ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡

ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡

አዎን! ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ሐዋርያት ነበሩ፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን የመሠረተው በሐዋርያት መሠረትነት ላይ ነው “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ አንተ ብጹዕ ነህ . . . እኔም እልሃለሁ አንተ ዐለት ነህ በዚይች ዐለት ላይም ቤተ ክርስቲያኔን አሠራታለሁ የሲዖል በሮችም አይበረታቱባትም፡፡ የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ ይሆናል በምድርም የምትፈታው በሰማይ የተፈታ ይሆናል”ማቴዎስ 16 ፥ 15፡፡

ከትንሣኤው በኃላም “ሰላም ለእናንተ ይሁን አብ እኔን እንደላከኝ እንዲሁ እኔ እናንተን እልካችኃለሁ ይህንንም ብሎ እፍ አለባቸውና እንዲህም አላቸው መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኃቸው ይሰረይላቸዋል ይቅር ያላላችኃቸው ግን አይሰረይላቸውም” ዮሐንስ ወንጌል 20 ፥ 22፡፡

ከላይ በተገለጸው መሰረት ቤተ ክርስቲያንን የመምራትና የማስተዳደር ስልጣንን ሐዋርያት ከጌታ ተቀብለዋል፡፡ቅዱስ ጳውሎስም “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሄርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” የሐዋሪያት ሥራ 20 ፥ 28፡፡ በማለት ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ልትመራ እንደሚገባ አስገንዝቦናል ሲኖዶስ ማለት የጳጳሳት ጉባኤ መሆኑን ልብ ይልዋል፡፡ ቤተክርስቲያንም ሐዋርያዊት ናት ስንል ሐዋርያዊት የሆነችው በሦስት ነገሮች ነው፡፡

በሢመት ሀረግ፡- ከሐዋርያት አንስቶ ያልተቋረጠ የሢመት ሀረግ መኖሩ ቤተክርስቲያንን ሐዋርያዊት አድርጓታል፡፡ ጌታችን ለሐዋርያቱ የሰጠው የክህነት ስልጣን ሳይቋረጥ በቀጥታ እየተላለፈ መምጣቱ አንዱ የሐዋርያዊትነቷ መገለጫ ነው፡፡

በትውፊትና በምሥጢር፡-  ቤተክርስቲያን የሐዋርትን ትውፊት ተቀብላ መተግበሯ ሐዋርያዊት አድርጓታል፡፡ እንደ ሐዋርያት ሲኖዶስ አላት፡ እንደ ሐዋርት ታጠምቃለች፡ እንደ ሐዋርያት ትቀድሳለች፡ ሥጋና ደሙን ታቀብላለች፡፡ ሐዋርያት የሠሩትን እንደ ሐዋርያት አድርጋ ትሠራለች፡፡ ከሐዋርያት የተለየ ሥርዓት ሊኖራት አይችልም፡፡ ይህ የሐዋርያዊትነቷ ሌላው መገለጫ ነው፡፡

በመጻሕፍት ትርጓሜ፡- ሐዋርያዊ ክትትሉን የጠበቀ የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ስላላት ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡ ሐዋርያት እንደተረጎሙት አድርጋ ትተረጉማለች፡፡ ሐዋርያት እንዳስተማሩት አድርጋ ታስተምራለች፡፡ ሐዋርያት ያላስተማሩትን አታስተምርም፡፡ በዚህም ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡

ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ በቅዱስ ሲኖዶስ መመራት የጀመረችው ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ለመሆኑ ምሥክሩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ የመጀመሪያው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የተደረገበትን ምክንያት ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ግብረ ሐዋርያትን በገለጸበት ጽሑፉ ላይ እንዲህ ተርኮታል፡- አንዳንዶችም ከይሁዳ ወረዱና፥ እንደ ሙሴ ስርዓት ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም ብለው ወንድሞችን ያስተምሩ ነበር፡፡ በእነርሱና በጳውሎስ በበርናባስም መካከል ብዙ ጥልና ክርክር በሆነ ግዜ ስለዚህ ክርክር ጳውሎስና በርናባስ ከእነርሱም አንዳንዶች ሌሎች ሰዎች ወደ ሐዋርያት ወደ ቀሳውስቱም ወደ ኢየሩሳሌምም ይወጡ ዘንድ ተቆረጠ። . . .በሐዋርያት ያደረ ቅዱስ መንፈስ በቅዱስ ጳውሎስም ያደረ ሆኖ ሳለ ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ ሌሎች ሰዎችን ጨምረው ለምን? ወደ ሐዋርያት መሄድ አስፈለጋቸው? የሚለው መጠይቅና መልሰ የቤተ ክርስቲያን እርከናዊ መዋቅር ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ የነበረ መሆኑን ያስገነዝበናል ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለተዋቀረው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የተገዙ መሆናቸውን ያሳያል ምክንያቱም ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቁና ያስተዳድሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳት አድርጎ የሾማቸው ናቸውና። ስለዚህ ለመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻው ወሳኝ አካል እነርሱ ነበሩ ይህ ሐዋርያዊ ውርስ ባላት የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንም የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ለዚህም ነው ሲኖዶሳዊት ያልሆነች ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት አይደለችም የምንለው፡፡

ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደ ምንረዳው የመጀመሪያው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ በሐዋርያው በቅዱስ ያዕቆብ ሊቀ መንበርነት ከ49 – 50 ዓ.ም ባለው ግዜ የተካሄደው ከላይ በተገለጸው መሠረት ከአሕዛብ ወገን ክርስትናን በተቀበሉና ከአይሁድ ወገን ክርስትናን በተቀበሉት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ለዚያ እልባት ለመስጠት ነበር ሐዋርያትም ግራ ቀኙን አድምጠው የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥተዋል።ሐዋርያትና ቀሳውስት ወንድሞችም በአንጾኪያና በሶርያ በኪልቅያም ለሚኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለሆኑ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርባሉ፡፡ ያላዘዝናቸው ሰዎች ከእኛ ወጥተው ትገረዙ ዘንድና ሕግን ትጠብቁ ዘንድ ይገባችኃል ብለው ልባችሁን እያወኩ በቃል እንዳናወጡአችሁ ስለ ሰማን ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነፍሳችውን ከሰጡት ከምንወዳቸው ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር የተመረጡትን ሰዎች ወደ እናንተ እንልክ ዘንድ በአንድ ልብ ሆነን ፈቀድን፡፡ራሳቸውም ደግሞ በቃላቸው ያንኑ ይነግሩአችሁ ዘንድ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል፡፡ ለጣዖት ከተሠዋ ከደምም ከታነቀም ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናል ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ ጤና ይስጣችሁ፡፡ ” የሐዋርያት ሥራ 15 ፥ 22 – 29፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከምድረ ፍልስጤም ወደ ሌሎቹ የሮማ ግዛቶች ግዛትዋን እያሰፋች በመጣች ግዜም መዋቅርዋ፤ ሐዋርያዊ ሠንሰለቱ እንደተጠበቀ ነበር፤ ከቤተ አይሁድም ከቤተ አሕዛብም የመጡ ከሐዋርያት የሰሙ ከሐዋርያት የተማሩ ሐዋርያውያን አባቶች በሐዋርያት መንበር እየተተኩ ሠንሰለቱ ሳይበጠስ ቀጥሉዋል እንደ ኤሬኒዮስ ናኤጲፋንዮስ አገላለጽ በቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ላይ ከቅዱስ ጴጥሮስ ቀጥሎ ደቀ መዝሙሩ የነበረው ሊኖስ ሲሆን (የዚህ አባት ስም በ2ኛ ጢሞቲዎስ 4 ፥ 21 ላይ ተጠቅሱዋል) አውሳብዮስ ግን የቅዱስ ጴጥሮስ ወራሴ መንበር ቀሌምንጦስ ነው ይላል፡፡ በቅዱስ ማርቆስ መንበር ላይ ቅዱስ ማርቆስ አሰተምሮ ያሳመነው፣ ያጠመቀውና በክህነት የወለደው ጫማ ሰሪ የነበረው አናንያስ ነበር የተሰየመው ፤ የቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረው ፖሊካርፕ እንዲሁም ሌሎችም ከሐዋርያት በቀጥታ ቤተ ክርስቲያንን የማስተዳደር ስልጣንን ተቀብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት የምንለው በሐዋርያው በቅዱስ ፊልጶስ አማካይነት በ34ዓ.ም ጥምቀትን ተቀበለች፥ በኃላም በአራተኛው ምዕተ ዓመት በሲኖዶስ ሕግ በቅዱስ ማርቆስ መንበር ሥር የተዋቀረች በመሆኑ ነው፡፡ የራስዋ መንበር ባለቤት የሆነችውም ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን በዓመጽ ተገንጥላ ሳይሆን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት በሥርዓቱ ነው፡፡ ለዚህም አባቶቻችን አያሌ ዘመናት በትእግስት የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያንን ደጅ ጠንተዋል፡፡ይህም የሐዋርያዊ ውርስ ሠንሰለቱ እንዲጠበቅ የከፈሉት መሥዋዕትነት ነው፡፡

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s