መግቢያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በልዩ ልዩ መንገድ ክርስትናን ስታስተምር የቆየች ጥንታዊትና ታሪካዊት ቤተክርስቲያን መሆኗ ይታወቃል፡፡ እነ አቡነ ተክለሃይማኖትና አባ ሳሙኤል ዘዋልድባን የመሳሰሉ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት በልዩ ልዩ የሀገራችን ኢትዮጵያ የቀድሞ ጠረፋማ አካባቢዎች የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ህዝቦችን በክርስትና አስተምረው ሲያጠምቁ በሚገባቸው ቋንቋ እንዳስተማሯቸው ወይም በደቀ መዛሙርቶቻቸው አማካኝነት እንደሰበኩ የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ አገልግሎታቸው ፍሬ ባላፈራ ነበር፡፡ የማንበብና የመፃፍ ክህሎት በየቋንቋው ከመስፋፋቱ አስቀድሞ በነበሩት ዘመናት ትምህርተ ወንጌልና ሥርዓተ ሃይማኖት ከቃል ባሻገር ከባህልና ከአኗኗር ጋር በተሰናሰለ ሁኔታ በቀደሙ አባቶቻችን ይሰጥ እንደነበረ የሚያሳዩ በርካታ ማኅበረሰባዊ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በአንድ ወቅት ትምህርተ ሃይማኖትን ከአኗኗራቸው ጋር አዛምደው ይዘው የነበሩ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በጊዜ ሂደት የሚመክርና የሚያስተምር ካህን፣ መምህር አጥተው ከቀደመ የክርስትና አምልኳቸው ቢለዩ እንኳ በባህላቸውና በአኗኗራቸው የቀደመውን ዘመን የክርስትና ላህይ የሚያሳዩ አሻራዎችን ይዘው የሚገኙበት ጊዜ አለ፡፡ የማንበብና መፃፍ ክህሎት የጥቂቶች ብቻ የነበረበት ዘመን አልፎ በተስፋፋበት የቅርብ ዘመን ታሪክ ግን ቤተክርስቲያናችን ለዘመኑ በሚመጥን መልኩ ምዕመናንን በየቋንቋቸው ከማስተማር አኳያ ከፍተኛ ድክመት እንዳለባት የታወቀ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮዋ አስቀድሞ የግዕዝን ቋንቋ ከቅርብ ዘመናት ወዲህ ደግሞ አማርኛን ቋንቋ የሚጠቀም በመሆኑ ሌሎች በኢትዮጵያ ውስጥና ከኢትዮጵያ ውጭም የሚነገሩ ቋንቋዎችን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት የመጠቀሙን ሁኔታ እጅግ አነስተኛ አድርጎታል፡፡ ይህም ቤተክርስቲያኗ እና አስተምህሮዋ በተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ብቻ ታጥሮ እንዲቆይ ከማድረጉ በተጨማሪ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብን በቋንቋው ወደሚያስተምሩ ሌሎች የእምነት/የሃይማኖት ተቋማት እንዲሄድ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ቤተክርስቲያኗ ለረጅም ዓመታት አገልግሎት እየሰጠች ብትቆይም በቋንቋው ያላስተማረችውን ሕዝብ ሌላው የእምነት ተቋም በአጭር ጊዜ (ለምሳሌ በ5 እና በ10 ወር) በቋንቋው እያስተማረ ሲወስደው ተመልካች ሆና መቆየቷ የታሪክ ተወቃሽ አድርጓታል፡፡ እጅግ ቢዘገይም በቅርብ ጊዜ የተጀመረው የስብከት፣ የመዝሙርና የቅዳሴ አገልግሎቶችን በኦሮምኛና በትግርኛ ቋንቋዎች የማጋጀትና የማሠራጨት ጅምር በሌሎች ቋንቋዎችም ተስፋፍቶ ሊቀጥል ይገባል፡፡ በተወሰኑ አከባቢዎች ለተወሰነ ጊዜ የሚደረገው የስብከተ ወንጌል እና ሌሎች አግልግሎቶችን በተሟላና ዘላቂ በሆነ መልኩ ለማስቀጠል መተባበር ይገባል እንላለን፡፡
በወላጆችና በልጆች መካከል ያለው የቋንቋ ልዩነት
በዝርወት ዓለም በሚኖረው ሕዝበ ክርስቲያን ዘንድ ያለው እውነታ የሚያሳየው አብዛኞቹ ልጆች እዛው የተወለዱ ከመሆናቸውም አንፃር የሀገሩን ቋንቋ አቀላጥፈው የሚናገሩ ነገር ግን የወላጆቻቸውን ቋንቋ ለመናገር የሚቸገሩ ናቸው፡፡ በሌላ መልኩ አብዛኞቹ ወላጆች ተወልደው ያደጉበትን የሀገራችን ቋንቋ አዘውትረው የሚናገሩ፣ የሚኖሩበትን ሀገር ቋንቋ ደግሞ በተወሰነ መልኩ ብቻ የሚናገሩ ናቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ በተለይም በቤተሰብ ደረጃ በወላጆችና በልጆች መካከል የቋንቋ ልዩነት ጎልቶ የሚታይ ከመሆኑም ባሻገር በመካከላቸው ላለው ቤተሰባዊ ትስስር መላላት ዋንኛ ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡ ስለሆነም ልጆች በጨቅላ ዕድሜያቸው ከቤተሰቦቻቸው ሊያገኙት የሚችሉትን መሰረታዊ የቤተክርስቲያናችን ትምህርት ከማጣታቸው በተጨማሪ፣ በዛው ዕድሜያቸው ለሌሎች መልካም ያልሆኑ ጠባያት (risk behaviors) የሚጋለጡበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ በተለይም ለመዋዕለ ህፃናት ከደረሱበት ዕድሜ በኋላ አንዳንድ ቤተሰብ እንደሚገልፀው “ሊያመልጡን ነው” በሚል ስጋት ውስጥ ይገባሉ፡፡
ይህም ስጋት ልጆቻችን ሃይማኖታቸውን፣ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን ሳናስተምራቸው ከልጅነት ወደ ወጣትነት ዕድሜ ተሻገሩ ከሚል ቁጭት የመጣ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ቁጭት ተግባርን ካልስከተለ ለባሰ ቁጭት ከመዳረግ ውጭ በራሱ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ይህንን ለማድረግ ያለው አማራጭ ግልጽ ነው፡፡ እርሱም በወላጆችና በልጆች መካከል ያለውን ትስስርና ተግባቦት ማጠናከር ነው፡፡ ይህ ከቋንቋ አንጻር ሲታይ ወላጆች ቋንቋቸውን ለልጆቻቸው በሚገባ ማስተማር እና/ወይም ልጆች በሚገባ የሚረዱትን ቋንቋ ለመናገር ጥረት ማድረግ ነው፡፡ ሩጫ በበዛበት እና ሰው ብዙ ሰዓትና ከአንድ ሥራ በላይ በሚሠራበት ሀገር ይህ ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ወላጅ ለልጆቹ በቂ ትኩረት ከሰጠ ይህን ማድረግ ከባድ አይሆንም፡፡
ልጆችን ወላጆቻቸው በሚናገሩት ቋንቋ ቢማሩ የተሻለ ነውን?
ልጆች መጀመሪያ የሚያገኟት ቤተክርስቲያን በቤት ውስጥ ያለችው የወላጆቻቸውና የቤተሰቦቻቸው አንድነት ናት፡፡ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ተመሳሳይ ቋንቋ በማይነጋገሩበት በዝርወት ዓለም ባሉ ኢትዮጵያውያን (ኤርትራውያን) ቤተሰቦች ዘንድ በቃል ሊተላለፉ የሚገባቸው የቤተክርስቲያን አስተምህሮዎችን ማስረዳት ከባድ ሲሆን ይታያል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ልጆችን ሃይማኖታዊ ትምህርት ከማስተማር አንጻር በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ያሉ ምዕመናን ሁለት ዓይነት ሀሳብ ያነሳሉ፡፡ በሁለቱም አስተሳሰቦች ላይ መልካምና ደካማ ጎናቸውን አብረው ያነሳሉ፡፡
የመጀመሪያው አስተሳሰብ ልጆቹ ሃይማኖታዊ ትምህርቱን ወላጆቻቸው በሚናገሩት ቋንቋ ቢማሩ የተሻለ ነው የሚል ነው፡፡ ይህ አማራጭ የቤተክርስቲያኒቱ መምህራን (አብዛኞቹ ከሀገር ቤት የመጡና የሚመጡ ስለሆኑ) በቀላሉ ሊያስተምሯቸውና ወላጆችም ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉበት ይችላሉ የሚል መልካም እይታ አለው፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታም አብዛኛው የቤተክርስቲያኒቱ አገልግሎት (ቅዳሴ፣ ስብከት፣ መዝሙር፣ ትምህርት) የሚሰጠው በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ስለሆነ ይህ አማራጭ ልጆች በአገልግሎቱ እንዲሳተፉ ያደርጋል፡፡ የሃይማኖት መጻሕፍትም የታተሙት በእነዚሁ ቋንቋዎች ስለሆነ ለልጆቹ የተሻለ ተደራሽነት ይኖራቸዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ይሆን ዘንድ ልጆቹ ከሃይማኖት ትምህርት አስቀድሞ የቋንቋ ትምህርት መማር ይኖርባቸዋል፡፡በዝርወት ዓለም የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ለልጆች በተገቢው ደረጃ ለማስተማር በማህበረሰቡና በቤተሰብ ደረጃ ያለው ቁርጠኝነት ይወስነዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ልጆች በሁለተኛ (አፋቸውን ባልፈቱበት) ቋንቋ ተምረውስ ምን ያህል ሃይማኖታዊው ትምህርት ሊዋሀዳቸው ይችላል የሚል አሉታው መከራከሪያ አለው፡፡ ሆኖም ግን የብዙ ወላጆች ፍላጎትም ስለሆነ የወላጆቻቸውን ቋንቋ በሚገባ ለተማሩና የቋንቋውን ክህሎት ላዳበሩ ልጆች ይህንን አማራጭ መጠቀም ይቻላል፡፡
ልጆቹ አቀላጥፈው በሚናገሩት ቋንቋ ቢማሩ ይመረጣልን?
ሁሉተኛው አማራጭ ልጆቹ የኦርቶዶካሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ትምህርት አቀላጥፈው በሚናገሩት፣ ትምህርት ቤትም በሚማሩበት ቋንቋ፣ በሀገሩ ቋንቋ ቢማሩ ይመረጣል የሚል ነው፡፡ ይህም ልጆቹ ሃይማኖታዊ ትምህርቱን በሚገባ እንዲረዱት ያደርጋል፡፡ ሳይቸገሩም በቀላሉ ይገባቸዋል፡፡ በተጨማሪም በአገሩ ቋንቋ በትጋት ከሚያስተምሩ ከአንዳንድ አኃት አብያተ ክርስቲያናት የሚማሩበት ዕድል ስለሚገኝ ተጨማሪ ግብአት ይሆናቸዋል፡፡ ይህም ለተወሰነ ጊዜ በደንብ ቢሰራበት ማለትም ልጆች ሃይማኖታዊውን ትምህርት አፋቸውን በፈቱበት ቋንቋ (ለምሳሌ በእንግዝኛ) ቢማሩ በቀላሉ ወደ ተምሮ ማስተማር ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ይህም ማለት በአንድ ዙር (cohort) በቋንቋቸው በሚገባ ሃይማኖታዊውን ትምህርት ከተማሩ የእነርሱን ታናናሾች ያስተምራሉ፡፡ እንደዚያ እያለ በቀጣይነት ለሚመጣው ትውልድም በሀገሩ ቋንቋ የሚያስተምሩ መምህራንን፣ የሚቀድሱ ካህናትን፣ የሚዘምሩ መዘምራንንና በሀገሩ ቋንቋ ተሰጥኦ የሚቀበሉ ምዕመናንን ማፍራት ይቻላል፡፡
ነገር ግን በኛ ቤተክርሰቲያን በሀገሩ ቋንቋ የሚያስተምሩ መምህራን እጥረት አለ፡፡ መደበኛ የሆኑት የቤተክርስቲያን ካህናትና መምህራን የእንግሊዝኛም ሆነ የሌላ የውጭ ሀገር ቋንቋ ስልጠና የሚወስዱበት አሠራር ስለሌለ እነርሱ በዝርወት ዓለም የተወለዱትን ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ህጻናትና ወጣቶች ማስተማር እንደሚከብዳቸው ግልጽ ነው፡፡ በእንግሊዝኛም ቋንቋ ጭምር እንዲያስተምሩ ታስቦ በተከፈቱ የቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊ ኮሌጆች ከሚመረቁ ደቀመዛሙርትም ብዙዎቹ እንኳን ለማስተማር ለመግባባት እንኳ የሚሆን የቋንቋ ክህሎት ያላቸው አይመስልም፡፡ በመደበኛው የሀገራችን ትምህርት የተማሩ የቤተክርስቲያችን ልጆችም ቢሆኑ ይህን ክፍተት ለመሙላት የሚያበቃ ክህሎትም ዝግጁነትም አላቸው ለማለት የሚያስችል ሁኔታ ያለ አይመስልም፡፡ ስለሆነም ሊያስተምሩ ይችላሉ የሚባሉትም የቋንቋ ውስንነት ያለባቸው ናቸው የሚል መመከራከርያ ይቀርባል፡፡
በጥቂት ቁርጠኝነቱ ባላቸው የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች አስተባባሪነት ልጆችን በሀገሩ ቋንቋ (ለምሳሌ በእንግሊዝኛ) ማስተማር ቢጀመር ልጆቹ የቤተክርስቲያኒቱን አስተምህሮ እንዲያውቁ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ቅዳሴው በግዕዝና በአማርኛ፣ ስብከቱ በአማርኛና በትግርኛ፣ መዝሙሩ በግዕዝና በአማርኛ፣ ሰዓታቱና ማሕሌቱ በግዕዝ፣ ካህናቱም እንዲሁ በእነዚህ ቋንቋዎች የሚናገሩ ከሆነ በእንግሊዝኛ የተማሩት ልጆች እንዴት ሆኖ ነው ከቤተክርስቲያኒቱ አገልግሎት ተሳታፊ የሚሆኑት? ቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ አገልግሎቱን በእንግሊዝኛ መስጠት እስከምትጀምር ድረስ ልጆችን በእንግሊዝኛ ማስተማር ብቻ የመፍትሔ ጅምር እንጂ በራሱ መፍትሔ አይሆንም፡፡ በዚህም የተነሳ ቤተክርስቲያን ይህንን አማራጭ ገፍታ እንዳትሠራበት መሰናክል ሆኖ ይገኛል፤ ለወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ስለሆነም አንዳንድ ምዕመናን ልጆቻቸውን በአኃት አብያተ ክርስቲያናት (ለምሳሌ በኮፕቲክ ቤተክርስቲያን) ወስደው እንዲያስተምሩ ምክንያት ሆኗል፡፡
ቤተክርስቲያን ቋንቋን የማስተማር መንፈሳዊ ኃላፊነት አለባትን?
ሁሉም ወላጅ ልጆቹ የራሱን ቋንቋ በሚገባ ቢናገሩለት ደስ ይለዋል፡፡ ለቤተሰባዊም ሆነ ለማኅበራዊው መስተጋብርም ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ለልጆቹም ቢሆን አንድ ተጨማሪ ቋንቋ አቀላጥፎ መናገር ለአእምሮም ሆነ ለስነ-ልቦና፣ ለማኅበራዊም ሆነ ለዓለም አቀፋዊ ትስስር ታላቅ ድርሻ እንደሚኖረው ግልጽ ነው፡፡ አዋቂዎችን ቋንቋ ከማስተማር ይልቅ ልጆችን ማስተማሩ ቀላል ስለሆነም ልጆችን የወላጆቻቸውን ቋንቋ ማስተማርና ማሳወቅ የወላጆችና ቤተሰቡ የሚኖርበት ማኅበረሰብ ኃላፊነት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ግን መንፈሳዊ ተቋም ከመሆኗ አንጻር ለሰው ልጅ ሁሉ በሚናገረው ቋንቋ የክርስቶስን ወንጌል የማስተማር መንፈሳዊ ኃላፊነት አለባት፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለቅዱሳን ሐዋርያት 72 ቋንቋ የገለጸላቸው በየሀገሩ እየዞሩ የሰውን ልጅ በቋንቋው እንዲሰብኩ ነበር፡፡ ዛሬም የቤተክርስቲያን መምህራን ልጆችንም ሆነ ወጣቶችን እንዲሁም አዋቂዎችን በቋንቋቸው የማስተማር መንፈሳዊ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከዚህ አንጻር የቤተክርስቲያን ድርሻ ሃይማኖታዊ ትምህርትን የሰው ልጅ በሚናገረውና በሚረዳው ቋንቋ ማስተማር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ቋንቋን ማስተማር የቤተክርስቲያን መሠረታዊ ዓላማዋ አይደለም፡፡ በቤተክርስቲያን ያሉ አገልጋዮች ግን ቋንቋን በማስተማር ማኅበራዊ አበርክቶ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ይህም ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል መማር ፈልገው የሚመጡ ልጆችን ሁሉ ሊያስተናግድ የሚችልና ደረጃውን የጠበቀ የቋንቋ መማሪያ ማዕከል (Language Academy) ቢሆን መልካም ነው፡፡ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያኑ በአንዳንድ ቅንነት ባለቸው ምዕመናን ተሳትፎ ብቻ ብልጭ ድርግም የሚልና ባለህበት እርገጥ ዓይነት ተከታታይነትና ዘላቂነት የሌለው የቋንቋ ትምህርት ግን የልጆችን ዕንቁ የሆነ የመማሪያ ጊዜ ከማባከን ውጭ ብዙም ፋይዳ አይኖረውም፡፡
በዓለማዊ አስተሳሰብም ሆነ በመንፈሳዊው አስተምህሮ ቋንቋ ያው የመግባቢያ ክህሎት ነው፡፡ የቤተክርስቲያን መምህራንም እንደ ሐዋርያት የሰውን ልጅ በቋንቋው ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡ እዚህ ላይ አንዳንዶች ቤተክርስቲያንን የቋንቋ ማስተማርያ አድርገው ከማሰብ ይልቅ የሃይማኖታዊ ትምህርት ተቋም አድርገው ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡ ወላጆችና ማኅበረሰቡ ቋንቋን ለማስተማር ቢተጉ፣ ቤተክርስቲያን ደግሞ መንፈሳዊውን ትምህርት ልጆች በሚረዱት ቋንቋ ብታስተምር ልጆቹ በመንፈሳዊውም ትምህርት ሆነ በቋንቋ ክህሎታቸው የታነጹ ሆነው እንዲያድጉ ማድረግ ይቻላል፡፡ ቋንቋን ማስተማር በማይቻልበት ሁኔታ ግን መንፈሳዊውን ትምህርት በቋንቋቸው የሚማሩበትን አማራጭ መውሰድ ያስፈልጋል እንጂ ገና ለገና ቋንቋ እስኪማሩ ብሎ የልጆችን የመማሪያ ጊዜ በከንቱ ማባከን አይገባም፡፡
መፍትሔው: ልጆችና ወጣቶች በሚናገሩት ቋንቋ ማስተማር ነው!
የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መሠረታዊ ዓላማ የክርስቶስን ወንጌል ለሰው ልጅ ሁሉ ያለምንም ልዩነት በሚገባው ቋንቋ ማስተማር፣ በአገልግሎትና በምስጢራት ማሳተፍና ለመንግስተ ሰማያት ማብቃት ነው፡፡ ማንኛውም የሰው ልጅ የቤተክርስቲያኒቱን እምነት፣ ሥርዓትና ትውፊት ለማወቅ ከሚናገረው ቋንቋ ውጭ ሌላ ቋንቋ መማር/ማወቅ አይጠበቅበትም፡፡ በራሱ ቋንቋ የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርት መማር፣ ከአገልግሎቱ መሳተፍ፣ ለሌሎችም ማስተማር ይገባዋል፡፡ የቤተክርስቲያን ትምህርትና አገልግሎትም በተወሰነ ቋንቋ ብቻ መታጠር የለበትም፡፡ ልጆችም፣ ወጣቶችም፣ አዋቂዎችም፣ አረጋውያንም በሚናገሩት ቋንቋ የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርት ሊማሩና ከአገልግሎትም ሊሳተፉ ይገባል፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮችም ምዕመናኑ በሚናገሩት ቋንቋ የሚያስተምሩና ለአገልግሎትም ይህንንኑ ቋንቋ የሚጠቀሙ ሊሆን ይገባል፡፡
በዝርወት ዓለም ተወልደው ለሚያድጉ ልጆችም ያለው የቋንቋ አጠቃቀምን የሚመለከተው የቤተክርስቲያኒቱ አስተምህሮ የተለየ አይደለም፡፡ ይህም በሚናገሩት ቋንቋ የቤተክርቲያንን ትምህርት እየተማሩ፣ በቋንቋቸው የቤተክርስቲያንን አገልግሎት እየተሳተፉ፣ በእምነትና በምግባር ተኮትኩተው ሊያድጉ ይገባል የሚል ነው፡፡ ልጆች በሚናገሩት ቋንቋ የሚያስተምሩ መምህራንን፣ የሚቀድሱ ካህናትን፣ የሚዘምሩ መዘምራንን፣ የሚጽፉ ሊቃውንትን ማፍራት ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱ ተቋማዊ ኃላፊነት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በዝርወት ዓለም ያለችው ቤተክርስቲያን በስደት፣ ለትምህርትና ለሥራ ከሀገር ቤት ለሚመጡት ምዕመናን ብቻ ትሆንና እነዚህ ከሌሉ የማትኖር ልትሆን ትችላለች፡፡ ቤተክርስቲያን ኩላዊት (የሁሉም፣ ዓለም ዓቀፋዊት) ናት ሲባልም ለሰው ልጅ በሚናገረው ቋንቋ ታስተምራለች ማለት ስለሆነ በአገልጋዮች ዘንድ ያለው የቋንቋ ስብጥር (Language diversity) ሊታሰብበትና ሊሠራበት ይገባል እንላለን፡፡
ከዚህ በተረፈ በአንዳንድ ወላጆችና አገልጋዮች ዘንድ እንደሚታየውም ልጆች በወላጆቻቸው ቋንቋ መማር ሳይፈልጉ እንዲማሩ ወይም በሚገባ በማይረዱት ቋንቋ ሃይማኖታዊ ትምህርት እንዲማሩ ተፅእኖ በማሳደር ሳይሆን በፍቅር ወደውት እንዲማሩ(በ)ት ማድረግ ይገባል፡፡ በተጽእኖ ማስተማር ለቋንቋው ያላቸውን ፍላጎትና አመለካከትም ሊቀይር ይችላል፡፡ ልጆችና ወጣቶች በሚናገሩት ቋንቋ ለእናስተምራቸው እንጂ በማይገባቸው ቋንቋ እንዲማሩ ባናስገድዳቸው መልካም ነው፡፡ ስለዚህ አስቀድሞ ቋንቋውን የማወቅ ፍላጎትን መፍጠር እና የቋንቋ ክህሎታቸውንም ማሳደግ ያስፈልጋል እንጂ ልጆችን ያለፍላጎታቸው ይህንን ቋንቋ ተማሩ ወይም በዚህ ቋንቋ ተማሩ ማለት ሕጋዊም፣ ሃይማኖታዊም መሠረት የለውም፡፡ በአጠቃላይ እያንዳንዱ ልጅ ወይም ወጣት በሚገባውና የተሻለ በሚረዳበት ቋንቋ የሚማርበትን አማራጭ መፍጠር ያስፈልጋል እንጂ ሁሉም ልጆች ወይም ወጣቶች በዚህ ወይም በዚያ ቋንቋ ብቻ ይማሩ የሚለው ጉንጭ አልፋ ክርክርም ለቤተክርስቲያን ዕድገት አይበጅም፡፡