የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት መሠረታዊ ዓላማዎች

Focus areasየልጆች መንፈሳዊ ትምህርትን ስናስብ በቅድሚያ ትኩረታችንን የሚስበው ይዘቱ (‘ምን ይማሩ?’ የሚለው) ነው። ወላጆችም ቢሆኑ ስለልጆቻቸው ትምህርት ሲያስቡ በቅድሚያ ማወቅ የሚፈልጉት ‘ምንድን ነው የሚማሩት?’ የሚለውን ነው። ልጆቻቸውንም ‘ምን ተማራችሁ?’ ብለው ነው የሚጠይቁት። የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት የሚመራበት ሥርዓተ ትምህርትም ተቀዳሚ ትኩረቱ ‘ልጆች ምን ይማሩ?’ የሚለው ጉዳይ ነው። ይህም የሥርዓተ ትምህርቱ መሠረት ነው። የመምህራን ምደባም ይሁን የትምህርቱ ስልት በትምህርቱ ይዘት ላይ ተመሥርቶ ነው የሚወሰነው። በዚህም መሠረት የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት ዋና ዓላማ ልጆች በመንፈሳዊና በሥጋዊ ሕይወታቸው ብቁ እንዲሆኑ ማስቻል ነው:: የመንፈሳዊ ሕይወታቸው ብቃትም በእምነታቸው ጽናትና በክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባራቸው ይገለጣል:: እያንዳንዱ መንፈሳዊ ትምህርትና ሥልጠና ይህን ታሳቢ ማድረግ ይኖርበታል::

ከዚህም አንጻር የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት ዋና ዋና ዓላማዎች የልጆችን እድሜና የቋንቋ ችሎታን ባገናዘበ መልኩ መንፈሳዊ ዕውቀትን፣ በጎ አመለካከትን፣ ክርስቲያናዊ እሴትንና የመንፈሳዊ አገልግሎት ክህሎትን እንዲያዳብሩ ማስቻል ነው:: እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሙሉ ክርስቲያናዊ ስብዕና የሚገነባው በዕውቀት ወይም በምግባር ላይ ብቻ ባተኮረ ትምህርት ሳይሆን በእነዚህ በአራቱም ላይ በሚያጠነጥን ተከታታይና ዘላቂነት ባለው ትምህርትና ተሞክሮ ነው:: በዘመናችን የሚታየው የመንፈሳዊ ሕይወት ዝለት አንዱና ዋናው መነሻ መንፈሳዊ ትምህርቶች ከነዚህ ከተጠቀሱት መሠረታዊ ዓላማዎች በአንዱ (በተለይ በዕውቀት ላይ) ወይም በሁለቱ ላይ ብቻ ስለሚያተኩሩ ነው:: እኛም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር የልጆችና መንፈሳዊ ትምህርት ዋና ዋና ዓላማዎች እንዳስሳለን፡፡

እምነት፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነትን በሚገባ ማሳወቅ

ልጆች በመንፈሳዊው ትምህርታቸው ስለ እግዚአብሔር አምላክነት፣ ስለፍጥረታት አፈጣጠር፣ በአጠቃላይ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ፣ እንዲሁም ስለቤተክርስቲያን ታሪክና ፈተናዎች በቂ ዕውቀትን እንዲጨብጡ ማስቻል ያስፈልጋል::  የልጆች  መንፈሳዊ ትምህርት ማካተት ከሚገባቸው አርዕስት መካከልም የእግዚአብሔር ባሕርይ እና ፈጣሪነት፣ ዓለማትን እንዴት እንደተፈጠሩ፣ የሰው ልጅ አፈጣጠርና የእግዚአብሔር ጥበቃ፣ ቅዱሳን መላእክትና ሰዎች እና ሥራቸው፣ ስለ ከበሩ ንዋየ ቅድሳት (ታቦትና ጽላት የመሳሰሉት)፣ ስለ ጌታችን ሥጋዌ (ሰው መሆን)፣ በነገረ ድህነት የእመቤታችን ድርሻ ክብርና ሕይወት፣ ጌታችን ያስተማረው ወንጌልና ያደረጋቸው ተአምራት፣ የጌታ በራሱ ፈቃድ መሰቀል መሞት እና መነሣት፣ ዕርገቱና ዳግም ምጽአቱን፣ ጽድቅና ኩነኔ፣ የቤተክርስቲያን ታሪክና የዘመን አቆጣጠር፣ በዓላትና አከባበራቸው…ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡

አመለካከት፡ ቀና አመለካከት እንዲኖራቸው ማድረግ

ልጆች ነገረ ሃይማኖትን በእውቀት ተኮር አሰጣጥ ቢማሩም ቀና አመለካከት ግን ከሌላቸው ጥረቱ ሁሉ ዋጋ የለውም:: ቤተክርስቲያንን የሚያሳድዱ ወገኖቻችን ስለቤተ ክርስቲያን አነሰም በዛ ያውቃሉ:: ለአስተምህሮዋም ሆነ አስተምህሮዋን ለመጠበቅ ሊሰራ ስለሚገባው ተቋሟ ያላቸው አመለካከት ግን ደዌ አለበት:: በመሆኑም የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት ዕውቀትን ከማስጨበጥ በተጨማሪ ልጆች ስለ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊት፣ ታሪካዊ ጉዞ ቅን አመለካከት ወይም አስተያየት እንዲኖራቸው ማገዝ አለበት:: በጎ አመለካከት የብዙ ነገሮች መሠረት ስለሆነ በልጅነታቸው መገንባት ይኖርበታል፡፡

እሴት፡ ኦርቶዶክሳዊ እሴቶችን ማስተማር

የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት ልጆች ኦርቶዶክሳዊ እሴቶችን ለምሳሌ እምነትን፣ ተስፋን፣ ፍቅርን፣ መረዳዳትን፣ መታገስን፣ ትህትናን፣ ፅናትን፣ መታዘዝን፣ ንጽሕናን ወዘተ ገንዘብ እንዲያደርጉ ማገዝ አለበት::  እነዚህ እሴቶች ለክርስትና ሕይወት መሠረታዊ ነገሮች ስለሆኑ ልጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ የሕይወታቸው አካል አድርገው ሊያድጉ ይገባል፡፡ እነዚህንም እሴቶች የሚማሩት በማየትና በመሳተፍ ስለሆነ ወላጆች፣ መምህራንና ሌሎች የቤተክርስቲያን ምዕመናን እነዚህ እሴቶችን በመተግበር ለልጆች አርአያ ሊሆኑ ይገባል፡፡

ሥርዓት፡ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን እንዲፈጽሙ ማስቻል

ልጆች ስለሃይማኖታቸው በቂ ዕውቀትና በጎ አመለካከት ቢኖራቸው በምግባር መተርጎም ካልቻሉ እንዲሁ ዋጋ ቢስ ነው:: ልጆች ሲያድጉ አንድ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኝ ሊኖረው የሚገባውን ሥነ-ምግባር ይኖራቸው ዘንድ ያስፈልጋል:: መንፈሳዊ ትምህርታቸውም ልጆች ክርስቲያናዊ ሕይወትን ለመኖር የሚያስችላቸውን ዘዴዎች ሥራ ላይ እንዲያውሉ ያደርጋል:: መንፈሳዊ ትምህርቱ የተለያዪ የክርስትና ሕይወት ተግባራትን እንዲማሩ ያግዛል:: ለምሳሌ ያህል ጸሎት እንዴት እንደሚጀመርና እንደሚፈጸም፣ ቤተ ክርስቲያን ሲገባ እንዴት መሳለም እንደሚገባ፣ በቅዳሴና በትምህርት ጊዜ ሊደረግ የሚገባ ተሳትፎ፣ ከቅዱስ ቍርባን በፊት፣ ጊዜና በኋላ የሚደረጉ ዝግጅቶችና ጥንቃቄዎች ልጆች መማርና ማወቅ እንዲሁም መፈጸም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህንንም ከመንፈሳዊ ትምህርቱ ሊያገኙ ይገባል። ስለ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን የምናስተምርበት መንገድም ልጆችም ሆኑ ሌሎች ምዕመናን ከምንፈጽመው የሚታይ ሥርዓት ባሻገር ያለውን ታላቅ መንፈሳዊ ምሥጢር በኦርቶዶክሳዊ ለዛ እንዲረዱ በማድረግ ይገባል እንጂ ጌታችን እንደወቀሳቸው ጸሀፍትና ፈሪሳዊያን የሥርዓትን መሰረታዊ ዓላማ በመዘንጋት መሆን የለበትም፡፡

ክህሎት፡ የመንፈሳዊ አገልግሎት ክህሎትን እንዲያዳብሩ ማድረግ

ልጆች በቤተክርስቲያን በሚሰጣቸው መንፈሳዊ ትምህርት መንፈሳዊ አገልግሎትን ለመፈጸም የሚሆኑ ክህሎቶችን እየተማሩ ማደግ አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ኦርቶዶክሳዊ (ያሬዳዊ) ዝማሬን ማጥናትና ማቅረብ፣ የቅዳሴ ተሰጥኦ መቀበል መቻል፣ በአገልግሎት ጊዜ የሚደረጉ ዝግጅቶች ማስተናገድ፣ በቋንቋቸው መጻፍና መናገር፣ ለታናናሾቻቸው የተማሩትን ማስተማር፣ መንፈሳዊ መርሐግብሮችን ማስተባበርና የመሳሰሉትን ክህሎቶች እያዳበሩ ሊያድጉ ይገባል፡፡ ማንኛውም ትምህርት በሚገባ ሊተረጎም የሚችለው ተማሪዉ ለትምህርቱ የሚገባ በቂ ልምምድ አድርጎ አስፈላጊውን ክህሎት ሲይዝ ነው፡፡ በቃል ከማስተማርም ሆነ በገቢር ከማሳየት ባሻገር ልጆችና ህጻናት በቤተክርስቲያን አገልግሎት እየተሳተፉ ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ ይገባል፡፡ ቤተክርስቲያን ሽህ ዘመናትን ተሻግራ ለዘመናችን ከነትውፊቷ የደረሰችው ልጆችና ወጣቶችን እንደ መርሐ ግብር ማሟያና በሚያይ አሰራር ሳይሆን በገቢር በሚያሳትፍ አሰራር ነው፡፡ ታላላቅ አባቶቻችን ቅዱሳን በጉባኤ ሲገኙ ከእነርሱ ይልቅ ወጣቶች የሆኑ ረድኦቻቸው (ረዳቶቻቸው) እንዲያስተምሩ፣ መናፍቃንንም እንዲረቱ ያደርጉ የነበሩት (ለምሳሌ ቅዱስ አትናቴዎስ) ከእውቀትና ምግባር ባሻገር የክህሎትን ትምህርት እየሰጧቸው ነበር፡፡

ሥነ-ምግባር፡ በክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር ማጎልበት 

ልጆች በልጅነታቸው ቤተክርስቲያን ሄዶ ማስቀደስን፣ እንደየአቅማቸው መጾምና መጸለይን፣ ምፅዋት መስጠትን፣ ሥራን ጠንክሮ መሥራትን፣ ሰውን ማክበርን፣ ከሌሎች ጋር ለምሳሌ ከጓደኛ ከጎረቤት ጋር በሰላም መኖርን…ወዘተ እየተማሩ ሊያድጉ ይገባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መጥፎ ከሆኑ ምግባራት ይርቁ ዘንድ በምክንያት ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ መልካም ነገርን ሲያደርጉ ጠቀሜታውን በሚገባ ተረድተውት እንዲያደርጉ፤ መልካም ያልሆነውን ሲተውት ጉዳቱን በሚገባ ተረድተውት እንዲሆን ማድረግ የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት ትኩረት መሆን ይኖርበታል፡፡ በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ መልካም ምግባራት ለክርስቲያን ህይወት መሰረታዊ የድህነት (የመዳን) መፈጸሚያ መንገዶች ናቸው እንጂ ለአንዳንዶች እንደሚመስላቸው “ስንችል” ብቻ የምንፈጽማቸው ከድህነታችን ጋር ያልተያያዙ የምንግዴ ትእዛዛት አይደሉም፡፡

ጥበብ፡ ጥበብን የሕይወታቸው መርህ እንዲያደርጉ ማስቻል

የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት ቀጣይ ሕይወታቸውን በማስተዋልና በጥበብ መምራት እንዲችሉ አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል፡፡ ውጥንቅጥ በበዛበት ዓለም እምነታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ በልጅነታቸው ይህንን ጥበብ ከቤተክርስቲያን መማር ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ በእምነት ከማይመስሏቸው ጋር አብሮ መኖርን፣ ስለሃይማኖታቸው ለሚጠይቋቸው ሁሉ በተገቢው ሁኔታ በጥበብ ማስረዳት መቻልን፣ በክርስትናቸው ምክንያት ፈተና ቢገጥማቸው በማስተዋልና በጥበብ ማለፍ መቻልን፣ በሥራ፣ በትዳር ሕይወትና በማኅበራዊ ኑሮ አርአያ መሆንን …. ወዘተ በቤተክርስቲያን ከሚሰጣቸው መንፈሳዊ ትምህርት ሊያገኙትና በሕይወት ተሞክሮአቸው ሊያዳብሩት ይገባል፡፡

በአጠቃላይ የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት እውነተኛ እምነትን፣ በጎ አመለካከትን፣ ክርስቲያናዊ እሴትን፣ የመንፈሳዊ አገልግሎት ክህሎትን፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን፣ ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባርንና በጥበብና በማስተዋል መኖርን ተቀዳሚ ዓላማዎች ሊያደርግ ይጠበቅበታል። ልጆች የሚማሩበት ሥርዓተ ትምህርትም በእነዚህ ዓላማዎች ዙሪያ የሚያጠነጥን መሆን ይኖርበታል። የሚያስተምሩት መምህራንም በእነዚህ ዓላማዎች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል። የማስተማሪያ ስልቱም እነዚህን ዓላማዎች የሚያሳካ መሆን ይጠበቅበታል። ትምህርት በዓላማ ከተመራ ውጤታማነቱ አጠያያቂ አይሆንም። ዓላማዎቹ በግልጽ ካልታወቁ ግን ወጅብ እንደሚያማታው ውኃ ሲዋልሉ መኖር ይሆናል። †

በልጆች መንፈሳዊ ትምህርት የሚሳተፉ መምህራን ሊያሟሏቸው የሚገቡ መስፈርቶች ምንድን ናቸው?

teachers

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሚሰጠውን የልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያኑ ልጆችን የሚያስተምሩ መምህራን ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ:: በመሆኑም የመምህራን ብዛትና ብቃት ለትምህርቱ ይዘትና አካሄድ ከሚሰጠው ትኩረት ባልተናነሰ መልኩ ሊታሰብበትና ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው:: ልጆችን ለማስተማር ቀናነትና ፍላጎት አስፈላጊ ቢሆኑም ሌሎች መሠረታዊ ክህሎቶችን አቀናጅቶ መያዝ ለትምህርቱ ውጤታማነት ወሳኝ ነው፡፡ በመጅመሪያ ደረጃ ልጆችንና ወጣቶችን በማስተማር በቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት መሳተፍ የሚፈልጉ ምዕመናን፣ ካህናትና መምህራነ ወንጌል መልካም አመለካከትንና ክርስቲያናዊ ምግባርን በቃልና በተግባር ማስተማር የሚችሉ መሆን ይገባቸዋል::

ወላጆችም ልጆቻቸው መንፈሳዊ ትምህርትን እንዲማሩ ወደ ቤተክርስቲያን ከመውሰዳቸው በፊት ማነው የሚያሰተምራቸው? የሚለው ጥያቄ በውስጣቸው እንደሚኖር አያጠያይቅም፡፡ እምነት የሚጣልባቸውና ለልጆች መልካም አርአያ የሚሆኑ መምህራን ካሉ ልጆቻቸውን በደስታ ይዘው ይመጣሉ፣ ያስቀጥላሉም፡፡ መንፈሳዊ ዕውቀት ቢኖራቸውም በመልካም ምግባር የማይታወቁ መምህራን ካሉ ግን ወላጆች ፍልጎት ቢኖራቸውም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርቱ ከማምጣት ወደኋላ ይላሉ፡፡ ቢያመጧቸውም ልጆቹ መልካምነትን ተምረው ላይመለሱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በቤተክርስቲያን ለልጆች መንፈሳዊ ትምህርትን የሚያስተምሩ (ለማስተማር የሚመለመሉ) መምህራን ወደ አገልግሎቱ ከመሰማራታቸው በፊት ለዚህ አገልግሎት የሚሆናቸውን መሠረታዊ መስፈርቶች ማሟላት አስፈላጊ ነው፡፡ ስለሆነም የአጥቢያ መንፈሳዊ ሰበካ ጉባዔ መምህራንን በሚመድብበት ጊዜ  አስፈላጊ የሆኑት መስፈርቶችን ማሳወቅ፣ ማረጋገጥና ተግባራዊነታቸውን መከታተል ይኖርበታል፡፡  እኛም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን ሊያሟሏቸው የሚገቡ ሰባት መሠረታዊ መስፈርቶችን እንዳስሳለን፡፡

ኦርቶዶክሳዊት እምነት 

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ተቀዳሚ ዓላማ ክርስትናን ሳይበረዝና ሳይከለስ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ ከመሆኑ አንጻር ለልጆች መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራንም የቤተክርስቲያኒቱን እምነት የሚያምኑና በዚህም የተመሠከረላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ በሕይወታቸውም እግዚአብሔርን የሚፈሩና ሰውን የሚያከብሩ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በእምነታቸው የሚጠረጠሩ ወይም ጥያቄ የሚነሳባቸው ወይም እውነተኛ እምነታቸውን ለማስመስከር ያልቻሉ ልጆችን ለማስተማር ከመሰማራታቸው በፊት ይህ ሊስተካከል ይገባል፡፡ አንዳንድ የተሐድሶ መናፍቃን ቤተክርስቲያንን ከሚጎዱባቸው መንገዶች አንዱ ሠርጎ በመግባት ልጆችን ኑፋቄ ማስተማርና የቤተክርስቲያኒቱን ቀጣይነት መፈታተን መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል፡፡ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ በደንብ ያልተረዱ አንዳንድ የልጆች መምህራንም ለዚህ እኩይ ተግባር መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ራሳቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡

መንፈሳዊ ዕውቀት 

ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን ራሳቸው  የቤተክርስቲያን ትምህርት ቢያንስ በሰንበት ትምህርት ቤት በተከታታይ ስልጠና የወሰዱና ልጆችን ለማስተማር የሚያበቃ መንፈሳዊ ዕውቀትን ያካበቱ መሆን አለባቸው፡፡ ልጆችን የሚያስተምሩ መምህራን መሠረታዊ የቤተክርስቲያን ትምህርትን ለምሳሌ አዕማደ ሚስጢር፣ ስነፍጥረት፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን፣ እንዲሁም ስለቤተክርስቲያን ታሪክና ፈተናዎች በቂ ዕውቀት ያላቸው መሆን ይኖርባቸዋልል፡፡  በተጨማሪም ሌሎች የእምነት ድርጅቶች ስለሚያነሷቸው ጥያቄዎች የሚያውቁና እና ስለሚኖሩበት ሀገርም በቂ ዕውቀት ያላቸው፤ በዚህም ዙሪያ ልጆች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ሊሠጡ የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡ በዘመናዊ ትምህርታቸውም ቢያንስ  ልጆችን ለማስተማር የሚያስችል የዕውቀት ደረጃ ላይ የደረሱ ቢሆኑ ይመረጣል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ስለልጆች አእምሮአዊ፣ ስሜታዊ፣ ማኅበራዊና ሞራላዊ የዕድገት ሂደት በቂ ዕውቀት ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡

የማስተማር ክህሎት 

መንፈሳዊ ትምህርትን ለማስተማር የማስተማር ልዩ ዝንባሌና ችሎታ  ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራንም ልጆችን የማስተማር ዝንባሌና ክህሎቱ ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ በቅድሚያ መምህራኑ ልጆችን ማስተማር እጅግ ትልቅ የቤተክርስተያን አደራ እንደሆነ የሚያውቁና የሚያምኑ ሊሆኑ ይገባል፡፡ የመንፈሳዊ ትምህርት ዋናው ዓላማ ልጆች የሚገባቸውን ዕውቀት እንዲቀስሙና መንፈሳዊ ዕውቀታቸወን እንዲያድግ እስከሆነ ድረስ፣ መምህራን ልጆች የሚናገሩትን ዋና (የአፍ መፍቻ) ቋንቋ መናገር የሚችሉ ሊሆኑም ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም የሚችሉ፣ ልዩ ልዩ የማስተማርያ ዘዴዎችን የሚያውቁ፣ ለማወቅና ሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው የሚያምኑ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ከልጆች ጋር በሚኖራቸው የትምህርት መርሐግብርም ልጆችን በእኩልነትና በፍቅር መያዝ የሚችሉ ሊሆኑ ይገባል፡፡

መልካም አመለካከትና ቁርጠኝነት  

ልጆችን ማስተማር ትልቅ ኃላፈነትና መስዋዕትነት የሚጠይቅ ተግባር ሲሆን በዚያው ልክም ትልቅ በረከት የሚያስገኝ አገልግሎት ነው፡፡ ስለዚህ ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራንም በሰው ልጅ የመሻሻልና የማደግ ባሕርይ የሚያምኑና ለዚህም በጎ አመለካከት ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ በጎ አመለካከት ለውጤታማ ሥራና ለመንፈሳዊ ሕይወት መሠረት ነው፡፡ ከዚህም አንጻር ልጆችን የሚያስተምሩ መምህራን ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊት፣ ታሪካዊ ጉዞ እንዲሁም ስለቤተክርስቲያን አጠቃላይ አገልግሎት በሚገባ የተረዱና ቅን አመለካከት  ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ በዚህ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎችንም በበጎ የሚመለከቱ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከዓለም ዓቀፍ ትስስር አንጻርም በዓለም ላይ ስላሉ አጠቃላይ ክስተቶች ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ያላቸውና የሚከታተሉ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ስለራሳቸው ባላቸው አመለካከትም በቀጣይነት ለመማርና ለመሻሻል ጽኑ ፍላጎት ያላቸው ቢሆኑ ለልጆችም መልካም አርአያ መሆን ይችላሉ፡፡ መንፈሳዊ ትምህርቱን በሚገባ ለመተግበርም መምህራኑ ከወላጆችና ከቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና ስብከተ ወንጌል ክፍል ጋር በመናበብ መሥራት እንደሚጠቅም የሚያምኑና ለዚህም የሚተጉ መሆን አለባቸው፡፡

ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር 

ልጆችን ከቃል ይልቅ ተግባር የበለጠ ያስተምራቸዋል፡፡ ስለዚህ ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት፣ ሥርዓትና ትውፊት ከማመን በተጨማሪ በክርስቲያናዊ ምግባራቸው አርአያ መሆን የሚችሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከክርስቲያናዊ ምግባራትም ለምሳሌ በመጾም፣ በመጸለይ፣ በማስቀደስ፣ በመቍረብ፣ በትሕትና፣ በክርስቲያናዊ አለባበስ ወዘተ ለልጆች ምሳሌ መሆን የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ መንፈሳዊ ዕውቀትና የማስተማር ክህሎት መልካም ስነ-ምግባር ካልታከለበት የልጆችን የማስተማር ሂደት ውጤታማ አያደርገውም፡፡ እምነቱ እያላቸው የማይተገብሩም ልጆችን ለማስተማር ከመሰማራታቸው በፊት ራሳቸውን በንስሐ ሕይወት አስተካክለው ክርስቲያናዊ ስነ-ምግባራትን መፈጸም ሊጀምሩ ይገባል፡፡ ከክርስቲያናዊ ስነ-ምግባር ጎን ለጎንም በዘመናዊ ትምህርታቸውና ሥራቸው (ለኑሮ በሚሠሩት ሥራ) ለልጆች አርአያ የሚሆኑ ቢሆኑ ደግሞ የተሻለ ይሆናል፡፡

መሠረታዊ ሥልጠና  

ለልጆች መንፈሳዊ ትምህርትን ማስተማር በቅንነት ብቻ ተነስቶ የሚገባበት ወይም እገሌ ያስተምር ተብሎ ምደባ የሚሠጥበት አገልግሎት አይደለም፡፡ ከላይ ከተጠቀሰው መንፈሳዊ ዕውቀት በተጨማሪ መምህራን የየሀገራቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ ባስገባ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ሥልጠና የወሰዱ መሆን አለባቸው። የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት የሚመራበትን ሥርዐተ ትምህርት ለመተግበር መምህራንን ማሰልጠን እና ሥርዐተ ትምህርቱን በሚገባ እንዲረዱት፣ እንዲተገብሩትና ለሌሎችም ማስረዳት እንዲችሉ ማደረግ ይገባል። በግልጽ የታወቀ ሥርዓተ ትምህርት በሌለበትና መምህራኑም በሥርዓተ ትምህርት በማይመሩበት ሁኔታ ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት ማስተማር ውጤታማነቱ  አጠያያቂ ነው፡፡

ሕግን ማወቅና ማክበር 

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን ስለልጆች አያያዝ፣ ከልጆች ጋር አብሮ ስለመሥራት፣ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች አያያዝንና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ሕግጋትን የሚያውቁና የሚያከብሩ መሆን አለባቸው፡፡ ይህንንም ከቤተክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት ጋር አጣጥመው በመተግበር ለልጆችም አርአያ መሆን አለባቸው፡፡ የመምህራኑም ስልጠና እነዚህን ሕግጋት የሚዳስስና ስለአተገባበራቸውም የሚገልጥ ሊሆን ይገባል፡፡ እንደየሀገራቱ ሁኔታም ከልጆች ጋር ለመሥራት የሚያስፈልግ የምስክር ወረቀት ካለ መምህራኑ ይህንን መያዛቸውን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ይህም ሲደረግ ልጆችን ከአእምሮአዊ፣ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጥቃት መጠበቅና በሚገባቸው መንገድ ማስተማር ይቻላል፡፡ ሕግ ባለበት ሀገር ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት ስለማያድን ሕግን ማወቅና እንዲተገበር ማድረግ መምህራኑ ልጆችን በሕጉ መሠረት እንዲይዙ ይረዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቤተክርስቲያን ልጆችን በሕግና በሥርዓት ይዛ ማስተማሯ ሕግን አክብራ ከመሥራቷ ባሻገር ለሌሎችም አርአያ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡

በአጠቃላይ ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን እምነት፣ ሥርዓትና ትውፊት ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ የሚያምኑና የሚፈጽሙ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ለመማር ማስተማሩም ውጤታማነት ይረዳ ዘንድ ስለልጆች ትምህርትና ዕድገት መልካም አመለካከት ያላቸውና የማስተማር ክህሎትንም ያዳበሩ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ልጆች በሚናገሩት ዋነኛ ቋንቋ ማስተማር የሚችሉና በቴክኖሎጂ በታገዘ የትምህርት አሰጣጥ ልምድ ያላቸው ቢሆኑ ደግሞ ትምህርቱ በሚገባው ደረጃ እንዲሰጥ ይረዳል፡፡ መምህራን በእምነታቸውና በሥነ-ምግባራቸው አርአያ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሚኖሩበትን ሀገር ሕግ የሚያውቁና የሚያከብሩ መሆን አለባቸው፡፡ እነዚህን መስፈርቶች የማያሟሉ መምህራን ላይ ወላጆች እምነት ስለማይጥሉባቸው ልጆቻቸውን ይዘው ለመምጣት ሊያመነቱ ይችላሉ፡፡

ስለዚህ ልጆችን የማስተማር ፍላጎቱ ያላቸው ኦርቶዶክሳዊያን ወንድሞችና እህቶች እነዚህ ልጆችን ለማስተማር የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ መስፈርቶች ተገንዝበውና አስፈላጊውን ስልጠና ወስደው ወደ አገልግሎቱ ሊገቡ ይገባል፡፡  የየአጥቢያው ቤተክርስቲያን ሰበካ መንሳዊ ጉባዔ አስተዳደርም ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን እነዚህን መሠረታዊ መስፈርቶችን የሚያሟሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባቸዋል፡፡ ይህም የሚደረግበት ዓላማ ልጆች በልጅነታቸው ሊያገኙት የሚገባውን መንፈሳዊ ትምህርት በተገቢው መንገድ እንዲማሩ ለማስቻል መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ እነዚህን መሠረታዊ መስፈርቶች የማያሟሉ ካሉ ደግሞ አሟልተው ወደ አገልግሎቱ እንዲገቡ ማገዝ ይገባል  እንላለን፡፡ †

 

ለልጆች መንፈሳዊ ትምህርት መሳካት ከወላጆች ምን ይጠበቃል?

parents role2

ወላጆች ወይም ቤተሰብ የልጆች የመጀመሪያው ትምህርት ቤት ናቸው። ለልጆች ፈሪሃ እግዚአብሔርን ማስተማር፣ የዚህ ዓለምን የሕይወትን ጣዕምና ትርጉምን ማሳወቅ እንዲሁም የስኬትን መንገድ ማመላከት በቀዳሚነት የወላጆች ኃላፊነት ነው። ወላጆች የልጆቻቸውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ፣ፍላጐትና ዝንባሌ መገምገም፣ አስፈላጊ ነገሮችን በአግባቡ በማቅረብ ልጆች መልካም ጠባያትን ይዘው እንዲያድጉ ማድረግ ለአካላዊ፣ ለማኅበራዊ፣ ለሞራላዊ እድገታቸው ሳይታክቱ እንደሚተጉት ሁሉ ልጆች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ጠንክረው፣ አምላካቸውን አውቀው የእግዚአብሔርን መንግስት እንዲወርሱ ሊተጉ ይገባል። ቅድስት ቤተክርስቲያን ለልጆች በምትሰጠው መንፈሳዊ ትምህርት ውስጥም ወላጆች ጉልህና የማይተካ ድርሻ አላቸው፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጦማር ወላጆች ለልጆች መንፈሳዊ ትምህርት መሳካት የሚያስፈልጉ ሰባት ዋና ዋና ድርሻዎችን እንዳስሳለን፡፡

መንፈሳዊ ትምህርቱ ለልጆች መሠረታዊ ነገር መሆኑን ማመን

ከሁሉ አስቀድሞ ወላጆች የልጆች የቤተክርስቲያንን ትምህርት መማር ለመንሳፋዊ ሕይወታቸው መሠረታዊ ነገር መሆኑን ማመን አለባቸው፡፡ ይህም ሲባል ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ቤተክርስቲያን ወስደው እንዲማሩ ለማድረግ በቅድሚያ ቤተክርስቲያን የምታስተምረው መንፈሳዊ ትምህርት ለልጆች መንፈሳዊ ሕይወት አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑን በማያወላውል መልኩ ማመን ይኖርባቸዋል ማለት ነው፡፡ በሌላ መልኩ በቤተክርስቲያን የሚሰጠው መንፈሳዊ ትምህርት ለልጆች መሠረታዊ መሆኑን በሚገባ ያላመነ/ች ወላጅ ልጁን/ልጇን ወደ ቤተክርስቲያን ለመውሰድ ሊያመነታ/ልታመነታ ይችላል/ትችላለች፡፡ ቢወስድም/ብትወስድም ምንና እንዴት እንደተማረ/ች አይ(ት)ከታተለውም፡፡  ስለዚህ የቤተክርስቲያን መምህራንና ካህናት አባቶች ወላጆችን ‹‹ልጆቻችሁን አምጡና ይማሩ›› ከማለት ጎን ለጎን ወላጆች በሚሠጠው መንፈሳዊ ትምህርት መሠረታዊነት፣ አስፈላጊነትና ተገቢነት ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ማረጋገጥ ይገባቸዋል፡፡

ልጆችን በሰዓቱምጣትና መመለስ

ወላጆች ቤተክርስቲያን ለልጆች የምትሠጠው መንፈሳዊ ትምህርት መሠረታዊ ነገር መሆኑን ካመኑበት ልጆችን ቤተክርስቲያን በምታዘጋጀው መረሐ ግብር መሠረት ይዞ መምጣት የሚቀጥለው ድርሻቸው ነው፡፡ ልጆችን ስለትምህርቱ ጠቃሚነት በሚረዱት መጠን ማስረዳት እና ፍላጎት እንዲያድርባቸው ማድረግ፣ ለትምህርቱ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች (ለምሳሌ የጽሕፈት መሣርያዎች) ማዘጋጀትና ልጆቹን በሰዓቱ ይዞ መምጣት የወላጆች ድርሻ ነው፡፡ ለዕድሜቸው በሚመጥናቸው ክፍል እንዲገቡም ማድረግና ጨርሰው ሲወጡም በሰዓቱ ተገኝቶ መልሶ ወደቤት መውሰድ የወላጆች ሁለተኛው ድርሻ ነው፡፡ ልጆች በቤተክርስቲያን በሚቆዩበት ሰዓትም መከታተል እንዲሁ የወላጆች ኃላፊነት ነው፡፡

በመማር ማስተማሩ ሂደት መሳተፍ

ወላጆች ልጆችን ማምጣትና መመለስ ብቻ ሳይሆን አቅማቸው በፈቀደ መጠን ልጆችን በማስተማር ሂደት ውስጥ መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ልጆች ምን እንደሚማሩ መገንዘብ፣ መማር ማስተማርን የሚተ,ስተጓጉሉ ወይም የስነ ምግባር ችግር ያለባቸው ልጆች  ካሉ በማባበል/በመምከር መምህራንን መርዳት፣ እንደየአስፈላጊነቱ የመማሪያ ቁሳቁሶችን በማስተካከል፣ ወንበር በማስተካከል፣ በመማሪያ ክፈፍሎችን የሚጣሉ ቆሻሻዎች በማንሳት፣ ከተቻለም በማስተማር መሳተፍና ትምህርቱ እንዲሻሻል የሚረዱ ገንቢ አስተያየቶችን በመስጠት መሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ወላጆቸ አስገዳጅ ጉዳይ ከሌለባቸው በቀር ከልጆች ጋር ተገኝተው ቢሳተፉ መልካም ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከልጆቹ ትምህርት ጎን ለጎን ወላጆችም ልምድ የሚለዋወጡበትና ልጆችን ለማሳደግ የሚረዳቸውን ትምህርት የሚያገኙበት መድረክ ማዘጋጀት ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ለዚህም የቤተክርስቲያን መምህራንና ካህናት አባቶች ለወላጆች የሚሆን የመማማሪያ መርሐግብር ወላጆችን ባሳተፈ መልኩ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡

ነገር ግን በአንዳንድ ወላጆች እንደሚታየው መደረግ የሌለባቸው ተግባሮች ለመጥቀስ ያህል፣ ልጆችን ወደቤተክረርስያን አምጥቶ ትቶ መሄድና የሚጨርሱበት ሰዓት ሲደርስ ብቻ ተመልሶ  መጥቶ መውሰድ፤ ከውጭ ሆኖ ከሌሎች ወላጆች ጋር ወሬ ማውራት፤ ምንም አስተዋፅኦ ሳያደርጉ የመማር ማስተማር ሂደቱን አፍራሽ በሆነ መልኩ መተቸት፤ የቤተክርስቲያኗን አቅም ያላገናዘበ ጥያቄ በመጠየቅ የመማር ማስተማር ሂደቱን ማብጠልጠል እና የመሳሰሉት ሥርዓተ ትምህርቱን በብዙ መልኩ ይጎዱታል፡፡

ማስጠናት/የቤት ሥራ አብሮ መሥራት/

ወላጆች በቤተክርስቲያን በሚሰጠው ትምህርት ከመሳተፍ በተጨማሪ ለልጆቻቸው የሚሰጠውን የቤት ሥራ  አብሮ በመስራት እና በማስጠናት ለመማር ማስተማሩ ድርሻቸውን ማበርከትና ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት ውጤታማ እንዲሆን በቤተክርስቲያንና በቤት የሚሰጠው ትምህርት መቀናጀትና በወላጆችና በመምህራን መካከል ያለው ግንኙነት መጠናከር ወሳኝ ነው፡፡ ስለዚህ ወላጆች ልጆቻቸው ከቤተክርስቲያን ተምረው የመጡትን ትምህርት መጠየቅ፣ ግልጽ ያልሆነ ነገር ካለ ማስረዳት፣ የቤት ሥራ አብሮ መሥራት፣ ያለፈውን ትምህርት መከለስ፣ ወደፊት ያለውን የትምህርት አርዕስት ማሳወቅና ለመምህራንም መረጃ መስጠት እንዲሁም ከመምህራኑ አስተያየት ካለ ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የልጆችን ዘመናዊ ትምህርት መከታተል እንደሚያስፈልገው ሁሉ  መንፈሳዊ ትምህርትን ሲማሩም መከታተል ይገባል፡፡ መንፈሳዊውም ዘመናዊውም ትምህርት ለልጆች ቀጣይ ሕይወት አስፈላጊ ነውና ልጆች በሁለት በኩል የተሳሉ ሆነው እንዲያድጉ መትጋት ያስፈልጋል፡፡

ለትምህርቱ  መሳካት የሃሳብ፣ የገንዘብና የቁስቁስ ድጋፍ ማድረግ

ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርትን በተከታታይነትና በቀጣይነት ለማስተማር ብዙ ግብዓት ያስፈልጋል፡፡ ተከታታይነት ያለውና ከዓመት ዓመት የሚቀጥል መንፈሳዊ ትምህርትን በበጎ ፈቃደኛ መምህራን ብቻ ማስተማር (የሚቻል ቢሆንም) ፈታኝ ነው፡፡ ስለሆነም በቤተክርስቲያኒቱ ያሉ መደበኛ አገልጋዮች በተቻለ መጠን ዋናውን ድርሻ መጫወት አለባቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መምህራኑና አስተባባሪዎቹ ከትምህርቱ ጋር በተያያዘ የሚያወጡትን ወጭ መሸፈን ያስፈልጋል፡፡  ለልጆቹ ማስተማሪያም ብዙ ዓይነት የማስተማሪያ ቁሳቁሶች ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህንም ማቅረብ ለቤተክርስቲያናን ለመምህራኑ ብቻ የሚተው ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህ ወላጆች ለሥርዓተ ትምህርቱ መሳካት የሚያስፈልገውን የገንዘብ እና የቁስቁስ ድጋፍ በማድረግ መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህም ሲባል የተለያዩ የማስተማሪያ መጻሕፍትንና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመስጠት/በማቅረብ ሊሆን ይችላል፡፡

በክርስቲያናዊ ሕይወት አርአያ መሆን

ከሁሉም በላይ ወላጆች ክርስቲያናዊ ሕይወትን በመኖር ለልጆቻቸው አርአያ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ አዘወትሮ ወደ ቤተክርስቲያን ልጆችን ይዞ በመሄድ፣ የቤተሰብ ጸሎት በማድረግ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ፣ ያሬዳዊ መዝሙራትን በማዳመጥ/በመዘመር፣ ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባራትን በመፈጸም፣ መልካም ያልሆኑ የቴሌቪዥን መርሐግብሮችንና ማኅበራዊ ሚዲያን ባለማየት፣ መልካም ስብእናን ይዞ ጠንክሮ መስራትን በማሳየት ለልጆች አርአያ መሆን ከወላጆች ይጠበቃል፡፡ የወላጆች ሕይወት የልጆች ማንነትና ሕይወት ላይ ታላቅ ተጽእኖ ስለሚኖረውና ልጆች የሚያዩትን ይዘው ስለሚያድጉ በሕይወት አርአያ መሆን ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያደርጉት ታላቅ ድርሻ ነው፡፡ በቤተክርስቲያን የሚሰጠው መንፈሳዊ ትምህርት የቤተሰብ አርአያነት ሲጨመርበት ለልጆቹ የተሟላ ይሆንላቸዋል፡፡

በልጆች መርሐግብር መሪ ተዋናይ መሆን

በቤተክርስቲያን ለልጆች ከሚሰጠው መንፈሳዊ ትምህርት ጎን ለጎን በሚተገብሩ ሌሎች የልጆች መርሐግብራት ይኖራሉ፡፡ ወላጆች በእነዚህ መርሐግብራት መሪ ተዋናይ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከእነዚህም ለምሳሌ ያህል የጉብኝት መርሐግብር (ቅዱሳት መካናትን መጎብኘት)፣ በዓለ ንግሥ ላይ የሚኖር የልጆች ዝግጅት፣ የልጆችን ልደት በጋራ ማክበር፣ የልጆች የጽዋ ማኅበር ማዘጋጀት፣ ከአንዱ የትምህርት እርከን ወደ ሌላው ሲሄዱ መንፈሳዊ ምርቃት ማዘጋጀት፣ በልጆች መካከል የሚደረጉ የተለያዩ መንፈሳዊ ይዘት ያላቸውና አስተማሪ የሆኑ የጨዋታና የውድድር መርሐግብር ማዘጋጀት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን በማቀድ፣ በማስተባበርና በመተግበር ወላጆች መሪ ተዋናይ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የወላጆቻቸውን ንቁ ተሳትፎ እያዩ የሚያድጉ ልጆችም እነርሱም ሲያድጉ መሪ ተዋናይ ይሆናሉ፡፡

በአጠቃላይ ልጆች በወደፊት ሕይወታቸው እምነታቸውን አውቀውና ጠብቀው፣ በመንፈሳዊ አገልግሎትም ተሳትፈው የዘላለም ሕይወትን ይወርሱ ዘንድ በልጅነታቸው መንፈሳዊ ትምህርትን እየተማሩ ማደግ ይኖርባቸዋል፡፡ በኦርቶዶካሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት መሠረትም ለልጆች መንፈሳዊ ትምህርትን ማስተማር የየአብያተ ክርስቲያናት ዋነኛ የመንፈሳዊ አገልግሎት አካል ነው፡፡ ለዚህም መሳካት ወላጆች ወሳኝ ድርሻዎች አሏቸው፡፡ ከእነዚህ መካከልም መንፈሳዊ ትምህርቱ ለልጆች መሠረታዊ ነገር መሆኑን ማመን፣ ልጆችን በሰዓቱ ማምጣትና መመለስ፣ በመማር ማስተማሩ ሂደት መሳተፍ፣ ማስጠናት/የቤት ሥራ አብሮ መሥራት/፣ ለትምህርቱ  መሳካት የሃሳብ፣ የገንዘብና የቁስቁስ ድጋፍ ማድረግ፣ በክርስቲያናዊ ሕይወት አርአያ መሆንና በልጆች መርሐግብር መሪ ተዋናይ መሆን በአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ ስለዚህም ወላጆች ልጆቻቸውን በመንፈሳዊ ትምህርት እየታነፁ እንዲያድጉ ማድረግ አንዱ የመንፈሳዊ አገልግሎትና የክርስቲያናዊ ሕይወት አካል መሆኑን ተገንዝበው፣ የየድርሻቸውንም ማበርከት ይገባቸዋል እንላለን፡፡ †

 

ልጆቻችን መንፈሳዊ ትምህርትን በቋንቋቸው ወይስ በቋንቋችን ይማሩ?

መግቢያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በልዩ ልዩ መንገድ ክርስትናን ስታስተምር የቆየች ጥንታዊትና ታሪካዊት ቤተክርስቲያን መሆኗ ይታወቃል፡፡ እነ አቡነ ተክለሃይማኖትና አባ ሳሙኤል ዘዋልድባን የመሳሰሉ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት በልዩ ልዩ የሀገራችን ኢትዮጵያ የቀድሞ ጠረፋማ አካባቢዎች የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ህዝቦችን በክርስትና አስተምረው ሲያጠምቁ በሚገባቸው ቋንቋ እንዳስተማሯቸው ወይም በደቀ መዛሙርቶቻቸው አማካኝነት እንደሰበኩ የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ አገልግሎታቸው ፍሬ ባላፈራ ነበር፡፡ የማንበብና የመፃፍ ክህሎት በየቋንቋው ከመስፋፋቱ አስቀድሞ በነበሩት ዘመናት ትምህርተ ወንጌልና ሥርዓተ ሃይማኖት ከቃል ባሻገር ከባህልና ከአኗኗር ጋር በተሰናሰለ ሁኔታ በቀደሙ አባቶቻችን ይሰጥ እንደነበረ የሚያሳዩ በርካታ ማኅበረሰባዊ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በአንድ ወቅት ትምህርተ ሃይማኖትን ከአኗኗራቸው ጋር አዛምደው ይዘው የነበሩ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በጊዜ ሂደት የሚመክርና የሚያስተምር ካህን፣ መምህር አጥተው ከቀደመ የክርስትና አምልኳቸው ቢለዩ እንኳ በባህላቸውና በአኗኗራቸው የቀደመውን ዘመን የክርስትና ላህይ የሚያሳዩ አሻራዎችን ይዘው የሚገኙበት ጊዜ አለ፡፡ የማንበብና መፃፍ ክህሎት የጥቂቶች ብቻ የነበረበት ዘመን አልፎ  በተስፋፋበት የቅርብ ዘመን ታሪክ ግን ቤተክርስቲያናችን ለዘመኑ በሚመጥን መልኩ ምዕመናንን በየቋንቋቸው ከማስተማር አኳያ ከፍተኛ ድክመት እንዳለባት የታወቀ ነው፡፡  

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮዋ አስቀድሞ የግዕዝን ቋንቋ ከቅርብ ዘመናት ወዲህ ደግሞ አማርኛን ቋንቋ የሚጠቀም በመሆኑ ሌሎች በኢትዮጵያ ውስጥና ከኢትዮጵያ ውጭም የሚነገሩ ቋንቋዎችን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት የመጠቀሙን ሁኔታ እጅግ አነስተኛ አድርጎታል፡፡ ይህም ቤተክርስቲያኗ እና አስተምህሮዋ በተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ብቻ ታጥሮ እንዲቆይ ከማድረጉ በተጨማሪ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብን በቋንቋው ወደሚያስተምሩ ሌሎች የእምነት/የሃይማኖት ተቋማት እንዲሄድ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ቤተክርስቲያኗ ለረጅም ዓመታት አገልግሎት እየሰጠች ብትቆይም በቋንቋው ያላስተማረችውን ሕዝብ ሌላው የእምነት ተቋም በአጭር ጊዜ (ለምሳሌ በ5 እና በ10 ወር) በቋንቋው እያስተማረ ሲወስደው ተመልካች ሆና መቆየቷ የታሪክ ተወቃሽ አድርጓታል፡፡ እጅግ ቢዘገይም በቅርብ ጊዜ የተጀመረው የስብከት፣ የመዝሙርና የቅዳሴ አገልግሎቶችን በኦሮምኛና በትግርኛ ቋንቋዎች የማጋጀትና የማሠራጨት ጅምር በሌሎች ቋንቋዎችም ተስፋፍቶ ሊቀጥል ይገባል፡፡ በተወሰኑ አከባቢዎች ለተወሰነ ጊዜ የሚደረገው የስብከተ ወንጌል እና ሌሎች አግልግሎቶችን በተሟላና ዘላቂ በሆነ መልኩ ለማስቀጠል መተባበር ይገባል እንላለን፡፡

በወላጆችና በልጆች መካከል ያለው የቋንቋ ልዩነት

በዝርወት ዓለም በሚኖረው ሕዝበ ክርስቲያን ዘንድ ያለው እውነታ የሚያሳየው አብዛኞቹ ልጆች እዛው የተወለዱ ከመሆናቸውም አንፃር የሀገሩን ቋንቋ አቀላጥፈው የሚናገሩ ነገር ግን የወላጆቻቸውን ቋንቋ ለመናገር የሚቸገሩ ናቸው፡፡ በሌላ መልኩ አብዛኞቹ ወላጆች ተወልደው ያደጉበትን የሀገራችን ቋንቋ አዘውትረው የሚናገሩ፣ የሚኖሩበትን ሀገር ቋንቋ ደግሞ በተወሰነ መልኩ ብቻ የሚናገሩ ናቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ በተለይም በቤተሰብ ደረጃ በወላጆችና በልጆች መካከል የቋንቋ ልዩነት ጎልቶ የሚታይ ከመሆኑም ባሻገር በመካከላቸው ላለው ቤተሰባዊ ትስስር መላላት ዋንኛ  ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡ ስለሆነም ልጆች በጨቅላ ዕድሜያቸው ከቤተሰቦቻቸው ሊያገኙት የሚችሉትን መሰረታዊ የቤተክርስቲያናችን ትምህርት ከማጣታቸው በተጨማሪ፣ በዛው ዕድሜያቸው ለሌሎች መልካም ያልሆኑ ጠባያት (risk behaviors) የሚጋለጡበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ በተለይም ለመዋዕለ ህፃናት ከደረሱበት ዕድሜ በኋላ አንዳንድ ቤተሰብ እንደሚገልፀው “ሊያመልጡን ነው” በሚል ስጋት ውስጥ ይገባሉ፡፡

ይህም ስጋት ልጆቻችን ሃይማኖታቸውን፣ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን ሳናስተምራቸው ከልጅነት ወደ ወጣትነት ዕድሜ ተሻገሩ ከሚል ቁጭት የመጣ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ቁጭት ተግባርን ካልስከተለ ለባሰ ቁጭት ከመዳረግ ውጭ በራሱ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ይህንን ለማድረግ ያለው አማራጭ ግልጽ ነው፡፡ እርሱም በወላጆችና በልጆች መካከል ያለውን ትስስርና ተግባቦት ማጠናከር ነው፡፡ ይህ ከቋንቋ አንጻር ሲታይ ወላጆች ቋንቋቸውን ለልጆቻቸው በሚገባ ማስተማር እና/ወይም ልጆች በሚገባ የሚረዱትን ቋንቋ ለመናገር ጥረት ማድረግ  ነው፡፡ ሩጫ በበዛበት እና ሰው ብዙ ሰዓትና ከአንድ ሥራ በላይ በሚሠራበት ሀገር ይህ ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ወላጅ ለልጆቹ በቂ ትኩረት ከሰጠ ይህን ማድረግ ከባድ አይሆንም፡፡  

ልጆች

ልጆችን ወላጆቻቸው በሚናገሩት ቋንቋ ቢማሩ የተሻለ ነውን?

ልጆች መጀመሪያ የሚያገኟት ቤተክርስቲያን በቤት ውስጥ ያለችው የወላጆቻቸውና የቤተሰቦቻቸው አንድነት ናት፡፡ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ተመሳሳይ ቋንቋ በማይነጋገሩበት በዝርወት ዓለም ባሉ ኢትዮጵያውያን (ኤርትራውያን) ቤተሰቦች ዘንድ በቃል ሊተላለፉ የሚገባቸው የቤተክርስቲያን አስተምህሮዎችን ማስረዳት ከባድ ሲሆን ይታያል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ልጆችን ሃይማኖታዊ ትምህርት ከማስተማር አንጻር በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ያሉ ምዕመናን ሁለት ዓይነት ሀሳብ ያነሳሉ፡፡ በሁለቱም አስተሳሰቦች ላይ መልካምና ደካማ ጎናቸውን አብረው ያነሳሉ፡፡

የመጀመሪያው አስተሳሰብ ልጆቹ ሃይማኖታዊ ትምህርቱን ወላጆቻቸው በሚናገሩት ቋንቋ ቢማሩ የተሻለ ነው የሚል ነው፡፡ ይህ አማራጭ የቤተክርስቲያኒቱ መምህራን (አብዛኞቹ ከሀገር ቤት የመጡና የሚመጡ ስለሆኑ) በቀላሉ ሊያስተምሯቸውና ወላጆችም ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉበት ይችላሉ የሚል መልካም እይታ አለው፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታም አብዛኛው የቤተክርስቲያኒቱ አገልግሎት (ቅዳሴ፣ ስብከት፣ መዝሙር፣ ትምህርት) የሚሰጠው በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ስለሆነ ይህ አማራጭ ልጆች በአገልግሎቱ እንዲሳተፉ ያደርጋል፡፡ የሃይማኖት መጻሕፍትም የታተሙት በእነዚሁ ቋንቋዎች ስለሆነ ለልጆቹ የተሻለ ተደራሽነት ይኖራቸዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ይሆን ዘንድ ልጆቹ ከሃይማኖት ትምህርት አስቀድሞ የቋንቋ ትምህርት መማር ይኖርባቸዋል፡፡በዝርወት ዓለም የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ለልጆች በተገቢው ደረጃ ለማስተማር በማህበረሰቡና በቤተሰብ ደረጃ ያለው ቁርጠኝነት ይወስነዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ልጆች በሁለተኛ (አፋቸውን ባልፈቱበት) ቋንቋ ተምረውስ ምን ያህል ሃይማኖታዊው ትምህርት ሊዋሀዳቸው ይችላል የሚል አሉታው መከራከሪያ አለው፡፡ ሆኖም ግን የብዙ ወላጆች ፍላጎትም ስለሆነ የወላጆቻቸውን ቋንቋ በሚገባ ለተማሩና የቋንቋውን ክህሎት ላዳበሩ ልጆች ይህንን አማራጭ መጠቀም ይቻላል፡፡ 

ልጆቹ አቀላጥፈው በሚናገሩት ቋንቋ ቢማሩ ይመረጣልን?

ሁሉተኛው አማራጭ ልጆቹ የኦርቶዶካሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ትምህርት አቀላጥፈው በሚናገሩት፣ ትምህርት ቤትም በሚማሩበት ቋንቋ፣ በሀገሩ ቋንቋ ቢማሩ ይመረጣል የሚል ነው፡፡ ይህም ልጆቹ ሃይማኖታዊ ትምህርቱን በሚገባ እንዲረዱት ያደርጋል፡፡ ሳይቸገሩም በቀላሉ ይገባቸዋል፡፡ በተጨማሪም በአገሩ ቋንቋ በትጋት ከሚያስተምሩ ከአንዳንድ አኃት አብያተ ክርስቲያናት የሚማሩበት ዕድል ስለሚገኝ ተጨማሪ ግብአት ይሆናቸዋል፡፡ ይህም ለተወሰነ ጊዜ በደንብ ቢሰራበት ማለትም ልጆች ሃይማኖታዊውን ትምህርት አፋቸውን በፈቱበት ቋንቋ (ለምሳሌ በእንግዝኛ) ቢማሩ በቀላሉ ወደ ተምሮ ማስተማር ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ይህም ማለት በአንድ ዙር (cohort) በቋንቋቸው በሚገባ ሃይማኖታዊውን ትምህርት ከተማሩ የእነርሱን ታናናሾች ያስተምራሉ፡፡ እንደዚያ እያለ በቀጣይነት ለሚመጣው ትውልድም በሀገሩ ቋንቋ የሚያስተምሩ መምህራንን፣ የሚቀድሱ ካህናትን፣ የሚዘምሩ መዘምራንንና በሀገሩ ቋንቋ ተሰጥኦ የሚቀበሉ ምዕመናንን ማፍራት ይቻላል፡፡

ነገር ግን በኛ ቤተክርሰቲያን በሀገሩ ቋንቋ የሚያስተምሩ መምህራን እጥረት አለ፡፡ መደበኛ የሆኑት የቤተክርስቲያን ካህናትና መምህራን የእንግሊዝኛም ሆነ የሌላ የውጭ ሀገር ቋንቋ ስልጠና የሚወስዱበት አሠራር ስለሌለ እነርሱ በዝርወት ዓለም የተወለዱትን ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ህጻናትና ወጣቶች ማስተማር እንደሚከብዳቸው ግልጽ ነው፡፡ በእንግሊዝኛም ቋንቋ ጭምር እንዲያስተምሩ ታስቦ በተከፈቱ የቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊ ኮሌጆች ከሚመረቁ ደቀመዛሙርትም ብዙዎቹ እንኳን ለማስተማር ለመግባባት እንኳ የሚሆን የቋንቋ ክህሎት ያላቸው አይመስልም፡፡ በመደበኛው የሀገራችን ትምህርት የተማሩ የቤተክርስቲያችን ልጆችም ቢሆኑ ይህን ክፍተት ለመሙላት የሚያበቃ ክህሎትም ዝግጁነትም አላቸው ለማለት የሚያስችል ሁኔታ ያለ አይመስልም፡፡ ስለሆነም  ሊያስተምሩ ይችላሉ የሚባሉትም የቋንቋ ውስንነት ያለባቸው ናቸው የሚል መመከራከርያ ይቀርባል፡፡

በጥቂት ቁርጠኝነቱ ባላቸው የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች አስተባባሪነት ልጆችን በሀገሩ ቋንቋ (ለምሳሌ በእንግሊዝኛ) ማስተማር ቢጀመር ልጆቹ የቤተክርስቲያኒቱን አስተምህሮ እንዲያውቁ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ቅዳሴው በግዕዝና በአማርኛ፣ ስብከቱ በአማርኛና በትግርኛ፣ መዝሙሩ በግዕዝና በአማርኛ፣ ሰዓታቱና ማሕሌቱ በግዕዝ፣ ካህናቱም እንዲሁ በእነዚህ ቋንቋዎች የሚናገሩ ከሆነ በእንግሊዝኛ የተማሩት ልጆች እንዴት ሆኖ ነው ከቤተክርስቲያኒቱ አገልግሎት ተሳታፊ የሚሆኑት? ቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ አገልግሎቱን በእንግሊዝኛ መስጠት እስከምትጀምር ድረስ ልጆችን በእንግሊዝኛ ማስተማር ብቻ የመፍትሔ ጅምር እንጂ በራሱ መፍትሔ አይሆንም፡፡ በዚህም የተነሳ ቤተክርስቲያን ይህንን አማራጭ ገፍታ እንዳትሠራበት መሰናክል ሆኖ ይገኛል፤ ለወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ስለሆነም አንዳንድ ምዕመናን ልጆቻቸውን በአኃት አብያተ ክርስቲያናት (ለምሳሌ በኮፕቲክ ቤተክርስቲያን) ወስደው እንዲያስተምሩ ምክንያት ሆኗል፡፡

ቤተክርስቲያን ቋንቋን የማስተማር መንፈሳዊ ኃላፊነት አለባትን?

ሁሉም ወላጅ ልጆቹ የራሱን ቋንቋ በሚገባ ቢናገሩለት ደስ ይለዋል፡፡ ለቤተሰባዊም ሆነ ለማኅበራዊው መስተጋብርም ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ለልጆቹም ቢሆን አንድ ተጨማሪ ቋንቋ አቀላጥፎ መናገር ለአእምሮም ሆነ ለስነ-ልቦና፣ ለማኅበራዊም ሆነ ለዓለም አቀፋዊ ትስስር ታላቅ ድርሻ እንደሚኖረው ግልጽ ነው፡፡ አዋቂዎችን ቋንቋ ከማስተማር ይልቅ ልጆችን ማስተማሩ ቀላል ስለሆነም ልጆችን የወላጆቻቸውን ቋንቋ ማስተማርና ማሳወቅ የወላጆችና ቤተሰቡ የሚኖርበት ማኅበረሰብ ኃላፊነት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ግን መንፈሳዊ ተቋም ከመሆኗ አንጻር ለሰው ልጅ ሁሉ በሚናገረው ቋንቋ የክርስቶስን ወንጌል የማስተማር መንፈሳዊ ኃላፊነት አለባት፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለቅዱሳን ሐዋርያት 72 ቋንቋ የገለጸላቸው በየሀገሩ እየዞሩ የሰውን ልጅ በቋንቋው እንዲሰብኩ ነበር፡፡ ዛሬም የቤተክርስቲያን መምህራን ልጆችንም ሆነ ወጣቶችን እንዲሁም አዋቂዎችን በቋንቋቸው የማስተማር መንፈሳዊ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከዚህ አንጻር የቤተክርስቲያን ድርሻ ሃይማኖታዊ ትምህርትን የሰው ልጅ በሚናገረውና በሚረዳው ቋንቋ ማስተማር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ቋንቋን ማስተማር የቤተክርስቲያን መሠረታዊ ዓላማዋ አይደለም፡፡ በቤተክርስቲያን ያሉ አገልጋዮች ግን ቋንቋን በማስተማር ማኅበራዊ አበርክቶ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ይህም ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል መማር ፈልገው የሚመጡ ልጆችን ሁሉ ሊያስተናግድ የሚችልና ደረጃውን የጠበቀ የቋንቋ መማሪያ ማዕከል (Language Academy) ቢሆን መልካም ነው፡፡ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያኑ በአንዳንድ ቅንነት ባለቸው ምዕመናን ተሳትፎ ብቻ ብልጭ ድርግም የሚልና ባለህበት እርገጥ ዓይነት ተከታታይነትና ዘላቂነት የሌለው የቋንቋ ትምህርት ግን የልጆችን ዕንቁ የሆነ የመማሪያ ጊዜ ከማባከን ውጭ ብዙም ፋይዳ አይኖረውም፡፡

በዓለማዊ አስተሳሰብም ሆነ በመንፈሳዊው አስተምህሮ ቋንቋ ያው የመግባቢያ ክህሎት ነው፡፡ የቤተክርስቲያን መምህራንም እንደ ሐዋርያት የሰውን ልጅ በቋንቋው ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡ እዚህ ላይ አንዳንዶች ቤተክርስቲያንን የቋንቋ ማስተማርያ አድርገው ከማሰብ ይልቅ የሃይማኖታዊ ትምህርት ተቋም አድርገው ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡ ወላጆችና ማኅበረሰቡ ቋንቋን ለማስተማር ቢተጉ፣ ቤተክርስቲያን ደግሞ መንፈሳዊውን ትምህርት ልጆች በሚረዱት ቋንቋ ብታስተምር ልጆቹ በመንፈሳዊውም ትምህርት ሆነ በቋንቋ ክህሎታቸው የታነጹ ሆነው እንዲያድጉ ማድረግ ይቻላል፡፡ ቋንቋን ማስተማር በማይቻልበት ሁኔታ ግን መንፈሳዊውን ትምህርት በቋንቋቸው የሚማሩበትን አማራጭ መውሰድ ያስፈልጋል እንጂ ገና ለገና ቋንቋ እስኪማሩ ብሎ የልጆችን የመማሪያ ጊዜ በከንቱ ማባከን አይገባም፡፡

መፍትሔው: ልጆችና ወጣቶች በሚናገሩት ቋንቋ ማስተማር ነው!

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መሠረታዊ ዓላማ የክርስቶስን ወንጌል ለሰው ልጅ ሁሉ ያለምንም ልዩነት በሚገባው ቋንቋ ማስተማር፣ በአገልግሎትና በምስጢራት ማሳተፍና ለመንግስተ ሰማያት ማብቃት ነው፡፡ ማንኛውም የሰው ልጅ የቤተክርስቲያኒቱን እምነት፣ ሥርዓትና ትውፊት ለማወቅ ከሚናገረው ቋንቋ ውጭ ሌላ ቋንቋ መማር/ማወቅ አይጠበቅበትም፡፡ በራሱ ቋንቋ የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርት መማር፣ ከአገልግሎቱ መሳተፍ፣ ለሌሎችም ማስተማር ይገባዋል፡፡ የቤተክርስቲያን ትምህርትና አገልግሎትም በተወሰነ ቋንቋ ብቻ መታጠር የለበትም፡፡ ልጆችም፣ ወጣቶችም፣ አዋቂዎችም፣ አረጋውያንም በሚናገሩት ቋንቋ የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርት ሊማሩና ከአገልግሎትም ሊሳተፉ ይገባል፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮችም ምዕመናኑ በሚናገሩት ቋንቋ የሚያስተምሩና ለአገልግሎትም ይህንንኑ ቋንቋ የሚጠቀሙ ሊሆን ይገባል፡፡

በዝርወት ዓለም ተወልደው ለሚያድጉ ልጆችም ያለው የቋንቋ አጠቃቀምን የሚመለከተው የቤተክርስቲያኒቱ አስተምህሮ የተለየ አይደለም፡፡ ይህም በሚናገሩት ቋንቋ የቤተክርቲያንን ትምህርት እየተማሩ፣ በቋንቋቸው የቤተክርስቲያንን አገልግሎት እየተሳተፉ፣ በእምነትና በምግባር ተኮትኩተው ሊያድጉ ይገባል የሚል ነው፡፡ ልጆች በሚናገሩት ቋንቋ የሚያስተምሩ መምህራንን፣ የሚቀድሱ ካህናትን፣ የሚዘምሩ መዘምራንን፣ የሚጽፉ ሊቃውንትን ማፍራት ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱ ተቋማዊ ኃላፊነት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በዝርወት ዓለም ያለችው ቤተክርስቲያን በስደት፣ ለትምህርትና ለሥራ ከሀገር ቤት ለሚመጡት ምዕመናን ብቻ ትሆንና እነዚህ ከሌሉ የማትኖር ልትሆን ትችላለች፡፡ ቤተክርስቲያን ኩላዊት (የሁሉም፣ ዓለም ዓቀፋዊት) ናት ሲባልም ለሰው ልጅ በሚናገረው ቋንቋ ታስተምራለች ማለት ስለሆነ በአገልጋዮች ዘንድ ያለው የቋንቋ ስብጥር (Language diversity) ሊታሰብበትና ሊሠራበት ይገባል እንላለን፡፡

ከዚህ በተረፈ በአንዳንድ ወላጆችና አገልጋዮች ዘንድ እንደሚታየውም ልጆች በወላጆቻቸው ቋንቋ መማር ሳይፈልጉ እንዲማሩ ወይም በሚገባ በማይረዱት ቋንቋ ሃይማኖታዊ ትምህርት እንዲማሩ ተፅእኖ በማሳደር ሳይሆን በፍቅር ወደውት እንዲማሩ(በ)ት ማድረግ ይገባል፡፡ በተጽእኖ ማስተማር ለቋንቋው ያላቸውን ፍላጎትና አመለካከትም ሊቀይር ይችላል፡፡ ልጆችና ወጣቶች በሚናገሩት ቋንቋ ለእናስተምራቸው እንጂ በማይገባቸው ቋንቋ እንዲማሩ ባናስገድዳቸው መልካም ነው፡፡ ስለዚህ አስቀድሞ ቋንቋውን የማወቅ ፍላጎትን መፍጠር እና የቋንቋ ክህሎታቸውንም ማሳደግ ያስፈልጋል እንጂ ልጆችን ያለፍላጎታቸው ይህንን ቋንቋ ተማሩ ወይም በዚህ ቋንቋ ተማሩ ማለት ሕጋዊም፣ ሃይማኖታዊም መሠረት የለውም፡፡ በአጠቃላይ እያንዳንዱ ልጅ ወይም ወጣት በሚገባውና የተሻለ በሚረዳበት ቋንቋ የሚማርበትን አማራጭ መፍጠር ያስፈልጋል እንጂ ሁሉም ልጆች ወይም ወጣቶች በዚህ ወይም በዚያ ቋንቋ ብቻ ይማሩ የሚለው ጉንጭ አልፋ ክርክርም ለቤተክርስቲያን ዕድገት አይበጅም፡፡

ኑ ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠበቃ እንሁናት!

መግቢያ

ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በመጀመሪያይቱ መልእክቱ በዘመኑ በታናሹ ኤስያ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች “በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሀት ይሁን (1ኛ ጴጥ 3፡15)” በማለት ስለ ክርስቲያናዊ ጥብቅና አስተምሯቸዋል፡፡ በዚህም መልእክቱ ስለ ክርስቲያናዊ ጥብቅና (Christian apologetics) ሁለት መሠረታዊ ነጥቦችን አስተምሯል፡፡ በመጀመሪያ ስለ መሠረተ እምነታችን፣ ስለቤተክርስቲያናችን ሥርዓትና ትውፊት “ለምን?” ብለው ምክንያትን (reason) ለሚጠይቁን መልስ ለመስጠት ሁል ጊዜ የተዘጋጀን መሆን እንደሚያስፈልግ ነግሮናል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ለሚጠይቁን መልስ ስንሰጥ በየዋህነት/በጥበብ/  (gentleness) (ሰዎችን ሳናሰናክል፣ ተገቢውን ክብር በመስጠት) እና በፍርሀት/በአክብሮት/(respect) (እግዚአብሔርን በመፍራት፣ ህጉን በመጠበቅ) መሆን እንዳለበት መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ክርስቲያናዊ ጥብቅና (ለቤተክርስቲያን ጥብቅና መቆም) አስቀድሞ ቅዱሳን ሐዋርያት ከዚያም በእነርሱ እግር የተተኩ ሊቃውንት አባቶች ሲፈጽሙት የነበረ ዋነኛ የአገልግሎታቸው ተግባር ነው፡፡ በእምነት በመጽናታቸው፣ ለእምነታቸው ጠበቃ ሆነው፣ እነርሱ የሕይወት መስዋእትነትን ከፍለው ኦርቶዶክሳዊት እምነትን ስላቆዩልን ዛሬ “አባቶቻችን” ብለን ስንናገር አናፍርባቸውም፡፡ ሃይማኖትን መጠበቅ፣ ለሃይማኖትም ጠበቃ መሆንን ያስተማሩን እነርሱ ናቸውና፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ታላቅ ቦታ ከሚሰጣቸው አዋልድ ቅዱሳት መጻሕፍት መካከል ሃይማኖተ አበው የተባለው ድንቅ መጽሐፍ አንዱ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በየዘመናቱ የተነሱ ሊቃውንት አባቶቻችን በየዘመናቸው የተነሱ መናፍቃንና አጽራረ ቤተክርስቲያን ላነሷቸው ልዩ ልዩ የክህደት ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረትነት የተሰጡ መልሶችንና ሃይማኖትን የሚያጸኑ መልእክቶችን የያዘ ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ስለ ሃይማኖቱ ጥብቅና መቆሙን ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ ሲጽፍለት “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፣ ሩጫውን ጨርሻለሁ፣ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ..” (2ኛ ጢሞ 4፡7) በማለት መስክሯል፡፡ ሐዋርያው ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ ሲል በአሕዛብ ፊት፣ በአይሁድ ፊት፣ በሮማውያን ፊት ስለ ክርስቶስ ወንጌል በመመስከር የፈጸመውን ክርስቲያናዊ ጥብቅና ሲናገር ነው፡፡

ክርስቲያናዊ ጥብቅና ለቤተክርስቲያን እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት የአገልግሎት ዘርፎች አንዱ ነው፡፡ ስለዚህ ነው “ለቤተክርስቲያን ጥብቅና መቆም” በነገረ-መለኮት ትምህርት አንድ ዘርፍ ሆኖ “ጥብቅና ለክርስትና” (Theology of Apologetics) ተብሎ የሚሰጠው፡፡ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ሥራቸው ይህ ነውና፡፡ በምዕመናንና በመንፈሳውያን ማኅበራትም አንዱ ወሳኝ ጉዳይ ሆኖ በመደበኛነት የሚሠራበት አገልግሎት ነው፡፡ ነገር ግን ስለክርስቲያናዊ ጥብቅና በቂ ግንዛቤና የተቀናጀ እንቅስቃሴ ካለመኖሩም ባሻገር አንዳንዶች ለቤተክርስቲያንና ለክርስትና እምነታቸው ጠበቃ የቆሙ እየመሰላቸው ራሳቸውንና ቤተክርስቲያንን እየጎዱ ይገኛሉ፡፡ እኛም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር ስለ ክርስቲያናዊ ጥብቅና ምንነት፣ አስፈላጊነት፣ አግባብ ያለው አፈጻጸም እንዲሁም ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች እንዳስሳለን፡፡

የክርስቲያናዊ ጥብቅና ምንነት

በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥር የሚኖር አንድ ክርስቲያን እምነቱን (ሃይማኖቱን) በተመለከተ አምስት ነገሮችን ማወቅ አለበት፡፡ እነዚህም ምን (dogma) እንደሚያምን፣ ለምን (reason) እንደሚያምን፣ ያመነውን እንዴት መፈጸም እንዳለበት (Cannon)፣ ያመነውን እንዴት ለሌሎች ማሳወቅ (sharing) እንዳለበትና እምነቱን የሚፈታተን አስተሳሰብ ሲመጣ እንዴት መከላከል (defense) እንዳለበት ማወቅ ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር ክርስቲያናዊ ጥብቅና ማለት ለቤተክርስቲያን አስተምህሮ፣ ሥርዓትና ትውፊት ጠበቃ (ጠባቂ፣ አስጠባቂ፣ ተከላካይ) መሆን ማለት ነው፡፡ የቤተክርስቲያን ጠባቂ ክርስቶስ ቢሆንም የሰው ድርሻ የሆነውን ማበርከት ክርስቲያናዊ ጥብቅና ይባላል፡፡ በአራተኛውና በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለተነሱት መናፍቃን እነ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ቅዱስ ቄርሎስና፣ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ የሰጡት ምላሽ በቤተክርስቲያን ታሪክ ተጠቃሽ የክርስቲያናዊ ጥብቅና አገልግሎት ነው፡፡

የክርስቲያናዊ ጥብቅና አስፈላጊነት

የክርስቲያናዊ ጥብቅና ዓላማዎች ብዙ ናቸው፡፡ የክርስቲያናዊ ጥብቅና ዋነኛ ዓላማ ግን የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት፣ ሥርዓትና ትውፊት እንዲጠበቅ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም ያመኑትና የተጠመቁት እስከመጨረሻው እንዲጸኑና ለመንግስተ ሰማያት እንዲበቁ ማድረግ ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ያላመኑት የክርስቶስን ወንጌል እንዲያውቁና እንዲያምኑ፣ አምነውና ተጠምቀውም ጸጋን ከሚያሰጡ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን እንዲካፈሉ፣ በእምነታቸው ጸንተው ምግባር ትሩፋትን ሠርተው፣ በእምነታቸውና በምግባራቸው ለቤተክርስቲያናቸው ጌጥና መታወቂያ ሆነው ሰማያዊውን መንግስት እንዲወርሱ ማድረግ ነው፡፡ የቤተክርስቲያን አስተምህሮም ሳይበረዝ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ የክርስቲያናዊ ጥብቅና ድርሻው ከፍተኛ ነው፡፡ ስለሆነም ለክርስትና ሃይማኖታቸው ጥብቅና የሚቆሙት ዋጋቸው በሰማያት ታላቅ ነው፡፡ ሐዋርያው ይሁዳ “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠች ሃይማኖት እንድትጋደሉ እለምናችለሁ” (ይሁዳ 1፡3) ያለውም ለሃይማኖታችን ጥብቅና እንድንቆም ነው፡፡ ለሃይማኖት መጋደል ማለትም በቃልና በተግባር ለክርስትናና ለቤተክርስቲያን ጥብቅና መቆም ማለት ነው፡፡

የክርስቲያናዊ ጥብቅና መንገዶች

ለኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጥብቅና የምንቆመው በአራት መንገዶች ነው፡፡

እውነተኛ እምነቷን፣ ሥርዓቷንና ትውፊቷን በመግለጥ: ሰዎች የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ፣ ሥርዓትና ትውፊት በሚገባ እንዲያውቁ፣ አውቀውም እንዲያምኑበት ማድረግ የክርስቲያናዊ ጥብቅና መጀመሪያውና መሠረታዊው ዓላማ ነው፡፡ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና አውቆ ማሳወቅ፣ ጠብቆ ማስጠበቅ ክርስቲያናዊ ጥብቅና ነው፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት የሰፈረውን እውነት፣ የሊቃውንተ ቤተክርስቲያንን ትምህርት አስተባብሮ ለሰዎች ማስተማር ቀዳሚው የክርስቲያናዊ ጥብቅና ሥራ ነው፡፡ ኀልወተ እግዚአብሔርን ለማያምኑ ሰዎች የተለያዩ የኀልወተ እግዚአብሔር መገለጫዎችን አደራጅቶ ማስተማርም ክርስቲያናዊ ጥብቅና ነው፡፡

በቤተክርስቲያን ላይ የሚነሱ መሠረተ ቢስ ወቀሳዎችን ሐሰትነታቸውን በማጋለጥ: ቤተክርስቲያን ያልሆነችውን ሆነች፣ ያላደረገችውን አደረገች፣ የማታደርገውን ታደርጋለች፣ ተግታ የምታደርገውን አታደርግም ለሚሉ ወገኖች ይህ  ወቀሳቸው እውነት እንዳልሆነ ማስረዳት ሁለተኛው የክርስቲያናዊ ጥብቅና ዘርፍ ነው፡፡ ለምሳሌ “ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ክርስቶስን አትሰብክም” ለሚሉ ወገኖች ቤተክርስቲያናችን ክርስቶስን ያልሰበከችበትና የማትሰብክበት ጊዜ እንደሌለ ምሳሌን በመጠቀም ማሳየት፣ “ቤተክርስቲያን ቅዱሳንን ታመልካለች” ለሚሉት እንዲሁ ቤተክርስቲያን እግዚአብሔርን ብቻ እንደምታመልክና ቅዱሳንን እንደምታከብር ማስረዳት፣ “ቤተክርስቲያን ስንፍናን ታስተምራለች” ለሚሉትም ቤተክርስቲያን ሥራን ምን ያህል ዋጋ ሰጥታ እንደምታስተምር፣ “የድህነት ምክንያት ናት… ወዘተ” ለሚሉትም ሁሉ በማስረጃ የተደገፈ በቂ ምላሽ መስጠት ክርስቲያናዊ ጥብቅና ነው፡፡ ይህንንም የምናደርገው ክርስቲያኖችን ከመጠበቅ አንጻር ነው፡፡

ቤተክርስቲያንን የሚያስነቅፉ አሰራሮች እንዲስተካከሉ የራስን ድርሻ ማበርከት: በዚህ ዘርፍ በመጀመሪያ ደረጃ እኛ ራሳችን የምንሠራው ቤተክርስቲያንን እንዳያስነቅፋት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለን አገልጋዮችም ሰዎች ነንና እንድንበረታ በጸሎት፣ እንድንጠነክር በሀሳብ (በምክር)፣ በተግባር መደጋገፍ ክርስቲያናዊ መገለጫችን ሊሆን ይገባል፡፡ ቤተክርስቲያንን የሚያስነቅፍ ሥራ የሚሠሩትም እንዲማሩና እንዲያውቁ፣ እንዲመከሩና እንዲታረሙ ለቤተክርስቲያን ሥርዓት ጥብቅና መቆም ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አልፈው ለሌሎች መሰናክል የሚሆኑ ከሆነ ደግሞ ለቤተክርስቲያንና ለእግዚአብሔር መንገር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንጻር የክርስቲያናዊ ጥብቅና ውጤት የቤተክርስቲያንን ሥርዓት የሚጠብቁና የሚያስጠብቁ (የቤተክርስቲያን ጠበቃዎችን) ማብዛት ነው፡፡

ምዕመናንን ሊያሳስቱና ሊያስቱ የሚችሉ ሐሰተኛ አስተምህሮዎች በቂ ምላሽ መስጠት: በዘመናችን እንደ አሸን ለፈሉት የሐሰት ትምህርቶች ለሁሉም ባይሆንም በክርስቲያኖች አእምሮ ጥያቄ የሚፈጥሩና ምዕመናንን ሊያስቱ ለሚችሉት በቂ ምላሽ መስጠት ከሊቃውንቱና ከሰባክያነ ወንጌሉ የሚጠበቅ ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉም ክርስቲያን የራሱ ድርሻ አለው፡፡ ሐሰተኛ አስተምህሮዎች ለምንና እንዴት ሐሰት እንደሆኑ፣ ብንከተላቸው ለድኅነት (ለጽድቅ) የማያበቁ መሆናቸውን ማጋለጥ ክርስቲያናዊ ጥብቅና ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ እውነተኛው ሃይማኖት (አስተምህሮ) ለምንና እንዴት እውነት እንደሆነ፣ ለመዳንም የሚያደርስ መሆኑን ማስረዳትም የዚሁ አካል ነው፡፡ ይህንንም ስናደርግ ዒላማችን ሰዎችን ያሳሳተው የስህተት አስተምህሮ ላይ ሆኖ ለተሳሳቱ ወገኖቻችን ግን ፍቅርን በማሳየት ሊሆን ይገባል፡፡ ሐሰተኛ ትምህርቶችንም ስንሞግት መሠረታዊ የሆኑ መረጃዎችን አደራጅተንና ተንትነን በማያዳግም መልኩ ሊሆን ይገባዋል እንጂ “አለባብሰው ቢያርሱ…” እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች

ለቤተክርስቲያን ጥብቅና ስንቆም መጠንቀቅ ያለብን ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ጥብቅና የምንቆምለትን የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ፣ ሥርዓትና ትውፊት ማወቅ፣ ማመንና መፈጸም ይኖርብናል፡፡ እኛ የማንፈጽመውን ነገር ሌሎችን ፈጽሙ እያልን ጥብቅና መቆም ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ አይደለምና፡፡ጠንቅቀን ሳናውቅ ጥብቅና ለመቆም ብንሞክር ተፈትነን ከጽናታችን ልንወድቅ እንችላለንና አስቀድመን ጠይቀን እንወቅ፡፡ ሌላውን ለማዳን አስቀድሞ ራስ መዳን ያስፈልጋልና አስቀድመን ራሳችንን እናድን፡፡ ያን ጊዜ ሌላውን ማሳወቅ፣ ለቤተክርስቲያንም ጠበቃ መሆን እንችላለን፡፡

በሁለተኛ ደረጃ  ለቤተክርስቲያን ጥብቅና የምንቆምበት መንገድ ሥርዓትን የተከተለና ለሌሎች አስተማሪ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለቤተክርስቲያን ጥብቅና የምንቆምበት መንገድ የራሳችንን ተአማኒነት የሚያሳጣ፣ ሰዎችን የሚጎዳ፣ ቤተክርስቲያንን የሚያሰድብ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳስተማረን በየዋህነትና በፍርሀት ለቤተክርስቲያን ጥብቅና እንቁም፡፡ ሌሎች ቤተክርስቲያንን ስለጎዱ (ጎድተዋታል ብለን ስላሰብን) እኛ እነርሱን ለመጉዳት አናስብ፡፡ ክርስትናችንንና ቤተክርስቲያንን የምንጠብቅበትን አካሄድ በጥላቻ በመነቃቀፍ ሳይሆን እግዚአብሔርን በመፍራት እናድርገው፡፡ በጥላቻና በክርክር የሚደረግ ከሆነ ክርክሩን ብንረታ እንኳን ሰውን ማትረፍ ላንችል እንችላለን፡፡ ብዙ መመለስ የሚችሉ ሰዎች ከአያያዝ ጉድለት ጠፍተው ቀርተዋልና ክርስቲያናዊ ጥብቅናችን በየዋህነት፣ በብልሀት፣ በመከባበርና በፍቅር ሊሆን ይገባል፡፡

እምነታችንንና ቤተክርስቲያንን ለመጠበቅ በምናደርገው ሂደት ውስጥ መስዋእትነት (የጊዜ፣ የሞራል፣ የገንዘብ፣ የሕይወት) መክፈል ካስፈለገ በጸጋ ለመቀበል መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ለቤተክርስቲያን ጠበቃ ለመሆን ስንተጋ ሠርተን ራሳችንን (ምድራዊ ኑሮአችንን) የምንለውጥበትን ጊዜና ጉልበት እንዲሁም አእምሮ ይወስድብናል፡፡ በአጽራረ ቤተክርስቲያንና የክርስትና መንገድ እውነትነት ባልገባቸው የዋሀን የስድብ፣ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሊከፈትብን ይችላል፡፡ ከዚህም አልፎ በሐሰት ክስ እየከሰሱ ሊያንገላቱንና ሊያሳስሩን እንዲሁም ጊዜያችንንና ገንዘባችንን ሊያስወጡን ይችላሉ፡፡ አልፎ አልፎም ማስፈራራት፣ የአካል ጉዳት፣ የሕይወት አደጋም ሊደርስብን ይችላል፡፡ ነገር ግን ዋጋችን በሰማይ ነውና በጽናትና በጥብዐት ለቤተክርስቲያን ጥብቅና ቆመን ቤተክርስቲያናችንን ከተኩላዎች ልንከላከል ይገባናል፡፡

ለቤተክርስቲያን ጥብቅና መቆም የሁሉም ክርስቲያን ኃላፊነት ነው፡፡ “እኛ ምን አገባን” ወይም “ሌሎች ይሠሩታል” ብለን የምንተወው ጉዳይ አይደለም፡፡ ክርስትናችንንና ቤተክርስቲያናችንን የምንጠብቀውም በመግደል ሳይሆን በመሞት፣ ጉዳትን በማድረስ ሳይሆን መከራን በመቀበል፣ በጦርነት ሳይሆን ሰላምን በመስበክ መሆኑን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ተምረናል፡፡ ብርሀነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም “ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ልናደርግ አንችልምና (2ቆሮ.13፡8)” እንዳለው እውነት በሆነው በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሠረተችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ የሚነሱ ለጊዜው የሚጎዷት የሚያጠፏት ይመስላቸዋል እንጂ እግዚአብሔር በደሙ የዋጃትና የሚጠብቃት ቤተክርስቲያን በደካሞች እጅ ልትጠፋ አትችልም፡፡ ቤተክርስቲያንን በማቃጠልና ክርስቲያኖችን በመግደል ቤተክርስቲያንን ማጥፋት የሚቻል ቢሆን ኖሮ በዘመነ ሰማዕታት የነበሩ ነገሥታት ባጠፏት ነበር፡፡ ነገር ግን እንደነ ቅዱስ ጊዮርጊስና ቅደስት አርሴማ ያሉ ታላላቅ ሰማዕታትን (የእውነት ምስክሮችን) እንድታፈራ አደረጓት እንጂ አላጠፏትም፡፡ በእውነት ላይ የሚነሱ ራሳቸው ይጠፋሉ እንጂ “የገሃነም ደጆች አይችሏትም” እንደተባለ (ማቴ 16፡18) እውነትን ሊያጠፏት አይችሉም፡፡ ለእውነት የሚተጉ፣ እውነት የሆነችውን ደገኛይቱን የሃይማኖት መንገድ የሚያቀኑ፣ ስለእውነተኛይቱ እምነት ጥብቅና የሚቆሙና ስለእውነትም መከራን የሚቀበሉ ግን በመጨረሻው ቀን ከእውነተኛው አምላክ የጽድቅ አክሊልን ይቀበላሉ፡፡ እኛም ለእውነት ጥብቅና ቆመን በቀኙ ለመቆም ያበቃን ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡

ወስብሃት ለእግዚአብሔር

የካህናት፣ የሰባክያንና የዘማርያን አለባበስ፡ ሁሉን በአግባብና በሥርዓት አድርጉ!

መግቢያ

የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ያልሆኑትን መስሎ ለመታየት የማስመሰል ጥረት ያደርጉ የነበሩ የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን አገልጋዮችን በገሰጸበት መልእክቱ “ሁሉን በአግባብና በሥርዓት አድርጉ” (1ኛ ቆሮ. 14፡40) ብሏል፡፡ አስተምህሮዋን በነቢያትና በሐዋርያት መሰረት ላይ ያጸናች ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንም መንፈሳዊ አገልግሎቷ በሥርዓት የሚመራ፣ ከግለሰባዊ ከንቱ ውዳሴ ይልቅ ህገ ሃይማኖትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያን የሚጎላባት በመሆኗ በእግዚአብሔር ቸርነት ሺህ ዘመናትን ለመሻገር ችላለች፡፡ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ማለት የተጻፈ ወይም በመንፈሳዊ ዓላማ በልማድ የዳበረ መንፈሳዊ አምልኮና አስተምህሮን የምንመራበት መክብብ ነው፡፡ ለሚሰራ ሥራ (ለሚፈጸም አገልግሎት) ተብሎ ሥርዓት ይተከላል እንጂ ሥርዓት በራሱ የሚቆም አይደለም፡፡ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ከፍ ያለ መንፈሳዊ ዓላማን የምንፈጽምበት መንገድ ነውና፡፡ ስለሆነም ማንኛውም የቤተክርስቲያን ሥርዓት ከፍ ያሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮዎቻችንና መንፈሳዊ እሴቶቻችንን ሊያጸና እንጂ ሊገዳደር አይገባውም፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጦማር የተዳሰሰው የካህናት፣ የሰባክያንና የዘማርያን (መዘምራን) አለባበስም ፍጹም መንፈሳዊነትን የተላበሰና ከግለሰቦች ስጋዊ ፍላጎት አንጻር ያልተቃኘ ሊሆን ይገባዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሺህ ዘመናት የአምልኮተ እግዚአብሔር ኀልወቷ ጠብቃ ካቆየቻቸው መንፈሳዊ ትውፊቶች መካከል መነኮሳት፣ ካህናት፣ መዘምራንና ምዕመናን በአገልግሎት ወቅት የሚለብሷቸው አልባሳት ይጠቀሳሉ፡፡ ካህናትም ሆኑ ምዕመናን የትንሣኤው ምስክሮች እንደሆኑ ቅዱሳን መላእክት ነጭ ነጠላ በመስቀል ቅርጽ አመሳቅለው ለብሰው ሞትን ያሸነፈ የክርስቶስን ትንሣኤ ይመሰክራሉ፡፡ ካህናት በጸሎተ ቅዳሴ ለአምልኮ የተለየ አለባበስ ይለብሳሉ፡፡ የመነኮሳት ከካህናት፣ የካህናት ከዲያቆናት አለባበሳቸው የተለየ ነው፡፡ የአልባሳቱ መንፈሳዊ ዓላማም ለተለየ መንፈሳዊ አገልግሎት መቆምን የሚያሳይ እንጂ ለውበት ወይም ለታይታ የሚደረግ አይደሉም፡፡

ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገልግሎት ወቅትም ሆነ በሌሎች ጊዜያት አለባበስን ያልሆኑትን መስሎ ለመታየት (ለማስመሰል) እንዲሁም ግለሰባዊ ስብዕናን ከፍ በማድረግ በሰዎች ዘንድ መንፈሳዊ ለዛ የሌለው መወደድን ለማግኘት ሲውል ታዝበናል፡፡ ለምሳሌ ቄሶች መነኮሳትን ለመምሰል የመነኮሳትን ዓይነት አለባበስ ሲለብሱ ሰባክያንና መዘምራንም ከመደበኛ ልብሰ ተክህኖ ውጭ ትውፊታዊ መሰረት የሌለው ቀሚስ በማድረግ፣ ሀብልና መስቀልን  ለታይታ በማንጠልጠል ሲደክሙ ይስተዋላሉ፡፡ ከዚያም ባሻገር ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች፣ ዘፋኞችና ሌሎችም ምዕመናን በዚህ መሰል የአለባበስ ፉክክር ውስጥ እየገቡ የቤተክርስቲያንን አልባሳት ልማድና ትውፊት ለየራሳቸው እውቅናና ዝና ሲጠቀሙበት እያስተዋልን ነው፡፡ በባቢሎን ምርኮ ዘመን የቤተመቅደስ ንዋያትን ያለአግባብ የሚጠቀሙትን የቀጣ እግዚአብሔር ዛሬም እንዳለ፣ ስለ ቤቱ፣ ስለ ሥርዓቱም እንደሚገደው ማወቅና መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

እነዚህ ሰርጎ ገብ ልማዶች በተለያዩ ምክንያቶች ትክክል መስለው እንዲቀርቡ፣ ከአለባበሶቹ ጀርባ ያለው ስር የሰደደ የከንቱ ውዳሴ ፍላጎትም በትክክለኛ እይታ ታይቶ ችግሮች እንዳይቀረፉ የተለያዩ ምክንያቶች የየራሳቸውን አሉታዊ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች አንዱ ስለዚህ ጉዳይ በአደባባይ የሚሞግቱ ጽሁፎችም ሆነ የኦዲዮ ቪዥዋል ምንጮች አለመኖር (ማነስ) ነው፡፡ አንዳንዶች “ቤተክርስቲያን ስንት አሳሳቢ ጉዳይ እያለባት በዚህ ጉዳይ ጊዜ ማባከን ወቅታዊ ላይሆን ይችላል” የሚል ምልከታ አላቸው፡፡ እውነትም የአለባበስ ጉዳይ ከላይ ሲታይ አሳሳቢ ያልሆነ ቀላል ጉዳይ ይመስላል፡፡ በአጽንኦት ለተመለከተው ግን የብዙ ዘመናውያን ችግሮች ማሳያ ነው፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች አንድ ካህን ወይም መምህር የተሻለ ተቀባይነት የሚያገኘው አለባበሱ ደማቅና ለፖስተር ማስታወቂያ የተመቸ ነው ተብሎ ሲታሰብ እንደሆነ በተደጋጋሚ ታዝበናል፡፡ በዚህም የተነሳ የአገልግሎቱ ትኩረት ከይዘት ወደ ቅርጽ እየተለወጠ መሄዱንና አስመሳይነትን በቋሚነት የሚያነብር ድባብ እየተፈጠረ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ከዚያም ባሻገር የአለባበስ ሥርዓት አልበኝነት ከተባባሰ  (ከ1990ዎቹ ፣ በተለይም ከ2000 ዓ.ም) በኋላ የችግሩን ምንጭ ከነባራዊው የቤተክርስቲያን ልማድ ጋር ከማገናዘብ ይልቅ ተበራክቶ ለሚያዩት ልማድ (ሁነት) የአስተምህሮ ድጋፍ ለመስጠት በሚመስል መልኩ ከሁነት በኋላ የሚሰጡ በልክ የተሰፉ ማሳመኛዎች (ex post facto justifications) በመጽሀፍ መልክ የሚጽፉ ሰዎች ስላሉ፤ እንደዚሁም እነዚህ መጤ ልማዶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከመስፋፋታቸው የተነሳ ብዙዎች መጤውን ልማድ የማይከተሉ የነበሩ አገልጋዮችም እየተጠለፉ ሲወድቁ እያስተዋልን ነው፡፡ በብዙ መመዘኛዎች ቤተክርስቲያንን በቅንነትና፣ በእምነት፣ በእውቀትና በመሥዋዕትነት የሚያገለግሉ በርካታ ካህናት፣ ሰባክያንና ዘማርያን በዚህ ልማድ መወሰዳቸው ለሌሎችም የስህተት ማስተባበያ አመክንዮ ሆኖ ሲቀርብ መስማት ያልተለመደ አይደለም፡፡ ብዙ ሰዎች ጉዳዩን በራሱ ከመመርመር ይልቅ “እገሌና እገሌ እንኳ እንደዚያ ይለብሱ የለም እንዴ?” በሚል ያልበሰለ አተያይ ግራ ሲጋቡ እናስተውላለን፡፡ በጊዜ ሂደትም አረሙ ሰብል፣ ሰብሉ አረም መስሎ ማደናገሩ አይቀርም፡፡ ስለሆነም ለመነሻ ይሆን ዘንድ በዚህች የአስተምህሮ ጦማር የካህናትን፣ የሰባክያነ ወንጌልንና የመዘምራንን አለባበስና ተያይዘው የሚታዩ ችግሮችን እንዳስሳለን፡፡ የመፍትሄ ሀሳብም እንጠቁማለን፡፡ ሌሎቻችሁም በጉዳዩ ላይ ብትጽፉ ወደተሻለ  ተጠየቃዊ ተግባቦት መድረስ ይቻላል ብለን እናምናለን፡፡

capes_all4

የካህናት አለባበስ በአገልግሎት ጊዜያት 

ልብሰ ተክህኖ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ነው፡፡

ልብሰ ተክህኖ (የክህነት ልብስ) የሚባለው ካህናት ለቤተመቅደስ አገልግሎት ሲፋጠኑ የሚለብሱት ለአገልግሎት የተለየ ልብስ ነው፡፡ ይህም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ነው፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ለሊቀ ነቢያት ሙሴ እንዲህ በማለት ትዕዛዝን ሰጥቶታል፡፡  “የተቀደሰውንም ልብስ ለክብርና ለመለያ እንዲሆን ለወንድምህ ለአሮን ሥራለት፡፡ አንተም የጥበብ መንፈስ ለሞላሁባቸው በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ተናገር፡፡ እነርሱም ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ ለአሮን ቤተመቅደስ የሚሆን የተለየ ልብስ ይሥሩ፤ የሚሠሩአቸውም ልብሶች እነዚህ ናቸው፤ ልብሰ እንግድዓ፣ ልብሰ መትከፍ፣ ቀሚስም፣ ዥንጉርጉር እጀ ጠባብ፣ መጠምጠሚያ፣ መታጠቂያም፤ እነዚህንም በክህነት ያገለግሉኝ ዘንድ ለወንድምህ ለአሮን፣ ለልጆቹም የተቀደሰ ልብስ ያድርጉ፡፡ ወርቅ፣ ሰማያዊና ሐምራዊ፣ ቀይ ግምጃ፣ ጥሩ በፍታም ይውሰዱ” (ኦሪት ዘጸአት 28፡2-5)፡፡ ይህንንም መሠረት በማድረግ ኦርቶዶካሳዊት ቤተክርስቲያን ልብሰ ተክህኖን ለቅዳሴ ጸሎትና ለሌሎች አምልኮተ እግዚአብሔር ለሚፈጸምባቸው አገልግሎቶች ትጠቀምበታለች፡፡ ለጽድቅ አገልግሎት የተመረጡ ካህናትም የአገልግሎታቸውን ክብር ለማሳየት የተለየ ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ሥርዓተ አምልኮን ይፈጽማሉ፡፡

በዚህም መሠረት በጸሎተ ቅዳሴ የሚሳተፉ አምስቱም ልዑካን በችግር ምክንያት ካልሆነ በቀር ተመሳሳይ ልብሰ ተክህኖ  (ብፁዓን ጳጳሳቱ የጳጳስ፣ ቀሳውስቱ የካህን፣ ዲያቆናቱም የዲያቆን) ማድረግ እንዳለባቸው ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ያስረዳል፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ያለ ምንም አሳማኝ የጤና ምክንያት የራሳቸውን ልብስ አሰፍተው የሚቀድሱ ሰዎች ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህም ልማድ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የጣሰ ከመሆኑም በላይ እየዋለ እያደረ ሲሄድ ሰዎች በራሳቸው ልብስ (ያለ ልብሰ ተክህኖ) የመቅደሱን አገልግሎት እንፈጽም ወደ ማለት ሊመራ ይችላል፡፡ ስለዚህም ካህናትና ምዕመናን እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት በጊዜ እንዲታረም የበኩላቸውን ድርሻ ሊያበረክቱ ይገባል፡፡ ምክር ለሚሰሙት መምከር ይገባል፡፡ ምክር ለማይሰሙትና ለተራ ውዳሴ ከንቱ ለሚያደርጉት ደግሞ የሚሳሱለትን ክብር ሆን ብሎ በመንፈግ ለጥቅማቸው መቅጣት ይሻላል፡፡

ልብሰ ተክህኖን ለታይታ ማድረግ ኃጢአት ነው፡፡

የልብሰ ተክህኖ ዓላማ ለተለየ አገልግሎት መቆምን በማሳየት ልዩ ለሆነ አምልኮ ልዩ የሆነ መንፈሳዊ አለባበስን መጠቀም ነው፡፡ የልብሰ ተክህኖ ዓላማ ማማር፣ መድመቅ ወይም ጎልቶ መታየት አይደለም፡፡ ይሁንና የእግዚአብሔርን ቤት ለማገልገል ምልክት እንዲሆናቸው የተሰጣቸውን ልብሰ ተክህኖ ለግል ታይታና ክብር የሚጠቀሙ አስመሳይ አገልጋዮች በየዘመናቱ ነበሩ፤ አሁንም አሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በሚያስተምርበት ጊዜ የአይሁድ አለቆችን ከነቀፈባቸው ምክንያቶች አንዱ የታይታና የማስመሰል አለባበሳቸው ነው፡፡ “የሚሠሩትን ሥራቸውን ሁሉ ለሰው ሊታዩ ይሠሩታልና፤ አሸንክታባቸውን ይዘረጋሉ፤ የልብሳቸውንም ዘርፍ ያስረዝማሉ፡፡ በማዕድ ጊዜ በክብር ስፍራ በምኩራብም በፊተኛው ወንበር መቀመጥን ይወድዳሉ፡፡” (ማቴ. 23፡5-6)እንዲል፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋል የሚገባን ጌታ የአይሁድ አለቆችን የወቀሳቸው ልብሰ ተክህኖ በመልበሳቸው ሳይሆን ለታይታ በማድረጋቸው ነው፡፡ ዛሬም ልብሰ ተክህኖን ለታይታና ለማስመሰል እንዲሁም ፎቶ በመነሳት በየማኅበራዊ ሚዲያው የሚለጥፉና ምድራዊ ታዋቂነትንና ዝናን የሚናፍቁ ‘ካህናት’ ለእነዚያ የአይሁድ ካህናት የተነገረው አምላካዊ ተግሳጽ ይመለከታቸዋል፡፡ 

በአለባበስ መነኩሴ መምሰል የሚፈልጉ ቀሳውስት

በቤተክርስቲያን ሥርዓት መነኮሳት ራሳቸውን ለመንፈሳዊ ህይወት ለይተው፣ ከጋብቻና ሌሎች ምድራዊ ደስታዎች ርቀው የሚኖሩ ናቸው፡፡ መነኮሰ ማለት ሞተ ማለት ስለሆነ መነኮሳት ለተግባረ ሥጋ የሞቱ መሆናቸውን ለማሳየት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በለበሳትና በመከራው ወቅት ገራፊዎቹ እጣ በተጣጣሉባት ሥርወጥ ቀሚስ አምሳል ቀሚስን ይለብሳሉ፤ አይሁድ በጌታችን ዘላለማዊ ንግስና በመዘበት በራሱ ላይ ባቀዳጁት አክሊለ ሶክ (የእሾህ አክሊል) አምሳል በራሳቸው ላይ አክሊልን (ቆብን) ያደርጋሉ፡፡  መነኩሴ ካህን ሆነም አልሆነም ቀሚስና ቆብ ማድረግ የቤተክርስቲያናችን ሥርዓት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትውፊትና ልማድ መሰረት ቀሳውስት እንዲሁም ሌሎች መነኮሳት ያልሆኑ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ህጋውያን (በጋብቻ ተወስነው መኖርን የመረጡ) ናቸውና እንደ መነኮሳት ለዓለም ሥራ የሞቱ ናቸው አይባልም፡፡ አለባበሳቸውም እንዲሁ ከመነኮሳት የተለየ ነው፡፡ መደበኛ ልብሰ ተክህኖ ከሚለበስባቸው ከቅዳሴና መሰል የአምልኮ ጊዜያት ውጭ ቀሳውስትና ሌሎች መነኮሳት ያልሆኑ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደማንኛውም ምዕመን መንፈሳዊና ማኅበራዊ እሴቶችን የጠበቀ አለባበስ፣ እንዲሁም እንደየክብራቸው እንደየማዕረጋቸው በቤተክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት የተለመደውን (ከመነኮሳት ጋር የማይምታታ) አለባበስ እንዲለብሱ የቤተክርስቲያን ሥርዓት ይፈቅዳል፡፡ እንደ ህጋዊው ሙሴ በቤተ እግዚአብሔር የተሾሙ የክርስቶስ መልእክተኞች ናቸውና ከሙሴ በተወረሰ ሥርዓት በራሳቸው ላይ ጥምጣም ይጠመጥማሉ፡፡

በኦሪት ዘፀአት 34፡29-35 ታሪኩ እንደተፃፈው ሊቀ ነቢያት ሙሴ በሲና ተራራ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመና ከጸለየ በኋላ ሁለቱን ጽላቶች ተቀብሎ ከተራራው ሲወርድ ፊቱ በብርሃን ተመልቶ ያንጸባርቅ ስለነበር እሥራኤል ዘሥጋ ቀርበው ሊያነጋግሩት አልቻሉም፡፡ ስለሆነም ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ተነጋግሮ በወጣ ጊዜ ፊቱን በጨርቅ ይሸፍንላቸው ነበር፡፡ አባቶቻችን ቀሳውስትና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ጌታችን እንደተናገረ “ሙሴና ነቢያትን (የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር)” ለምዕመናን እንዲያስተምሩ የተሾሙ ናቸውና ከሙሴ በተወረሰ መንፈሳዊ ትውፊት በራሳቸው ላይ ነጭ ጥምጣምን ይጠመጥማሉ፡፡ (ማቴ. 23፡2፣ ሉቃስ 16፡29) ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ (በተለይም ከሀገር ውጭ ባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያክርስቲያናት) እየተዘወተረ የመጣው ልማድ ህጋውያን ካህናት (ቀሳውስት) እንደ ሥርዓቱ የካህናትን አክሊል አድርገው ከመቀደስ ይልቅ የመነኮሳትን አስኬማ የሚመስል ቆብ ማድረግ ጀምረዋል፡፡

ከጸሎተ ቅዳሴ ባሻገርም በሌሎች “በህዝብ የመታያ” ተብለው በሚታሰቡ ጊዜያት ቀሳውስት (ቄሶች) ከመነኩሴ ጋር የሚመሳሰል አልባሳትን ማዘውተር በአንዳንድ የከተማ አካባቢዎችና በውጭ ሀገራት ባሉ አጥቢያዎች እየተለመደ መጥቷል፡፡ መነኩሴ ሳይሆኑ መነኩሴ መምሰል ምን ያደርጋል? በቀደመው ልማድ ቀሳውስት ከመደበኛ ልብስ በላይ ነጠላ እና (ወይም) ጥምጣም ያደርጋሉ እንጂ እንደ መነኩሴ ቀሚስና አስኬማ ማድረግ የቀሳውስት መለያ አይደለም፡፡ የዚህ መሰረቱ የማይታወቅ አዲስ ልማድ መነሻ ምንድን ነው? የሚለውን በተመለከተ ልዩ ልዩ መላምት መስጠት ይቻላል፡፡ መንፈሳዊ አመክንዮ ግን የለውም፡፡ የቀሳውስት ቆብ የማጥለቅ ልማድ እንደ አሁኑ በአንዳንድ ቦታዎች የተለመደ ከመምሰሉ በፊት በልዩ ልዩ ቀልድ መሰል ማባበያ የተጀመረ ነው፡፡ ከእነዚህ አንዱ “የፀሐይ መከላከያ ቆብ” የሚለው መሰረተ ቢስ አመክንዮ ሲሆን ሌላው “የክብር ቆብ” የሚባለው ወለፈንድ አገላለጽ ነው፡፡ ይሁንና በሰው ዘንድ ያልተገባ ክብርን ለማግኘትና ያልሆኑትን ለመምሰል የሚደረግ አስመሳይነት የክብር ሳይሆን የክብረ ቢስነት ማሳያ ነው፡፡ ለመሆኑ የዚህ መጤ ልማድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ምን ያህልስ አሳማኝ ናቸው? እስኪ ለምሳሌ ያህል የተወሰኑትን ምክንያቶች እንመልከት፡፡ 

ከነጠላና ጥምጣም ይልቅ ቀሚስና ቆብ ለሥራና ኑሮ ስለሚቀል ነው?

አንዳንድ ሰዎች በአንዳንድ ከተሞችና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ቀሳውስት ለጀመሩት ይህን መሰል ልማድ እንደ መከራከሪያ የሚያቀርቡት ነጠላና ጥምጣም ማድረግ ለሥራና ኑሮ ስለሚከብድ ነው የሚለው ነጥብ ነው፡፡ እውነት ነው ነጠላና ጥምጣም አድርጎ መደበኛ ሥራን ማከናወን ሊከብድ ይችላል፡፡ ይሁንና ነጠላና ጥምጣም ማድረግ ቀሚስና ቆብ ከማድረግ ይቀላል እንጂ አይከብድም፡፡ ቀሳውስት ህጋውያን እንደመሆናቸው ኑሮን ለማሸነፍ ላይ ታች ማለታቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህ በሁሉም ጊዜ ነጠላና ጥምጣም ማድረግ አለባቸው የሚል ሥርዓትም ልማድም የለም፡፡ በገጠሩ የሀገራችን ክፍል ያሉ ደገኛ ካህናት በዋናነት እንደሌላው ገበሬ እያረሱ ቤተሰባቸውን እንደሚያስተዳድሩ ይታወቃል፡፡ በዚህም ጊዜ እንደ ካህን መስቀላቸውን ይዘው፣ እንደ ማንኛውም ሰው ደግሞ ለሥራቸው በሚገባ አለባበስ ተግባራቸውን እንደሚፈጽሙ ይታወቃል፡፡ በከተማም ቢሆን ከተወሰኑ በመጤው ልማድ ከተሸነፉ ቦታዎች ውጭ ካህናት የመነኩሴ የሚመስል ቆብ አያደርጉም፡፡ ቀሚስና ቆብ ማድረግ ጥምጣም ከማድረግ ይልቅ “ለሥራ የሚያመች” ነው ሊባል አይችልም፡፡ስለዚህ በማይመስል አመክንዮ ተደግፎ አዲስ ሥርዓት ማንበር አያስፈልግም፤ ምክንያታዊም መንፈሳዊም አይደለምና፡፡

ቀሳውስት ከሌላው ተለይተው ለመታወቅ እንደ መነኩሴ መልበስ አለባቸው?

በአንዳንዶች ዘንድ መነኩሴ የሚያስመስለው አለባበስ ከሚመረጥባቸው ምክንያቶች አንዱ “ነጠላ መልበስማ ማንም ሊለብስ ይችላል፣ ስለዚህ ካህናት ተለይተው እንዲታወቁ ቀሚስና ቆብ ያስፈልጋል” የሚለው መከራከሪያ ነው፡፡ ቀሳውስት ለምዕመናን መንፈሳዊ ሀኪሞቻቸው ናቸውና በየሄዱበት ሁሉ ምዕመናን ለይተው ቢያውቋቸው ጠቃሚ ነው፡፡ ለሚቻላቸው ቀሳውስት ሁሉ በተቻለ መጠን የቤተክርስቲያንን ሥርዓትና ልማድ በጠበቀ መልኩ ቢታወቁ መንፈሳዊ ክብሩም ጥቅሙም ከቀሳውስቱ ይልቅ ለምዕመናን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መልእክተኛ የሆነ ካህን በቡራኬው፣ በጸሎቱ፣ በምክሩ፣ በማጽናናቱ፣ በመናዘዙና በመሳሰለው አገልግሎቱ ይረዳናልና፡፡ ይሁንና ተለይቶ ለመታወቅ ሲባል ከቤተክርስቲያን ሥርዓትና ልማድ ያፈነገጠ አለባበስ መልበስ ግን አሳማኝ አመክንዮ ሊቀርብለት አይችልም፡፡ ቀሳውስት በማትመረመር ክህነታቸው፣ በልዩ መንፈሳዊ አገልግሎታቸው፣ ለምዕመናን በሚሰጡት ትምህርትና ልዩ ልዩ የኖላዊነት (ጠባቂነት) ሚና በልዑል እግዚአብሔርና በገዛ ደሙ በዋጃት በቅድስት ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የታወቁ ናቸው፡፡ ከዚህ የተለየ የውዳሴ ከንቱ ፍለጋ መታወቂያ መፈለግ መንፈሳዊ ጤንነትን አያሳይም፡፡ ቀሳውስት ልብሰ ተክህኖ ከሚደረግባቸው የአምልኮተ እግዚአብሔር ጊዜያት ውጭ ቀሚስም ሆነ ቆብ ማድረግ የቤተክርስቲያኒቱ ሥርዓት፣ ልማድ አይደለም፡፡ ይልቁንም ከሌሎች የተኮረጀ የአለባበስ ሥርዓትን ማዘወተር ቤተክርስቲያኒቱን የራስዋ የሆነ የአለባበስ ሥርዓት የሌላት ያስመስላታል፡፡

ታዲያ ከበስተጀርባው ያለው አመክንዮ ምንድን ነው?

የካህናት የአገልግሎት ሥልጣን ቀሚስን በማስረዘም፣ ደማቅ ቀለም ያለው ልብስ በመልበስ፣ ጎላ ያለ ፎቶ ተነስቶ በየማኅበራዊ ሚዲያው በመለጠፍ አይገለጥም፡፡ ይህ መስሎ የመታየት አባዜ ርካሽ ተወዳጅነትን ከመሻት፣ ምድራዊ ታዋቂነትን ከመናፈቅ፣ የከንቱ ውዳሴ እስረኛ ከመሆን የሚመነጭ አላፊ የአለባበስ ፉክክር ነው፡፡ አንዳንዶቹ ይህንን የሚያደርጉበት ምክንያት መልካም ካህን መስሎ በመታየት የየዋሀን ምዕመናንን ገንዘብ ዘርፎ በአቋራጭ ለመክበር መቋመጥ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆኑን ለተወሰኑ ጊዜያት በልብስ ውስጥ በተደበቀ ምንፍቅና ወይም ሌብነት የቆዩ ብዙ የሥም “ካህናት” ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሁሉንም ትተውት ፍጹም ዓለማዊ መሆናቸው ነው፡፡ በመንፈሳዊው ዕውቀት ሳይበስሉ፣ በእውነተኛው እምነት ሳይጠነክሩ፣ ራሳቸውን በጾምና በጸሎት ሳይገዙ፣ የሚያማምሩ አልባሳትን ብቻ የሚገዙ፣ ሕይወታቸውን ሳይቀይሩ ልብሳቸውን በየዕለቱ የሚቀያይሩ ለራሳቸው ፍላጎት እንጂ ለቤተክርስቲያን ሥርዓት ያልቆሙ መሆናቸውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ አይነት አለባበስ እውነተኞቹ አገልጋዮችም እንዳይጠለፉ እንዲህ አይነቱን ልማድ በቤተክርስቲያን ሥርዓት ማረም ያስፈልጋል፡፡ ምዕመናንም ከእነዚህ የአለባበስን ፋሽን ተከታይ ከሚመስሉ ሐሰተኛ ሰዎች ራሳቸውንና ገንዘባቸውን ሊጠብቁ ያስፈልጋል፡፡ የቤተክርስቲያንን አገልግሎት በዕውቀት፣ በጉልበትና በገንዘብ ልንደግፍ እንጂ የግለሰቦችን ቤትና ኑሮ ልናቋቁም አልተጠራንምና፡፡

እነዚህ ሰዎች የሚመርጧቸው ቀለማት በዓለም እንዳሉ ዘፋኞች ጎልቶ ለመታየት እጅግ የደመቁ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ ከእነርሱ ውስጥ የባሰባቸው ደግሞ ነጭ ቀሚስ በቀይ ቆብ ዓይነት አለባበስ እየለበሱ ደርዝ የሌለው የመታየት ፍላጎታቸውን ግልጽ ያደርጉታል፡፡ዓላማቸውም መንፈሳዊ ሳይሆን ዓለማውያን ዘናጮች እንደሚያደርጉት ከሌላው አለባበሳቸው ጋር የሚናበብና ለዓይን የሚማርክ (“ማች” የሚያደርግ) የሚሆንባቸውን ጊዜያትም ታዝበናል፡፡ እነዚህ ሰዎች በእግዚአብሔር ቃል የሚቀልዱ ነውረኞች ስለሆኑ ዓላማቸው እየታወቀ “ለምን እንዲህ አደረጋችሁ?” ሲባሉ የማይገናኘውን የከበሩ ቅዱሳንን ህይወት ለማደናገሪያነት ያቀርቡታል፡፡ በዚህ መልኩ የራስን ጥፋት ለመሸፈን በአስመሳይነት ከሚጠቅሷቸው ታሪኮች አንዱ በውዳሴ ማርያም ትርጓሜ ታሪኩ የሚነገርለት የደገኛው ጻድቅ አባት የቅዱስ ባስልዮስ ታሪክ ነው፡፡ ይህ ጻድቅና ተጋዳይ አባት ቅንዋት ታጥቆ፣ ማቅ ለብሶ በትህርምት እየኖረ ለወንጌል ክብር ሲል ያማረ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ ወንጌልን ሲያስተምር ክብርና ልዕልናውን ሰምቶ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ወደ እርሱ የመጣው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በልቡ አዝኖበት ነበር፡፡ የወንጌል መምህር ልታይ ልታይ ማለት የለበትምና፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ባስልዮስ ያማረ ልብስ መልበሱ ስለ ክብረ ወንጌል ነበር እንጂ እርሱስ በውስጡ ቅንዋትን የታጠቀ ተሐራሚ ነበር፡፡ በአለባበሱም ለማስመሰል የማይገባውን የለበሰ አልነበረም፡፡ የዘመናችን አስመሳዮች የራሳቸውን የመታየት በሽታ ለመሸፈን ቅዱስ ባስልዮስን ሲጠቅሱ አለማፈራቸው ይገርማል፡፡

ሰባክያን አለባበስ

በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የካህናት ማሰልጠኛ ተቋማት በአንዱ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት የአጭር ሣምንታት ሥልጠና ከሚወስዱ ሰልጣኞቹ አንዱ የጠየቀው ጥያቄ በዘመናችን በሰባኬ ወንጌልነት ሰበብ ከንቱ ውዳሴ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎችን አስተሳሰብ ሊገልጽ ይችላል፡፡ ሰልጣኙ ከመምህራኑ ለአንዱ እንዲህ በማለት ጠየቀ “እንግዲህ ሰልጥነን ከወጣን የሰባኪ ቀሚስ ለብሰን፣ መስቀል አንጠልጥለን እንዳናስተምር የሚከለክለን ማን ነው?” የዚህ ሰልጣኝ ጭንቀት የተማረውን የእግዚአብሔር ቃል ወንጌልን ለተጠሙ ምዕመናን እና አህዛብ ማድረስ ሳይሆን ከእርሱ የቀደሙ ከንቱ ውዳሴ ፈላጊዎች ሲያደርጉት እንዳየው ማንነቱን በቀሚስ ሸፍኖ የበላይ መስሎ የመዘባነን ፍላጎት እንደነበረው ነው፡፡ ከሚያስተምሩት ወንጌል ይልቅ ስለሚለብሱት ሥርዓትን ያልተከተለ የማስመሰል ቀሚስ የሚጨነቁ ሰዎች እውነተኛ ምዕመናንን “ስለምትለብሱት አትጨነቁ” እያሉ ለማስተማር አለመሳቀቃቸው ይገርማል፡፡ ለማሳያነት የተጠቀምንበት ሰልጣኝ በከንቱ ደከመ እንጂ ቀሚስ ለመልበስና መስቀል ለማንጠልጠል እምነትም፣ ትምህርትም፣ እውቀትም፣ ሹመትም ሲያስፈልግ አይታይም፡፡ ከዚያ ይልቅ ድፍረትና ማን አለብኝነትን የተላበሱት ከራሳቸው ራስ ወዳድ ዓላማ በላይ ማሰብ የማይችሉት የአስተሳሰብ ድሆች ለዚህ ነገር የፈጠኑ ናቸው፡፡ እምነትም፣ ትምህርትም፣ እውቀትም የሌላቸው ብዙዎች የዋሐን ምዕመናንን ለማጭበርበር ቀሚስ መልበስንና መስቀል ማንጠልጠልን እንደሚጠቀሙ የታወቀ ነውና፡፡   

ካህናት (ቀሳውስት) በቅዳሴና መሰል አገልግሎቶች ከሚለበሱ መደበኛ የካህናት ልብሶች (ልብሰ ተክህኖ) በቀር ቀሚስም ሆነ ቆብ ማድረግ ዘመናዊ ታይታን የመፈለግ አስመሳይነት የወለደው፣ መንፈሳዊ የት መጣ የሌለው ልማድ መሆኑን አይተናል፡፡ ካህን (ቄስ) ሳይሆኑ (ዲያቆን ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ) በልዩ ልዩ ቦታዎች ቀሚስ መልበስ ከሚያዘወትሩ ሰዎች መካከል “ዘመናዊ” ሰባክያንና ዘማርያን የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አንድ ሰባኪ ለመስበክ የግድ መነኩሴ የሚያስመስል ቀሚስ፣ እንደ እውነተኞቹ መነኮሳት ለቅንዋት (ራስን ለመጎሰም ከልብስ በታች የሚታጠቁት ሰንሰለት) ሳይሆን ለሰው እይታ የሚንጠለጠል በመስቀል ቅርጽ የተሰራ ሀብልና ጌጥ ማንጠልጠል የቤተክርስቲያን መለያ እስኪመስል ድረስ አደባባዮቻችንን በጊዜ ሂደት መሙላት ከጀመረ ሁለትና ሦስት አስርት ዓመታት እያለፈው ነው፡፡ ይህም ከቤተክርስቲያናችን ትውፊትና ልማድ ያፈነገጠ፣ በጊዜ ሂደት ግን መንፈሳዊ ለማስመሰል እየተሞከረ ያለ ልማድ ነው፡፡ የተለያዩ አካላት ለዚህ ልማዳቸው የማይናበቡ ልዩ ልዩ አመክንዮዎችን ያቀርባሉ፡፡ እነዚህን ማሳመኛ ተብለው የሚቀርቡ ሀሳቦች እንመልከታቸው፡-

ከመንፈሳዊ ተቋማት የተመረቁ ሰባክያን አለባበስ

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን በሺህ ዘመናት ኀልወቷ አስተምህሮዋን አጽንታ የቆየችው ልዩ በሆነ ሀገርኛ አደረጃጀትና አመራር የሚሰሩ በርካታ የአብነት ትምህርት ቤቶች በየገዳማቱና አድባራቱ ሊቃውንትን በመጠቀም ተተኪ ደቀመዛሙርትን በማፍራታቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ሀገር በቀል የትምህርት ዘርፍ እስካሁን ድረስ ለቤተክርስቲያን መከታ የሆኑ አያሌ ሊቃውንትን እያፈራ ይገኛል፡፡ ይሁንና ከ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኋላ ከዘመናዊ ትምህርት መስፋፋትና ከማኅበረሰባችን አኗኗር ዘይቤ ለውጥ እንዲሁም ተያያዥ ምክንያቶች የተነሳ ሀገርኛ ቅርጽ ካለው የአብነት ትምህርት ቤት በተጨማሪ የዘመናዊ ትምህርትን ቅርጽና አካሄድ የተከተሉ መንፈሳዊ የትምህርት ተቋማት አስፈላጊነታቸው እየጨመረ መጣ፡፡ ይሁንና የቤተክርስቲያን አስተዳደር ለዚህ ሽግግር ተገቢውን ተቋማዊ ዝግጅት ያደረገ አይመስልም፡፡ እነዚህ መንፈሳዊ የትምህርት ተቋማት በዘመናዊ መልኩ መንፈሳዊ ትምህርት (ቲዮሎጂ) የሚያስተምሩት በጣት የሚቆጠሩ ተቋማት ሲመሰረቱ አንግበው ከተነሱለት ዓላማ ዋነኛው የውጭ ሀገራት ቋንቋ በማጥናት የቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ለሌሎች ዓለማት (በተለይም ለአፍሪካና ካሪቢያን ወገኖቻችን) መድረስ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ የተቀደሰ ዓላማ ቢያዝም ተቋማቱ ሀገራዊ መልካቸውን ከዓለም አቀፍ የትምህርት አሰጣጥ ዘይቤ ጋር አዛምደው መያዝ የቻሉ አይመስልም፡፡ በመደበኛ የሀገራችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ካለው ጋር ከሚመሳሰል ስር የሰደደ የትምህርት ጥራት ችግር ባሻገር መንፈሳዊ አስተምህሮን እንደ ሥጋዊ ጥበብ ለእውቅናና ክብር ፍለጋ የሚፈልጉት እየበዙ ሲመጡ ይስተዋላል፡፡ ለዚህ እንደማሳያ ከሚሆኑን ጉዳዮች አንዱ የቤተክርስቲያናችን ትውፊት መሰረት የሌለው የምሩቃኑ ወይም የተማሪዎቹ አለባበስ ነው፡፡

አንድ የመንፈሳዊ ትምህርት ተቋም ምሩቅ ቀሚስና ካልለበሰ፣ ሀብልና መስቀል ካላንጠለጠለ የተማረ የማይመስለው ትውልድ እየተፈጠረ ነው፡፡ እነዚህ የትምህርት ተቋማት ከጣልያን ወረራ በኋላ የተከፈቱ በዋናነትም ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት የተስፋፉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በእነዚህ ዘመናት ደግሞ ሀገራዊ እሴቶችን “የፈረንጅ” በሚመስሉ ልማዶች መተካትን እንደ እውቀት የሚቆጥር ኮራጅ ትውልድና ሀገራዊ መዋቅር ተፈጥሯል፡፡ የመንፈሳዊ ኮሌጆቹ ደቀመዛሙርትም በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የተለመዱትን አለባበሶች መኮረጅን የሥልጣኔ መገለጫ አድርገው ያሰቧቸው ይመስላል፡፡ በመሰረቱ መንፈሳዊ ኮሌጆቹ ደቀመዛሙርቶቻቸው የተለየ አለባበስ እንዲለብሱ ማድረጋቸው  በራሱ ችግር የለውም፡፡ ይሁንና ዓላማውና አጠቃቀሙ ታውቆ በመንፈሳዊ እይታ ሊጠቀሙበት ሲገባ ፋሽን ማሳመሪያ፣ ገበያ መሰብሰቢያ መሆኑ ነው መሰረታዊ ችግሩ፡፡ ይህ አለባበስ የመታየት ልማድ የወለደው እንጂ በተቋማቱ ከመማር ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ ከመማሪያ ግብዓቶች እጥረት የተነሳ ካልሆነ በቀር በመንፈሳዊ የትምህርት ተቋማት ወንዶችም ሴቶችም እኩል የመማር መብት እንዳላቸው ግልጽ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህም ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው እህቶቻችን በተቋማቱ እየተመረቁ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በተቋማቱ የሚመረቁ ሴቶች እንደ ወንዶቹ “የሰባኪ ቀሚስ”፣ ሀብልና መስቀል ይዘው በአገልግሎት ቦታዎች ቢገኙ ግብረ መልሱ ምን ይሆናል? መገመት አይከብድም፡፡ አያችሁ? ቀሚስ፣ ሀብልና መስቀል እወደድ ባይ ልማድ የፈጠረው የታይታ ልማድ እንጂ ከመንፈሳዊ ተቋም ምሩቅነት ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡

የሌሎች ሰባክያነ ወንጌል አለባበስ

ቀሚስ መልበስን ልማድ ያደረጉ በዘመናዊ መልክ የተደራጁ መንፈሳዊ የትምህርት ተቋማት በቤተክርስቲያናችን ያላቸው ታሪክ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡ በብዛት መስፋፋት የጀመሩበት ጊዜም ካለፉት 20 እና 30 ዓመታት አይዘልም፡፡ በቤተክርስቲያናችን ስብከተ ወንጌል በዋናነት በአብነት ትምህርት ቤት መምህራን፣ በደቀመዛሙርቶቻቸው፣ በእውነተኞች ባህታውያን፣ በደጋግ መነኮሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና ከእነዚህ በተማሩ ቀናኢ ምዕመናን ሲሰጥ የኖረ ነው፡፡ በእነዚህ የሺህ ዘመናት ቆይታዎች ሰባክያነ ወንጌል ከነጠላና (ወይም) ጥምጣም (የሚገባቸው) ከመደበኛ ልብሰ ተክህኖ ውጭ የሚለብሱት ቀሚስ፣ የሚያንጠለጥሉት ሀብልና መስቀል አልነበረም፡፡ ለታይታ የሚደረግ፣ ምንዳ የሚጠየቅበት ስብከተ ወንጌል ለቤተክርስቲያን ባዕድ የነበረ መሆኑ ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረገ ይመስላል፡፡ የታይታ ልማዱ መስፋፋት ከከተሞችና በውጭ ሀገራት በሚገኙ አጥቢያዎች ገዝፎ መታየቱ በአጋጣሚ የሆነ ነገር አይደለም፡፡ በእነዚህ ቦታዎች መንፈሳዊ አገልግሎትን በገንዘብ መተመንና ለገንዘብ ሲሉ ማገልገል እየተለመደ መጥቷልና፡፡ ይህም የታይታ ልማዱ መንፈሳዊ አገልግሎትን ለግላዊ የገንዘብና የክብር ጥቅም ማስገኛነት ለመዋል ዋና መሳሪያ መሆኑን ያስረዳናል፡፡

ስለሆነም “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” እንደተባለ በአብነት ትምህርት እውቀታቸው የተመሰከረላቸው፣ አልያም ቢያንስ የተመሰከረላቸውን ሊቃውንት አሰረ ፍኖት እንደ አቅማቸው የሚከተሉ ሰባክያነ ወንጌል እንደየማዕረጋቸው ከነጠላቸው በላይ ጥምጣምና ካባ ያደርጋሉ፡፡ መነኮሳት የምንኩስና ልብሳቸውን፣ ባህታውያን ለታይታ ሳይሆን ለጽድቅ የሚያደርጉትን አለባበስ ለብሰው ያስተምራሉ፡፡ሌሎች ቀሚስ፣ ሀብልና መስቀል የሚያዘወትሩት ደግሞ በመንፈሳዊ ትምህርት ተቋማት ያልተማሩ ነገር ግን በራሳቸው እይታም ሆነ በእውነት ምስክርነት “በተቋማቱ ከተማሩት አናንስም” ብለው የሚያስቡ ሰዎች መሆናቸውን ከልምድ መረዳት እንችላለን፡፡ አንዳንዶችም የምስክር ወረቀት (ሰርትፊኬት) ስልጠና መውሰድ “ቀሚስ ለመልበስ ፈቃድ እንደሚያሰጥ” የሚያምኑ ይመስላሉ፡፡ እውነታው ግን በቅዳሴና መሰል የአምልኮ አገልግሎቶች ከሚለበሱ መደበኛ የካህናት ልብሶች (ልብሰ ተክህኖ) ውጭ የሚለበሰው ቀሚስ፣ የሚንጠለጠለው ሀብልና መስቀል የቤተክርስቲያንን ትውፊት ያልተከተለ ለተርዕዮ የሚደረግ ልማድ መሆኑ ነው፡፡

“የግል” ዘማሪያን አለባበስ

የዘማርያኑ ጉዳይ ከላይ ስለ ሰባክያኑ ከተነገረው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ መዝሙርና መዘምራን ምንጊዜም የቤተክርስቲያን አካላት ናቸው፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን መዝሙር በዋናነት እንደቅዱሳን መላእክት በኅብረት የሚዜም ነው፡፡ በቤተክርስቲያን ታሪክ መዘምራን በአገልግሎት ወቅት የሚለብሱት ልብስ ነጠላን በመስቀል ቅርጽ መልበስና እንደየማዕረጋቸው የተማሩት ጥምጣምን መጠምጠም እና/ወይም ካባ መደረብ ናቸው፡፡ ካላፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በካሴትና በሲዲ መዝሙራትን በማተም፣ እንዲሁም በቤተክርስቲያን አውደ ምህረት በግለሰብ ዘማርያን መዝሙር ማቅረብ እየተስፋፋ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ ይህ የዘማርያን አገልግሎት በቅንነት ከተያዘ ምዕመናን ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ቋንቋ ሆኖ ያገለግላል፡፡

ይሁንና  መንፈሳዊ መዝሙርን በካሴት ወይም በሲዲ በማሳተም ለሽያጭ ማቅረብ “ቀሚስ የመልበስ ያልተጻፈ ፈቃድ” ማግኛ የሚመስላቸው ሰዎች በዝተዋል፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ዘማርያን በቪዲዮ የተቀረጹ መዝሙሮችን ሲያሳዩ ወይም በአውደ ምህረት ሲዘምሩ እንደ ቀደመው ልማድ፣ ታይታ ባለመፈለግ የምዕመናንን ልብስ (ነጠላ) በመልበስ ነበር፡፡ ነገር ግን በጊዜ ሂደት (ባለፉት 20 ዓመታት) መዝሙር የገንዘብና እውቅና ምንጭ መሆን ጀመረ፡፡ ያን ጊዜ ዘማርያኑም እንደ ዘፋኞች የታዋቂነት ስሜት (sense of celebrity status) እያጠቃቸው ስለመጣ “ከሰው ለመለየት” በሚል ፈሊጥ ቀሚስ መልበስ፣ ሀብልና መስቀል ማንጠልጠል ፋሽን እየሆነ መጣ፡፡ የማይገባውን ቀሚስ መልበስ ክብር ነው ከተባለ መዝሙርን መሸጥ እንደ አርቲስት ሊያስደንቅ ቢችልም ሳይሸጥ ከሚዘምረው የበለጠ ክብር የሚያሰጥ አለመሆኑ ግን ግልጽ ነው፡፡ በመስጠት እንጂ በመሸጥ መንፈሳዊ ክብር አይገኝምና፡፡ ስለሆነም መዝሙር ማሳተም ከዚህ መሰል አለባበስ ጋር ምንም የሚያገናኘው አመክንዮ የለም፡፡ ለምሳሌ የምናከብራቸው፣ የምንወዳቸው መንፈሳውያን ሴት ዘማርያን “ተመሳሳይ ቀሚስ” ሳይለብሱ፣ ሀብልና መስቀል ሳያንጠለጥሉ ማገልገል ከቻሉ ወንዶቹ ለታይታ የሚለብሱት ለምንድን ነው?

ታይታ የሚወዱት ቀሚስ ለባሽ ሰባክያንና መዘምራን ካላቸው አሳዛኝና አስቂኝ ልማድ ውስጥ ጎልቶ ለመታየት ሲሉ የሚመርጧቸው የልብስ ቀለማት ናቸው፡፡ ይህም ፉክክራቸው ከዘፋኞች ጋር መሆኑን ያሳብቅባቸዋል፡፡ ሰባክያንና መዘምራን ከቀሚስ ቀለም መብዛት የተነሳ ትዝብትንና መጥፎ ስምን ያተርፋሉ፡፡ በየቀለማቱ ቀሚስ እያሰፉ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ቀለም ያለው ሲለብሱ የተለያየ ተቀጥላ ስም እየወጣላቸው መዘባበቻ ይሆናሉ፡፡ ለእነርሱ የተለያየ ስም የሚሰጡም ይሰናከሉባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ቀይ ቀሚስ ሲለብሱ “ቀለሙ”፣ ደማቅ ቀሚስ ሲለብሱ “ደመቀ”፣ የሚያበራ ሲለብሱ “አበራ”፣ የጎላ ቀለም ያለው ሲለብሱ “ቦጋለ”…ወዘተ እየተባሉ ራሳቸውን ትዝብት ላይ ይጥላሉ፡፡ ይህን ሁሉ ራስ ተሰናክሎ ሰውንም ማስናከል ያመጣው ሥርዓትን ያልተከተለ አለባበስ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን አለባበስ

በአንዲት ኢትዮጵያውያን የሚኖሩባት የምዕራባውያን ከተማ የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ በዓል ለማክበር ከኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የተጋበዙ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እና ከፕሮቴስታንቶች የተጋበዙ የኪነት ቡድን (Choir) አባላት የየራሳቸውን መዝሙር በሚያቀርቡበት ሰዓት የለበሱት አለባበስ ይገርም ነበር፡፡ ከሰንበት ት/ቤት የተጋበዙት መዘምራን ኢትዮጵያዊ ውርስ የሌለውን ዩኒፎርም ሲለብሱ ከፕሮቴስታንቶች የተጋበዙት ደግሞ በአንጻሩ የኢትዮጵያውን መገለጫ የሆነውን ነጭ ልብስ ለብሰው ታድመው ነበር፡፡ ምንም እንኳ ከአጨፋፈራቸው ሥርዓት አልባነት እንዲሁም ሴቶቹ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ትዕዛዝ ጸጉራቸውን ባለመሸፈናቸው የተነሳ ፕሮቴስታንቶቹ መንፈሳዊ ላህይ ባይኖራቸውም  ነጭ ልብስ ለብሰው መታየታቸው የተሻለ ነበር፡፡ ይህን የሚታዘብ ሰው በዚያ ሰዓት እንዲህ ብሎ ሊያስብ ይችላል “ኦርቶዶክሳውያኑ ሌሎችን መምሰል የሚያስከብር መስሏቸው የሌሎችን ሲናፍቁ አባቶቻቸው ለዘመናት የጠበቁትን መንፈሳዊ መገለጫ ሌሎቹ ለማላገጫነት ይጠቀሙበታል፡፡”

ሰንበት ትምህርት ቤት ሕፃናትና ወጣቶች ትምህርተ ሃይማኖትንና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን እየተማሩ የሚያድጉበት በቤተክርስቲያን ትልቅ ድርሻ ያለው የአገልግሎት ክፍል ነው፡፡ ሰንበት ተማሪዎች ለቤተክርስቲያን ከሚያበረክቱት አገልግሎት አንዱ መዝሙራትን በጋራ አጥንተው መዘመር ነው፡፡ ብዙዎቹም ለዚህ አገልግሎት የሚጠቀሙበት አልባሳት (uniform) አሏቸው፡፡ በዘመናችን እንደምናየው ከተለያየ ቀለምና በተለያየ ቅርፅ (አንዳንዶቹም የዲያቆናትን አልባሳት ለማስመሰል በሚመስል መልኩ) የሚሰሩ ቀሚስ፣ በራስ የሚደፋ ቆብ፣ በትከሻ ወርዶ በወገብ የሚታሠር ተንጠልጣይ ያለቸው ተጨማሪ ጌጦች ያሉበት የሰንበት ትምህርት ቤት ዩኒፎርም ዋና የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያን መገለጫ ሆኗል፡፡ በአደባባይ በዓላትም ከምስጋና መዝሙሩ ይልቅ የአልባሳቱ ቀለምና ጌጥጌጥ ላይ ያለው ፉክክር እየጎላ የመጣባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ የፖለቲካ ፍክክሩም እየጦዘ ሲመጣ የሰንበት ተማሪዎች ዩኒፎረም በሰንደቅ ዓላማ ቀለማት ማሸብረቅ ጀምረዋል፡፡ የሰንበት ት/ቤት መዋቅር በቤተክርስቲያናችን እንዲመሰረት በቃለ አዋዲ የደነገጉልን አባቶቻችን ሰንበት ተማሪዎች ስለሚለብሱት ልብስ ሲደነግጉ “ዩኒፎርም” የሚለውን አገላለጽ መጠቀማቸው ልማዱ ከማን የመጣ እንደሆነ በግልጽ ያሳየናል፡፡ ይህ እውነት ቢሆንም ይህ ልማድ ከሌሎች መምጣቱ በራሱ ልማዱን ስሁት ሊያደርገው አይችልም፡፡ እንዲያውም መነኩሴ መምሰል ከሚፈልጉ ቀሳውስትና ያለ ምንም መሰረት ቀሚስና መስቀል ከሚያደርጉ ዘመናውያን ሰባክያንና ዘማርያን ይልቅ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን አለባበስ ግለሰባዊነት የማይታይበት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

በዘመናችን የምናየው የሰንበት ተማሪዎች ዩኒፎርም ቀድሞ የቤተክርስቲያኒቱ ሥርዓት ያልነበረ፣ ከካቶሊካውያን የተወረሰ፣ ዘመን አመጣሽ ልማድ ከመሆኑ በላይ ከእርሱ ጋር ተያይዞ የመጣው የቀለማትና የመታየት ውድድር ግን ቤተክርስቲያኒቱን አይጠቅማትም፡፡ ይልቁንም ከሃይማኖታዊ አውድነት ይልቅ ወደ ምድራዊ ጥበብ (Art) መገለጫነት ሊለውጣት ይችላል፡፡ በአንዳንድ በዓላት ላይ ከመንፈሳዊ መዝሙርና ልባዊ አምልኮ ይልቅ እንደ ፖሊስ ማርሽ ቡድን ከመንፈሳዊነቱ ይልቅ ሥጋዊነቱ የሚጎላ ትርኢት ማሳየትን ቁም ነገር አድርገው የሚወስዱ አገልጋዮችም የዚህ ክፉ ልማድ ነጸብራቆች ናቸው፡፡ አገልግሎቱንም የልብ ሳይሆን የልብስ ያደርገዋል፡፡ ሕጻናትና ወጣቶቹም ከአስተምህሮውና ከሥርዓቱ ይልቅ ትኩረታቸው አልባሳቱ ላይ እንዲያደርጉ ያደርጋቸዋል፡፡ ጥንት የነበረው የመዘምራን አለባበስ ነጭ ሲሆን አንዳንዴ የቤተክርስቲያኒቱ ዓርማ የሆነው መስቀል ወይም የሰማዕታት ምልክት የሆነው ቀይ ምልክት ይደረግበታል፡፡ ይህም ከሥርዓቱና ከትውፊቱ ጋር አብሮ ከመሄዱም ባሻገር የሰው ልጆች እንደመላእክት ሆነው የሚያመሰግኑ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህንን አይነት አለባበስ ሲለብሱ የሚታዩት ዘማርያን ካህናትና የአንዳንድ ማኅበራት (ለምሳሌ የማኅበረ ቅዱሳን) ዘማርያን ናቸው፡፡ በተረፈ የተለያየ አሸንክታብ ቀለም የበዛባቸው ዩኒፎርሞች ግን እንኳን ከሰማያውያን ጋር አንድ ሊያደርጉን ይቅርና እርስ በእርሳችንም እያለያዩን ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

በአለባበስ ላይ ለሚታዩ ችግሮች መፍትሔው ምንድን ነው?

በአለባበስ ሰንበት ተማሪው ዲያቆን መምሰል፤ ዲያቆኑ፣ ሰባኪው፣ ዘማሪው ቄስ መምሰል፤ ቄሱ መነኩሴ መምሰል፤ መነኩሴው ጳጳስ መምሰል፤ ጳጳሱ ፓትርያርክ መምሰል ሥር የሰደደ የማስመሰል ችግር ማሳያ ነው፡፡ የአለባበስ ጉዳይ ትዕምርታዊ ነውና ያልሆኑትን መስለው መታየት የሚፈልጉት ሰዎችም የሚያሳዩት በውስጣቸው ያለውን ደካማ መንፈሳዊ ስብዕና ነው፡፡ ስለሆነም መፍትሄው በዋናነት ወደ ከንቱ ውዳሴ ከሚገፋና ለተርዕዮ ብቻ ከሚያፋጥን ፍጹም ዓለማዊ እይታ ራስን መከልከል ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ምንኩስናን የምድራዊ ክብርና ዝና ምንጭ፣ በቤተክርስቲያን የገንዘብ አስተዳደር ላይ ለማዘዝ የሚያበቃ የምድራዊ ባለስልጣንነት መነሻ አድርጎ የሚያስብ ዘመን አመጣሽ በሽታ የችግሩ ማዕከል ስለሆነ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል፡፡ በአጠቃላይ በቀለምና በጌጣጌጥ አሸንክታብ የታጀበ አለባበስ የቤተክርስቲያኒቱን ሥርዓት ካለመከተሉም ባሻገር የአገልጋዮችንና የምዕመናንን መንፈሳዊ ሕይወት የሚያደበዝዝና ዓለማዊነትን እያጎላ መጥቶ በመጨረሻም ለውድቀት የሚዳርግ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረ ሁሉም በአግባብና በሥርዓት ቢመራ መልካም ነው እንላለን፡፡

ቤተክርስቲያናችን በሥርዓትና በትውፊት የዳበረ የአገልግሎት አለባበስ አላት፡፡ የቤተክርስቲያን መለያ የሆኑ የመነኮሳትን ቀሚስና አስኬማ መናፍቃን ለማጭበርበር ሲያደርጉት ብዙዎቻችን ስህተት መሆኑን አስረግጠን እንናገራለን፡፡ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ሥርዓተ ቤተክርስቲያን የሚገደን ሌሎች ሲጥሱት ብቻ ነው? የራሳችን ልማድና ሥርዓት በራሳችን አገልጋዮች እወደድ ባይነት ሲቃለልና ባዕድ ልማድ ሲቀላቀልበት የማይገደን ከሆነ ወገንተኝነታችን ለእውነትና ለቤተክርስቲያን አይደለም ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ የካህናቱ፣ የዘማርያኑና የምዕመናኑ ቅድሚያ ትኩረት አገልግሎቱ ላይ ሆኖ ይህ አገልግሎትም ሲፈጸም የቤተክርስቲያናችንን አስተምህሮ የዋጀና ሥርዓቷን የጠበቀ እንዲሆን መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ለሥራና ለኑሮ የማይመቹ አለባበሶች ካሉም ሥርዓቱን ጠብቆ ማሻሻል ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ጥምጣም መጠምጠም ለሁሉም ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ ጥምጣም መጠምጠም ከባድ ሆኖባቸው በዚያ ምክንያት ወደ ቀሚስና ቆብ ለሚሄዱ ሰዎች መፍትሄ አለ፡፡ በተለያየ ምክንያት ከብዷቸው ከችግር የተነሳ ሌሎችን ለመምሰል ቀሚስና ቆብ ለሚያደርጉትም በአንዳንድ የውጭ ሀገራት አጥቢያዎች እንደሚታየው ተዘጋጅተው የሚሸጡ ጥምጣሞችን መጠቀም አማራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እኛ ሥርዓቱን ካላከበርነው “ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ…” እንደሚባለው ይሆናል፡፡ 

ከቅዳሴ ውጭ ባሉ አገልግሎቶች ከመነኮሳት ውጭ ያሉ ሌሎች አገልጋዮች አለባበስን በተመለከተ ግልጽ የሆነ የሚነበብ ሥርዓት አለመኖሩ በብዙዎች ዘንድ ለሥርዓት አልበኝነቱና ግራ ለመጋባቱ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይሁንና በዓለማዊ የህግ መርህም ሆነ በቤተክርስቲያን ልማድ ለእያንዳንዱ ጥቃቅን ጉዳይ ሁሉ አስገዳጅ ህግና ሥርዓት ማውጣት የሚደገፍ አካሄድ አይደለም፡፡ ለመንፈሳዊት ቤተክርስቲያን የአገልጋዮች ግላዊ አለባበስና ደካሞቹ የሚሳሱለት “ግርማ ሞገስ” ዋና ጉዳይዋ አይደለምና የግድ ግልጽ ሥርዓት ያስፈልጋል ማለት አሳማኝ ላይሆን ይችላል፡፡ ከዚያ ይልቅ ነገሮችን ለህሊና ፍርድ እየተው በቅንነት መንፈሳዊ ግዴታን መወጣት የተሻለ የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ፡፡ ይህ ማለት ግን ግልጽ ህግና ሥርዓት ያልተደነገገባቸው ጉዳዮች በልማድና በአመክንዮ አይዳኙም ማለት አይደለም፡፡ አባታችን አቤል ግልጽ የመሥዋዕት አቀራረብ ሥርዓት ባልነበረበት ዘመን በንጹህ ህሊና ተመርቶ ያቀረበው መሥዋዕት የተወደደ እንደሆነ ሁሉ ወንድሙ ቃየል ግን “በግልጽ አልታዘዝኩም” የሚል በሚመስል እሳቤ ህሊናውን ተቃርኖ ያቀረበው የሰነፍ መሥዋዕት የመንፈሳዊ ሞቱ ዋዜማ ነበር፡፡ እንግዲህ ይህን ህገ መጽሐፍ የሚረዱ፣ የሚያስረዱ፣ የሚተነትኑ መምህራን እንዴት ይህን ማስተዋል ተሳናቸው? ምናልባት በራስ ላይ መፍረድ ከፍርዶች ሁሉ ከባዱ ስለሆነ ይሆናል፡፡ ለከንቱ ውዳሴ መታየትን የሚጠየፉ፣ ከስጋዊ ውበት ይልቅ መንፈሳዊ ዓላማን ያስቀደሙ የደጋግ አባቶቻችን አምላክ በዘመናችን ላሉ ካህናት፣ ሰባክያንና መዘምራን ማስተዋልን ያድልልን፡፡ አሜን፡፡

ስብከትና ፖለቲካ፡ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን!

እንደ መግቢያ

የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ የእውነተኛ መንፈሳዊ መምህር ትኩረት ምን መሆን እንዳለበት ባስረዳበት መልዕክቱ “አይሁድ ምልክትን ይጠይቃሉ፤ የጽርዕ (ግሪክ) ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፡፡ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአህዛብም ስንፍና ነው፡፡” (1ኛ ቆሮ. 1፡23) በማለት አስተምሯል፡፡ ይህንን መንፈሳዊ መመሪያቸው በማድረግ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አውደ ምህረት እውነተኛውን የክርስቶስን ወንጌል የሚሰብኩ እውነተኛውን የሃይማኖት መንገድ የሚያቀኑ አያሌ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን አሉ፡፡ በእነዚህ ሊቃውንት አስተምህሮና በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ረዳትነት ምዕመናን የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው፣ በእምነት ጸንተው፣ ምግባር ትሩፋትን ሠርተውና ከምስጢራተ ቤተክርስቲያን ተካፋይ ሆነው ዓለም ሳይፈጠር የተጋጀላችውን መንግስተ ሰማያትን እንደሚወርሱ እሙን ነው፡፡ 

የእግዚአብሔር የምህረት ቃል ከሚፈስበት አውደ ምህረት እንደ አይሁድ ምልክትን (ተዓምርን) መናፈቅ፣ ወይም ስለ ተዓምር አብዝቶ መጨነቅ አይገባም፡፡ ይሁንና በዘመናችን በእምነት ከሚዳሰስ የወንጌል እውነት ይልቅ በዓይን የሚታይ የማጭበርበርና መሰል ምልክቶች የአንዳንድ የእምነት ቦታዎች መገለጫ መሆን ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እንደ ግሪክ ሰዎች በመንፈሳዊ አውደ ምህረት ምድራዊ ጥበብን ማውራትና ቤተክርስቲያንን የምድራዊ ጥበብ መመጻደቂያ ቦታ የሚያስመስሉ ሰዎች አሉ፡፡ በተለይም ጥራዝ ነጠቅ ሰባክያን በዓለም ላይ ያለውን ግሳንግስ ሁሉ (ያዩትንና የሰሙትን) በአውደ ምህረት በመዘብዘብ አላዋቂነታቸውን ከማጋለጣቸውም በላይ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የሚገለጥበትን የቤተክርስቲያን አውደ ምህረት ያሰድባሉ፡፡ እነዚህ መምህራን በቁንጽል መረዳት ያለቦታቸው ከሚተነትኗቸውና ምዕመናንን ግራ ከሚያጋቡባቸው ምድራዊ ጥበቦች አንዱ ፖለቲካ (ሃይማኖታዊ ስብከትንና ምድራዊ ፖለቲካን ያለአግባብ ማዳቀልና መቀላቀል) ነው፡፡

ከዚህም አንጻር በመንፈሳዊው አውደ ምህረት ላይ ፖለቲካንና ስብከትን የሚቀላቅሉ አንዳንድ ሰባኪዎች በየዘመናቱ ነበሩ፡፡ ዛሬም በእኛም ዘመን ምንም ምን ያልተቀላቀለበት ንጹህ መሥዋዕት እውነተኛውን የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ ተናግረው የምዕመናኑን መንፈሳዊ ሕይወት ማነጽ ሲገባቸው አንዱን የፖለቲካ ቡድን በማሞገስ ሌላውን ደግሞ በመውቀስ ላይ የተጠመዱ አንዳንድ ካህናትና ሰባክያነ ወንጌል አሉ፡፡ ምዕመናኑም በእነዚህ ሰዎች ዓይን ያወጣ ፖለቲካዊ ወገንተኝነትና የቤተክርስቲያንን አውደ ምህረት ለፖለቲካ ዓላማ በመጠቀማቸው እያዘኑ ይገኛሉ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ክርስቲያኖችም ይህ መጥፎ ጅምር እየሰፋ ሄዶ ቤተክርስቲያኒቱን የፖለቲከኞች መሣርያ እንዳያደርጋት ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛል፡፡ እኛም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር የስብከትና የፖለቲካን ልዪነት፣ ግንኙነትና ሰባኪው ማድረግ ያለበትን ጥንቃቄ እንዳስሳለን፡፡

ፖለቲካ ምንድን ነው?

ሰው በተፈጥሮው ፖለቲካዊ ጠባይ ያለው ፍጡር ነው፡፡ ፖለቲካ ማለት የምድራዊ መንግስት የአመራር ሥርዓትና ስልት ነው፡፡ በአንድ ሀገር አመራር ላይ ግለሰቦች፣ ቡድኖች ወይም የመንግስት አካላት የሚያደርጉት አሉታዊም ሆነ አወንታዊ ተጽእኖ ፓለቲካ ሊባል ይችላል፡፡ በመንግስት መዋቅር ስልጣንን መያዝና በዚያም ሕዝብን ማገልገል እንዲሁ ፖለቲካ ሊባል ይችላል፡፡ አንድ ሀገር ስለምትመራበት ጥብብ የሚያጠና የትምህርት ጥናት ዘርፍም የፖለቲካ ሳይንስ ይባላል፡፡ አንድ ሀገር ወይም ሕዝብ በመንግስትነት (ራሱን በማስተዳደር) ከታወቀ የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ ኀልወት አለው ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ በመንግስትና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት፣ በመንግስትና በመንግስት መካከል ያለው ግንኙነት ፖለቲካ ይባላል፡፡ ይህንን የመንግስት ፖለቲካ የሚመሩ በዚሁ ሙያ የሰለጠኑ፣ ወይም በልምድና በፍላጎት የተሰማሩ ባለስልጣናት፣ ተገዳዳዳሪዎች ወይም ሌሎች ሀሳብ አመንጭዎች (ፖለቲከኞች) አሉ፡፡ መንግስታቸው ከሕዝብ ጋር ወይም ከሌላ መንግስትና ሕዝብ ጋር ሊኖረው የሚገባውን የአመራር ስልት በተማሩት ትምህርትና ባላቸው ልምድ፣ ከሀገሪቱ ህግጋት አንጻር፣ በሥራ ልምዳቸውና ከላይ በሚሰጣቸው አመራር ለቆሙለት ዓላማ ይጠቅማል ያሉትን ሀሳብ ያራምዳሉ፡፡ የፖለቲካ ሥራ በእነዚህ ሰዎች ሲሠራ ያምርበታል፡፡ 

ስብከትስ ምንድን ነው?

የክርስቶስን ወንጌል ለሕዝብ ማድረስ ስብከት ይባላል፡፡ የወንጌል ሰባኪ ትኩረቱ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ስላለው የአምላክና የአምላኪ፣ የፈጣሪና የፍጡር፣ የአባትና የልጅ ግንኙነት እንዲሁም በሰውና በሰው መካከል ስላለው የወንድማማችነት ግንኙነት በሰፊው ተንትኖ ለሰው ማስረዳት፣ በእምነት እንዲጸኑም ማገዝ ነው፡፡ የስብከተ ወንጌል ዓላማው ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት እንዲጠነክርና እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ ሊያሳድግ የሚችል ፍቅር በሰዎች መካከል እንዲሰፍን ማድረግ ነው፡፡ ለስብከት የሚያስፈልገውም መንፈሳዊ የቅዱሳት መጻሕፍት እውቀት፣ ሌላውን ሊያንጽ የሚችል መንፈሳዊ ሕይወት፣ ከእግዚአብሔር የተሰጠ የመስበክ/የማስተማር ጸጋ፣ የስብከት ዘዴ እና የጸና እምነት ነው፡፡ ወንጌልን የሚያስተምር ሰባኪ ስለፖለቲካ ጥናትና እውቀት (የራሱ የሆነ የፖለቲካ አመላካከት) ቢኖረውም ወንጌልን በሚያስተምርበት ጊዜ ፖለቲካ ውስጥ እንዳይገባ መጠንቀቅ አለበት፡፡ ሰባኪ ለምዕመናን መንፈሳዊ ሕይወት የሚያስፈልገውንና ሕይወታቸውን የሚያንጸውን የእግዚአብሔር ቃል እንጂ የሚያውቀውን ሁሉ ወይም ሰዎች እንዲናገርላቸው የሚፈልጉትን ነገር መስበክ የለበትምና፡፡

እግዚአብሔርን መፍራትና የሀገር መሪዎችን ማክበር

የቤተክርስቲያን አዕማድና ብርሃናት የሆኑት የወንጌል ሰባኪዎች እነ ቅዱስ ጳውሎስ በክርስቶስ ወንጌልና በምድራዊ ፖለቲካ መካከል ያለውን ልዪነትና ግንኙነት ጠንቅቀው ያውቁ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩት ምዕመናን ምንም እንኳን በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምነው ነፃ የወጡ ቢሆኑም በሀገር ደረጃ ደግሞ አለቃ የሌላቸው መስለው እንዳይታዩ ይመክሯቸው ነበር፡፡ ‹‹ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ስለዚህ ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል፤ የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ… ሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ (ሮሜ 13፡1-17)›› በማለት ነበር ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረው፡፡

በዚህም መሠረት እግዚአብሔርን መፍራት የሀገር መሪዎችን ደግሞ ማክበር በቤተክርስቲያን ጥንተ ስብከት የታወቀ ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ስለዚህ ሲናገር ‹‹ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፤ ለንጉሥም ቢሆን፥ ከሁሉ በላይ ነውና፤ ለመኳንንትም ቢሆን፥ ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና ተገዙ›› ብሏል (1ኛ ጴጥ 2፡13-14)፡፡ የጥበብ መጀመሪያ የሆነው እግዚአብሔርን መፍራት ማለት ሕግጋቱን መጠበቅ ነው፡፡ መሪዎችን ማክበር ማለት ስለሀገር ስለሕዝብ አንድነትና ነጻነት እነርሱ በሚያዙት (በሚያወጡት ህግ/ፖሊሲ/መመሪያ)መሠረት መሠማራት ማለት ነው፡፡ የሀገር መሪዎችን ማክበርና ለሥርዓታቸው መገዛት ማለት ግን የአምባገነን መንግስታት አፈ ቀላጤ የሆኑ ሰዎች እንደሚመስላቸው ግፈኞች የሀገር መሪ ስለሆኑ ብቻ ያለመመርመር መገዛት፣ ያለመጠየቅ መታዘዝ ይገባል ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንስ ክርስቲያኖች “ሰማያዊ ንጉስ እግዚአብሔር፣ ሰማያዊ ሀገር መንግስተ ሰማያት አለችንና ለማንኛውም ምድራዊ ባለስልጣንና ሀገር አንገዛም፣ አንታዘዝም፡፡” በማለት መንፈሳዊ ዓላማቸውን ለምድራዊ አድመኝነት መሸፈኛ እንዳያደርጉት የተነገረ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ይልቅ ባለስልጣኖችን የሚፈራ ሰባኪ የእነርሱ ፍላጎት ተገዢ ይሆናል፡፡ ሰባኪው እነዚህን ጽንሰ ሃሳቦች በጤናማ አእምሮ አስተውሎና ተርጉሞ ለተሰባኪያኑ ቢያሰማ በፖለቲካውና በወንጌል ትምህርት መካከል ሰላምና መስመርን ጠብቆ አብሮ መሥራት ይመሠረታል፡፡

ፍርድ ተጓደለ ደሃ ተበደለ የሚል ስብከት

ሰባኪው ለማንኛውም የፖለቲካ ባለስልጣን ወይም ለማንኛውም ገዥም ይሁን ተገዳዳሪ ቡድን ቋሚ በሚመስል መልኩ ሳይወግን በሕዝብ ዘንድ ‹‹ፍርድ ተጓደለ ደሃ ተበደለ›› ብሎ መምከርም ሆነ መገሰፅ ይችላል/ይገባልም፡፡ ይህንንም የሚያደርገው ራሱ በራሱ በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ በሰፈረው እውነት መነሻነት እንጂ በሌላ አካል ተጽእኖ የሌላ መሣርያ በመሆን አይደለም፡፡ ድሃ ሲበደል፣ ሲሰቃይ፣ ሲጮህ እነርሱ ቸል የሚሉትንና ሊያገለግሉት የተሾሙትን ሕዝብ በደል፣ ስቃይና ችግር የማይመለከቱትን ባለስልጣኖች በነሄሮድስ የደረሰውን የእግዚአብሔር መቅሰፍት አስረጅ አድርጎ ቢገስጻቸው የሐዋርያ ወጉ ነው (የሐዋ ሥራ 12፡20-24)፡፡

የወንጌል ሰባኪ የፖለቲካ ባለስልጣኖችን በተግሳጽ ብቻ ሳይሆን በምክርም ማስረዳት ይገባዋል፡፡ የያዙት ስልጣን ከእግዚአብሔር የተገኘ መሆኑን፣ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ግን በራሳቸው ምንም ሊያደርጉ አለመቻላቸውን (ዮሐ 19፡11) ገልጦ ሊነግራቸው ይገባል፡፡ ዛሬ ያሉበትም የዳኝነት መድረክ ነገ የሚያልፍና የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሊያገለግሉበት የተሰጣቸው መሆኑን ቢቀበሉትም ባይቀበሉትም እውነቱን የማስተላለፍ ግዴታ አለበት፡፡‹‹ደሃ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ›› ብሎ የሚሰብክ ሰባኪ በደልንና ፍርድን በመጽሐፍ ቅዱስ መነጽርነት መመልከት ይኖርበታል፡፡ አንዱን በዳይ የሚኮንን ሌላውን በዳይ ቸል የሚል ወይም የሚያበረታታ፣ ለአንዱ ተበዳይ የሚጮህ ለሌላው ተበዳይ ግን ጸጥ የሚል ከሆነ ይህ እውነተኛ የወንጌል ሰባኪ አይደለም፡፡

የሰላምን ዋጋ እና የጦርነትን አስከፊነት የሚያሳይ ስብከት

በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያለ አንድ ሰባኪ ስለ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሁኔታ የሚያውቅ መሆን ይኖርበታል፡፡የሰላም እጦት፣ ግጭትና ጦርነት ሀገራዊ ቅርጽ ከመያዛቸው በፊት በግለሰቦች ራስ ወዳድነት የሚጸነሱ ናቸው፡፡ በትዕቢተኞች ሰዎች የሚመሩ ሀገራትም ሌሎችን በግፍ ማስገበርን፣ ማጭበርበርንና ማዋረድን እንደ መልካም ምግባር መደጋገማቸው አይቀርም፡፡ ሰባኬ ወንጌል ከሚሰጠው ትምህርት ጋር በተያያዘ መልኩ በእውቀትና በመረጃ ተመስርቶ የሰላም እጦት፣ የግጭትና የጦርነት ምንጭ የሆኑ አስተሳሰቦችና አሰራሮችን ቢነቅፍ፣ ቢተች የተገባ ነው፡፡ የኃያላን ሀገራት መንግስታት በታዳጊው ሀገር መንግስት ላይ የሚያደርጉትን ተጽእኖ ማለት የኢኮኖሚና የወታደራዊ የበላይ ነኝ የሚለው መንግስት በደካማው መንግስት ላይ የሚያሳየውን የትዕቢት ጠባይ በወንጌል ሰባኪው ሊወገዝ ይችላል፡፡

አንዳንድ መንግስታት የራሳቸውን ርዕዮተ ዓለም ሌሎች ሕዝቦችና መንግስታት ሁሉ እንዲይዙላቸው ይፈልጋሉ፡፡ የእነርሱን ፖለቲካዊ ሃሳብ ተገዥዎችና ምጽዋተኞች እንዲሆኑ በሃይማኖት አሳቦና የሃይማኖት ልብስ ለብሶ መጽሐፍ ቅዱስን አስይዞ ቢጽ ሐሳውያንን በመላክ በሚሰጠው ርዳታ በማስፈራራት በሌላም በብዙ ዓይነት መንገድ ይጥራሉ፡፡ ሃሳቡ ተቀባይ ቢያጣ ርዳታውን ያቆማሉ፡፡ የጥፋት መልእክተኞችን እየላኩ የውስጥ ለውስጥ ብጥብጥ እንዲነሳና ደም እንዲፋሰስ በጎረቤት ያሉ የወንድማማች ሀገሮችን በሃሳብ በመከፋፈል እርስ በእርሳቸው እንዲፋጁ በማድረግ የሚፈጽመትን ሰይጣናዊ ወንጀል ሰባኪው ቢያወግዝ የተገባ ነው፡፡ ያንን የፖለቲካ ሰዎች እንዴት እንደሚመለከቱት ሰባኪው በሰፊው ሊያስረዳ ይገባል፡፡ ይህንንም በቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ሰዎችም ዘንድ በሰፊው ሊያስረዳ ይገባል፡፡

ሰባኪው በዓለም ዙሪያ በየዘመናቱ በተደረጉ ጦርነቶች ለበርካቶች ሞት፣ መቁሰል፣ ስደትና ጉስቁልና ምክንያት የሆነውን ጦርነት እንደገና ለመቀስቀስ የሰውን ደም በከንቱ ለማፍሰስ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጦር መሣርያው ገበያ የደራ መሆኑን ገልጦ የጦርነት ነጋሪት ጎሳሚዎችን በብርቱ ሊወቅሳቸው ይገባል፡፡ ጦርነት በዓለም በሚገኙ ወገኖቻቻን ላይ ያደረሰውን ጉዳት በመዘርዘር በአካል ጉድለት የሚገኙ ስንት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዳሉ፣ እንዲሁም ለሰው ልጆች መታወቂያ የሚሆኑና በብዙ ድካም የተሠሩ እቃዎችና የባህል መሣርያዎች እንደወደሙ፣ ብዙ ሕዝብ የሚኖርባቸው ከተሞች ከነዋሪዎቻቸው ጋር በሃይድሮጂን ቦምብ መጋየታቸውን በአስረጅ ጠቅሶ ጦርነትን ሲያወግዝ በጦርነት ሳቢያ በሰው ደም የሚነግዱ የጦር መሣርያ ቸርቻሪዎችን የፖለቲካ መሪዎችንም ቢገስጽ ሁለገብ ሰባኪ ይሆናል፡፡ 

ነገር ግን ዓለም እንደልማዱ የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማ ካለ ግን የጦር ወዳድ መንግስታት እንደ ኮራዚን እንደ ቤተ ሳይዳ እንደ ሰዶምና ገሞራ ህልውናቸው ጠፍቶ የሚቀር መሆኑን ሰባኪው በማስጠንቀቂያ ቃል ማስረዳት አለበት፡፡ ጦርነት የብዙዎቻችንን ቤት አራቁቶ የብዙዎቻችንንም ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ያጠፋ ከአንዳንድ የፖለቲካ መሪዎች እንደ ሂትለርና ሞሶሎኒ ካሉ ሰዎች ጭንቅላት የሚመነጭ መርዝ መሆኑን ማስተማር የሰባኪው ድርሻ ነው፡፡ ይህንን በማድረግ የጦርነት ምንጭ ከሚፈልቅበት የሰዎች ልቦና ይደርቅ ዘንድ መንፈሳዊው ሰባኪ ታላቅ ድርሻ አለው፡፡ ነገር ግን የጦርነትን አስከፊነት የሚሰብክ ሰባኪ አንዱን ጦርነት እያወገዘ ሌላውን ቸል እያለ (እየደገፈ) ሳይሆን ለእውነት ብቻ ወግኖ በቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃነት መሆን ይኖርበታል፡፡ ሰላምንም የሚሰብክ ሰባኪ እንዲሁ የሰላም ባለቤት እግዚአብሔር እንደሆነና ሰዎችም ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እንዲኖሩ በመምከር መሆን አለበት፡፡  

ጠንካራ የሥራ ባህልንና ያለንን ማካፈልን የሚያበረታታ ስብከት

የተወደደው መምህራችን ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረን ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ምድራዊ ባለጸግነትንና ሥልጣኔን አታወግዝም፤ ለምድራዊ ባለጸግነትና ጥቅም ሲሉ ሌሎችን የሚያሳድዱና የሚጎዱትን ግን ታወግዛቸዋለች፣ ትነቅፋቸዋለች፡፡ በዓለማችን ዋነኛው የግጭትና የጦርነት ምንጭ የመሪዎችና የሌሎች ኃያላን እኔ ብቻ ይድላኝ ማለት፣ ራስ ወዳድነትና ለሌላው አለማሰብ ናቸው፡፡ የወንጌል ሰባኪ በእግዚአብሔር ገንዘብ ሰው የሰውን ደም በማፍሰስ፣ ሕይወትን በመቅጠፍ (በጦርነት) ፈንታ ሰው የሚድንበትን፣ በኢኮኖሚም የሚበለጽግበትን የስልጣኔ በር መክፈትና የተራበው የሰው ዘር ምግብ በልቶ እግዚአብሔርን እያመሰገነ የሚያድርበትን መንገድ ብናመላክት እግዚአብሔር የሚደሰት መሆኑን በይፋ መስበክ ይገባዋል፡፡ 

ስለሆነም መንፈሳዊው ሰባኪ ሰዎች ጠንካራ የሥራ ባህልን እንዲያዳብሩና በድካማቸው ያፈሩትን ሀብትም ያለመሰሰት ለሌሎች እንዲያካፍሉ (ለተቸገሩት እንዲመጸውቱ) ተግቶ ማስተማር ይገባዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ምጽዓት ለፍርድ ሲገለጥ ከምግባራት ሁሉ በላይ በደገኛ ምጽዋት የተገለጸ ፍቅርን ይወድዳልና፡፡ ይህም የተራቡትን ማብላት፣ የተጠሙትን ማጠጣት፣ የታረዙትን ማልበስ፣ የታሰሩትን መጎብኘት፣ እንግዶችን ያለልዩነት መቀበል፣ ለደሃ አደጉ መሟገትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በድካሙ ያገኘውን ሀብትና ንብረት ለሌሎች በቸርነት የሚያካፍል ማኅበረሰብ ውስጥ ለሀብትና ንብረት ብሎ ሰዎችን የሚገል፣ የሚያፈናቅል፣ የሚያሳድድ ምግባር በጊዜ ሂደት ቦታ ማጣቱ አይቀርምና፡፡

የፖለቲካና የስብከት ልዩነት

ስብከትና ፖለቲካ ዓላማቸው የተለያየ ነውና እውነተኛ የወንጌል ሰባኪ ፖለቲካና ስብከት የሚለያዩበትን ጠንቅቆ ማወቅ አለበት፡፡ በቤተክርስቲያንና በፖለቲካ (በምድራዊ መንግስት ወይም ሌላ ተገዳዳሪ የሀሳብ ባለቤቶች) መካከል መደበላለቅ ለመፍጠር ዛሬም አንዳንድ አድርባዮች ይሞክራሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ፈተና የተጀመረው በእኛ ዘመን አይደለም፡፡ ቤተክርስቲያን ስትጀመር ጀምሮ የነበረና እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ የሚኖር ፈተና ነው፡፡ የቤተክርስቲያን ራስ የሆነውን ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከቄሳር ባለስልጣኖች ጋር ለማጣላት የሞከሩ ሄሮድሳውያን ራት አግባዎች ‹‹ለቄሳር ግብር መስጠት ይገባል ወይስ አይገባም?›› የሚል ጥያቄ አቅርበውለት ነበር፡፡ የእነርሱ ሃሳባቸው አይገባም ቢላቸው ከቄሳር መንግስት ጋር ለማጋጨት ነው፡፡ ይገባል ቢላቸው ደግሞ ይህስ ጥሩ የሃይማኖት መምህር አይደለም ብለው አላዋቂውን ሕዝብ ለማወናበድ ነበር፡፡ መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የቤተክርስቲያን ምዕመናን አለቃ የለሾች አለመሆናቸወን ሲገልጥ ‹‹የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ግን ለእግዚአብሔር መስጠት ይገባል›› አላቸው (ማቴ 22፡15-22)፡፡ አሁንም ሰባኪው የፖለቲካውንና የወንጌልን ልዩነት አጥርቶ ካወቀ ከስህተቱ ይጠነቀቃል፡፡ ለገዢዎች እንድንታዘዝ ለእነርሱም የሚገባውን ሁሉ እንድናደርግ ቅዱሳት መጻሕፍት አዘዋል፡፡ እንድንሰብክ የታዘዝነው ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን ብቻ ነው (1ኛ ቆሮ 1፡23)፡፡

politics vs sibket

ፖለቲካን የሚደግፍ/የሚነቅፍ ስብከት

አንዳንድ ሰባክያን ስለሁላችን የተሰቀለውን ኢየሱስ ክርስቶስን፣ ያስተማረውን ትምህርተ ሃይማኖት እንዲሁም የመሰረታትን ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አሰራር መስበክ፣ መመስከርና ማብራራት ሲገባቸው በየጊዜው የሚነሱ ባለስልጣኖችን (መኳንንቱን) በማሞገስና በማሞካሸት እንጀራቸውን ያበሰሉ (በባለስልጣናቱና በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ተወዳጅነት የሚያገኙ) እየመሰላቸው ወንጌልን ለመስበክ መስቀል ጨብጠው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው በቤተክርስቲያን አውደምህረት የፖለቲካ (ፖለቲካን የቀላቀለ) ንግግር ያደርጋሉ፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ሊያገለግሉ ሲገባ በመንፈሳዊ አውደ ምህረት በፖለቲካዊ እሳቤ ለሚደግፏቸው የመንግስት አካላት ወይም ሌሎች ተገዳዳሪዎች የምርጫ ቅስቀሳ የሚመስል መንፈሳዊ ለዛ የሌለው ትርክት በመንፈሳዊነት ካባ ያቀርባሉ፡፡ 

በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር ያከበራቸው ቅዱሳን ገድልና ድርሳን እንዳይነገር ውኃ በማይቋጥር ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንታኔ በጸጉር ስንጠቃ የሚቃወሙ በማሳችን ውስጥ የበቀሉ የመንገድ ዳር አረሞችም ዓላማቸው መንፈሳዊ ስላልሆነ “ለምን ነገረ ቅዱሳን በአውደ ምህረት ይተረካል?” በሚሉበት ምንፍቅናን የተሞላ አንደበታቸው የሚወዷቸውን ፖለቲከኞች ነቢይና መልአክ ለማስመሰል ሲጣደፉ እናስተውላለን፡፡ መንፈሳዊውን አውደ ምህረት እንደ ቅዱስ ቃሉ ለመንፈስ ቅዱስ ሀሳብ ከማስገዛት ይልቅ  የእኛ ለሚሏቸው ተገዳዳሪ ፖለቲከኞች ፈቃድ ማስፈጸሚያ ያደርጉታል፡፡ በዚህም የተነሳ የበርካታ ምዕመናን መንፈሳዊ አንድነት ይፈተናል፡፡ አድር ባዮቹ አገልጋዮች ግን በቅዱስ መጽሐፍ እንደተነገረው “ለመንጋው የማይራሩ ምንደኞች” ስለሆኑ መንፈሳዊውን አውድ ለስጋዊ ፉክክር በማዋላቸው የተነሳ የሚጠፉት በጎች (ምዕመናን) ጉዳይ አያስጨንቃቸውም፡፡

እነዚህ በወንጌል የሚነግዱ ግለሰቦች ከምድራውያን ጌቶቻቸው ወይም ከጌቶቻቸው ወዳጆች የሚያገኙት  ሙገሳ፣ ክብርና ጥቅም ስለሚያሳሳቸው በጥፋት ላይ ጥፋት ሲጨምሩ አይታወቃቸውም፡፡ ይህን የወንጌል ስብከት ሳይሆን ፖለቲካዊ ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት የተቀመጡ ምዕመናን ሰባኪዎቹን ይታዘቧቸዋል፡፡ እነዚህ ሰባኪያን በቤተክርስቲያን የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ምዕመናን ሊኖሩ እንደሚችሉም መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ሌሎች ሰባኪዎች ደግሞ የተነሡበትን የስብከታቸውን ርዕስ በሚፈለገው መንገድ ማብራራት ሲያቅታቸው አንዱን የፖለቲካ አመራር በመንቀፍ የሌላውን ደግሞ በመደገፍ የፓርቲ መሪዎች የሚያደርጉትን ዓይነት ስብከት ይሰብካሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ የሰባኪዎች መመሪያን አለማወቅ የቤተክርስቲያንን ዓላማና የአመራር አቅጣጫ አለማስተዋል ነው፡፡ ይህም ቤተክርስቲያንንና ምዕመናንን ከመከፋፈል በቀር አንዳች ጠቀሜታ የለውም፡፡

የፖለቲካዊ ስብከት ምሣሌዎች እንደ ማሳያ

ምሣሌ 1፡ በአንድ ወቅት በአንዲት የኢትዮጵያ ከተማ የመስቀል በዓል የቤተክርስቲያን አባቶች፣ ምዕመናንና የመንግስት ባለስልጣናት ባሉበት በአደባባይ እየተከበረ እያለ አንድ ካህን መልእክት ለማስተላለፍ ወደ መነጋገሪያው ሰገነት መጡ፡፡ በንግግራቸውም “መስቀል ኃይል ነው፣ መስቀል ቤዛ ነው፣ መስቀል መድኃኒት ነው፣ መስቀል ልማት ነው አሉ፡፡ እኒህ ካህን ከዘረዘሯቸው ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ መጽሐፋዊና ትውፊታዊ ሲሆኑ የመጨረሻውና “መስቀል ልማት ነው” የሚለው ወለፈንድ አገላለጽ ግን ምንም መንፈሳዊ መሰረት የሌለውና በጊዜው ከነበረው ገዥ ፖለቲካዊ ትርክት አኳያ የምድራውያን ባለስልጣናትን ቀልብ ለመሳብ የተጨመረ የአድር ባይነት መገለጫ ነው፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍት ምሥጢር ተተንትኖ በማያልቅበት የከበረ በዓል ላይ ካህኑ ከቃለ እግዚአብሔር ይልቅ ፖለቲከኞችን የሚያስደስት የመሰላቸውን እንግዳ አገላለጽ መጠቀማቸው ትኩረታቸው ለቃለ እግዚአብሔር ሳይሆን ለሚያጎነብሱላቸው የፖለቲካ ሹማምንት መሆኑን ያሳብቅባቸዋል፡፡

ምሣሌ 2፡ በአንዲት ኢትዮጵያውያን የሚኖሩባት የምዕራባውያን ከተማ የጥምቀት በዓል እየተከበረ እያለ የዕለቱን ወንጌል የሚያስተምሩት መምህር መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ማግባቱን አንስቶ ለመውቀስ እንዳልፈራ እየጠቀሰ ማስተማር ጀመረ፡፡ እየደጋገመም ዮሐንስ ለሄሮድስ ህገ አራዊት አልታዘዝም አለ እያለ ይናገር ነበር፡፡  “ህገ አራዊት” የሚለውን ቃል ከመደጋገሙ የተነሳ ቅዱስ ዮሐንስን የተመለከቱትን ቅዱሳት መጻሕፍት (ወንጌልና ገድለ ዮሐንስን ጨምሮ) ላልተረዳ ሰው የመምህሩ ሀሳብ ከመጻሕፍቱ የሚቀዳ ሊመስለው ይችላል፡፡ ነገር ግን “ህገ አራዊት” የሚለው አገላለጽ አንድ ታዋቂ የሀገራችን ፖለቲከኛ በዘመናቸው የነበረውን መንግስት ለመተቸት የተጠቀሙበት እንጂ ከቅዱስ ዮሐንስ ታሪክም ሆነ ንግግር ጋር የማይገናኝ ነው፡፡ በዝርወት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ኢትዮጵያ ጉዳይ የጎላ ፖለቲካዊ ፍላጎት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ የመምህሩ ፍላጎትም ተሰብሳቢዎቹ ሊሰሙት ይፈልጋሉ ብሎ ያሰበውን ፖለቲካዊ ምልከታ በመግለጽ ወገንተኝነትን ማሳየት ይመስላል እንጂ ለጥምቀት ከሚሰጠው የአስተምህሮ ትኩረት ጋር በፍጹም አይሄድም፡፡ እንደሚታወቀው ቅዱስ ዮሐንስ ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ማግባቱን አንስቶ ያደረገው ተግሳጽና ውጤቱ ከጥምቀት ዕለት ይልቅ ለቅዱስ ዮሐንስ በዓል (ዘመን መለወጫ) የሚስማማ ነው፡፡ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ፖለቲካዊ ስብከትን የሚያዘወትሩ ሰዎች ግን የሚጨነቁት ስለ ንግግራቸው ፖለቲካዊ ፋይዳ እንጂ መንፈሳዊ ወቅታዊነት ወይም ተገቢነት (timeliness or appropriateness) አይደለም፡፡ ተነግሮ የማያልቅ ጥልቅ ምሥጢርና አስተምህሮ ባለበት በጥምቀት ዕለት ለበዓሉ ከሚስማማ ትምህርት ይልቅ ለፖለቲከኞች ማባበያ የሚሆን ንግግርን እንደ ወንጌል መናገር መምህሩ ትኩረታቸው ለቃለ እግዚአብሔር ሳይሆን ሊያስተላልፉት ለፈለጉት ፖለቲካዊ መልእክት መሆኑን ያስታውቅባቸዋል፡፡

ምሣሌ 3፡ በአንዲት የምዕራባውያን ከተማ ዓመታዊ በዓል እየተከበረ ባለበት የዕለቱ መምህር የዕለቱን ወንጌል፣ ስለ ዕለቱ በዓል ምንነት ከማብራራት ይልቅ ስለ አንድ የፖለቲካ ባለስልጣን ብቻ ሲያወሩ ለማስተማር የነበራቸውን ጊዜ ጨርሰውታል፡፡ ይህንን ባለስልጣን ‹‹ነቢዩ ሙሴ ነው›› ብለው ሲያሞጋግሱ ለሌላው ደግሞ የፈርዖንን ግብር ሰጥተው የራሳቸውን ፖለቲካዊ ንግግር ሲያደርጉ ውለዋል፡፡ ይህንን የሚወዱትን ፖለቲከኛ “ነቢይ” ወይም “በልዩ ሁኔታ ከእግዚአብሔር የተላከ መሲህ” ለማስመሰል የእግዚአብሔርን ቃል እያዳቀሉ ወይም እያጣመሙ የሚፈልጉትን ፖለቲካዊ ትርክት አቅርበዋል፡፡ ከዚህም አልፎ አንድን የፖለቲካ መሪ የባህራንን የዕዳ ደብዳቤ ካጠፋለት ከሊቀ መላእክት ከቅዱስ ሚካኤል ጋር ማነፃፀር የሚያስከትለውን ጉዳት መገመት አያስቸግርም፡፡ ዓመት በዓሉን ሊያከብር የመጣ ምዕመን መማር ያለበት በዕለቱ ቤተክርስቲያን የምታስተላልፈውን መንፈሳዊ አስተምህሮ እንጂ የፖለቲከኞችን ወገንተኛ የአቋም መግለጫ አይደለም፡፡ የኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችንን በነቢያትና በሐዋርያት ደገኛ አስተምህሮ ላይ መመስረት ለማስረዳት ዓይነተኛ አጋጣሚ በሆነው፣ እጅግ ብዙ የመጻሕፍት ንባብና ትርጓሜ በሚሰጥበት ቀን አንድ መምህር ጊዜ ተርፏቸው ስለ ወገንተኛ ፖለቲካ የሚያወሩ ከሆነ፣ በተለይም ደግሞ ከምዕመናን ወገን የተወሰኑትን መንፈሳዊ ባልሆነ መነሻ የሚያስከፋና የሚፈርጅ ንግግር የሚናገሩ ከሆነ ትኩረታቸው ለቃለ እግዚአብሔር ሳይሆን በፖለቲካዊ ኀልዎት የሚወድዱትን ለማሞገስ፣ የሚጠሉትን ለመውቀስ መሆኑ ይታወቅባቸዋል፡፡

እነዚህ ምሣሌዎች ለማሳያነት የቀረቡ ናቸው፡፡ በይዘታቸውም እንደ ቅደም ተከተላቸው በስብከት ጊዜ እንደዋዛ የሚቀርቡ ፖለቲካዊ ምልከታዎችን፣ መንፈሳዊ የት መጣ (መነሻ) የሌላቸውን እምቅ (coded) ፖለቲካዊ ቃላት በመጠቀም የሚተላለፉ ፖለቲካዊ ወገንተኝነቶችን እንዲሁም በአንጻራዊነት ግልጽ ሊባሉ የሚችሉ የፖለቲካዊ ወገንተኝነት ማሳያ የሚሆኑ ንግግሮችን ይወክላሉ ብለን እናምናለን፡፡ እነዚህ ምሣሌዎች ለማሳያነት ቀረቡ እንጂ ሌሎች ብዙ ምሣሌዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ አንዳንዶች በቤተክርስቲያን አውደ ምህረት ቆመው የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም ቡድኖች ሊዋቀሩበት ስለሚገባ ፖለቲካዊ መስፈርት መመሪያ ሲሰጡ ይታያሉ፡፡ ለሚፈልጉት ፖለቲካዊ ሰልፍ በቤተክርስቲያን አውደ ምህረት የሚቀሰቅሱ፣ የማይፈልጉትን ፖለቲካዊ ሰልፍ ደግሞ በዛው አውደ ምህረት ላይ ሲነቅፉ የሚታዩም አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የሚወዱትን ፖለቲከኛ መልአክ እያስመሰሉ የሚጠሉትን ፖለቲከኛ ደግሞ ከሰይጣን ጋር እያመሳሰሉ የእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል ብቻ ሊነገርበት የሚገባውን የቤተክርስቲያን አውደ ምህረት (የምህረት አደባባይ) የመሸነጋገያ ወይም መወነጃጀያ ሰገነት ያስመስሉታል፡፡ በአጠቃላይ በመንፈሳዊ አውደ ምህረት ፖለቲካዊ ስብከት የሚያሰሙ ሰዎች የቤተክርስቲያንን ለዛ የማይረዱ “ቅኔው ሲያልቅበት ቀረርቶ የጨመረውን” ምስኪን የቆሎ ተማሪ ይመስላሉ፡፡

ትምህርተ ሃይማኖት በሚነገርበት፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን በሚተነተንበት አውደ ምህረት ከቅዱሳት መጻሕፍት ምሥጢር ይልቅ ለወገንተኛ ፖለቲካዊ ትርክት ጊዜ የሚተርፋቸው ሰባክያን መንፈሳዊ ዓላማ አላቸው ብሎ መገመት አይቻልም፡፡ ይህም በመንፈሳዊ እይታ ያለመብሰል ማሳያ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸው አስቀድሞ “ጌታ ሆይ በዚህ ወራት ለእስራኤል ልጆች መንግስትን ትመስላለህን?” (ሐዋ. 1፡6) በማለት የጠየቁት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካስተማራቸው መንፈሳዊ ትምህርትና ተስፋ ይልቅ በእስራኤላውያን ፖለቲከኞች ዘንድ የትኩረት አቅጣጫ የነበረው ከሮም ቅኝ ግዛት የመውጣት ሀሳብ በልባቸው የበለጠ ቦታ ስላገኘ ነበር፡፡ በእምነት በጎለመሱ ጊዜ ግን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ “አይሁድ ምልክትን ይጠይቃሉ፤ የጽርዕ (ግሪክ) ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፡፡ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአህዛብም ስንፍና ነው፡፡” (1ኛ ቆሮ. 1፡23) ይላሉ፡፡ የመንፈሳዊ ስብከት ዓላማም የአይሁድን ዓይነት ምልክት ናፋቂነትም ሆነ የግሪክ ሰዎችን  ዓይነት በራስ ጥበብ መመካት የሚያስናፍቅ ሳይሆን በእግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት የተገለጠልንን የእግዚአብሔርን ማዳን መመስከርና ማወጅ ምዕመናንንም ወደ ድኅነት መንገድ መመለስ ነው፡፡

ፖለቲካን በቤተክርስቲያን መስበክ የሚያመጣው ጉዳት

ቅዱሳን አበው በቅዱሳት መጻሕፍት ባስቀመጡት መመሪያ ካልሆነ በቀር በቤተክርስቲያን ስም ወንጌልን እንዲያስተምር የተሰየመው ካህን (ሰባኬ ወንጌል) በተንኮል፣ መመሪያን ባለማወቅ ወይም በሞኝነት ወደማይገባው (ጠብቆም ላልቶም ይነበብ) ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ ከዘባረቀ ማንንም ቢደግፍ ድጋፉ፣ ማንንም ቢነቅፍም ነቀፋው ያስነቅፈዋል እንጂ አያስመሰግነውም፡፡ ከራሱም አልፎ ሃይማኖቱን፣ ቤተክርስቲያኑን ያስነቅፋል፡፡ በሌላው ዘንድም እንዲጠላ ያደርጋል፡፡ የቤተክርስቲያን እምነትና ቀኖና ከፖለቲካ ሕግና መመሪያ የተለየ እንደመሆኑ መጠን ስብከትም ከፖለቲካ የተለየ መሆኑን ሰባኪው ማስተዋል አለበት፡፡ እንግዲህ የወንጌል ሰባኪዎች ትምህርተ ሃይማኖትን ብቻ እንዲሰብኩ የሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን መመሪያ ነው፡፡ 

ፖለቲካን በቤተክርስቲያን አውደ ምህረት ላይ መስበክ ብዙ አስከፊ ጉዳቶች አሉት፡፡ በመጀመሪያ የእግዚአብሔር ቃል የሚነገርበትን፣ የሰው ልጅ ምግበ ነፍስን የሚያገኝበትንና እግዚአብሔር የሚከብርበትን አውደ ምህረት ለምድራዊ ዓላማ ማዋል እግዚአብሔርን ማሳዘን ቤተክርስቲያንንም ማስወቀስ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በሐዋርያት (የእግዚአብሔር መልእክተኞች) እግር የተተኩ ሰባክያን የተላኩበት ዓላማ የላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ለሰው ልጅ ለማድረስ እንጂ የላካቸውን የእግዚአብሔርን ነገር ትተው ለሰው እንዲታዘዙ አይደለም፡፡ ይህን በማድረግ አለን የሚሉትን ሐዋርያዊ ዓላማ አጠያያቂ ያደርጉታል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ እግዚአብሔር ረድቶአቸው የእርሱን ቃል ለመስማት ሰምተውም ሕይወታቸውን ለማዳን በእግዚአብሔር ቤት ለተሰበሰቡ ምዕመናን በእውነተኛው የእግዚአብሔር ቃል ፈንታ አላፊውን ምድራዊ ፖለቲካ መስበክና በመካከላቸው ልዩነትን መፍጠር የሰውን ልጅ በነፍስም በሥጋም መጉዳት ነው፡፡ ይህንን ያዩ/የሰሙ ምዕመናን ደግሞ ከቤተ እግዚአብሔር ሊርቁ ይችላሉ፡፡ ሰባኪውም ምዕመናንን የሚሰበስብ ከመሆን ይልቅ የተሰበሰቡትን የሚበትን ይሆናል፡፡ አንዳንድ ባለስልጣኖች (ፖለቲከኞች) ለሕዝቡ መልእክት ለማስተላለፍ በሚል ሽፋን የቤተክርስቲያንን አውደ ምህረት ለፖለቲካ ቅስቀሳ የሚጠቀሙበት ከሆነም ጉዳቱ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡

ስለዚህ የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን ስብከታችን እንደ አይሁድ ምልክትን የሚናፍቅ፣ እንደ ግሪክ ሰዎች በእግዚአብሔር ዘንድ ሞኝነት በሆነ በምድራዊ ጥበብ መመካትን የሚያመጣ መሆን የለበትም፡፡ ይልቁንስ በስብከታችን ለፍጥረታዊ ሰው ሞኝነት የሚመስለውን በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት የተገለጠውን የእግዚአብሔር ማዳን፣ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ከጌታ ተምራ የጠበቀችውን ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዓተ እምነት በማወጅ፣ በመመስከርና በመተንተን በበረቱ ውስጥ ያሉ የእግዚአብሔር በጎች (ምዕመናን) በእምነትና በምግባር እንዲጸኑ፣ ከበረቱ ውጭ ያሉት የእግዚአብሔር በጎች (ምዕመናን) ደግሞ ወደ በረቱ እንዲገቡ ማድረግ ይገባናል፡፡ የቤተክርስቲያንን አውደ ምህረትም ለእግዚአብሔር ቃል ብቻ ልናደርገው ይገባል እንጂ ፖለቲካንና ስብከትን እየቀላቀልንና እያዳቀልን ሰውና እግዚአብሔርን ልናሳዝን አይገባም፡፡ ለቅዱሳን ሐዋርያት፣ ለሐዋርያውያን አበውና በየዘመኑ ለተነሱ እውነተኛ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ጥበብ መንፈሳዊን የገለጸ፣ ለሰማዕትነት በፍርድ አደባባዮች ቆመው እንኳ የሚናገሩት ቃለ እግዚአብሔር ለማንኛውም ሥጋዊ ዓላማ እንዳይዛነፍባቸው አንደበታቸውን የጠበቀ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በዘመናችን ላሉ መምህራንና ሊቃውንትም ቃል ኪዳኑን አያርቅብን፡፡ ለህዝባችንም ማስተዋሉን ያድልልን፡፡

ስብሃት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር፡፡ አሜን፡፡