መጻጉዕ (የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት): ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ!

ከቅዱስ ያሬድ በተገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የበዓላት ቀኖና መሰረት የዐቢይ ጾም አራተኛው ሰንበት “መጻጉዕ” ይባላል፡፡ መጻጉዕ ማለት “በሽተኛ” ማለት ነው፡ በዚህ ዕለት ጌታችን በቤተ ስዳ መጻጉዕን ማዳኑን ቤተክርስቲያን ትሰብካለች፡፡ ለ 38 ዓመታት ያህል በጽናት፣ በትዕግስት፣ በተስፋ ፈውስን እየተጠባበቀ በመጠመቂያው አጠገብ የኖረ መጻጉዕን በአልጋው ተኝቶ ሳለ ደዌው እንደጠናበት ፈውስ እንደዘገየበት አይቶ “አዎን” እንደሚለው እያወቀ መጻጉዕን ‹‹ልትድን ትወዳለህን?” አለው። ይህን ማለቱ የሰውየውን የመዳን ፍላጎት ለማንቃት፣ ለሰው ያለውን ክብር ለመግለጽ፣ የመዳን ተስፋን ለመስጠት፣ መዳንም በውኃው ብቻ ሳይሆን በቃሉም መሆኑን ለማመልከት፣ ለድኅነተ ነፍስም ለማዘጋጀት ነው። መጻጉዕም በትህንትና (መዳን ብፈልግም አይደል እዚህ ይህን ሁሉ ዘመን የምጠባበቀው ሳይል) “ሰው የለኝም” በማለት የመዳን ጉጉቱን ከወዳጅ አልባነቱ ጋር ገለጠ። ጌታም “ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው፡፡ ወዲያው አፈፍ ብሎ በፍጥነት ያን ሁሉ ዘመን የተሸከመችውን ጠንካራ አልጋ ተሸክሟት ሄደ (ዮሐ 5፡1-9)።

ጌታችን መጻጉዕን “ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” ያለው ስለ ሦስት ነገር ነው፡፡ አንደኛው ቅዱስ ኤስድሮስ እንዳለው አልጋው ጠንካራ የብረት አልጋ ነበረና ጽንዓ ተአምራቱን ለማሳየት ነው፡፡ በዚህም እንደ ሕመምተኛ ሳይሆን እንደ ሙሉ ጤነኛ ሆኖ መሄዱን የሚያመለክት ነው። ሁለተኛው ምህረትን ማድረግ ከወግ አጥባቂዎች የተሳሳተ የሕግ አከባበር እንደምትበልጥ ለማሳየት ነው። አልጋውን ተሸክሞ በመሄዱ አይሁድ አይተው ጠይቀውታልና። ሦስተኛው አልጋውን ተሸክሞ መሄዱ ወደዚያ እንዲመለስ የሚያደርገው ነገር ምንም እንደሌለና መዳኑንም እየመሰከረ እንዲሄድ ነው።

ይህ ሰንበት የሕሙማን ፈውስ መታሰቢያ ዕለት ነው። የሰንበቱም ስያሜ በዕለቱ የሚነበቡትን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢርና የጾመ ድጓውን ይትበሀል ተከትሎ የተሰየመ ነው፡፡ በመልእክታቱ የሚነበቡት (ገላ 5፡1 እና ያዕ 5፡14) ስለ ድውያን መፈወስ የሚያወሱ ናቸው፡፡ ከሐዋርያት ሥራ የሚነበውም እንዲሁ (ሐዋ 3፡1)፡፡ የዕለቱ ምስባክ እንዲሁ የድውያንን መፈወስ የሚሰብክ ሲሆን “እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ላይ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ ከበሽታው የተነሳ ይለውጥለታል፡፡ እኔስ  “አቤቱ ይቅር በለኝ፤ አንተን በድያለሁና ለነፍሴ አስተስርይላት” አልሁ፡፡” ይላል (መዝ 40:3)

ጌታችን መጻጉዕን የፈወሰባት ቦታ ቤተ ሳይዳ ሳትሆን ቤተ ስዳ ናት፡፡

ቤተ ስዳ (Bethesda)  በይሁዳ ግዛት ከሚገኙና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራቱን ከፈጸመባቸው ሥፍራዎች አንዷ ናት፡፡ ቤተ ሳይዳ (Bethesaida) ደግሞ በገሊላ አውራጃ የምትገኝ ከተማ ነበረች፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በይሁዳ ኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ ያለችዋን ቤተ ስዳን ‹‹በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ስዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። (ዮሐ 5፥2)›› ብሎ ሲገልጻት በገሊላ የምትገኘዋን ቤተ ሳይዳን ደግሞ ‹‹እነርሱም ከገሊላ ቤተ ሳይዳ ወደሚሆን ወደ ፊልጶስ መጥተው ጌታ ሆይ፥ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን ብለው ለመኑት(ዮሐ 12፥21)›› ብሎ ገልጿታል፡፡

ቤተ ስዳና ቤተ ሳይዳ የተለያዩ ቦታዎች ከመሆናቸው በተጨማሪ የስማቸውም ትርጉምም እንዲሁ የተለያየ ነው፡፡ ቤተ ስዳ ማለት ‹‹ቤተ ሣህል (የጸጋ/የምህረት ቤት)›› ማለት ሲሆን፣ በግሪኩ ቤተ ዛታ ወይም ቅልንብትራ ትባላለች፡፡ ቤተ ስዳ ባለ አምስት በር መመላለሻ አምስት ዓይነት ድውያን ፈውስን ከመጠመቂያው ውኃ ሲጠባበቁ የሚኖሩባት የጌታችን ማዳን የተገለጠባት ሥፍራ ናት።  የእግዚአብሔር መልአክ ውኃውን ሲባርክ/ሲያናውጥ ቀድሞ የገባ የሚነጻባት በዕለቱ ከአንድ በቀር ለሌላው ፈውስ የማይደገምባት ቦታ ነበረች። ለዚህም ነው ይህች ስፍራ መጠመቂያና መመላለሻ ያላት በመሆኗ የምህረት ቤት የተባለቸው፡፡ እንደስሟ ትርጓሜ ‹‹ቤተ ስዳ›› የተባለችበትም ምክንያት የሰሎሞን ቤተ መቅደስ አጠገቧ የሚገኝ ሲሆን ለቤተመቅደሱ መስዋእት የሚሆኑ በጎች ሁሉ በዚህ መጠመቂያ ሳይጠመቁ ወደ መስዋእቱ መሰዊያ ቦታ አይቀርቡ ስለነበረ ነው (ዘሌ 9፡2)። ጌታችን በቤተ ስዳ መዳንን ይጠባበቅ የነበረውን መጻጉዕን ፈውሷል፡፡

በቤተ ስዳ መጠመቂያ ይፈጸም የነበረው ድኅነት ምሳሌው እንዲህ ነው፡፡ ውኃውን ያናውጥ (ይባርክ) የነበረው መልአክ የቀሳውስት ምሳሌ፣ ውኃው የጥምቀት ምሳሌ፣ አምስቱ መመላለሻ (እርከን) የአምስቱ አዕማደ ምስጢር፣ የአምስቱ ድውያንና የአምስቱ ፆታ ምዕመናን ምሳሌ ናቸው፡፡ ቤተ ስዳ በዕለተ ቀዳሚት የሚፈወሰው አንድ ሰው ብቻ ነበር፡፡ አንድ ብቻ መሆኑ አለመቅረቱን ሲያሳይ አለመደገሙ ደግሞ ፍጹም እንዳልነበረ ያሳያል፡፡

በአንጻሩ ቤተ ሳይዳ ማለት ደግሞ “የማጥመጃ ቤት” ወይም ‹‹የዓሳ ቤት›› የሚል ትርጉም ያላትና በተለይ ከሐዋርያቱ አሳ አጥማጆቹ ወንድማማቾች እና ቅዱስ ፊልጶስ የነበሩባት መንደር ነበረች (ዮሐ·1፡45)። ይህች ከተማ ‹‹የዓሳ ቤት›› የተባለችውም ከገሊላ ባህር ዳር የምትገኝ ስለሆነችና ዓሳ የሚያሰግሩ ሰዎች የሚነግዱባት ስለነበረች ነው። በዚህ በሞቀ ንግዷ የተነሳ ከተማዋ የተሰበከላትን ወንጌል ለመስማት ባለመቻሏ ጌታችን በተናገረው ትንቢት መሰረት ከሌላዋ ከተማ ከኮራዚን ጋር አብረው ጠፍተዋል (ማቴ 11፣21)፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ሳይዳም ድውያንን ፈውሷል (ማር 8፡22-25)፡፡

መጻጉዕ ያዳነውን አላወቀውም ነበር፡፡

ጌታችን መጻጉን ያዳነበት ዕለት ሰንበት ነበረ። ስለዚህ አይሁድ የተፈወሰውን ሰው “ሰንበት ነው አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም” አሉት።  እርሱ ግን “ያዳነኝ ያ ሰው። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ” ብሎ መለሰላቸው። እነርሱም፥ “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰው ማን ነው?” ብለው ጠየቁት። ዳሩ ግን በዚያ ስፍራ ሕዝብ ሰለ ነበሩ ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ነበርና የተፈወሰው ሰው ማን እንደ ሆነ አላወቀም። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና፥ “እነሆ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ” አለው። ሰውዬው ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገረ። ስለዚህም በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር (ዮሐ.5፥10-16)።

አይሁድ ይህ ሰው በዚያ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ታሞ ድኅነትን እየተጠባበቀ እንደነበር አሳምረው ያውቁ ነበር። ነገር ግን ከዳነ በኋላ አልጋውን ተሸክሞ ሲሄድ ሲያገኙት የጠየቁት ስለመዳኑ (እንዴት እንደዳነ) አልነበረም። ‘እንኳን ለመዳን አበቃህም’ አላሉትም። በቀጥታ የጠየቁት ጥያቄ ‘በሰንበት አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ማነው?’ ነበር ያሉት። ይህም የሚያመለክተው አይሁድ ከሰው ልጅ ድኅነት ይልቅ ያሳስባቸው የነበረው የሕጋቸው መከበር አለመከበር እንደነበር ነው። ስለዚህም ነው ጌታችን ሰንበት ስለሰው ልጅ ተፈጠረች እንጂ የሰው ልጅ ስለ ሰንበት አልተፈጠረም (ማር 2:27)፤ በሰንበትም መልካምን ማድረግ ተፈቅዷል (ማቴ 12:12) በማለት ያስተማረው።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅና ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ በትርጓሜያቸው እንዳስተማሩት ይህ የዳነው ሰው ያዳነውን ያላወቀው ብዙ ሰው ስለነበረ ኢየሱስም ካዳነው በኋላ ፈቀቅ ብሎ ስለነበር ነው እንጂ “ታሞ የተነሳ ያዳነውን ረሳ” እንደሚባለው አልነበረም። ጌታችን ብዙ ሰው በነበረበት በጸጥታ አድኖት ፈቀቅ ያለው የትህትናው ነገር (አድናቆትንና ጭብጨባን ስላልፈለገ) ነው። መጀመሪያ መታዘዙን እንዲያሳይም ነው። አንድም መጀመሪያ የአካል ሕመሙን አድኖት ኋላ ደግሞ ከነፍስ ሕመም ሊያድነው ነው። አንድም የዚህ ሰው ትኩረት (ሠላሳ ስምንት ዓመት ታሟልና) መዳኑ ላይና አልጋውን ተሸከም እንደተባለው መሸከም ላይ ስለነበር ነው። “ያዳነኝ ያ ሰው አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ” ማለቱ ግን መዳኑን የመሰከረበት ነው። ይህንን ማለቱ እውነት ነውና። ያዳነው (ጌታችን) ያዘዘውንም (አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለውን) ፈፅሟል። ኋላም ጌታችን ሲያገኘው “እነሆ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ” ማለቱ የነበረበት በሽታ በኃጢአት ምክንያት የመጣ እንደነበር ይጠቁማል የሚሉ ሊቃውንት አሉ። “ሠላሳ ስምንት ዓመት ከመታመም በላይ የባሰ ምን አለ?” ቢሉ ሲኦል አለና በነፍስ ከሚመጣ ቅጣት ይጠበቅ ዘንድ ሲያስጠነቅቀው ነው።

ሊቃውንት የዳነው ሰው ወደ ቤተ መቅደስ መሄዱም ስለመዳኑ ምስጋናን ሊያቀርብ ነው ብለው ያስተምራሉ። የዳነው ልክ ያዳነውን እንዳወቀ ሄዶ ለአይሁድ ያዳነው ኢየሱስ መሆኑን መናገሩ አንድም (አይሁድ ይፈሩ ነበርና) ጠይቀውት ስለነበር በጠየቁት መሠረት መመለሱ ነው። መዳኑ የሚያስደስታቸው መስሎት እንጂ በጌታችን ላይ እያሴሩበት እንደሆነ አልተረዳም። መጽሐፍም ‘ያዳነው ኢየሱስ እንደሆነ ለአይሁድ ተናገረ’ ይላል እንጂ “ሰንበትን እንድሽር ያደረገኝ እርሱ ነው” ብሎ ተናገረ አይለንም። ይህንን አይሁድ ጌታን ለመክሰስ ቢጠቀሙበትም ይህ ሰው አንዳንድ መተርጉማን እንደሚሉት ጌታችንን እንዲከሱት መረጃ ይሁናችሁ ብሎ ለክፋት በመተባበር የተናገረው አይደለም። አንዳንድ መተርጉማንም “ወርቅ ላበደረ ጠጠር” የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር በመጥቀስ ይህ ሰው በሊቶስጥራ አደባባይ “በሰንበት አድኖኛል ብሎ በጌታችን ላይ በሐሰት መስክሮበታል፤ በጥፊም መትቶታል” ብለው እንደሚያስተምሩ ብናውቅም ወንጌላውያን ግን እርሱ መሆኑን አይነግሩንም። እንደነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ያሉ ሊቃውንትም እንዲህ አይነት ትርጓሜ አላስተማሩም።

የዐቢይ ጾም አራተኛው ሰንበት እኛም የታመሙትን መጎብኘት እንዳለብን የምንማርበት ነው፡፡

ይህ ሳምንት “መጻጉዕ” ጌታችን ድውያንን ስለመፈወሱ የሚነገርበትና እኛም ባለን አቅም በነፍስ በሥጋ የተቸገሩትን ሁሉ መርዳትና ማገዝ እንዳለብን የምንማርበት ሳምንት ነው፡፡ ሕሙማንን መጠየቅ፣ የታሰሩትን መጎብኘትና ማስፈታት፣ የተራቡትን ማብላት፣ የተጠሙትን ማጠጣት፣ የታረዙትን ማልበስ ያዘኑትን ማረጋጋት ከጌታችን የተማርናቸው ክርስቲያናዊ ምግባራት ናቸው፡፡ ይህንን በማስተዋል የሚያስፈልገንን ሁሉ የሰጠንንና ከክፉ ነገር የጠበቀንን አምላክ ውለታውን እያሰብን ልናመሰግነው ይገባል፡፡ መጻጒዕ የነበረበትን ደዌ ሥጋ ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አራቀለት/አዳነው፡፡ ያንን ተስፋ ያልነበረውን በሽተኛ ከደዌ ሥጋው ፈውሶ ሕይወትን የሰጠው አምላክ፣ እኛንም በውስጥ በአፍአ ካለብን ደዌ ሥጋና ደዌ ነፍስ እንዲፈውሰን፤ ቁስለ ኃጢአታችንን እንዲያደርቅልን፣ በሕይወትና በጤና እንዲጠብቀን የእርሱ የጌታችን ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡

Leave a comment