ቤተክርስቲያን ዘላለማዊትና የማትታደስ ናት፡፡
ዘላለማዊነት አንዱ የቤተክርስቲያን መገለጫ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ዘላለማዊት ናት፡፡ መሠረቷ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ ነውና እርሷም ዘላለማዊት ናት፡፡ በአካለ ሥጋ ያሉ ክርስቲያኖችና በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን ከክርስቶስ ጋር ያላቸው አንድነት ዘላለማዊ ነውና ቤተክርስቲያንም ዘላለማዊት ናት፡፡ ዘላለማዊ ናት ስንል ዘላለማዊነቷ በመጠበቅ (ጠብቆ ይነበብ) እንጂ በመታደስ (እየታደሰች) አይደለም፡፡ ክርስቶስ የምታረጅ፣ የምትለወጥ ወይም የምትጠፋ ቤተክርስቲያን አልመሠረተም፡፡ የማያረጅ ነገር ደግሞ አይታደስም፡፡ ሁል ገዜ አዲስ ነውና፡፡ ከዚህ ውጭ ቤተክርስቲያን ትታደስ ማለት ግን የሚከተሉትን መሠረታዊ ስህተቶች/ክህደቶች ያስከትላል፡፡
- ቤተክርስቲያን ትታደስ ማለት፡- ሐዋርያዊ መሠረት አያስፈልጋትም በየጊዜው ሌላ መሠረት ያስፈልጋታል ማለት ነው፡፡
- ቤተክርስቲያን ትታደስ ማለት፡- መሥራቿ አጉድሎ ነው የመሠረታት ናትና እኛ እናሟላት እንደማለት ነው፡፡
- ቤተክርስቲያን ትታደስ ማለት፡- በእርሷ የነበሩ በእርሷ የኖሩ አልፀደቁም እንደማለትም ነው፡፡
- ቤተክርስቲያን ትታደስ ማለት፡- የምትፈጽማቸው ምሥጢራት ለድኅነት አያበቁምና ይሻሻሉ ማለት ነው፡፡
- ቤተክርስቲያን ትታደስ ማለት፡- እኛ ከቀደሙት የተሻልን ነንና የተሻለች ቤተክርስቲያን እንመሥርት እንደማለት ነው፡፡
ስለዚህ ቤተክርስቲያን ትታደስ የሚለው አስተሳሰብ መሠረታዊ ስህተት ነው፡፡ አምስቱ አዕማደ ምሥጢራት የሚቀየሩ ወይም የሚሻሻሉ አይደሉም፡፡ ጸንተው የሚኖሩ እንጂ፡፡ ነገር ግን ሁለት በቤተክርስቲያን ዘንድ እድሳት የሚያስልጋቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነርሱም የቤተክርስቲያን አስተዳደርና የክርስቲያኖች ሕይወት ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ከቤተክርስቲያን አስተምህሮ አንጻር በየጊዜው እየታዩ ሊሻሻሉ ይችላሉ፡፡ አስተዳደሩን ማዘመን ያስፈልጋል፡፡ የምዕመናን ሕይወት ደግሞ በንስሐ እየታደሰ ይኖራል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ሰውን የምታድሰው ቤተክርስቲያን እራሷ አትታደስም፡፡