ዘወረደ፡ ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም

ዐቢይ ጾም ‹‹ዐቢይ›› የተባለው የዓለማት ፈጣሪ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአርአያነት ጾሞ የመሠረተው ጾም ስለሆነ ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ካሉት ሰባት የአዋጅ አጽዋማት ረጅሙ (55 ቀን ያለው) ስለሆነ ደግሞ ‹‹ሁዳዴ›› ይባላል፡፡ ኢትዮጵያዊው የዜማና የቅዱሳት መጻሕፍት ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በዓቢይ ጾም ውስጥ የሚገኙትን ስምንት ሣምንታት ለትምህርት፣ ለአዘክሮና ለምስጋና በሚመች መልኩ ልዩ ስያሜዎች ሰጥቷቸዋል፡፡ ስለሆነም በእያንዳንዱ ሳምንት (ሰንበት) የሚነበቡ፣ የሚተረጎሙ፣ የሚዘከሩ፣ የሚዘመሩ ልዩ ልዩ መጽሐፍ ቅዱሣዊ ኩነቶችና አስተምህሮዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ የመጀመሪያው ሰንበት ‹‹ዘወረደ›› ይባላል፡፡ በዚህ ሰንበት ዕለት በቤተክርስቲያናችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ለማዳን ከሰማይ ስለመውረዱ የሚነገርበትና የሚዘመርበት በመሆኑ ‹‹ዘወረደ›› ተብሏል፡፡ በዚህ ዕለት የሚነበበው የወንጌል ክፍል ‹‹ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፤ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው (ዮሐ 3፡13)›› የሚለው ይገኝበታል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ቃል የተናገረው ስለ ሰማያዊው ምሥጢር ለኒቆዲሞስ ባስተማረበት ጊዜ ነበር፡፡

ለመሆኑ ‹‹ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም›› ማለት ምን ማለት ነው? ይህንን ጥቅስ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጉም ባለመረዳት ለክህደታቸው የሚመች የመሰላቸውን ቃል እየመዘዙ ክደው የሚያስክዱ፣ ተጠራጥረው የሚያጠራጥሩ መናፍቃንም  በአላዋቂ አዕምሮ፣ በኢአማኒ ልቦና ያለ አውዱ በመጥቀስ በተለያዩ ቅዱሣት መጻሕፍት የተመሰከሩ፣ በታሪክ የታወቁ የቅዱሣን ሰዎችን እርገት እንዲሁም የቅዱሳን መላእክትን ለተልእኮ ከሰማይ ወደ ምድር፣ ከምድር ወደ ሰማይ መውረድና መውጣት ለመቃወም ይጠቀሙበታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስና የቤተክርስቲያን ታሪክ ግን የቅዱሳን ሰዎችን ዕርገትና የቅዱሳን መላእክትን  ለተልእኮ መውረድና መውጣት ያለጥርጥር ያስረዳናል፡፡ እኛ የሐዋርያትን ፈለግ የምንከተል ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ግን ከቅዱሳን መካከል ነቢዩ ኤልያስንና ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክን ጨምሮ የተወሰኑ ቅዱሳን ሞትን ሳይቀምሱ ማረጋቸውን፣ ቅዱሳን መላእክት የሰው ልጆችን ጸሎትና የእግዚአብሔርን የማዳን ብስራት ይዘው ከሰማይ ወደ ምድር፣ ከምድር ወደ ሰማይ መመላለሳቸውን፣ ሌሎች ቅዱሳንም በስጋ ተነጥቀው (ዐርገው) የሰማያትን ምስጢር በተዓምራት ማየታቸውን፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግልም በልጇ ኃይልና ስልጣን ከሞት ተነስታ ማረጓንና በሰማያት፣ በሰማያዊ መዓርግ በልጇ ቀኝ መቆሟን እናውቃለን፤ እናምናለን፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ‹‹ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም›› የሚለው ቃል ምሥጢሩ ምንድን ነው? ሊቃውንት አባቶች እንዳስተማሩት ይህ የጌታችን ቃል የሚከተሉትን አምስት ነጥቦች ያስረዳል፡፡

  1. ፍጹም ሰው፣ ፍጹም የባህርይ አምላክ ከሆነ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ማያዊ እውቀት የባህርዩ የሆነ፡ ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ እውቀትን ገንዘብ ያደረገ ምድራዊ መምህር የለም፡፡ ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ እውቀትን ገንዘብ ያደረገ ከሰማይ የወረደው ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ከምድራዊያን መምህራን በራሱ ወደ ሰማይ ወጥቶ፡ ተመልሶ ወርዶ ያየውን የሚያስተምር የለም፡፡ እርሱ ከሰማይ የመጣው ግን ሰማያዊ ምስጢርን ለማስተማር (ለመግለጥ) የራሱ ባህርይ (የባህርዩ) ነው፡፡
  2. ከጌታችን በቀር በኅልውና ያየውን የሚገልጥ፡ በሰማይ ሆኖ በህልውና ያየውን በህልውና የሰማውን መጥቶ የሚያስተምር ምድራዊ መምህር የለም፡፡ በሰማይ ሆኖ በህልውና ያየውን በህልውና የሰማውን የራሱን ምሥጢር ያስተማረ እርሱ ብቻ ነው፡፡ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው፡፡
  3. ከጌታችን በቀር ከሰማያዊ ዙፋን የወረደ የለም፡፡ ሰማይ የልዕልና ስፍራ፣ የእግዚአብሔር ዙፋን ነው፡፡ በዚያ ዙፋን የተቀመጠ፣ ሰውንም ለማዳን ከዙፋኑ የወረደ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሌላ በዚያ ዙፋን የተቀመጠ ከዚያ ዙፋንም የወረደ የለም፡፡ ሰውን ለማዳን ከዙፋኑ የወረደው በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው፡፡
  4. ከጌታችን በቀር በራሱ ፈቃድ ከሰማይ የወረደ የለም፡፡ ፍጡራን (መላእክትና ሰዎች) ወደ ሰማይ ቢወጡም ቢወርዱም በራሳቸው ፈቃድ አይደለም፡፡ በራሱ ፈቃድ በአባቱ ፈቃድ ከሰማይ የወረደ ወደ ሰማይም የወጣ እርሱ ብቻ ነው፡፡ በራሱ ፈቃድ ከሰማይ የወረደው በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው፡፡
  5. ከጌታችን በቀር በባህርይው መለወጥ የሌለበት፣ አንድ ባህርይ የሆነ፣ ይህንንም በራሱ ፈቃድ የወሰነ የለም፡፡ ከሰማይ የወረደው ወደ ሰማይ የወጣውም አንድ አካል አንድ ባህርይ ነው፡፡ ከሰማይ አንድ አካል አንድ ባህርይ ሆኖ ወርዶ፡ ሁለት ባህርይ ሁለት አካል ሆኖ ወደ ሰማይ የወጣ አይደለም፡፡ ልክ አንድ አካል አንድ ባህርይ ሆኖ እንደወረደ አንድ አካል አንድ ባህርይ ሆኖ ወጣ ማለት ነው፡፡ አንድ ባህርይ ሆኖ ወርዶ አንድ ባህርይ ሆኖ ወደ ሰማይ የወጣው በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው፡፡

ዘወረደ በተባለችው በዚህች የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሰንበት ወልደ እግዚአብሔር ስለ ድኅነታችን መውረዱን እያሰብን ስናመሰግን የመውረዱንም ምክንያት በሚገባ ከመረዳት ጋር ሊሆን ይገባል፡፡ ጌታችን ከሰማይ የወረደው፣ ከድንግል ማርያም የተወለደው፣ በዚህ ምድር ላይ እንደ ሰው ተመላልሶ ያስተማረው ስለ ሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንደኛው ለቤዛነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለአርአያነት ነው፡፡

ለቤዛነት፡- በእርሱ የሚያምን የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው፣ የሰው ልጅ ዳግመኛ እንዳይጠፋ፤ እርሱ ስለእኛ ተሰቅሎ ቤዛ ሊሆነን፤ ዓለም በልጁ ቤዛነት እንዲድን እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ስለወደደ ለቤዛነት ከሰማይ ወረደ፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር ለዘላለም ንጉስ ነው፤ በምድር መካከልም መድኃኒትን አደረገ (መዝ 73፡12)›› እንዳለ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን በዓለም እንዲፈርድ አልላከውም፡፡ መድኃኒት ሆኖ እንዲያድነን እንጂ፡፡ ስለዚህ በእርሱ የሚያምን አይፈረድበትም፤ በእርሱ ያላመነ ግን በአንዱ የእግዚአብሔር ልጅ  ስላላመነ ተፈርዶበታል እንደተባለ በስሙ አምነን ቤዛ ይሆነን ዘንድ ወረደ፣ ተወለደ፡፡

ለአርአያነት፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለሙ ሁሉ ሊያበራ፣ ብርሀን የሆነውን ሕገ ወንጌልን ሊሠራልን ወረደ፡፡ የሰውንም ልቡና በወንጌል ሊያበራ ወረደ፡፡ ሕግን የሰራ እርሱ የሰራውን ሕግ እየተገበረ አርአያ ሆኖ ሊያስተምረን ወረደ፡፡ ነገር ግን “ክፉ የሚያደርግ ብርሃንን ይጠላል፤ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሀን አይመጣም፡፡” እንደተባለ ክፉ የሚያደርጉ በብርሃን ክርስቶስ አያምኑም፣ አርዓያ ሆኖ የፈጸመውን ሕግም አይፈጽሙም፤ ብርሀንን ለማጥፋት ይጥራሉ እንጂ፡፡ ክፉ የሚያደርጉ (የጨለማ ሥራ የሚሠሩ) ወደ ጨለማ ይሄዳሉ፡፡ በአንፃሩ እውነትን የሚያደርግ ወደ ብርሃን ይመጣል፡፡ ሥራውም በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደሆነ እንዲገለጥ ወደ ብርሃን ይመጣል፡፡ እንደተባለ መልካም የሚያደርጉ በእርሱ ያምናሉ፡፡ መልካም የሚያደርጉ የብርሃን ልጆች ወደ ብርሃን ክርስቶስ ይመጣሉ፤ በቅዱስ ስሙ ያምናሉ፣ አርዓያነቱንም ይከተላሉ፡፡

ክፉዎች አይሁድ ጌታን የሰቀሉት የጨለማ ሥራቸው እንዳየይገለጥ ነበር፡፡ ዛሬም አንዲሁ ነው፡፡ የጨለማ ስራቸው እንዳይገለጥ የሚፈልጉ ነውረኞች እውነተኞችን ሲያሳድዱ ይኖራሉ፡፡ የህይወት ባለቤት፣ የብርሃን አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአርአያነትና ለቤዛነት ከመጣ ከእኛ የሚጠበቀው በፍፁም ፍቅር በተሞላ የአባትና የልጅ ፍርሀት ሆነን ለእርሱ መገዛት ነው፡፡ በዚሁ በመጀሪያው የዐቢይ ጾም ሰንበት በሚሰበከው በቅድስት ቤተክርስቲያናችን ምስባክ ልበ አምላክ ዳዊት ‹‹ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሀት፣ ወተሐሰዩ ሎቱ በረዓድ/በፍርሀት ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ተገዙ፣ በረዓድም ደስ ይበላችሁ (መዝ 2፡11)›› እንዳለ በፍቅር በተሞላ ፍርሀት ሆነን ጌታችንን ልንገዛለት፣ ልናመልከው ይገባል፡፡ ቤዛ አርአያ ለሆነን ጌታ እንጂ ለሰይጣንና ለስጋችን ፈቃድ እንዲሁም በሥጋ ፈቃድ ለሰለጠኑ ምድራውያን ኃይለኞች ልንገዛ አይገባም፡፡ እኛ ክርስቲያኖች መልካምን የምናደርገውም ቅጣትን (ሞትን) ፈርተን ሳይሆን እኛን ለማዳን ከዙፋኑ የወረደውንና የእኛን ሥጋ ለብሶ በመልዕልተ መስቀል ላይ ቤዛ የሆነልንን ወልደ እግዚአብሔር ወልደ ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስን ፈርተን (አፍቅረን) ሊሆን ይገባል፡፡ ‹‹ልጅ አባቱን ያከብራል፤ ባሪያም ጌታውን ይፈራል፤ እኔስ አባት ከሆንኩ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንኩ መፈራቴ ወዴት አለ? (ሚክ 1፡6-7›› እንዳንባል ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት ‹‹በፍርሀት ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ተገዙ›› እንዳለው በፍርሀት ሆነን ለእርሱ ልንገዛ ይገባል፡፡ ፍርሀትም ሲባል ሥጋዊና መንፈሳዊ ፍርሀት አለ፡፡

ሥጋዊ ፍርሀት፡- ሰው ኃጢአትን ሠርቶ ከገነት ከወጣ በኋላ የመጣበትና ከመጨነቅ የሚመነጭ ፍርሀት ነው፡፡ ረሀብን፣ በሽታን፣ ጦርነትን፣ አደጋን ጉዳት ያደርስብኛል ብሎ መፍራት ሥጋዊ ፍርሀት ነው፡፡ ምድራዊ ሕግን ስንተላለፍ ፖሊስን የምንፈራው ፍርሀት የሥጋ ፍርሀት ነው፡፡ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ በሥጋ በነበረበት ዘመን ሕዝቡ የአይሁድ ካህናትን ይፈሩ ነበር፡፡ ይህ ፍርሀት ግን ሥጋዊ ፍርሀት ነበር፡፡ የሙሴን ህግ ያለአግባብ በመጠቀም ሕዝቡን ያሰቃዩት ስለነበር ነው የአይሁድ ካህናት ይፈሩ የነበረው፡፡   እንዲህ አይነቱ ፍርሀት በጤና ጉዳትን በማድረስ ለአእምሮ መታወክ ከመዳረግ ውጭ ምንም አይጠቅምም፡፡ ይህ አይነት ፍርሀት ከክርስቲያኖች ላይ መወገድ እንዳለበት ጌታችን ለሐዋርያቱ ‹‹ ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ።›› በማለት እንዲሁም ለምኩራቡ አለቃ ‹‹እመን እንጂ አትፍራ›› በማለት አስተምሯል፡፡ ማቴ 10፡28 ማር 5፡36

መንፈሳዊ ፍርሀት፡- ይህ ፍርሀት ከፍቅር ከማክበር የሚመነጭ ፍርሀት ነው፡፡ እግዚአብሔር አንዲህ እየወደደኝ እንዴት እበድላለሁ የሚል ፍርሀት መንፈሳዊ ነው፡፡ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ያህል ውለታ ውሎልኝ እንዴት እተወዋለሁ የሚል ፍርሀት ከዚህ ይመደባል፡፡ ይህ አይነት ፈሪሀ እግዚአብሔር የጥበብ መጀመሪያና ሰውንም ከኃጢአት የሚጠብቅ ነው፡፡ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት ‹‹ቅዱሳኑ ሁሉ እግዚአብሔርን ፍሩ(መዝ 33፡14)›› እንዳለ እንዲህ አይነቱ ፍርሀት የሕይወት ምግብ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘድን እግዚአብሔርን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው (ምሳ 14፡27)።›› እንዳለው መንፈሳዊ ፍርሀት የሕይወት መገኛ ነው፡፡ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በሌላም ሥፍራ ‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩት ሁሉ፥ በመንገዶቹም የሚሄዱ ምስጉኖች ናቸው (መዝ 128፡1)›› እንዳለው መንፈሳዊ ፍርሀት የቅድስና ሥራ ነው።

ለአርዓያ ዓለም ከሰማየ ሰማያት የወረደው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ አይሁድ ሊቃናት በማስጨነቅ ሳይሆን በፍቅር እንደሚመራ፣ እንደሚያስተዳድር በመዋዕለ ሥጋዌው አሳይቶናል፡፡ ከተናቁት ጋር በመቆም፣ መምህርና ጌታ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ፣ ንጹሐ ባሕርይ ሲሆን በበደልና በኃጢአት የተዳደፉትን ሰዎች በፍቅር ቀርቦ ወደ ጽድቅ በመመለስ አርዓያነቱን አስመስክሯል፡፡ ይህ እርሱ ፍጹም ፍቅርና ትህትና መንፈሳዊና ሥጋዊ ስልጣናቸውን ለትምክህትና ለከንቱ ውዳሴ ሲሉ ያለ አግባብ ይጠቀሙ ለነበሩ የአይሁድ ሊቃናት ተግባራዊ ተግሳጽ ነበር፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፍቅሩና በትህትናው በጎቹን በመልካም መንገድ የሚመራ እረኛ መሆኑ እረኝነታቸውን ረስተው በበጎቻቸው የሚነግዱ ሊቃናተ አይሁድን ስላወካቸው በቅናት ተነሳስተው ያለ ኃጢአቱ ለመከራ መስቀል አደረሱት፡፡ እርሱ ግን ለመከራ መስቀል በመታዘዝ ሰውን የማዳን ቃልኪዳኑን፣ ፈቃዱን፣ የአባቱን  ፈቃድ፣ የመንፈስ ቅዱስን ፈቃድ ፈጸመ፡፡ በመውረዱ በመወለዱ ቤዛነትን አገኘን፤ ከድቅድቅ ጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን ተሻገርን፡፡

ዛሬም በቤዛነቱ ያገኘነውን የመዳን ጸጋ በእምነትና በመታዘዝ እየፈጸምን አርዓያነቱን ተከትለን እስከ ዕለተ ምጽዓት እንድንጠብቅ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ በተለይም በጾማችን ወራት የሰው ፍቅር አገብሮት ከሰማየ ሰማያት ለወረደው፣ በሥጋ ማርያም ለተገለጠው፣ ለሥጋችንና ለነፍሳችን ቤዛ፣ ለህይወታችን መርህ (አርዓያ) ለሆነን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ እንድንገዛ ፈቃዱንም አብዝተን እንድንፈጽም ታዘናል፡፡ የወንጌሉም የምስባኩም (መዝሙረ ዳዊት) ዓላማ ይህንን ማስገንዘብ ነው፡፡ በቤተክርስቲያን የተሾሙ፣ የክርስቶስ እንደራሴዎች የሆኑ ካህናትም ልዩ ሊቀ ካህናት የሆነውን የምስጢራት ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አርዓያ በማድረግ እንደ አይሁድ ሊቃናት መንፈሳዊ ስልጣንን ለትምክህትና ለከንቱ ውዳሴ ከመጠቀም ርቀው በጎች የተባሉ ምዕመናንን በፍቅርና በትህትና፣ እግዚአብሔርንም በመፍራት ሊመሩ ያስፈልጋል፡፡ በጎች የተባልን ምዕመናንም የክርስቶስ እንደራሴ የሆኑ ካህናት አባቶቻችንን እየታዘዝን በፍቅርና በፍርሃት የእግዚአብሔርን ቃል መሰረት አድርገን ልንኖር ይገባል፡፡ ይህን ስናደርግ ለእኛ ብሎ የወረደ የተወለደ ቤዛም የሆነልንን የክርስቶስን ፈቃድ ፈጽመን በሰማይ ባለች ነፃ በምታወጣ በኢየሩሳሌም በቀኙ ከሚቆሙ ንጹሐን ቅዱሳን ኅብረት እንደመራለን፡፡  በጾማችን ወራት ፈቃዱን ፈጽመን በመንፈሳዊ ፍርሀት ለእርሱ ተገዝተን መንግስቱን ለመውረስ ያብቃን፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s