነትም ይህንን ተስፋ ያረጋግጥልናል፡፡ የእግዚአብሔርን (የሰማዩን) መንግስት አላየነውም፡፡ እምነት ይህንን ያላየነውን ነገር ያስረዳናል፡፡ ሳይንስ ይህንን ሊያደርግ አይቻለውም፡፡  እምነት በፍጹም እውነት (absolute truth) ላይ እንጂ እንደ ሳይንስ በአንጻራዊ እውነት (relative truth) ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡

ሃይማኖት ማለት ደግሞ እምነትና አምልኮን በአንድ ላይ አጣምሮ የያዘ  የእምነትና የአምልኮ ሥርዓት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔርን አምነን የምናመልክበት ሥርዓት (system) ሃይማኖት ይባላል፡፡ የዚህም አስተምህሮ ትምህርተ ሃይማኖት ይባላል፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔርን እናምናለን፡ እርሱንም እናመልካለን፡፡ እርሱን ምን ብለን እንደምናምንና እንዴት እንደምናመልክ (የአምልኮ ሥርዓት እንደምንፈጽም) የሚገልጽ ሃይማኖት ነው፡፡ ስለዚህ የእምነት መገለጫው ሃይማኖት ነው፡፡

አንዲት ሃይማኖት/እምነት ማለት ምን ማለት ነው? ኤፌ 45.

የዚህ መነሻው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት” ብሎ ያስተማረው ነው (ኤፌ 4፡4-5)፡፡ ይህንን የጻፈበትም ዓላማ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ይተጉ ዘንድ (በመካከላቸው መለያየትን ያስወግዱ ዘንድ) ነበር።  በዚህ አገላለጽ መሠረት አንዲት ሃይማኖት ማለት የሚከተሉትን ትርጉሞች እንሚይዝ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡

አንዲት ሃይማኖት ማለት በአንድ አምላክ ማመን ነው፡፡

የአዳም አምላክ የአብርሀምም አምላክ ነው፡፡ ያው የአብርሀም አምላክ የይስሐቅም የያዕቆብም የሙሴም የዳዊትም የጴጥሮስም የእኛም አምላክ ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ያመነውን አምላክ እርሱ እንዳመነው አድርገን ካመንን እርሱ እንዳመለከውም አድርገን ካመለክን ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በሃይማኖት አንድ ነን፡፡ ልጆቻችንም እንደዚህ ካመኑ እንደዚህም ካመለኩ አንዲት ሃይማኖት ተጠብቃ ኖረች ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አንዲት ሃይማኖት ማለት በአንድ (በቁጥርም በባህሪም) አምላክ ማመንንና እርሱንም በአንድ አይነት አምልኮ ማምለክ ነው፡፡በብሉይም በሐዲስም ያለው አምላክ አንድ ነው፡፡ ሐዋርያው አንዲት ሃይማኖት ያለው ስለአንዱ አምላክ የሚሰብክ መሆኑን ለማስረገጥና ክርስትናም ቀደም ከነበረው ሃይማኖት በገሃድ በመገለጥ የቀጠለ ነው እንጅ ክርስትና አዲስ መጥ ሃይማኖት አይደለም ለማለት ነው፡፡

አንዲት ሃይማኖት ማለት በአንዲት ጥምቀት መወለድ ነው፡፡

የሃይማኖት መግቢያ በር በአንድ አምላክ አምኖ መጠመቅ ነው፡፡ ጥምቀትም ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ መወለድና የክርስቶስን ቤተሰብን መቀላቀል ነው፡፡ እያንዳዳችን የምንጠመቃት ጥምቀት አንዲት (በቁጥር) ናት፡፡ አትደገምም፡፡ ልጅ ከተባልንና ወደ እቅፉ ከገባን በኋላ ደግሞ ሌላ ስም ስለማይሰጠን ፣ ዳግመኛ ልጅነትም ስለማይኖር ፣ ጥምቀታችን አንዲት ብቻ ናት እንላለን ፡፡  ሁላችንም የተጠመቅናት የልጅነት ጥምቀት ዓላማዋ አንድ ነው፡፡ ይህም ልጅነትን ማግኘት ነው፡፡ በመጠመቃችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድነትን ፣ ኀብረትን እንፈጥራለን ፤ ሞትና ትንሣዔውን እንጋራለን ፤ መንፈሳዊ የጸጋ ልጅነትንም እናገኛለን ፡፡  ያ የልጅነት ጸጋም አንድ ነው (አይለያይም)፡፡ ስለዚህ ይህችን አንዲት ጥምቀት ተጠምቆ ልጅነትን አግኝቶ ከአንድ ከክርስቶስ ቤተሰብ የተቀላቀለ አንዲት ሃይማኖት ነው የሚከተለው ለማለት አንዲት ሃይማኖት አለ፡፡

አንዲት ሃይማኖት ማለት በአንድና ለአንድ ተስፋ መጠራት ነው፡፡

በአንድ አምላክ አምኖ አንዲት ጥምቀትን የተጠመቀ የሚጠባበቀው አንድ ተስፋ ነው፡፡ እርሱም ተስፋ መንግስተ ሰማያት (የዘላለም ሕይወትን) ነው፡፡ ለአንዱ ሌላ ለሌላው ሌላ ተስፋ የለም፡፡ አንድ ተስፋ እንጂ፡፡ ለአንድ ተስፋ የተጠራ በተላያየ ሃይማኖት ሊሆን አይችልም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ስለአንዲት ተስፋ ሰብከውላቸው ያመኑ ክርስቲያኖች አንድ ሃይማኖት ነበሩ፡፡ ጴጥሮስ ለተገረዙት ፣ ጳውሎስ ደግሞ ለአሕዛብ ቢያስተምርም ፣ ሃይማኖታችን አሁንም አንዲት ናት ፡፡ ስለዚህ ነው አንዲት ሃይማኖት ያለው፡፡

አንዲት ሃይማኖት ማለት አንድ አካል መሆን ነው፡፡

አንዲት ሃይማኖት ማለት አንድ አካል አንድ መንፈስ መሆን ነው፡፡ ሐዋርያው ይህንን ሲገልፅ “አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና… አካል ብዙ ብልቶች እንጂ አንድ ብልት አይደለምና…እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ።  (1ቆሮ 12፡27)።” ጌታም “እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ ዮሐ 15፡5።” እንዳለ በአንዱ ግንድ ላይ የተመሠረትን ነን፡፡ የተለያየ ጸጋ ቢኖረንም የአንዱ የክርስቶስ አካል ስለሆንን አንድ ሃይማኖት ነን እንጂ ብዙ ሃይማኖቶች አይደለንም፡፡

አንዲት ሃይማኖት ማለት በአንድ መንፈስ መመራት ነው፡፡

ክርስቶስ ካረገ በኋላ ቤተክርስቲያንን የሚመራት በሐዋርያት ላይ የወረደው መንፈስ ቅዱስ ነው (ሐዋ 2፡1)፡፡ ዛሬም ቤተክርስቲያንን በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል የሚመራት መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ”ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል እንዲል (1ቆሮ 12፡27)።”  በአንድ መንፈስ ቅዱስ የምንመራ አንድ እምነት አንድም ሃይማኖት እንጂ ብዙ እምነት ወይም ብዙ ሃይማኖት ሊኖረን አይችልም፡፡ ስለዚህም አንዲት ሃይማኖት ማለት አንድ መንፈስ ቅዱስ የሚመራት ማለት ነው፡፡

አንዲት ሃይማኖት ማለት አንድ ጊዜ የተሰጠች ማለትም ነው፡፡

ሃይማኖት አንድ ጊዜ የተሰጠች አንዲት ናት፡፡ ይህንንም “ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ (ይሁዳ 1፡3)።” ይህችም ሃይማኖት ኢየሱስ ክርስቶስ ራስ ሆኗት በአለት ላይ የመሠረታት ናት (ማቴ 16፡16)፡፡ በዚህ መሠረት ሃይማኖት ደግማ ደጋግማ የምትሰጥ አይደለችም፡፡ ለሐዋርያት የተሰጠችው ያችው ሃይማኖት ናት ዛሬም በእኛ ዘመን መኖር ያለባት፡፡ በዚህም መሠረት ሃይማኖት የምትጠበቅ (conservative) እንጂ በየጊዜው የምትሻሻል (progressive) አይደለችም፡፡ ስለዚህ ሃይማኖት አንዲት ናት፡፡

አንዲት ሃይማኖት ማለት አንዱን ክርስቶስን መምሰል ማለት ነው፡፡

ከአንዱ ከክርስቶስ እርሱን (ክርስቶስን) መምሰል እንዳለብን ተምረናልና ሃይማኖት አንዲት ናት፡፡ ስለዚህ ነገር ሐዋርያው “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? … ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን (ሮሜ 6፡4-5)” ብሏል፡፡  ጌታችንም “መምህራችሁ፣ ሊቃችሁ፣ አባታችሁ አንድ ነው (ማቴ 23፡8)፡፡” ብሎ አስተምሯል፡፡ እኛ ክርስቶስን መምሰል እንዳለብንም ሲናገር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተ እኔን ምሰሉ (1ኛ ቆሮ 11፡1)” ብሏል፡፡ ጌታችንም “ከእኔ ተማሩ (ማቴ 11፡29)” “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ (1ኛ ጴጥ 1፡16)” ብሎ ገልጾታል፡፡  እንግዲህ በሃይማኖት መኖር ማለት አንዱን ክርስቶስን መምሰል ከሆነ ሃይማኖትም አንዲት ናት ማለት ነው፡፡

አንዲት እምነት ወይስ አንዲት ሃይማኖት?

አንዳንዶች “በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ‘አንድ ሃይማኖት’ ቢልም በሌሎች ቋንቋዎች ግን ‘አንድ እምነት’ ነው የሚለው ስለዚህ አንድ እምነት ያላቸው የተለያዩ ሃይማኖቶች ሊኖሩ ይችላሉ::” ብለው ይከራከራሉ፡፡ ነገር ግን ከላይ እንደተገለጸው ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በእምነት ብቻ ሳይሆን በአምልኮም አንድ መሆን ማለትም እርሱ  ያመነውን ማመን: እንዳመነው አድርጎ ማመን እርሱም እንዳመለከው አድርጎ ማምለክ ነው ፍጹም ሊያደርግ የሚችለው፡፡ የአንዲት እምነት መገለጫዋ አንዲት ሃይማኖት ናት፡፡ የተለያየ እምነት እንጂ አንዲት እምነት በተለያየ ሃይማኖት አትገለጥም፡፡  አንዲት እምነት የምትገለፀው በአንዲት ሃየማኖት ነው፡፡ ይህም መገለጫው በአንድ አምላክ ማመለክ፣ አንዲት ጥምቀት መጠመቅ፣ ለአንድም ተስፋ መጠራት  ናቸው፡፡ ስለዚህ እምነትም ሃይማኖትም አንዲት ናት፡፡

ይህ እውነተኛይቱን እምነትና እውነተኛይቱን ሃይማኖት (በተረዳ ነገር ያወቅናትን) የሚመለከት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሌሎች እምነቶች እንደነበሩና እንደሚኖሩ  ግን በሐዋርያትም ዘመንም የታወቀ ነበር፡፡ 1ኛ ዮሐ 4፡1-3

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s