ሕግጋተ ወንጌል (ክፍል ፬): ሐሰትን በሕሊናህ አትፍጠር፣ በአንደበትህ አትናገር፣ በመሐላ ለማጽናትም አትድከም

ጌታችን ፍጽምት በሆነችው ሕገ ወንጌል በአራተኛው አንቀጽ ያስተማረው ፍጹም እውነተኛ መሆን እንደሚገባና መሐላም እንደማያስፈልግ ነው። ይህንንም “ደግሞ ለቀደሙት በውሸት አትማል ነገር ግን መሐላዎችህን ለጌታ ስጥ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ። ከቶ አትማሉ፤ በሰማይ አይሆንም የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም አይሆንም የእግሩ መረገጫ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አይሆንም የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም አትማል፥ አንዲቱን ጠጉር ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና። ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው (ማቴ 5:33-37)” በማለት አስተምሯል። ይህች ሕገ ወንጌል በሐሰት አትመስክር እና የእግዚአብሔር አምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ ከሚሉት ሕግጋተ ኦሪት ጋር የተያያዘች ናት።

አራተኛዋ ሕገ ወንጌል እውነተኛነት ላይ የምታተኩር ናት።

አራተኛዋ ሕገ ወንጌል ስለመሐላ የተነገረች ብትመስልም መሠረታዊ መልእክቷ ግን እውነተኛነትን (በሕይወታችን ዘመን ሁሉ ሙሉ እውነትንና እውነትን ብቻ መናገርን (Truthfulness)፣ በእውነትም መኖርን (Integrity)) የሚመለከት ነው። እውነተኛነት ሕግ ብቻ ሳትሆን የሕይወት መንገድም ናት። እውነት በቃልም በተግባርም (ለእግዚአብሔር በመታዘዝ፣ ከእርሱም ጋር በመኖር) የሚገለጥ ክርስቶስን የምንመስልበት አንዱ መንፈሳዊ ባህርይ (virtue) ነው። ክርስቶስ እውነት ነውና (ዮሐ 14:6)፣ በአንደበቱም ሐሰት አልተገኘበትምና (1ኛ ጴጥ 2:22)። በተቃራኒው ሐሰትን መናገር ከእግዚአብሔር ይለየናል፣ በሰዎች እንዳንታመን ያደርገናል፣ የሐሰት አባት ከሆነው ከዲያብሎስ እንድንሆን ያደርገናል፣ በመጨረሻም የዘላለም ሕይወትን ያሳጣናል።

ሐሰትን የመናገር (መዋሸት) አዙሪትም (cycle) እንዲህ ነው (ሐሰት ማለት ከእውነት የራቀ፣ እውነት ያልሆነ ነገር ማለት ነው። ውሸት ደግሞ ሐሰትን ተናግሮ ሰውን የማታለል ድርጊት ነው። በዚህች ጽሑፍ ሁለቱን በተለዋዋጭነት እንጠቀማለን)። በመጀመሪያ ሰው የፍርሃት ወይም የሆነ ነገርን የማጣት ስሜት ሲሰማው እውነትን ተናግሮ የሚመጣውን በጸጋ ከመቀበል ይልቅ ሐሰትን በአእምሮው ውስጥ ያስባል (ይፈጥራል)። ከዚያም በሀሳቡ ለመቀጠል ከወሰነ በአንደበቱ ይናገረዋል። በቀጣይም በመሐላ በመሸፈን ወይም ሌላ ሐሰት በመጨመርና በሌሎች በተለያዩ መንገዶች ሐሰትነቱ እንዳይጋለጥበት ይከላከላል። እንደዚህ እያለ አንዱ ሐሰት ሌላውን እየወለደ ሐሰት መናገር ይለመድና ኃጢአት የማይመስልበት ደረጃ ይደርሳል። ከዚህ አልፎም ሐሰትን ተናግሮ ማታለል እንደ ጥበብ የሚቆጠርበት አመለካከት አስፍኖ የሐሰት ባሪያ ያደርጋል።

እውነትን መናገር በነፃነት መኖር ነው። ጌታችን ያመኑትን አይሁድ “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” (ዮሐ 8:32) እንዳላቸው እውነት ነፃ ያወጣናል። እውነት (በግእዙ ጽድቅ) ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። አንድም እውነት የእግዚአብሔር ቃል ነው (ዮሐ 17:17)። አንድም እውነት የክርስቶስን ወንጌል በሕይወት መኖር ነው (ዮሐ 8:31)። ይህ እውነት ነፃ የሚያወጣን ከኃጢአት ባርነት ነው (ዮሐ 8:34)። ይህ እውነት ነፃ የሚያወጣን ከርግማንና ከሞት ነው (ሮሜ 6:22 8:1-2)። ጌታችን “እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ (ዮሐ 8:36)” እንዳለው እውነት በጽድቅ እንኖር ዘንድ ነፃ ያወጣናል።

አንደበት የነፍስ ነባቢነት መገለጫ ሲሆን የተፈጠረውም እግዚአብሔርን ለማመስገን፣ እውነትንም ለመመስከር ነው። አንደበት ከዚህ አገልግሎት ውጪ ሲውል ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ “አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በሰውነታችን ክፍሎች መካከል ዐመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፤ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፤ በገሃነምም ይቃጠላል (ያዕ 3:6)” በማለት እንደጻፈልን ጥፋትን ያመጣል። እሳት ራሱ ተቃጥሎ ሌላውንም ያቃጥላል። አንደበትም ካልተገታ እንዲሁ ነው። እንዲሁም “ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው (ያዕ 3:14-15)” በማለት በእውነት ላይ መዋሸት ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከአጋንንት መሆኑን አስተምሮናል።

እውነትን ብቻ መናገር የልባችንንና የአንደበታችንን ንጽሕና የምናረጋግጥበት ነው። እግዚአብሔር በልባችን የምናስበውን ሁሉ ያውቃል፣ በአንደበታችን የምንናገረውንም ሁሉ ይሰማል፣ በግብር የምንፈፅመውንም ሁሉ ይመለከታል። ሰው እውነትንም ሐሰትንም ሲናገር በእግዚአብሔር ፊት ይናገራል፣ ያልሆነውን በሰው ለመታየት ብሎ ሲያስመስልም በእግዚአብሔር ፊት ግብዝነትን ያደርጋል። በልባችን በምናስበው፣ በአንደበታችን በምንናገረውና በግብር በምንፈፅመው መካከል መጣረስ ሲኖር ከእውነተኛነታችን ፈቀቅ ብለናል ማለት ነው። በኅሊናችን የምናስበውን ሰው ማወቅ የሚችለው በምንናገረው ቃል ነው። ከአንደበታችን የሚወጣው ቃል በልባችን መዝገብ ያለው ነገር የሚገለጥበት ነው። ጌታችን ስለዚህ ሲያስተምር “መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል(ሉቃ 6:45)” ብሏል። በአንደበታችን የምናገረው እንደሚያስጠይቀንና እንደሚያስፈርድብን ሲናገርም “እኔ እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህና ከቃልህም የተነሣ ትኰነናለህ (ማቴ 12:37)” ብሏል።

ሐሰትን መናገር መንፈሳዊ፣ ስነልቦናዊና ማኅበራዊ ጉዳቶችን ያስከትላል። ሐሰትን መናገር ልብን፣ ሕሊናንና አንደበትን የሚያጎድፍ፣ ንስሐም የሚያስፈልገው ክፉ ኃጢአት ነው። ሐሰትን የተናገረ ሰው ይጋለጥብኛል ብሎ ይጨነቃል፣ ወንድሙን በመዋሸቱም ለራሱ የሚሰጠው ዋጋና በራስ መተማመኑ ይወርዳል፣ የተናገረውን ውሸት ለመከላከልም ሲል ሌላ የመዋሸት አዙሪት ውስጥ ይገባል። ሐሰትን የተናገረ ሰው ከሰውነት ክብር እየቀለለ፣ ውሸቱም እየተገለጠ ይሄዳል። የተዋሸው ሰው ደግሞ ሐሰቱን እውነት ነው ብሎ በተሳሳተ መንገድ ሄዶ ራሱንና ሌላም ሰው ሊጎዳ ይችላል። ውሸት መሆኑን ሲያውቅ ደግሞ አእምሮው ይጎዳል፣ በወንድሙ የመከዳት ስሜት ይሰማዋል፣ ሌሎች ሰዎች የሚናገሩትን ሁሉ መጠራጠር ይጀምራል።

እውነትን ብቻ መናገር በሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ ያለንን ታማኝነት (Integrity) የምናጸናበት ነው። በልባችን የምናምንበትን ብቻ ስንናገርና ስናደርግ፣ የምንናገረውንና የምናደርገውንም ከልብ ስናምንበት እውነተኝነታችንን እናጸናለን። እውነተኞች ስንሆን በልባችን በምናስበው፣ በግል በምንናገረውና ሰው ባለበት (በአደባባይ ወይም በሚዲያ) በምንናገረው መካከል ልዩነት አይኖርም። በአንጻሩ ሐሰትን መናገር በሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ ያለንን ታማኝነት የሚያሳጣ ነው። ሐሰትን መናገር ሌላ ጊዜ እውነት ብንናገር እንኳን በሰዎች እንዳንታመን የሚያደርግ ክፉ ኃጢአት ነው። ይህንን ያለመታመን ችግር ለመፍታት ነው የመሐላ አስፈላጊነት የሚመጣው። ይህችን እውነትን ብቻ መናገር ላይ የምታተኩረዋን ሕግ በጥልቀት ከማየታችን በፊት ስለመሐላ ጥቂት እንበል።

መሐላ ያስፈለገው የሰዎች ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ስለነበር ነው

መሐላ በብሉይ ኪዳን ቃልን ለማጽናት፣ አመኔታን ለማግኘትና ቃል ኪዳንን ለማረጋገጥ ይውል ነበር። ምክንያቱም ያለ መሐላ ሰዎች የሚናገሯቸው ነገሮች ላይ ያለው እምነት የላላ ስለነበር መሐላ ለእውነትነቱ እንደ ዋስትና/ማረጋገጫ ይውል ነበር። ከዚህ ጀርባ ያለው እውነታ ሰዎች የሚናገሩትን ነገር እውነትነት እንዳለ ለመቀበል ያስቸግር ስለነበር ተጨማሪ ማረጋገጫ ቃል ማስፈለጉ ነው። በአጭር ቃል የሰዎች ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ነበር ማለት ነው። በዘመኑ በእስራኤል ዘንድ በሐሰትም ጭምር መሐላ በዝቶ ስለነበር መሐላ በአጠቃላይ ሳይሆን በሐሰት መማል ተከልክሎ ነበር። ይህም “አትስረቁ፥ አትካዱም፥ ከእናንተም እርስ በርሳችሁ ሐሰት አትነጋገሩ። በስሜም በሐሰት አትማሉ፥ የአምላካችሁንም ስም አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ (ዘሌ 19:12)” በማለት የተቀመጠው ሕገ ኦሪት ነው። እንዲሁም “ሰው ለእግዚአብሔር ስእለት ቢሳል፥ ወይም ራሱ በመሐላ ቢያስር፥ ቃሉን አይስበር፤ ከአፉ እንደ ወጣው ሁሉ ያድርግ (ዘኍ 30:2)” በማለት የታዘዘው መሐላን ስለመጠበቅ ያዛል።

ይህ የመሐላ ጉዳይ “የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ” ከሚለውና “በሐሰት አትመስክር (ሐሰትን አትናገር)” ከሚሉት ሁለት ትዕዛዛት ጋርም የተገናኘ ነበር። ምክንያቱም ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ (በሐሰት መሐላ) እንዳይጠሩ፣ በሐሰትም በስሙ መሐላን እንዳይፈጽሙ የተሠራ ሕግ ነበርና። እነዚህ ሕግጋት የተሠሩት ሰዎች በአምላካቸው ስም መሐላን መፈጸማቸው የእውነተኝነታቸው ማረጋገጫ ዋስትና ተደርጎ እንዲወሰድ ነበር። መሐላ ከሕገ ኦሪት አስቀድሞ የነበረ ሲሆን (ዘፍ 21:23–24) ሕገ ኦሪት የተጻፈ ህግ (“Written law”) ባልነበረበት ዘመን መሐላ በሥርዓት እንዲሆንና በእውነት ብቻ እንዲፈጸም ለማድረግ የተሠራች ናት። ነገር ግን በሐሰትም መሐላን መፈጸም በዕለት ተዕለት የሰዎች ተግባቦት ውስጥ ተስፋፍቶ ነበር። ያለመተማመን (distrust) ከመንሰራፋቱ የተነሳ ሰዎች በእውነትም እንኳን መሐላን ቢፈጽሙ ለመቀበል አስቸጋሪ ነበር። ይህ ምሁራን “ሐሰት የመናገር አስከፊነቱ የተነገረው ሐሰት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ተናጋሪው ከዚያ በኋላ መታመን አለመቻሉ ነው” እንደሚሉት ነው።

ፈሪሳውያን ለመሐላ ደረጃ አውጥተው በወርቅና በመባ መማልን በቤተ መቅደስና በመሰዊያ ከመማል አስበልጠውት ነበር። በዚህም የተነሳ ጌታችን “እናንተ ማንም በቤተ መቅደስ የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በቤተ መቅደስ ወርቅ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል የምትሉ፥ ዕውሮች መሪዎች፥ ወዮላችሁ። እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? ወርቁ ነውን? ወይስ ወርቁን የቀደሰው ቤተ መቅደስ? ደግማችሁም። ማንም በመሠዊያው የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በላዩ ባለው መባ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል ትላላችሁ። እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? መባው ነውን? ወይስ መባውን የሚቀድሰው መሠዊያው? እንግዲህ በመሠዊያው የሚምለው በእርሱና በእርሱ ላይ ባለው ሁሉ ይምላል፤ በቤተ መቅደስም የሚምለው በእርሱና በእርሱ በሚኖረው ይምላል፤ በሰማይም የሚምለው በእግዚአብሔር ዙፋንና በእርሱ ላይ በተቀመጠው ይምላል (ማቴ 23:16-22)” በማለት ገስጿቸዋል።

ጌታችን “ከቶ አትማሉ” ያለ እውነተኛነት መታወቂያችን እንዲሆን ነው።

ጌታችን ይህችን ‘ከቶ አትማሉ’ የምትለዋን ሕገ ወንጌል የሠራው በእርሱ የምናምን ክርስቲያኖች በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የምንናገረው ሁሉ እውነትና እውነት ብቻ እንዲሆን ለማድረግ ነው። ክርስቲያን ሁልጊዜ እውነትን ብቻ የሚናገር ከሆነ መሐላን መጨመር አያስፈልገውም። የሚሰሙትም ሁልጊዜ እውነት እንደሚናገር ያውቃሉና የተናገረውን ሁሉ እውነት ነው ብለው ይቀበሉታል። ከእርሱ የእውነት ቃል ውጭ ሌላ ዋስትና ወይም ማረጋገጫን አይፈልጉም። በክርስቶስ የሚያምን ክርስቲያን መታወቂያው እውነትን መናገር ሊሆን ይገባልና እውነት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ይህችን ሕገ ወንጌል ሠራልን። አዎን እውነተኛ ክርስቲያን የሚናገረው ቃል ራሱን ችሎ በራሱ የሚቆም ስለሆነ ሌላ ደጋፊ አያስፈልገውም። እንደሚዋሽ የሚጠረጠር ሰው ግን ማረጋገጫ ያስፈልገዋል። ጌታችን ያስተማረው ማረጋገጫ የማያሻትን እውነትን እንድንናገር ነው።

ጌታችን “በሰማይ አይሆንም የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም አይሆንም የእግሩ መረገጫ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አይሆንም የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም አትማል፥ አንዲቱን ጠጉር ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና” በማለት ያስተማረው በወቅቱ እስራኤላውያን በአምላካቸው ስም መሐላን ላለመፈጸም (ለመሸሽ) ሲሉ በሰማይ፣ በምድር፣ በኢየሩሳሌምና በራሳቸው ይምሉ ስለነበር እነዚህ ሁሉ የእግዚአብሔር ናቸው፣ በእነዚህ መሐላን መፈጸም በእግዚአብሔር ከመማል አያስመልጥም ሲላቸው ነው። ሰማይም ዙፋኑ፣ ምድርም የእግሩ መረገጫ፣ ኢየሩሳሌምም ዙፋኑ ስለሆነች የራሱ ናቸው። እኛም ራሳችን የራሳችን አይደለንም። ስለዚህ በእነዚህ መማል በእርሱ እንደመማል ይቆጠራልና ነው ይህንን ያለው። ይህ የተከለከለው መሐላ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ያለው ነው እንጂ በፍርድ ቤት (በዳኞች) የሚፈጸመውን ቃለ መሐላ፣ የጤና ባለሙያዎች የሚያደርጉትን ቃለ መሐላ፣ ሙሽሮች የሚፈጽሙትን ቃል ኪዳን የሚመለከት አይደለም። ክርስትና የሚለካው በተግባራዊና ዕለታዊ አኗኗራችን እንጂ አማኝ ለመምሰል የምድር ስርዓትን ሁሉ በመቃወም አይደለም። የምድር ስርዓት የተግባራችን ማሳያ በመሆኑ እኛ ከተለወጥን የፈጠርነውን ስርዓት በማስመሰል ሳይሆን በእውነት መለወጣችን አይቀርም።

እውነተኛነት አዎን የሆነውን አዎን፣ አይደለም የሆነውን አይደለም ማለት ነው።

ጌታችን ያስተማረው አዎን (Yes) የሆነውን አዎን (Yes) እንድንል፣ አይደለም (No) የሆነውን አይደለም (No) እንድንል ነው። ይህም በንግግራችን ፍጹም እውነተኛ መሆንን የሚያጠይቅ ነው። ክርስቲያኖችም በንግግራቸው ሁሉ ብርሃንን ብርሃን፣ ጨለማን ጨለማ፣ ነጩን ነጭ፣ ጥቁሩን ጥቁር በማለት ፍጹም እውነተኛ ሆነው ታማኝነታቸውን ለማረጋገጥ መሐላም ይሁን ሌላ አይነት ዋስትና የማይሹ እንዲሆኑ ነው። ይህም እውነተኛነት ከልብ ንጽሕና የሚመነጭ ነው። ልቡ ንጹሕ የሆነ ቃሉም ሐሰት ያልተቀላቀለበት እውነት ይሆናልና። ከዚህ አንጻርም የጌታችን ሕገ ወንጌል እውነትን መናገር ፀባያችን እንዲሆንና በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ታማኝ እንድንሆን የተሠራች ናት። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ጌታችን ያስተማራትን ሕገ ወንጌል በመልእክቱ ሲያስረዳ “ከሁሉም በፊት፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በሰማይ ቢሆን በምድርም ቢሆን በሌላ መሐላም ቢሆን በምንም አትማሉ፤ ነገር ግን ከፍርድ በታች እንዳትወድቁ ነገራችሁ አዎን ቢሆን አዎን ይሁን፥ አይደለምም ቢሆን አይደለም ይሁን ( ያዕ 5:12)” ብሏል።

ጌታችን ይህችን ፍጽምት ሕገ ወንጌል ፈጽሞ አብነት ሆኖናል። አስቀድሞ በነቢዩ ኢሳይያስ “በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም ነበር (ኢሳ 53:9)” እንደተባለው በእርሱ ሐሰት አልተገኘበትም። እርሱም በወንጌሉ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ (ዮሐ 14:9)” እንዳለው እውነት ሆኖልናል። እርሱ በባህርይው እውነት ስለሆነ ሐሰት በእርሱ ዘንድ የለችም። እርሱ የእውነት ምንጭ ነውና እርሱ የሚናገረውም ሁሉ ከእውነት የሚመነጭ ነውና በትምህርቱም “እውነት እውነት እላችኋለሁ” እያለ እውነት የምትለውን ቃል ሁለት ጊዜ በመድገም አስተምሮናል። ይህንን ያደረገው መለኮታዊና ጥልቅ የሆነውን እውነት ያስተማረው እርሱ ነቢይ ሳይሆን አምላክ ራሱ መሆኑን ለመግለጥም ጭምር ነው። ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም ይህንኑ ሲመሰክር “እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ (1ኛ ጴጥ 2:22)” በማለት በአፉ አንዳች ተንኮል እንዳልተገኘበት ተናግሯል። ከእኛም የሚጠበቀው እርሱን አብነት አድርጎ እውነትን ብቻ መናገር ነው።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ (ኤፌ 4:25)” በማለት እውነትን ብቻ እንድንነጋገር አስተምሮናል። እንዲሁም “እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፥ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና (ቆላ 3:9)” በማለት ውሸትን እንድናስወግድ ጽፎልናል። አስቀድሞም ጠቢቡ ሰሎሞን “ውሸተኛ ከንፈር በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው (ምሳሌ 12:22)” ብሎ ይህንኑ አረጋግጦልናል። አዎን! መዋሸት (ሐሰትን መናገር) የአንደበትን ቅድስና የሚያረክስ ክፉ ኃጢአት ነውና ከፈጸምነው በንስሐ ልንታጠብ፣ ለወደፊትም አንደበቴን ጠብቅልኝ ብለን ልንጸልይ ይገባናል።

ነቢዩ ዘካርያስም “የምትሠሩት ነገር ይህ ነው፤ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤ በበር አደባባያችሁም የእውነትንና የሰላምን ፍርድ ፍረዱ፤ ሁላችሁም በባልንጀራችሁ ላይ ክፉን ነገር በልባችሁ አታስቡ፤ የሐሰትንም መሐላ አትውደዱ፤ ይህን ነገር ሁሉ እጠላለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር። (ዘካ 8:16-17)” በማለት እውነትን እንድንናገር በትንቢቱ አስተምሮናል። ቅዱስ ዮሐንስም በራዕዩ “በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው። ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው። በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም (ራእይ 14:5)” በማለት ጻድቃን በአፋቸው ውሸት እንዳልተገኘባቸው ተናግሯል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንኪያስ እውነቱን ስለ ነገርኋችሁ ጠላት ሆንሁባችሁን? (ገላ 4:16)” በማለት እንደተናገረው እውነትን የሚናገሩ በዓለም ሲኖሩ ይጠላሉ፣ ይሳደዳሉ፣ መከራን ይቀበላሉ። ቅዱሳን ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃንና ሰማዕታት መከራን የተቀበሉት እውነትን ስለሰበኩ ብቻ ነው። እውነትን መያዝ፣ ለእውነት መቆም ሽልማትን የሚያስገኘው በወዲያኛው ዓለም ነው። ስለዚህ ነው ጠቢቡ ሰሎሞን “እውነትን ግዛ አትሽጣትም፥ ጥበብን ተግሣጽን ማስተዋልንም (ምሳ 23:23)” በማለት የሚመክረን። እውነትን መግዛት ማለት እውነትን መያዝ፣ መጠበቅ፣ በእውነትና ለእውነት መኖር ማለት ነው። እውነትን አትሽጣት ማለቱ ደግሞ ለመወደድ፣ ለገንዘብ፣ ለስልጣን ወይም ለሌላ ምድራዊ ጥቅም ብለህ ከእውነት ፈቀቅ አትበል ማለቱ ነው።

እውነቱን እውነት፣ ሐሰቱን ሐሰት ከማለት የወጣ ከክፉው ከዲያብሎስ ነው

ከእውነት የወጣ በንስሐ ካልተመለሰ በቀር ፍርድ ይጠብቀዋል። እባብ ለሔዋን ዕፀ በለስን ብትበሉ ሞትን አትሞቱም በማለት የሰውን ልጅ በመዋሸት አሳሳተ። በዚህም በልቡ እንዲሳብ፣ የሰው ልጅም ራሱን እንዲቀጠቅጠው ተፈረደበት። ቃየን እግዚአብሔር ወንድምህ አቤል ከወዴት አለ ብሎ ሲጠይቀው አላውቅም ብሎ በመዋሸት ኃጢአቱን ለመደበቅ ሞከረ። ተቅበዝባዥም ሆኖ ቀረ። ያዕቆብ ኤሳው ነኝ በማለት አባቱ ያዕቆብን በማታለል በረከትን ወሰደ። ኋላ ግን የያዕቆብ ልጆች ዮሴፍ ሞቷል በማለት ያዕቆብን ዋሽተውን ብዙ ዘመን ሲያዝን ኖረ። ግያዝ ከንዕማን ስጦታን ተቀብሎ ለነቢዩ ኤልሳዕ አልተቀበልኩም ብሎ በመዋሸቱ በለምጽ ተመታ። አክአብና ኤልዛቤል በሐሰት ናቡቴን አስገደሉት፣ በኋላ ግን እግዚአብሔር ቀጣቸው። ቅዱስ ጴጥሮስ አይሁድን ፈርቶ ክርስቶስን አላውቀውም ብሎ ካደ፣ በኋላ ግን ምርር ብሎ አልቅሶ ሊቀ ሐዋርያት ሆነ።

ጌታችን አዎን የሆነውን አዎን አይደለም የሆነውን አይደለም ከማለት የወጣ ከክፉው ነው ያለው ሐሰትን ያስገባ ለዚያም ማረጋገጫ የሚሆን መሐላን የሚሻ ከዲያብሎስ ነው ሲል ነው። እርሱ የሐሰት አባት ነውና። ጌታችን ለአይሁድ “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና (ዮሐ 8:44)” በማለት እንደተናገረው ከጌታችን ሕገ ወንጌል የወጣ ከክፉው (ከዲያብሎስ) ነው። “ዲያቢሎስ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ” የሚለው ቃል ዲያቢሎስ ሥጋን በጦር መሣሪያ ሳይሆን ነፍስን በኃጢአት ከእግዚአብሔር በመለየት የሚገድል መሆኑን የሚያመለክት ነው (ሮሜ 5:12)። ይህም በአዳምና በሔዋን የጀመረው ነው።

አስቀድሞ ሳጥናኤል በእውነት የቆመ መልአክ ነበረ። ነገር ግን በእውነት አልቀጠለም። ጌታችን “እውነት በእርሱ ስለሌለ በእውነት አልቆመም” ማለቱ ዲያቢሎስ ከእውነት የተለየው በራሱ ፈቃል (ውሳኔ) መሆኑን የሚያመለክትና በእውነት (በእግዚአብሔር) ላይ ያመፀ መሆኑን የሚያመለክት ነው። እውነት ማለት ቃል ብቻ ሳይሆን ምግባር፣ መታዘዝና ከእግዚአብሔር ጋር መሆን ነው። እነዚህ ሁሉ ከዲያብሎስ ዘንድ ስለሌሉ እውነት በእርሱ ዘንድ የለም። ስለዚህ እርሱ የቆመው በእውነት ሳይሆን በሐሰት ነው። ሐሰትን ሲናገርም ከራሱ ይናገራል ማለት ራሱ ፈጥሮ (ከወደቀ ባህርይው አፍልቆ) ይናገራል ማለት ነው፣ የቆመለት ዓላማውና ሥራው ነውና። እርሱ ሐሰተኛ ነው የተባለውም አምላክ ሳይሆን አምላካችሁ ነኝ በማለቱና ቀጥሎም ሔዋንን ሞትን አትሞቱም ብሎ ሐሰትን በመናገሩ ነው። የሐሰት አባት የተባለውም ሐሰትን በሰው ልብ ውስጥ ስለሚተክል፣ ሰዎችም ሐሰትን ሲናገሩ በግብር እርሱን ስለሚመስሉት ነው። ዲያብሎስን በግብር መምሰል እጅግ ከባድ ኃጢአት ነውና ከእንደዚህ ዓይነቱ ኃጢአት እንጠበቅ ዘንድ ክቡር ዳዊት “አንደበትህን ከክፉ ከልክል፥ ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ (መዝ 34:13-14)” በማለት ተናግሯል።

ልቡን እያሳተ ራሱን የሚያታልል ሰው አምልኮ ከንቱ ነው

ራስን ማታለልም ከእውነት በተቃራኒ መቆም ነው። ይህም በብዙ መንገድ ይገለጣል። አንደኛው ቃለ እግዚአብሔርን እየሰሙ በተግባር አለመፈፀም፣ ነገር ግን በሰው ፊት የሚፈፅም መስሎ ለመታየት መሞከር ነው። ሐዋርያው ያዕቆብ ስለዚህ “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳልና፥ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል። አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው (ያዕ 1:22-26)” በማለት ቃሉን እያወቁ አለመፈፀም ራስን ማታለል መሆኑን አስተምሯል። ጌታችንም በወንጌሉ “ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል (ማቴ 7:26)” በማለት አስተምሮናል።

ይህ የእግዚአብሔርን ቃል በዐውደ ምሕረት እየሰበኩ እነርሱ የማያደርጉትንም ይመለከታል። ይህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ “በሕግም የእውቀትና የእውነት መልክ ስላለህ፥ የዕውሮች መሪ፥ በጨለማም ላሉ ብርሃን፥ የሰነፎችም አስተማሪ፥ የሕፃናትም መምህር እንደ ሆንህ በራስህ ብትታመን፤ እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ዘርፋለህን? በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን? በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሮሜ 2:20-24)” በማለት እንዳስተማረው ነው።

ሁለተኛው ራስን ማታለል ያልሆኑትን ነኝ ብሎ ማሰብ ነው። ለምሳሌ ሳያውቁ አውቃለሁ፣ ጥበበኛ ሳይሆኑ ጥበበኛ ነኝ ብሎ ማሰብ፣ መናገር፣ መስሎ ለመታየት መሞከር ነው። በተለይም ከተማሩት ይዘት (relevant content) ይልቅ ስለተማሩት የትምህርት ዘርፍ፣ ስለያዙት አካዳሚክ መዓርግ ወይም ስለተማሩበት ትምህርት ቤት ታላቅነት ደጋግመው የሚናገሩ በዚህ ይካተታሉ። የሚናገሩት/የሚጽፉት ማወቃቸውን ለማሳወቅ እንጂ አድማጫቸውን ወይም አንባቢውን ለመጥቀም አይደለም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ አይነቱ ራስን ማታለል ሲናገር “ማንም ራሱን አያታልል፤ ከእናንተ ማንም በዚች ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን (1ኛ ቆሮ 3:18)” ብሏል። እንዲሁም በገላቲያ መልእክቱ “አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና (ገላ 6:3)” በማለት አስተምሯል። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም በራእዩ “ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ…(ራእ 3:17)” በማለት የገለፀው ይህንን አይነቱን ራስን ማታለል ነው። ራስን ማታለል የምንለውም ልቦናችን ማንነታችንን በሚገባ እያወቀው አንደበታችን ከእውነታው በተቃራኒ፣ ድርጊታችንም ያንን ለማስመሰል መሞከሩ ነው።

ሦስተኛው አይነት ራስን ማታለል ኃጢአት የለብኝም ወይም የምሄድበት መንገድ ፍጹም ነው ብሎ ማሰብ፣ ጻድቅ መስሎ ለመታየት መሞክርም (ግብዝነት – Hypocrisy) ነው። ወንጌላዊው ዮሐንስ በመልእክቱ “ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም አናደርግም፤…ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም (1ኛ ዮሐ 1:6-8)” በማለት ያስተማረው ከእንደዚህ አይነቱ ራስን ማታለል እንድንጠበቅ ነው። በኃጢአት እየኖርን ኃጢአት የለብንም ወይም በጽድቅ ነው የምንኖረው ማለት ራስን ማታለል ነው። ጠቢቡ ሰሎሞንም “ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው (ምሳ 14:12)” በማለት የተናገረው በመሰለን ብቻ እየተጓዝን ራሳችንን እንዳናታልል ነው። እውነተኛ ከሆንን ግን ኃጢአታችንን አምነን፣ ንስሐ ገብተን የጽድቅን መንገድ ልንከተል ይገባናል።

አራተኛው ሰዎች በእውነተኛው ዓለማዊ ውድድር ሲወድቁ ምድራዊ ዓላማን ለማሳካት መንፈሳዊውን ዐውድ መጠቀም ነው። እነዚህ ሀሳባቸው ምድራዊ ነው (ፊልጵ 3:19)። ራሳቸው መድረክ ላይ ቆመው የሚናገሩትን በልባቸው አያምኑበትም። ለእነዚህ መንፈሳዊነት ማሳኪያ (means) እንጂ ግብ (end) አይደለም። መንፈሳዊውን ዐውድ የሚፈልጉት ምድራዊ ዓላማቸውን ለማሳካት እንጂ ለጽድቅ አገልግሎት አይደለም። ይህም ትጉህ አገልጋይ መስሎ በመገኘት ብዙ ተከታይ በማፍራት፣ ታዋቂነትን በማግኘት፣ ገንዘብ በመሰብሰብ፣ ትስስርን (Network) በመፍጠር ወዘተ ይጀመራል። ይህ ከደረጀ በኋላ ወደ ቢዝነስ ይቀየራል (ወደ ገንዘብ ይመነዘራል)። ወይም ደግሞ ስልጣን ለመያዝ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን ጥሩ መደላድል ይሆናል። ሀብት ማፍራቱ ወይም ስልጣን መያዙ ባልከፋም ነበር። ነገር ግን እነዚህ ሀብት ካገኙ ወይም ስልጣን ከያዙ በኋላ እውነተኛ ማንነታቸው ይገለጣል። በፊት ሲሰብኩ ወይም ሲጽፉ ከነበሩት መንፈሳዊ ነገር በተቃራኒ ሲፈጽሙ ይገኛሉ። ከእንደዚህ አይነቱ ከንቱነት ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባናል።

በዐውደ ምሕረትና በሚዲያ የሚቀርብ ውዳሴ ከንቱና ሽንገላ ገፅታን አይገነባም።

ውዳሴ ከንቱ ስንል የማይረባ፣ የማይጠቅም፣ የተናቀ፤ ተርታ፣ ከዚህም አልፎ የሚጎዳ፣ በምድራዊ ክብር የሚያስቀር ውዳሴ ማለታችን ነው፡፡ ውዳሴ ከንቱ ባልተሠራ ነገር ወይም በተጋነነ መልኩ ሰዎች እኛን ሲያወድሱን፣ እኛ ሰዎችን ስናወድስ፣ ወይም እኛ ራሳችንን ስናወድስ (ለመወደስ ስንሻ) የሚከሰት ነው። ሽንገላ ማለት ደግሞ ሰው ያልሠራውን ሠራ ብሎ በውሸት ማሞገስ፣ ያልሠሩትን ሠራሁ ወይም የማይችሉትን እችላለሁ ብሎ ማታለል፣ በግብዝነትና በሚያማምሩ ቃላት ጥቅምን ለማግኘት መሞከር ነው። ውዳሴ ከንቱና ሽንገላ በአንዳንዶች ዘንድ የዳቦ ስም ወጥቶላቸው “ገፅታ ግንባታ” ይባላሉ። ይህም ውዳሴ ከንቱ ያለዋጋ የሚያስቀር ሳይሆን ታዋቂነትን የሚያተርፍ፣ ሽንገላም ትርፍ የሚያስገኝ መስሎ እንዲታይ አድርጎታል። ሁለቱም ግን ከእውነት የተለዩ ድርጊቶች ስለሆኑ የኃጢአት እንጂ የጽድቅ ሥራዎች አለመሆናቸውን ማስታወስ ይገባል።

ከንቱ ውዳሴና ሽንገላ የገነነበት ዘመን ቢኖር ይህ ዘመን ነው። በዓለም ያለውን ሽንገላ ብንተወው እንኳን በዐውደ ምሕረት ያለው የከንቱ ውዳሴና ሽንገላ ያስጨንቀናል። በዐውደ ምሕረት ላይ አለቃውን “የልማት አርበኛ”፣ ሰባኪውን “የወንጌል አርበኛ”፣ የቤተ ክርስቲያን የቁርጥ/የስስት ልጅ፣ ዘማሪውን “ታዋቂ ዘማሪ” ወይም “ዳግማዊ ያሬድ” እያሉ መሸንገል የተለመደ ሆኗል። የመዓርግ ስምም በየአደባባዩ ላልተማረ እየታደለ ሊቀ፣ መጋቤ፣ በኩረ፣ ልሳነ፣ መልአከ፣ ሙሓዘ፣ መምህረ፣ አራት አይና ወዘተ የሚባሉ ከትውፊት የተፋቱ የመድረክና የማኅበራዊ ሚዲያ ሰዎች በዝተዋል። እነዚህን በዚህ የመዓርግ ስም መጥራት ሽንገላ መሆኑ ግልፅ ነው። ምክንያቱም ይህንን የሚናገሩ ሰዎች ልባቸው የሚናገሩት እውነት እንዳልሆነ ያውቀዋልና። የሚናገሩትም ለራሳቸው ጥቅም እንጂ ለሚሸነግሉት ሰው አይደለም (ይሁዳ 1:16)። ዐውደ ምሕረት ላይ የቆመ ሰው ሁሉ በዚያ ያሉትን የመዓርግ ስም ያላቸውን ‘አገልጋዮች’ ሁሉ መጥራትም አስልቺ ልማድ ሆኗል። የቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ወንጌል የሚሰበክበት እንጂ የሰዎች መዓርግ አልባ የመዓርግ ስሞች በየጊዜው የሚዘረዘሩበት አይደለም።

ልበ አምላክ የተባለ አባታችን ዳዊት ስለከንቱ ውዳሴና ሽንገላ ሲናገር “እርስ በርሳቸው ከንቱ ነገርን ይናገራሉ፤ በሽንገላ ከንፈር ሁለት ልብ ሆነው ይናገራሉ። የሽንገላን ከንፈሮች ሁሉ እግዚአብሔር ያጠፋቸዋል (መዝ 12:2-3)” ብሏል። እንዲሁም “በአፋቸው እውነት የለምና፥ ልባቸውም ከንቱ ነው፤ ጕሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸው ይሸነግላሉ (መዝ 5:9)” በማለት ስለሚሸነግሉ ሰዎች ማንነት ተናግሯል። ጠቢቡ ሰሎሞንም “ሐሰተኛ ምላስ ያቈሰላቸውን ሰዎች ይጠላል፤ ልዝብ አፍም ጥፋትን ያመጣል (ምሳሌ 26:28)” የሽንገላ መጨረሻው ጥፋት መሆኑን ተናግሯል። እንዲሁም “ወዳጁን በለዘበ ቃል የሚናገር ሰው ለእግሩ መርበብን ይዘረጋል (ምሳሌ 29:5)” በማለት ሽንገላ የጥፋት ወጥመድ መሆኑን ተናግሯል።

ለሁላችን አርአያና ቤዛ ሊሆን ሥጋን የተዋሐደውን ክርስቶስን ከፈሪሳውያን አንዱ “መምህር ሆይ፥ እውነተኛ እንደ ሆንህ በእውነትም የእግዚአብሔርን መንገድ እንድታስተምር እናውቃለን፥ ለማንምም አታደላም፥ የሰውን ፊት አትመለከትምና፤ እንግዲህ ምን ይመስልሃል? ንገረን ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? (ማቴ 22:16 ማር 12:14 ሉቃ 20:21)” በማለት በጠየቀው ጊዜ የልቡን አውቆ ተገቢውን መልስ ሰጥቶታል። ከንቱ ወዳሴንና ሽንገላን ማስወገድ እንደሚገባን ሲያስተምረንም “ከሰው ክብርን አልቀበልም (ዮሐ 5:41)” ብሏል። ወንጌላዊ ዮሐንስም በክርስቶስ አምነው መመስከር የፈሩትን “ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና (ዮሐ 12:43)” በማለት ገልጿቸዋል።

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም “እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፥ በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ (ሮሜ 16:18)” በማለት ሽንገላ የዋሆችን የማታለያ ስልት መሆኑን በግልፅ አስተምሯል። እንዲሁም “እንደምታውቁ፥ እያቈላመጥን ከቶ አልተናገርንም፥ እግዚአብሔርም እንደሚመሰክር እያመካኘን በመጐምጀት አልሠራንም፤ የክርስቶስም ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልንከብድባችሁ ስንችል፥ ከእናንተ ቢሆን ወይም ከሌሎች ክብርን ከሰው አልፈለግንም (1ኛ ተሰ 2:5-6)” በማለት ሐዋርያት በአገልግሎታቸው ማንንም እንዳልሸነገሉ መስክሯል። ክርስቲያኖችም በሽንገላ እንዳይታለሉ “ከዚህ የተነሣ በማይታዘዙት ልጆች ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ይመጣልና ማንም በከንቱ ንግግር አያታልላችሁ (ኤፌ 5:6)” በማለት አስጠንቋል።

በሐሰተኛ ታሪኮችና ትርክቶች መነገድ ለቤተ ክርስቲያን ፈተና ነው

አንዳንድ በዘመናችን የምናያቸው ‘አገልጋዮች’ እዚህ ቦታ እንዲህ አይነት ተአምር ተደረገ፣ እገሌ የሚባል አጥማቂ/ባህታዊ ታላላቅ ተአምራትን ይሠራል፣ እንዲህ ያለ ነገር ከሰማይ ወረደ፣ እንደዚያ ያለ ነገር ከመሬት ተቆፍሮ ተገኘ እና የመሳሰሉትን በማለት ምዕመናን ወደዚያ ስፍራ እንዲጎርፉ ያደርጋሉ። አንዳንዶችም የጥንት ዘመን ታሪክ ነው በማለት በዚህ ቦታ ወይም በዚህ ጊዜ እንደዚህ ተደርጎ ነበር በማለት በቂ መረጃ ማቅረብ የማይቻልበትን ይልቁንም ከሌሎች እውነተኛ ታሪኮች ጋር ለማስታረቅ የሚከብድ ታሪክን ይጽፋሉ፣ ይናገራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች ቤተ ክርስቲያን ከቶ በሌለችበት ጉዳይ ቤተ ክርስቲያን እንደዚህ አይነት በደል ፈጽማ ነበር ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ቤተ ክርስቲያን የማታስተምረውን ታስተምራለች ወይም የምታስተምረውን አታስተምርም እያሉ ውዥንብር ይፈጥራሉ። በሁሉም አቅጣጫ ያሉ በእውነት ላይ ያልተመሠረቱ ታሪኮችና ትርክቶች እንዲሁም አሉባልታዎች ቤተ ክርስቲያንን ይፈትኗታል እንጂ አንዳች አይጠቅሟትም። በተለይም ‘በአገልጋዮች’ የሚነገረው ዓላማው ምንም ይሁን ምን እውነት ካልሆነ የቤተ ክርስቲያንን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባ የሚችል አደገኛ ነገር እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። ምዕመናንንም እንደዚህ አይነት ነገር ሲሰሙ አሜን ብሎ ከመቀበል ይልቅ ቆም ብለው ሊመረምሩ ይገባል።

መዋሸት የቢዝነስ ስልት፣ የኑሮ ብልሃት፣ የስኬት ምስጢር አይደለም።

በሥራ፣ በንግድና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና በዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር በተያያዘ የሚታየው ‘ሐሰት’ ብዙ መልክ ያለው ነው። በሥራ ሰዓት ሳይገኙ እንደተገኙ ሪፖርት ማድረግ፣ ያልተሠራውን ተሠርቷል ብሎ ሪፖርት ማቅረብ፣ በመደበኛ ደመወዝ ልንሠራው ለሚገባን ሥራ መማለጃን መቀበል፣ የሒሳብ ሰነዶችን ማምታታት ወዘተ ይገኙበታል። እንዲሁም ሳይማሩ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ መያዝ፣ ለተለያየ ዓላማ የሐሰት የጋብቻ ምስክር ወረቀት ማሠራት፣ የሐሰት የሥራ ልምድ ወይም የድጋፍ ደብዳቤ ማቅረብ ይገኙበታል። የአቅርቦቶች ዋጋን ያለአግባብ መጨመር፣ ግብር (Tax) ለመቀነስ በማሰብ ገቢን ወይም ትርፍን መቀነስ፣ ወጪን ማብዛት፣ በCash ብቻ መቀበል ወዘት ያካታል። ሳይታመሙ ሐሰተኛ የሐኪም ማስረጃ ማቅረብም ከዚሁ ይመደባል። በማኅበራዊ ሚዲያ የራስ ያልሆነን (ድብቅ) ስም መጠቀም፣ አንድ ተቋም ያልሠራውን ሠራ የሠራውን አልሠራም ብሎ ስም ማጥፋትም ምድቡ ከዚህ ነው። በአጠቃላይ ይህንን ከመሰለው ሐሰት ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባናል። እግዚአብሔርም ሐሰተኛ ወሬን እንዳንቀበል፤ ከሐሰተኞች ጋርም እንዳንተባበር ትዕዛዝን ሰጥቶናል (ዘጸ 23:1)።

ሁሉን አዋቂ የሆነውን እግዚአብሔርን መዋሸት አይቻልም

እግዚአብሔር ሁሉን የሚያውቅ አምላክ ነው። በነቢዩ ኤርምያስ አድሮ “እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኵላሊትንም እፈትናለሁ (ኤር 17:10)” እንዳለው እርሱ ልብና ኩላሊትን መርምሮ ያውቃል። ነገር ግን የሰው ልጆች እግዚአብሔርንም ከመዋሸት አልተመለሱም። ሐናንያና ሳጲራ መንፈስ ቅዱስን ለማታለል በመስማማታቸው የሞት ቅጣትን ተቀብለዋል (ሐዋ 5:1-11)። እግዚአብሔር የማያይ መስሎት የተከለከለውን ወስዶ በመሬት ቀብሮ የደበቀው አካንም መጨረሻው በድንጋይ ተወግሮ መሞት ነበር (ኢያሱ 7:13-25)። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም (ገላ 6:7)” በማለት እግዚአብሔር የማይመለከት እየመሰለን እንዳንስት አስጠንቅቋል። እግዚአብሔር አስቀድሞ በነቢዩ ሚልክያስ “እኔ ታላቅ ንጉሥ ነኝና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ ስሜም በአሕዛብ ዘንድ የተፈራ ነውና በመንጋው ውስጥ ተባት እያለው ለጌታ ተስሎ ነውረኛውን የሚሠዋ ሸንጋይ ሰው ርጉም ይሁን (ሚል 1:14)” በማለት ተናግሯል። በልብ እግዚአብሔር የማይወደውን እያሰቡ በአንደበት እግዚአብሔርን ማክበርም እንዲሁ እግዚአብሔርን መዋሸት ነው። ጌታችንም በወንጌሉ “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ ምሳሌ 15:7-8 ማር 7:6” በማለት የተናገረው ልብና አንደበት ተራርቀው ቢያገኛቸው ነው።

ሐሰትን በመሐላ ወይም በሌላ ሐሰት ለማጽናት አትድከም

ሐሰትን ከሕሊናህ ልትሸፍነው አትችልም። ሐሰትነቱን ሕሊናህ ያውቀዋልና። ከእግዚአብሔርም ልትሸሽገው አትችልም። ከእርሱ የሚሰወር ነገር የለምና። ጌታችን ስለዚህ “የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፥ የማይታወቅም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተሸሸገ የለም (ሉቃ 8:17)” ብሏል። ምናልባት ሐሰትን በመሐላ ልትከላከለው ወይም በሌላ ሐሰት ልትሸፍነው የምትችለው ከተወሰኑ ሰዎች ሊሆን ይችላል። እርሱም ለጊዜው ነው እንጂ ጊዜው ሲደርስ እውነቱ መውጣቱ አይቀርም። ሰው እንኳን መዋሸትህን ባያውቀው አንተው ራስህ ሌላ ጊዜ መዋሸትህን ረስተኸው እውነቱን ትናገረዋለህ። ጠቢቡ ሰሎሞን “የእውነት ከንፈር ለዘላለም ትቆማለች፤ ውሸተኛ ምላስ ግን ለቅጽበት ነው (ምሳ 12:19)” ያለው ሐሰት ልትጸና የማትችል ስለሆነች ነው። ስለዚህ ሐሰትን መሸፈን አይቻልህምና በኃጢአት ላይ ኃጢአትን ከመጨመር ተፀፅተህ መዋሸትህን አምነህ ይቅርታ ጠይቀህ እውነቱን ተናገር እንጂ በመሓላ ወይም በሌላ ሐሰት ለመሸፈን አትድከም።

እውነተኛነት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው

ለክርስቲያን እውነትን መናገር አማራጭ ሳይሆን መሠረታዊና ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው። የእውነተኛነት ሕይወት የአልጋ በአልጋ ጉዞ ሳይሆን ዋጋን የሚያስከፍል ነው። ሲመቸን የምንይዘው ፈተና ሲበዛ የምንተወው እውነተኛነት የለም። እውነትን እያወቁ አለመመስከርም ከሐሰተኝነት የሚቆጠር ነው። ክርስቶስ እውነት ስለሆነ ክርስትናም በዚህ እውነት ላይ የተመሠረተች ናት። እውነት የሆነው የክርስቶስ ልጆች ከሆንን እንደ እርሱ እውነተኞች ልንሆን ይገባናል። ከእርሱ ጋርም ኅብረት የሚኖረን እውነተኞች ስንሆን ብቻ ነው። እውነትን መናገር በብርሃን መመላለስ ነው። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ “ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል (1ኛ ዮሐ 1:7)” እንዳለው እውነትን ስንይዝ በብርሃን እንመላለሳለን። ሐሰትን የሚናገር ግን እርሱ በጨለማ የሚመላለስ የሐሰት አባት ከሆነው ከዲያብሎስ ነው።

የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው (ራእ 21:8)። ስለዚህ እውነትን መናገር የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችን የሚረጋገጥበትና ከሐሰት አባት ከዲያብሎስ የምንለይበት ታላቅ ስነምግባር መሆኑን ልንረዳና ልንተገብረው ይገባል። ስሙን ለማወደስ ክብሩንም ለመውረስ የተፈጠርን ሁሉ አንደበታችን ዋነኛ አገልግሎቱ እውነት የሆነውን እግዚአብሔርን ለማመስገን፣ እውነተኛ ቃሉንም በሰው ፊት ለመመስከር ነው። ለእነዚህ ዓላማዎች የተፈጠረውን አንደበታችንን ሐሰትን ለመናገር መዋል የለበትም። በአንደበታችን ሐሰት ከተናገርን ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔርን ቃል ብንናገርስ እንዴት ልንታመን እንችላለን?

እውነተኛነት የሰላም መሠረት ናት። እውነተኛ ስንሆን የውስጥ (የሕሊና) ሰላም እናገኛለን። ሐሰትን ከተናገርን ግን በተናገርኩት ምን ይመጣብኝ ይሆን ወይም ይታወቅብኝ ይሆንን እያልን የሕሊና ሰላም እናጣለን። እውነተኛ ስንሆን ከሌሎች ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ጋር ሰላም ይኖረናል፣ ከሰው ሁሉ ጋርም በሰላም እንኖራለን። “ዋሽቶ ማስታረቅ” የሚል ብሂል ለክርስቲያን አይስማማም። ክርስቲያን እውነትን ተናግሮ እንጂ ዋሽቶ አያስታርቅም። ምክንያቱም ውሸት ያጣላል እንጂ ሰላምን አያረጋግጥም። ሐሰትን ስንናገር ግን ከእውነተኞች ወይም ሌላ አይነት ሐሰት ከያዙት ጋር እንጋጫለን። እውነተኛ ስንሆን ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም ይኖረናል። የእውነት አምላክ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ይሆናል። የእርሱ ከእኛ ጋር ከመሆን በላይ ለሕይወታችን የሚያስፈልገን ነገር የለም። ስለዚህ ሐሰትን በሕሊናችን አንፍጠር፣ በአንደበታችንም አንናገር፣ በመሐላ ለማጽናትም አንድከም። ይቆየን።

Leave a comment