እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን እንደ እንግዳ ደራሽ በድንገት የተቋቋመች አይደለችም፡፡ ይህች አውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን እንደ ወሃ ደራሽ በድንገት የደረሰችም አይደችም፡፡ አማናዊቷ ቤተክርስቲያን እንደ ወፍ ዘራሽ በድንገት የተመሠረተችም አይደለችም፡፡ ዓለም ከተፈጠረበት ዘመን ከተቆጠረበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ምሳሌዎች እተመሰለች (በምሳሌዎች እየተገለጸች) በጥላ ውስጥ የነበረችና የኖረች ናት እንጂ፡፡
ሌሎች ራሳቸውን ቤተክርስቲያን የሚሉ ድርጅቶች ግን እንደዚህ አይደሉም፡፡ መሥራቾቻቸው ሰዎች ሰለሆኑ በድንገት ወይም በጥናት በሰው ሀሳብ የተመሠረቱና የሚመሠረቱ ናቸው፡፡ ያ የተመሠረቱበት ሀሳብና ዓላማ ሲያረጅ መታደስ ያስፈልጋቸዋል፤ አለበለዚያ ይፈርሳሉ፡፡ እንደ ምድራዊ ተቋም በሰው አስተሳሰብ የሚመሩ ናቸውና፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ አንዳንዶች ህገ ደንቡ ወይም አሠራሩ ወይም አመራሩ አልመች ሲላቸው ተገንጥለው ሌላ የራሳቸው ‘ቤተክርስቲያን’ ይመሠርታሉ፡፡ እንደዚያ እንደዚያ እያለ ዛሬ በሺዎች የሚቆጠሩ የእምነት ድርጅቶች ለመመሥረት በቅተዋል፡፡ አማናዊት ቤተክርስቲያን ግን እንደዚህ አይደለችም፡፡ ዘላለማዊና አንዱ አምላክ የመሠረታት ዘላለማዊትና አንዲት ናት እንጂ፡፡
የክርስቶስ ሐዋርያት ክርስቲያን ተብለው (ሐዋ 11፡26)፣ እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያንም በክርስቶስ ደም ተዋጅታና (ሐዋ 23፡20) አማናዊት ሆና እስክትገለጥ ድረስ በሕገ ልቡናና በሕገ ኦሪት ዘመን ብዙ ምሳሌዎች ነበሯት፡፡ ምሳሌ ያው ምሳሌ ነው፡፡ እውነተኛውን ነገር ለማስረዳት እንጂ ለመተካት የሚቀርብ አይደለም፡፡ እነዚህ ምሳሌዎች ለእውነኛይቱ የክርስቶስ ቤተከርስቲያን እንጂ ለሌሎች ራሳቸውን ቤተክርስቲያን ብለው ለሰየሙት ድርጅቶች የሚስማሙ አይደሉም፡፡ ለመረዳት ያህል በሕገ ልቡናና በዘመነ ኦሪት ሥርዓተ አምልኮ ይፈጽምባቸው ከነበሩት የቤተክርስቲያን ምሳሌዎች ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በኖኅ መርከብ ትመሰላለች (ዘፍ 7፡1)፡፡
በማየ አይህ /በጥፋት ውሃ/ ጊዜ ነፍሳት ከሞተ ሥጋ የዳኑባት ያቺ የኖኅ መርከብ የእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ምሳሌነቷም እንደሚከተለው ነው፡፡ ያቺ የኖኅ መርከብ ሦስት ክፍል ነበራት፡፡ ቤተክርቲያንም ቅድስት ፣ መቅደስ፣ ቅኔ ማህሌት የሚባሉ ሦስት ክፍሎች አሏት፡፡ የኖኅ መርከብ በውስጧ የነበሩት ነፍሳት ሁሉ ከጥፋት ውሃ ድነዋል፡፡ ወደ ቤተክርስቲያንም በክርስቶስ አምነው ተጠምቀው ሥጋ ወደሙን የተቀበሉ ከሞተ ነፍስ ይድናሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ቤተክርስቲያን በኖኅ መርከብ ስትመሰል ዓለም ደግሞ በጥፋት ውኃው ትመሰላለች፡፡ በቤተክርስቲያን በጥምቀት ገብተው እንደ ሕጉና ሥርዓቱ የሚኖሩ ሲድኑ እምቢ ብለው በዓለም የቀሩት ደግሞ በኃጥአት ምክንያት (በጥፋት ውኃ) ይጠፋሉና ምሳሌው ገላጭ ነው፡፡
ኖኅ መርከብን እንዲሠራ ያዘዘው እግዚአብሔር ነው፡፡ ቤተክርስቲያንንም የመሠረታት ራሱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ኖኅ ወደ መርከቡ ይገቡ ዘንድ ጥሪ ያስተላለፈው ለሁሉም ነው፡፡ ቤተክርስቲያንም የሰው ልጅ ሁሉ አምኖ ይድን ዘንድ የድኅነት ጥሪዋን ለሁሉም ነው የምታስተላልፈው፡፡ የኖኅ መርከብ ፈቃደኛ ሆኖ ለመጣ ሁሉ (ለእንስሳትም ጭምር) በቅታለች፡፡ ቤተክርስቲያንም አምኖ ለመጣ ሁሉ የሚበቃ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ያላት ናት፡፡ የኖኅ መርከብ የጥፋት ውኃ እስጎድል በውስጧ የነበሩትን ጠብቃ አቆይታ የጥፋት ውኃ ከጠፋ በኋላ ወደ መልካም ምድር አድርሳቸዋለች፡፡
ቤተክርስቲያንም ክርስቲያኖችን በዚህ ምድር ላይ ከኃጢአት ጠብቃ አቆይታ ለሰማያዊ ክብር ታበቃለችና በኖኅ መርከብ መመሰሏ ይህንን ምሥጢር አጉልቶ ስለሚያሳይ ነው፡፡ በተጨማሪም የጥፋት ውኃው እየሞላ ሲሄድ የኖኅ መርከብ ከምድር ከፍ ከፍ እያለች ትሄድ ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን የዓለም ፈተና ሲበዛባት በውስጥዋ የሚኖሩት (በፈተና የሚፀኑት) የሚያገኙት ክብር እንደዚሁ ከፍ ከፍ እያለ ይሄዳል፡፡ ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር ኖኅን አሰበ፣ የጥፋት ነፋስን አሳለፈ፣ ውኃውም ጎደለ፡፡ በቤተክርስቲያን ላይም የሚመጣውን ፈተና እንደዚሁ እግዚአብሔር ያሳልፋል፡፡
እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች (ዘፍ 18፡1)፡፡
“በቀትርም ጊዜ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የአድባር ዛፍ ተገለጠለት። ዓይኑንም አነሣና እነሆ፥ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ፤ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነስቶ ሮጠ፥ ወደ ምድርም ሰገደ፥ እንዲህም አለ። አቤቱ፥ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ፤ ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፥ እግራችሁን ታጠቡ፥ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፤ ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፥ ልባችሁንም ደግፋ ከዚያም በኋላ ትሄዳላችሁ፤ ስለዚህ ወደ ባሪያችሁ መጥታችኋልና። እነርሱም። እንዳልህ አድርግ አሉት።” ዘፍ 18፡1-5
አብርሃም ሥላሴን በቤቱ በእንግድነት የተቀበለባት ያቺ የአብርሁም ድንኳን (ኀይመተ አብርሃም) የእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ አብርሃም ሥላሴን በእንግድነት በቤቱ ድንኳን ስር እንደተገኙ በቤተክርስቲያን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ያድራሉ፡፡ በአብርሃም ድንኳን ውስጥ አብርሃም ምሥጢረ ሥላሴን እንደተማረ በቤተክርስቲያንም ምሥጢረ ሥላሴ ይነገራልና፡፡ በአብርሃም ድንኳን ድሀ ሀብታም፣ ነጭ ጥቁር፣ የተማረ ያልተማረ፣ ኃጥእ ጻድቅ ሳትል እንግዳ እንደተቀበለች ቤተክርስቲያንም ያለ አድሎ ሁሉን በእኩል አይን ትቀበላለች፡፡ በአብርሃም ድንኳን ምግበ ሥጋ ይመገቡባት እንደነበር በቤተክርስቲያንም ሥጋ ወደሙና ቃለ እግዚአብሔር እንመገባለን፡፡ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ቤተክርስቲያን በአብርሀም ድንኳን ትመሰላለች፡፡
በአብርሀም ድንኳን ውስጥ የነበሩት ሁሉ የየራሳቸው ምሳሌ አላቸው፡፡ አብርሀም የካህናት ምሳሌ ነው፡፡ መስዋዕትን ለእግዚአብሔር ሲሰዋ የነበረ ነውና፡፡ በአብርሀም ቤት ይስተናገዱ የነበሩት እንግዶች የክርስቲያኖች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያን በዚች ምድር ላይ ሲኖር እንግዳ ነውና፡፡ ምግበ ነፍስንም (የእግዚአብሔር ቃልንና የክርስቶስን ሥጋና ደም) ወደ ቤተክርስቲያን ቀርቦ ይመገባል፡፡ አብርሀም ቤት ሳይሠራ በድንኳን ውስጥ እድሜውን ሁሉ ኖሯል፡፡ ፍፁማን አገልጋዮችም እንደ አብርሀም ዓለምንና ጣዕሟን ሁሉ ንቀው ቤተክርስቲያንን ተጠግተው ይኖራሉና አብርሀም የእነዚህ አርአያ ነው፡፡ ሥሉስ ቅዱስ በአብርሀም ቤት ተገኝተው ቤቱን በበረከት ሞልተውታል፡፡ ዛሬም እንደዚሁ በእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ላመኑትና ለታመኑት ሁሉ ድኅነትን ያድላሉ፡፡
ከዚህ ሌላ ሰይጣን እንግዶች ወደ አብርሃም ድንኳን እንዳይሄዱ ይከለክል እንደነበር በትርጓሜ መጻሕፍት ሊቃውንት አስተምረዋል፡፡ ይህም ምሳሌው ክርስቲያኖች ወደ እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ሲሄዱ የተለያዩ ፈተናዎች እያቀረበ ሊያስቀራቸው እንደሚሞክር የሚያሳይ ነው፡፡ እንግዶች ቢቀሩም ሥሉስ ቅዱስ ተገኝተዋል፡፡ በቤተክርስቲያንም ሰዎች በተለያዩ ፈተናዎች ምክንያን ሳይሄዱ ቢቀሩ እንኳን እግዚአብሔር አገልግሎቱን እንደሚባርክ የሚያረጋግጥ ምሳሌ ነው፡፡
እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በሞሪያም ተራራ ትመሰላለች (ዘፍ 22፡12)፡፡
‹‹ከእነዚህም ነገሮች በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፥ እንዲህም አለው። አብርሃም ሆይ። አብርሃምም። እነሆ፥ አለሁ አለ። የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ሂድ፤ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው አለ።አብርሃምም በማለዳ ተነሥቶ አህያውን ጫነ፥ ሁለቱንም ሎሌዎቹንና ልጁን ይስሕቅን ከእርሱ ጋር ወሰደ፥ እንጨትንም ለመሥዋዕት ሰነጠቀ፤ ተነሥቶም እግዚአብሔር ወዳለው ቦታ ሄደ።
እግዚአብሔር ወዳለውም ቦታ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያውን ሠራ፥ እንጨትንም ረበረበ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያው በእንጨቱ ላይ አጋደመው። አብርሃምም እጁን ዘረጋ፥ ልጁንም ያርድ ዘንድ ቢላዋ አነሣ። የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ጠራና። አብርሃም አብርሃም አለው፤ እርሱም። እነሆኝ አለ። እርሱም። በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፥ አንዳችም አታድርግበት፤ አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደ ሆንህ አሁን አውቄአለሁ አለ። አብርሃምም ዓይኑን አነሣ፥ በኋላውም እነሆ አንድ በግ በዱር ውስጥ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፤ አብርሃምም ሄደ በጉንም ወሰደው፥ በልጁም ፋንታ መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው።›› ዘፍ 22፡1-14
እግዚአብሔር አበ ብዙኀን አብርሃምን አንድ ልጅህን ሠዋልኝ ባለው ጊዜ የዋሁ ይስሀቅ ሊሠዋበት ያለው ያ የሞርያ ተራራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም በህሊናው ይስሀቅን ቀብሮ እንጨት ፣ ቢለዋ፣ እሳት፣ ይዞ በደብረ ሞርያ ላይ ቢላውን አንሰቶ ሊሰዋው ሲል እግዚአብሔር ድምፁን አሰማው እንዲህ ብሎ “ አብርሃም አብርሃም ከብላቴናው ላይ እጅህን አንሳ ለምትወደው ልጅህ አልራራህምና አንተ እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንክ አውቃለሁ” ባለው ጊዜ ዞር ሲል በዕፀ ሣቤቅ የታሰረ ነጭ በግ አየ፡፡
ይስሐቅ የአዳምና ልጆቹ ምሳሌ ነው፡፡ በእርሱ ፈንታ እውነተኛው በግ ታርዶ አድኖታልና፡፡ ዕፀ ሣቤቅ የእመቤታችን ምሳሌናት፡፡ ዕፀ ሣቤቅ በይስሐቅ ፈንታ የተሰዋውን ነጭ በግ አሰገኝታለች፡፡ እመቤታችንም ለአዳምና ለልጆቹ ቤዛነት የተሰዋውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስገኝታለች፡፡ ነጭ በግ ደግሞ የክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ በይስሐቅ ፈንታ ተሰውቶ አዳምንና ልጆቹን አድኗልና፡፡ በሞሪያ ተራራው ላይ ይስሐቅ ያይደለ በጉ እንደተሰዋ በቤተክርስቲያንም የሩቅ ብዕሲ ደም ሳይሆን መለኮት የተዋሀደው ነፍስ የተለየው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ይፈተታል፡፡ ለዚህም ነው ይህች እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በሞሪያ ተራራ የምትመሰለው፡፡
እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በያዕቆብ ሐውልት ትመሰላለች (ዘፍ 35፡13-15)፡፡
‹‹እግዚአብሔርም ለያዕቆብ ከሁለት ወንዞች መካከል ከሶርያ ከተመለሰ በኋላ እንደ ገና ተገለጠለት፥ ባረከውም።እግዚአብሔርም፡- ስምህ ያዕቆብ ነው፤ ከእንግዲህም ወዲህ ስምህ ያዕቆብ ተብሎ አይጠራ፥ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ አለ፤ ስሙንም እስራኤል ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም አለው፡- ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ፤ ብዛ፥ ተባዛም፤ ሕዝብና የአሕዛብ ማኅበር ከአንተ ይሆናል፥ ነገሥታትም ከጕልበትህ ይወጣሉ። ለአብርሃምና ለይስሐቅም የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ፥ ከአንተም በኋላ ለዘርህ ምድሪቱን እሰጣለሁ። እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ከተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ። ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ቦታ የድንጋይ ሐውልት ተከለ፤ የመጠጥ መሥዋዕትንም በእርሱ ላይ አፈሰሰ፥ ዘይትንም አፈሰሰበት። ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የተነጋገረበትን ያን ቦታ ቤቴል ብሎ ጠራው።›› ዘፍ 35፡9-15
ቤቴል (ቤት-ኤል) ማለት የእግዚአብሔር ቤት ማለት ነው፡፡ ያቺ ሀውልት እግዚአብሔር ከያዕቆብ ጋር የተነጋገረባት ስፍራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በቤቴል እግዚአብሔር ለያዕቆብ ተገለፀለት፡፡ በቤተክርስቲያንም አምኖ ለቀረበ እግዚአብሔር በረድኤት ይገለፅለታል፡፡ በቤቴል እግዚአብሔር ያዕቆብን ባርኮታል፡፡ በቤተክርቲያንም ተግቶ የጸለየ እግዚአብሔር በረከትን ያበዛለታል፡፡ በቤቴል እግዚአብሔር የያዕቆብን ስም ለውጦ እስራኤል ብሎታል፡፡ ሰውም ወደ ቤተክርስቲያን ሲመጣ አዲስ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን ተቀብሎ አዲስ ማንነትን (ክርስትናን) ይዞ በአዲስ ስም (በክርስትና ስም) ይጠራል፡፡ እግዚአብሔር በቤቴል ያደረገው ሁሉ ዛሬ በቤተክርስቲያን ለሚደረገው ምሳሌ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በቤተል እግዚአብሔር እስራኤል ለተባለው ያዕቆብ ‹‹ለአብርሃምና ለይስሐቅም የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ፥ ከአንተም በኋላ ለዘርህ ምድሪቱን እሰጣለሁ።›› ሲል የዘላለም ኪዳነን ሰጥቶታል፡፡ ይህ ኪዳን ቤቴል በተባለችው ቤተክርስቲያንም ጸንተው ለኖሩት ለቅዱሳን የተሰጠ ኪዳን ነውና ያቺ እግዚአብሔር ለያዕቆብ የተገለፀባት ስፍራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ መሆኗ በተረዳ ነገር ላይ የተመሠረተ እንጂ በአጋጣሚ የተወሰደ አይደለም፡፡
ልክ እንደ ቤቴል ሰውና እግዚአብሔር የሚነጋገሩባት ስፍራ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ በዚያች ስፍራ ያዕቆብ የድንጋይ ሐውልትን መትከሉ ቤተክርስቲያን የተመሠረተችበትን ጽኑዕ መሠረት ያሳያል፡፡ ያዕቆብ በሐውልቱ ላይ ዘይትን አፈሰሰ፡፡ ይህም ዛሬም አዲስ ቤተክርስቲያን እንዴት እንደሚከብር ያሳያል፡፡ በዚያች ቦታ ላይ ያዕቆብ የመጠጥን መስዋዕት እንዳቀረበ በቤተክርስቲያንም አማናዊው የክርስቶስ ደም ለመስዋዕትነት ይቀርባል፡፡ በቤቴል ያዕቆብ የተከላት ሐውልት የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት ስንል እነዚህ ሁሉ ትንታኔዎችን በማስተዋል ነው፡፡
እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በደብረ ሲና ትመሰላለች (ዘፀ 34፡1)፡፡
‹‹እግዚአብሔርም ሙሴን። በእነዚህ ቃሎች መጠን ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ አለው። በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ እንጀራም አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። በጽላቶቹም አሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ። እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ሁለቱ የምስክር ጽላቶች በሙሴ እጅ ነበሩ፤ ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ተነጋገረ የፊቱ ቁርበት እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር።›› ዘፀ 34፡27-29
ሊቀ ነቢያት ሙሴ በደብረ ሲና አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመና ከጸለየ በኋላ ዐሥርቱ ቃላተ የተጻፈበትን ጽላት /ታቦተ ጽዮን/ ከእግዚአብሔር እጅ ተቀበለ፡፡ በቤተክርስቲያንም ክርስቲያኖች በጾምና በጸሎት ተግተው ሰማያዊ ክብርን (ቃል ኪዳንን) ያገኛሉና ቤተክርስቲያን በደብረ ሲና ተራራ ተመስላለች፡፡ በደብረ ሲና ተራራ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል በቃል ተነጋግሯል፡፡ በቤተክርስቲያንም በጾምና በጸሎት የተጉ አባቶች ከእግዚአብሔር ጋር ይነጋገራሉና ምሳሌነቱ ትክክለኛና ተገቢም ነው፡፡ ሙሴ ከደብረ ሲና ተራራ ሲወርድ ፊቱ እያበራ ነበር፡፡ በቤተክርስቲያን የኖረ ሰው ከዚህ ዓለም ተለይቶ ሲሄድ በመላእክት ታጅቦ እንደዚህ እያበራ ነውና ምሳሌነቱ ጽኑዕ ነው፡፡
እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በደብተራ ኦሪት ትመሰላለች (ዘፀ 40፡1)፡፡
‹‹እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። ከመጀመሪያው ወር በፊተኛው ቀን የመገናኛውን ድንኳን ማደሪያ ትተክላለህ። በእርሱም ውስጥ የምስክሩን ታቦት ታኖራለህ፥ ታቦቱንም በመጋረጃ ትጋርዳለህ። ገበታውንም አግብተህ በእርሱ ላይ የሚኖረውን ዕቃ ታሰናዳለህ፤ መቅረዙንም አግብተህ ቀንዲሎቹን ትለኵሳለህ። ለዕጣንም የሚሆነውን የወርቅ መሠዊያ በምስክሩ ታቦት ፊት ታኖራለህ፥ በማደሪያውም ደጃፍ ፊት መጋረጃውን ትጋርዳለህ። ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውንም መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው ደጅ ፊት ታኖረዋለህ።›› ዘፀ 40፡1-6 ይህች በብሉይ ኪዳን የነበረች ደብተራ ኦሪት ምሳሌነቷ በሐዲስ ኪዳን ላለችው አማናዊት የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ነው፡፡
እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በሰሎሞን ቤተመቅደስ ትመሰላለች (1ኛ ነገ 9፡1)፡፡
‹‹ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት፥ የንጉሡን ቤትና ሰሎሞን የወደደውን የልቡን አሳብ ሁሉ ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በገባዖን ለሰሎሞን እንደ ተገለጠለት ዳግመኛ ተገለጠለት። እግዚአብሔርም አለው፡- በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ። …እናንተና ልጆቻችሁ ግን እኔን ከመከትል ብትመለሱ፥ የሰጠኋችሁንም ትእዛዜንና ሥርዓቴን ባትጠብቁ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ ብትሰግዱላቸውም፥ እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር አጠፋቸዋለሁ፤ ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ፤ እስራኤልም በአሕዛብ ሁሉ መካከል ምሳሌና ተረት ይሆናሉ። ከፍ ከፍ ብሎ የነበረውም ይህ ቤት ባድማ ይሆናል፤ በዚያም የሚያልፍ ሁሉ እያፍዋጨ። እግዚአብሔር በዚህ አገርና በዚህ ቤት ስለምን እንዲህ አደረገ? ብሎ ይደነቃል። መልሰውም፡- ከግብጽ ምድር አባቶቻቸውን ያወጣውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ትተው ሌሎችንም አማልክት ስለ ተከተሉ፥ ስለ ሰገዱላቸውም፥ ስለ አመለኩአቸውም፥ ስለዚህ እግዚአብሔር ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣባቸው ይላሉ።›› 1ኛ ነገ 9፡1-8
ከደብተራ ኦሪት ቀጥሎ እግዚአብሔር አምላክ እንደልቤ ብሎ ያከበረው ቅዱስ ዳዊት በዘመኑ ለአምላኩ ቤተ መቅደስ ሊሠራ ቢፈልግም ቤተመቅደስ የሆነ የኦርዮን ሠውነት አፍርሰሃልና አትሠራም ነገር ግን ልጅህ ይሠራዋል ብሎ ቃል ገባለት፡፡ ንጉሥ ሠሎሞንም ቃል እንደተገባለት ውብና ያመረ በወርቅ የተለበጠ ቤተ መቅደስ ሠርቷል፡፡ ይህችም ቤተ መቅደስ ለአማናዊቷ ቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ‹‹ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ›› እንዳለ በዚያች ቤተመቅድስ እግዚአብሔርና ሰው ተገናኝተዋልና የአማናዊት ቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በዚህች ቤተመቅደስም ክርስቶስ ተገኝቶ ባርኮ ከወንበዴዎች አፅድቶ ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ያለው የአማናዊት ቤተክርስቲያን ምሳሌ ስለሆነች ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ለእርሱ ስንታዘዝ ብቻ ነው፡፡
ነገር ግን ትዕዛዙን የማንጠብቅና በእርሱም ላይ የምናምጽ ከሆነ ‹‹እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር አጠፋቸዋለሁ›› እንዳለ እድል ፈንታችን የዘላለም ሕይወት አይሆንም፡፡ የማንታዘዝ ከሆነ ‹‹ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ›› እንዳለ በምድር ያለችው ቤተክርስቲያን ለፈተና ትዳረጋለች፡፡ ከእርሱ ፈቀቅ የምንል ከሆነ ‹‹እስራኤልም በአሕዛብ ሁሉ መካከል ምሳሌና ተረት ይሆናሉ።›› እንዳለ በእኛም ላይ እንደዚሁ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በቤተክርስቲያን ስንኖር እግዚአብሔርን ፈርተን እርስ በእርስም በፍቅር እየኖርን ሊሆን ይገባል፡፡ በጥልና በክርክር ወይም በዘረኝነትና በመከፋፈል የምንኖር ከሆነ ግን የዚህ ትንቢት መፈፀሚያ መሆናችን አይቀርም፡፡
እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በደብረ ታቦር ትመሰላለች፡፡ ማቴ 17፡1-8
በአዲስ ኪዳን ከተገለጹት የቤተክርስቲያን ምሳሌዎች መካከል አንዱ ደብረ ታቦር (የታቦር ተራራ) ነው፡፡ በዚህ ተራራ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሀነ መለኮቱን ገልፆበታል፡፡ ይህንን ድንቅ ምስጢር ወንጌላዊ ማቴዎስ ‹‹ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን፥ ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ። እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር። ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና፥ ተነሡ አትፍሩም አላቸው። ዓይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም(ማቴ 17፡1-8)።›› በማለት አስፍሮታል፡፡
በአባቶች አመስጥሮ የታቦር ተራራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ‹‹ከስድስት ቀን በኋላ›› የሚለው ምሳሌው ቤተክርስቲያን በስድስተኛው ሺህ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደምትመሠረት የሚያሳይ ነው (ትርጓሜው በስድስተኛው ወር መልአኩ (ሉቃ 1፡26)….እንደሚለው ነው)፡፡ በደብረ ታቦር ሦስቱን ደቀመዛሙርት ብቻ ይዞ መውጣቱ ምሥጢረ ክህነት ለሁሉም ሳይሆን ለካህናት ብቻ የሚፈፀም ምሥጢር መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ብርሀነ መለኮቱንም የገለፀላቸው ለእነዚህ ብቻ ነበር፡፡
በደብረ ታቦር ክርስቶስ ብርሀነ መለኮቱን ገለጸ፡፡ በቤተክርስቲያንም እንደዚሁ የክርስቶስ ማደሪያው ናት፡፡ በደብረ ታቦር ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን ሙሴ ከብሔረ ሙታን ሐዋርያቱ ደግሞ በአካለ ሥጋ ያሉት በአንድነት ከአምላካቸው ጋር ተገኝተዋል፡፡ ቤተክርስቲያንም በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳንና በአካለ ሥጋ ያሉ ክርስቲያኖች ከአምላካቸው ጋር ያላቸው አንድነት ናትና የደብረ ታቦር ምሳሌ ጠንካራ መሠረት ያለው ነው፡፡ በቤተክርስቲያንም በቅዳሴ የሚሳተፉት ልዑካን አምስት ናቸው፡፡ ኤልያስና የሙሴ የሁለቱ ቀሳውስት፣ ሦስቱ ደቀመዛሙርት የሦስቱ ዲያቆናት ምሳሌ፣ ጌታችንም የመስዋዕቱ ምሳሌ ናቸው፡፡ ሊቃውንት አባቶች ይህንን ምሳሌ ከነምስጢሩ እንደዚህ አብራርተው አስተምረዋል፡፡
በዚያ በደብረ ታቦር ተራራ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን:- ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ።›› እንዳለው በቤተክርስቲያንም ከቅዱሳንና ከቅዱሳን አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ምንኛ መልካም ነው? የክርስትናም ዓለማው ሰው ይህንን ሰላም አግኝቶ ከአምላኩ ጋር እየተነጋገረ በቤተክርስቲያን ይኖር ዘነድ ነው፡፡