መግቢያ
በቤተ ክርስቲያን የረጅም ዘመን ታሪክ ሚዲያ ወሳኝ ሚና ነበረው። በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ጥንታውያን ሀገራት ፣ አብያተ ክርስቲያናት ለሚዲያ የሚያስፈልጉ የጽሁፍ ፊደላትን ከመቅረፅ ጀምሮ የነበራቸው ጉልህ ሚና የታወቀ ነው። በዘመናችንም የዘመኑን የቴክኖሎጂ ዕድገት የሚጠቀሙ ጠንካራ ሚዲያዎች መበራከት ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ጥንካሬ እጅግ አስፈላጊ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጥቅም ላይ የዋለው ማኅበራዊ ሚዲያም የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ከማስፋፋት አንፃር ታላቅ ድርሻ አለው። ትምህርተ ወንጌልን በተለያዩ መንገዶች (በጽሑፍ፣ በድምጽ፣ በስዕል፣ በድምጽ ወምስል) እና ቋንቋዎች በማሰራጨት ያላመኑት እንዲያምኑ፣ ያመኑት እንዲጸኑ፣ የተሳሳቱት እውነቱን ተረድተው እንዲመለሱ ለማድረግ ሚዲያ ወሳኝ ሚና መጫወት ይችላል።
ይሁንና ማኅበራዊ ሚዲያዎቻችን በመንፈሳዊ አስተምህሮ ውስጥ ያላቸው አስተዋጽኦ ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አንጻር በየጊዜው መፈተሽና መልካም የሆነው እንዲቀጥል መበረታታት፣ የሚስተካከለው ደግሞ በጊዜ መስተካከል ያስፈልገዋል። ከዓመታት በፊት መንፈሳዊ አገልግሎትና የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በሚል ጽሑፍ ማቅረባችን ይታወሳል። በዚህች የአስተምህሮ ጽሑፍ እኛ እንደ ተከታታይና ታዛቢ ሆነን ያስተዋልናቸውን የማኅበራዊ ሚዲያዎችን በተግባር የተገለጡ እውነተኛ ገፅታዎች እንዳስሳለን። በእኛ ምልከታ መሠረትም የሚታዩባቸውን ጉልህ ድክመቶችና ሊጠናከሩ ይገባል የምንላቸውን መልካም ጅምሮችንም እናሳያለን። ከመንፈሳዊ አገልግሎት አንጻርም የሚዲያዎች አደረጃጀት፣ ዓላማና፣ አሠራር ምን ቢሆን የተሻለ እንደሚሆን የሚጠቁሙ ሀሳቦችንም እናቀርባለን።
የሚዲያዎች አደረጃጀት
አንድ በዘመናችን ያሉ ‘መንፈሳዊ’ ሚዲያዎችን የሚዳስስ ሰው የአደረጃጀት፣ የዓላማ፣ እና የትኩረት አቅጣጫቸው የሚለያይ ብዙ ‘መንፈሳዊ ነን’ የሚሉ ሚዲያዎችን ያገኛል። እነዚህም ሚዲያዎች በአደረጃጀታቸው በሁለት ተከፍለው ሊታዩ ይችላሉ። የመጀመሪያዎቹ መደበኛ ሚዲያዎች (mainstream media) ሲሆኑ የአስተዳደር መዋቅር፣ ቢሮና ቢሮክራሲ፣ ኤዲቶሪያል ቦርድ፣ የቴሌቪዥን እና/ወይም ራዲዮ ፕሮግራም ያላቸው እንዲሁም የየራሳቸው አሠራር ያላቸው ናቸው። እነዚህ በብዙ ምዕመናን የሚታወቁና ተአማኒ ተደርገው የሚወሰዱም ናቸው። እንደነዚህ አይነት ሚዲያዎች መዋቅራቸው በሰው ኃይል ቢጠናከር፣ በዘርፉ በሰለጠነ ባለሙያ ቢመሩና አሠራራቸው የበለጠ ቢሻሻል፣ ከእውነተኛው ምንጭ ብቻ የተቀዳውን የሊቃውንት አስተምህሮ ብቻ ቢያቀርቡ ለክርስትና ሕይወታችን ብዙ ይጠቅሙናል። ሁለተኞቹ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲሆኑ እነርሱም በሁለት ይከፈላሉ።
የመጀመሪያዎቹ የትብብር (የቡድን) ማኅበራዊ ሚዲያዎች (Collaborative channels) ናቸው። እነዚህም በተለያየ አጋጣሚ የተዋወቁ ወይም አብረው ያገለግሉ የነበሩና ተመሳሳይ ራዕይ/ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ተሰባስበው የፈጠሯቸው ወይም በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን፣ በሰንበት ትምህርት ቤት፣ በማኅበራት ወዘተ ስም የተከፈቱ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ናቸው። ሲመሠረቱ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ነው ተብሎ ብዙ ሰው ቢያሳትፉም እንኳን ሲሠሩ ግን በጥቂት የቡድን አባላት (core members) ብቻ የሚዘወሩ ናቸው። የቡድን ሚዲያዎች ብዙዎቹ በYoutube የሚተላለፉ ሲሆኑ ጥቂቶቹ የሳተላይት ቲቪ ተከራይተው ያስተላልፋሉ። ከእነዚህ መካከል ያሉ አንዳንድ ሚዲያዎች መንፈሳዊ ነን ብለው ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን በማቅረብ ቢጀምሩም ቀስ በቀስ ወቅታዊ ጉዳዮችን ወደ ማቅረብ ይገባሉ። ሲከራርሙም ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ይሰምጣሉ። በቅርብ ዓመታት እንዳስተዋልነውም አንዳንዶቹ ሚዲያዎች ጦርነት ሲቀሰቀስ ዋና የጦርነት ተንታኝና ግንባር ቀደም ጥላቻ አፋፋሚ ሆነው ከርመው ጦርነቱ ሲቆም “ግብረ ዘወሀብከኒ ፈጸምኩ” ብለው ወደ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ተመልሰዋል።
ሁለተኞቹ ደግሞ የግለሰብ ማኅበራዊ ሚዲያ (Personal social Media) ሲሆኑ አንድ ግለሰብ ብቻውን የሚናገርባቸው ወይም የሚጽፍባቸው፣ ወይም መሰሎቹን እየጋበዘ አብረው የሚያወጉባቸው ‘ሚዲያዎች’ ናቸው። ለስሙ ሚዲያ ቢባሉም ከግለሰቡ የግል ማኅበራዊ የትሥሥር ገጾች ብዙም የተለዩ አይደሉም። በእነዚህ አይነት ሚዲያዎች የሚተላለፍ መረጃ፣ መልዕክት ወይም ትምህርት የግለሰቡ ዕውቀት፣ አመለካከትና ልምድ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው። በእነዚህ ሚዲያዎች የሚቀርበው መልእክት፣ ትምህርት ወይም መረጃ ሌላ ምንጭ እስካልተጠቀሰለት ድረስ የግለሰቡ ኃላፊነት ነው፣ ተጠያቂ የሚሆነውም ግለሰቡ ነው። በእነዚህ ሚዲያዎች ለሚቀርብ ጉዳይ ቤተ ክርስቲያን እንደ ተቋም ልትጠየቅበት አይገባም። ነገር ግን ግለሰቦቹ ‘የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ነው’ ብለው የሚያሰራጩት መረጃ ትክክለኛ ካልሆነ ቤተ ክርስቲያን ከሁሉም ቀድማ ልትጠይቃቸው ይገባል።
ከአደረጃጀት ጋር በተያያዘ በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተመሥርተው ቤተ ክርስቲያንን ርዕሰ ጉዳይ አድርገው የሚሠሩ ሚዲያዎች ላይ የሚስተዋለው ዋናው ችግር የሚዲያ (communication) ሙያ (ዕውቀትና ክህሎት) አለመኖር ነው። ብዙዎቹ የሚዲያው ባለቤቶችና የሚዲያ ዝግጅት የሚያቀርቡት የሚዲያ ሙያ የላቸውም። ብዙዎቹ ሰባኪ፣ ዘማሪ፣ ካህን፣ ሰንበት ተማሪ እና የመሳሰሉት ሲሆኑ ምንም አይነት ለሚዲያ የሚሆን ትምህርት ሳይማሩ በድፍረት ራሳቸውን በአንድ ጀምበር የሚዲያ ሙያተኛ ሆነው ያገኙ ናቸው። ብዙዎቹ መስበክ፣ መዘመር ወይም መርሀግብር መምራት ስለቻሉ ብቻ ጥሩ የሚዲያ ባለሙያ የሚሆኑ ይመስላቸዋል። ይህ ግን ፈጽሞ የተሳሳተ ነው። የሚዲያዎቹ መሠረታዊ ችግር የሚመነጨውም ከዚህ ነው። የሚዲያ ሙያን በትክክል ካልተማረና ልምድ ካልቀሰመ ሰው ጥራት ያለው ሥራን መጠበቅ አይቻልም።
የተለበጠ ስማቸው
የብዙዎቹ መንፈሳዊ ሚዲያዎች (በተለይም በዩቲዩብ የሚተላለፉት) ስማቸው በአብዛኛው ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ ወይም ከቅዱሳት መጻሕፍት የተወሰዱ መንፈሳዊ ቃላትን የያዘ፣ በመንፈሳዊ ቃላት የተዋበ (የተለበጠ) ነው። ይህ መልካም ጅምር ነው። አንዳንዶች ደግሞ “እገሌ” ሚዲያ ወይም “ቤተ እገሌ” ተብለው በሰውየው ስም ይጠራሉ። ይህ አይነቱ አሰያየም ግን በግለሰብ ታዋቂነት ላይ የመንጠልጠል ወይም የግለሰብን ዝና የመገንባት ነገር እንዳይገባበት ስጋት አለን። ሚዲያዎቹ በግለሰብ የሚመሩ ከሆነ ግን ከተፈጥሯቸው አንጻር በግለሰቡ ስም መጠራታቸው ተገቢ ይመስለናል።
ብዙዎቹ ሚዲያዎች ራሳቸውን ሲገልጹም “የቤተ ክርስቲያን እውነተኛው አስተምህሮ የሚተላለፍባቸው፣ የቤተ ክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና የጠበቁ” እንደሆነ አድርገው ነው። በእውነቱ ይህ አገላለጽ ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ የሚጠበቅበት መሆኑ ባያጠያይቅም እጅግ ከባድና በቀላሉ ሊታይ የማይገባው ነው። አንድ ሚዲያ ራሱን የቤተ ክርስቲያን እውነተኛው አስተምህሮ የሚተላለፍበት ለማለት ቢያንስ ከሚከተሉት መስፈርቶች አንዱን ማሟላት ይኖርበታል። አንደኛው ለሚያቀርበው ትምህርት ተጠያቂ የሆኑ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት መሠረት ማድረግ ይኖርበታል። ሁለተኛው ደግሞ በቤተ ክርስቲያን የታወቁ መጻሕፍትን በምንጭነት መጠቀምና መጥቀስ ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ደግሞ የሚቀርበው ትምህርት በግልጽ የሚታወቅ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ (general fact) ሊሆን ይገባል። ይህ ባልሆነበት እውነተኛው “የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የሚተላለፍበት” ብሎ በመጥራት ብቻ እውነተኛ ማድረግ አይቻልም። “የቤተክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና የጠበቁ” የሚባሉት የቤተክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና መጠበቃቸው በምን ይታወቃል? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ይህንን ለማረጋገጥ ሚዲያው የቤተ ክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና መሠረት ያደረገ ኤዲቶሪያል መመሪያን ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልገዋል። ይህ በሌለበት “የቤተክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና የጠበቀ” ማለቱ ብቻ የጠበቀ አያደርገውም።
ስለራሳቸው ማስታወቂያ ሲሠሩም ከዓለማዊ ሚዲያ በተኮረጀ የማስታወቂያ ስልት ራሳቸውን የክርስትና አስተምህሮ ውኃ ልክ አድርገው፣ ራሳቸውን የቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ድምፅ እንደሆኑ ቆጥረው፣ የመንግሥተ ሰማያት መግቢያ ቁልፍ በእነርሱ እጅ ያለ ያህል አስመስለው ነው። ይህንን የሚሰማ የዋህ ምዕመንም እነዚህ ሚዲያዎች ከቤተ ክርስቲያን የበላይ አካል ፍቃድ የተሰጣቸው፣ ይዘታቸውም የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ የጠነቀቀና ከመንፈሳዊ ነገር ውጭ የማያቀርቡ ሊመስለው ይችላል። እውነታው ይህ ቢሆን እጅግ ደስ ባለን ነበር። ነገር ግን በጣም የሚያሳስበው አንዱ ጉዳይ ይህ ራሱ ነው። ራሱን መንፈሳዊ ሚዲያ ነኝ ብሎ የተነሳ ሚዲያ፣ ለእውነት እቆማለሁ ብሎ ማንም ሳይጠይቀው አቋሙን የገለጠ ሚዲያ እንዴት ስለራሱ ማንነት ሳይቀር ይዋሻል የሚለው ነገር እጅግ ያስጨንቃል። ስለራሱ ማንነት እውነት ያልተናገረ ሚዲያ ስለቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሲናገርስ እውትነቱን አለመጠራጠር እንዴት ይቻላል?!
ብዙዎቹ ዓላማችን ብለው የሚያስተዋውቁትና በእውነታው ዓለም የሚያራምዱት ዓላማ ይለያያል። ከዚህም የተነሳ አብዛኞቹ መንፈሳዊ/ሃይማኖታዊ አስተምህሮን፣ ወቅታዊ ጉዳዮችን፣ ባህልን (ማኅበረሰባዊ አኗኗርን) እና ፖለቲካዊ ርዕዮትን እንደየ አየሩ ጠባይ ቀላቅለው ሲያቀርቡ ይስተዋላል። አሠራራቸውም በአብዛኛው ተጠያቂነት (accountability) የሌለበት፣ ደረጃውን የጠበቀ አሠራር (standard) የሌለው፣ ወጥ መርኃግብር (format) ያልተቀረፀለት፣ አድማጭ ተመልካቹን ያላገናዘበ፣ ወይ ዓለማዊ ወይ መንፈሳዊ የማይባል ይዘት ያለው መልእክት የሚቀርብበት ነው። የአንዳንዶቹ ሚዲያዎች ዋናው ዓላማም ዕይታን (view) መሳብ ብቻ ይመስላል። ከዚህም አልፎ ሚዲያዎች እርስ በእርስ ከመደጋገፍ ይልቅ መደጋገም፣ እርስ በእርስ መነታረክ፣ መፎካከርና መጠላለፍ ይታይባቸዋል።
የተገለጠ ግብራቸው
ከሁሉ አስቀድመን በተሠጠቻቸው መክሊት በቀናነትና በትጋት፣ በትህትናና ራስን በመግዛት በአካልም በሚዲያም፣ በገጠርም በከተማም የሚያገለግሉት አበው፣ አኀውና አኃት አገልግሎታቸው ይሰምር ዘንድ፣ ሌላውም የእነርሱን አርአያ ይከተል ዘንድ፣ እነርሱም እስከመጨረሻው ጸንተው የአገልግሎታቸውን ፍሬ የዘላለም ሕይወትን ያገኙ ዘንድ የዘወትር ጸሎታችን ነው። በዘመናችን ያሉ መንፈሳዊ ነገርን እናቀርባለን የሚሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በተግባር የተገለጡ ጠባዮችን ግን እንደሚከተለው እናቀርባለን።
በሚዲያ መቅረብ ያለበትንና የሌለበትን ለይቶ ያለማወቅ
አንድ ሚዲያ ሥራ ሲጀምር ምን መልእክት (message) እንደሚያቀርብ፣ ለምን እንደሚያቀርብ (objectives)፣ ለማን እንደሚያቀርብ (target audience)፣ በማን እንደሚቀርብ (communication professionals)፣ እንዴት እንደሚተላለፍና (Channel) በማስተላለፉ ምን ለውጥ ሊያመጣ እንደሚፈልግ (anticipated outcome) ጠንቅቆ አውቆ ዝርዝር ዕቅድ ማዘጋጀት ይጠበቅበታል። ነገር ግን ከይዘት አንጻር: አንዳንዶቹ መንፈሳዊ ነን የሚሉ ሚዲያዎች የሚያቀርቡትንና ለምን ወይም ለማን እንደሚያቀርቡ እንኳን በአግባቡ የሚያስተውሉት አይመስሉም። ለምሳሌ “ካህኑ ቀደሱ፣ የንግሥ በዓል ተከበረ፣ ጳጳሱ ባረኩ” ብለው የዜና ዘገባ የሚያቀርቡትን መመልከት ይቻላል። ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ጸሎትን ቀርጸው ለሕዝብ የሚያስተላልፉ ምን ዓላማን ለማሳካት እንደሆነም አይገባንም። የውጭ ዜናም ብለው ሲያቀርቡ በሌላ ሀገር ያለን የተለመደ መንፈሳዊ አገልግሎት ዜና አድርገው ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሕልም አየሁ፣ ጌታ ተገልጦልኝ እንዲህ ብሎኛል፣ እመቤታችን ተገልጣ እንዲህ ብላኛለች፣ ከቅዱሳን እንዱ ተገልጦልኝ እንዲህ አለኝ፣ ተአምራት ተደረገልኝ የሚሉ ሰዎችን ሳይመረምሩ ያቀርባሉ። ይህ አይነቱ አሠራር ከየዋህነት/ካለማወቅ ሊመነጭ ቢችልም በጊዜ ካልታረመ ውሎ አድሮ ችግር መፍጠሩ አይቀርም።
የሚዲያ መመሪያዎችን አለማክበር
ዋና ዋናዎቹ የማኅበራዊ ሚዲያ ማኅበረሰብ መመሪያዎች (1) እውነትነቱ ያልተረጋገጠ ወይም አሳሳች መረጃን አለመለጠፍ፣ (2) ሰውን እና የሰውን ሀሳብ ማክበር፣ (3) የሰዎችን ግላዊ መረጃም ሆነ ፎቶ ያለፈቃዳቸው አለመለጠፍ፣ (4) የጥላቻ ንግሮችን ማስወገድ፣ (5) የሰዎችን ስም አለማጥፋት፣ (6) ብጥብጥን ሁከትን ወይም ግጭትን የሚያስነሳ ወይም የሚያባብስ መረጃ አለመለጠፍ፣ (7) ስድብ እና የሰዎችን አእምሮ ሊጎዱ የሚችሉ ይዘት ካላቸው ነገሮች ሁሉ መከልከልን ያካትታሉ። እነዚህ መሠረታዊዎቹ ሲሆኑ መንፈሳዊ ነገር አቀርባለሁ ከሚል ሚዲያ ደግሞ ከእነዚህም በላይ ይጠበቃል። እነዚህ የማኅበራዊ ሚዲያ ማኅበረሰብ መመሪያዎችን አለማክበር በራሱ እንደየሁኔታው የህግ ተጠያቂነት ሊያስከትል የሚችል ጥፋት ነው። መንፈሳዊ ነን የሚሉ ሚዲያዎች ከሁሉ አስቀድመው እነዚህ መመሪያዎችን በማክበር ራሳቸው ከህገ ወጥነት መራቅ አለባቸው። በምድራዊ ሕግ እንኳ ጥፋት ወይም ወንጀል እየፈጸሙ ወንጌልን በሚገባ መስበክ አይቻልምና። ሕግጋተ ወንጌል ከእነዚህ መመሪያዎች በላይ ናቸውና እነዚህ መሠረታዊ መመሪያዎችን ያላከበረ የእግዚአብሔርን ሕግ አከብራለሁ ቢል እርሱ ግብዝና ሐሰተኛ ነው። አንዳንዶች እነዚህን መመሪያዎች በመጣሳቸው ምክንያት ማኅበራዊ ሚዲያቸው ሲዘጋባቸው (አልተዘጋባቸውም ማለትም ሙሉ በሙሉ መመሪያውን ያከብራሉ ማለት አይደለም) ልክ እንደ ተጋድሎ ወይም ጽድቅ ይቆጥሩታል። ምንም እንኳ አንዳንድ መመሪያዎች ወይም ክልከላዎች ግልጽነት የሚጎድላቸው ወይም በአድሏዊነት የሚፈጸሙ ቢሆንም እጅግ የሚበዙት ግን የተገቡ ናቸው። ስለዚህ መንፈሳዊ ነን የሚሉ ሚዲያዎች ሌላውን ከማስተማራቸው በፊት ራሳቸውን ሊያስተምሩና መመሪያን አክብረው ሊሠሩ ይገባል እንላለን።
ሰውን ከቤተ ክርስቲያን ማስቀረት
ማኅበራዊ ሚዲያ ቤተ ክርስቲያን ለምትሰጠው አገልግሎት አጋዥ/ማሟያ እንጂ ምትክ መሆን እንደሌለበት በጽኑ እናምናለን። በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተላለፈው መልእክትም ሰውን ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመራ እንጂ እዚያው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንዲቆይ ማድረግ የለበትም እንላለን። ይሁንና በተጨባጭ የሚታየው ግን እንደዚህ አይመስልም። ማኅበራዊ ሚዲያው ሰውን የራሱ ተከታይ በማድረግ ከቤተ ክርስቲያን እያስቀረው ነው። ይህም በተለያየ መንገድ ነው። አንደኛው ማኅበራዊ ሚዲያው ራሱ “ዲጂታል ቤተ ክርስቲያን” የመሆን አዝማሚያ እያሳየ ያለ ይመስለናል። ስብከትና ትምህርት በማኅበራዊ ሚዲያው ይሰጣል፣ ጸሎትም ቡራኬም በማኅበራዊ ሚዲያው ይሰጣል፣ ቅዳሴውም ንግሡም በማኅበራዊ ሚዲያው ይተላለፋል፣ ምፅዋቱም በኦንላይን ይሰበሰባል። ይህ ቆይቶ “ሁሉም አገልግሎት እዚሁ ካለ ታዲያ ለምን ቤተ ክርስቲያን እሄዳለሁ?” የሚል ሀሳብ ያመጣል። ይህ እየቆየ ሲሄድ አገልጋዩም አንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሄጄ 100 ሰው ከማገለግል በማኅበራዊ ሚዲያ 1000 ሰው ባገለግል ይሻላል ወደሚል ሀሳብ ሊመራ ይችላል። ሁለተኛው ሰው በቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ላይ ያለው አመኔታ እንዲቀንስ በማድረግ ነው። ይህም አንድም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን ስም በማጥፋት፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ የተሻለ አገልግሎት ያለ በማስመሰል ነው። ሦስተኛው ምዕመናን ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱበትን ጊዜ በመሻማት ነው። በጠዋት ተነስቶ ቤተ ክርስቲያን ከመሳለም ይልቅ ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ጊዜውን የሚያሳልፈው ምዕመን ጥቂት አይደለም። አንዳንድ ጊዜም በንግሥና በሌሎች መርኃግብሮች በሞባይል ፎቶ የሚያነሳውና ቪዲዮ የሚቀርፀው ሰው ከመብዛቱ የተነሳና ያነሱትን ፎቶም ይሁን የቀረፁትን ቪዲዮ ለምን ዓላማ እንደሚያውሉትና እነማን ጋር እንደሚደርስ ስለማይታወቅ ጥቂት የማይባል ሰው በዚህ ድርጊት ተሳቅቆ ይቀራል ወይም ርቆ ይቆማል። ስለነዚህ ጉዳቶች በቂ ግንዛቤ መፈጠር እንዳለበት ይሰማናል። ቤተ ክርስቲያን የምንሄደው አምልኮታችንን ለመፈጸም እንጂ ያለ ፈቃዳችን የሚዲያ ግብአት ለመሆን አይደለም።
ክርስቲያናዊ ስነ-ምግባራትን ማዳከም
የማኅበራዊ ሚዲያዎች መብዛትና ያልተገደበ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ክርስቲያናዊ ሕይወትን በብዙ መንገዶች ያዳክማል። የመጀመሪያው በማስረሳት ነው። በገሀዱ ዓለም ልንተገብራቸው የሚገቡ ስነ-ምግባራትን ቀስ በቀስ ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ መስተጋብር (online interaction) በማምጣት ስነ-ምግባር ማለት ማኅበራዊ ሚዲያን መስማት ወይም መከታተል፣ መውደድ፣ ጥሩ ሀሳብ ወይም አስተያየት መስጠት፣ ሰብስክራይብ ማድረግ፣ ማጋራት፣ ለሚዲያው ዕድገት ገንዘብ መለገስና የመሳሰሉት እንዲመስሉን ያደርጋል። በሂደትም እውነተኞቹን ክርስቲያናዊ ስነ-ምግባራት እንድንረሳቸው ሊያደርገን ይችላል። ሁለተኛው በመነጠል ነው። ማኅበራዊ ሚዲያን ያለገደብ መከታተል በገሀዱ ዓለም አጠገባችን ያሉ አብረውን የሚኖሩ ሰዎችን በመተው ኦንላይን ብቻ የምናውቃቸው በአካል አይተናቸው ከማናውቃቸው ሰዎች ጋር ብቻ ብዙ ጊዜ እንድናሳልፍ ያድርጋል። በዚህም በአካል አብረውን ከሚኖሩ ወንድሞቻችን፣ እኅቶቻችንና ቤተሰቦቻችንን ቀስ በቀስ እንድንነጠል ያደርገናል። ይህም መነጠል የክርስትና ሕይወታችንን እንዲሁም የአእምሮ ጤናችንን ይጎዳዋል። በሦስተኛ ደረጃ የምናነሳው የማኅበራዊ ሚዲያ ሱሰኝነት ነው። ያልተገደበ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ብዙ የማያስፈልጉ ፎቶዎችን፣ ጽሑፎችንና ቪዲዮዎችን እንድንመለከት ያደርጋል። ይህም አእምሮአችንን ቀስ በቀስ የማኅበራዊ ሚዲያ ተገዢ ሊያደርገው ይችላል። ለሥጋችንና ለነፍሳችን መልካም ሥራ የምንሠራበትን ጊዜም አላስፈላጊ ነገሮችን በመመልከት እያሳለፍን ለድህነት እንዳረጋለን። ይህንን ለመግታት ማኅበራዊ ሚዲያን በአግባቡና ለተወሰኑ አገልግሎቶች ብቻ መጠቀም ይገባል።
ፍቅርና ጥላቻን ማደባለቅ
ማንኛውም ሚዲያ በተለይም መንፈሳዊ ነኝ የሚል ማኅበራዊ ሚዲያ በሰዎችና በማኅበረሰብ መካከል ሰላም፣ ፍቅርና ፍትሕ እንዲሰፍን መሥራት ይጠበቅበታል። ከስነ-ምግባር (ethical principles) አንጻርም ማንንም የማይጎዳ (Doing no harm)፣ ሰውን የሚጠቅም (Doing good)፣ የሰው ልጆችን ተፈጥሮአዊ ነጻነት የሚያከብር (Respecting peoples freedom) እና ፍትሐዊ (Ensuring fairness) መሆን የግድ ይላል። ነገር ግን አንድ ጊዜ ፍቅርን ሌላ ጊዜ ጥላቻን የሚሰብኩትን፣ ዛሬ ሰላምን ነገ ጦርነትን የሚያወድሱትን፣ ዛሬ መስቀል የያዘ ካህን ነገ ነፍጥ ያነገበ ሽፍታ የሚያሳዩትን ሚዲያዎችን አስተውለናል። ዛሬ መንፈሳዊ መልእክትን ፍቅርን መደጋገፍን፣ እርቅን ሰላምን አስተላልፈው ነገ “በለው፣ አጥፋው” የሚሉትን ተመልከቱ። እራሳቸው ያወገዙትን ራሳቸው የሚያወድሱ፣ ራሳቸው የረገሙትን መልሰው የሚመርቁ፣ በመንፈሳዊ አስተሳሰብ ይቅርና በጤነኛ አእምሮ እንኳን የማይታሰብ ይዘት ያላቸውን ተመልከቱ። ይህንን እያደረጉ መንፈሳዊ ሚዲያ ነን ሲሉ አንዳች ኃፍረት አይሰማቸውም።
ቀመር-ተኮር አገልግሎትን ማስፋፋት
የማኅበራዊ ሚዲያ ጠቋሚ ቁጥሮች (indicators/statistics) ማለትም የእይታ፣ ማጋራት፣ አስተያየት እና ሰብስክራይበር ቁጥሮች መንፈሳዊ አገልግሎት መለካት በሌለበት ሚዛን እንዲለካ ከማድረጋቸውም በላይ አገልጋዮችንም አላስፈላጊ ውድድር ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል። ይህም ቆይቶ ትሁት አገልጋዮችን ሳይሆን ታዋቂና ዝነኛ ግለሰቦችን (media celebrities) ይፈጥራል። በሌላ በኩል የሚዲያ አገልግሎት ገንዘብ እንደሚያስፈልገው በግልጽ ይታወቃል። ለዚህም ሕጋዊውን መንገድን ተከትሎ ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን እና ሌሎች ወጭዎችን የሚሸፍን ገንዘብ ማፍራት አያስነቅፍም። ነገር ግን መንፈሳዊ አገልግሎትን ለግል ሀብት/ገንዘብ ማግኛነት ዋና መንገድ ማድረግ ግን ሲሞናዊነት ነው። ከዚህ አንጻር የአንዳንድ መንፈሳዊ ነን የሚሉ ሚዲያዎች ዓላማ like, comment እና subscriber መሰብሰብ ይመስላል። ለእነዚህ አይነት ሚዲያዎች ምዕመናን ‘ቁጥር’ ናቸው። እነዚህ ሚዲያዎች እይታን እስካበዛላቸው ድረስ ምንም ዓይነት ዝግጅትና ማንንም አይነት እንግዳ ያቀርባሉ። አንድ ጊዜ ስብከት፣ ሌላ ጊዜ የንግድ ማስታወቂያ የሚሠሩ መንፈሳዊ ሚዲያዎችም አሉ። ዋናው ግባቸው በመንፈሳዊ አገልግሎት ምክንያት ያገኙትን ስምና ተሰሚነት ለገንዘብ ማግኛነት ማዋል ነው። የሚያቀርቧቸው ሰዎችም አወዛጋቢ፣ መልዕክቶችም አከራካሪ የሚሆኑት ተቀዳሚ ዓላማቸው እይታ ለማብዛት ስለሆነ ነው። ከዚህም የሚገኝ ገቢን ወይም ማስታውቂያ ለመሥራት መመቻቸትን ግብ ያደረገ ነው።
ለአጭበርባሪዎች ተጋላጭነት
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ግልፅ እና ስውር ስም ያላቸው ብዙ አጭበርባሪዎች አሉ። በግልፅ ስማቸው በማኅበራዊ ሚዲያ በቤተ ክርስቲያን ስም እገሌ የሚባል ገዳም እንርዳ፣ እገሌ የሚባል ቤተ ክርስቲያን እንሥራ፣ በዚህ ቦታ ያሉ የተጎዱ ክርስቲያኖችን እንርዳ እያሉ በየጊዜው የተለያየ ምክንያት እየፈጠሩ ገንዘብ የሚሰብስቡ ወገኖች አሉ። ምዕመናን በቀናነት የሚሰጡት ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ለተፈለገው ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ ከባድ ነው። ሌሎችም በቤተ ክርስቲያን ስም በተከፈተና ምዕመናን መንፈሳዊ አገልግሎትን ጠብቀው በሚከታተሉት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለያዩ መጻሕፍት፣ የመዝሙርና የስብከት ሲዲዎች፣ የአንገት መስቀል፣ የካህናት መስቀል፣ የምግብ ግብዓቶችንና የተለያዩ አልባሳትን ይነግዱበታል። የተለያዩ ስፖርታዊ ውድ ድሮችንም ያስተዋውቃሉ፣ ያስተላልፈሉም። ከፍ ሲልም ‘የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንዲህ አይነት ቢዝነስ ያስፈልገናል’ እያሉ የተለያዩ አክስዮኖችን ያሻሽጡበታል። አንዳንዴም ስለ እመቤቴ ስለ አዛኝቷ (የተቸገረ ሰው አለመሆኑን ልብ ይሏል) እየተባለ በግልፅ ይለመንበታል። በዚህ መንገድ የሚሰበሰብ ገንዘብ ለሌላ እኩይ ዓላማ አለመዋሉንም እርግጠኛ መሆን ያዳግታል። በዚህ ጉዳይ ሁሉም መንቃት እንዳለበት እናምናለን።
ገፅታ መገንባትና ማፍረስ
የመንፈሳዊ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ትኩረት መንፈሳዊውን አስተምህሮ ማስተላለፍ ላይ መሆን እንዳለበት እናምናለን። ከዚህም አንጻር እውነተኞች አገልጋዮችን በውዳሴ ከንቱ መካብ ያለባቸው አይመስለንም። አስተምህሯቸው ችግር ያለበት ወይም አከራካሪ የሆኑትንም ቢሆን ሊቃውንቱን በመጠየቅ ማጥራት ያስፈልጋል እንጂ የተለያየ ስም እየለጠፉ ስም ማጥፋቱ በተለይም መንፈሳዊ ነኝ ከሚል ሚዲያ አይጠበቅም። በሌላ በኩል የአንዳንድ ሚዲያዎች ትኩረት ደግሞ ገጽታ ግንባታ ላይ ያተኩራል። የሆነ ግለሰብ (አገልጋይን) ማስተዋወቅና ታዋቂ ማድረግ (“ማፈመስ”) በተግባር የተገለጠ ዓላማቸው ነው። በታቀደና ተገማች በሆነ መልኩ የአንድን አገልጋይ ስብከቶች፣ መጻሕፍት፣ ፎቶዎች፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎች ደጋግመው የሚያቀርቡት ከመንፈሳዊነት ይልቅ ‘ግለሰብ አምላኪ” ቢባሉ ይቀላል። በሌላም አንጻር በግል ጠብም ሆነ በቅናት የማይወዱትን አገልጋይ የተለያየ ስም እየሰጡ ሲያብጠለጥሉ የሚውሉ ሚዲያዎችም አሉ። ይህም በምዕመናን መካከል አንድነትን ሳይሆን መከፋፈልን የሚያስፋፋ ዋነኛ ምክንያት እየሆነ መጥቷል። ታላላቅ የቤተክርስቲያን አባቶች ሳይቀሩ በነዚህ ሚዲያዎች የተለያየ ስም እየተሰጣቸው ሲብጠለጠሉ ይውላሉ። ይህም ምዕመናን በአገልጋዮች ላይ ያላቸው እምነት እንዲቀንስ ብዙ አስተዋጽኦ አድርጓል። በተጨማሪም አንድ አገልጋይ ሲያጠፋ offline እንዲመከርና እንዲታረም ከማድረግ ይልቅ ጉዳዩን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የመቀባበል ነገር ይታያል። ይህ ከክርስቲያን የማይጠበቅ አሳፋሪ አካሄድ ስለሆነ ሊታረም ይገባዋል።
ጽሑፍና ዝግጅት መስረቅ
አንዳንድ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ደግሞ በሌላ ሚዲያ ላይ የቀረበ ጽሑፍን ወይም ዝግጅትን ምንጩን ሳይጠቅሱና ሌላ ምንም አይነት ዕሴት ሳያክሉበት እንደ ወረደ ያቀርባሉ። ራሳቸውን “አቅራቢ” ብለው ይሰይማሉ። ምንም እንኳን የእግዚአብሔርን ቃል ማስፋፋት ባያስነቅፍም ምንጭን መጥቀስ ግን ይገባል። የአንድ ጽሑፍን ወይም ዝግጅትን ምንጭ መጥቀስ የራስን ተአማኒነት ይጨምራል እንጂ ብዙዎች ‘የሌላ ነው ብዬ ካቀረብኩማ የሚዲያዬ ክብር ይቀንሳል’ ብለው እንደሚያስቡት አይደለም። ይልቁንም በተለይ መንፈሳዊውን ጉዳይ አቀርባለሁ ለሚል ሚዲያ የሚከፋው ነገር የጽሑፍን ወይም የዝግጅትን ምንጭ በግልጽ አለመጥቀስ ነው። ይህ ከመስረቅ (ሌብነት) ተለይቶ አይታይም። እንግዲህ መንፈሳዊነትና ሌብነት አብረው ሊሄዱ ስለማይችሉ ይህ መስተካከል አለበት። አንዳንድ ማኅበራዊ ሚዲያዎች “ምንጩን ከጠቀስኩማ ለሌላ ሚዲያ ነጻ ማስታወቂያ መሥራት ነው” የሚሉ ገጥሞናል። በእውነት ይህ አሳፋሪ ምቀኝነት ነው። ምንጭ መጥቀስ የሙያ ታማኝነት (integrity) እንጂ ማስታወቂያ መሥራት አይደለም። ሚዲያ ምንጭ የሚጠቅሰው ለሙያው ታማኝነት ብሎ ነው። የሙያ ታማኝነት ያጣ ሚዲያ ደግሞ ሁሉንም ነገሩን ያጣል፣ ሚዲያ ተብሎም መጠራት የለበትም።
ፖለቲካ ዘመም መሆን
ከፖለቲካ ዘመምነት እንጻር የእኛን ማኅበራዊ ሚዲያዎች በአምስት ከፍለን ልናያቸው እንችላለን። የመጀመሪያዎቹ “አደግዳጊ” ሲሆኑ ስልጣንና ገንዘብ ላለው ሁሉ የሚያደገድጉ ናቸው። ሁለተኞቹ ደግሞ “ብሶተኞች” ሲሆኑ በመንግሥት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በመንፈሳዊነት ስም ተከልለው የሚያቀርቡ ናቸው። ሦስተኞቹ “ሁሉን አቀፍ” ሲሆኑ ሁሉንም የፖለቲካ አመለካከት በእኩል እናያለን የሚሉ (በተጨባጭ ግን የየራሳቸው ጎራ ያላቸው) ናቸው። አራተኞቹ “ተለዋዋጭ” ሲሆኑ የተወሰነ አቋም የሌላቸው፣ እንደ አየሩ ጸባይ ወደነፈሰበት የሚተሙና ማንም ተነስቶ የሚነዳቸው፣ እንደ በቀቀን የተባለውን የሚደግሙ የገደል ማሚቶዎች ናቸው። የመጨረሻዎቹ “የቄሳርን ለቄሳር” ያሉ ሲሆኑ ሙሉ ትኩረታቸው መንፈሳዊው አስተምህሮ ላይ ነው። ለእኛ የሚያስፈልጉን የቄሳርን ለቄሳር ብለው መንፈሳዊው ጉዳይ ላይ ብቻ የሚያተኩሩት ናቸው።
የመፍትሔ ሀሳቦች
ለመደበኛው ሚዲያዎች: ፍትሐዊና አሳታፊ የሚዲያ ሥርዓት ይኑር።
አሁን ባሉበት ሁኔታ በግለሰቦችና በቡድኖች የሚዘወሩ ሚዲያዎችን ወደ ሥርዓት ማስገባት አስቸጋሪ ይሆናል። አመራሮቹም ‘እናውቃለን’ የሚሉ ስለሆኑ ለማስተማርም ፈታኝ ነው። ብዙ ተከታይም ስላላቸው ዝም ብሎ መተውም አደጋ አለው። ለእነዚህ ይሆናል የምንለው መፍትሔ አሳታፊ የሆነ (engaging) የሚዲያ ሥርዓት መዘርጋት ነው። አሳታፊ የሆነ የሚዲያ ሥርዓት ሲኖር ብዙ መምህራን እና አገልጋዮች በመደበኛው ሚዲያ ስለሚስተናገዱ በግለሰብና በቡድን ሚዲያ ላይ ማዘወተር ይቀንሳሉ። ምዕመናንም መደበኛውን ሚዲያ ስለሚከታተሉ የግለሰብና የቡድን ማኅበራዊ ሚዲያዎች ራሳቸውን ያሻሽላሉ ወይም በራሳቸው ይከስማሉ።
ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደር: የሚያሠራ መመሪያና ደንብ ይተግበር።
መንፈሳዊ ዓላማ አለን ብለው፣ ሃይማኖታዊ ስምን አንግበው፣ የቤተክርስቲያንን ሥርዓትና ትውፊት እንጠብቃለን ብለው ለሚመሠረቱ ሚዲያዎች የአደረጃጀት መመሪያ ያስፈልጋቸዋል። የባለሙያዎች የሙያ ብቃትና የትምህርት ዝግጅት፣ ለሚዲያ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ተገቢነትና በቂነት የሚገልጥ ግልፅ መመሪያ ያስፈልጋል። የትኩረት አቅጣጫና የአሠራር ደንቦችም አብረው ሊዘጋጁና ሊተገበሩ ይገባል። የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መመሪያና ደንብ አዘጋጅቶ ከማስፈጸም በተጨማሪ መንፈሳዊነትን ብቻ ግብ አድርገው የሚሠሩ ሚዲያዎችን በሀሳብ፣ በሙያ፣ በገንዘብና በቁሳቁስ ሊደግፋቸውና ሊያበረታታቸው ይገባል። በተለይም የቋንቋ ብዙኃነት ባለበት ሀገር በተለያዩ ቋንቋዎች ወንጌልን ለማዳረስ የሚያደርጉትን ጥረት ሊደገፍ ይገባዋል። ምዕመናንም እንደዚህ አይነት ሚዲያዎች እንዲጎለብቱ የየራሳቸውን ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህንን በማድረግ እውነተኞቹን ማሳደግ ፣ በመከታተል፣ አስተያየት በመስጠትም ማበረታታት ይገባል።
ለማኅበራዊ ሚዲያዎች: ቤተ ክርስቲያንን እናስቀደም።
አንድ በመንፈሳዊ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር የሚዲያ ባለሙያ ሰው የሚፈልገውን ወይስ ለሰው የሚያስፈልገውን ላቅርብ፣ ብዙ ተመልካች የሚያገኘውን ላቅርብ ወይስ ትክክለኛውን ላቅርብ የሚለው ላይ በግልጽ መወሰን ያስፈልገዋል። በግልም ሆነ በቡድን መንፈሳዊ ሚዲያን የሚመሩ አካላት ከራሳቸው ፍላጎትና ጥቅም ይልቅ ቤተ ክርስቲያንን ሊያስቀድሙ ይገባል እንላለን። ይህንን ለማንም ብለው ሳይሆን ለእውነትና ለራሳቸው ተአማኒነት ብለው ማድረግ አለባቸው። ተደራሽ ዓላማቸው በግል ታዋቂ መሆን ወይም ቤተ ክርስቲያንን የሚያክል ግዙፍ የሚዲያ ተቋም መገንባት ሳይሆን ምዕመናንን ማስተማርና መጠበቅ ሊሆን ይገባል። በመንፈሳዊነት ዓይን ታዋቂነትም ይሁን የታላቅ የሚዲያ ተቋም ባለቤት መሆን ከንቱ ናቸው። ከእነዚህ ሁሉ አንድን ኃጢአተኛ በንስሐ እንዲመለስ ማድረግ ይበልጣል። ስለዚህ የግል የቁስ ድህነትን ለማጥፋት ሳይሆን የምዕመናን ድኅነትን ማስፋት ትኩረታቸው ሊሆን ይገባል እንላለን።
ለምዕመናን: የምንከታተለውን ሚዲያ እንምረጥ።
“ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ ሁሉ ግን አይጠቅምም” እንደተባለ (1ኛ ቆሮ 6:12) የምንመለከታቸውን ሚዲያዎችን መምረጥ አለብን። ጊዜ ወርቅ ነውና ያለንን ጊዜ የማይጠቅም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማዋል የለብንም። የማኅበራዊ ሚዲያዎችን ይዘት በመንፈሳዊ ሚዛን መመዘን ይገባናል እንጂ ብዙ ተከታይ ስላላቸው ብቻ ልንከታተላቸው አይገባም። መጥፎ ሚዲያዎች መንፈሳዊ ሕይወት ላይም ጉዳት እንደሚያደርሱም መገንዘብ ይኖርብናል። የምንመለከተውን መምረጥ ያለብን ራሳችን ነን። ምዕመናንም ይሁኑ ሌሎች አገልጋዮች ምን ዓይነት ሚዲያዎችን መመልከት ወይም መከታተል እንዳለባቸው እንዲያውቁ ግልፅ የሆነ መረጃ መስጠት ይገባል። በዚህም መሠረት ምዕመናን በመመሪያ የተደራጁና መንፈሳዊ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለባቸውን ሚዲያዎችን መርጠው ሊከታተሉ ይገባል። መከታተል ብቻ ያይደለ ሊሳተፉባቸውና ሊደግፏቸውም ጭምር ይገባል። ይህ ሲሆን መልካም ሚዲያዎች ያድጋሉ።
ማጠቃለያ
ሚዲያ የቤተ ክርስቲያንን እውነተኛ አስተምህሮ ከማስፋፋት አንጻር ታላቅ ሚና እንዳለው እሙን ነው። በተለይ በዚህ በቴክኖሎጂ ዘመን መንፈሳዊ ሚዲያ እጅግ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን በአውደ ምሕረት የሚሠራው ሥርዓት በሚዲያ ላይም ከነባራዊ ሁኔታ ጋር ተገናዝቦ ሊፈጸም ይገባዋል። ለዚህም የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና ምዕመናን ተቀራርበው ለሠሩ ይገባል። ሚዲያዎችም በቂ የትምህርት ዝግጅትና ልምድ ባላቸው ግብረ-ገብ በሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ሊመሩ ይገባል። ከዚህ በተረፈ ግን በሚዲያ ላይ የሚታየው ችግር የመንፈሳዊነት መዳከምና የዓለማዊነት ጠባይ መግነን ነጸብራቅ ስለሆነ ሁሉም መንፈሳዊነትን ማሳደግ ላይ ሊያተኩር ይገባል እንላለን። በገሃዱ ዓለም የሌለን መንፈሳዊነት ሚዲያ ላይ ልናገኘው አንችልምና።
Pingback: ይድረስ ለሰባኪው: ለምን በከንቱ ይደክማሉ? | አስተምህሮ ዘተዋሕዶ