ዕረፍትሽን እያሰብን ሰላም እንልሻለን!

ዕረፍታ ለማርያም

ጥር 21 ቀን እመቤታቸን ቅድስት ድንግል ማርያም ያረፈችበት ቀን ነው፡፡ በዚህ ዕለት ቅድስት ቤተክርስቲያናችን የእመቤታችንን ዕረፍት በማሰብ ታከብራለች፡፡ አብ የመረጣት፣ ወልድ የተወለደባት፣ መንፈስ ቅዱስ ያከበራት  ማኅደረ መለኮት (የመለኮት ማደሪያ) የከበረች እመቤት ያረፈችበት ዕለት ነው፡፡ ያቺ ቅዱስ ገብርኤል ‹‹ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ›› ያላት፣ ቅድስት ኤልሳቤጥ ‹‹የጌታዬ እናት›› ብላ ያመሰገነቻት፣ ክቡር ዳዊት ‹‹ልጄ›› ብሎ የዘመረላት፣ ጠቢቡ ሰሎሞንም ‹‹እህቴ›› ብሎ የተቀኘላት፣ ለወንጌላዊው ዮሐንስ ‹‹እናትህ እነኋት›› የተባለችው የተወደደች እመቤታችን ያረፈችበት ዕለት ነው፡፡

ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በመዝሙር፣ አፈ በረከት ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ፣ ደገኛው ቅዱስ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ፣ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ በሰዓታት፣ ቅዱሳን መላእክትን በምስጋና የመሰላቸው ቅዱስ ያሬድ በማኅሌት ያመሰገኗት ከንግግርና ከቋንቋዎች ሁሉ በላይ የሆነ ምስጢር የተፈፀመባት እመቤት ያረፈችበት ዕለት ነው፡፡ ዕረፍቷም በመልክአ ማርያም ‹‹ሰላም ለፀአተ ነፍስኪ እንበለ ፃዕር ወፃማ፡ ያለመጨነቅና ያለፃእር ከሥጋዋ ለተለየች ነፍስሽ ሰላምታ ይገባል›› እንደተባለው ያለመጨነቅና ያለፃእር ነበር፡፡ ያለ አንዳች መጨነቅ ጌታን የወለደቸው እመቤት ያለ አንዳች መጨነቅ ቅድስት ነፍስዋን ከክብርት ሥጋዋ ተለይቶ በቃለ አቅርነት በዝማሬ መላእክት ጌታችን አሳርጓታል፡፡  እርሷ፡-ሦስት ዓመት በእናት በአባቷ ቤት፣ አስራ ሁለት ዓመት በቤተመቅደስ፣ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከልጇ ጋር፣ አስራ አምስት ዓመት በዮሐንስ ቤት፣ በአጠቃላይ ስድሳ አራት ዓመት በዚህ ምድር ላይ ኖራ ዐርፋለች፡፡ለዚህም በህይወተ ሥጋ በኖረችበት ዘመን ልክ ቅዱስ ኤፍሬም ውዳሴ ማርያምን በ64 አንቀጽ ከፍሎ 64 ጊዜ ሰአሊ ለነ ቅድስት ብለን እንድናመሰግናት አድርጓል፡፡

በጥር 21 ቀን እመቤታችን ጌታችን አየሱስ ክርስቶስ፣ ቅዱሳን መላእክትና ደጋግ ቅዱሳን አባቶች በተገኙበት እጅግ ታላቅ በሆነ ክብር ባረፈችበት ዕለት ሐዋርያት በጌቴሴማኒ ሊቀብሯት ሲሉ በክርስቶስ ትንሳኤ ያፈሩት አይሁድ የክርስቶስ የሆኑትን ማሳደድ ልማዳቸው ነበርና “እርሷንም እንደ ልጇ ተነሳች አረገች እንዳይሉ፣ ሥጋዋን እናቃጥል” ብለው በክፋት ተነሱባቸው፡፡ ከአይሁድም ወገን የሆነ ታውፋንያ የሚባል ሰው የከበረ ሥጋዋን ለማቃጠል ሲታገል፣ በተዓምራት ተቀጣ፤  ሥጋዋ ከጌቴሴማኒ ተነጥቆ በገነት በዕፀ ሕይወት ስር እስከ ነሐሴ 14 ቀን ቆይቷል፡፡ ኋላም በልጇ ኃይልና ስልጣን ከሞት እንድትነሳና እንድታርግ አድርጓታል፡፡ ይህም በጥልቀት በጥር 21 እና ነሐሴ 16 ስንክሳር ላይ በሰፊው ተጽፎ ይገኛል፡፡

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዕረፍት ባሰብን ጊዜ በአላዋቂ ልቡና ሊፈጠር የሚችል አንድ ጥያቄ አለ፡፡  እርሱም፡- ከቤተክርስቲያን ወገን ሞትን እንዳያዩ የተወሰዱ ቅዱሳን (ሄኖክ፣ ኤልያስ…) አሉ፡፡ እርሷ የኃያሉ እግዚአብሔር መቅደሱ፣ እናቱ፣ ታቦቱ፣ መንበሩ ሆና እያለች ስለምን ሞትን ቀመሰች? ለምንስ እንደነዚህ ቅዱሳን አላሳረጋትም? የሚል ጥያቄ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሥራ አይመረመርም፣ ፍጡርም የሥራውን አመክንዮ ያለ መንፈስ ቅዱስ አጋዥነት መርምሮ ማወቅ አይቻለውም፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍትን ምስጢራት ስንመረምር በጥልቅ መረዳትና መንፈሳዊነት መሆን አለበት፡፡ ማረግ ብቸኛ የፅድቅ ሚዛን አለመሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ሴት እንደ ሄኖክ ፃድቅ ነበር፣ መጥምቁ ዮሐንስም እንደ ኤልያስ ባህታዊ፣ ገባሬ ተዓምር ነበር። ሄኖክና ኤልያስ ሲያርጉ ሴትና መጥምቁ ዮሐንስ ግን አርፈዋል። ከዚህ ምድር በሞተ ሥጋ ተለይቶ የነበረው ሊቀ ነቢያት ሙሴም በብሔረ ሕያዋን ከነበረው ከኤልያስ ጋር በደብረ ታቦር በአንድነት ተገልጠዋል፡፡ ማቴ 17፡1-5

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ፍጥረታዊ ሰው ለሚያነሳቸው ክርክሮች የቤተክርስቲያን ሊቃውንት በአፍም በመጽሐፍም ሲመልሱ ኖረዋል፣ ወደፊትም እንዲሁ ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡ እመቤታችን ሞተ ሥጋን ማየቷን ሊቃውንት አባቶቻችን በሦስት ምክንያቶች እንደሆነ ያስተምራሉ፡-

ጌታች የለበሰው የአዳምን ሥጋ መሆኑን ለማስረገጥ፡ በመንፈስ ቅዱስ  የቅዱሳት መጻሕፍትንና የታሪክ ድርሳናትን ስንመረምር “ምድራዊት ሴት ብትሆን ኖሮ ሰማይንና ምድርን ለፈጠረ አምላክ እንዴት ማደሪያው ልትሆን ትችላለች?” የሚሉ ወገኖች ነበሩና የሰው ልጅ መሆኗን፣ ክርስቶስም የለበሰው የአዳምን ሥጋ መሆኑን ለማስረገጥ ነው፡፡ የሥጋን ሞት በመሞቷ የአዳም ዘር መሆኗ (ከሰማይ የመጣች አለመሆኑ) ታወቀ፡፡

ጌታችን በፍርዱ አድልዎ እንደሌለበት እንዲታወቅ፡ ሥጋን የለበሰ ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ግድ ነውና ህይወት የተባለ የክርስቶስ እናት እመቤታችንም እንደ ከበሩ የጌታ ባለሟሎች በሞተ ስጋ ተወስዳለች፡፡ ዛሬም በሥጋ ያለነው ወደፊትም የሚኖሩት ሞትን ይቀምሳሉ፡፡በብሔረ ሕያዋንም ያሉት እንዲሁ፡፡ሞት ለማንም የማይቀር ፍርድ ነውና፡፡ ይህም በመጽሐፈ ዚቅ  ‹‹ለምንት ይዜኃር ኃያል በኃይሉ ወባዕል በብዝኃ ብዕሉ ኢያድለወ፤  ሞተ ክርስቶስ ለሥጋ አባሉ፤ ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐፅብ ለኵሉ፡፡ ኃይለኛ በኃይሉ ለምን ይታጀራል? ባለ ጸጋም በሀብቱ ብዛት፡፡ ክርስቶስ ለአካሉ አላደላም፤ ሞትስ ለሟች ይገባዋል፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ማርያም ሞት ግን አስደናቂ ነው፡፡›› ተብሎ ተገልጿል፡፡

በምድር የነበራት የኃዘንና የስደት ዘመን እንዲያበቃ፡ እመቤታችን ህይወቷ ከህፃንነቷ ጀምሮ በብዙ ፈተና የተሞላ ነበር፡፡ በተለይም ስምኦን አረጋዊ በቤተመቅደስ ‹‹በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል›› ብሎ እንደተነበየላት (ሉቃ 2፡35) በግብፅ ስደት፣ በቀራኒዮ ስቅለት፣ በአይሁድ ክፋት የደረሰባት መከራና ኃዘን አብቅቶ ወደ ዘላለም ደስታ ትገባ ዘንድ ሞትን ቀምሳለች፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ወዳጄ ሆይ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ ነዪ፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ፤ ዝናሙም አልፎ ሔደ፡፡ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፤ የዜማም ጊዜ ደረሰ፡፡ የቍርዬም ቃል በምድር ላይ ተሰማ፤›› /መኃ.2፥10-14/ ›› እንዳለ ኃዘኗ ያልፍ ዘንድ ወደ ዘላለም ደስታም ትገባ ዘንድ ዐርፋለች፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ለዛቲ ብእሲት ሠረቀ ላዕሌሃ ብዕለ ጸጋሁ ለአብ ወአግዓዛ እምእኩይ ውስተ ሠናይ እሞት ውስተ ሕይወት፤ በድንግል ማርያም ላይ የአብ የባለጸግነቱ ብዛት ተገለጠ፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከክፉ ዓለም ወደ በጎ ዓለም አሸጋግሯታልና፤›› ያለውም ይህንን ያመለክታል፡፡

አሁን እርሷ፡- በልጇ ቀኝ በክብር ቆማ በከበረ ምስጋና ታመሰግነዋለች፣ የከበረ ስሙን ከፍ ከሚያደርጉት ቅዱሳን ጋርም በመንፈሳዊ አንድነት ታከብረዋለች፣ ከገቡ ከማይወጡበት ሰማያዊ ሀገር ትኖራለች፡፡ ስደት፣ መከራ፣ ኃዘን ከሌለባት ሀገር አለች፡፡ በዕለተ ምጽዓት ቅዱሳን ሩጫቸውን ጨርሰው አክሊል ከሚቀዳጁበት ስፍራ አለች፡፡ ‹‹በአምላካችን ከተማ እግዚአብሔር ለዘላለም ያፀናታል›› እንደተባለ (መዝ 47፡8) በዚያ ከፍጡራን ሁሉ በላይ በሆነ በታላቅ ክብርና ጸጋ ለዘላለም ትኖራለች፡፡

እኛም የዕረፍቷን ዕለት በምስጋና በዝማሬ እናከብረዋለን፡፡ ቅዱሳን ያረፉበትን ቀን በደስታ ከበሮ እየመታን እየዘመርን እናከብራለን፡፡ ዕረፍቷን የምናከብረው ለእርሷ ክብርን ለመጨመር አይደለም፤ ራሳችን እንከብርበት ዘንድ ነው እንጂ፤ በረከትን ረድኤትን እናገኝበት ዘነድ ነው እንጂ፡፡ እርሷን ስናከብር – ልደቷን ዕረፍቷን ዕርገቷን ስናከብር – ያከበራትን ልጇንም እናከብራለን፤ በረከቷንም እናገኛለን፡፡

በምድር ላይ በአካለ ሥጋ ያሉ ሰዎችን ልደት በባህላዊ መንገድ ስናከብር፡ በመወለዳቸው ደስ ይላቸው ዘንድ አብረን በመደሰት ነው፡፡ በሕይወተ ሥጋ የተለዩንን ዘመዶቻችንን ስናስብ ደግሞ ‹‹ነፍስ ይማር›› እያልን በመጸለይ ነው፡፡ የቅዱሳንንና የእመቤታችንን ልደትንና ዕረፍትን ስናስብ ግን እንደዚህ አይደለም፡፡  እነርሱን እያመሰገንን፣ ተጋድሏቸውን እያሰብን፣ ያከበራቸውን አምላክ እያከበርን፣ ክብራቸውንም እያደነቅን፣ በረከታቸው ረድኤታቸው አማላጅነታቸው ይደርሰን ዘንድ እየተማጸንን ነው እንጂ፡፡ የእመቤታችንንም ዕረፍት ስናከብር ይህንን እያስተዋልን ሊሆን ይገባል፡፡ ልመናዋ ፍቅሯ አማላጅነቷ የልጅዋም ቸርነት በሁላችን ላይ አድሮ ይኑር፡፡ አሜን፡፡

1 thought on “ዕረፍትሽን እያሰብን ሰላም እንልሻለን!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s