የነገዋን ቤተክርስቲያን ተረካቢዎች የሚሆኑ ልጆችን በቤተክርስቲያንና በቤተሰብ ደረጃ መንፈሳዊ ትምህርትን እያስተማሩ ማሳደግ የቤተክርስቲያን፣ የመምህራንና የወላጆች ኃላፊነት ነው። ይህንንም ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ልጆች መንፈሳዊ ትምህርትን የሚማሩበትን ስልትና ዘዴ ማወቅና በሚገባ መተግበር ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው። በሥርዓተ ትምህርትም ይሁን ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ለልጆች የሚሰጠው መንፈሳዊ ትምህርት ውጤታማ የሆኑ የማስተማሪያ ስልቶችን ሊጠቀም ይገባል። ከዚህም አንጻር ብዙዎች “ውጤታማ ሊያደርጉን የሚችሉ የማስተማሪያ ዘዴዎች የትኞቹ ናቸው?” ወይም “ልጆች መንፈሳዊ ትምህርትን እንዴት ብናስተምራቸው ነው ውጤታማ የምንሆነው?” ሲሉ ይጠይቃሉ። እኛም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት ለማስተማር የሚረዱ ስልቶችን እና ዘዴዎችን እንዳስሳለን።
የተማሪዎች፣ የትምህርቱና የጊዜው አከፋፈል
መንፈሳዊ ትምህርት ለማስተማር ልጆችን በዕድሜያቸው መክፈል ያስፈልጋል። ይህም ከ 5 ዓመት በታች፣ ከ 5-9 ዓመት፣ ከ 10-12 ዓመትና ከ 13-15 ዓመት በመክፈል ሊሆን ይችላል። ብዙ ተማሪዎችና በቂ መምህራን ካሉ ግን በዘመናዊው ትምህርት የክፍል ደረጃቸው (በዓመት) ተለይተው ቢማሩ ይመረጣል። የትምህርት ዘመኑን ደግሞ በክፍለ ወራት (term) (እንደየሁኔታው በሢሦ ወይም በግማሽ ዓመትም ሊሆን ይችላል) ከፍሎ ማስተማር ይገባል። የትምህርቱንም ይዘት እንዲሁ በትምህርት ዓይነት (courses) ከፍሎ ትይይዝና ተከታታይነት ባለው መልኩ ማዋቀር ያስፈልጋል። በዚህ መሠረት የተዘጋጀ ሥርዓተ ትምህርት ካለ እርሱን ከነባራዊው ሁኔታ ጋር አጣጥሞ መጠቀም የተሻለ ነው። ነገር ግን እንዲህ አይነቱ ሥርዓተ ትምህርት ብዙዎችን ባሳተፈ መልኩ የተዘጋጀና በባለሙያዎች አስተያየት የዳበረ መሆን ይኖርበታል። በግለሰቦች የተዘጋጁ አንዳንድ ሥርዓተ ትምህርቶች ብዙ ውስንነት ስለሚኖርባቸው በዝግጅቱ ብዙ ባላሙያዎች የተሳተፋበትን ሥርዓተ ትምህርት መጠቀሙ ይመከራል።
የማስተማሪያ ዘዴዎች
ልጆችን የማስተማሪያ ዘዴዎች ብዙና የተለያዪ ሲሆኑ በልጆች ትኩረት ላይ በመመስረት በሰባት መደባት ይከፈላሉ። መምህራንና ወላጆች አስቀድመው የልጆችን ትኩረት የሚስበውን የማስተማሪያ ዘዴ ማወቅ ይገባቸዋል። መምህራኑ የልጆቹን ዝንባሌና ፍላጎት እያዩ እነዚህን ዘዴዎች በማቀያየርና በማሰባጠር ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ። ሁሉንም ዘዴዎች ተንትኖ ማቅረብ ስለማይቻል ጎልተው የሚታዪትና ብዙ ጊዜ የምንጠቀምባቸው ዘዴዎች እንደሚከተለው በሰባቱ ምድቦች ቀርበዋል።
በማድመጥ ላይ ለሚያተኩሩ: Auditory
በዚህ ምድብ የሚገኙት የማስተማሪያ ዘዴዎች የልጆችን የመስማት/የማዳመጥ ክህሎት የሚጠቀሙ ናቸው። ለአብነት ከሚጠቀሱት ዘዴዎች መካካልም በመተረክ/በትረካ (Stories) መልክ የሚቀርቡ ትምህርቶች የአብዛኛቹን ልጆች ቀልብ ይስባሉ። ነገር ግን ለአዋቂዎች የሚቀርብ አይነት የስብከት ዘዴን የሚጠቀም ከሆነ ትረካውን ቢሆን ዋጋው አነስተኛ ነው። በተጨማሪም በትረካ ዘዴም ቢሆን ሁል ጊዜ አንድ መምህር ብቻ የሚያስተምር ከሆነ የብዙዎች ፍላጎት ይቀንሳል። መምህሩም ይሰለቻል።
ሌላው በዚህ ምድብ የሚጠቀሰው ዘዴ በመዝሙር/በዝማሬ (spiritual Songs) ማስተማር ነው። ልጆች በመዝሙር መልክ የሰሙትን በፍጥነት ይይዙታል። ነገር ግን ንባቡንና ዜማውን ብቻ ሳይሆን ትርጉምንና ምስጢሩንም አብሮ ማስጠናት ይገባል። በሌላ በኩል የልጆች መዝሙር ማጥናትና ማቅረብ ለትምህርትና ለምስጋና እንጂ ልጆችን በየጊዜው መድረክ ላይ እያዘመሩ “ልጆች እያስተማርን ነውና እዩልን!” ለሚመስል ከንቱ ተወዳጅነትን ፍለጋ መዋል የለበትም።
በማንብብና በመጻፍ ላይ ለሚያተኮሩ: Linguistic
ልጆች የተነገሩትን በመጻፍና የተጻፈውንም በማንበብ መንፈሳዊ ትምህርትን ሊማሩ ይችላሉ። መጻፍና ማንበብን (Writing/reading) ማስተማር ብቻውን ግን መንፈሳዊ ትምህርት አይደለም። ማንበብና መጻፍ በጽሑፍ ያለውን ለማወቅ፣ ዕውቀትንም በጽሑፍ ጽፎ ለማስተማር ጠቀሜታው ታላቅ ስለሆነ ልጆች በትምህርት ሰዓትና በቤት ሥራ መልኩ እየጻፉና እያነበቡ መንፈሳዊ ትምህርትን እንዲማሩ ማድረግ ይገባል። በተጨማሪም ልጆች በልጅነታቸው ቅዱሳን መጻሕፍትን (የጸሎት መጻሕፍትን ጨምሮ) እያነበቡ እንዲማሩ ማድረግ ይገባል። ማንበብና መጻፍ ብዙም ፍላጎት ለሌላቸው ልጆች ግን ሌሎች ዘዴዎችን መጠቀሙ ይመረጣል።
በመመልከት ላይ ለሚያተኮሩ: Visual
ማየትንና መመልከትን ከሚጠቀሙ ዘዴዎች መካከል ስዕል (Paintings/pictures) በቅድሚያ ይጠቀሳል። በጽሑፍ ከሠፈረ ብዙ ሐተታ ይልቅ አንድ ስዕል የበለጠ ያስተምራል። በቤተክርስቲያን ያሉትን ቅዱሳን ስዕላትን በተለየ መልክ በማዘጋጆት ልጆችን በስዕል ማስተማር ይቻላል። በተጨማሪም ንዋየ ቅድሳትንና መንፈሳዊ የዜማ መሣሪያዎችን በማሳየት ስለአገልግሎታቸውና ስለምስጢራቸው ለልጆች በቀላሉ ማስተማር ይቻላል። ሁለተኛው በማየት ላይ የሚያተኩረው የማስተማሪያ ዘዴ በምስል (visuals) ማስተማር ነው። ይህም የልጆችን የአሻንጉሊት ፊልሞችን ይጨምራል። ይህንን ልጆች ይወዱታል። ሆኖም ግን ሱስ እንዳይሆንባቸው አልፎ አልፎ ብቻ መጠቀም ይገባል። በሌላ በኩል በቴሌቪዥን ወይም በኮምፒርተር /በመቀመሪያ/ ላይ ብቻ የሚያተኩር ትምህርት በቀጣይ የመማር ፍላጎትን ይገድላል። የልጆችንም አዕምሮ ዕድገት ይቀንሳል። ሌላው ልጆች በማየት የሚማሩበት መንፈሳዊ አገልግሎት (ቅዳሴ፣ ጥምቀት፣ ተክሊል፣ ወዘተ) ሲከናወን በማየት ነው። በልጅነታቸው ያዩት መልካም ነገርም በውስጣቸው ተቀርጾ ያድጋሉ።
በማስላት/በስሌት ላይ ለሚያተኮሩ: Logical
በእንቆቅልሽ (Puzzles) ማስተማር በዚህ መደብ ይጠቀሳል። የስሌት ዝንባሌ ላላቸው ልጆች የስሌት ሰንጠረዥና ሌሎች የአእምሮ ሥራን የሚጠይቁ የማስተማሪያ ዘዴዎችን በማዘጋጀት ማስተማር ያስፈልጋል። ስሌትን የሚሹ የቤተክርስቲያን ትምህርቶች (ለምሳሌ ባሕረ ሃሳብ) ለወጣቶች በሰንጠረዥ መልክ አዘጋጅቶ ማስተማር ይቻላል። እንዲሁም የቅዱሳንን ስም ከገድላቸው ጋር በማዛመድ፣ የቤተክርስቲያንን አሠራር በፕላስቲክ ጡቦች በመገንባት፣ ዋና ዋና የቤተክርስቲያን ታሪኮችን ከተፈጸሙበት ዘመን ጋር በማቀናጀት እንቆቅልሾችን አዘጋጅቶ ማስተማር ይገባል።
በመሥራት/በድርጊት ላይ ለሚያተኮሩ: Physical
በተሳትፎ/በመስራት (Activities) ልጆችን ማስተማር ውጤታማነቱ ከፍተኛ ነው። ስለጸሎት ለማስተማር እንዲጸልዩ በማድረግ፣ ስለ ምጽዋት ለማስተማር እንዲሰጡ በማድረግ፣ ቅዳሴ አብረው እንዲያስቀድሱ በማድረግ፣ በልጆች ጽዋ ማኅበራት እንዲሳተፉ በማድረግ በመሳተፍ የሚማሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል። በመጽሐፍ ቅዱስ የተመዘገቡ ክንዋኔዎችንም አስመስለው እንዲሠሩ በማድረግ በድርጊት ማስተማር ይገባል። በተጨማሪም በልምምድ/ሠርቶ በማሳየት/ እንደ መስቀል፣ ጸናጽል፣ ከበሮ፣ መቆምያ እና የመሳሰሉትን ከቀላል ነገሮች እየሠሩ (Demonstration) እንዲማሩ ማድረግ ይገባል።
በማኅበራዊ ተግባቦት ላይ ለሚያተኮሩ: Social
ይህ ዘዴ መንፈሳዊ ዕውቀትን ከማስተማሩ ባሻገር ልጆች የማኅበራዊ ተግባቦት ክህሎትን እንዲያዳብሩ ያግዛል። ልጆች መርኃግብር ተዘጋጅቶላቸው ቅዱሳን መካናትን እንዱጎበኙ ማድረግ (Excursion) ልጆችን ብዙ ቁምነገር ያስተምራቸዋል። ወጣቶች ትኩረትን በሚስቡ አርዕስት ላይ ውይይት (Discussion) እንዲያደርጉ የውይይት መርኃግብር ማዘጋጀትም እርስ በእርሳቸው እንዲማማሩ ይረዳል። ከዚህ በተጨማሪ በውድድርና (Competitions) በጭውውት/ድራማ (role playing) መልክም መንፈሳዊ ይዘት ያለውን ትምህርት ለልጆች ማስተማር ያስፈልጋል።
በራስ/በግል ጥረት ላይ ለሚያተኮሩ: Solitary
አንዳንድ ልጆች በራሳቸው ጥረት መማር (self-study) ያስደስታቸዋል። እንደነዚህ ዓይነት ልጆች ብቻቸውን ሆነው ማንበብ፣ መጻፍ፣ ማሰብ፣ አዲስ ነገርን መፈለግ ስለሚወዱ የማስተማሪያ ስልቱም እንዲሁ ይህንን የሚያበረታታ ሊሆን ይገባዋል። ስለ አንድ ቅዱስ እንዲያጠኑና እንዲጽፉ ማድረግ፣ ስለ አንድ የቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረቱን እንዲፈልጉና እንዲያቀርቡ ማድረግ፣ አንድ መንፈሳዊ ክንዋኔ እንዲተነትኑ ማድረግ፣ ለዚህም የሚሆን በቂ መረጃ መስጠት ለነዚህ ልጆች ጥሩ ማስተማሪያ ዘዴ ነው።
የማስተማሪያ ዘዴዎች አመራረጥ
የማስተማሪያ ስልቶች አመራረጥ በትምህርቱ ይዘት፣ በመምህራን ዝንባሌ/ክህሎት፣ በልጆች ፍላጎትና በመማሪያ ቁሳቁስ አቅርቦት ላይ የተመሠረተ ይሆናል። ለሁሉም ልጆች አንድ አይነት ስልት መጠቀም ውጤታማ አያደርግም። ሁል ጊዜም ተመሳሳይ የማስተማሪያ ዘዴን መጠቀምም እንዲሁ ለልጆች አስልቺ ይሆናል። መምህራን እንደ ተማሪዎቻቸው የዕውቀትና የእድሜ ደረጃ እንዲሁም እንደሚሰጠው የትምህርት አይነት ልዩ ልዩ ዘዴዎችን መጠቀም ይኖርባቸዋል። በሁሉም ጊዜና ቦታ ወይም ለሁሉም ትምህርት ፍቱን የሆነ አንድ ወጥ የማስተማሪያ ዘዴ የለም። ይልቁንም የመምህራን የፈጠራ ችሎታ ወሳኝነት አለው።
እያንዳንዱ ልጅ ልዩ የሆነ የመማሪያ ዘዴ ሊስማማው ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ግን ሁሉንም ወይም አብዛኛውን የስሜት ሕዋሳት የሚያካትት ትምህርት ውጤታማ ይሆናል፡፡ ከ3 እስከ 6 ዓመት ያሉት ሕፃናት ብዙ በሚታይና በሚዳሰስ ነገር ይመሰጣሉ። ከ7 ዓመት በላይ ያሉ ደግሞ በረቀቁ ጉዳዮች ላይም ንቁዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ እንደ ዕድሜያቸው የተለያዩ ዘዴዎችን እየቀያየሩ ማስተማር ተማሪዎችን ይስባል፡፡ አሳታፊ የማስተማሪ ዘዴዎች መምህር ተኮር ከሆኑ ዘዴዎች ይልቅ ውጤታማ ናቸው፡፡ ይሁንና ጥቂት ልጆችን ብቻ ማሳተፉ ግን ሌሎች እንደተገለሉ ወይም በዕውቀት ያነሱ እንደሆኑ ይሰማቸውና ትምህርቱን እንዲጠሉት ያደርጋል::
በዝቅተኛ፣ በመካከለኛና በከፍተኛ የዕውቀት ወይም የቋንቋ ደረጃዎች ያሉትን ልጆች ለይቶ ማወቅና ተገቢውን ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል:: ተማሪዎች ብዙ እንዲያውቁ ካለ ጉጉት የተነሳ ጫና የሚፈጥሩ መምህራን በተማሪዎቻቸው ብዙም አይወደዱም። በተለይ በምዕራቡ ዓለም ይህ ጉዳይ አይወደድም። ከዚያ ይልቅ ነገሮችን እያዋዙ ተማሪዎች ለትምህርታቸው ፍላጎት እንዲጨምሩ የሚያደርጉ መምህራን ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ያለበቂ ድጋፍና ክትትል ተማሪዎችን በነጻነት ስም መልቀቁ ትርጉም የለውም:: በአጠቃላይ ግን ከወላጆችና ከተማሪዎች ጋር የመማር ማስተማር ሂደቱን በተመለከተ ቀጣይነት ያለው ምክክር ማካሄዱ አዋጭ የሆኑ ዘዴዎችን ለማግኘትና ለመምረጥ ያግዛል::
የትምህርት አቀራረብ ስልቶች
የተለመደው የትምህርት አቀራረብ ልጆችና መምህራን በአካል (ፊት ለፊት) (face-to-face) ተገናኝተው የሚማማሩበት ሁኔታ ነው። ይህ አቀራረብ ተመራጭ ቢሆንም በመምህራኑና በወላጆች የጊዜ ገደብ የተወሰነ ነው። ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት በተለይ የኢንተርኔት አገልግሎት ባስተማማኝ ሁኔታ ባለበት በውጭው ዓለም ትምህርቱን በቀጥታ በማስተላለፍ (virtual) ልጆቹም መምህራንም ከቤታቸው ሆነው ትምህርቱን ማካሄድ ይቻላል። ወላጆችም ልጆቻቸው የሚማሩትን መከታተል ይችላሉ። ሦስተኛው የትምህርት አቀራረብ ደግሞ ተቀርጾ በተቀመጠ (recorded) መንገድ ነው። ይህም በኤሌክትሮኒክስ መሣርያዎች ወይም በድረ ገጽ ላይ ሊቀመጥ ይችላል። ልጆች አመቺ ጊዜ በሚኖራቸው ሰዓት ከፍተው ሊማሩበት ይችላሉ። ይህ ግን የወላጆችን ንቁና ቀጣይነት ያለው ክትትል ይጠይቃል።
ማበረታቻ/ሽልማት
ለልጆች ማበረታቻ መስጠት የመማር ማስተማር ሂደቱን እንደሚያጎለብተው አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን አሰጣጡና የስጦታው አይነት ወሳኝነት አለው፡፡ ስጦታ/ሽልማት የሚሰጠው ልዩ ችሎታ ወይም ጥረት ወይም ውጤት ወደፊት በቀጣይነት እንዲደረግ ለማበረታቻ ነው እንጅ ስለተደረገው ለማመስገን ብቻ አይደለም፡፡ ስጦታ ከቃል ምስጋና እስከ ቁሳቁስ ወይም ገንዘብ ሽልማት ሊለያይ ይችላል፡፡ ይህም እንደ ተሸላሚው ፍላጎትና ዕድሜ ይለያያል፡፡ ያም ሆኖ ስጦታው ላቅ ያለና ለምን እንደተሰጠ ለተቀባዩም ለተመልካቹም መገለጽ አለበት፡፡ የሚደረገው ስጦታም ፍጹም እኩልነትንና ፍትህን ያገናዘበ መሆን ይኖርበታል፡፡ አንድን ልጅ ዛሬ ላደረገው አመስግኖ ነገ ተመሳሳይ ለሠራ ልጅ ምስጋናን መንፈግ አያስፈልግም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሽልማት ላቅ ላሉ ሥራዎች እንጅ በሆነ ባልሆነው ነገር ሁሉ መሰጠት የለበትም:: የአሰጣጡም ሁኔታ እንደየ ሽልማቱ ይለያያል። ሽልማቱ ትልቅ ከሆነ ካህን ወይም ዲያቆን ወይም ሌላ ተሰሚነት ያለው ሰው ቢሰጥ ይመረጣል፡፡ ሽልማት እንደየሁኔታው በቡድንም ሆነ በተናጥል ሊሰጥ ይችላል፡፡ ሽልማቱ በተሸላሚው ወዲያው ሥራ ላይ ሊውል የሚችል ቢሆን የሚኖረው ዋጋ ይጨምራል፡፡ ገና ላልተከናወነ ሥራም ሽልማት ሊዘጋጅ ይችላል፡፡ ይህም ልጆች ለሽልማቱ ሲሉ ይበልጥ ጥረት እንዲያደርጉ ሊያግዛቸው ይችላል:: ሽልማቱ በመምህራን በቤተ ክርስቲያን እና ወይም በወላጆች ሊዘጋጅ ይችላል፡፡ ተሸላሚውን መምረጥ ግን የመምህራን ሥራ ነው፡፡
ክትትልና ምዘና
መንፈሳዊ ትምህርት ይዘቱ መንፈሳዊ ቢሆንም ክትትልና ምዘና ያስፈልገዋል፡፡ ከዚህም አንጻር በተለያዩ ደረጃዎች የሚማሩ ልጆች የትምህርት አቀባበላቸው ቀጣይነት ባለው መልኩ መመዘን አለባት፡፡ የምዘናው ዋና ዓላማም የተሻለ ትምህርት አሰጣጥ እንዲኖር የሚያግዝ መረጃ ለመሰብሰብ ነው፡፡ በተጨማሪም በከፍተኛ በመካከለኛና በዝቅተኛ የዕውቀት ደረጃዎች የሚገኙትን ልጆች ለይቶ ይበልጥ በሚስማማቸው መልኩ ትምህርትና ድጋፍ ለማድረግ ነው፡፡ በትምህርቱ መጨረሻ ላይ ከሚደረግ ምዘና ይልቅ በየደረጃው የሚደረግ ምዘና የላቀ ዋጋ አለው። ይህ ዓይነቱ ምዘና ለመሻሻል እድል ይሰጣል፡፡ ምዘና ከመደረጉ አስቀድሞ የምዘናውን አይነት፣ ዓላማና ብዛት እንዲሁም የሚደረግበትን ጊዜ ለተማሪዎችና ለወላጆች (ኮርሶች ከመጀመራቸው በፊት) መነገር አለበት::
ምዘናዎች ሙሉ በሙሉ ሽምደዳን/ማስታወስን የሚያበረታቱ ብቻ መሆን የለባቸውም:: ለምዘናዎች በቂ ጊዜና ዝግጅት መሰጠትም አለበት፡፡ እንዲሁም በምዘና ወቅት ምቹ የክፍል ሁኔታዎችም መኖር አለባቸው፡፡ ከምዘና ጋር በተያያዘ ዋናው መታወቅ ያለበት ነገር የሚሰጠው ትምህርት የሚደረገውን ምዘና ይመራል እንጅ ምዘናው ትምህርት አሰጣጡን አይመራም፡፡ በሌላ በኩል በምዘናው ዝቅተኛ ውጤት የሚያመጡ ልጆች ካሉ የበታችነት እንዳይሰማቸውና ጓደኞቻቸው እንዳያጣጥሏቸው ምዘናው ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል፡፡ በስተመጨረሻም የምዘና ውጤቶች በተደራጀና ምሥጢራዊ በሆነ መልኩ በመረጃ ቋት በቋሚነት መያዝ አለባቸው፡፡
የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት በቀጣይነትና በተከታታይነት የሚከናወን የቤተክርስቲያን አገልግሎት ስለሆነ ክትትልና ምዘናውም እንዲሁ በቀጣይነት የሚከናወን መሆን ይኖርበታል። ራሱን የቻለ ዕቅድና ግብ/ዓላማ ተቀምጦለት አፈጻጸምን (performance)፣ ጥራትን (quality)፣ የአጭር ጊዜ ውጤትን (outputs)፣ የመካከለኛ ጊዜ ለውጥንና (outcome) የረጅም ጊዜ ተጽዕኖን (impact) የሚመዝንና መረጃውንም ሥራ ላይ የሚያውል መሆን ይጠበቅበታል።
በጣም ጥሩ ፅሁፍ ነው። እኔ በምኖርበት አሜሪካን ሀገር ዋነኛ የወላጆች ችግር ኦርቶዶክሳዊ የሆነ ለልጆች የተዘጋጀ የአማርኛና እንግሊዝኛ የመፅሀፍ ቅዱስ ታሪኮች መፅሀፍት አለመኖር ነው። በመሆኑም ብዙ ወላጆች በሌላ ፀሀፍት የተዘጋጁ መፅሀፍትን ለመጠቀም ይገደዳሉ።
LikeLike