አቡነ ዘበሰማያት: አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር

በአብ ስም አምነን አብን ወላዲ ብለን፥ በወልድ ስም አምነን ወልድን ተወላዲ ብለን፥ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምነን መንፈስ ቅዱስን ሠራፂ ብለን፥ ምንም ለአጠይቆ አካላት ሦስት ብንል በባህርይ በህልውና በፈቃድ በሥልጣን አንድ አምላክ ብለን በማመን፤ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ በዚህች የአስተምህሮ ትምህርታዊ ጽሑፍ በአምላክነቱ የሰውን ልጅ ሁሉ ጸሎት የሚቀበል እርሱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ስትጸልዩም እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ” ብሎ ያስተማረውንና እምነትን፣ ተስፋን፣ ፍቅርን፣ ትህትናንና፣ ልመናን በአንድነት አዋሕዶ የያዘውን ጸሎት (ማቴ 6:9-13 ሉቃ 11:1-4) ማብራራት እንጀምራለን። ጽሑፋችንንም በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ጥልቅ ትምህርት ላይ እንመሠርታለን። የቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስን፣ የቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያን፣ የቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያን፣ የቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግንና የቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊንም ትምህርቶች እንጠቅሳለን። የጽሑፋችንንም ማጠንጠኛ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሊቃውንት አስተምህሮ እናደርጋለን።

ይህ ጸሎት በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን የጸሎት ሁሉ መጀመሪያና ማሳረጊያ መሆኑ ይታወቃል። የግልም ሆነ የማኅበር ጸሎት የምንጀምርበትና የምናሳርግበት፣ ከአንዱ የጸሎት ርዕስ ወደሌላው የምንሸጋገርበት የምስጋና ማዕዶት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት ያስተማረው፣ ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ሐዋርያነ አበው እንዲሁም በየዘመናቱ የተነሱ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት በቤተክርስቲያን ትውፊት ጠብቀው ያስተላለፉልን የሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ውርስ ነው። በዚህች የአስተምህሮ ጦማር በየዕለቱ የምንጸልየውን ጸሎት ትርጉም ከቅዱሳት መጻሕፍት፣ ከቅዱሳን ሊቃውንት ትንታኔና ከቤተክርስቲያን ትውፊት አኳያ እንዳስሳለን።

ንሕነ፣ ለነ፣ዚአነ/የእኛ፣ ለእኛ፣ ስለእኛ

በዚህ ጸሎት “እኔ፣ ለእኔ፣ ስለእኔ” ሳይሆን “እኛ፣ ለእኛ፣ ስለእኛ” እያልን እንጸልያለን። “አባቴ ሆይ” ሳይሆን “አባታችን ሆይ”፣ “የዕለት እንጀራዬን ስጠኝ” ሳይሆን “የዕለት እንጀራችንን ስጠን”፣ “በደሌን ይቅር በለኝ” ሳይሆን “በደላችንን ይቅር በለን”፣ “ወደ ፈተና አታግባኝ” ሳይሆን “ወደ ፈተና አታግባን”፣ “ከክፉ ሁሉ አድነኝ” ሳይሆን “ከክፉ ሁሉ አድነን” እያልን እንጸልያለን። የአንድ አባት ልጆች ነንና በግልም በማኅበርም ጸሎት ቢሆን “እኛ፣ ለእኛ፣ ስለእኛ” እያልን እንጸልያለን። በዚህም እያንዳንዳችን ስለብዙዎቻችን፣ ብዙዎቻችንም ስለእያንዳንዳችን በመጸለይ ግለኝነትንና ራስ ወዳድነትን እናጠፋለን፣ መንፈሳዊ ኅብረታችንን እናጠናክራለን። ቤተ ክርስቲያን (የምዕመናን ኅብረት) የክርስቶስ አካሉ፣ እያንዳንዳችንም ብልቶች ነንና (1ኛ ቆሮ 12:26-27) “እኛ፣ ለእኛ፣ ስለእኛ” እያልን እንደዚህ እጸልያለን። ስለዚህም ሐዋርያው “በአንድ ልብ ሆናችሁ በአንድ አፍ እግዚአብሔርን፥ እርሱም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት፥ ታከብሩ ዘንድ፥ የትዕግሥትና የመጽናናት አምላክ እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ፈቃድ እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ መሆንን ይስጣችሁ (ሮሜ 15:5)” በማለት እንዳስተማረን በአንድ ልብ፣ በአንድ አሳብ ሆነን እንጸልያለን።

አቡነ/አባታችን ሆይ

እግዚአብሔር የፈጠረን (ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣን (ዘፍ 1:26)) ልጆቹ ነንና በፍቅሩ የሚጠብቀን፣ የሚመግበን ነውና “አባታችን” እንለዋለን። ብንጠፋም ዘጠና ዘጠኙን መላእክት ትቶ የፈለገን ቸርና ይቅር ባይ አምላክ ስለሆነ “አባታችን” ብለን ጸሎታችንን ወደ እርሱ እናቀርባለን። ጌታችን ቅዱሳን ሐዋርያቱን (በተለየ አካል በሥጋዌ ከመገለጡ አስቀድሞ የተወለዱትን፣ በዕድሜ አረጋዊ የነበሩትን ጨምሮ) “ልጆች ሆይ” በማለት ጠርቷቸዋል (ዮሐ 13:33 21:5)። ይህም አባትነቱ እንደ ስጋ አባት ብቻ እንዳልሆነ ያስረዳናል። እኛም “አባታችን” ስንል እጅግ የበዛ ምሕረቱንና ሰው ሆኖ ያዳነንን እናስባለን። የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያትን የሚያወርሰን ስለሆነም አባታችን እንለዋለን። ጌታችን “አባት ሆይ” ብሎ “አባታችን ሆይ” እንድንል አርአያ ሆኖናል (ማቴ 26:42 ሉቃ 22:42)። “ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ” እንዳለው ለእርሱ የባህርይ፣ ለእኛ የጸጋ አባታችን ነውና “አባታችን ሆይ” ብለን እንጸልያለን። አንድም ስንጸልይ የክርስቶስ አካል ሆነን፣ ክርስቶስን ለብሰን፣ በመንፈስ ቅዱስ ተመርተን ስለሆነ “አባታችን” ማለታችን ምሥጢረ ሥላሴን ያጠይቃል። እንዲሁም በምሥጢረ ሥጋዌ ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ (የአብ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ) ሥጋችንን ተዋሕዶ ያዳነን መሆኑን ያጠይቃል። በምስጢረ ጥምቀትም ጌታችን ለኒቆዲሞስ “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው (ዮሐ 3:5-6)” ብሎ ባስተማረው መሠረት ዳግመኛ ተወልደን “አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብለናልና (ሮሜ 8:15)” አባታችን እንለዋለን።

ቅዱስ ጴጥሮስ “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።” (1ኛ ጴጥ 1:5) እንዳለው ዳግመኛ ስለወለደን አባታችን ብለን እንጠራዋለን። ዳግመኛ የተወለድነው ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ (1ኛ ጴጥ 1:23)። በምስጢረ ቁርባንም “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ” እንዳለው ሥጋውን በልተን ደሙንም ጠጥተን እርሱ አባቴ (የባህርይ) እንዳለው እኛም አባታችን (የጸጋ) እንለዋለን። በምስጢረ ትንሣኤ ሙታንም ዘላለማዊ መንግሥቱን እንደሚያወርሰን እያሰብን አባታችን እንለዋለን። እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋር እንደ አባትና ልጅ ያለንን መቀራረብ (የራራልን፣ የሚራራልን መሆኑን) እንገልጽበታለን። ለአንዳንዶች እንደሚመስላቸው “አባታችን” የሚለው በሥጋ አባት፣ እናት እንደምንለው “ጾታን” የሚያመለክት አገላለጽ አይደለም።

ዘበሰማያት/በሰማያት የምትኖር

በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን የስነ ፍጥረት አስተምህሮ በዓለማችን ለቅድስና አገልግሎት የተመረጡ ሰባት ሰማያት እንዳሉ ተምረናል። ከእነዚህ ሰማያት ሦስቱ የቅዱሳን መላእክት ዓለማት ናቸው። እግዚአብሔር ግን “ሰማይ ዙፋኔ ነው” እንዲል መጽሐፍ ለክብሩ መግለጫ ሰማያትን ቢጠቀምም በሰማያትም ሆነ በምድር የሚወሰን አይደለም። ስለሆነም “በሰማያት የምትኖር” ስንል በልዕልና በአርያም የምትኖር ማለት ነው እንጂ የተወሰነ ቦታን የሚያሳይ አይደለም። እግዚአብሔር ከሁሉ በላይና የሚተካከለው የሌለ መሆኑን ያመለክታል። “በሰማያት” የምንለው ከሰባቱ ሰማያት በጸሎታችን ተስፋ የምናደርጋት፣ መላእክትና ጻድቃን የሚገናኙባት መንግሥተ ሰማያትን ነው። እርስዋ የእግዚአብሔር ዙፋን ናት። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ “ሰማይ ማለት የነፍስ ንጽሕናና የእግዚአብሔር ማደሪያ መሆን ነው” በማለት ተናግሯል። ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግም “ጸሎት መሰላል ናት፣ ነፍሳችን ወደ እግዚአብሔር የምትደርስባት መሰላል። በሰማይ የምትኖር ስንል የነፍሳችን በዚህች መሰላል ወደ እግዚአብሔር መድረስን መናፈቋን ያመለክታል” ብሏል። ስለዚህም በአንቃዕዶ ልቡና ወደ ሰማያት እየሄድን “በሰማያት የምትኖር” እንለዋለን።

ጌታችንም “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ (ማቴ 5:16)፤ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም (ማቴ 18:14)፤ አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም አባት ብላችሁ አትጥሩ (ማቴ 23:9)፤ እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው? (ሉቃ 11:13)፤ ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት (ማር 11:25)” በማለት ያስተማረው ትምህርት በልዕልና ያለውን አባታችንን ያመለክታሉ።

ይትቀደስ ስምከ/ስምህ ይቀደስ

ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በቅዳሴው እንደጻፈው እግዚአብሔር በቅድስናው የተቀደሰ ነው። እርሱ በሰማያውያን መላእክት በማያቋርጥ ምስጋና ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ሲባል የሚኖር ቅዱስና ዘላለማዊ አምላክ ነው (ኢሳ 6:3 ራዕይ 4:8)። እኛ “ስምህ ይቀደስ” በማለታችን የምንጨምርለት፣ ባለማለታችንም የምናጎድልበት ቅድስና የለም። ‘ስምህ ይቀደስ’ የምንለው ስለራሳችን መንፈሳዊ ሕይወት ብለን ነው። “ስምህ ይቀደስ” ማለት ስምህ በእኛ ይቀደስ፣ ይመስገን ማለት ነው፡፡ እርሱ “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ (1ኛ ጴ 1:16)” እንዳለው ቅድስናው በሕይወታችን ይገለጥ ዘንድ “ስምህ (በአንደበታችን፣ በሕይወታችን) ይቀደስ” እንላለን። አንድም የእግዚአብሔርን ቅድስና በቃልና በሕይወት ለሰዎች በመመስከር (ማቴ 5:16) ሰዎች ቅድስናውን አውቀው ያምኑበትና ስሙን ይቀድሱ (ያመሰግኑ) ዘንድ፣ ቅድስናንም ገንዘብ ያደርጉ ዘንድ “ስምህ ይቀደስ” ብለን እንጸልያለን። እግዚአብሔር አስቀድሞ ለሙሴ “እኔ ግን በእስራኤል ልጆች መካከል እቀደሳለሁ” (ዘሌ 22:32) እንዳለው እኛም እስራኤል ዘነፍስ ስሙን በቃልና በሕይወት/በምግባር እንቀድሳለን፣ በዚህም እንቀደስበታለን።

እኛ ስሙን ልንቀድስ ክብሩንም ልንወርስ ተፈጥረናልና “ስምህ ይቀደስ” ብለን እናመሰግነዋለን። “ስምህ” የምንለው የእግዚአብሔርን ኃያልና ጽኑዕ ስም ነው። ስሙ መሐሪና ይቅር ባይ ነው። “ስምህ” ስንልም በሕልውና ለዘላለም የሚኖረውን የባህርይ አምላክ እግዚአብሔርን ማለታችን ነው። ይህም ሰማይና ምድር ካለፉ በኋላ በመንግሥቱ ሲገለጥ ከቅዱሳን መላእክት ጋር የምናመሰግነውን ምሥጋና እየናፈቅን ነው። ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ “ጌታ ሆይ፥ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና” (ራዕ 15:4) እንዳለው በዚያች ቀን ስሙን እናከብራለን። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “በዚያም ቀን በቅዱሳኑ ሊከብር፥ ምስክርነታችንንም አምናችኋልና በሚያምኑት ሁሉ ዘንድ ሊገረም ሲመጣ” (2ኛ ተሰሎ 1:10) እንዳለው ያችን በቅዱሳኑ የሚከብርበትን ቀን እየናፈቅን ስምህ ይቀደስ እንላለን። ወንጌላዊው ዮሐንስም በመልእክቱ “ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን” (1ኛ ዮሐ 3:2) የእርሱን በክብር መገለጥ እያሰብን “ስምህ ይቀደስ” እንላለን።

ትምጻእ መንግሥትከ/መንግሥትህ ትምጣ

ጌታችን “የእግዚአብሔር መንግሥት እንሆ በመካከላችሁ ናት” ብሎ አስተምሮናል (ሉቃስ 10:20-21)። ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት የምትመጣ፣ የምትሄድ አይደለችም። መንግሥትህ በልባችን ትገለጽልን በሉ ሲለን ነው እንጂ። እኛም ሁላችን ሰማያዊ ዜግነታችን ከዚያ ነው (ፊልጵ 3:20)። ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ “የእግዚአብሔር መንግሥት የምትመጣው ክርስቶስ በልባችን አድሮ ሕይወታችን ሲለወጥ” ነው በማለት አስተምሯል። በዚህ መሠረት “መንግሥትህ ትምጣ” ስንል ክርስቶስ በልባችን አድሮ ሕይወታችን ትለወጥ ማለታችን ነው። ይህም የሚፈጸመው በምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ቁርባኑ ነው። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ “የእግዚአብሔር መንግሥት ፍትሕና ምሕረት የነገሠባት፣ በጸጋ ወደ ፍጹምነት የደረሰች ነፍስ ናት፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ ያለአንዳች መከልከል ይፈጸምባታልና” ብሏል። ስለዚህ “መንግሥትህ ትምጣ” ስንል ነፍሳችንን ፍጽምት አድርግልን ማለታችን ነው። ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ደግሞ “የእግዚአብሔር መንግሥት በንጽሐ ልብ በሚያምኑት ውስጥ የተተከለች ገነት ናት” በማለት ተናግሯል። እኛም “መንግሥትህ ትምጣ” ስንል በልባችን ውስጥ ይህችን ገነት ትከልልን እያልን ነው።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በበኩሉ “የእግዚአብሔር መንግሥት በሁሉም ቦታ፣ ለሁሉም ሰው ቃለ ወንጌል የሚሰበክባት ቤተ ክርስቲያን ናት” ሲል ገልጿታል። እኛም “መንግሥትህ ትምጣ” ስንል “ቤተ ክርስቲያናችንን በሁሉም ቦታ፣ ለሁሉም ሰው ቃለ ወንጌል የሚሰበክባት አድርግልን” ማለታችን ነው። ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም ደግሞ የእግዚአብሔር መንግሥት መምጣት ሲገልጽ “የዲያቢሎስ መሸነፍ የእውነት መንገሥ ነው” ብሏታል። እኛም “መንግሥትህ ትምጣ” ስንል እውነት ትንገሥ ማለታችን ነው። ሁሉም ቅዱሳን አበው ግን የእግዚአብሔር መንግሥት መምጣት ማለት የክርስቶስ ዳግም መምጣት እንደሆነ አስምረውበታል። ስለዚህ “መንግሥትህ ትምጣ” ስንል የእርሱን መምጣት (ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምንገባባትን ዕለተ ምፅዓትን) እየናፈቅን ነው።

ወይኩን ፈቃድከ በከመ በሰማይ ከማሁ በምድር/ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን

ይህ ለራሳችን ፈቃድ ሳይሆን ለእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንገዛ መሆናችንን የምንገልጽበት ነው። ጌታችንም በጌቴሴማኒ መከራን ለመቀበል ሲዘጋጅ “ፈቃድህ ትሁን” በማለት አብነት ሆኖናል (ማቴ 26:42 ሉቃ 22:42)። ቅዱሳን ሐዋርያትም እንዲሁ (ሐዋ 21:14 1ኛ ጴጥ 4:19 1ኛ ዮሐ 2:17)። የእግዚአብሔር ፈቃድ የሰው ልጆች ሁሉ ከኃጢአታቸው በንስሐ ነጽተው በቅድስና እርሱን መስለው እንዲኖሩ ነው (ቅዱስ አትናቴዎስ)። በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር ፈቃድ የሰማይ መላእክት ለእግዚአብሔር በፍጹም መታዘዝ ያለማቋረጥ የሚያመሰግኑት ነው፣ እኛም በቅድስና ሕይወት በምድር እንደ መላእክቱ ልናመሰግነው ፈቃዱ ነው (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)። የሥጋ ፈቃድ ለእግዚአብሔር ፈቃድ እንዳንገዛ ይከለክለናል፣ በዚህ ጸሎትም ከእርሱ ፈቃድ ውጭ የሥጋም ሆነ የኃጢአት ፈቃድ እንዳይገዛን እንጠይቃለን (ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ)። የእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉም ሰው ወደ እውነት እውቀት እንዲመጣና እንዲድን ነው፣ ይህ የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ይሳካ ዘንድ በዚህ ጸሎት እንጠይቀዋለን (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚህ “ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው” (1ኛ ጢሞ 2:4) ብሏል። የእግዚአብሔር ፈቃድ ለእኛ በጎ የሆነ ሁሉና መዳናችን ነው (ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ)። ዋናውና የመጨረሻው የእግዚአብሔር ፈቃድ ግን የሰው ልጅ ወደ ቀደመ ክብሩ መመለሱ ነው፣ ይህም ፍጹም የሚሆነው የሚታየው ዓለም አልፎ የማይታየው ዓለም ሲመጣ ነው።

ሲሳየነ ዘለለ ዕለትነ ሀበነ ዮም/የዕለት ምግባችንን ስጠን ዛሬ

“የዕለት ምግባችንን ስጠን” ስንል በቀጥታ ትርጉም ለሥጋዊ ሕይወታችንን የሚያስፈልገንን ስጠን ማለታችን ነው። ‘የዕለት’ ማለታችንም የሚበቃንን ያህል ማለታችን ነው፣ የቅንጦት ወይም የተትረፈረፈ አንጠይቅም (ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ)። ‘ምግባችንን’ የሚለውም ለመሠረታዊ ፍላጎታችን ብቻ መጠየቃችንን ያመለክታል (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ማቴ 6:25-34)። ‘ዛሬ (this day)’ ማለታችንም ለዛሬ የሚሆነንን ስጠን፣ ለነገም እንደምት ሰጠን የታመንህ ነህ ማለታችን ነው። ‘የዕለት ምግባችንን’ ስንል ነፍሳችንን ለዘላለማዊ ሕይወት የሚያበቃውን ከሰማይ የወረደ መና የተባለውን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ማለታችን ነው (ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ)። ከቅዱስ ምስጢር እንሳተፍ ዘንድ ‘የዕለት ምግባችንን ስጠን’ እንላለን። እርሱ “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና (6:54-55)” ብሏልና።

አንድም የነፍስና የሕሊና ምግብ የሚሆነውን ቅዱስ ቃሉን ይመግበን ዘንድ “የዕለት ምግባችንን ስጠን” እንለዋለን (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)። አንድም የዕለት ምግብ በእምነት የሚያጸና፣ ወደ መልካም ምግባር የሚመራ፣ በፈተና የሚያበረታ የመንፈስ ስጦታን ያመለክታል (ቅዱስ ባስልዮስ)። በመጨረሻም “አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ ከማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፥ በአሥራ ሁለቱ በእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዙፋኖች ትቀመጡ ዘንድ ለመንግሥት እሾማችኋለሁ” (ሉቃ 22:30) እንደ ተባለው በክርስቶስ በማመናችን ፈቃዱንም በመፈጸማችን የሚገኘውን ዘላለማዊ ክብር ስጠን ማለታችን ነው። “ሲሳየነ” የሚለው የግእዝ ቃል በአማርኛ “እንጀራችንን”፣ በእንግሊዝኛ “ዳቧችን (bread)” ተብሎ ተተርጉሟል። ነገር ግን “ምግባችን” የሚለው ቃል ለግእዙ የሚቀርብ ስለሆነ እርሱን ተጠቅመናል። ዋናው መልእክት ግን እንጀራም፣ ምግብም ብቻ ሳይሆን ለሥጋችንም፣ ለነፍሳችንም የሚያስፈልገንን ሁሉ የምንጠይቅበት ጸሎት መሆኑ ነው። ይህንንም የሚያረጋግጥልን በግሪኩ ያለው ቃል ἐπιούσιον (epiousion) ትርጉሙ ለሕይወት (ለሥጋዊም ለመንፈሳዊም) የሚያስፈልገንን የሚል መሆኑ ነው።

ኅድግ ለነ አበሳነ ወጌጋየነ ከመ ንህነኒ ንኅድግ ለዘአበሰ ለነ/በደላችንንም ይቅር በለን እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል

እኛ የበደሉንን ይቅር ስንል እግዚአብሔር እኛን ይቅር ይለናል (ማቴዎስ 6:13-15)። ይቅር ማለት እግዚአብሔር እኛንም ይቅር እንዲለን በር ትከፍታለች (ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ)። የበደሉንን ይቅር ስንል እግዚአብሔርን እንመስለዋለን (ቅዱስ አትናቴዎስ)። ይቅር ማለት የእግዚአብሔር ልጆች ልብስ ናት (ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ)። ይቅር ማለት ልባችንን ከክፉ ሀሳብና ኃጢአት ንጹሕ ታደርጋለች። ይቅር ማለት የበደለውንም የተበደለውንም ታድናለች (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ)። ክርስቲያናዊ አንድነታችንንም ታጠናክራለች። ይቅርታ ማድረግ ክርስቶስ በመስቀል ላይ “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ብሎ የሰጠንን ይቅርታ ታጠይቃለች። ለመጨረሻው የፍርድ ቀንም የተዘጋጀን ታደርገናለች። ይቅር የሚሉ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይገባሉ፣ ይቅርታን የማያደርጉ ግን በውጭ ይቀራሉ። እዚህ ላይ “ይቅር እንደምንል” ስንል ላለፈው ጊዜ ወይም ለሚመጣው ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁል ጊዜ በሕይወታችን ዘመን ሁሉ መሆኑን ልብ ይሏል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “በቁጣችሁ ፀሐይ አይግባ ለዲያብሎስም ፈንታ አት ስጡት” (ኤፌሶን 4:27) እንዳለው በየዕለቱ ይቅር ማለት ይኖርብናል።

በሌላ በኩል “እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል” የሚለው የአማርኛው ሐረግ ውስጥ “እንደምንል” የሚለው ቃል ግልጽነት ላይ የተወሰነ ግርታ ይስተዋላል። በአንድ ወገን “እንደምንል” ማለት ለእግዚአብሔር ለማሳየት መሞከር ያስመስልብናል የሚሉ ወንድሞችና እኅቶች “እንድንል” በሚለው ለመተካት ይሞክራሉ። ሌሎች ደግም አስቀድመን እኛ የበደሉንን ይቅር ማለት ስላለብን “እንዳልን” ወደሚለው ቃል ያዘነብላሉ። ከቅዱሳት መጻሕፍት ያለው ቃል ግን “እንደምንል (as we forgive)” የሚለው ሲሆን የድርጊት ቅደም ተከተልንም ይሁን ለእግዚአብሔር ለማሳየት መሞከርን አያመለክትም። እኛ በደሉንን ይቅር ስንል እግዚአብሔርም እኛን ይቅር እንደሚለን የሚያመለክት ቃል ነው።

የበደሉንን ይቅር ሳንል ይህን ብንል ግን “አስቀደመህ ከወንድምህ ታረቅ (ማቴ 5:24)” የሚለው ቅዱስ ቃል ይወቅሰናል። እኛ የበደሉንን ይቅር ሳንል “በደላችንን ይቅር በለን እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል” ብለን ብንጸልይ የተናገርነው ቃል ራሱ ይፈርድብናል። ለሌሎች እንዳደረግነው ለእኛም ይደረግልናል። እኛ ለማድረግ የማንወደውን ይቅርታ ለእኛ እንዲደረግልን መጠበቅ የለብንም። በሥርዓተ ቅዳሴውም ዲያቆኑ “ይህ የአባቶቻችን የሐዋርያት ትእዛዝ ነው። ሰው በልቦናው ቂምንና በቀልን ቅንዓትንና ጠብን በባልንጀራው ላይ በማንም ላይ ቢሆን አይያዝ” በማለት ያውጃል። እንዲሁም በቅዳሴ እግዚእ “ነፍሳችሁን ተመልከቱ፡ ስውነታችሁን ንጹሕ አድርጉ፡ የባልንጀራችሁንም በደል አታስቡ፡ እግዚአብሔር ያያል፡ ልቡናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ፡ ወደ ሕይወት መድኃኒት እንቅረብ፡ ጸጋ ሆኖ የተስጠንንም ሥጋውንና ደሙን በእግዚአብሔር ጥበብ እንቀበል” በማለት ባልንጀራችንን ይቅር እንድንል ያዘናል።

ኢታብአነ እግዚኦ ውስተ መንሱት/አቤቱ ወደ ፈተናም አታግባን

ይህንን የምንለው እግዚአብሔር ወደ ፈተና የሚያስገባ አምላክ ሆኖ አይደለም። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ “ማንም ሲፈተን በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል” (ያዕ 1:13-14) እንዳለው እግዚአብሔር ሰውን አይፈትንም። ለፈተና አትተወን፣ በፈተናም እንዳንወድቅ አበርታን ለማለት ነው እንጂ። እኛ በእግዚአብሔር ላይ ተደግፈን የምንኖር ደካሞች ነን፣ እግዚአብሔር ካልረዳን በቅጽበት እንወድቃለን (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)። በዚህም እኛ ፈተና የሚያሸንፈን ደካማ መሆናችንን ገልጸን መለኮታዊ እርዳታን የምንጠይቅበት ጸሎት ነው። ፈተና የሚባለውም ማንኛውም ከመልካም ወደ መጥፎ ነገር የሚወስድ ሁሉ ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኛ ጋር ከሌለ ፈተና አስከፊ ይሆንብናል። ስለዚህ ብርታት የሚሆነንን መንፈስ ይሰጠን ዘንድ “ወደ ፈተና አታግባን” እንለዋለን (ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ)። ወደ ፈተና አታግባን ስንልም ፈተና የብርሃን ወይም የጨለማ ልጆች መሆናችን የሚለይበት ነውና ከጨለማው አበጋዝ ከዲያብሎስ የፈተና መረብ ጠብቀን ማለታችን ነው። በአጠቃላይ ተፈትኖ ከመውደቅ ጠብቀን ማለታችን ነው።

አላ አድኅነነ ወባልሓነ እምኲሉ እኩይ/ከክፉ ሁሉ አድነን እንጂ

‘እኩይ/ክፉ’ የተባለ በዋናነት ሰይጣን (ዲያብሎስ) ነው። እርሱ የክፋት ሁሉ ምንጭ ነውና ከሚዋጋን ከእርሱ ጠብቀን ስንል “ከክፉ ሁሉ አድነን” እንላለን። አንድም ‘ክፉ’ የተባለ ኃጢአትና በኃጢአት ምክንያት የሚመጣ ሞት ነው፣ በኃጢአት ባርነት ከመያዝ አድነን ስንል “ከክፉ ሁሉ አድነን” እንለዋለን። አንድም ‘ክፉ’ ከተባለ በውስጣችን ካለ ክፉ ሀሳብና የሥጋ ፍላጎት አድነን ማለታችን ነው። ወደ ኃጢአትና ወደ ሞት የሚመራው ይህ ነውና። በሌላም መልኩ ከምናየውና ከማናየው ጠላት፣ ከሚጎዳን ክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቀን ዘንድ ነው (ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም)። እንዲሁም በመንፈሳዊ ውጊያ ብርታትን እናገኝ ዘንድ፣ ይህንንም ድል አድረገን ለጽድቅ እንድንዘጋጅ ነው። በመጨረሻም ‘ክፉ’ ከተባለ የገሃነመ እሳት ፍርድ አድነን ማለታችን ነው።

እስመ ዚኣከ ይእቲ መንግሥት ኃይል ወስብሐት ለዓለመ ዓለም/መንግሥት የአንተ ናትና ኃይል ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ

በምስጋና የጀመርነውንና በልመና የቀጠልነውን ጸሎት በምስጋና ለመዝጋት “መንግሥት ያንተ ናትና” ብለን ዘላለማዊ መንግሥቱን፣ ከሁሉ በላይ የሆነ፣ የፍጥረት ሁሉ ገዥ እርሱ ብቻ መሆኑን እንመሰክራለን። የጠየቅነውን ሁሉ ሊሰጠን ፈቃዱ ብቻ ሳይሆን የሚችል ኃያል አምላክ እንደሆነና እንደምንታመንበትም እናረጋግጣለን። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስም መንግሥት፣ ኃይል፣ ምስጋና ከአብ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ (አንድነትና ሦስትነት) ጋር አያይዞ አስተምሯል። ይህም “አንድ አምላክ አንዲት መንግሥት አንዲት ሥልጣን አንዲት አገዛዝ” እንደሚለው ያለ ነው። ክቡር ዳዊትም “አቤቱ፥ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና ታላቅነትና ኃይል፥ ክብርም፥ ድልና ግርማ ለአንተ ነው፤ አቤቱ፥ መንግሥት የአንተ ነው” (1ኛ ዜና 29:11) እንዳለው ይህ ምስጋና አስቀድሞ የነበረ ነው። ጻድቁ ኢዮብም “ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደሆንህ አሳብህም ይከለከል ዘንድ እንደማይችል አወቅሁ” በማለት እንደገለጸው (ኢዮብ 42:2) ኃይል፣ ክብር ምስጋና ላንተ ይሁን እንላለን። በመጨረሻም ክርስቶስ በኃይልና ክብር ዳግመኛ እንደሚመጣ ዘላለማዊ መንግሥቱንም እንደሚያወርሰን ያለንን እምነትና ተስፋ የምንገልጽበት የጸሎት ክፍል ነው። ‘አሜን’ ማለታችንም ያቀረብነው ምስጋና እውነት መሆኑን የምናረጋግጥበት ‘የቃል ፊርማችን’፣ የለመንነው ልመና እንዲፈጸምልን በእምነት የምንማጸንበት የእምነት ተስፋችን ነው።

ማጠቃለያ

ይህ ጌታችን ያስተማረን “አባታችን ሆይ” ብለን የምንጸልየው መሠረታዊ (Foundational) ጸሎት በዘወትር ጸሎት፣ በቅዳሴና በሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶች ሁሉ የምንጸልየውና ብዙዎቻችን በቃላችን የምናውቀው፥ በይዘቱ አጭር በምስጢሩ ግን እጅግ ጥልቅ የሆነ ጸሎት ነው። ይህ ጸሎት የአምልኳችን መሠረት ሲሆን ከፈጣሪያችን ጋር ዘወትር የምንነጋገርበት መገናኛ ድልድይ ነው። በውስጡም ትላንትና፣ ዛሬ፣ ነገና እስከ ዘለዓለም ያለውን አስተምህሮ የያዘ ነው። ይህ ጸሎት ጌታችን “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” (ማቴ 6:33) በማለት ያስተማረው በግልጽ የሚታይበት ነው። ይህንን ጸሎት ስንጸልይ ጥልቅ ምስጢሩንም ለመረዳት ያግዘን ዘንድ ይህችን ጽሑፍ አዘጋጅተናል። ይህም ውቂያኖስ ከሆነው የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አንዲት ጠብታ የማንሳት ያህል ነውና በዚህች ጽሑፍ የቀረበው ውስን ብቻ መሆኑን እየገለጽን ሰፊውን አስተምህሮ አንባቢያን ከዋናው ምንጭ ይቀዱ ዘንድ እንጋብዛለን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ኃይል፣ ክብር፣ ምስጋና ለዘለዓለሙ አሜን።

Leave a comment