በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሚሰጠውን የልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያኑ ልጆችን የሚያስተምሩ መምህራን ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ:: በመሆኑም የመምህራን ብዛትና ብቃት ለትምህርቱ ይዘትና አካሄድ ከሚሰጠው ትኩረት ባልተናነሰ መልኩ ሊታሰብበትና ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው:: ልጆችን ለማስተማር ቀናነትና ፍላጎት አስፈላጊ ቢሆኑም ሌሎች መሠረታዊ ክህሎቶችን አቀናጅቶ መያዝ ለትምህርቱ ውጤታማነት ወሳኝ ነው፡፡ በመጅመሪያ ደረጃ ልጆችንና ወጣቶችን በማስተማር በቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት መሳተፍ የሚፈልጉ ምዕመናን፣ ካህናትና መምህራነ ወንጌል መልካም አመለካከትንና ክርስቲያናዊ ምግባርን በቃልና በተግባር ማስተማር የሚችሉ መሆን ይገባቸዋል::
ወላጆችም ልጆቻቸው መንፈሳዊ ትምህርትን እንዲማሩ ወደ ቤተክርስቲያን ከመውሰዳቸው በፊት “ማነው የሚያሰተምራቸው?” የሚለው ጥያቄ በውስጣቸው እንደሚኖር አያጠያይቅም፡፡ እምነት የሚጣልባቸውና ለልጆች መልካም አርአያ የሚሆኑ መምህራን ካሉ ልጆቻቸውን በደስታ ይዘው ይመጣሉ፣ ያስቀጥላሉም፡፡ መንፈሳዊ ዕውቀት ቢኖራቸውም በመልካም ምግባር የማይታወቁ መምህራን ካሉ ግን ወላጆች ፍልጎት ቢኖራቸውም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርቱ ከማምጣት ወደኋላ ይላሉ፡፡ ቢያመጧቸውም ልጆቹ መልካምነትን ተምረው ላይመለሱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በቤተክርስቲያን ለልጆች መንፈሳዊ ትምህርትን የሚያስተምሩ (ለማስተማር የሚመለመሉ) መምህራን ወደ አገልግሎቱ ከመሰማራታቸው በፊት ለዚህ አገልግሎት የሚሆናቸውን መሠረታዊ መስፈርቶች ማሟላት አስፈላጊ ነው፡፡ ስለሆነም የአጥቢያ መንፈሳዊ ሰበካ ጉባዔ መምህራንን በሚመድብበት ጊዜ አስፈላጊ የሆኑት መስፈርቶችን ማሳወቅ፣ ማረጋገጥና ተግባራዊነታቸውን መከታተል ይኖርበታል፡፡ እኛም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን ሊያሟሏቸው የሚገቡ ሰባት መሠረታዊ መስፈርቶችን እንዳስሳለን፡፡
ኦርቶዶክሳዊት እምነት
የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ተቀዳሚ ዓላማ ክርስትናን ሳይበረዝና ሳይከለስ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ ከመሆኑ አንጻር ለልጆች መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራንም የቤተክርስቲያኒቱን እምነት የሚያምኑና በዚህም የተመሠከረላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ በሕይወታቸውም እግዚአብሔርን የሚፈሩና ሰውን የሚያከብሩ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በእምነታቸው የሚጠረጠሩ ወይም ጥያቄ የሚነሳባቸው ወይም እውነተኛ እምነታቸውን ለማስመስከር ያልቻሉ ልጆችን ለማስተማር ከመሰማራታቸው በፊት ይህ ሊስተካከል ይገባል፡፡ አንዳንድ የተሐድሶ መናፍቃን ቤተክርስቲያንን ከሚጎዱባቸው መንገዶች አንዱ ሠርጎ በመግባት ልጆችን ኑፋቄ ማስተማርና የቤተክርስቲያኒቱን ቀጣይነት መፈታተን መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል፡፡ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ በደንብ ያልተረዱ አንዳንድ የልጆች መምህራንም ለዚህ እኩይ ተግባር መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ራሳቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡
መንፈሳዊ ዕውቀት
ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን ራሳቸው የቤተክርስቲያን ትምህርት ቢያንስ በሰንበት ትምህርት ቤት በተከታታይ ስልጠና የወሰዱና ልጆችን ለማስተማር የሚያበቃ መንፈሳዊ ዕውቀትን ያካበቱ መሆን አለባቸው፡፡ ልጆችን የሚያስተምሩ መምህራን መሠረታዊ የቤተክርስቲያን ትምህርትን ለምሳሌ አዕማደ ሚስጢር፣ ስነፍጥረት፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን፣ እንዲሁም ስለቤተክርስቲያን ታሪክና ፈተናዎች በቂ ዕውቀት ያላቸው መሆን ይኖርባቸዋልል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች የእምነት ድርጅቶች ስለሚያነሷቸው ጥያቄዎች የሚያውቁና እና ስለሚኖሩበት ሀገርም በቂ ዕውቀት ያላቸው፤ በዚህም ዙሪያ ልጆች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ሊሠጡ የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡ በዘመናዊ ትምህርታቸውም ቢያንስ ልጆችን ለማስተማር የሚያስችል የዕውቀት ደረጃ ላይ የደረሱ ቢሆኑ ይመረጣል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ስለልጆች አእምሮአዊ፣ ስሜታዊ፣ ማኅበራዊና ሞራላዊ የዕድገት ሂደት በቂ ዕውቀት ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡
የማስተማር ክህሎት
መንፈሳዊ ትምህርትን ለማስተማር የማስተማር ልዩ ዝንባሌና ችሎታ ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራንም ልጆችን የማስተማር ዝንባሌና ክህሎቱ ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ በቅድሚያ መምህራኑ ልጆችን ማስተማር እጅግ ትልቅ የቤተክርስተያን አደራ እንደሆነ የሚያውቁና የሚያምኑ ሊሆኑ ይገባል፡፡ የመንፈሳዊ ትምህርት ዋናው ዓላማ ልጆች የሚገባቸውን ዕውቀት እንዲቀስሙና መንፈሳዊ ዕውቀታቸወን እንዲያድግ እስከሆነ ድረስ፣ መምህራን ልጆች የሚናገሩትን ዋና (የአፍ መፍቻ) ቋንቋ መናገር የሚችሉ ሊሆኑም ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም የሚችሉ፣ ልዩ ልዩ የማስተማርያ ዘዴዎችን የሚያውቁ፣ ለማወቅና ሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው የሚያምኑ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ከልጆች ጋር በሚኖራቸው የትምህርት መርሐግብርም ልጆችን በእኩልነትና በፍቅር መያዝ የሚችሉ ሊሆኑ ይገባል፡፡
መልካም አመለካከትና ቁርጠኝነት
ልጆችን ማስተማር ትልቅ ኃላፈነትና መስዋዕትነት የሚጠይቅ ተግባር ሲሆን በዚያው ልክም ትልቅ በረከት የሚያስገኝ አገልግሎት ነው፡፡ ስለዚህ ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራንም በሰው ልጅ የመሻሻልና የማደግ ባሕርይ የሚያምኑና ለዚህም በጎ አመለካከት ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ በጎ አመለካከት ለውጤታማ ሥራና ለመንፈሳዊ ሕይወት መሠረት ነው፡፡ ከዚህም አንጻር ልጆችን የሚያስተምሩ መምህራን ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊት፣ ታሪካዊ ጉዞ እንዲሁም ስለቤተክርስቲያን አጠቃላይ አገልግሎት በሚገባ የተረዱና ቅን አመለካከት ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ በዚህ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎችንም በበጎ የሚመለከቱ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከዓለም ዓቀፍ ትስስር አንጻርም በዓለም ላይ ስላሉ አጠቃላይ ክስተቶች ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ያላቸውና የሚከታተሉ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ስለራሳቸው ባላቸው አመለካከትም በቀጣይነት ለመማርና ለመሻሻል ጽኑ ፍላጎት ያላቸው ቢሆኑ ለልጆችም መልካም አርአያ መሆን ይችላሉ፡፡ መንፈሳዊ ትምህርቱን በሚገባ ለመተግበርም መምህራኑ ከወላጆችና ከቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና ስብከተ ወንጌል ክፍል ጋር በመናበብ መሥራት እንደሚጠቅም የሚያምኑና ለዚህም የሚተጉ መሆን አለባቸው፡፡
ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር
ልጆችን ከቃል ይልቅ ተግባር የበለጠ ያስተምራቸዋል፡፡ ስለዚህ ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት፣ ሥርዓትና ትውፊት ከማመን በተጨማሪ በክርስቲያናዊ ምግባራቸው አርአያ መሆን የሚችሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከክርስቲያናዊ ምግባራትም ለምሳሌ በመጾም፣ በመጸለይ፣ በማስቀደስ፣ በመቍረብ፣ በትሕትና፣ በክርስቲያናዊ አለባበስ ወዘተ ለልጆች ምሳሌ መሆን የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ መንፈሳዊ ዕውቀትና የማስተማር ክህሎት መልካም ስነ-ምግባር ካልታከለበት የልጆችን የማስተማር ሂደት ውጤታማ አያደርገውም፡፡ እምነቱ እያላቸው የማይተገብሩም ልጆችን ለማስተማር ከመሰማራታቸው በፊት ራሳቸውን በንስሐ ሕይወት አስተካክለው ክርስቲያናዊ ስነ-ምግባራትን መፈጸም ሊጀምሩ ይገባል፡፡ ከክርስቲያናዊ ስነ-ምግባር ጎን ለጎንም በዘመናዊ ትምህርታቸውና ሥራቸው (ለኑሮ በሚሠሩት ሥራ) ለልጆች አርአያ የሚሆኑ ቢሆኑ ደግሞ የተሻለ ይሆናል፡፡
መሠረታዊ ሥልጠና
ለልጆች መንፈሳዊ ትምህርትን ማስተማር በቅንነት ብቻ ተነስቶ የሚገባበት ወይም እገሌ ያስተምር ተብሎ ምደባ የሚሠጥበት አገልግሎት አይደለም፡፡ ከላይ ከተጠቀሰው መንፈሳዊ ዕውቀት በተጨማሪ መምህራን የየሀገራቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ ባስገባ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ሥልጠና የወሰዱ መሆን አለባቸው። የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት የሚመራበትን ሥርዐተ ትምህርት ለመተግበር መምህራንን ማሰልጠን እና ሥርዐተ ትምህርቱን በሚገባ እንዲረዱት፣ እንዲተገብሩትና ለሌሎችም ማስረዳት እንዲችሉ ማደረግ ይገባል። በግልጽ የታወቀ ሥርዓተ ትምህርት በሌለበትና መምህራኑም በሥርዓተ ትምህርት በማይመሩበት ሁኔታ ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት ማስተማር ውጤታማነቱ አጠያያቂ ነው፡፡
ሕግን ማወቅና ማክበር
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን ስለልጆች አያያዝ፣ ከልጆች ጋር አብሮ ስለመሥራት፣ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች አያያዝንና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ሕግጋትን የሚያውቁና የሚያከብሩ መሆን አለባቸው፡፡ ይህንንም ከቤተክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት ጋር አጣጥመው በመተግበር ለልጆችም አርአያ መሆን አለባቸው፡፡ የመምህራኑም ስልጠና እነዚህን ሕግጋት የሚዳስስና ስለአተገባበራቸውም የሚገልጥ ሊሆን ይገባል፡፡ እንደየሀገራቱ ሁኔታም ከልጆች ጋር ለመሥራት የሚያስፈልግ የምስክር ወረቀት ካለ መምህራኑ ይህንን መያዛቸውን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ይህም ሲደረግ ልጆችን ከአእምሮአዊ፣ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጥቃት መጠበቅና በሚገባቸው መንገድ ማስተማር ይቻላል፡፡ ሕግ ባለበት ሀገር ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት ስለማያድን ሕግን ማወቅና እንዲተገበር ማድረግ መምህራኑ ልጆችን በሕጉ መሠረት እንዲይዙ ይረዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቤተክርስቲያን ልጆችን በሕግና በሥርዓት ይዛ ማስተማሯ ሕግን አክብራ ከመሥራቷ ባሻገር ለሌሎችም አርአያ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡
በአጠቃላይ ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን እምነት፣ ሥርዓትና ትውፊት ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ የሚያምኑና የሚፈጽሙ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ለመማር ማስተማሩም ውጤታማነት ይረዳ ዘንድ ስለልጆች ትምህርትና ዕድገት መልካም አመለካከት ያላቸውና የማስተማር ክህሎትንም ያዳበሩ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ልጆች በሚናገሩት ዋነኛ ቋንቋ ማስተማር የሚችሉና በቴክኖሎጂ በታገዘ የትምህርት አሰጣጥ ልምድ ያላቸው ቢሆኑ ደግሞ ትምህርቱ በሚገባው ደረጃ እንዲሰጥ ይረዳል፡፡ መምህራን በእምነታቸውና በሥነ-ምግባራቸው አርአያ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሚኖሩበትን ሀገር ሕግ የሚያውቁና የሚያከብሩ መሆን አለባቸው፡፡ እነዚህን መስፈርቶች የማያሟሉ መምህራን ላይ ወላጆች እምነት ስለማይጥሉባቸው ልጆቻቸውን ይዘው ለመምጣት ሊያመነቱ ይችላሉ፡፡
ስለዚህ ልጆችን የማስተማር ፍላጎቱ ያላቸው ኦርቶዶክሳዊያን ወንድሞችና እህቶች እነዚህ ልጆችን ለማስተማር የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ መስፈርቶች ተገንዝበውና አስፈላጊውን ስልጠና ወስደው ወደ አገልግሎቱ ሊገቡ ይገባል፡፡ የየአጥቢያው ቤተክርስቲያን ሰበካ መንሳዊ ጉባዔ አስተዳደርም ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን እነዚህን መሠረታዊ መስፈርቶችን የሚያሟሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባቸዋል፡፡ ይህም የሚደረግበት ዓላማ ልጆች በልጅነታቸው ሊያገኙት የሚገባውን መንፈሳዊ ትምህርት በተገቢው መንገድ እንዲማሩ ለማስቻል መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ እነዚህን መሠረታዊ መስፈርቶች የማያሟሉ ካሉ ደግሞ አሟልተው ወደ አገልግሎቱ እንዲገቡ ማገዝ ይገባል እንላለን፡፡ †