አምስቱ አዕማደ ምስጢራት፡ መግቢያ

ትምህርተ ሃይማኖት ወደ እግዚአብሔር የምታደርሰውን ፍኖተ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር መንገድ) የምናውቅበትና ዘላለማዊ ሕይወትን የምንጎናጸፍበትን “ርትዕት ሃይማኖት” የምንገነዘብበት ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖትን ዶግማ (መሠረተ እምነት) እና ቀኖና (ሥርዓተ ቤተክርስቲያን) ብለው በሁለት ይከፍሉታል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት መሠረት እንደሆኑ የምታምነውና የምታስተምረው አምስቱ አዕማደ ምስጢራትን ነው፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጦማር የአምስቱ አዕማደ ምስጢራት- መግቢያ የመግቢያ ክፍል የሚቀርብ ሲሆን የአንዳንድ ቃላትን ትርጉም በመግለጽ እንጀምራለን፡፡

እግዚአብሔር: እግዚአብሔር የሚለው ቃል ከግዕዝ የተገኘ ሲሆን “እግዚእ” ማለት ጌታ ማለት ነው፡፡ “ብሔር” ማለት ደግሞ ዓለም ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ማለት የዓለም ጌታ (ፈጣሪ፣ ገዥ) ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ እግዚአብሔር እንዳለ ለማረጋገጥ አይሞክርም፡፡ የእግዚአብሔርን ህልውና መሠረት አድርጎ ይጀምራል እንጂ፡፡ ዘፍ 1፡1 እግዚአብሔር በዕብራይስጥ የሚጠራባቸው ሦስት ስሞች አሉ፡፡ እነዚህም ኤል (ኃያል አምላክ)፣ ያህዌ (ያለና የሚኖር፣ እንደ ፈቃዱ የሚሠራ) እና አዶን (ጌታ) የሚሉት ናቸው፡፡ በጽርዕ አልፋና ኦሜጋ (መጀመሪያውና መጨረሻው) ይባላል፡፡ መለኮት ማለት መላኪ(ገዥ) ማለት ነው፡፡ አምላክ ማለትም ፈጥሮ የሚገዛ ማለት ነው፡፡

እምነትና ሃይማኖት: እምነት የሚለው ቃል መሠረታዊ ቃሉ ግዕዝ ሲሆን ትርጓሜውም ማመን ወይም መታመን ማለት ነው፡፡ ማመን ማለት ስለእግዚአብሔር የሰሙትንና የተረዱትን እንዲሁም የተቀበሉትን ትምህርት እውነት ነው ብሎ በልብ መቀበል ነው (ሮሜ 10፡17)፡፡ መታመን ደግሞ ያመኑትንና የተቀበሉትን እምነት በሰው ፊት ሳይፈሩና ሳያፍሩ መመስከር ነው፡፡ ማቴ 10፡32 ሮሜ 10፡9 ሐዋርያው ቅዱሰ ጳውሎስ ስለ እምነት ሲናገር “እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው።” ብሏል፡፡ ዕብ 11፡1 ያለ እምነትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡   ሃይማኖት ማለት ለዓለም ፈጣሪ አለው ብለው የሚያምኑት እምነት ነው፡፡ ለዓለም ፈጣሪ አለው ብለው የሚመሰክሩት ቃል ነው፡፡ ሃይማኖት ሰው ፈጣሪውን የሚያመልክበት፣ የእግዚአብሔር ልጅ የሚሆንበት፣ ጽድቅንም የሚሠራበት፣ የዘላለም ሕይወትን የሚያገኝበት መንገድ ነው፡፡ ሃይማኖትም አንዲት ናት፡፡ ኤፌ 4፡5

ዶግማና ቀኖና: ትምህርት ሃይማኖት (የሃይማኖት ትምህርት) በሁለት ይከፈላል፡፡ ይኸውም ዶግማና ቀኖና በሚል ነው፡፡ ዶግማ ቃሉ የግሪክ ሲሆን ፍችውም የእምነት መሠረት ማለት ነው፡፡ ዶግማ ወይም እምነት አይጨመርበትም፤ አይቀነስበትም፤ አይሻሻልም፤ ችግርና ፈተናም ቢመጣ እስከ ሞት ድረስ አጥብቀን የምንይዘው ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ የፈጠረ፤ ቢመረምር እንጂ የማይመረመር ሁሉን ቻይ አምላክ፤ የሚሳነው ነገር የሌለ ፈጣሪ፤ የሰማይና የምድር ባለቤት የሠራዊት ጌታ ሕያው እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር (ፈጣሪ) የአካል ሦስትነት አለው፡፡ በመለኮት፣ በመፍጠር፣ በሥልጣን፣ በአገዛዝ፣ በፈቃድ ግን አንድ ነው፡፡ በሦስትነቱ አብ፤ ወልድ፤ መንፈስ ቅዱስ ሲባል በአንድነቱ አንድ መለኮት አንድ እግዚአብሔር ይባላል፡፡ በአዳም ምክንያት ከመጣው የዘለዓለም ሞትና ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ የወጣነው ከሦስቱ አካላት በአንደኛው አካል ማለትም በወልድ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህን የመሰለው መሰረታዊ ትምህርት ዶግማ ወይም መሰረተ እምነት ይባላል፡፡

ቀኖና የሚለው ቃልም የግሪክ ሲሆን ሥርዓት ማለት ነው፡፡ ቀኖና በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ያደጉ ክርስቲያኖች የሚመሩበት ሥርዓት ስለሆነ፤ በሃይማኖት አባቶች ወይም በቅዱስ ሲኖዶስ አማካኝነት እንደጊዜው ሁኔታ የሚሻሻል በመሆኑ የሚጨመርበት፤ የሚቀነስለት ነው፡፡ ለምሳሌ በቤተ ክርስቲያናችን የቀዳስያን ብዛት መነሻው አምስት ነው፡፡ ምናልባት ከአምስቱ አንዱ፤ ሁለቱ፤ ሦስቱ ቢታጡና ሌላም ተፈልጎ እስከ መጨረሻ የማይገኝ ከሆነ ከአቅም በላይም የሆነ ችግር ከገጠመ ሁለቱ ወይም አንዱ ብቻ ቀድሰው ማቁረብ ይችላሉ፡፡ 1ኛ ቆሮ. 14፥40፡፡ 2ኛተሰ. 3፥6-7 ቀኖና (ሥርዐት) የሚወሰነው በሃይማኖት አባቶች እንደሆነና ወንጌልን የሚያስተምር ሰው ለሚያስተምራቸው ክርስቲያኖች በሃይማኖት አባቶች የተወሰነ ቀኖና ማስተማርና መሰጠት እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ያስረዳል፡፡ “በየከተማውም ሲሄዱ፥ ሐዋርያትና ቀሳውስት በኢየሩሳሌም ያዘዙትን /የወሰኑትን/ ሥርዐት አስተማሯቸው፡፡ አብያተ ክርስቲያናትም በሃይማኖት ጸኑ ዕለት ዕለትም ቁጥራቸው ይበዛ ነበር፡፡” ሐዋ. 16፥4-5፡፡

ቤተክርስቲያን፡ እንደ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አመሥጥሮ ቤተ ክርስቲያን ማለት እግዚአብሔር ግዕዛን ካላቸው ፍጥረታት ጋር ያለው ግንኙነት ነው፡፡ ይህም ሦስት አይነት ትርጉም አለው፡፡ ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች ኅብረት፡ የክርስቲያኖች አንድነት ነው (1ኛ ቆሮ 11፡28)፡፡ ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች መኖሪያ፡ የእግዚአብሔር ቤት ነው፡፡ “ቤት” ማለት መኖሪያ ማለት እንደሆነ ሁሉ “ቤተክርስቲያን” ማለት የክርስቲያኖች ቤት/መኖሪያ የእግዚአብሔር ቤት ማለት ነው (ዮሐ 2፡ 16)፡፡  እዚህ ላይ ህንፃ ቤተክርስቲያን ስንል አገልግሎቱንም ጭምር የሚያመለክት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በተጨማሪም ቤተክርስቲያን ሲል ምዕመናንን ነው፡፡ የእያንዳንዱን ክርስቲያን ሰውነት የሚያመላክት ነው (1ኛ ቆሮ 3፡16)፡፡ ይህም ማለት ቤተክርስቲያን ከክርስቶስ የተገኘ እንደሆነ ነው፡፡

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእምነትና የሃይማኖት መሠረት የሆኑት አምስቱ አዕማደ ምስጢራት ናቸው፡፡ ሃይማኖት የሚባለውም እነዚህን ምስጢራት ተቀብሎ ሁሉን ማድረግ ከሚችል ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ነው፡፡ አምስት መሆናቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን ሌሎችን ደግሞ አስተምር ዘንድ በማኅበር እልፍ ቃላት በልሳን ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ልናገር እወዳለሁ።” (1ኛቆሮ 14፡19) ያለውን መነሻ ያደረገ ሲሆን የስያሜያቸው ትንታኔ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

አዕማድ ማለት ምን ማለት ነው?

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት መፍቻ ቁልፍ የግእዝ ቋንቋ እንደ መሆኑ መጠን በተለይም በቤተክርስቲያን ጥቅም ላይ የሚውሉ ቃላት ምንጫቸው ግእዝ ነው፡፡ “አዕማድ” የሚለውም ቃል መገኛው “አምድ” የሚለው የግዕዝ ቃል ነው፡፡ “አምድ” የሚለው ቃል የነጠላ ቁጥርን የሚገልፅ ሲሆን “አዕማድ” ሲሆን ደግሞ ብዙ ቁጥርን ይገልፃል፡፡ ትርጉሙም በቃላዊ ፍቺው ለቤት ሲሆን ምሰሶ ማለት ነው፡፡ ምሰሶ ቤትን ደግፎ እና አቅንቶ እንደሚይዝ ሁሉ አምስቱ አዕማደ ሚስጥራትም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን አቅንተውና ደግፈው ስለሚይዙ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ ዐምድ ለጽሕፈትም ይውላል፡፡ የገጽ ስፋትንም በመክፈል ለንባብ መመጠኛነት ያገለግላል፡፡ በዚህ ፍቺም ባህርየ ሥላሴን ከልክ አልፈን እንዳንመረምር የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡

አምድ በቁሙ ምሰሶ ብለን የምንጠራው እና ቤቱ እንዳይዘም ወይም ወደ አንድ ጎን እንዳያዘነብል፤ ሚዛኑን እና ልኩን ጠብቆ እንዲቆም የሚያደርግ ነው። በአምድ የተሠራ ቤት አይዛባም ያለዓምድ የተሠራ ቤት ግን ይፈርሳል አይጸናም፡፡ ቤት በአምድ (በኮለም) እንደሚጸና ሃይማኖትም በእነዚህ አዕማደ ምሥጢራት ተጠቃሎ ይገለጻል፤ ምዕመናንም እነዚህን ምሥጢራት በመማር ጸንተው ይኖራሉ። እንደዚህም ሁሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አዕማድ የተባሉ ምሥጢራት ይዞ የተገኘ ሰው ልቡናው በፍቅረ እግዚአብሔር በተስፋ መንግስተ ሰማያት ይጸናል፡፡ እነዚህን አምስቱን እምነታት ሳይዝ የተገኘ ልቡናው በፍቅረ እግዚአብሔር በተስፋ መንግስተ ሰማያት አይጸናም፡፡

“ሁሉም ነገር ድጋፍ ያስፈልገዋል” የሚለው ሃሳብ ለቤቶች ብቻ ሳይሆን ከዚያም ባለፈ ለብዙ ነገሮች ያገለግላል፡፡ ብዙ የፍልስፍና ሊቃውንት ሰዎች ሁሉ ህይወታቸው በተገቢው መንገድ ለመምራት ሲሉ የሚቀበሏቸው መሰረታዊ እምነቶች (fundamental beliefs) እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ በዓለም ላይ ከፍተኛ ህዝብ ይከተላቸዋል የሚባሉት ሃይማኖቶችም ሳይቀሩ መሰረታዊ እምነት የሚሏቸው አሏቸው፡፡ ለአብነትያህል፡- በእስልምናው ሃይማኖት አምስቱ የእስልምና መሰረቶች (The Five Pillars of Islam) ሲኖሩ በቡድሂዝም እምነት ደግሞ አራቱ እውነታዎች (The Four Noble Truths) ይገኛሉ፡፡

በቅድስት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ምሰሶዎች አንድን ቤት ደግፈው እንደሚይዙት ሁሉ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትንም ቀጥ አድርገው የሚይዙ ምሰሶዎች አምስቱ አዕማደ ምስጢራት ናቸው፡፡ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት እንደሚያስተምሩት ከሆነ አንድ ሰው አምስቱን አዕማደ ምስጢራት በጥንቃቄ ካወቀ የኑፋቄ ማዕበል አይጥለውም፡፡ ከእምነቱም አይናወጽም፡፡ በህይወቱ የተለያዩ መከራዎች ቢመጡበትም በእነዚህ ትምህርቶች በኩል ራሱን ያፀናል፡፡ እነዚህን አዕማድ ያላወቅ በሙሉ ልቡ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኝ ነኝ ማለት አይችልም፡፡ በዚህም ምክንያት እነዚህን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

ለምን ምስጢራት ተባሉ?

ቅድስት ቤተክርስቲያን አምስቱን አዕማድ “የምስጢር ትምህርቶች” ትላቸዋለች፡፡ “ምሥጢር” የሚለው ቃል “አመሠጠረ” ከሚለው ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን ስውር ፣ ድብቅ ፣ ሽሽግ ማለት ነው፡፡ ምሥጢር በሁለት ይከፈላል፡፡ እነርሱም የፈጣሪ ምሥጢር (ሊገለጥ የማይችል፤ ከ እስከ የሌለው ምሥጢር) እና የፍጡራን ምሥጢር (በጊዜ የሚገለጥ /የሚታወቅ/፤ የሰውና የመላእክት ምሥጢር) ናቸው፡፡ ሊቃውንቱም አምስቱ አዕማደ ምስጢራት ስለምን ምሥጢር እንደተባሉ ሲያብራሩ በዓይኔ ካላሣያችሁኝ በእጄ ካላሲዛችሁኝ ብሎ አላምንም አልማርም ይሉ ዘንድ አይገባም በቃል ተምሮ በልቡና ተመራምሮ አዎን ብሎ የሚማሯቸው ስለሆኑ ምሥጢር ተባሉ በማለት ገልጸዋል፡፡(ሃይ. አበው ዘአትናትዮስ 14÷ 39 ሃይ. አበው ዘኤራቅሊስ 11÷24 1ኛ ቆሮ 14፥19 1ኛ ሳሙ 17፥40)፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ በመኾኑ፣ በመንፈሳዊው አእምሮና ዓይን፣ ጆሮና እጅ ካልሆነ በቀር በነፍሳዊውና በስጋዊው አእምሮና ዓይን፣ ጆሮና እጅ ብቻ ሊታሰብና ሊታይ፣ ሊሰማና ሊዳሰስ ስለማይቻል ትምህርቱና እውቀቱ “ምስጢር” ተባለ። አምስቱ አዕማደ ምስጢራት “ምስጢር” የተባሉበት ምክንያት በሚከተሉት ሦስት ቁም ነገሮች በበለጠ ይብራራል።

አንድ፡ ረቂቅ እና ስውር ስለሆነው አምላክ የሚናገሩ አስተምህሮቶች ስለሆኑ ነው። የእግዚአብሔርን የአንድነትና የሦስትነት ነገር፣ ቀጥሎ ከሦስቱ አካላት አንዱ ሰው የመሆኑ ነገር፣ እንዲሁም ሰው ከእግዚአብሔር በመንፈስ የመወለዱን ነገር፣ ደግሞም ሰው የሆነውን አምላክ ሥጋውን በመብላትና ደሙን በመጠጣት በእግዚአብሔር መንግስት ለዘለአለም ሕያው ሆኖ የመኖርን ነገርና በመጨረሻም ሰው ለዘላለማዊው ህይወት ወይም ሞት በማይበሰብስ አዲስ አካል እንደገና የመነሳቱን ነገር የሚያስረዳ ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ ትምህርት የሚያስረዱ በመሆኑ ነው።

ሁለት፡ ትምህርቶቹን በሥጋዊ ጥበብ ለመረዳት የማይቻል በመሆኑ ነው። ትምህርቱና እውቀቱ እንደሥጋዊ ትምህርትና እውቀት ተፅፎ የሚቀርብና ተነቦ የሚጠና፣ በሥጋዊው ቁሳቁስ ግዙፍ ማስረጃነት እየተደገፈ የሚሰጥ ሳይሆን በአንድ ወገን ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ልቦና በእውነተኛ አምልኮ ፈልቆ የሚናገሩትና የሚያስተምሩት፣ በሌላው ወገን ደግሞ በእውነተኛ ፍላጎት በተመሰረት ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ልቦና ሆነው የሚሰሙትና የሚማሩት ረቂቅ የእግዚአብሔር ነገር ስልሆነ ነው።

ሦስት፡ ቤተክርስቲያን ለአማንያን ብቻ የምትነግረው እና የምታስተምረው በመሆኑ ነው። ለማያምኑ የማይገለጥ፣ ለሚያምኑ ግን በእውነተኛው መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ የእውቀት ቁልፍ ከፍተው በዚያው በፍፁም ብርሃን ካዩት በኋላ አክብረው የሚጠብቁት “የማይጠፋ እንቁ” በመሆኑ ነው። (ማቴ. 7፡6፣ ማቴ. 13፡11)

አዕማደ ምስጢራት ምን ምን ናቸው?

አዕማደ ምስጢራት አምስት የሆኑት አራቱ ባህርያተ ሥጋና (አፈር፣ ውኃ፣ እሳትና ነፋስ) አምስተኛው ባህርየ ነፍስ (ልባዊት፣ ነባቢት፣ ሕያዊት የሆነች) ምሳሌ ያደረገ ሲሆን በዮሐ 5፡1 ያለችው አምስት እርከኖች የነበራት መጠመቂያም የእነዚህ ምሳሌ ናት፡፡ ያቺ መጠመቂያ ለድኅነተ ሥጋ ነበረች፤ አዕማደ ምሥጢር ግን ለድኅነተ ነፍስና ለድኅነተ ሥጋ ናቸው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አምስቱን አዕማደ ምስጢራት በረቂቅነታቸው እና በአኳሃን ቅደም ተከተላቸው እንደሚከተለው ታስቀምጣቸዋለች፡፡ እነዚህም ምሥጢረ ሥላሴ (የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት የምንማርበት)፣ ምሥጢረ ሥጋዌ (የአምላክን ሰው መሆን የምንማርበት)፣ ምሥጢረ ጥምቀት (ስለ ዳግም መወለድ የምንማርበት)፣ ምሥጢረ ቁርባን (ስለ ክርስቶስ ሥጋና ደም የምንማርበት) እና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን (ስለ ዳግም ምጽዓት የምንማርበት) ናቸው። አምስቱ አዕማደ ምሥጢር በአፈጻጸማቸው በሦስት ይከፈላሉ ። እነዚህም ምሥጢረ ሥላሴና ምሥጢረ ሥጋዌ አምነን የምንቀበላቸው፤ ምሥጢረ ጥምቀትና ምሥጢረ ቁርባን አምነን የምንተገብራቸው፤ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን አምነን በተስፋ የምንጠብቀው ናቸው። ከዚህ ቀጥሎ ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ምስጢራቱን ያብራራሉ፡፡

  1. ምስጢረ ሥላሴ፡  “አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፡፡” ማቴ 28፡20
  2. ምስጢረ ሥጋዌ፡  “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።” ዮሐ 1፡14
  3. ምስጢረ ጥምቀት፡ “ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል።” ማር 16፡16
  4. ምስጢረ ቁርባን፡ “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፡፡” ዮሐ 6፡54
  5. ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን፡  “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፡፡” ዮሐ 11፡23

 የአዕማደ ምስጢራት መሠረት ምንድን ነው?

አዕማደ ምስጢራት ይዘት ምንጭ የጌታና የሐዋርያት ትምህርት ነው፡፡ ‪ይሁን እንጅ አነሳሱ በጸሎተ ሃይማኖት ወይም አባቶቻችን ምዕመናንን በትክክለኛው ሃይማኖት ለማጽናትና መናፍቃንን ድል ለመንሳት በተካሄዱ በጉባዔ ኒቂያና ጉባዔ ቁስጥንጥንያ ነው፡፡ ‪‎ከዚህ በኋላ አባቶቻችን ጸሎተ ሃይማኖትን መሰረት በማድረግ ከብሉያት ከሐዲሳትና ከሊቃውንት መጽሃፍት በማውጣጣት አምስቱ አዕማደ ምሥጢራትን አዘጋጅተዋል፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ መሰረት የሆኑት አምስቱ አዕማደ ምስጢራት መሰረታቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ያድርጉ እንጂ ስያሜ መሰረታቸው 318ቱ ሊቃውንት በኒቂያ አርዮስን ካወገዙ ቦኋላ ካስታወቁት የሃይማኖት ቀኖና (ጸሎተ ሃይማኖት) ነው፡፡

በጸሎተ ሃይማኖት “ነአምን በአሃዱ አምላክ እግዚአብሔር(በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን)” ሲል በእግዚአብሔር አብ ያለውን እምነት፣ “ወነአምን በአሃዱ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ (በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን)” ሲል በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት፣ “ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ (በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን)” ሲል በመንፈስ ቅዱስ ያለውን እምነት በመግልጽ ምስጢረ ሥላሴን ያጸናል፡፡ እንዲሁም “ዘበእንቲአነ ለሰብእ ወበእንተ መድኃኒትነ ወረደ እምሰማያት፣ ተሰብእ ወተሠገወ እመንፈስ ቅዱስ፤ ወእማርያም እምቅድስት ድንግል (ስለእኛ ስለ ሰዎች ስለመዳናችን ከሰማይ ወረደ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ፈጽሞ ሰው ሆነ)” በማለት ምስጢረ ሥጋዌን ያጸናል፡፡ በተጨማሪም “ወነአምን በአሃቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን (በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን)” በማለት ሥጋ ወደሙ የሚፈተትበትን ቤተ-ክርስቲያን በመጥቀስ ምስጢረ ቁርባንን ያጸናል፡፡ “ወነአምን በአሃቲ ጥምቀት (በአንዲት ጥምቀትም እናምናለን)” በማለት ምስጢረ ጥምቀትን ያጸናል፡፡ “ወንሴፎ ትንሳኤ ሙታን (የሙታንንም መነሳት ተስፋ እናደርጋለን)” በማለት ምስጢረ ትንሳኤ ሙታንን ያጸናል፡፡

አዕማደ ምስጢርን ማወቅ ለምን ይጠቅማል?

በሥጋዊ ዐይን እግዚአብሔርን ማየትና በውስን አዕምሮ ሐልዎተ እግዚአብሔርን መመርመር አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ  ስለራሱም ይሁን ለእርሱ አንክሮና ተዘክሮ ስለተፈጠሩት ፍጥረታት ገና ያልደረሰባቸው ነገሮች አሉ፡፡ እግዚአብሔር ግን እርሱ በወደደው መጠን ለአባቶቻችን ለቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት አዕምሮአቸው ሊረዳው በሚችለው መጠን በብዙ ምሳሌና በብዙ ጎዳና ማንነቱን ገልጾላቸዋል (ዕብ 1፡1-2)፡፡ እግዚአብሔርንም የምናውቀው እርሱ ራሱን ለሰው ልጆች በገለጠው መጠንና የሰው ልጅ መረዳት በሚችለው መጠን ብቻ ነው፡፡

አንድ ሰው በዚህ ዓለም ሲኖር አምስቱን አዕማደ ምስጢራት በሚገባ ከተማረ በሕይወቱ ምንም እንኳን ነፋሳት ቢነፍሱ ጎርፍም ቢጎርፍ ከእምነቱ ምንም ሊያናውጠው አይችልም፡፡ እነዚህ ትምህርቶች ከደሙና ከአጥንቱ ተዋሕደው የዚህን ዓለም ፈተና እንዲቋቋም ያስችሉታል፡፡ አዕማደ ምስጢራትን ያወቀና ያመነ እና የሥላሴ ልጅነትን በጥምቀት ያገኘ አባት እናት ቢሞቱበት በሥላሴ አባትነት ይጽናናል፡፡ መከራ ቢደርስበት አምላክ ሰው ሆኖ በዚህ ምድር ላይ የደረሰበትን መከራ እያሰበ ከምንም አይቆጥረውም፡፡ ረኀበ ነፍስ ቢደርስበት ቅዱስ ሥጋውን ይበላል፤ ክቡር ደሙንም ይጠጣል፡፡ በእምነቱ ምክንያት እንገድልሀለን ቢሉት ትንሣኤ ዘጉባዔን (ትንሣኤ ሙታንን) ተስፋ ያደርጋል፡፡ ይህም በመሆኑ ቅድስት ቤተክርስቲያን ከኅሊና እግዚአብሔር እንዳይርቅና ከእግዚአብሔር ጋር በእምነት እንዲጸና እነዚህን ምሰሶዎች (ምስጢራት) ታስጨብጠዋለች፡፡ በእነዚህ ምሰሶዎች (ምስጢራት) የተደገፈ ጠላቶቹን አጋንንትንና መናፍቃንን ድል ያደርጋል፡፡ በአጠቃላይ አዕማደ ምስጢራትን በሚገባ ማወቅ ሃይማኖትን በሚገባ ለመረዳት፣ ከጥርጥርና ከኑፋቄ ለመጠበቅና በሃይማኖት ጸንቶ ጽድቅን ለመፈጸም ይጠቅማል፡፡

11 thoughts on “አምስቱ አዕማደ ምስጢራት፡ መግቢያ

  1. ቃለ ሂወት ያስማልን፡ በእውነት ከዚህ በላይ ትልቅ ነገር ምን አለ፡ ይሂን አውቀን ተርድተን እንድንጓዝበት የእኛ ፍቃድ ያስፈልጋል ከዛም እግዚአብሔር ይርዳን፡ የሂወት መንገዳችን ይሂ መስርታዊ ትምህርት ብቻ ነው፡

    Like

    • 1. ከሌላ ሃይማኖት ተከታይ ጋር የተደረገ ወሲብ ግንኙነት የንስሓ ስርዓት እንዴት ነው?
      2. አዕማደ ምስጢራት ያልተማረ ክርስቲያንስ እንደ ክርስቲያን ፆም ፀሎት ቢያደርግ ይቆጠርለታል?
      3. ከቆረበ ከተጠመቀ ብዙ አመታት ያሳለፈ ክርስቲያንስ አሁን እንደ ክርሰቲያን ይቆጠራል ?
      መልሱን በጉጉት ነው የምጠብቀው ። አመሰግናለሁ

      Like

      • ሰላም ልዩ፣ ለጥያቄሽ እናመሰግናለን። በጥያቄሽ ቅደም ተከተል ከቤተክርስቲያን የተማርነውን አቅርበንልሻል።                            
        1• የንስሓ ስርዓት በዋናነት በንስሓ አባትና ልጅ መካከል በምስጢር የሚፈፀም ስለሆነ ለሁሉም ተመሳሳይ ስርዓት ብቻ ላይፈፀም ይችላል። ከኃጢአት ሁሉ የሚከፋው ዝሙት ነው። በተለይም በሃይማኖት ከማይመስሉት ጋር ሲፈፀም በደልነቱ ይከፋል። ይሁንና ከምንም በላይ የሰውን መመለስ የሚፈልግ አምላካችን ከተፀፀትን፣ ከተናዘዝን፣ ይምረናል። የንስሓ አፈፃፀሙ በቄሱ ስልጣን የሚወሰን ቢሆንም ከእምነት ክደው ለሚመለሱ ሰዎች የሚፀለይ ጸሎት ጸልየው የንስሐ ጥምቀት ሊያጠምቁ ይችላሉ። ይህ ማለት ግን ቄዳር ካልተጠመቀ ንስሓው ችግር አለበት ማለት አይደለም።                                  
        2• አዕማደ ምስጢራትን መማር የሁሉም ክርስቲያን ግዴታ ነው። ነገር ግን አለመማሩ ፆሙና ጸሎቱን አያሳንሱበትም። ከእውቀት ይልቅ ምግባር ይበልጣል። ነገር ግን “ምግባር ይበልጣል” በሚል ከእውነተኛ ትምህርት ርቀው ፆምና ጸሎት ብቻ ቢያደርጉ ሰይጣን ባለማወቃቸው ገብቶ ከሁሉም ሊያሰናክላቸው ይችላልና መሰረተ ሃይማኖትን ስርዓተ ቤተክርስቲያንን በሚገባ መማር ያስፈልጋል።                            
        3• ክርስትና ከማይጠፋ ዘር መወለድ ነው። ክርስቲያን ከቅዱስ ቁርባን ርቆ መኖር የለበትም። ነገር ግን ከቆረበ ብዙ ጊዜ ስለሆነው ወይም በኃጢአት ውስጥ ስላለ ከክርስቶስ ኅብረት (ክርስቲያን ከመሆን) አይለይም። የበለጠ ወደቅዱሳን ኅብረት ለመደመር ግን ንስሓ ገብቶ መመለስ ያስፈልጋል። ለዚያ ነው በጸሎተ ቅዳሴ ካህኑ ጸሎተ ንስሓ ሲጸልይ “ወንዶቹንም ሴቶቹንም ከቅድስት ቤተ ክርስቲያንህ ጨምራቸው” የሚለው። በኃጢአት የተለየ በንስሐ ይመለሳል። ሰይጣን ግን ተንኮለኛ ስለሆነ ኃጢአተኛውን ተስፋ ለማስቆረጥ “አንተኮ ከዚህ በኋላ ክርስቲያን ልትባል አይገባም” እያለ በቀቢፀ ተስፋ ተይዞ በኃጢአት እንዲበረታ ያደርገዋል።

        Liked by 1 person

  2. እናንተ ሰዎች ማንነታችው አይታወቅ። በጣም ይገርመኛል። በአሁን ሰኣት ሁላችን ውዳሴ ፈላጊ ነው። ደግሞ የትምህርታቸው ጥልቀት ብቻ ሳይሆን በቀላል ማንም ሊረዳው በጣም በጸዳና ልብን ሰርስሮ በሚገባ አረፋተ ነገር አቀማመጥ አስቅምጥችሁ ልክ አስተማሪ እንዳል ነው የሚገባኝ እኔ ሳነበው። እግዚአብሔር በስውር የምሰሩትን በግልጽ እንደሚከፍላችሁ እርግጠኛ ነኝ። እግዚአብሔር ይስጣችሁ። እኔ በጣም ብዙ ነገር ተምሬበታለው። ከምንም በላይ የሃሳብ ፍሰቱ ይገርመኛል። የእግዚአብሔር እርዳታ በእርግጠኝነት አለበት ብዬ አስባለው።

    Like

  3. ቃለ ሂወት ያሰማልን መንግስተ ሰማያትን ያውርስልን አንድ ማወቅ የፈለኩትን ነገር ነበር ከቻላችሁ ፖስት ብታደርጉልኝ በእግዚአብሄር ስም ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው ወይ ደግሞ ማግኘት የምችለበትን መንገድ ብትጠቁሙኝ ገድለ ቅዱስ ያሬድ ፈልጌ ነበር ስሁሉም ነገር በእግዚአብሄር ስም አመሰግናለሁ

    Like

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s