አንቀጸ ብፁዓን ፲ – እግዚአብሔርን መምሰል : ይህን ብታውቁ፥ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ።

የቀደሙት ሊቃውንት በማቴዎስ ወንጌል ያሉትን ዘጠኙን አንቀጸ ብፁዓን ትርጓሜ ካብራሩ በኋላ አሥረኛውን በዮሐንስ ያምጣዋል ብለው ነበር። በኋላም  በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 13 ቁጥር 17 የሚገኘውን ቃል ሲያብራሩ ደግሞ አሥረኛውን ብፁዓን በዮሐንስ ያመጣዋል ያልነው ይህ ነው ብለውታል። ይህ አንቀጽ አጠቃላይ ትኩረቱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውን አርአያነትና ምሳሌነት በመከተል እርሱን መምሰል (እርሱ እንዳደረገልን እኛም ለሌሎች ማድረግ) ላይ ነው። ይህንን የሚያውቁና የሚያደርጉትም ብፁዓን ተብለዋል።

የዚህ አንቀጸ ብፁዓን መሠረቱ ጌታችን በጸሎተ ሐሙስ የሐዋርያቱን እግር ማጠቡ ነው።  ወንጌላዊ ዮሐንስ ስለዚህ ሲጽፍ “እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፥ እንዲህም አላቸው። ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል።  እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም። መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም። ይህን ብታውቁ፥ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ (ዮሐ 13:12-17)” በማለት ጽፎልናል።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ ሰው የሆነው ለአርአያነትና ለቤዛነት ነው። በመስቀል ቤዛ ሆኖ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሶታል። አርአያ የሆነን ደግሞ እርሱ አድርጎ እናንተም እንዲሁ አድርጉ በማለት ነው። በዚህም እርሱን እንድንመስለው ፍጹም ምሳሌ ሆኖናል። ይህ ክርስቶስን የመምሰል ምስጢር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ (1ኛ ቆሮ 11:1)” በማለት ያስተማረው ነው። ይህ የተወደደ ሐዋርያ ለደቀመዝሙሩ ለጢሞቴዎስ “እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር (ወልደ እግዚአብሔር ሥጋን ተዋሕዶ እኛን ያዳነበት ምሥጢር) ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ (1ኛ ጢሞ 3:16)” በማለት እንደጻፈው እግዚአብሔርን የመምሰል ምስጢር እጅግ ታላቅ ነው። ይህም አምላክ ሰው የሆነበት፣ ሰውም አምላክ የሆነበት ታላቅ ምሥጢር ነው። ሐዋርያው “ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን (ሮሜ 6፡5)” ያለው ይህንን እግዚአብሔርን መምሰልን የሚያስረግጥ ነው። በዚህች ጽሑፍ በአሥረኛው አንቀጸ ብፁዓን ሥር ያሉትን ለክርስትና ሕይወትና ለመንፈሳዊ አገልግሎት መርህ የሚሆኑ ዋና ዋና ትምህርቶችን እንዳስሳለን።

ግብር ከነቢብ አስቀድሞ ማገልገልን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርአያ በመሆን ወንጌልን ያስተምር የነበረው በመጅመሪያ በግብር (በማድረግ) ከዚያም ያደረገውን ያስተውሉ ዘንድ በነቢብ (በቃል) በመናገር ነበር። ተጠምቆ ተጠመቁ በማለት ስለጥምቀት፣ ጾሞ ጹሙ ስለጾም፣ ጸልዮ ተግታችሁ ጸልዩ በማለት ስለጸሎት፣  ዲያቢሎስን ድል አድርጎ ድል አድርጉት በማለት ስለፊተና፣ ድውያንን ፈውሶ ድውያንን ፈውሱ በማለት ስለማዳን፣  ዞሮ አስተምሮ ሂዱና አሕዛብን አስተምሩ በማለት ስለስብከተ ወንጌል፣ መከራን ተቀብሎ መከራ አለባችሁ በማለት መከራን ስለመታገሥ አስተምሮናል። በዚህም የወንጌል ክፍል እግራቸውን አጥቦ እርስ በእርሳቸው እግራቸውን እንዲተጣጠቡ አስተማራቸው። መጀመሪያ በግብር (በተግባር) አሳያቸው፣ ከዚያ በነቢብ (በቃል) ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን ብሎ አስተማራቸው።

በዚህም መንፈሳዊ አገልግሎት መጀመሪያ ክርስትናን በሕይወት መኖር ከዚያም የኖሩትን ሕይወት ለሌሎች መስበክ መሆኑን አርአያ ሆኖልን አስተምሮናል። በዚሁ የወንጌል ክፍልም “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ (ዮሐ 13:35)” በማለት የክርስትናችን መገለጫ በሕይወት መስበክ መሆኑን አስተምሮናል። ለደቀ መዛሙርቱም “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ (ማቴ 5:16)”  በማለት የሚታይ መልካም ሥራ ለመንፈሳዊ አገልግሎት እጅግ አስፈላጊ ነገር መሆኑን አስተምሯል። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም በመልእክቱ ይህንን ሲያስረግጥ “ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ (1ኛ ዮሐ 3:18)” ብሎ ክርስትና የተግባር ሕይወት ሊሆን እንደሚገባ ጽፎልናል።

መንፈሳዊ አግልግሎት በተግባር የሚኖሩትን ሕይወት በቃል መስበክ መሆኑን የሚያውቁ፣ በሕይወትና በቃል የሚሰብኩ ንዑዳን ክቡራን ናቸው። በአንጻሩም ያልኖሩትንና የማይኖሩትን ሕይወት የሚሰብኩ ግብዞች መጀመሪያ ራሳቸውን ሊያስተምሩ ይገባል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለእነዚህ ሲናገር “ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህን? በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን? በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደ ተጻፈ ( ሮሜ 2:21-24)” በማለት መጀመሪያ ራሳቸውን ሊያስተምሩ እንደሚገባ አስተምሯል።

ዝቅ ብላችሁ በትሕትና ማገልገልን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ።

ትህትና የመንፈሳዊ አገልግሎት ታላቅ መርህ ነው። ትህትና የጎደለው አገልግሎት መንፈሳዊ አገልግሎት አይደለም። ጌታችን የማዳን ሥራውን ሁሉ ያከናወነው በትህትና ነው። የተወለደው ከነገሥታት ሳይሆን ከአንዲት ብላቴና ነው። የተወለደውም በቤተ መንግሥት ሳይሆን በከብቶች በረት ነው። ያደገውም እንዲሁ በትህትና ነው። በጥምቀቱ የትሕትናን ሥራ ሠርቷል። በመዋዕለ ስብከቱ ሁሉ በትህትና ያገለግለን ነበር። በጸሎተ ሐሙስም እርሱ ጌታና መምህር ሲሆን ዝቅ ብሎ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ። ፊልክስዮስ ይህንን “ምስጢረ ትህትና ፍጽምት” ብሎታል። በዚህም ጌታችን ምስጢረ ትህትናን አስተማረን።

በሌላውም የወንጌል ክፍል ጌታችን “ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤ እንዲሁ የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም (ማር 10: 43-45)” በማለት ትህትና ታላቅ የመሆን ምስጢር መሆኗን አስተምሯል። እንዲሁም “ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፥ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን። በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው? የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ (ሉቃ 22: 26-27)” በማለት ምስጢረ ትህትናን መሥርቷታል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም  “ሀብታም ሲሆን፥ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ (2ኛ ቆሮ 8:9)” በማለት ጌታችን ምን ያህል በትሕትና ትሕትናን እንዳስተማረ ለቆሮንቶስ ሰዎች ጽፏል።

ስለዚህ ይህን ብታውቁ ብታደርጉትም ሲል የክርስትና ሕይወትና አገልግሎት በትህትና የሚደረግ እንደሆነ ብታውቁ በትህትናም ብትፈጽሙት ንዑዳን ክቡራን ናችሁ ማለቱ ነው። እርሱ የደቀ መዛሙርቱን እግር ዝቅ ብሎ በትህትና እንዳጠበ እናንተም ራሳችሁን ዝቅ አድርጋችሁ አገልግሉ፣ በሕይወታችሁም አስተምሩ ሲል ነው። የትሕትናን አስፈላጊነት ማወቅ፣ ስለትሕትናም መስበክ በቂ አይደለም። መጀመሪያ ትህትናን በተግባር መፈጸም ይገባል። ራስን በከፍታ ቦታ አስቀምጦ፣ ሊቅ ነኝ ወይም ታዋቂ ነኝ እያሉ ስለትህትና መስበክ ግብዝነት ነው። ይህንን የመሰለው የግብዝነት አገልግሎት በፈሪሳውያን ዘንድ የተለመደ ስለነበር ጌታችን የክርስትና ሕይወትና የመንፈሳዊ አገልግሎት መሠረት ትህትና (ዝቅ ብሎ ማገልገል) መሆኑን በዚህ አስተምሯል።

ምሳሌ (አርአያ) እንደሁንኩላችሁ ብታውቁ እኔ እንዳደረኩላችሁ ብታደርጉ ብፁዓን ናችሁ።

ክርስትና ክርስቶስን የመምሰል ሕይወት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “አኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተ እኔን ምሰሉ” እንዳለው (1ኛ ቆሮ 11:1) የክርስትና ሕይወትም የመንፈሳዊ አገልግሎትም ክርስቶስን በመምሰል የሚፈጸም ነው። ጌታችንም የደቀ መዛሙርቱን እግር ካጠበ በኋላ “እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና (ዮሐ 13:15)” በማለት የሰጣቸው መርህ በአገልግሎት እርሱን አብነት እንዲያደርጉ ነው። በዚህም መንፈሳዊ አገልግሎት የሚባለው በአጭር ቋንቋ ሲገለጽ ክርስቶስ ለእኛ ያደረገውን ለሌሎች ማድረግ ነው። የክርስትና ሕይወትን በተግባር ሲገለጽ ክርስቶስን በሕይወት መምሰል ነው።

አዲስ ትዕዛዝን በሰጠበት ክፍልም ጌታችን “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ (ዮሐ 13:34)”  በማለት ክርስትና ማለት እርሱ እንደወደደን (እርሱ በወደደን ምሳሌነት) እርስ በእርሳችን መዋደድ ማለት መሆኑን ነግሮናል። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ስለዚህ ሲናገር “በእርሱ (በክርስቶስ) እኖራለሁ የሚል እርሱ (ክርስቶስ) እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል (1ኛ ዮሐ 2:6)” በማለት ይህንን አስተግጦልናል።  እንዲሁም ጌታችን “የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ (በእግርም በግብርም)፥ እኔም ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል (ዮሐ 12:26)” ማለቱ ይህንኑ ያብራራልናል።

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስም ስለክርስቶስ ምሳሌነት በተናገረበት መልእክቱ “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና (1ኛ የጴጥ 2:21)” ብሏል።  ቅዱስ ጳውሎስም “ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ (ፊልጵ 2:7-8)” ክርስቶስ ቤዛችን እና አርአያችን መሆኑን ተናግሯል። እንግዲህ ይህንን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ ሲል ክርስቶስ ለነፍሳችሁ ቤዛ ሆኖ ለሕይወታችሁ አርአያ እንደሆናችሁ ብታውቁ (ብታምኑ) የእርሱንም ምሳሌነት (አርአያነት) ብትከተሉ ንዑዳን ክቡራን ናችሁ ሲለን ነው።

የሚወዷችሁን ብቻ ሳይሆን የሚጠሏችሁንም ብታገለግሉ ብፁዓን ናችሁ።

ጌታችን አስቀድሞ ስለ ሕግጋተ ወንጌል ሲያስተምር ክርስቲያኖች የሚወዷቸውን ብቻ ሳይሆን የሚጠሏቸውን ጭምር መውደድ እንዳለባቸው ሲናገር “እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ (ማቴ 5:45-48)” ብሏል።

ወንጌላዊው ሉቃስም ይህንን የጌታችንን ቃል  “ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፥ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፥የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ (ሉቃ 21:27-28)” በማለት ጽፎልናል። በዚያች በጸሎተ ሐሙስ ጌታችን እግራቸውን ያጠበው የሚወዱትን ሐዋርያትን ብቻ ሳይሆን የሚክደውንና አሳልፎ የሚሰጠውን ይሁዳን ጭምር ነበር። በዚህም አገልግሎታችሁ ለሚወዷችሁ ብቻ ሳይሆን ለሚጠሏችሁም ጭምር ነው ሲል ነው። እንዲሁም ፍቅራችን ለሚወዱን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሊሆን እንደሚገባ ሲያስተምረን ነው ይሁዳ በታጠበው እግሩና ባደፈው ልቡ ሄዶ አሳልፎ እንደሚሰጠው እያወቀ እስከመጨረሻው ድረስ ፍቅርን የሰጠው። በመስቀል ላይ ለመዳናችን ቤዛ በሆነባት ሰዓትም “አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው (ሉቃ 23:34)” በማለት ለሚገድሉት ምህረትን አድርጓል።

እንግዲህ ይህንን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ ሲል እኔ የሚክደኝን አሳልፎ የሚሰጠኝን ጭምር እንደወደድኩ፣ እግሩንም እንዳጠብኩ ፍቅራችሁ ሁሉንም በመውደድ ይሁን፣ አገልግሎታችሁም ለሚጠሏችሁ ጭምር ይሁን ማለቱ ነው። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የምናገለግል ወንድሞች እስኪ ራሳችንን እንመርምር። የምናገለግለው ማንን ነው የሚወዱንን (ይወዱናል ብለን የምናስባቸውን)፣ የሚያድንቁንን፣ በክብር የሚቀበሉንን፣ ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚሰጡንን ብቻ ነውን? አገልግሎታችንን የሚነቅፉትን እናስተምራለን? ለራሳችን መዳን ሲባል እንድንሻሻል አስተያየት የሚሰጡንን እንወዳለን? እንግዲ ክርስቶስ ያደረገው ይመሰክርብናልና ራሳችንን እናስተምር።

በፍቅር መታዘዝን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም። መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም (ዮሐ 13:16)” ብሎ ሲናገር ደቀ መዛሙርቱን ከራሱ ጋር እያነጻጸረ ማስተማሩ ነው፡፡ ምድራዊ መሪ (ፕሬዘዳንት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር) ባለስልጣኖቹን (ሚኒስትሮቹን) ያዝዛል፤ እነርሱም እነርሱም የሚላቸውን ለመፈጸም ይታዘዙታል፡፡ አልታዘዝም ቢሉ ግን ከስልጣናቸው ወርደው ሌላ ሰው ይተካል፣ በሕግ ሊጠየቁም ይችላሉ። ክርስቲያኖች ሁሉ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ስለሆንን ፈርተን ሳይሆን ወድደንና ፈቅደን ለእርሱ መታዘዝ ይገባናል። ሰው ወይም መልአክ ሳይሆን እርሱ ራሱ ክርስቶስ ዝቅ ብሎ በተግባር አስተምሮን ሳለ፥ ዝቅ ብለን አናገለግልም ወይም ዝቅ በሎ ለማገልገል የማይፈቅድ ልቡና ካለን ግን “እኛ ከአንተ እንበልጣለን” እንደማለት ይቆጠርብናል፡፡ ይህ ደግሞ ሳጥናኤልን ያዋረደው ታላቅ ክህደት ነው።

ጌታችን ስለመታዘዝ ያስተማረበት ምሳሌም “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ አንደኛው ቀርቦ። ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ አለው። እርሱም መልሶ። አልወድም አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ።  ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው እርሱም መልሶ። እሺ ጌታዬ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም። ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው? ፊተኛው አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል (ማቴ 21:28-32)” ይላል። በዚህም በመታዘዝ የራሳችሁን ሳይሆን የሰማይ አባታችሁን ፈቃድ አድርጉ ሲል ነው። እንግዲህ ይህንን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ ሲል ለሰማይ አባታችሁ መታዘዝ እንዳለባችሁ ብታውቁ ብትታዘዙም ንዑዳን ክቡራን ናችሁ ማለቱ ነው።

ማወቅ ብቻ ሳይሆን የምታውቁትን ብትተገብሩት ብፁዓን ናችሁ።

ክርስትና ክርስቶስን መምሰል ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን አየሱስ ክርስቶስ በተግባር ዝቅ ብሎ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቦ  “እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል” የሚለውን አዲስ ትዕዛዝ ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ ማለቱ  አንድም  አንዳችሁ አንዳችሁን በትሕትናና በፍቅር በማገልገል (በመርዳት) የክርስትና ሕይወታችሁን አጽኑ ሲል ነው። አንድም እኔ በጸሎተ ሐሙስ እንዳደረግሁላችሁ እናንተም በየዓመቱ በጽሎተ ሐሙስ (ሕጽበተ ሐሙስ) የምዕመናንን እና የካህናትን እግር በማጠብ ትሕትናን በተግባር አስተምሩ ሲል ነው። አንድም በዚህች የምስጢር ቀን በተባለች ሐሙስ (ምስጢረ ቁርባንን የመሠረተባት ቀን ናትና) በሰጠኋችሁ አዲስ ኪዳን መሠረት (ይቅር በመባባል) ምስጢረ ንስሐን ፈጽሙ፣ በንስሐ ለነጹት ምስጢረ ቁርባንንም ፈጽሙ ሲል ነው (ማቴ 26:26-28)።

የመጨረሻው መልእክቱም “ጌታ ሆይ! ይህን እኮ አሳምረን እናውቀዋለን፡፡ የምናውቀውን ነገር የምትነግረን ለምንድነው?” ለሚሉት ፈሪሳውያንና ተረፈ ፈሪሳውያን “ማወቅስ ታውቁታላችሁ፡፡ ነገር ግን ንዑዳን ክቡራን የሚያሰኛችሁ አውቃችሁ ብትሠሩት እንጂ ማወቃችሁ ብቻ አይደለም” ለማለት ነው። በሉቃስ ወንጌል “የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ያ ባሪያ እጅግ ይገረፋል፤ ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል (ሉቃ.12፡47-48)” እንዳለው አይሁዳውያን ከእናንተ በላይ ቃለ እግዚአብሔርን ያውቃሉ፤ ነገር ግን አያደርጉቱምና ንዑዳን ክቡራን አይደሉም፤ እናንተ ግን ብታውቁ ብታደርጉትም ንዑዳን ክቡራን ናችሁ ሲል ነው።

እግዚአብሔርን መምሰል

እግዚአብሔርን መምሰል የሕይወታችን ተስፋ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስ ሲጽፍለት “እግዚአብሔርን ለመምሰል ግን ራስህን አስለምድ። ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፥ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል። ይህ ቃል የታመነ ሁሉም እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ይህን ለማግኘት እንደክማለንና፥ ስለዚህም እንሰደባለን፤ ይህም ሰውን ሁሉ ይልቁንም የሚያምኑትን በሚያድን በሕያው አምላክ ተስፋ ስለምናደርግ ነው። 1ኛ ጢሞ 4:7-10″ በማለት ነው እግዚአብሔርን መምሰል ያለውን ተስፋ የተናገረው። እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ እንደሆነ ሲያስተምረንም ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው (1ኛ ጢሞ 6:6)” ብሏል። ስለዚህም ለደቀመዝሙሩ “አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል (1ኛ ጢሞ 6:11)” በማለት እግዚአብሔርን መምሰልን ገንዘብ እንዲያደርግ አስተምሮታል።

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስም “የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ (2ኛ ጴጥ 1:2-3)” በማለት እግዚአብሔርን መምሰልን የተማርነው ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ጽፏል። በተጨማሪም “ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥ በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ (2ኛ ጴጥ 1:5-7)” በማለት በመጽናት እግዚአብሔርን መምሰልን፣ እግዚአብሔርን በመምሰልም ፍቅርን እንድንጨምር አስተምሮናል።

እንዲሁም የክርስቶስን ዳግም ለፍርድ መምጣት እግዚአብሔርን በመምሰል መጠበቅ እንዳለብም ሲያስተምረን “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል። የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤  ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን (2ኛ ጴጥ 3:9-13)” ብሏል።

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ለተሰሎንቄ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ እግዚአብሔርን ስለመምሰል “ደግሞ እናንተ ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀብላችሁ፥ እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ፤ ስለዚህም በመቄዶንያና በአካይያ ላሉት ምእመናን ሁሉ ምሳሌ ሆናችሁላቸው (1ኛ ተሰ 1:6-7)” በማለት በብዙ መከራ ሆነው ዝቅ ሲል ሐዋርያትን ከፍ ሲል ክርስቶስን መስለው ለሌሎች ምሳሌ እንደሆኑላቸው ተናግሯል። እነዚህ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ክርስቶስን የመሰሉት በመከራው ስለነበር ሐዋርያው “እናንተ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከአገራችሁ ሰዎች ተቀብላችኋልና (1ኛ ተሰ 2:14)” በማለት መስክሮላቸዋል።

ይህ የተወደደ ሐዋርያ “ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤ መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል (ቲቶ 2:11-14)” በማለትም እግዚአብሔርን በመምሰል እንድንኖር አስተምሮናል።

በአጠቃላይ እግዚአብሔርን መምሰል ወይም ክርስቶስን መምሰል ስንል እርሱን ምሳሌያችን ማድረግ ማለት ነው። ፍጹም የሆነ የክርስትናችን ምሳሌ ክርስቶስ ነውና። ሁሉም አንቀጸ ብፁዓን ውስጥ ፍጹም ምሳሌ የሆነን እርሱ ነው። ከዚያም ቀጥሎ በእርሱ የታመኑ ቅዱሳን ናቸው። ይህ አሥረኛው አንቀጸ ብፁዓን ማጠቃለያ ስለሆነ በዋናነት እርሱን መምሰል እንዳለብን ያስተምረናል። ለዚህም በመጀመሪያው አንቀጽ ላይ የተናገረውን የትህትናን ነገር በተግባር አሳይቶ ምሳሌ ልሆንላችሁ ይህንን እንዳደረግሁ አስተዋላችሁን አላቸው። ቅዱሳን ሐዋርያት ይህንን አስተውለው በአገልግሎታቸውም በሕይወታቸውም እርሱን ምሳሌ አድረገው እስከ ሰማዕትነት ድረስ ታመኑ፣ የክብርን አክሊልንም ከእርሱ ተቀበሉ። እኛም እንደ እነርሱ እርሱን ምሳሌ አድርገን በክርስትናችን ጸንተን መንግሥቱን ለመውረስ ያብቃን። አሜን