መዳንም በሌላ በማንም የለም: ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ

ምክንያተ ጽሕፈት

በመጽሐፍ ቅዱስ የተመዘገበው የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት በቅዱሳን ሰዎች የተጻፈ ነው፡፡ የሚተረጎመውም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ጥበብ መንፈሳዊን ከእውነተኛ ምንጭ በተማሩ ሰዎች ነው፡፡ ይሁንና የበጎ ነገር ጠላት ዲያብሎስ በሀሰተኛ መምህራን እያደረ የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብ ይቆነጻጽላል፣ ትርጓሜአቸውንም ያጣምማል፡፡ ሐዋርያዊ ውርስ የሌላቸው፣ ቅዱሳት መጻሕፍትንም እንደግለሰብ ድርሰት በልብ ወደድ የሚተረጉሙ ሰዎች ትርጓሜአቸውን አጣመው ያለአውዳቸው እየጠቀሱ ራሳቸው ግራ ተጋብተው ምዕመናንን ግራ ከሚያጋቡባቸው የተወደዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት አንዱ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ የጻፈልንና በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 4፡12 የተጻፈው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ያስተማረው ትምህርት “መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰው የተሰጠ ሌላ ስም ከቶ የለምና” በማለት ፣ የተናገረው ምስክርነት ነው፡፡

ይህ የቅዱስ ጴጥሮስ ምስክርነት ጥልቅ የክርስትና ሃይማኖት መሠረተ እምነትን የሚያስረዳ ቃል ነው፡፡ ይሁንና “እምነታቸውን” ቤተክርስቲያንን በመቃወም ላይ ብቻ የመሠረቱ ሰዎች ልዩ ልዩ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮዎችን ለመቃወም ያለ አውዱ ይጠቀሙታል፡፡ ስለ በሽተኞች ፈውስና ሌሎች ተዓምራት፣ ስለ ቅዱሳን ሰዎች አማላጅነት፣ ስለ ቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ሲነገር እንዲሁም ስለሌሎች ማንኛውም ዓይነት መንፈሳዊ ውይይት ሲነሳ ሁሉንም በራሳቸው አላዋቂነት ልክ እያሰቡ ሌሎች መንፈሳዊ ሀሳቦችን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ጋር ያለአግባብ እየቀላቀሉ “መዳንም በሌላ በማንም የለም” የሚለውን አምላካዊ ቃል መልዕክት ሰው እንዳይረዳው ያደርጋሉ፡፡ የዛሬ አስተምህሮ ጦማር ዓላማ የዚህን አምላካዊ ቃል ትርጉም ማብራራትና በግምት የሚደረጉ የአጽራረ ቤተክርስቲያንን ማሳሳቻዎች ለይቶ ማሳየት ነው፡፡

የሐዋርያት ሥራ (ገድለ ሐዋርያት)

“መዳንም በሌላ በማንም የለም” የሚለውን የቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት ለመረዳት የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን ዓላማ መረዳት እንዲሁም ለቅዱስ ጴጥሮስ ንግግር መነሻ የሆነውን ታሪክ ማንበብ ይጠቅማል፡፡ የሐዋርያት ሥራ በዋናነት ቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታ ትንሣኤ በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዓመታት ያደረጉትን መንፈሳዊ ተጋድሎ፣ ያስተማሩትን ሐዋርያዊ ትምህርት እና የተቀበሉትን ልዩ ልዩ ሰማዕትነት የሚያትት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው፡፡ የባህርይ አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ ሊቃናት ክፋት ለመስቀል ሞት ተላልፎ ቢሰጥም እርሱ ግን የመጣበት ዓላማ ነበርና በሞቱ ሞትን አጥፍቶ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን አውጇል፡፡ በልዩ ልዩ ተዓምራት የተገለጠው የክርስቶስ ትንሣኤ ግን ለአይሁድ ሊቃናት የሐሰተኝነታቸው ማረጋገጫ፣ የግፈኝነታቸው ማሳያ፣ ከቀናች የአባቶቻቸው ሃይማኖትና ተስፋ ተለይተው ራሳቸው በፈጠሩት ሃይማኖታዊ ካባ ባለው ምድራዊ ክብርና ዝናን ብቻ በሚፈልግ አሳፋሪ ማንነት መተብተባቸውን የገለጠ ነበር፡፡ ስለሆነም በማናቸውም መንገድ የክርስቶስን ትንሣኤ ማስተሀቀር (ማስተባበል) የተንኮላቸው ሁሉ ማዕከል ነበር፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመስቀል አይሁድ ከጠቀሱት የማስመሰል ክስ አንዱ የእግዚአብሔር ልጅ፣ እግዚአብሔር መሆኑን በመጽሐፋቸው የተጻፈውን እንኳ እንዳያምኑ ልባቸውን አክብደው ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይገባው “ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር በሀሰት ያስተካክላል” በማለት የፈጠሩት የክህደት ንግግራቸው ነው፡፡ የሰይጣንን ተንኮል በደቀመዛሙርቱ ትምህርትና የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የሆኑ ልዩ ልዩ ተዓምራት ማፍረስ ልማዱ የሆነ እግዚአብሔር ደግሞ አላዋቂና ፈሪ የነበሩ ሐዋርያቱን ሳይቀር አዋቂና ደፋሮች አደረጋቸው፤ በእነርሱም እያደረ እንድንበት ዘንድ የተሰጠንን የክርስቶስን ሥም (ማንነት) በይፋ በመግለጥ ሊቃናተ አይሁድን አሳፈራቸው፣ ቤተክርስቲያንንም አጸናት፡፡

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከተጻፈባቸው ዓላማዎች ዋናው አይሁድ ጌታችን በሰው ባህርይ መገለጡን አይተው አምላክነቱን ይክዱ ያስክዱ ነበርና ስለእኛ በፈቃዱ ሰው መሆኑ፣ በመካከላችን መመላለሱ፣ መከራ መቀበሉ ከአብ ከመንፈስቅዱስ በክብር እንደማያሳንሰው ማስረዳት ነው፡፡ ለዚህም ነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በተዓምራትና በትምህርት ነገረ ክርስቶስን በማጉላት የትንሣኤውን ኃይል የሚመሰክረው፡፡ የጌታችን የትንሣኤው ኃይል ከተገለጠባቸው ሐዋርያዊ አስተምህሮዎችና ተዓምራትና መካከል በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ሦስት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ያደረጉት ተዓምርና በተዓምሩ ምክንያት ቅዱስ ጴጥሮስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ አራት ያስተማረው የጌታችንን ትንሣኤ የሚያስረግጥ አስተምህሮ ይጠቀሳሉ፡፡

የቤተክርስቲያን የጸሎት ሰዓት

ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና ፍቁረ እግዚእ (የጌታ ወዳጅ) ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ “በጸሎት ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት ወደ መቅደስ ይወጡ ነበር፡፡” (ሐዋ. 3፡1) ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ስለ እውነት ፍርድህ ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ” (መዝ. 118፡ 164) እንዳለ በነቢያትና በሐዋርያት መሰረትነት በጸናች (ኤፌ. 2፡20) ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከሚታወቁት ሰባቱ የጸሎት ጊዜያት አንዱ የተሰዓት (የቀኑ ዘጠኝ ሰዓት) ጸሎት ነው፡፡ ዘጠኝ ሰዓት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ተፈጸመ” ብሎ ቅድስት ነፍሱን ከክቡር ሥጋው የለየባት ሰዓት ስለሆነች ቅድስት ቤተክርስቲያን በተለየ ሁኔታ በጸሎት የምታስባት ሰዓት ነች፡፡ በአጽዋማት ጊዜ ቅዳሴ ተቀድሶ ሥጋውና ደሙ ለምዕመናን የሚሰጥባት የከበረች የጸሎት ሰዓት ነች፡፡ በሐዋርያት ሥራ 10፡3 እንደተመለከተው ቅዱሳን መላእክት የሰዉ ልጆችን ጸሎት ወደ መንበረ ጸባኦት የሚያሳርጉባት የከበረች የጸሎት ሰዓት ነች፡፡ የኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ትውፊት ምንጮች የሆኑ ቅዱሳን ሐዋርያትም በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ ይወጡ ነበር፡፡

በመቅደስ ደጅ ምጽዋት የሚለምን በሽተኛ

ቅዱሳን ሐዋርያት ወደ ቤተመቅደስ ሲሄዱ “ከእናቱ ማኅፀንም ጀምሮ እግሩ ሽባ ሆኖ የተወለደ…ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ ሁልጊዜ እየተሸከሙ መልካም በሚልዋት በመቅደስ ደጃፍ [ያስቀምጡት የነበረ በሽተኛ] ጴጥሮስና ዮሐንስንም ምጽዋት ይሰጡት ዘንድ ለመናቸው፡፡” (ሐዋ. 3፡2-3) የድኅነትን ነገር መቀለጃ የሚያደርጉ ሰዎች ድኅነት “በእምነት ብቻ” እንደሆነ አስመስለው ቅዱሳት መጻሕፍትን በማጣመም ፆም፣ ጸሎት፣ ምጽዋት፣ ስግደትና ሌሎችም በጎ ምግባራት ከድኅነት ጋር የማይገናኙ እንደሆኑ አስመስለው ምዕመናንን ከጽድቅ መንገድ ለመለየት ይደክማሉ፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ግን እምነት ያለምግባር ከነፍስ እንደተለየ ሥጋ የሞተ መሆኑን (ያዕ. 2፡14-26) በማስተማር ምዕመናን እንደ አቅማቸው ምጽዋትን ለተቸገሩት እንዲሰጡ፣ የተቸገሩትን የማይረዳ ምዕመንም በዕለተ ምጽአት እንደሚፈረድበት በአጽንኦት ታስተምራለች፡፡ (ማቴ. 25፡31-46) ከዚህም የተነሳ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ዘመን ምጽዋትን የሚፈልጉ ችግረኞች መጠለያ መሆኗ የታወቀ ነው፡፡ ከሐዋርያት የተማረችው ነውና፡፡

የቅዱሳን ሐዋርያት ተዓምር

ከእናቱ ማኅጸን ጀምሮ ሽባ ሆኖ የተወለደው ሰው ቅዱሳን ሐዋርያት ወደ ቤተ “መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ይሰጡት ዘንድ ለመናቸው፡፡” እነርሱ ግን እርሱ ከጠበቀው የገንዘብ ምጽዋት የበለጠውን የፈውስ ምጽዋት ሰጡት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ወርቅና ብር የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ ሂድ” አለው፡፡ (ሐዋ. 3፡3-6) አይሁድ ናዝሬትንና ከናዝሬት የሚወጡ ሰዎችን ይንቋቸው ነበር፣ ናዝሬት የወንበዴዎች ከተማ ነበረችና፡፡ ለዚያ ነው ምሁረ ኦሪት የነበረው ናትናኤል ቅዱስ ፊልጶስ ሙሴና ነቢያት የተናገሩለትን “የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው” ባለው ጊዜ “በውኑ ከናዝሬት ደግ ሰው ሊወጣ ይቻላልን?” ያለው፡፡ (ዮሐ. 1፡46-47) ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” ሽባውን ማዳኑ ለአይሁድ ልዩ መልእክት ነበረው፡፡ “እናንተ ከናዝሬት በመገኘቱ (ናዝሬት በማደጉ) የናቃችሁት፣ በሀሰት ፍርድ ለመስቀል ሞት አሳልፋችሁ የሰጣችሁት፣ ትንሣኤውን ለመደበቅ የሀሰት ምስክር ገዝታችሁ ከወቀሳ ለመዳን የምትደክሙበት ኢየሱስ ክርስቶስ የክብር ትንሣኤው ማሳያ የሆነ ይህን ተዓምር በእኛ እጅ አደረገ” ማለቱ ነው፡፡

የትንሣኤው ኃይልና የኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት

ቅዱሳን ሐዋርያት ተዓምራቱን የማድረጋቸው ዓላማ የክርስቶስን የትንሣኤ ኃይል መግለጥ ነበር፡፡ የእስራኤል ሰዎች ከእናቱ ማኅጸን ጀምሮ ሽባ ሆኖ የተወለደውን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ሥም፣ በደቀመዛሙርቱ አማካኝነት መፈወስ ባዩ ጊዜ ተደነቁ፡፡ ቅዱሳን ተዓምራትን የሚያደርጉት እንደዘመናችን ጋጠወጥ መናፍቃን፣ ጠንቋዮች፣ መተተኞችና ከንቱ ውዳሴ ፈላጊዎች ለራሳቸው አንዳች ክብር ወይም ጥቅም ፈልገው አይደለም፡፡ ስለሆነም ሰዎች ሁሉ በተደነቁ ጊዜ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “እናንት የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ ይህን ለምን ታደንቃላችሁ? እኛንስ በኀይላችንና በጽድቃችን ይህን ሰው በእግሩ እንዲሄድ እንዳደረግነው አስመስላችሁ ለምን ታዩናላችሁ?…የሕይወትን ባለቤት ግን ገደላችሁት፤ እግዚአብሔርም ከሙታን ለይቶ አስነሣው፤ ለዚህም እኛ ምስክሮቹ ነን፡፡ ስሙን በማመን ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን እርሱ ስም አጸናው፤ እርሱንም በማመን በፊታችሁ ይህን ሕይወት ሰጠው፡፡” (ሐዋ. 3፡12-16) በማለት መሰከረ፡፡

ይህ ምስክርነት የክርስቶስን እውነተኛ አምላክነት (ሞትን በስልጣኑ ድል ማድረጉን) እንደገለጠው ሁሉ የአይሁድ ሊቃናት (አለቆችን) ሀሰተኛነት የገለጠ ነበርና የአይሁድ የቤተመቅደስ አለቆች፣ በተለይም “ትንሣኤ ሙታን የለም” ብለው የሚያስተምሩትን የምንፍቅና አስተምህሮ ያፈረሰባቸው ሰዱቃውያን መከራ ሊያጸኑባቸው ተሰበሰቡ፤ ቅዱሳን ሐዋርያትንም በማን ስምና በማን ኀይል ተዓምራቱን እንዳደረጉ ጠየቋቸው፡፡(ሐዋ. 4፡1-7) በአይሁድ ሀሳብ ሐዋርያት ማስፈራራታቸውን አይተው የተዓምራቱን ባለቤት፣ የትንሣኤያችን በኩር የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ከመስበክ (አምላክነቱን፣ አዳኝነቱን፣ ቤዛነቱን ከመመስከር) የሚቆጠቡ መስሏቸው ነበር፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ግን አይሁድን በኃጢአታቸው ወቅሶ፣ የክርስቶስን ትንሣኤ መስክሮ፣ በሽተኛውም የተፈወሰው በክርስቶስ ሥም በማመን መሆኑን ነገራቸው፡፡

ይልቁንም “መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰው የተሰጠ ሌላ ስም ከቶ የለምና” (ሐዋ. 4፡12) በማለት ሰቃልያነ እግዚእ አይሁድን አሳፈራቸው፡፡ አይሁድ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥም (የክርስቶስን አምላክነት፣ ትንሣኤውን ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱን) እንዳያስተምሩ በከለከሏቸው ጊዜም ቅዱሳን ሐዋርያት “እግዚአብሔርን ያይደለ እናንተን ልንሰማ በእግዚአብሔር ፊት ይገባልን? እስኪ እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ፡፡ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም እንል ዘንድ አንችልም፡፡” (ሐዋ. 4፡19-20) በማለት በጽናት ቆመዋል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ሳያምኑ፣ ይልቁንም ትንሣኤውን እየካዱ መዳን በሌላ በማንም የለምና፡፡

መዳን ማለት ምን ማለት ነው?

በቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ መዳን ማለት በዋናነት የዘላለምን ሕይወት ማግኘት ማለት ነው፡፡ ከዚያም ባሻገር ግን መዳን ማለት እንደ አገባቡ ከስጋ ደዌ፣ ከአጋንንት እስራት መፈወስንም ያሳያል፡፡ ጌታ በወንጌል “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ትሻለች” (ማቴ. 16፡4) እንዳለ በእምነት የደከሙ ሰዎች ተዓምር ናፋቂ ስለሆኑ መዳን ሲባል የሚታያቸው ሥጋዊ ድህነት ብቻ ነው፡፡ ከበሽታ መዳን፣ ሀብትና ንብረት ማግኘት፣ በምድር በሰዎች ዘንድ ከፍ ብሎ መታየት መዳን ይመስላቸዋል፡፡ ለዚያ ነው በዘመናችን ያሉ መናፍቃንና መሰሎቻቸው የትምህርታቸው ሁሉ መሰረት የሀሰት ተዓምራት የሆነው፡፡ እነዚህ ደካሞች “መዳንም በሌላ በማንም የለም” የሚለውን ቅዱስ ቃል ከምድር ከፍ በማይል ሀሳባቸው ለልዩ ልዩ የሥጋ  ደዌ የተነገረ ይመስላቸዋል፡፡ ምዕመናንና ምዕመናት በቅዱሳን ቃልኪዳን፣ በቤተክርስቲያን ጸሎት ከደዌ ሥጋ ሲድኑም ብርቅ ይሆንባቸዋል፡፡ በውስጣቸው ያደረ የበጎ ነገር ጠላት ዲያብሎስም ከምድራዊ ሀሳባቸው ከፍ እንዳይሉ ስለሚፈልግ በደካማ አመክንዮ በቅዱሳን ቃል ኪዳን ሰዎች ከደዌ ሥጋ መዳናቸው “መዳንም በሌላ በማንም የለም” በማለት ቅዱስ ጴጥሮስ ከተናገረው ጋር የሚጋጭ አስመስለው ይከራከራሉ፡፡

እንግዲህ ምን እንላለን? ለእነዚህ ሰዎች የቅዱሳንን ቃል ኪዳን ከማስረዳት በዓይናቸው የሚያዩትን የዓለም ስርዓት ዓይናቸውን ገልጠው እንዲያዩ ማገዝ ይቀላል፡፡ ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁም? የእግዚአብሔር ሥጋዊ መግቦት በእምነት የማይገደብ እንደሆነ፣ ቸር የሆነ አምላክ ለክፉዎቹም ለደጎቹም የምህረት ዝናብን እንደሚያዘንብ፣ የቸርነት ፀሐይን እንደሚያወጣ መረዳት አትችሉም? እናንተ አላዋቂዎች አንድ እግዚአብሔርን የካደ ሰው እንኳ በክፉ ሥጋዊ ደዌ ቢታመም እግዚአብሔርን የማያውቁ ምድራውያን ጠበብት ሲያድኑት አላያችሁም? በስጋዊ ደዌ የታመመን ሰው ምድራውያን ጠበብት በህክምና ሲያድኑት የእግዚአብሔር የማዳን እጅ የሌለችበት ይመስላችኋል? ምንም እንኳ ምድራዊ ጥበብና በቅዱሳን የሚገለጥ ተዓምር የተለያዩ ቢሆኑም ምሳሌው በተዓምራት የሚፈጸም ስጋዊ ድህነትን ለመረዳት ይጠቅመናል፡፡ በዚህ ጊዜም ከምድር ከፍ ያላለ ቅዱሳት መጻሕፍትን በግምት የሚተረጉም፣ የሐዋርያትን የሕይወትና የትምህርት ውርስ የማይከተል የማያስተውል ልቦናችሁ “መዳንም በሌላ በማንም የለም” እያለ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጉም እንዳትረዱ ሲጋርድባችሁ ለምን መንቃት አትችሉም? እስኪ ከአይሁድ ተማሩ፡፡

ሊቃናተ አይሁድ ሽባውን ሰው ቅዱሳን ሐዋርያት ድኅነተ ሥጋ ስለሰጡት ተደንቀው “በማን ስምና በማን ኀይል” (ሐዋ. 4፡7) ተዓምራቱ እንደተደረገ ለማወቅ ጓጉተው ነበር ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ የመጡት፡፡ ሥጋዊ ሰው ምንጊዜም የሚታየው ሥጋዊ ክብር፣ ሥጋዊ ድህነት፣ ሥጋዊ ደስታ ብቻ ስለሆነ መንፈሳዊው ክብር፣ መንፈሳዊው ድህነት፣ መንፈሳዊው ደስታ አይታሰበውም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ሽባውን ከአካላዊ በሽታ ያዳኑት እርሱና ተዓምራቱን ያዩ ሁሉ ወደ እውነተኛው ድኅነት (ዘላለማዊ ሕይወት) እንዲመለሱ የዘላለም ሕይወት ምንጭ የሆነውን አይሁድ በናዝራዊነቱ ያቃለሉትን የመዳናችንን ራስ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያምኑበት ምልክት እንዲሆናቸው ነው፡፡ ስለሆነም አይሁድ ለሥጋዊ ተዓምር ሲሰበሰቡ ቅዱስ ጴጥሮስ ልባቸውን ከፍ አደረገው “መዳንም በሌላ በማንም የለም” በማለት መንፈሳዊውን ተዓምር የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው መሆን፣ በዚህም ሰውም አምላክም ሆኖ በሐዲስ ኪዳን መካከለኛነቱ የሰውን ባሕርይ ተዋህዶ በአምላካዊ ስልጣኑ ከኃጢአት ፍርድ የተቤዠን መሆኑን እንዲያምኑ አስተማራቸው፡፡

የተቀደሰ ሐዋርያ ጳውሎስ “አሁንም ወንድሞቼ ሆይ ዘወትር እንደምትሰሙኝ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን ሳልኖርም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ሆናችሁ ለድኅነታችሁ ሥሩ [መዳናችሁን ፈጽሙ]” (ፊልጵ. 2፡12) እንዳለ መዳን ማለት የዘላለምን ሕይወት መውረስ፣ ጌታችን በዳግም ምጽዓት በክበበ ትስብእት፣ በግርማ መለኮት በተገለጠ ጊዜ በቀኙ ከሚቆሙት፣ የሕይወትን ቃል ከሚሰሙት ቅዱሳን ወገን (ማቴ. 25፡31-46) ለመሆን መብቃት (መታደል) ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “መዳንም በሌላ በማንም የለም” ሲል በኢየሱስ ክርስቶስ ሳያምኑ የዘላለም ሕይወት አይገኝም ማለቱ ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዳያስተምሩ ይከለክሏቸው የነበሩ አይሁድ ራሳቸውን የነቢያት ወራሾች፣ እውነተኛ ሃይማኖተኞች አስመስለው ያቀርቡ ነበርና ቅዱስ ጴጥሮስ “በኢየሱስ ክርስቶስ ሳታምኑ ስመ እግዚአብሔርን ብትጠሩ፣ በነቢያት ብትመኩ መዳን አትችሉም” ሲላቸው ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ

በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን መሰረታዊ አስተምህሮ ለድኅነት መሠረት የሆኑ አምስት ዋና ዋና መሠረተ እምነቶች (ዶግማዎች) አሉ፤ እነርሱም አምስቱ አዕማደ ምስጢራት ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ እንኳ ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቆም አይችልም፡፡

  1. በምስጢረ ሥላሴ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ህይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ባለው ፍጹም አንድነትና ልዩ ሦስትነት ያላመነ ሰው መዳን በሌላ በማንም አያገኝም፡፡
  2. በምስጢረ ሥጋዌ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ለማዳን ንጽሕት፣ ቅድስት ከሆነች፣ ከአዳም ተስፋ፣ ከዳግሚት ሄዋን፣ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ መወለዱን፣ በመወለዱም ከአምላካዊ ክብሩ እንዳልተለየ የማያምን ሰው መዳን በሌላ በማንም አያገኝም፡፡
  3. በምስጢረ ጥምቀት ጥምቀትን በባህረ ዮርዳኖስ ከመሠረተ፣ በመስቀል በተሰቀለ ጊዜ ሌንጊኖስ የተባለ ሮማዊ ወታደር ጎኑን በጦር ሲወጋው ለልጅነት ጥምቀት፣ ለድህነት ጥምቀት ንፁህ ውሃና ደም በፈሰሰው በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት አምኖ፣ መስክሮ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ያልተጠመቀ ሰው መዳን በሌላ በማንም አያገኝም፡፡
  4. በምስጢረ ቁርባን ሕብስቱን ለውጦ ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሀደው  ሥጋ፣ ወይኑን ለውጦ ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሀደው ደም ባደረገ (በሚያደርግ)፣ ለዘላለምም በቤተክርስቲያን አድሮ ይህን አምላካዊ ተዓምር በሚፈጽም በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ የጌታን ቅዱስ ሥጋውን፣ ክቡር ደሙን ለልጅነት፣ ለስርየተ ኀጢአት የማይቀበል (የማይበላ የማይጠጣ) ሰው መዳን በሌላ በማንም አያገኝም፡፡
  5. በምስጢረ ትንሣኤ ሙታን አስቀድሞ ለዓለም ቤዛነትና አርአያነት በትህትና ከመጣበት አመጣጥ በተለየ በክበበ ትስብእት (በሰው ሥጋና አካል)፣ በግርማ መለኮት (በደብረታቦር ተራራ እንደተገለጠው ያለ መለኮታዊ ግርማ) በሚገለጥ በቀናች ሃይማኖት፣ በደገኛ ምግባር ጸንተው የሚጠብቁትን ወደ ዘላለማዊ ሕይወት፣ በሰይጣን ማታለል በመናፍቃን ማጭበርበር ተታለው ከቀናች ሃይማኖት፣ ከደገኛ ምግባር የራቁትን ወደ ዘላለም ቅጣት የሚልክ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመጣ የማያምን፣ ለዚያች የፍርድ ቀንም በአካለ ሥጋ እያለ የማይዘጋጅ ሰው መዳን በሌላ በማንም አያገኝም፡፡

ስለሆነም “መዳንም በሌላ በማንም የለም” ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የቤተክርስቲያን ራስና መሰረት መሆኑን፣ እምነትም ምግባርም ያለእርሱ ዋጋ ቢስ መሆኑን ማመን፣ መቀበል፣ በሕይወትም መኖር ማለት ነው እንጂ በመዳን ጉዞ ከእያንዳንዱ ምዕመን እምነትና ምግባር፣ በአጸደ ስጋና በአጸደ ነፍስ ካሉ ቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ፣ እንዲሁም ከቅዱሳን መላእክት ረዳትነት ጋር የሚነጻጸር ወይም የሚምታታ አይደለም፡፡

ማነጻጸሪያ ምሳሌዎች

የመዳን እውነተኛ መንፈሳዊ ትርጉም ከላይ እንደተብራራው መሆኑን ካየን እያንዳንዱ ሰው ለድኅነት እንዲበቃ የተለያዩ አካላትን ተመጋጋቢ ድርሻ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ሀሰተኞች በሰው ልጅ መዳን የእግዚአብሔርን ድርሻና የቅዱሳን ሰዎችና መላእክትን ድርሻ ባለመረዳት ወይም ሆነ ብሎ በማምታታት ብዙ ምዕመናንን ግራ እንደሚያጋቡ ይታወቃል፡፡ የቤተክርስቲያን መሰረታዊ ትምህርት ግልጽ ነው፡፡ በአጸደ ሥጋ ያሉ ክርስቲያኖች ጸሎትና ትምህርት፣ በአጸደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን ምልጃ፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት በቅዱሳት መጻሕፍት በተገለጠችው የቀናች ሃይማኖትና ደገኛ ምግባር እንድንጸና የሚረዳን በቤተክርስቲያን በኩልም ወደ ሕይወት ባለቤት እግዚአብሔር የሚያቀርበን አጋዥ እንጅ መሠረተ እምነትን የሚተካ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት፣ ከእግዚአብሔር ቸርነት የተለየ ሌላ መንገድ አይደለም፡፡

ቤተክርስቲያን (እያንዳንዱ ምዕመን እንዲሁም ማኅበረ ምዕመናንን የሚወክሉ የቤተክርስቲያን አካላት) ያላስተማረችው፣ ወንጌልን ያላስረዳችው ሰው ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ሊያውቅ ይችላል? (ሮሜ 10፡14) ቅዱሳን ሰዎች በቃልኪዳናቸው ያልረዱት፣ ቅዱሳን መላእክት በጥበቃቸው ከሰይጣን ፈተና፣ ከኃጢአት  እስረኝነት ተላቆ መንፈሳዊ ፍሬን አፍርቶ በሕይወቱ ጌታን እንዲያስደስት ያላገዙት ሰው እንዴት ትምህርተ ወንጌልን ሊፈጽማት ይችላል? (መዝ. 105፡23፣ ሉቃ. 13፡6-9) የቤተክርስቲያን ጥረት፣ የቅዱሳን ጸሎት፣ የመላእክት ርዳታ ከእግዚአብሔር ቸርነት የተለየ የሚመስለው ሰውስ በእውነት መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ሊረዳ ይችላል? እነዚህን ጥያቄያዊ ማብራሪያዎች የበለጠ ለመረዳት ሁለት ማነጻጸሪያ ታሪኮችን በምሳሌነት እናንሳ፡፡

ምሳሌ 1: የእስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ ወደ ከነአን ጉዞ

በኦሪት ዘፀዓት እንደተመዘገበው እግዚአብሔር አምላካችን በስሙ ያመኑትን፣ በምግባራቸው ያስደሰቱትን ሰዎች ከእስራኤል ዘሥጋ መካከል ለይቶ ከግብጽ ወደ ከነአን አሻግሯቸዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ የእስራኤል ዘሥጋ ታሪክ የሚነግረን ምድራዊ የታሪክ ሽኩቻዎች ዋና ዓላማዎቹ ስለሆኑ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ (በ1ኛ ቆሮ 10፡1-13) መልእክቱ እንዳስተማረን እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ ወደ ከነአን ያደረጉት ምድራዊ ጉዞ እኛ ከምድር ወደ መንግስተ እግዚአብሔር የምናደርገው መንፈሳዊ ጉዞ ምሳሌ ስለነበረ ነው፡፡ በእስራኤል ጉዞ ከተደረጉት ድንቅ ተዓምራት አንዱ ያስቸግራቸው የነበረ ፈርኦን ሰራዊትን በባህረ ኤርትራ አስጥሞ እነርሱን በደረቅ ያሻገራቸው የእግዚአብሔር የቸርነት ስራ ነው፡፡

ይህን ታሪክ “መዳንም በሌላ በማንም የለም” ከሚለው ንባብ ጋር በተነጻጻሪ መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ እግዚአብሔር ምንም ቸር ቢሆንም የነጻነት አምላክ ነውና ማንንም በማስገደድ ከነጻ ፈቃዱ ውጭ አያድነውም፡፡ በባህረ ኤርትራ በተደረገው ተዓምር እያንዳንዱ እስራኤላዊ፣ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴና ሌሎች እስራኤልን ይመሩ የነበሩ ሰዎች፣ በደመና ይመራቸው የነበረ የእግዚአብሔር መልአክ (ቅዱስ ሚካኤል)፣ የሙሴ በትር የየራሳቸው ድርሻ ነበራቸው፡፡ የማናቸውም ድርሻ ግን ከእግዚአብሔር ቸርነት ጋር የሚጋጭ ወይም የሚወዳደር አልነበረም፡፡ የእያንዳንዳቸው ጥረት ፈቃደ እግዚአብሔር እንዲፈጸም በማድረጉ ሁሉም በየድርሻቸው ይመሰገናሉ፡፡ የሙሴ በትር ከሌሎች በትሮች የተለየችው ለዚያ ነው፡፡ ባሕረ ኤርትራን ተሻግረው ምድረ ርስት የደረሱት እስራኤል በመንገድ ከተቀሰፉት የተለዩትና የተመሰገኑት ለዚያ ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ፣ ኢያሱና ካሌብ እስከ አሁን ድረስ ለቀናች አገልግሎታቸው የሚመሰገኑት ለዚህ ነው፡፡ በወቅቱ በአካለ ሥጋ ያልነበሩት፣ በጸሎታቸው በቃልኪዳናቸው እስራኤል እንዲሻገሩ የረዱ ቀደምት አበው (ለምሳሌ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ) በተለየ ሁኔታ የሚመሰገኑት ለዚህ ነው፡፡ እስራኤልን ቀን በደመና፣ ሌሊት በብርሃን እየመራ የድኅነት ምሳሌ ወደሆነች ከነአን ያደረሳቸው የእግዚአብሔር  መልአክ መጋቤ ብሉይ ቅዱስ ሚካኤልም በእስራኤል ረዳትነቱ በልዩ ሁኔታ የሚመሰገነው ለዚህ ነው፡፡ (ዘፀ. 23፡20-23)

እነዚህ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደየድርሻቸው ተለይተው ተወስተዋል፣ ተመስግነዋል፡፡ ነገር ግን የአንዳቸውም ድርሻ ከእግዚአብሔር ማዳን ጋር እንደማይጋጭ ይልቁንም የእግዚአብሔር የማዳን ስራ መገለጫዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት  “እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፣ ቤትን የሚሠሩ በከንቱ ይደክማሉ፤ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፣ የሚጠብቁ በከንቱ ይተጋሉ” (መዝ. 126፡1) እንዳለ የእግዚአብሔር ቸርነትና የሰው ልጆች ጥረት እርስ በርስ የሚፎካከሩ ሳይሆኑ የሚመጋገቡ፣ የተያያዙ መሆናቸውን መረዳት ይገባል፡፡ አንተ የዋህ ቤትን የሚሰራው፣ ከተማን የሚጠብቀው እግዚአብሔር እንደሆነ ታምናለህ? በዚህ እምነት የተነሳ ግን  ያለ እግዚአብሔር ቤትን መስራት፣ ከተማን መጠበቅ አይቻልም ብለህ እጅህን አጣጥፈህ ትቀመጣለህ? የሚሰሩትንስ “አትድከሙ ቤትን የሚሰራው፣ ከተማን የሚጠብቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው” ትላለህ? እርግጠኛ ነኝ ቢያንስ ለሆድህና ለኑሮህ ስትል እንደዚያ አትልም፡፡ ታዲያ በተመሳሳይ አመክንዮ ሰይጣን ከጽድቅ መንገድ ሊያወጣህ “መዳንም በሌላ በማንም የለም” የሚለውን ያለቦታው ያለትርጉሙ እየጠቀሰ ሲያታልልህ ለምን ትወናበዳለህ? የሰው ድርሻ ሌላ፣ የመላእክት ድርሻ ሌላ፣ የሌሎች ፍጥረታት ድርሻ ሌላ፣ እግዚአብሔር ድርሻ ሌላ መሆኑን እንዳትረዳ “ብቻ፣ ብቻ፣ ብቻ” በሚል ሰይጣናዊ ማዘናጊያ አዚም ያደረገብህ ማን ነው?

ምሳሌ 2: በወይኑ ቦታ የተተከለችው በለስ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በነገረ ድህነት የቅዱሳን መላእክትን ድርሻ በምሳሌ ካስረዳባቸው ትምህርቶች አንዱ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 13፡6-9 የተመዘገበው ምሳሌአዊ ታሪክ ነው፡፡ ከታሪኩ እንደምንረዳው አንድ ሰው በወይኑ ቦታ የተተከለች በለስ ነበረችው፡፡ ከበለሷም ፍሬ ፈልጎ በተደጋጋሚ (ሦስት ጊዜ) ቢመጣም ፍሬ ሊያገኝባት አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ የወይኑን ጠባቂ ጠርቶ ፍሬ ያላገኘባትን በለስ እንዲቆርጣት አዘዘው፡፡ የበለሷ ጠባቂ ግን “አቤቱ አፈር ቆፍሬ በሥሯ እስከ አስታቅፋት፣ ፍግም እስካፈስባት ድረስ የዘንድሮን እንኳ ተዋት፡፡ ምናልባትም ለከርሞ ታፈራ እንደ ሆነ፣ ያለዚያ ግን እንቆርጣታለን፡፡” በማለት ስለ በለሷ አዝኖ ተሟገተላት፡፡

የወይን ባለቤት የተባለ አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ወይን የተባልን በስሙ አምነን ፍሬ (በጎ ምግባር) ማፍራት እንዳለብን የታዘዝን ምዕመናን ነን፡፡ (ኢሳ. 5፡1፡19) የወይን ጠባቂ የተባለው እያንዳንዱን ምዕመን ከሚጠብቁ ቅዱሳን መላእክት አንዱ ነው፡፡ (ማቴ. 18፡10፣ ራዕይ. 4፡1-11) ቅዱሳን መላእክት በቀናች ሃይማኖት ጸንተን፣ በበጎ ምግባራት ፍሬ አፍርተን መዳን የሚገኝበትን ሕይወት እንድንይዝ ይረዱናልና፡፡ (ዕብ. 1፡14) በበለሷ ምሳሌ ለበለሷ መዳን የበለሷ ድርሻ እንክብካቤውን ተጠቅማ የሚጠበቅባትን ፍሬ ማፍራት ነው፡፡ የመልአኩ ድርሻ በለሷን በሚያስፈልጋት ሁሉ እየረዳ ፍሬ እንድታፈራ ማድረግ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ድርሻ በለሷ ፍሬ እንድታፈራ መልአኩን እየላከ፣ ተፈጥሮን እየገሰፀ ኃይል ብርታት መሆን ነው፡፡ የበለሷ ፍሬ ማፍራት የመዳን ምሳሌ ነው፡፡ አንተ የዋህ አንተ በለሷን ስትሆን  “መዳንም በሌላ በማንም የለም” የሚለውን ቅዱስ ቃል እንደሰይጣን ያለቦታው፣ ያለትርጉሙ እየጠቀስክ እግዚአብሔር የሾመልህን ቅዱሳን መላእክት የምታቃልል፣ ለመዳንህ ያላቸውን ድርሻ የምታጥላላ ከማን ተምረኸው ነው?

ማጠቃለያ

የጸጋ ሁሉ ምንጭ አምላካችን እግዚአብሔር የማዳን ስራውን በቅዱሳን ሰዎችና መላእክት አማካኝነት ይገልጣል፡፡ በስሙ አምነን ህይወትን የምናገኝበት አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማዳን የባህርይ ገንዘቡ እንጅ ከማንም የተቀበለው አይደለም፡፡ በአንጻሩ ቅዱሳን ሰዎችና መላእክት ከጌታ በተቀበሉት ጸጋ ሰዎችን ከደዌ ስጋ ያድናሉ ወደዘላለማዊ ሕይወት በሚደረገው የመዳን ጉዞም በትምህርታቸው፣ በተዓምራታቸው፣ በጥበቃቸው፣ በአማላጅነታቸው እያገዙ በክርስቶስ ቤዛነት ያመኑ ሰዎችን ይረዳሉ፡፡ ለምሳሌ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፣ ያድናቸውማል” (መዝ. 33፡7) ማለቱ ለቅዱሳን የተሰጠውን የማዳን ጸጋ ያስረዳናል፡፡ በአጸደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን ሰዎች፣ ሰዎችን ወደ ጽድቅ መንገድ የሚመሩ ቅዱሳን መላእክት እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው በመዳን ጉዞ ያላቸውን ሱታፌ ከማይነጻጸረው የእግዚአብሔር ማዳን ጋር ማምታታት አይገባም፡፡ “መዳንም በሌላ በማንም የለም” የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል ያለ አውዱ እየጠቀሱ ለዘላለም ሕይወት ለመብቃት በምናደርገው ጉዞ የእያንዳንዱን ምዕመን እምነትና ምግባር፣ በአጸደ ስጋም ሆነ በአጸደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳንን ጸሎትና አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክትን ረዳትነት ከኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ጋር ተነጻጻሪ ወይም ተፎካካሪ አስመስለው የሚያቀርቡ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ሳይረዱ አለማወቃቸውን በጩኸት ብዛት ለመሸፈን የሚሞክሩ ደካሞች ናቸው፡፡

እነዚህን ሰዎች ስናይ ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ጆርጅ ኦርዌል የተባለ ደራሲ “የእንስሳት እድር” (Animal Farm) በተባለ ድርሰቱ በሞኝነትና አላዋቂነት ገጸባሕርይ የጠቀሳቸው  በጎች ሊታወሱን ይችላሉ፡፡ በድርሰቱ የተጠቀሱት በጎች አንድ አስቂኝ ጠባይ ነበራቸው፡፡ በጎቹ ያሰባሰቧቸውን ሕግጋት በሙሉ የመረዳት አቅም የላቸውም፡፡ እነርሱ የሚያውቁት አለቆቻቸው የሆኑት አሳማዎች በተንኮል ቀባብተው የሚሰጧቸውን ነገር ሁሉ ያለመገምገም እየተቀበሉ ጉሮሮአቸው እስኪንቃቃ ድረስ “Four legs good; two legs bad” (አራት እግር ጥሩ ነው፤ ሁለት እግር መጥፎ ነው) እያሉ መጮህና ልሂቃኑ ከፍ ያለ መረዳት የሚጠይቀውን ትምህርት እንዳያስተምሩ፣ ሌሎችም እንዳይረዱ መረበሽ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን የምታስተምረውን የነገረ ድኅነት ምስጢር የማይረዱ ደካሞችም የማያውቁትን ይቃወማሉ፤ ደርዝ በሌለው የአላዋቂነት ድፍረታቸውም ራሳቸው ክደው ሌሎችን ያስክዳሉ፣ የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብና ትርጉም ያጣምማሉ፡፡ የቅዱሳን አምላክ፣ የሰራዊት (ቅዱሳን መላእክት) ጌታ አምላካችን እግዚአብሔር ከሰይጣን ማታለል፣ ከመናፍቃን ክህደት ተጠብቀን በቀናች ሃይማኖት በበጎ ምግባር ጸንተን እንድንኖር ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

“መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰው የተሰጠ ሌላ ስም ከቶ የለምና”

ስብሃት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር፡፡ አሜን፡፡

ደብረ ምሥጢራት ታቦር

Debretabor2.1

በዲያቆን ሙሉነህ ጌቴ

መግቢያ

በታቦርሂ አመ ቀነጸ መለኮትከ ፈረስ፤ ኢክህሉ ስሒቦቶ ሙሴ ወኤልያስ፡፡ የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ ቄሰ ገበዝ ሐዲስ ኪዳናት እና ልጃቸው የቅኔዋ ንግሥት እሙሐይ ገላነሽ ሐዲስ በደብረ ጽላሎ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ለደብረ ታቦር በዓል የተቀኙት የመወደስ ቅኔ ሲሆን “ለዓለም” በመባል ከሚጠራው የአንድ መወድስ ቅኔ ክፍል ውስጥ አንደኛውና ኹለተኛው ቤት ቅኔ ነው፡፡ ቄሰ ገበዝ ሐዲስ ኪዳናት በቅኔ ማኅሌት ሆነው “በታቦርሂ” ብለው ቤቱን ሲጨርሱ በምቅዋመ አንስት (በሴቶች መቆሚያ) ያለችው በቅኔ የሰከረችው ሕጻኒቱ ልጃቸው ገላነሽ “ኢክህሉ ስሒቦቶ ሙሴ ወኤልያስ” ብላ ቅኔውን ከአባቷ ነጥቃ (ዘርፋ) ተቀኘች፡፡ የቅኔው ትርጉምም በደብረ ታቦር ተራራ የመለኮትህ መገለጥ ፈረስ በዘለለ ጊዜ ሙሴና ኤልያስ ሊገቱት አልቻሉም ማለት ሲሆን ምሥጢሩም ሙሴና ኤልያስ ታቦር ተብሎ በሚጠራው ተራራ የተገለጠውን ግርማ መለኮትህን ማየት ተሳናቸው ማለት ነው፡፡ ይኸውም መለኮት ብርሃኑን ብልጭ ባደረገ ጊዜ ፍጡሩ ዐይን ግርማ መለኮትን የማየት አቅም ስለተሳነው ሙሴ “ይኄይሰኒ መቃብርየ/መቃብሬ ይሻለኛል/” ብሎ ወደ መቃብሩ ኤልያስም በሠረገላው ወደ መኖሪያው /ወደ ተሰወረበት ቦታ ማለትም ብሔረ ሕያዋን/ ተመልሰዋል፡፡

ታቦር የተራራ ስም ሲሆን ከገሊላ ባሕር በምዕራባዊ ደቡብ በኩል 10 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቆ በመገኘት 572 ሜትር ከባሕር ጠለል (ወለል) ከፍ ይላል፡፡ በዚህ ተራራም ባርቅ ሲሳራን አሸንፎበታል፤ ጌታችንና አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው በሚያስተምርበት ወቅት ምሥጢረ መንግሥቱን እና ብርሃነ መለኮቱን ለነቢያት እና ለሐዋርያት ገልጦበታል፡፡ በመሆኑም ይህ ተራራ የምሥጢራት ተራራ ተብሎ ይጠራል፡፡ ከባሕረ ዮርዳኖስ ቀጥሎ ምሥጢረ መለኮት የተገለጠበት ዐምደ ምሥጢራት የሆነ ተራራ ነው፡፡ ስለዚህ የምሥጢራት መገለጫ ኾኖ ያገለገለ ተራራም ነቢያት ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ልበ አምላክ ዳዊት “ደብረ እግዚአብሔር ደብር ጥሉል፤ደብር ርጉዕ ወደብር ጥሉል/የእግዚአብሔር ተራራ (ታቦር) የለመለመ /በምሥጢር/ ነው፤የረጋና የለመለመ /በምሥጢራት መገለጫነት/ ነው”፡፡ በሌላም ቦታ “ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌስሑ፤ወይሴብሑ ለስምከ/ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል፤ስምህንም ያመሰግናሉ” ይላል፡፡ /መዝ 88፣12/

ከአራቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ የኾነው ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም “ኑ ወደ እግዚአብሔር ተራራ/ታቦር/ ፣ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፤ በጎዳናውም እንሄዳለን፡፡” /ኢሳ 2፣3/ ከላይ የተጠቀሱት ነቢያት አበው የታቦርን ተራራ “የእግዚአብሔር ተራራ” /ምሥጢራተ እግዚአብሔር የተገለጠበት/ በማለት ሲጠሩት ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ “ቅዱሱ ተራራ” ሲል ይጠራዋል፡፡  2ጴጥ1÷18  ደብረ ታቦር የሚለው ቃል የተራራውም ኾነ የብርሃነ መለኮት መገለጥ በዓል መጠሪያ ኾኖ ያገለግላል፡፡ በተራራነቱ የታቦር ተራራ ወይም ታቦር የተባለ ተራራ ተብሎ ሲተረጎም በበዓልነቱ ሲጠራ ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮት የተገለጠበት ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዐበይት/ታላላቅ/ በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡ በዚህች አጭር የአስተምህሮ ጦማር የደብረ ታቦርን በዓል የአከባበር ታሪካዊ አመጣጥና ባሕላዊ አከባበር ሳይኾን በቅዱሱ ተራራ የተገለጡትን ትምህርታተ እግዚአብሔር መጠነኛ ዳሰሳ እናደርጋለን፡፡

ትምህርተ እግዚአብሔር (Apophatic Theology)

ወተወለጠ ራእዩ በቅድሜሆሙ ወአብርሀ ገጹ ከመ ፀሐይ ወአልባሲሁኒ ኮነ ጸዐዳ ከመ ብርሃን /መልኩም በፊታቸው ተለወጠ ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ኾነ (ሜቴ 17÷2)፡፡” በደብረ ታቦር በጉልህ ከተቀመጡት ምሥጢራት አንዱ የእግዚአብሔር አይገለጤነት ትምህርተ መለኮት (Apophatic Theology) ነው፡፡ ቅዱሳን አበው በእግዚአብሔር የባሕርይ ግብራት ጋር በሚያደርጉት ተዋሕዶ እግዚአብሔርን በተምሳሌት ይገልጡታል፡፡ ምክንያቱም ፍጡሩ አንደበታችን እና ቋንቋችን የተገደበው በተፈጠሩ ነገሮች ላይ ብቻ ነው፡፡ ንግግራችን ከጊዜ እና ከቦታ ውጭ አልፎ መናገር እና መግለጽ ፈጽሞ አይችልም፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ከጊዜና ከቦታ ውጪ ነው፡፡ ዘላለማዊውንና መጠንና ወሰን የሌለውን እግዚአብሔርን በጊዜ የተፈጠረውና በተፈጠረው ዓለም የተወሰነው ሰውና ቋንቋው የነጥብና የፍንጭ ያክል ካልሆነ በስተቀር አከናውኖ ሊጠራውና ሊገልጸው ፈጽሞ አይቻለውም፡፡ እግዚአብሔር እኛ ስለ እሱ /እግዚአብሔር/ ከምንናገረውና ከምናስበው ማንኛውም ነገር በማይነጻጸር ሁኔታ ይበልጣል፡፡ ስለዚህ ስለ እግዚአብሔር የምንናገረው ትምህርተ መለኮታችን በአብዛኛው ስዕላዊ እና ተምሳሌታዊ ነው፡፡ ይህ ስዕላዊና ተምሳሌታዊ አገላለጽም ቢሆን እግዚአብሔርን የፍንጭ ወይም የነጥብ ካልኾነ በቀር ሊገልጸው አይችልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እና ቅዱሳን አበው እግዚአብሔርን  ከሚገልጡባቸው ስዕላዊና ተምሳሌታዊ መግለጫዎች መካከል ጨለማና ብርሃን ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ብርሃን ነው ወይም ጨለማ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ ኹለቱም እግዚአብሔርን እንደየአቅማቸው ለማስረዳት ይሞክራሉ እንጂ አንዳቸውም እግዚአብሔርን ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር ብርሃን ነው ሲባል ብርሃን መገለጫው ነው ማለት እንጂ ገልብጠን ብርሃን እግዚአብሔር ነው ብንል የሚያስኬድ አይደለም፡፡

ጨለማ፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ጨለማ የሚለውን ቃል የእግዚአብሔርን አይደረሴነት ለመግለጥ ተጠቅሞበታል፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በሲና በረሃ ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር በተዘጋጀ ጊዜ እግዚአብሔር ወዳለበት ጨለማ እንደገባ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ያስረዳናል ‹‹ሕዝቡም ርቀው ቆሙ፤ ሙሴም እግዚአብሔር ወዳለበት ጨለማው ቀረበ›› (ዘጸ 20÷21)፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊትም ‹‹ወረሰየ ጽልመተ ምስዋሮ /መሰወሪያውን  ጨለማ አደረገ›› (መዝ. 17፡11) በማለት የሊቀ ነቢያት ሙሴን ኀይለ ቃል ያጸናዋል፡፡ ኹለቱም በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው የተናገሩት አበው ነቢያት እግዚአብሔር ጨለማ ሳይሆን በጨለማ እንደሚያድር ያረጋግጡልናል፡፡ በጨለማ ያድራል መባሉም አእምሮዋት/ኅሊናት ተመራምረው ሊደርሱበት የማይችሉ ምጡቀ ልቡና፣ረቂቀ ኅሊና መሆኑን ያመለክታል፡፡ ጨለማነቱም ያለው በእግዚአብሔር ዘንድ ሳይሆን በእኛ አእምሮ ውስጥ ነው፡፡ ለምሳሌ የፀሐይን ብርሃን ማየት የተሳነው ዐይነ ስውር ሰው ጨለማው ያለው ከእሱ ነው እንጂ ከፀሐይ እንዳልሆነ ኹሉ ጨለማነቱ ያለው በእግዚአብሔር ዘንድ ሳይሆን በእኛ ውስጥ ነው፡፡ በነቢዩ ሙሴና በልበ አምላክ ክቡር ዳዊት ጎራ ሆነው እግዚአብሔርን በተምሳሌታዊ አገላለጥ ከሚገልጡት ቅዱሳን አበው መካከል ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ አንዱ ነው፡፡

ብርሃን፡ ይህን መንገድ ተከትለው ስለ እግዚአብሔር አይደረሴነት ከሚያስተምሩት ቅዱሳን አበው መካከል ቅ/ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት ይገኝበታል፡፡ እግዚአብሔርን ብርሃን በሚለው ቋንቋ ለመግለጥ መሠረቱ ነባቤ መለኮት ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ጨለማም በእርሱ ዘንድ ጥቂትስ እንኳን የለም›› (1ኛ ዮሐ 1÷5)፡፡ እግዚአብሔር ብርሃን እንደሆነ በይበልጥ የተገለጠው ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ባደረገው ብርሃናዊ አስተርእዮ ነው፡፡ ስለዚህ ብርሃናዊ አስተርእዮ ከጻፉት ሦስቱ ወንጌላውያን አንዱ የሆነው ቅዱስ ማቴዎስ “ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ ፤ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ” በማለት የእግዚአብሔርን ብርሃናዊነት ገልጧል (ማቴ 17÷2)፡፡ ይህ እግዚአብሔርን በብርሃን ወክሎ መግለጥ በብዙ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የሚዘወተር ሲሆን የሊቃውንት ቅዱሳን ፈጣሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነስቶ እስከሚያርግበት ጊዜ ባሉት አርባ ቀናት ውስጥ ካስተማረውና ኪዳን ተብሎ ከሚጠራው ትምህርት ውስጥ “እግዚአብሔር ዘብርሃናት” በሚባለው የጸሎት ክፍል ውስጥ ይህ አገላለጥ ጎልቶ ይታያል፡፡ “ዘመንጦላዕቱ ብርሃን ወቅድመ ገጹ እሳት ወመንበረ ስብሐቲሁ ዘኢይተረጐም ወምዕራፈ ተድላሁ ዘኢይትነገር ዘአስተዳለወ ለቅዱሳን ወበመልበስቱ መዛግብተ ብርሃን / መጋረጃው ብርሃን፣ በፊቱ እሳት የሚቦገቦግ፣ የጌትነቱ መንበር የማይተረጎም፣ ለቅዱሳን ያዘጋጀው የደስታ ማረፊያ የማይነገር፣ መጎናጸፊያው የብርሃን መጎናጸፊያ የሆነ እግዚአብሔር ….”፡፡

ኪዳን በተባለው መጽሐፍም “ፀሐይ ዘኢየዐርብ ወማኅቶት ዘኢይጠፍእ ፀሐይ ዘዘልፈ ያበርህ ዲበ ቅዱሳን/የማይጠልቅ ፀሐይ፣ የማይጠፋ ብርሃን፣ በቅዱሳን ላይ ዘወትር የሚያበራ ፀሐይ” ሲል እግዚአብሔርን ተምሳሌታዊ በሆነ አገላለፅ ይገልጠዋል፡፡ በደብረ ታቦር /በምሥጢሩ ተራራ/ የታየው ብርሃን ግን በዕለተ እሑድ የተፈጠረ ብርሃን አይደለም፡፡ ይህ ብርሃን መለኮታዊ ብርሃን፣ ያልተፈጠረና ለሌሎች ብርሃናት ምንጭ የሆነ ብርሃን ነው፡፡ ይህ ብርሃን ኖኅና ሙሴ ሲወለዱ እንደከበባቸው፣ ሙሴ ከ40 ቀን የደብረ ሲና ቆይታ በኋላ  ኹለቱን ጽላት ተቀብሎ ሲመጣ እስራኤላውያን በሙሴ ላይ ያለውን ብርሃን ማየት ተስኗቸው ‹‹ሙሴ ተገልበብ ለነ/ ሙሴ ሆይ የፊትህን ብርሃን ማየት ተስኖናልና ፊትህን ተሸፈንልን” (ዘፀ. 34፡29-30) እንዳሉት ቅዱሳን ሲበቁ እንደሚጎናጸፉት ያለ ብርሃን አይደለም:: ይህ ብርሃን መለኮታዊ በመሆኑና ሌላ መግለጫ ቃል በመጥፋቱ ብርሃን በሚለው ተምሳሌት ተጠራ እንጂ ከብርሃን በላይ የሆነ ነው፡፡ የሰው ዐይን ፍጡሩን ብርሃን እንጂ ያልተፈጠረውን ብርሃን መመልከት አይችልም፡፡ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የተሟሸ ዐይን መለኮታዊውን ብርሃን በመለኮትነቱ ልክ ማየት ፈጽሞ የማይቻል ቢሆንም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የተወሰነለትን ያህል መመልከት መቻሉን በደብረ ታቦር አየን፡፡

“ወእም ከመ ጥቀ ታሤንዩ ግብረ ወትኔጽርዎ ይከውን ለክሙ ከመ ማኅቶት እንተ ታበርህ ውስተ መካነ ጽልመት እስከ ታበርህ ለክሙ ዕለት ወይሠርቅ ለክሙ ቤዝ ውስተ ልብክሙ ዘያበርህ / በአንብቦ መጻሕፍት ጽሙዳን ብትሆኑ ፀሐይ እስኪያበራላችሁ ድረስ ያጥቢያ ኮከብ እስኪወጣላችሁ/ አእምሮ መንፈሳዊ በልቡናችሁ እስኪሳልባችሁ/ ድረስ በጨለማ ቦታ እንደሚያበራ ፋና ይሆንላችኋል” (2ጴጥ 1÷19) ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ አገላለጹ ከሰው የሚገኘውን ዕውቀት በፋና፣ ከእግዚአብሔር የሚገኘውን ዕውቀት ደግሞ በፀሐይ መስሎ ተናግሯል፡፡ ‹‹ሃይማኖት እንተ ትጠረይ እም ተምህሮ ኢታግዕዞ ለሰብእ እምኑፋቄ ወእምትሕዝብት / ከመማር የምትገኝ ሃይማኖት ሰውን ከጥርጣሬ ነጻ አታወጣውም›› እንዳለ መጸሐፍ በምርምርና በአስተውሎት /Knowledge of Empiricism and Reason/ ከሚገኝ የዕውቀት ብርሃን ይልቅ እግዚአብሔር በልባችን የሚያትምልን የዕውቀት ብርሃን /Knowledge of Revelation/  እንደ ፀሐይ ያበራል፡፡ (መዝ118÷105)፤2ቆሮ 4÷6)፡፡ ይህ እግዚአብሔር ጸጋውን አሳድሮ ዐይነ ሥጋችንንና ዐይነ ልቡናችንን የሚያበራው ብርሃን ያልተፈጠረውን መለኮታዊውን ብርሃን ለማየት ያስችላል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ኹለንተናቸው የበራላቸው ኹለቱ ነቢያት አበው /ሙሴና ኤልያስ/ እና ሦስቱ የምሥጢር ሐዋርያት /ቅ/ጴጥሮስ፣ቅ/ዮሐንስና ቅ/ያዕቆብ/ መለኮታዊውን ብርሃን እንደ ዐቅማቸው ለማየት ደረሱ፡፡

ወንጌላውያኑ መለኮታዊውን ብርሃን የሚገልጡበት ነገር ቢያጡ በተፈጠረው ብርሃን መስለው ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ ብለው ተናገሩ፡፡ ቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት የተገለጠውን መለኮታዊ ብርሃን አይቶ መቋቋም የሚችል ዐይን ስላልነበራቸው “ወወድቁ በገጾሙ ዲበ ምድር /በግንባራቸው ወደ ምድር ወደቁ፡፡” ይህን አይደረሴ መለኮታዊ ብርሃን የትምህርተ መለኮት ሊቃውንት ከጨለማ ጋር አብረው በማጣመር “Dazzling Darkness, Radiance of Divine Darkness, Blinding Light” ብለው ይጠሩታል፡፡ ከዚህ የማይገለጥ አንጸባራቂ መለኮታዊ ብርሃን የተነሳ ቅዱስ ጴጥሮስ የሚናገረው ነገር እንዳጣ፣ያየውንም ነገር መሰየሚያ ቃል እንዳጣ፡ “ወኢየአምር ዘይብል / የሚለውን /የሚናገረውን አያውቅም/” በማለት ኹለቱ ወንጌላውያን አስቀምጠውታል (ማር 9÷6 ፤ሉቃ 9÷33)፡፡ ለዚህ ብርሃነ መለኮት መገለጥና በተገለጠው ብርሃነ መለኮት ፊት ለመቆም አለመቻልን ነበር ባለ ቅኔው ሐዲስ ኪዳናትና ልጃቸው እሙሐይ ገላነሽ ሙሴና ኤልያስ መለኮት ፈረስን መግታት ተሳናቸው ያሉት፡፡

በደብረ ታቦር የተገለጠው ብርሃን ያልተፈጠረ መለኮታዊ ብርሃን ነው፡፡ ፍጡሩን ብርሃንና መለኮታዊውን ብርሃን ስም እንጅ ግብርና ባሕርይ ፈጽሞ አያገናኛቸውም፡፡ መለኮታዊው ብርሃን ዘላለማዊ ብርሃን ነው፡፡ “ብርሃን ዘእምቅድም / ቅድመ ዓለም የነበረ ብርሃን /ባሕርይ/” እንዲል  (መጽሐፈ ኪዳን)፡፡ ፍጡሩን፣ ለሰው ልጆች በሥጦታ /በጸጋ/ የሚታደለውን ብርሃን ደግሞ መጻሕፍት በተለያየ አገላለጽ ይገልጡታል፡፡ “አምላከ ብርሃን፣ ወሀቤ ብርሃን / ረቂቁን ብርሃን የሰጠ፣ ግዙፉን ብርሃን የፈጠረ” በማለት ግዙፋኑ ብርሃናት ፀሐይ፣ጨረቃ፣ከዋክብትና ከእነርሱ የሚመነጨው ረቂቁ ብርሃን ለሰው ልጆች በሥጦታ የተበረከተ እንደሆነ መጻሕፍት ይገልጣሉ (መጽሐፈ ኪዳን)፡፡ ከዚህ ግዙፍ ብርሃን ባሻገር ግን በተጋድሎ ብዛት ቅዱሳን የሚታደሉት ረቂቅ ብረሃን አለ፡፡ ይህን ብርሃን “ብርሃን ዘኢይትረከብ / ያለ በጎ ሥራ የማይገኝ ብርሃን” ሲል ይገልጠዋል (መጽ.ኪዳን)፡፡

የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ለማየት የሚያደርሰውን ብርሃን ለማግኘት ተስፋ አድርጎ ይኖራል፡፡ ይህን አስመልክቶ “ወብርሃነ ለነ ዘኢይጠፍእ አሰፎከነ / የማይጠፋ ብርሃንን ለእኛ ተስፋ አስደረግከን” (መጽሐፈ ኪዳን)፡፡ ይህ ብርሃን ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለመላእክትም ጭምር በጥንተ ተፈጥሮ ዕውቀት ሆኗቸው መለኮታዊውን ብርሃን እንዲረዱ አድርጓቸዋል፡፡ “ዝንቱ ብርሃን ኮኖሙ ጥበበ ወአእምሮ” እንዲል መጽሐፍ፡፡ ይህን ፍጡር ብርሃን ዕውቀት አድርገው መላእክት መለኮታዊውን ብርሃን እንደጎበኙት መጽሐፈ ኪዳን “ዘያፈትዎሙ ለመላእክት የሐውጽዎ ለዘእምቅድመ ዓለም ብርሃን / ዓለም ሳይፈጠር የነበረውን ብርሃን ያዩት ዘንድ መላእክትን ደስ የሚያሰኛቸው” በማለት ያስረዳል፡፡

ትምህርተ ሥላሴ /Doctrine of Holy Trinity/

በምሥጢራዊው ቅዱስ ተራራ በታቦር ከምናገኛቸው መሠረታዊ ትምህርቶች መካከል ትምህርተ ሥላሴ ዋነኛው ነው፡፡ የምሥጢሩ ተራራ ታቦር በእግዚአብሔር አይገለጤነት ትምህርተ እግዚአብሔር (Apophatic Theolgy) ጀምሮ የእግዚአብሔርን የባሕርይ አንድነትና የባሕርዩ ግርማ መገለጫ ከሆኑት መካከል ብርሃን አንዱ መሆኑን ካስረዳ በኋላ ይህ በባሕርይ አንድ የሆነ እግዚአብሔር አካል ስንት እንደሆነ ወደ ማመላከት ያመራል፡፡ ይህ ትምህርት ወደ ጥልቁና አይመረመሬው ትምህርተ ሥላሴ ይወስደናል፡፡ በደብረ ታቦር ጌታችንና አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮታዊ ግርማ የመገለጡ ዋነኛ ምክንያት በብሉይ ኪዳን ስለ እግዚአብሔር አንድ ገጽነት ይታመን የነበረውን የስህተት አስተምህሮ አርሞ እግዚአብሔር በአካል እና በገጽ ሦስት እንደሆነ ለምዕመናነ እግዚአብሔር በሰፊው ለማስረዳት ነው፡፡ ይህ የምሥጢረ ሥላሴ አስተምህሮ በብሉይ ኪዳን በስውር ሁኔታ በብዙ ስፍራዎች ላይ የተገለጠ ሲሆን በአዲስ ኪዳን ግን በአገላለጥ ብቻ ሳይሆን በእይታም በሚረዳ መልኩ ተገልጧል፡፡ ከእነዚህ አስተርእዮታት (መገለጦች) መካከል ከባሕረ ዮርዳኖስ ቀጥሎ ደብረ ታቦር አንዱ የምሥጢረ ሥላሴ የምሥጢር ቁልፍ ነው፡፡

በባሕረ ዮርዳኖስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲጠመቅ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት ባለመገለጥ ቁልፍ ተዘግቶ የኖረው ምሥጢረ ሥላሴ “ተርህወ ሰማይ/ ሰማይ ተከፈተ” በሚል አንቀጽ የመገለጡን ምስራች እንደ ሰማን ምሥጢረ ሥላሴ በአንድ መገለጥ የሚረዳ አይደለምና በታላቁ የምሥጢራት ተራራ  በደብረ ታቦር ይህ የሰማይ መከፈት ምሥጢር ተደገመ፡፡ በኹለቱ ታላላቅ የምሥጢር መካናት እግዚአብሔር አንድነት ሦስትነቱን በምንረዳው ልክና መጠን ገለጠልን፡፡ በታቦር ተራራ ብርሃነ መለኮቱ ለተገለጠ ለኢየሱስ ክርስቶስ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ወሎቱ ስምዕዎ / የምወደው ልጄ ይህ ነው እሱንም ስሙት” የሚል መለኮታዊ ቃል ከባሕርይ አባቱ ከአብ ዘንድ ተሰማ፡፡ እጅግ በጣም ታላቅና ድንቅ ድምፅ ነው! ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔ እና አብ አንድ ነን፤ እኔን ያየ አብን አየ፤ እግዲህ ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ እያጠመቃችኋቸው አሕዛብን ኹሉ አስተምሩ” (ዮሐ 10፣30፣ ዮሐ 14፣9፣ ማቴ 28፣19) እያለ ስለ እግዚአብሔር የባሕርይ አንድነትና የአካል ሦስትነት የሚያስተምራችሁን ትምህርተ እግዚአብሔር ስሙት፣ተቀበሉት፣እመኑበት በማለት እግዚአብሔር አብ የግርማው መገለጫ በሆነው በደመናው ውስጥ ሆኖ አዘዘን፡፡ በመሆኑም የታቦር ተራራ የምጢራት ኹሉ መሠረት የሆነው ምሥጢረ ሥላሴ ለኹለተኛ ጊዜ በጉልህ የተገለጠበት የምሥጢራተ መለኮት ዐደባባይ ነው፡፡

ትምህርተ ተዋሕዶ/አንድ አካል አንድ ባሕርይ/

በአንድ ብርሃነ መለኮት መገለጥ የሥላሴን የባሕርይ አንድነት፣አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ብሎ በመግለጥ የሥላሴን የአካል ሦስትነት ከተረዳን በኋላ የወልድን በተዋሕዶ ሰው መሆን የምንረዳበት ትምህርት በምሥጢሩ ተራራ በታቦር የተገለጠው ትምህርተ እግዚአብሔር ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስቱ የምሥጢር ሐዋርያት ጋር ወደ ረጅም ተራራ ወጥቷል፡፡ ከሐዋርያቱ ጋርም ቃል በቃል በአካል ተነጋግሯል፡፡ በእነዚህ ድርጊቶች የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም ሰውነት በፍጽምና እንረዳለን፡፡ ይህ ፍጹም ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን በመግለጥ ነቢያትንና ሐዋርያትን በግርማ መለኮቱ ፍጹም ማስፈራቱም፣ “ይህ የባሕርይ ልጄ ነው” የሚል መለኮታዊ ድምጽ ከአብ መሰማቱ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም አምላክነት በተገለጠ ሁኔታ ያስረዳል፡፡ አንዱ አካል በአንድ ጊዜ በተዋሕዶ ሰውም አምላክም መሆኑን በምሥጢሩ ተራራ በታቦር ተረድተናል፡፡ በአዳም ፍዳ መነሻነትና በግሉ በሚሰራው ኀጢአት ምክንያት የቀደመ የገዢነት፣ የተፈሪነት ክብርን አጥቶ በፍጥረታት ኹሉ ሲረገጥና ሲቀጠቀጥ  የኖረ ሥጋ /ባሕርየ ሰብእ/ በተዋሕዶ የመለኮት ገንዘብ ኹሉ ገንዘቡ ኾኖለት በመለኮታዊ ግርማው በቅዱሱ ተራራ የነበሩትን ቅዱሳን ፍጹም አስደነገጠ፤ በብርሃኑ ዓለምን አበራ፤ የአብ የባሕርይ ልጅ ለመባል በቃ፤ ሙታንን በሥልጣኑ ከያሉበት ማስነሳትና ከሕያዋን ጋር ማነጋገር ቻለ፤ጌታ፣ እግዚአብሔር፣አምላክ  ለመኾን በቃ፡፡ ረቂቁ መለኮትም ከሥጋ ጋር ባደረገው ፍጹም ተዋሕዶ የሥጋን ገንዘብ ኹሉ ገንዘቡ በማድረጉ ወደ ምሥጢሩ ተራራ ሲወጣ ታየ፤ ተዳሰሰ፤ ወጣ፤ ተለወጠ፤ ወዘተ የሚሉ ሰውኛ ግሶች ተነገሩለት፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት

ዓለም የተፈጠረው በእግዚአብሔር ቃል /ወልድ እንደሆነ የሚድነውና የሚጠፋው በእግዚአብሔር ቃል /ወልድ/ ነው፡፡ “ዘየአምን በወልድ ቦ ሕይወት ዘለዓለም / በወልድ ያመነ የዘላለም ሕይወት አለው” (1ኛ ዮሐ. 5፡12) እንዳለ ወንጌላዊው ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ነው ብለው ካላመኑ በስተቀር ድኅነት ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ አረጋዊው ስምዖን “እነሆ ይህ ሕጻን ከእስራኤል መካከል ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሳታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ይሆን ዘንድ የተሠየመ ነው” (ሉቃ 2÷34) እንዳለ ለዓለም ድኅነትም ሆነ ሞት ምክንያቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ዓለም ለምንፍቅናዋና ውድቀቷ መሠረት የምታደርገው የኢየሱስ ክርስቶስን እግዚአብሔርነት መካድ ነው፡፡ በምሥጢሩ ተራራ በታቦር ግን ለዓለም መውደቅና መነሳት ምልክት የኾነው የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትን ማመን ለዓለም በግልጥና በሚረዳ ቦታ፣በሚረዳ ቋንቋ ተገልጧል፡፡ “የምወደው ልጄ ይህ ነው” ከማለት በላይ ለኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት ሌላ ምስክርነት አያሻም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ አይደለም ብሎ መካድ እግዚአብሔር አብ የባሕርይ አምላክ አይደለም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ፍጡር ፍጡርን ፣ፈጣሪ ፈጣሪን በባሕርያቸው ይወልዳሉ እንጅ ፍጡር ከፈጣሪ በባሕርይ ሊወለድ አይቻለውም፡፡ ወይም ፈጣሪ ፍጡርን በባሕርይው ወለደ ማለት ለባሕርዩ አይስማማውም፡፡

በሌላ አገላለጽ የፍጡር የባሕርይ ልጅ ፍጡር፣ የፈጣሪ የባሕርይ ልጅ ፈጣሪ ነው፡፡ ታዲያ ራሱ አብ ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ ልጄ ነውና እሱ የሚላችሁን ኹሉ አምናችሁ ተቀበሉት ብሎ ካዘዘን፣ እንዲሁም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ “እምቅድመ ይትፈጠር አብርሃም ሀሎኩ አነ / አብርሃም ሳይፈጠር በቅድምና ነበርሁ” (ዮሐ. 8፡58) እያለ ዘላለማዊነቱን የሚነግረንን ኢየሱስ ክርስቶስን እግዚአብሔርነቱን አለመቀበልና በእግዚአብሔርነቱ አለማመን የአብን ቃል መካድና የአብንም እግዚአብሔርነት ፈጽሞ መካድ አይደለምን?! ሊቃውንት አባቶቻችን “ወልድ  ሲነካ አብ ይነካል” ብለው እንዳስቀመጡት በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት አለማመንና አለመታመን በኢየሱስ ክርስቶስ ተጠግቶ የእግዚአብሔር አብንም እግዚአብሔርነት ፍጹም መካድ ነው፡፡ ይህ ድርጊት ደግሞ ወደ እግዚአብሔር የለሽነት ጥልቅ አዘቅት የሚከት ወደር የለሽ ክህደት ነው፡፡ በምሥጢሩ ተራራ ግን የኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት በግልጥ ቀርቧል፡፡ ብርሃነ መለኮቱ ስለታየበት፣ምሥጢረ ሥላሴ ስለተገለጠበት፣የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ስለተነገረበት ከዓለም ተራራዎች ኹሉ ለይቶ ቅዱስ /ልዩ/ በማለት በሚጠራው በቅዱሱ ተራራ በታቦር ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ  በዐይኑ የተመለከተውን፣በልቡናው ያስተዋለውን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር እንዳገኘው እንዲህ በማለት መስክሮልናል፡፡

“እስመ ኢኮነ መሐድምተ ጥበብ ዘተሎነ ወአመርናክሙ ቦቱ ኀይሎ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወምጽአቶ ወሀልዎቶ…. /ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ዓለም መኖሩን፣አምጻኤ አለማትነቱን፣ በሥጋ መምጣቱን ስናስተምራችሁ የተከተልነው የፍልስፍና ተረት አይደለምና፣ የእርሱን ገናናነት እኛ ራሳችን አይተን ነው እንጅ ከገናናው ክብር ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው’ የሚል ያ ደምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ገንዘብ አድርጓልና፡፡ ይህንም ቃል እኛ በተቀደሰው ተራራ አብረነው ሳለን ከሰማይ እንደወረደለት ሰምተነዋል›› (2ጴጥ 1÷16-18)

ነገረ ቤተክርስቲያን

በምሥጢሩ ተራራ በታቦር ከተገለጡት ምሥጢራት ነገረ ቤተ ክርስቲያን ይገኝበታል፡፡ በደብረ ታቦር በሕይወተ ሥጋና በሕይወተ ነፍስ ያሉ ምእመናን በአንድ ላይ ተገኝተው ምሥጢረ መለኮትን ተመልክተዋል፡፡ አንዱ ለአንድ ሲጸልይ ተስተውለዋል፡፡ አንድነትን፣ አብሮ መኖርን ሲመኙ ታይተዋል፡፡ ይህ የቤተክርስቲያን ጠባይ ነው፡፡ በደብረ ታቦር የተገለጠው ምሥጢር ዛሬም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እየተገለጠ ይኖራል፡፡ ቤተክርስቲያን የኹለት ዓለማት ምእመናን አንድነት ናት፡፡ ምሥጢረ መለኮት የሚገለጥባት፣ አንዱ ለሌላው የሚኖርባት፣ አንዱ ለሌላው የሚጸልይባት፣ በዐፀደ ሥጋና በዐፀደ ነፍስ ያሉ ምእመናንና የመላእክት ተዋሕዶ /አንድነት/፣ የምሕረት ዐደባባይ ናት፡፡

ትምህርተ ትንሣኤ ምውታን

ነገረ ትንሣኤ ምውታን ከጥንት ጀምሮ ለብዙ ሰዎች የክህደታቸው መነሻ ሆኖ የቆየ ዐቢይ ምሥጢር ነው፡፡በክርስቶስ ዘመነ ሥጋዌ ወቅት ሰዱቃውያን የሚባሉ ቡድኖች ሰው ከሞተ በኋላ ነፍሱና ሥጋው ተዋሕደው ይነሳል የሚለውን የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስን አስተምህሮ አምርረው ይቃወሙ ነበር፡፡ኢየሱስ ክርስቶስም ሰው ዘላለማዊ ፍጡር እንደሆነና ከሞት በኋላ መልአካዊ ህላዌ እንደሚኖረው ገሥጾ አስተምሯቸዋል፡፡በዘመነ ሐዋርያት ጊዜም ብዙ ተረፈ ሰዱቃውያንና አሕዛባውያን ተነስተው ስለ ትንሣኤ ምውታን በጥልቀት ያስተምር የነበረውን ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስን ተቃውመውታል፡፡ቅዱስ ጳውሎስም “ሀሎኑ ዘይብል እፎኑ ይትነሥኡ ምውታን ወበአይ ነፍስቶሙ የሐይዉ ኦ አብድ አንተ ዘትዘርእ አኮኑ ዝንቱ ነፍስት ዘይትወለድ ዘትዘርእ ዳእሙ ሕጠተ እመኒ ዘሥርናይ ወእመኒ ዘባዕድ ወእግዚአብሔር ይሁቦ ነፍስተ ዘከመ ፈቀደ/ ሙታን እንዴት ይነሳሉ? በየትኛው ሰውነታቸውስ ይነሳሉ? የሚል አለን አንተ ሰነፍ አንተ የምትዘራው ቅንጣት የሥንዴም ቢሆን ሌላም ቢሆን እግዚአብሔር እንደወደደ አካልን ይሰጠዋል፡፡” (1ቆሮ15፡35-38)

ዛሬም በዘመናችን ለሚኖሩ ለብዙ ከሃድያን ፈላስፎችና ባለ ሳይንሶች/ሳይንቲስቶች የክህደታቸው ዋና መነሻ ትንሣኤ ምውታንን መካድ ነው፡፡ ከሞት በኋላ ስላለው ዘላለማዊ ሕይወት መስማት ፈጽመው አይፈልጉም፡፡ የምሥጢረ ትንሣኤ አስተምህሮ ሰነፎች የፈጠሩት ተረት ተረት እንደሆነ አድርገውም ይገምታሉ፡፡በቅዱሱ መጽሐፍ እንደተጻፈልን ግን በመዝገበ ምሥጢራቱ በታቦር ተራራ ትንሣኤ ምውታን በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባር ተገልጧል፡፡ ከሞተ አንድ ሽህ አምስት መቶ ዓመት ገደማ የሚሆነው ሊቀ ነቢያት ሙሴ በቅዱሱ ተራራ በታቦር በሕይወተ ሥጋ ተገልጦ ሕይወትን ከሰጠው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በግልጥ ተነጋግሯል፡፡ በዚህ የምሥጢራት ተራራ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ማዕከል የሆነው የምሥጢረ ምውታን አስተምህሮ በቃል ብቻ ሳይወሰን በተግባር ተገለጠ፡፡ ትምህርተ ትንሣኤ ምውታን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አምስቱ አእማደ ምሥጢራት ብላ ከምታስተምረው የሃይማኖቷ መሠረት ከቆመባቸው ምሰሶዎች አንዱ ሲሆን መነሻዋም መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ የነገረ ተዋሕዶው ሊቅ ቅዱስ ቄርሎስ የትስብእት ምሳሌ አድርጎ በተረጎመው ዕፀ ጳጦስ ላይ አድሮ በጊዜያዊው ሥጋዊ ሞት ከሥጋዊው ዓለም ለተለዩት አብርሃም፣ይስሐቅና ያዕቆብ አምላክ እንደሆነ የነገረው እግዚአብሔር ራሱን ሙሴን ነፍስና ሥጋውን አዋሕዶ ከመቃብር አስነስቶ በቃል ያስተማረውን በተግባር አሳይቶታል፡፡

መቼም ቢሆን አንድን ነገር/ድርጊት/ በተግባር ከማሳየት የሚበልጥ ነገሩን/ድርጊቱን/ የሚያስረዳ ስልት አይገኝም፡፡ የታቦርን ተራራ የትምህርተ ትንሣኤ ምውታን ማሳያ ቤተ ሙከራ አድርጎ መመልከት ይቻላል፡፡ በብሉይና4 በአዲስ ኪዳን ሲነገርና ሲተረጎም ላለውና ለነበረው ምሥጢረ ትንሣኤ ምውታን ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ ከመቃብር፣ነቢዩ ኤልያስ ደግሞ ከተሰወረበት መምጣታቸውና በደብረ ታቦር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መነጋገራቸው የትንሣኤ ምውታን ማረጋገጫ ማኅተም ነው፡፡ አምላከ አማልክት ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዱቃውያንን “አነ ውእቱ እግዚአብሔር አምላከ አብርሃም ወአምላከ ይስሐቅ ወአምላከ ያዕቆብ ኢኮነኬ አምላከ ምውታን አላ አምላከ ሕያዋን ውእቱ/ እኔ እግዚአብሔር የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅም አምላክ፣ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤ እንግዲህ የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም” (ማቴ. 22፡32) በማለት ስለ ትንሣኤ ምውታን በጎላ በተረዳ መልኩ አስተምሯቸዋል፡፡

በዮሐንስ ወንጌልም “በመቃብር ያሉ ቃሉን የሚሰሙባት ጊዜ ትመጣለችና ስለዚህ አታድንቁ፡፡ መልካም የሰሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሰሩም ለፍርድ ትንሣኤ ይነሳሉ በማለት ስለ ምሥጢረ ትንሣኤ መውታን አስተምህሮ አስረድቷል (ዮሐ 5፡28-29)፡፡” በአጠቃላይ ሞት የሥጋ፣የኅሊናና የነፍስ ሞት ተብሎ የሚመደብ ሲሆን የሥጋ ሞት የነፍስ ከሥጋ ጊዜያዊ መለየት ሆኖ ከጊዜያዊነት ወደ ዘላለማዊነት የምንሸጋገርበት መሻጋገሪያ ድልድይ፣ከምድራዊነት ወደ ሰማያዊነት ከፍ የምንልበት መወጣጫ መሰላል፣ከእንስሳዊነት ግብር ወደ መላእክታዊነት ግብር የምናድግበት፣ለዘላለማዊነት የምንጸነስበት ማኅፀን ነው፡፡ በአንድ በአዳም በደል ኀጢአትና ሞት ወደ ዓለም እንደገቡ በአንድ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ትንሣኤና ሕይወት ወደ ዓለም ገብተዋል፡፡(ሮሜ 5፡12-21፣ 1ቆረ15፡51-56፣ ሕዝ 37፣1-14)

ይህ ታላቁ የምሥጢረ ትንሣኤ አስተምህሮ በታላቁ የታቦር ተራራ ለዓለም ኹሉ ተገልጧል፡፡ ስለ ምሥጢረ ትንሣኤ ምውታን ቅዱሳት መጻሕፍት የተናገሩትን ምስክርነት ስለማይቀበሉ ሰነፎች ሰዎች የትምህርተ እግዚአብሔር ሊቁ አባታችን አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የተናገረውን ግሣጼያዊ ትምህርት እንደወረደ በማቅረብ የያዝነውን ንኡስ ርእሰ ጉዳይ ለማጠቃለል እንወዳለን፡፡ “እንግዲህስ ስለ ሙታን መነሣት የሚናገሩ የመጻሕፍት ምስክርነት ይበቃናል፡፡ በእነዚህ ጥቂት የመለኮት ቃሎች ካላመኑ ከዚህ የበዛም ብንናገር አያምኑም፡፡ መስማት ለተሳነው ሰው የመለከት ድምፅ በጆሮዎቹ አይገባም፤ ማየት የተሳነውም የፀሐይ ብርሃን አይታጠውም፤ ሰነፍም ስንፍናው ጥበብ ይመስለዋል፤ የጥበበኞችንም ነገር እንደ ጥራጊ ይጥለዋል፡፡ የምድርን አፈር በውሃ ብታጥባት በጭቃ ላይ ጭቃን ትጨምራለህ፤ማንጻትም አትችልም፤ሰነፍንም በጥበብ ቃል ብትገሥጸው በስንፍናው ላይ ስንፍናን ይጨምራል፤ዐዋቂም ልታደርገው አትችልም” (መጽሐፈ ምሥጢር ገጽ 358-359)፡፡

ስብሃት ለአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡ ይቆየን፡፡

ፍልሰታ ለማርያም፡ ሰአ(ዐ)ሊ ለነ ቅድስት!

“ፍልሰታ” የሚለው ቃል ፈለሰ፣ ተሰደደ(ተገለጠ)፣መከፈት፣ መገለጥ፣ የመዝጊያ የመጋረጃ ከሚለው የግእዝ ስርወ ቃል የተገኘ ሲሆን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ትንሣኤ ይመለከታል፡፡ “ፍልሰት” የሚለው ቃል ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር መሔድን ያመለክታል፡፡ “ፍልሰታ ለማርያም” ሲባልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መወሰዷን (ማረጓን)፣ በኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትውፊትና ቀኖና መሠረት ከሰባቱ የአዋጅ አጿማት መካከል አንደኛው ጾመ ፍልሰታ ለማርያም ሲሆን ከህጻናት ጀምሮ እስከ አረጋውያን የሚጾም ታላቅ ጾም ነው፡፡

እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ዓመት በእናት በአባቷ ቤት፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ፣ ዘጠኝ ወር በዮሴፍ ቤት፣ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር፣ ዐሥራ አራት ዓመት በወንጌላዊው በዮሐንስ ቤት ከኖረች በኋላ በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩  ቀን ዐርፋለች፡፡ በሐዋርያት ውዳሴ፣ ዝማሬና ማኅሌት ነሐሴ ፲፬ ቀን ከተቀበረች በኋላ እንደሌሎቻችን ትንሣኤ ዘጉባኤን መጠበቅ ሳያስፈልጋት ነሐሴ ፲፮ በልጇ ስልጣን ተነሥታ በይባቤ መላእክት ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ “ተለዐለት እምድር ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ በየማነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ዐረገች፡፡ በሰማይም ከልጅዋ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች” በማለት ወደ ሰማይ ማረጓንና በክብር መቀመጧን ተናግሯል፡፡ ከሺሕ ዓመት በፊትም አባቷ ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” ሲል የተናገረው ትንቢት ይህንኑ የእመቤታችንን ክብር የሚመለከት ነው (መዝ. ፵፬፥፱)፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጦማርም ነገረ ፍልሰቷን እንዳስሳለን፡፡

“እንደ ልጇ ‹ተነሣች፤ ዐረገች› እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት” (አይሁድ)

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥር ፳፩ ቀን በ፵፱ ዓ.ም በ፷፬ ዓመቷ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድና ድካም ባረፈች ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያት ሊቀብሯት ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሔዱ፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታችንን የሰቀሉት አይሁድ “እንደ ልጇ ‹ተነሣች፤ ዐረገች› እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት” ብለው ሥጋዋን ሊያጠፉ በዓመፃ ተነሡ፡፡ ከእነርሱም መካከል ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ የአልጋውን አጎበር ይዞ ሊያወርዳት ሲል የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጆቹን ቀጣው፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ጨምሮ እመቤታችንን በደመና ነጥቆ ወደ ገነት ወስዶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም እመቤታችን ያለችበት ቦታ እንዲገለጥላቸው ባረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ጀመሩ፡፡

Filseta2

“ተንሥአት እሙታን፡ ማርያም ድንግል ከመ ትንሣኤ ወልዳ ዘልዑል/ እንደ ልጇ ትንሣኤ ባለ ትንሣኤ ተነሳች/” (ቅዱስ ኤፍሬም)

ሐዋርያት እመቤታችን ካረፈችበት ቀን ከጥር ፳፩ ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ ድረስ ጥያቄያቸውንና ጸሎታቸውን ባያቋርጡም ከሰው ተለይተው ሱባዔ ገብተው ጾም ጸሎት የጀመሩት ግን ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ነው፡፡ ቀድሞስ የክብር ባለቤት የጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ኾነው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ተሰውራባቸው እንዴት ዝም ብለው ይቀመጣሉ? ቅዱሳን ሐዋርያት ሁለት ሱባዔ (ዐሥራ አራት ቀናት) ካደረሱ በኋላም የነገሩትን የማይረሳ፣ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታቸውን ሰምቶ ነሐሴ ፲፬ ቀን የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው በክብር ገንዘው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀንም በልጇ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስልጣን፣ እንደ ልጇ ከሙታን ተለይታ ተነሥታለች፡፡መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤያችን በኩር ሆኖ በሞተ በሦስተኛው  ቀን ሙስና መቃብርን (የመቃብርን ሥልጣን) አጥፍቶ ሞትን ድል አድርጎ በገዛ ሥልጣኑ ተነሥቷል፡፡ እናቱ እመቤታችንም በልጇ ሥልጣን፤  እንደ ልጇ ትንሣኤ (ከመ ትንሳኤ ወልዳ ) በሦስተኛው ቀን ተነሥታ ትንሣኤ ዘጉባኤን ሳትጠብቅ በክብር ዐርጋለች፡፡ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ የክብርና የሕይወት ትንሣኤ ሲሆን ሁለተኛ ሞትን አያስከትልም ትንሣኤ ዘጉባኤንም አይጠብቅም፡፡

“አይዞህ! አትዘን፤ ባልንጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃልና ደስ ይበልህ!” (ድንግል ማርያም)

ይህ ቃል እመቤታችን ለሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የተናገረችው ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ወንጌለ መንግስትን ሲሰብክ ቆይቶ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ ጠፈር ላይ አገኛት፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?›› ብሎ ትንሣኤዋን ባለማየቱ ኀዘን ስለ ተሰማው ከደመናው ይወድቅ ዘንድ ወደደ፡፡ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” እንዲል፡፡ እመቤታችንም ‹‹አይዞህ! አትዘን፤ ባልንጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃልና ደስ ይበልህ!›› ብላ ከሙታን ተለይታ መነሣቷንና ማረጓን ለሐዋርያት እንዲነግራቸው አዝዛ የያዘቸውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡ ከዚያም እርሷ ወደ ሰማይ ዐረገች፤ እርሱም ወደ ኢየሩሳሌም ወረደ፡፡ ቅዱስ ቶማስ ትእዛዟን ተቀብሎ በክብር ከተሰናበታት በኋላ ወደ ሐዋርያት ሔዶ እንዳልሰማ እንዳላየ መስሎ ‹‹የእመቤታችን ነገር እንደምን ኾነ?›› ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አግኝተን ቀበርናት›› ሲሉት “አይደረግም ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንደምን ይሆናል?” አላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በፊት የክርስቶስን ትንሣኤ መጠራጠሩን ጠቅሶ እየገሠፀ መከራከሩንና መጠራጠሩን ትቶ ስለ እመቤታችን መቀበር እነርሱ የሚነግሩትን ዅሉ አምኖ መቀበል እንደሚገባው ለቅዱስ ቶማስ አስረዳው፡፡

“ወንድሞቼ! አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ” (ቅዱስ ቶማስ)

ቅዱስ ቶማስም የያዘውን ያውቃልና ጸጥ ብሎ የቅዱስ ጴጥሮስን ተግሳጽ ሲሰማ ቆየ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ተቈጥቶ የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ለቅዱስ ቶማስ ለማሳየት ሔዶ መቃብሯን ቢከፍት የእመቤታችንን ሥጋ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ደንግጦ ቆመ፡፡ ቅዱስ ቶማስም ‹‹ወንድሞቼ! አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ›› ብሎ እመቤታችን የሰጠችውን ሰበን ለሐዋርያት ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ ሰበንም ሊቁ በመልክዓ ማርያም ድርሰቱ “ሰላም ለግንዘተ ሥጋኪ በእደ ሐዋርያት አርጋብ፣ በአፈወ ዕፍረት ቅድው ዘአሣበ ሤጡ ዕፁብ…እመቤቴ ማርያም ሆይ ዋጋው እጅግ ብዙ በሆነና መዓዛው በሚጣፍጥ ሽቱ በሐዋርያት እጅ ለተገነዘው ንጹሕ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡” እንዳለው ቅዱሳን ሐዋርያት ሞገሳቸውን እመቤታችንን ለመቅበር የገነዙበት ነበር፡፡ እነርሱም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት እየተደሰቱ ሰበኑን ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ በየሀገረ ስበከታቸውም ሕሙማንን ሲፈውሱበትና ገቢረ ተአምርሲያደርጉበት ኖረዋል፡፡ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን በቅዳሴ ጊዜ ሠራዒ ዲያቆኑ በሚይዘው መስቀል ላይ የሚታሠረው መቀነት መሰል ልብስ፤ እንደዚሁም አባቶች ካህናት በመስቀላቸው ላይ የሚያደርጉት ቀጭን ልብስና በራሳቸው ላይ የሚጠመጥሙት ነጭ ሻሽ የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፤ቅዱሳን ሐዋርያት ለበረከት ተካፍለውታልና፡፡

“ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?” (ቅዱሳን ሐዋርያት)

ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የእመቤታችንን ዕርገት ባየ በዓመቱ ቅዱሳን ሐዋርያት “ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?” ብለው ከየሀገረ ስብከታቸው ተሰባስበው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዋን ይሰጣቸው (ዕርገቷን ያሳያቸው) ዘንድ ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ይዘው ጌታችንን ጠየቁት፡፡ እርሱም ልመናቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችንን መንበር፤ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፤ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ እመቤታችንንም ሐዋርያትንም አቍርቧቸዋል፡፡ እነርሱም እመቤታችንን በዓይናቸው ከማየት ባሻገር አብረው ሥጋውን ደሙን ተቀብለዋል፡፡

ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን ያለው ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ይሁን፡፡ (ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን)

የእመቤታችንን የትንሣኤና የዕርገት ትምህርት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን ያለው ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ኾኖ በምእመናን ዘንድ መጾም እንደሚገባው ሥርዓት ሠርተውልናል (ፍት.ነገ.አን.፲፭)፡፡ ይህ ጾምም ‹‹ጾመ ማርያም (የማርያም ጾም)›› ወይም ‹‹ጾመ ፍልሰታ ለማርያም (የማርያም የፍልሰቷ ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡ በጾሙም መጨረሻ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ ይከበራል፡፡ በእመቤታችን የትንሣኤ በዓል ላይ ተንሥአት እሙታን ማርያም ድንግል! ከመ ትንሣኤ ወልዳ ዘልዑል” ማለትም “ድንግል ማርያም ከሙታን ተለይታ ተነሣች! ይህውም ልዑል አምላክ ልጇ እንደተነሳው ትንሳኤ ነው!” የሚለውን የምስራች ቃል ምእመናን ይለዋወጣሉ። ይህ የደስታ መንፈስና ስርአት እንደልጇ ዘመነ ትንሳኤ እስከ ነሓሤ 21 ቀን ድረስ ይቀጥላል። የመልክአ ማርያም ደራሲም ‹‹ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ ደባትረ ብርሃን ኀበ ተተክሉ፤ ለገነተ ጽባሕ በማዕከሉ (እመቤቴ ማርያም ሆይ በምስራቃዊ ተክለ ገነት መካከል የብርሃን ድንኳኖች ወደተተከሉበት ለዐረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል)›› ያለውም ይህንን ያመለክታል፡፡

በጾመ ፍልሰታ  የእመቤታችን ከፅንሰቷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ ይነበባል (ሰዓሊ ለነ ቅድስት/ሰአሊ ለነ ቅድስት)፡፡

በጾመ ፍልሰታ ወቅት በቤተክርስቲያናችን በየቀኑ በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱና በቅዳሴው በሚደርሰው ቃለ እግዚአብሔር ነገረ ማርያም ማለትም የእመቤታችን ከመፀነሷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ፣ ለአምላክ ማደሪያነት መመረጧ፣ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ክብሯ፣ ርኅርራኄዋ፣ ደግነቷ፣ አማላጅነቷ፣ ሰውን ወዳድነቷ በስፋት ይነገራል፡፡ እመቤታችንን ከሚያወድሱ ድርሳናት መካከልም በተለይ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ነገረ ድኅነትን ከነገረ ማርያም ጋር በማዛመድ የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም፤ እንደዚሁም ነገረ ድኅነትን ከምሥጢረ ሥጋዌ (ከነገረ ክርስቶስ) እና ከነገረ ማርያም ጋር በማመሣጠር የሚያትተው ውዳሴ ማርያምም በስፋት ይጸለያል፤ ይቀደሳል፤ ይተረጐማል፡፡ በሰንበታት የሚዘመሩ መዝሙራት፤ በየዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ለተዋሕዶ መመረጧን፣ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን፣ ክብሯን፣ ቅድስናዋን፣ ንጽሕናዋን የሚያወሱ ናቸው፡፡ የእመቤታችን ንጽህና የነገረ ድህነት፣ የጌታችን ቤዛነት መነሻ፣ መሰረት ነውና፡፡

በጾመ ፍልሰታ ገዳማውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለማውያንም ሱባዔ ይገባሉ፡፡

በጾመ ፍልሰታ ገዳማውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለማውያንም በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእመቤታችን አማላጅነት የሰይጣንን ፈተና ድል ለማድረግ እንዲቻላቸው ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በየገዳማቱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ በዓት አዘጋጅተው፣ ሱባዔ ገብተው፣ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፡፡ እንደዚሁም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ ይህ ጾም ለእመቤታችን ያለንን ፍቅርም የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ኦርቶዶክሳውያን ሕፃናት በአብዛኛው ትምህርተ ወንጌል የሚማሩት፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉት በዚህ በጾመ ፍልሰታ ነው፡፡ ጌታችን በስሙ ሁለትም ሦስትም ኾነን ለጸሎትና ለመልካም ሥራ ብንሰባሰብ እርሱ በመካከላችን እንደሚገኝ የገባልንን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ (ማቴ. ፲፰፥፳)፣ ሁላችንም በጾመ ፍልሰታ ሳምንታት በጌታችን፣ በእመቤታችንና በቅዱሳን ሐዋርያት ስም በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመማር ባሻገር ብንጾም፣ ብንጸልይ፣ ብናስቀድስ፤ እንደዚሁም ሥጋውን ደሙን ብንቀበል በበረከት ላይ በረከትን፤ በጸጋ ላይ ጸጋን እናገኛለን፡፡ በኋላም ሰማያዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንችላለን፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው በቤተክርስቲያናችን በፆመ ፍልሰታ በተለየ መልኩ ከሚነበቡ፣ ከሚተረጎሙ ቅዱሳት መጻሕፍት አንዱ ውዳሴ ማርያም ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ከደግነቱ የተነሳ እመቤታችን ተገልጣለት ውዳሴ ማርያምን ደርሶ አመስግኗታል፡፡ ምስጋናውም በሰባቱ ዕለታት የተከፈለ ፷፬ ምዕራፎች ያሉት ነው፡፡ ፷፬ መሆኑም እመቤታችን በዚህ ምድር በሥጋ የኖረችበትን ዘመን ያጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ደግሞ በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ “ሰዐሊ ለነ ቅድስት/ሰአሊ ለነ ቅድስት” (ቅድስት ሆይ ለምኝልን) የሚለውን ጨምሮበታል፡፡ ሰዐሊ ለነ ቅድስት ተብሎ በዐይኑ ‘ዐ’ ሲጻፍ አዕምሮውን ለብዎውን (ማስተዋሉን) ሳይብን አሳድሪብን ማለት ነው፡፡ ሰአሊ ለነ ቅድስት ተብሎ በአልፋው ‘አ’ ሲጻፍ ለምኝልን ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከታወቁ የሕግ ምንጮች ከቅዱሳን አባቶቻችን በተማረችው መሰረት “ሰዐሊ ለነ ቅድስት/ሰአሊ ለነ ቅድስት” እያለች እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ትለምንልን ዘንድ በጸሎትና በምልጃ ታሳስባለች፡፡

እኛም የእመቤታችንን ዕረፍትና ትንሣኤ በማሰብ ከልጇ ከወዳጇ የሚገኘውን ጸጋና በረከት ተስፋ በማድረግ የአባቶቻችንንና የእናቶቻችንን ፈለግ ተከትለን በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታን እንጾማለን፤ የምንችል ደግሞ ንስሐ ገብተን አስቀድሰን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እንቀበላለን፡፡ ነገር ግን በሕግ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ በዚህ ወቅትም ኾነ በሌላ ጊዜ ሥጋውን ደሙን የሚቀበሉ ወጣቶች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም አረጋውያንና ሕፃናት ብቻ ሳይኾኑ ወጣቶችም ጭምር የመቍረብና የመዳን ክርስቲያናዊ ተስፋ እንዳለን በመረዳት ራሳችንን ገዝተን፣ ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል መንግሥቱን ለመውረስ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ አምላካችን በማይታበል ቃሉ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ፤ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው›› በማለት ተናግሯልና (ዮሐ. ፮፥፶፬)፡፡የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋና በረከት አይለየን፡፡ ጽንዕት በድንግልና፣ ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን፣ አዕምሮውን ለብዎውን ሳይብን አሳድሪብን፡፡

ምንጭ፡- ነገረ ማርያም፣ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ፣ ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ፣ መልክአ ማርያም፣ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገፅ

 

 

አሐቲ ቤተክርስቲያን፡ በቃልና በተግባር

debre eliasአርዮስን ለማውገዝ በጉባዔ ኒቅያ የተሰበሰቡ ቅዱሳን አባቶች (ሠለስቱ ምዕት) ‹‹ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባዔ ዘሐዋርያት/ከሁሉ በላይ በምትሆን የሐዋርያት ጉባዔ በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን›› በማለት ቤተክርስቲያን አንዲት (አሐቲ) መሆንዋን ደንግገዋል፡፡ ለቤተክርስቲያናችንም ይህ የቤተክርስቲያን አንድነትን የሚያስረግጠውን ድንጋጌ የሃይማኖት ጸሎት (ጸሎተ ሃይማኖት) ዋና መመሪያዋ ነው፡፡ ቅድስት ቤተክርስተያን በቅዳሴዋም ‹‹ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተክርስቲያን አሐቲ ቅድስት ጉባዔ እንተ ሐዋርያት ርትዕት በኀበ እግዚአብሔር/በእግዚአብሔር ፊት የጸናች ስለምትሆን የሐዋርያት ጉባዔ አንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ጸልዩ›› እያለች ታውጃለች፡፡ በእነዚህና መሰል ጸሎቶች የቤተክርስቲያንን አንድ (አሐቲ) መሆን ስትመሰክር ትኖራለች፡፡ በዚህ የአስተምህሮ ጦማር ቤተክርስቲያን አንዲት ናት ሲባል የአንድነቷ መሠረትና መገለጫዎች ምን እንደሆኑ በአጭሩ እናቀርባለን፡፡

ቤተክርስቲያን መሪዋ አንድ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

የቤተክርስቲያን መሪዋ አንድ ነው፡፡ እርሱም መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስም ተጠሪነቱ ለአንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ በአንዱ መንፈስ ቅዱስ የምትመራ አንዲት ቤተክርስተያን እንጂ ከአንድ በላይ ቤተክርስቲያን የለችም፡፡ ያችውም ከቅዱሳን ሐዋርያት የተማረችውን ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ከሐሰት ትምህርትና ከመናፍቃን ቅሰጣ በመለየት በምድር ያለች የሰማያዊት ኢየሩሳሌም አምሳል የሆነች የክርስቶስ ቤተክርስቲያን፣ በቀጥተኛነቷና ክህደት ባለመቀላቀሏ ኦርቶዶክሳዊት የምትባል፣ በጌታችን ፍጹም አምላክነትና ፍጹም ሰውነት ተዋህዶ በማመኗ ደግሞ ተዋህዶ የምትባል ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረተልን አንዲት ቤተክርስቲያንን ነው፡፡ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ቤተክርስቲያን አልመሠረተም፡፡ እንድንመሠረትም አላስተማረንም፡፡ ከዘመናት በኋላ ቤተክርስቲያን ተከፋፍላ እውነት ያልተዋጠላቸው ወገኖች ራሳቸውን እየለዪ የራሳቸውን ‘ቤተክርስቲያን’ በየዘመናቱ ቢመሠርቱም እውነተኛዋ ቤተክርስቲያን ግን አንዲት ናት፡፡ ስትመሠረትም፣ ከተመሠረተችም በኋላ፣ ዛሬም፣ እስከዓለም ፍጻሜም አንዲት ሆና ትኖራለች፡፡ በየዘመናቱ የሚነሱ ደገኛ አገልጋዮችም በመንፈስ ቅዱስ የተገለጠላቸውን እውነት እየመሰከሩ በዚች አሐቲ ቤተክርስቲያንም በመንፈስ ቅዱስ የሚከናወኑትን ምስጢራት ተካፍይ በመሆን በክርስትናቸው ጸንተው ለክብር ይበቃሉ፡፡

የቤተክርስቲያን  ራሷ እና መሠረቷ አንዱ ክርስቶስ ነው፡፡

ክርስቶስ የቤተክርስቲያን ራስ ነው፡፡ እርሱ የቤተክርስቲያን መሠረትም ነው (ማቴ 16፡16)፡፡ በክቡር ደሙ የዋጃትም እርሱ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር ወልድ ሰው በመሆኑ ከሰው ባህርይ ጋር በተዋሕዶ አንድ ሆኖ የመሠረታት ናት፡፡ ክርስቶስ ትናንት ዛሬና ነገ እስከ ዘለዓለም ድረሰ ያው ነውና የመሠረታት ቤተክርስቲያንም አንዲት ሆና ትኖራለች፡፡ ”እኔ የወይን ግንድ ነኝ፣ እናንተም ቅርጫፎች ናችሁ’ እንዳለው ሁላችን በአንዱ ግንድ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተመሠረትን ቅርጫፎች ነን፡፡ ቤተክርስቲያንም በዚህ አንድ ግንድ ላይ የተመሠረቱ ክርስቲያኖች ኅብረት ስለሆነች አንዲት ናት፡፡ በአንድ ግንድ ላይ የተመሠረትን ልንለያይና ልንከፋፈል አይገባም፡፡ ‹‹ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (1ኛ ቆሮ 3 : 11)›› እንደተባለው አሐቲ ቤተክርስቲያን በዚህ መሠረት ላይ የተመሠረተች ስለሆነች ሌላ አዲስ መሠረት ወይም እንደ አዲስ መመሥረት አያስፈልጋትም፡፡ አንዳንዶች ባለማወቅ አንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ሲተክሉ ራሳቸውን ‹‹መሥራች›› ብለው ይጠራሉ፡፡ ይህ አባባል ከምድራዊ ሕግ አሰራር የተቀዳ፣ በአብዛኛውም ቤተክርስቲያንን ለግል ጥቅምና ዝና መጠቀሚያነት የሚያስቡ የብኩን ትውልድ አካላት የሚጠቀሙበት ነው፡፡ የአሐቲ ቤተክርስቲያን መሥራች ራሱ ክርስቶስ ስለሆነ ይህ አባባል ለስሕተት ይዳርጋል፡፡

የቤተክርስቲያን ዓላማዋ አንድ ነው፡፡

የአሐቲ ቤተክርስቲያን ዓላማዋ አንድ ብቻ ነው፡፡ እርሱም ለሰው ልጅ ሁሉ ቅዱስ ወንጌልን በማዳረስ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምኖ፣ በስሙም ተጠምቆ፣ ምግባር ትሩፋትን ሠርቶ የእግዚአብሔርን መንግስት እንዲወርስ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ የተለየ ዓላማ ያላት ቤተክርስቲያን የለችም፡፡ ከዚህ የተለየ ምድራዊ ዓላማ ይዘው በቤተክርስቲያን ስም የሚጠሩ ስብስቦች ሐሰተኛ እንጂ እውተኛ፣ ምድራዊ እንጂ ሰማያዊ ቤተክርስቲያን ሊባሉ አይችሉም፡፡ እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ተቋም ስለሆነች ዓላማዋም ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን አንዳንድ ምድራዊ ዓላማ ያላቸው ‘አገልጋዮች’ በቤተክርስቲያን ቢኖሩም የቤተክርስቲያንን ዓላማ ግን ምድራዊ አያደርጉትም፡፡  በምድር ያለችው ቤተክርስቲያን ምሳሌ የሆነቻት ሰማያዊት ኢየሩሳሌምም አንዲት ናት፡፡ በምድር ባለችው አንዲት ቤተክርስቲያን የጸኑት ክርስቲያኖች እንደሚሰበሰቡ ሁሉ ነጻ በምታወጣ በኢየሩሳሌም ሰማያዊትም የጸደቁት፣ በጌታ ቀኝ የሚቆሙት ይሰበሰባሉ፡፡

ቤተክስቲያን የአንድነት ጉባዔ ናት፡፡

ቤተክርስቲያን በምድር ያሉ ክርስቲያኖች፣ በሰማይ በአፀደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን፣ እንዲሁም ቅዱሳን መላእክት በአንድነት ለምስጋና የሚተጉባት የሰማይ ደጅ ናት (ዘፍጥረት 28፡17)፡፡ እነዚህ ሁሉ ቅዱሳን ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው አንድነት (ውህደት) ነው ቤተክርስቲያን የሚባለው፡፡ በዚህም መሠረት ቤተክርስቲያን ሁሉም ሰውና መላእክት በአንድነት የሚያመሰግኑባት እንጂ ሰው በየወገኑ እየተከፋፈለ የሚወነጃጀልባት አውድ አይደለችም፡፡ አንድነትን በአደባባይ ለይምሰል እየሰበኩ በተግባር ግን ልዩነትን የሚያስፋፉ ወገኖችም በንስሐ እስካልተመለሱ ድረስ ከቤተክርስቲያን ወገን አይደሉም፡፡ ራሳቸውን ቤተክርስቲያን (የክርስቶስ ቤተመቅደስ) ሳያደርጉ በሕንጻ ቤተክርስቲያን አካባቢ ስለተመላለሱ ብቻ የቤተክርስቲያን አካል አይሆኑም፡፡ እውተነኞቹ ክርስቲያኖች በቤተክርስቲያን ያላቸው አንድነት በፍቅር የተገነባ የመንፈስ አንድነት ስለሆነ አንዱ ለሌላው ስለመልካም ነገር የሚጸልይበት አንድነት ነው፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋል የሚያስፈልገን ቤተክርስቲያን የአንድነት ጉባዔ ናት ሲባል የአምልኮ፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የመተሳሰብ፣ የመተባበር፣ የመደጋገፍ ጉባዔ ናት ማለት ነው፡፡

የቤተክርስቲያን አስተምህሮ አንድ ነው፡፡

ቤተክርስቲያን በየትኛውም የዓለም ክፍል ብትኖር፣ በየትኛውም ዘመን ብታስተምር፣ በየትኛውም ቋንቋ ብትሰብክ መሰረታዊ አስተምህሮዋ አንድ ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ፣ ስለሰው ልጅም መከራን ተቀብሎ ሞትን ድል አድርጎ እኛን ከሲኦል ወደገነት እንደመለሰን የሚመሰክርና ሰውም ይህንን አምኖና ተጠምቆ መልካም ምግባርን ሠርቶ እንዲድን የሚያስተምር አስተምህሮ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‘እኛ ከሰበክንላችሁ ወንጌል ውጭ የሚሰብክላችሁ የሰማይ መልአክም ቢሆን የተወገዘ ይሁን’ ያለው የቤተክርስቲያን አስተምህሮ አንድ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ እርሱም ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ ማስተማር፣ እንዲሁም እርሱ ባስተማረው፣ ሐዋርያት በሰበኩት፣ ሐዋርያነ አበውና ደጋግ ሊቃውንት በመንፈስ ቅዱስ ምሪት አጽንተው በጠበቁት ኦርቶዶክሳዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት ያለመወላወል መጽናት ነው፡፡ ሁሉም ሐዋርያት ያስተማሩት ይህንኑ አንዱን የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ነው፡፡ በዘመናችን ያሉት ስድስቱ ኦሪየንታል አብያተ ክርስቲያናትም (ማለትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ የግብፅ ኦርቶዶክስ፣ የሶርያ ኦርቶዶክስ፣ የአርመን ኦርቶዶክስ፣ የሕንድ ኦርቶዶክስና የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት) አንድ ናቸው ስንል በአስተምህሮ (በዶግማ) ነው፡፡ በተለያየ ሀገር ሆነው የየራሳቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ቢኖራቸውም በአስተምህሮ አንድ ስለሆኑ የአንዲት ቤተክርስቲያን አካል ናቸው እንጂ የተለያዩ አይደሉም፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በአንዲት ቤተክርስቲያን ውስጥ ሆነው አስተምህሮዋን የማይቀበሉና የየራሳቸውን ፍልስፍና የሚያስተምሩ የውስጥ መናፍቃን የአንዲት ቤተክርስቲያን አካል አይደሉም፡፡

ቤተክርስቲያን የአንድ እግዚአብሔር ቤት ናት፡፡

በአንዲት ቤተክርስቲያን ያሉት ክርስቲያኖች የሚያምኑትና የሚያመልኩት፣ ቤተክርስቲያንም የምትሰብከው በዘመናት የማይቀየር የማይጨመርበት በፍጹም አንድነት በልዩ ሦስትነት የሚመሰገን አንድ አምላክ ነው፡፡ እርሱም አንድ እግዚአብሔር ነው፡፡ ቤተክርስቲያንም የእግዚአብሔር ቤት ናት፡፡ ጌታችን ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች (ማቴ 21፡13)›› ያለውም ለዚህ ነው፡፡ አንዲት ቤተክርስቲያን የአንዱ የእግዚአብሔር ቤት ናትና ‘የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን’ ትባላለች (ሐዋ 20፡23)፡፡ አንዱን እግዚአብሔርን የምታመልክ ቤተክርስቲያን የሰው ዘር ሁሉ እርሱን ስም ቀድሶ ክብሩን እንዲወርስ ታስተምራለች፡፡ ‹‹ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ (ዘጸ 20፡3)›› ብሎ ለሙሴ ትዕዛዝን የሰጠውም በቤተክርስቲያን የሚመለከው እርሱ ብቻ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ቤት ናት ማለት የሰው ፈቃድ (ፍላጎት) ሳይሆን ፈቃደ እግዚአብሔር የሚፈጸምባት ናት ማለት ነው፡፡ የሰው ዝና ወይም ሥራ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቸርነቱ፣ መግቦቱና ከሀሊነቱ የሚነገርባት ናት ማለት ነው፡፡ በቤተክርስቲያን የሚሰበሰበው ሰው እግዚአብሔርን ብሎ የመጣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ነው ማለት ነው፡፡ በቤተክርስቲያን የሚፈጸመው አገልግሎትም ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መስዋዕት እንጂ ምድርዊ ትርፍን ለማግኘት የሚደረግ አይደለም ማለት ነው፡፡ አሐቲ ቤተክርስቲያን የአንዱ የእግዚአብሔር ቤት ናት ስንል ይህንን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡

ቤተክርስቲያን ክርስቲያኖች ከአንድ ምስጢር የሚካፈሉባት ናት፡፡

ቤተክርስቲያን ያመንን ሁሉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ (ማየ ገቦ) አንዲት ጥምቀትን ተጠምቀን የስላሴ ልጅነትን የምናገኝባት፣ የአንዱን ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በአንድነት ተካፍለን፣ ተቀብለን የዘላለም ሕይወትን የምንወርስባት ቤት ናት፡፡ በቤተክርስቲያን ሁላችንም የተጠመቅነው ጥምቀት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የሁላችንም ጥምቀት የስላሴን ልጅነት የምታሰጥ ጥምቀት ናት፡፡ ይህም በጥምቀታችን አንድ መሆናችንን ያሳያል፡፡ በአሐቲ ቤተክርስቲያን የሚፈተተው የአንዱ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ነው፡፡ ሁላችንም የምንቀበለው ይህንን የአንዱን የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ነው፡፡ በዚህም ሁላችንም የዘላለም ሕይወትን እንወርሳለን፡፡ ይህም በቤተክርስቲያን ያለንን የመንፈስ አንድነት ያሳያል፡፡ እነዚህ ምሥጢራት በየትም ቦታ፣ በማንኛውም ጊዜ፣ ለማንኛውም ሰው፣ በማንኛውም ካህን ቢፈጸሙ ዋጋቸው አንድ መሆኑ የቤተክርስቲያንን አንድነት ያመለክታል፡፡ በአንዲት ቤተክርስቲያን (በአባታችን በእግዚአብሔር ቤት) ከአንድ ምስጢር የተካፈልንና የምንካፈል የአንድ አባትና የአንድ እናት ልጆች ከማንም በላይ አንድ መሆን ይጠበቅብናል፡፡ እንደ ጠዋት ጤዛ ረግፎ ለሚጠፋው የሥጋ ፍላጎታችን ብቻ ስንል ከአንድ አባትና እናት የተወለዱት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከአባታቸው ቤት ከእናት ቤተክርስቲያን እንዲርቁ ምክንያት ብንሆን ግን በፍርድ ቀን ዋጋችን ይጠብቀናል፡፡

አንዲት (አሐቲ) ቤተክርስቲያን ማለት ‘በአንድ ሲኖዶስ እንመራለን’ ማለት ብቻ አይደለም፡፡ የቤተክርስቲያን አንድነት በአስተዳዳር መነጽር ብቻ መታየት የለበትም፡፡ በአስተዳደር አንድነት ከሆነ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዓለም አቀፍ የአስተዳዳር አንድነት ያለው ነው፡፡ በሁሉም ዓለም ያሉት ካቶሊካዊያን በአንድ ፖፕ ይመራሉና፡፡ የቤተክርስቲያን አንድነት ግን ከአስተዳደር አንድነት በላይ ነው፡፡  በአንድ ሲኖዶስ ስር ሆነው በቋንቋ፣ በዘር፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በመንደርተኝነትና በምድራዊ ጥቅም የተሳሰሩ ወገኖች የየራሳቸው ‘ቤተክርስቲያን’ ይዘውና ደሴት ሠርተው የሚኖሩበት ሁኔታ የአሐቲ ቤተክርስቲያንን ጽንሰ ሐሳብ ምሉዕ አያደርገውም፡፡ አንዱ የሌላውን መልካም ካልተመኘ፣ ሁሉ ስለሰው ሁሉ ድኅነት ካልሠራ፣ አንዱ ስለሌላው ካልጸለየ፤ በአንጻሩ መደጋገፍ ሳይሆን መነቃቀፍና መፎካከር ከነገሠ አሐቲ ቤተክርስቲያን ነን የሚለውን የቃል ብቻ ያደርገዋል፡፡ ይህ በሽታ በተለይም በዝርወት ምድር በሚገኙ ቤተክርስቲያንን በዋናነት የባህልና የማኅበረሰባዊ ትስስር ማጠንከሪያ፣ የእውቅና ፈላጊ አጭበርባሪዎች ዋሻ ባደረጉ ቦታዎች ይስተዋላል፡፡

አሐቲ (አንዲት) ቤተክርስቲያን ስንል ሕይወታችን የአንድ አባትና የአንድ እናት ልጆች መሆናችንን፣ እንዲሁም በአንድ አምላክ የምናምን፣ አንዲት መንግስተ ሰማያትን ተስፋ የምናደርግ የክርስቶስ ቤተሰቦች (ክርስቲያኖች) መሆናችንን በእምነትና በተግባር የሚመሰክር ሊሆን ይገባል፡፡ በአጠቃላይ የቤተክርስቲያን አንድነት በእምነት (በአንድ አምላክ በማመን)፣ በፍቅር (የአንድ አባትና የአንድ እናት ልጆች መሆናችንና በአንድ በክርስቶስ ፍቅር መዋደዳችን) እንዲሁም በተስፋ (አንዲት መንግስተ ሰማያትን ተስፋ የምናደርግ መሆናችንን) የሚገለጥ ነው እንጂ በቃላት ‘አንድ ነን’ ወይም ‘አንድ ሆነናል’ በማለት ብቻ የምናረጋግጠው አይደለም፡፡ የቤተክርስቲያን አምላክ እግዚአብሔር የሰይጣንን ተንኮል ያፍርስልን፣ አንድነታችንንም ያጽናልን፡፡ አሜን፡፡

 

የእውቀት እምነትና የእውነት እምነት

እምነት ማለት እግዚአብሔር ታማኝ አምላክ በመሆኑ የተናገረውን በፍጹም ልብ ተቀብሎ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ላይ ማረፍ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው ‹‹እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው።›› ዕብ 11፡1 በመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጥ እምነት ሁለት ነገሮችን ሊያመለክት ይችላል፡፡ አንደኛው የእውቀት እምነት (የአጋንንት እምነት፣ የሞተ እምነት) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እውነተኛ እምነት (የተስፋ እምነት፣ በሥራ የተገለጠ እምነት) ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት የእምነት ዓይነቶች መካከል ያሉት ዋና ዋና ልዩነቶች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

እግዚአብሔርን ማወቅ አንጻር

የእውቀት እምነት ብቻ ያላቸው አጋንንት እግዚአብሔርን ያውቃሉ፡፡ ይህንን ዓለም እንደፈጠረ እነርሱንም እንደፈጠረ ያውቃሉ፡፡ ሰውም እርሱን አምኖ እንደሚድን ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን እውቀታቸው ከእውቀትነት አያልፍም፡፡ እውቀታቸው ወደ መልካም ምግባር አይቀየርም፡፡ እግዚአብሔርን ማወቅ ብቻ እውነተኛ እምነት አይሆንምና እነርሱ በእውቀታቸው አይድኑበትም፡፡ ስለዚህ ነው የአጋንንት እምነት የእውቀት እምነት የሚባለው፡፡ በሐዋርያት ዘመን ክፉ መንፈስ ለማውጣት የሞከሩት ያገኙት ምላሽ ‹‹ኢየሱስንስ አውቀዋለሁ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተሳ እነማን ናችሁ?›› የሚል ነበር። ሐዋ 19፡13-16 አጋንንት ኢየሱስን አውቀዋለሁ ከማለት አልፈው ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ›› እና ‹‹የእግዚአብሔር ቅዱሱ›› ብለው ተናግረዋል፡፡

በአንጻሩ እውነተኛ እምነት ያለው ሰው እግዚአብሔርን ያውቃል፡፡ እውቀቱም ተስፋ ያለበት ስለሆነ እውነተኛ እምነት ይሆንለታል፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ተስፋ አለውና፡፡ ብበድለውም እንኳን አምላኬ ይቅርባይ ስለሆነ በንስሐ ብመለስ ይቅር ይለኛል፣ ልጁም ያደርገኛል ብሎ ያምናል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ያለው እውቀት ፍቅር ስላለበት አይታበይበትምና፡፡ 1ኛቆሮ 8፡1 እውቀቱን ለጽድቅ ዓላማ ይጠቀምበታል፡፡

እምነትን በሥራ መግለጥ አንጻር

የእውቀት እምነት ብቻ ያላቸው አጋንንት እግዚአብሔርን ያምናሉ፡፡ ይህም ማለት እርሱ አምላክ እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ ስለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል። አንተ ከንቱ ሰው፥ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን?›› ያዕ 2፡19-20 ያለው፡፡ የእነርሱ እምነት መልካም ሥራ የሌለበት በክፋት የተመላና የእውቀት ብቻ ነውና፡፡ እንደዚሁም የእውነተኞች ማኅበራት፣ ጽዋና ማዕድ እንዳለ የአጋንንትም አለ፡፡ ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹ከአጋንንትም ጋር ማኅበረተኞች እንድትሆኑ አልወድም። የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም። 1ኛ ቆሮ 10፡20-21›› ብሎ ባስተማረው ይታወቃል፡፡

እውነተኛ እምነት ያለው ሰው ግን እምነቱ በሥራ (በተግባር) የተገለጠ ነው፡፡ እምነቱን በሥራ (ትዕዛዛትን በመፈጸም) ያሳያል፡፡ ላመነው አምላክ ሕጉን በመፈፀም ይታመናል፡፡ ከሚያምኑትም ጋር ማኅበር ይመሠርታል፣ ጽዋንም ይጠጣል፣ በማዕድም ይካፈላል፡፡ ከአጋንንት ማኅበር ግን ይርቃል፡፡ ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አይጠመድም፡፡

እግዚአብሔርን መፍራት አንጻር

የእውቀት እምነት ብቻ ያላቸው አጋንንት እግዚአብሔርን ይፈራሉ፡፡ የሚፈሩትም ያጠፋናል፣ ያቃጥለናል፣ ይቀጣናል ብለው ነው፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ‹‹ወደ ማዶም ወደ ጌርጋሴኖን አገር በመጣ ጊዜ፥ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ኢየሱስ ሆይ፥ የእግዚአብሔር ልጅ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልትሣቅየን ወደዚህ መጣህን? እያሉ ጮኹ። ማቴ 8፡28-34›› እና በማርቆስ ወንጌል ‹‹በዚያን ጊዜም በምኩራባቸው ርኵስ መንፈስ ያለው ሰው የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ። ማር 1፡23-25›› የተጠቀሱት የአጋንንት እግዚአብሔርን መፍራት ያሰቃየናል/ያጠፋናል ከሚል የመነጨ ነው፡፡

እውነተኛ እምነት ያለው ሰውም እግዚአብሔርን ይፈራል፡፡ የሚፈራው ግን ከፍቅር የተነሳ ነው እንጂ ያሰቃየኛል/ያጠፋኛል ከሚል አስተሳሰብ  አይደለም፡፡ አምላኩን ስለሚወደው ከማክበር የተነሳ ይፈራዋል፡፡ ትዕዛዙንም ከፍቅር የተነሳ ይጠብቃል፡፡ ‹‹ከወደዳችሁኝስ ትዕዛዜን ጠብቁ›› (ዮሐ. 14፡15) እንደተባለ፡፡ እግዚአብሔርንም መፍራት የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ስለሆነ በእውነተኛ እምነት ያለ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፡፡ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፣ በረዓድም ደስ ይበላችሁ” (መዝ. 2፡11) እንዳለ እውነተኛ እምነት ያለው ሰው እግዚአብሔርን መፍራቱ በደስታ የሚፈጸም ነው፡፡

የእግዚአብሔርን ቃል መጥቀስ አንጻር

ጌታችንን ዲያብሎስ በገዳመ ቆሮንቶስ በፈተነው ጊዜ ካቀረበለት ፈተናዎች መካከል አንዱ ‹‹መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር›› የሚል ነበር ማቴ 4፡6 ይህም አስቀድሞ በነቢዩ ዳዊት በመዝሙር የተነገረ ቃል ነው፡፡ እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስ ለልጁ ጢሞቴዎስ በጻፈው መልእክቱ ‹‹መንፈስ ግን በግልጥ፡- በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል፡፡ 1ኛ ጢሞ 4፡1-2›› ሲል አስጠንቅቆታል፡፡ ይህም ማለት የእውቀት እምነት ብቻ ያላቸው አጋንንት የእግዚአብሔርን ቃል ለጥፋት ዓላማ እያጣመሙ ይጠቅሱታል ማለቱ ነው፡፡

እውነተኛ እምነት ያለው ሰውም መጽሐፍ ቅዱስን ያነባል፣ ይጠቅሳል፣ ያስተምራል፡፡ የሚጠቅስው ግን ለትክክለኛው ዓላማ በትክክለኛው መንገድ (ባለማጣመም) ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን ቃል የሚጠቅሰው ሕይወት ስለሆነ ሕይወትን ለማግኘትና ሐዋርያት ባስተማሩት መሠረት ነው፡፡ መጽሐፍ ‹‹በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል›› (ኤፌ. 2፡20) እንዳለ በእውነተኛ እምነት ያለ ሰው በዚህ መሠረት ላይ ታንጾ የመጽሐፍን ቃል ለድኅነት ዓላማ ይጠቀምበታል፡፡

ተአምራትን ማድረግ አንጻር

የእግዚአብሔር ምርጦች ተአምራትን እንደሚያደርጉ ሁሉ የእውቀት እምነት ብቻ ያላቸው አጋንንትም በሰው ላይ አድረው ተአምራትን ያደርጋሉ፡፡ ለዚህም ሙሴና አሮን በፈርኦን ፊት ምልክትን ሲያሳዩ ጠንቋዮችም በአስማታቸው እንደዚያው አድርገው ነበር፡፡ ‹‹ አሮንም በትሩን በፈርዖንና በባሮቹ ፊት ጣለ፥ እባብም ሆነች። የግብፅም ጠንቋዮች በአስማታቸው በትራቸውን ጣሉ፥ እባቦችም ሆኑ፤ የአሮን በትር ግን በትራቸውን ዋጠች። ዘፀ 7፡ 9-10›› በሁለተኛውም ተአምር ‹‹አሮን በትሩንም አነሣ፥ በፈርዖንና በባሪያዎቹም ፊት የወንዙን ውኃ መታ፤ የወንዙም ውኃ ሁሉ ተለውጦ ደም ሆነ። የግብፅም ጠንቋዮች በአስማታቸው እንዲሁ አደረጉ፡፡ ዘፀ 7፡20-22›› በሦስተኛውም ‹‹አሮንም በግብፅ ውኆች ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጓጕንቸሮቹም ወጡ። ጠንቋዮችም በአስማታቸው በግብፅም አገር ላይ ጓጕንቸሮችን አወጡ። ዘፀ 8፡6-7›› ነገር ግን የአጋንንት ተአምር ከዚህ በላይ መዝለቅ አልቻለም፡፡ የሙሴና የአሮን ግን እስራኤልን ወደ ከነዓን እስከማድረስ ድረስ ነበር፡፡

እውነተኛ እምነት ያለው ሰውም ተአምራትን ሊያደርግ ይችላል፡፡ ብዙ ቅዱሳን ብዙ ተአምራትን አድርገዋልና፡፡ ተአምራትን ማድረግ ግን ብቸኛ የቅድስና መገለጫ አይደለም፡፡ ቅዱሳን ተአምራትንም ያደረጉት በእግዚአብሔር ኃይል ነው፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋል የሚያስፈልገው ነገር አንድ ሰው ተአምር ማድረጉ ብቻ እውነተኛ አያስብለውም፡፡ በማን ኃይል ነው ተአምር የሚያደርገው የሚለው ነው መሰረታዊው ነጥብ፡፡ የተዓምር ዓላማ ሰውን ለትምህርት ተገዢ ማድረግ ነው፡፡ የእውነተኞችን ተዓምር የሚያይ ለእውነት ትምህርት፣ የሐሰተኞቹን ተዓምር የሚያይ ደግሞ ለሐሰት ትምህርት ተገዢ የመሆን እድላቸው ሰፈ ነው፡፡ ዛሬ እውነተኛ ተዓምር አይቶ፣ ተዓምሩን ብቻ አድንቆ የመጣ ሰው ነገ የሐሰት ተዓምር ሲያይ ከተዓምሩ ጋር የሚዛመደውን ትምህርትና ስርዓት ሳይመረምር ለስህተት ትምህርት ይጋለጣል፡፡ ይህም በየዘመኑ በተደጋጋሚ የታየ እውነታ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን የምትቆመው በተዓምር ሳይሆን በትምህርት መሆኑን መረዳት ይኖርብናል፡፡ ጌታችንም ያስተማረው፣ ሐዋርያትም የነገሩን፣ በቤተክርስቲያን ታሪክም የሚታወቀው ይሔው ነው፡፡

እግዚአብሔርን መምሰል አንጻር

የእውቀት እምነት ብቻ ያላቸው አጋንንት አምላክ ነን አምልኩን ብለው ሰውን ያታልላሉ፡፡ በጌታ ስም በቅዱሳንም ስም በደካማ ሰው ላይ አድረው እንዲሁም መልካቸውን እየለዋወጡ ያታልላሉ፡፡ ስለዚህ ነው ሐዋርያው ‹‹እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና። ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል። 2ኛ ቆሮ 11፡13-15›› ያለው፡፡

እውነተኛ እምነት ያለው ሰው ግን ክርስቶስን ይመስላል፡፡ ሐዋርያው ‹‹እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተ ደግሞ እኔን ምሰሉ (1ኛ ቆር 11፡1)›› እንዳለው ክርስቶስን ይመስላል፡፡ እውነተኛ ክርስቲያን ራሱን አይለዋውጥም፡፡ ሌላውንም አያታልልም፡፡ እውነተኛ ማንነቱን ብቻ ይገልጣል እንጂ፡፡ ይህች እውነተኛ ማንነቱም በቀናች ሃይማኖት፣ በበጎ ምግባር ያጌጠች ክርስቲያናዊ ሕይወት ናት፡፡

ዘላለም ሕይወት አንጻር

የእውቀት እምነት ብቻ ያላቸው አጋንንት ምንም አውቀት ቢኖራቸውም በእውቀታቸው መልካም ነገርን ስለማይሠሩበት  መጨረሻቸው የዘላለም እሳት ነው፡፡ በራዕየ ዮሐንስ ‹‹ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ። ራዕ 20፡10›› እንደተባለው መጨረሻቸው ይኸው ነው፡፡

በእውነተኛ እምነት ያለ ሰው ግን መጨረሻው የዘላለም ሕይወት ነው፡፡ እውነተኛ ክርስቲያን በዚህ ምድር ላይ በተጋድሎ ኖሮ ሩጫውን ሲጨርስ የጽድቅ አክሊልን ከአምላኩ ዘንድ ይቀበላል፡፡

ስለዚህ በውሸት “እምነት” ከተባለ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ለሥጋዊ ዓላማና ግብ ከሚያጣምም፣ እውነተኛ የመጽሐፍ ቅዱስን ዓላማ ከማይከተል፣ በተግባር ከማይገለጥ፣ በሐሰት ተዓምራት ላይ ከተመሰረተ የአጋንንት ዓይነት “እምነት” ተለይተን ከቅዱሳን ሐዋርያት በእምነት የተቀበልነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ያለመበረዝና ያለመቀላቀል ተቀብለን፣ እምነታችንን በምግባራት አስጊጠን፣ በእውነተኛ ተዓምራት እንዲሁም በቅዱሳን ሁሉ ሕይወት የተገለጠችውን የእውነት እምነት ያለማመንታት ጠብቀን የመንግስቱ ወራሾች የክብሩ ቀዳሾች እንሆን ዘንድ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡ የእውነት እምነትን የጠበቁት፣ ለእኛም በዘመናት መካከል በሕይወት የተገለጠች ሃይማኖታቸውን ከሰይጣን መከራ ጠብቀው፣ ድል በማትነሳ ረድኤት፣ ጥርጥር በሌለባት እምነት የጸኑት የቅዱሳን ሁሉ በረከት ከእኛ ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡

 

ቅዱሳን ሐዋርያት፡ ንጹሐን የሆኑ የሕግ ምንጮች

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ የጾመ ሐዋርያት መጨረሻ ላይ ሐምሌ 5 ቀን ጴጥሮስ ወጳውሎስ በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልካሙን የክርስትና ገድል ተጋድለው ሰማዕትነት የተቀበሉበትን ቀን በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዓት ታከብራለች። በተመሳሳይ መልኩ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የሌሎችንም ቅዱሳን ሐዋርያት ዜና ገድላቸውን መዝግባ በመያዝ አገልግሎታቸውን ትዘክራለች፤ በጸሎታቸው፣ በምልጃቸው፣ በቃልኪዳናቸው ትማጸናለች፡፡ እኛም ኦርቶዶክሳውያን ሁላችን የቤተክርስቲያንን ፈለግ ተከትለን እንዲሁ እናደርጋለን፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት የቤተክርስቲያን አዕማድ ናቸው፡፡ በእነዚህ አስተምህሮና የመጻሕፍት ትርጓሜ ላይ የተመሠረተች ቤተክርስቲያንም ‹‹ሐዋርያዊት›› ትባላለች፡፡ በዚህ አጭር የአስተምህሮ ጦማርም የቤተክርስቲያን አዕማድ የተባሉ የቅዱስ ጴጥሮስና የቅዱስ ጳውሎስን ታሪክ ምሳሌነት በመጠቀም ስለ ሐዋርያት እንዲሁም የሐዋርያትን ሥልጣንና ኃላፊነት እስከ ዓለም ፍጻሜ ስለሚሸከሙ የቤተክርስቲያን ካህናት እንዳስሳለን፡፡

የሐዋርያትን ስያሜ በተመለከተ ቅዱስ ሉቃስ እንዲህ ሲል አስፍሮታል፡፡ ‹‹በእነዚያም ወራት ይጸልይ ዘንድ ወደ ተራራ ወጣ፡፡ ሌሊቱን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ፡፡ በነጋም ጊዜ ደቀመዛሙርቱን ጠራ፡፡ ከእነርሱም 12 መረጠ፡፡ ደግሞም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው (ሉቃ 6፡12-14)፡፡›› የሐዋርያት (የካህናት) ሲመት እንዴት መሆን እንዳለበት ሥርዓትን ሲሠራ በመጀመሪያ ወደ ተራራ ወጣ፡፡ ተራራ የተባለች ቤተክርስቲያን ናት፡፡ በዚያም ሲጸልይ አደረ፡፡ የሐዋርያት ሲመት ከእግዚአብሔር ነውና የእርሱን ፈቃድ መጠየቅ እንደሚገባ በዚህ አስተማረ፡፡ ከዚያም ከመምረጥ በፊት መጥራት ይቀድማልና ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፡፡ የተጠራ ሁሉ አይመረጥምና 12ቱን ብቻ መረጣቸው፡፡ በእርሱ በራሱ ፈቃድ መረጣቸው፡፡ ስማቸውንም ሐዋርያት ብሎ በክብር ሰየማቸው፡፡ ሐዋርያ የሚለው ቃል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለ12ቱ ደቀ መዛሙርት የሰጣቸው ስም (ስያሜ) ነው፡፡ ለመሆኑ ሐዋርያ ማለት ምን ማለት ነው? የአንድ ሐዋርያ ኃላፊነትስ ምንድን ነው? እኛስ ለእግዚአብሔር ሐዋርያት ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?

ሐዋርያ ማለት የተመረጠ (ምርጥ) ማለት ነው፡፡

ሐዋርያ ማለት በሰው ፈቃድ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ ሰውን ለማገልገል ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለሚከናወነው መንፈሳዊ አገልግሎት የተመረጠ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያት አንተ ለዚህች አገልግሎት የመረጥከውን ሹም እንዳሉ (ሐዋ 1፡26) መራጩ እግዚአብሔር ነው፡፡ የሐዋርያነት ምርጫው በገንዘብ አይደለም፡፡ ሲሞን በገንዘቡ ሊመረጥ አስቦ ከነገንዘቡ ጠፍቷልና (ሐዋ 8፡18)፡፡ በዝምድናም አይደለም፡፡ መራጩ ሁሉንም እኩል የሚያይ ፍትሐዊ ንጉሥ ነውና፡፡ በእውቀት ብዛትም አይደለም፡፡ እውቀት ያስታብያልና፤ያልፋልምና (1ኛ ቆሮ 8፡1)፡፡ የሐዋርያነት ምርጫው በጸሎት (በእግዚአብሔር ፈቃድ) ነው እንጂ፡፡ ስለዚህ ሐዋርያት በጌታ ፈቃድ ተመረጡ፡፡ ሲመርጣቸውም በተራራው ሲጸልይ ያደረው ይህንን ሊያስተምር ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰምዖንን ከአሳ አጥማጅነት ጠርቶ ስሙን ወደ ጴጥሮስ (ዐለት) ቀይሮ በግብሩም ሰውን በወንጌል እንዲያጠምድ አድርጎታል፡፡ ሳውልን ደግሞ ከአሳዳጅነት ጠርቶ ስሙም ወደ ጳውሎስ (ብርሃን) ተቀይሮ የክርስቲያኖች አሳዳጅ የነበረው የቤተክርስቲያን አምድ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ባለትዳሩ ጴጥሮስን በአረጋዊነት፣ ድንግል የነበረውን ጳውሎስን በወጣትነት የጠራቸው ለሐዋርያነትም የመረጣቸው በእርሱ በራሱ ፈቃድ ነበር፡፡ አንዱ ኦሪትን ያላወቀ፣ ሌላው ኦሪትን የጠነቀቀ ቢሆኑም ሁለቱንም ለሐዲስ ኪዳን የሐዋርያነት አገልግሎት ጠራቸው፡፡

ሐዋርያ ማለት የተላከ (መልእክተኛ) ማለት ነው፡፡

ሐዋርያ ማለት እግዚአብሔር የላከው፤ የእርሱንም ወንጌል የሚመሰክር መልእክተኛ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያ የእግዚአብሔር በጎች ከጠፉበት እንዲፈልግ የተላከ መልእክተኛ ማለት ነው፡፡ እንደ በግ በተኩላ መካከል የተላከ፣ የዋህና ብልህ ሆኖ በጎችን ከተኩላዎች የሚታደግ መልእክተኛ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያ ለዓለሙ ሁሉ እስከ ዓለም ዳርቻ የተላከ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነው፡፡ ለእገሌ ወገን ወይም ለተወሰነ ልሳን ተናጋሪዎች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የተላከ መልክተኛ ማለት ነው፡፡ በሄደበትም ያላመኑትን እያስተማረ  እያጠመቀ ደቀ መዝሙር የሚያደርግ  መልክተኛ ነው (ማቴ 28፡28)፡፡ ጌታ በእርገቱ ዕለት ‹‹እስከምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ›› (ሐዋ 1፡8) እንዳለው እስከ ዓለም ዳርቻ ለተላከለት ዓላማ ምስክር የሚሆን ማለት ነው፡፡ የክርስቶስ ምስክር ማለትም የእርሱን ቃል የሚመሰክር ማለት ነው፡፡ ሰላምን የሚሰብክ፣ ሃይማኖትን የሚያጸና፣ ትውልድን የሚያንጽ የክርስቶስ መልእክተኛ እውነተኛ ሐዋርያ ይባላል፡፡ የሰይጣን መልእክተኞች ደግሞ የሐሰት ሐዋርያት ይባላሉ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ እውነተኛ ሐዋርያ (መልእክተኛ) ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እያስተማረ ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ ሲደርስ ሰዎች ማን እንደሚሉት ሐዋርያትን ጠየቃቸው። ሐዋርያትም “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፣ አንዳንዱ ኤልያስ ነው፥ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል” ሲሉ መለሱለት። ጌታችንም ‹‹ለመሆኑ እናንተስ ምን ትሉኛላችሁ›› ብሎ ስለ እርሱ ያላቸውን ግንዛቤ ጠየቃቸው።በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ›› ሲል መሰከረ። ጌታችን “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ አንተ ብፁዕ ነህ፤በሰማያትያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና። እኔምእልሃለሁ፥ አንተ ዐለት ነህ፥ በዚያች ዐለት ላይም ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፥የሲኦል በሮችም አይበረታቱባትም” (ማቴ. 16፡13-19)። ይህ እውነተኛ የጴጥሮስ ምስክርነት ለቤተክርስቲያን መሠረት ሆኗል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ስምንት ምዕራፎችን የያዘ ሁለት መልእክታትን ጽፎ ለክርስቲያኖች ሁሉ ምስክር ሆኗል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም እውነተኛ የወንጌል መልእክተኛ ነበር፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎቱንም የጀመረው ጌታ ካረገ በሰባት ዓመት በኋላ ነበር፡፡ በተለይም በወቅቱ አሕዛብ ይባሉ የነበሩትን በማስተማር ክርስትናን ያስፋፋ ታላቅ ሐዋርያ ነበር፡፡ አራት ታላላቅ ሐዋርያዊ ጉዞዎችን በማድረግ ወንጌልን በዘመኑ ሁሉ የመሰከረ የክርስቶስ ሐዋርያ ነበር፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አንድ መቶ ምዕራፎችን የያዙ አሥራ-አራት መልእክታትን ጽፏል። ይህን በማድረጉ የታሠረ የተንገላታ ነገር ግን ሁል ጊዜ ስለ ቤተክርስቲያን ሲያስብ የነበረ ታላቅ ሐዋርያ ነበር፡፡

ሐዋርያ ማለት የሚከተል (ተከታይ) ማለት ነው፡፡

በሌላም በኩል ሐዋርያ ማለት ተከታይ ማለት ነው፡፡ ክርስቶስን የሚከተል የክርስቶስ ሐዋርያ ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ‹‹ተከተሉኝ›› ብሎ እንደጠራቸው ሁሉ ሐዋርያ ማለት ተከታይ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያት ጌታን የተከተሉት በሁለት መንገድ ነው፡፡ የመጀመሪያው በመዋዕለ ሥጋዌ (በሥጋው ወራት) በእግር ተከትለውታል፡፡ ከዋለበት እየዋሉ ካደረበት እያደሩ ከእግሩ ሥር ቁጭ ብለው እየተማሩ በእግር ተከትለውታል፡፡ ሁሉን ትተው ተከትለውታል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በግብር (በሕይወትና በአገልግሎት) መከተል ነው፡፡ እርሱ እንደጾመ እየጾሙ፣ ዞሮ እንዳስተማረ ዞረው እያስተማሩ፣ መከራን እንደታገሰ መከራን እየታገሱ ተከትለውታል፡፡

ሁሉን ትቶ እግዚአብሔርን የሚከተል በመጨረሻ ታላቅ ዋጋ አለው (ማቴ 19፡27)፡፡ በሕይወቱና በአገልግሎቱ ሁሉ እግዚአብሔርን የሚያስቀድም፣ እንደ እግዚአብሔር ሕግ የሚመራ ሐዋርያ ነው፡፡ ‹‹ፍለጋውን ትከተሉ ዘንድ ምልክትን ሊተውላችሁ እርሱ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአል›› (1ና ጴጥ 2፡21) እንደተባለው እውነተኞቹ ሐዋርያት ክርስቶስን መስለውታል፤ ተከትለውታልም፡፡ እውነተኛ ሐዋርያ ክፉ ምኞትን የማይከተል፣ የዓለምን ጣዕም የማይከተል ሊሆን ይገባዋል፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድና የዓለምን ጣዕም አብሮ መከተልም አይቻልም፡፡ ሐዋርያ ገንዘብንም አይከተልም፡፡ ሐዋርያ አርአያ ሆኖ ሌሎችን ወደ እግዚአብሔር የሚመራ መንፈሳዊ መሪም ጭምር ነው፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን ሲከተል ጌታችን በደብረታቦር ብርሃነ መለኮቱን ገልጾለታል፡፡ በደብረ ዘይት ተራራም ነገረ ምጽአቱን ሰምቶ፣ በጸሎተ ሐሙስም በጌታ እግሩን የታጠበ ሐዋርያ ነው፡፡ ጌታችን በተያዘባት በዚያች ሌሊት ግን ጌታን አላውቀውም ብሎ ሦስት ጊዜ ክዶታል፡፡ ነገር ግን አምርሮ በማልቀሱ ጌታችን ወደ ቀደመ ክብሩ መልሶት በጥብርያዶስ አደራን ተቀበለ፡፡ በበዓለ ሃምሳም በአንድ ትምህርት ሦስት ሺ ሰዎችን አሳምኖ ተጠምቀዋል፡፡ ጌታችንን አምኖ የሚከተል ቢወድቅም እንኳን በንስሐ ተነስቶ ይደምቃል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ጌታን ተከተለ፡፡ በግብር በአገልግሎት ተከተለው፡፡ ጌታችን ዞሮ እንዳስተማረ ቅዱስ ጳውሎስም ዞሮ አስተምሯል፡፡ እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተ ደግሞ እኔን ምሰሉ ያለው እርሱ ክርስቶስን በሕይወት ስለተከተለው ነው፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችንን ‹‹ሁሉን ትተን ተከተልንህ፣ እንግዲህ ምን እናገኛለን?›› ሲል በጠየቀ ጊዜ ጌታም “የተከተላችሁኝ እናንተ በዳግም ልደት በ12ቱ ዙፋን ትቀመጣላችሁ፤በ12ቱም ነገደ እሥራኤል ትፈርዳላችሁ። ስለስሜም ቤትን፣ ወይም ወንድሞችን፣ ወይም እኅቶችን፣ ወይም አባትን፣ ወይም እናትን፣ ወይም ሚስትን፣ ወይም ልጆችን፣ ወይም ርስቱን የተወ መቶ እጥፍ ዋጋ ያገኛል” ብሎ መመለሱ እውነተኞቹ ሐዋርያት ያላቸውን ታላቅ ክብር ያሳያል (ማቴ. 19፡27-28)።

ሐዋርያ ማለት የሚጠብቅ (ጠባቂ) ማለት ነው፡፡

ሐዋርያ ማለት ጠባቂ ማለት ነው፡፡ የጌታውን በጎች፣ ጠቦቶች፣ ግልገሎች የሚጠብቅ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያ ጌታ በደሙ የዋጃትን ቤተክርስቲያንን የሚጠብቅ ታማኝ አገልጋይ ማለት ነው (ሐዋ 23፡20)፡፡ ተኩላ ሲመጣ በጎቹን ትቶ የማይሸሽ፣ ከተኩላም ጋር ተመሳጥሮ በጎቹን አሳልፎ የማይሰጥ፣ ራሱን ስለ በጎቹ አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ እውነተኛ ሐዋርያ ነው (ዮሐ 10፡11)፡፡ ሐዋርያ የእግዚአብሔርን በጎች ቃለ እግዚአብሔርንና የክርስቶስን ሥጋ ወደሙን እየመገበ የሚንከባከብና መንፈሳዊ ሕይወታቸውን የሚያሳድግ ነው፡፡ እውነተኛ ሐዋርያ በጎቹ በኃጢአት ቢታሰሩ በንስሐ የሚያስፈታ ታማኝ አገልጋይ ነው፡፡ እውነተኛ ሐዋርያ በጎቹን በስማቸው የሚያውቃቸው፤ በጎቹም ድምፁን የሚያውቁት ጠባቂ ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቸር ጠባቂ እንደሆነ (ዮሐ 10፡11) የእርሱም ሐዋርያት ቸር ጠባቂዎች ነበሩ፡፡ የጠባቂነቱን ኃላፊነት በቅዱስ ጴጥሮስ አማካኝነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ‹‹ምሳ ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ግልገሎቼን አሰማራ አለው።  ደግሞ ሁለተኛ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ጠቦቶቼን ጠብቅ አለው። ሦስተኛ ጊዜ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። ሦስተኛ። ትወደኛለህን? ስላለው ጴጥሮስ አዘነና። ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ኢየሱስም። በጎቼን አሰማራ። (ዮሐ 21፡15-17)

ሐዋርያ ማለት እንደራሴ (ተወካይ) ማለት ነው፡፡

ሐዋርያ ማለት በምድር ላይ ያለ የክርስቶስ እንደራሴ ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ካረገ በኋላ በምድር ላይ ያሉ ተወካዮች (ምስክሮች) ሐዋርያት ናቸው፡፡ ሐዋርያት የማሰር የመፍታት ስልጣንን የተሰጣቸው የክርስቶስ እንደራሴዎች ናቸው (ማቴ 18፡18)፡፡ እናንተን የተቀበለ እኔን ይቀበላል ያለውም ለዚህ ነው፡፡ በርኩሳን መናፍስት ላይ ስልጣንን የሰጣቸውም የእርሱ እንደራሴዎች ስለሆኑ ነው (ማቴ 10፡1)፡፡ ሕሙማንን በተአምራት እንዲፈውሱ ስልጣን የሰጣቸው፤ በደዌ የገባውን በተአምራት በክህደት የገባውን በትምህርት እንዲያስወጡ ስልጣንን የሰጣቸው፤ ሰውና እግዚአብሔርን የሚያስታርቅ ስልጣንን የሰጣቸው፤ በመጨረሻው ቀን (ባስተባሩት ወንጌል) የመፍረድ ስልጣን የሰጣቸው (ማቴ 19፡28) የእርሱ ተወካዮች ስለሆኑ ነው፡፡ ይህም ስልጣን ለሠሩበት ክብርን ያስገኘ ለማይሠበት ደግሞ የሚያስጠይቅ ነው፡፡

ሐዋርያት ጌታ በሰጣቸው ስልጣን ብዙ ተአምራትት አድርገዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በየስፍራው ሁሉ ሲዞር በልዳ ወደሚኖሩ ቅዱሳን ደግሞ ወርዶ በዚያም ከስምንት ዓመት ጀምሮ በአልጋ ላይ ተኝቶ የነበረውን ኤንያ የሚሉትን አንድ ሰው ፈውሶታል (ሐዋ.9፡32-33)።  በኢዮጴም ጣቢታ የሚሉአት አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፥ ትርጓሜውም ዶርቃ ማለት ነው፤ እርስዋም መልካም ነገር የሞላባት ምጽዋትም የምታደርግ ነበረች። በዚያም ወራት ታመመችና ሞተች፤ ጴጥሮስም ሁሉን ወደ ውጭ አስወጥቶ ተንበርክኮም ጸለየ፥ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ። ጣቢታ ሆይ፥ ተነሺ አላት። እርስዋም ዓይኖችዋን ከፈተች ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ተቀመጠች። እጁንም ለእርስዋ ሰጥቶ አስነሣት፤ ቅዱሳንንና መበለቶችንም ጠራ ሕያውም ሆና በፊታቸው አቆማት። (ሐዋ. 9፡36-41)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ታላላቅ ተአምራቶችና ድንቅ ያደርግ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፥ ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር (ሐዋ. 19፡11-13)። አውጤኪስ የሚሉትም አንድ ጎበዝ በመስኮት ተቀምጦ ታላቅ እንቅልፍ አንቀላፍቶ ነበር፤ ጳውሎስም ነገርን ባስረዘመ ጊዜ እንቅልፍ ከብዶት ከሦስተኛው ደርብ ወደ ታች ወደቀ፥ ሞቶም አነሡት። ጳውሎስም ወርዶ በላዩ ወደቀ፥ አቅፎም። ነፍሱ አለችበትና አትንጫጩ አላቸው። ወጥቶም እንጀራ ቆርሶም በላ፤ ብዙ ጊዜም እስኪነጋ ድረስ ተነጋገረ እንዲህም ሄደ። ብላቴናውንም ደኅና ሆኖ ወሰዱት እጅግም ተጽናኑ። (ሐዋ. 20፡7-12)

የቅዱሳን ሐዋርያት ክብር

ክርስትና ፈተናና መከራ የበዛበት ስለሆነ እውነተኛ ሐዋርያ ማለት በዚህ መከራ ውስጥ የሚጋደልና እርሱ ለክብር በቅቶ ሌሎችንም ለክብር የሚያበቃ ማለት ነው፡፡ የሐዋርያት አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ መከራን እንደተቀበለ እነርሱንም በምድር ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዞአችሁ ብሎ ተስፋን እንዲሰንቁ አስቀድሞ ነግሯቸዋል፡፡ ወንጌልን ስላስተማሩ የጨለማ ሥራ ይሠሩ የነበሩ ሥራቸው እንዳይገለጥባቸው ‹‹ብርሃንን ለማጥፋት›› ሲሉ ሐዋርያት ላይ መከራ አጽንተውባቸዋል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ በእሥር ተንገላተዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በድንጋይም ተወግሯል፡፡ እነዚህ ሁለቱ የቤተክርስቲያን አዕማድ የሆኑት ሐዋርያት ያረፉትም በሰማዕትነት ነው፡፡ ሁለቱም ያረፉት በ67 ዓ.ም. ኔሮን ቄሣር በቅድስት በቤተክርስቲያን ላይ መራር ትእዛዝን ባስተላለፈበት ዘመን ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ቁልቁል ተዘቅዝቆ በመሰቀል፥ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ በ74 ዓመት ዕድሜው በሮም ከተማ በኦስትያ መንገድ አንገቱን ተሰይፎ ክብረ ሰማዕትነት ተሸልመዋል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ አስቀድሞ ስለዚህ የሰማዕትነት ክብር ሲናገር ‹‹በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል። መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም (2ኛ ጢሞ 4፡6-8)›› ብሏል፡፡ ቤተክርስቲያናችንም እነዚህን ሐዋርያት ሁል ጊዜ ታስባቸዋለች፡፡ ቤተክርስቲያን የሐዋርያትን ክብር የምታስበው በሐዋርያት ጾምና በበዓለ ሐዋርያት ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ ባለው ቅዳሴ ነው፡፡ በቅዳሴው ሁሉ ከሐዋርያት መልእክት ሁለት እንዲሁም ከሐዋርያት ሥራ የዕለቱን ክፍል እያነበበች መልእክታቸውንና አገልግሎታቸውን ታስባለች፡፡ ለምሳሌ ከቅዳሴው የሚከተለውን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስ ሠናየ መልእክት ፈዋሴ ዱያን ዘነሣእከ አክሊለ ሰአል ወጸሊ በእንቲአነ ያድኅን ነፍሳተነ በብዝኃ ሣህሉ ወምሕረቱ በእንተ ስሙ ቅዱስ” (ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስ መልእክትኽ የበጀ ያማረ ድውያንን የምታድን አክሊልን የተቀበልክ ሆይ በይቅርታውና በቸርነቱ ብዛት ስለ ቅዱስም ስሙ ሰውነታችንን ያድን ዘንድ ስለኛ ለምን ጸልይም)

ተውህቦ መራኁት ለአቡነ ጴጥሮስ ፣ ወድንግልና ለዮሐንስ ወመልእክት ለአቡነ ጳውሎስ እስመ ውእቱ ብርሃና ለቤተ ክርስቲያን” (ለአባታችን ለጴጥሮስ መክፈቻ ፣ ለዮሐንስም ድንግልና ፣ ለአባታችን ለጳውሎስም የቤተ ክርስቲያን ብርሃኗ ርሱ ነውና መልእክት ተሰጠው)›› (መጽሐፈ ቅዳሴ)፡፡

 ቤተክርስቲያናችን ለቅዱሳን ሐዋርያት ያላትን ክብር ከምትገልጽባቸው መካከል አንዱ የሐዋርያትሥራ ከመነበቡ በፊት ካህኑ “ንጹሐን ከሚኾኑ ከሕግ ምንጮች የተገኘ ጥሩ ምንጭ፣ ይኸውም የሐዋርያት የሥራቸው ነገር ነው፤”ብሎ የሚያውጀው ይገኝበታል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት እንደዚህ ንጹሐን የሚሆኑ የሕግ ምንጮች፤ አገልግሎታቸውም ጥሩ ምንጭ ነው፡፡

እኛና ቅዱሳን ሐዋርያት

በዘመናችን ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚተጉ (በተለይ በክህነቱ) ሐዋርያት ናቸው፡፡ እነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ እነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ እነ አቡነ አረጋዊ የእኛ ሐዋርያት ነበሩ፡፡ ስልጣን ከኃላፊነትና ከተጠያቂነት ጋር የተሰጠው ለዚህም የሚተጋ እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊ አገልጋይ ዛሬም እንደ ጥንቱ ሐዋርያ ነው፡፡ ይህን ስልጣን የሰጣቸው አምላካችን እግዚአብሔር ስለሆነ ስልጣናቸውንና እነርሱን ልናከብር ይገባል፡፡ እግዚአብሔር አክብሮአቸዋልና፤ በማክበራችንም እንከብርበታለንና ማክበር ይኖርብናል፡፡ በዚህች ምድር ላይ ላሉ እውነተኞች የክርስቶስ ሐዋርያት ልንጸልይላቸውም ይገባል፡፡ የሃይማኖትን መንገድ ያቀኑ ዘንድ፤ ፈተና ይርቅላቸው ዘንድ በጸሎታችን ልናግዛቸው ይገባል፡፡ ቤተክርስቲያንም ይህ ጸሎት በቅዳሴው ጸሎት እንዲካተት ያደረገችው ለዚህ ነው፡፡ በአፀደ ገነት ያሉት ሐዋርያት በረከታቸው  እንዲደርሰን መታሰቢያቸውን ማድረግ፣ በምድር ያሉት ደግሞ ቡራኬያቸው እንዲደርሰንና በሄድበት ሁሉ እንዲጠብቀን ጸሎታቸውን መሻት ያስፈልገናል፡፡ የአገልግሎታቸውንም ዋጋ ማስተዋል ይገባናል፡፡ በህፃንነት ብንጠመቅ በካህን፣ በወጣትነት ተክሊል ብናደርግ በካህን፣ ከዚህ ዓለም በሞት ብንለይ ጸሎተ ፍትሐት የሚደርስልን በካህን፣ የኃጢአት ሥርየት የምናገኘው በካህን፣ ሥጋውንና ደሙን ብንቀበል በካህን፣ በደዌ ብንያዝ መንፈሳዊ ሕክምና የምናገኘው በካህን ነውና የሐዋርያት አገልግሎት በሕይወታችን ያላቸው ዋጋ ታላቅ ነው፡፡

ሐዋርያዊት የሆነችው ቤተክርስቲያናችን ቅዱሳን ሐዋርያትን የምትዘክረው ስለብዙ ምክንያቶች ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የምታመልከው አምላክ መርጧቸው ተከትለውታልና እነርሱን ማከበር እርሱንም ማክበር ስለሆነ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ቅዱሳን ሐዋርያት ራሳቸው የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ሆነው የሐዲስ ቤተክርስቲያንን በምድር ላይ የመሠረቱት እነርሱ ናቸውና ቤተክርስቲያንም ራሷ የሐዋርያት ጉባዔ ናትና ሐዋርያትን ዘወትር ትዘክራቸዋለች፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ቤተክርስቲያን በአስተምህሮ የቅዱሳን ሐዋርያትን የመጻሕፍት ትርጓሜ፣ በክህነት አገልግሎት ከሐዋርያት በቀጥታ የመጣ የሲመት ሀረግ ስላላትና ራስዋም ሐዋርያዊት ስለሆነች ሐዋርያትን ትዘክራቸዋለች፡፡ አራተኛው ምክንያት ደግሞ በቤቱና በቅጥሩ የማያልፍ ስም ስለተሰጣቸው፣ በአስራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ እስከመፍረድ የሚደርስ ክብርና ስልጣን ስለተሰጣቸው በረከታቸው ይደርሰን ዘንድ እንዘክራቸዋለን፡፡ በመጨረሻም ወንጌል፣ ክርስትናና ቤተክርስቲያን 2ሺ ዘመናት አልፈው ከእኛ ዘመን የደረሱት በየዘመናቱ በነበሩት የሐዋርያት አገልግሎት ነው፤ በገሊላና በአካባቢዋ ብቻ ተሰብካ የነበረችው ወንጌል እስከ ዓለም ዳርቻ የደረሰችው በሐዋርያት አገልግሎት ነው፤ ብዙ ጻድቃን ሰማዕታት ሊቃውንትን ያፈራነው የሐዋርያት አገልግሎት ወደ ሕዝብ በመድረሱ ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን ሐዋርያት እነርሱ እየቀለጡ ለእኛ ያበሩልን ስለሆኑ የክርስትናችንን ነገር ስናስብ እነርሱን ዘወትር እንዘክራቸዋለን፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን ሐዋርያት በረከት አይለየን፡፡

ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር፡ ርስታችንን አጥብቀን እንያዝ (ክፍል ፬)

እንዴት እንዘምር?13322084_1095910523807229_7837358580726615838_n.jpg

ባለፉት ሦስት ተከታታይ ክፍል የመዝሙርን ምንነትና ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ምን መምሰል እንደሚገባው አውስተናል:: አስተምህሮ በዚህ አራተኛና የመጨረሻ ክፍል ኦርቶዶክሳዊ መዝሙርን እንዴት መዘመር እንዳለብን በመጠቆም ከአዘማመር ጋር በተያያዘ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋሉ ችግሮችን ታሳያለች፤ መፍትሔዎችንም ትጠቁማለች፡፡

መዝሙር ጸሎት ስለሆነ በማስተዋል በእምነት ልንዘምር ይገባል

መዝሙር ስንዘምር ዜማውን ብቻ በማሰላሰል ሳይሆን የመዝሙሩን ምስጢር አውቀን በእምነት ሊሆን ይገባል:: “አምናችኹም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ” እንደሚል (ማቴ ፳፩:፳፪):: ስንዘምር ልባችን ወደ ሌላ ሃሳብ ተወስዶ በሥጋዊ ስሜት የሚቀርብ ከሆነ የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ እንደማንሳት እንዲሁ በከንፈር ማክበር ብቻ ይሆንብናል (ዘጸ ፳:፯ ኢሳ ፳፱:፲፫):: ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል” (ሉቃ ፲፱:፳፭) እንዳለን ህሊናችን ወደ ሌላ ሃሳብ እንዳይወሰድ ልቡናችንን እየሰበሰብን መዝሙሩም የምእመናንን ልብ ለቃለ እግዚአብሔር የለሰለሰ እንዲሆን የሚያዘጋጅ መሆን አለበት:: መዝሙር ለመላእክትና በመንፈሳዊ ተጋድሎ ላሉ ምግባቸው እንደሆነ ሁሉ በፍጹም እምነት ሳናወላውል ልቡናን በመሰብሰብ ይህን ስጦታ የምንመገበው እግዚአብሔር አምላክ ድካማችንን አለማመናችንን እንዲረዳው በመማጸን ነው::

ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በእምነት ባለማወላወል ወደ እግዚአብሔር ብንቀርብ ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ ለምነን የምናጣው እንደሌለ ይነግረናል (ያዕ ፩:፮-፰):: ስለሆነም መዝሙር ስንዘምር በልማድ ቃላትን በመደጋገምና ለመርሃ ግብር ማሟያ ለይስሙላ ሳይሆን በእምነትና በተመስጦ መዘመር ይገባል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከአገልግሎታችን ሁሉ በላይ ዝማሬያችንን በእምነት ሲሆን ደስ ያሰኘዋል (ዕብ ፲፩:፮):: ለምሳሌ በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በዓል ሠለስቱ ደቂቅን ከእቶን እሳት እንዳዳናቸው እኛም ከበዓሉ በረከትን እንዲሰጠን ስንለምን (ስንዘምር) እንደ ሦስቱ ህጻናት ባለመጠራጠር በእምነት ለዚያም በሚያበቃ ተጋድሎ እንዲሆን ያስፈልጋል:: በሌላም የጌታችንን መድኃኒታችንን ስቅለት እያሰብን ስንዘምር ክርስቶስን በእውነት የተከተሉትን እያሰብን እኛም በጊዜውም ያለጊዜውም በመታመን በቀራንዮ የነበረውን በህሊናችን እየሳልን ነው (ገላ ፫:፩)::

መዝሙር መስዋዕት ስለሆነ በንጹህ ልብ ሊቀርብ ይገባል

ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መስዋዕት ስለሆነ በልዑል እግዚአብሔር ፊት የተወደደ መስዋዕት ሁኖ እንዲቀርብ ራስን ለንስሐ በማዘጋጀት ልቡናን በማንጻት ሕይወታችንን ልዑል እግዚአብሔር የሚቀበለው እንዲሆን በማድረግ ሊሆን ይገባል:: መዝሙረኛው ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።” እንዳለ የዝማሬ መስዋዕታችን ንጹሕ ልብን እንዲሰጠን የቀናውንም መንፈስ በልቡናችን እንዲያኖርልን በመማጸን ነው (መዝ ፶:፲-፲፯ ሉቃ ፲፰:፲-፲፬):: እግዚአብሔር ትሁትና የዋህ በሆነ በተሰበረ ልብ የሚቀርብን ዝማሬ ይመለከታል:: ከቃየልና አቤል መስዋዕት የምንማረው እግዚአብሔር አምላክ ወደ መስዋዕቱ እንደተመለከተና የአቤልን መስዋዕት ንጹህ መስዋዕት አድርጎ እንደተቀበለ ነው::

እኛም በዝማሬያችን በአንድ ልብ በንጹህ ህሊና ቁመት ዝማሬያችንንም መስዋዕት አድርገን ከማቅረብ አስቀድሞ ይህን እግዚአብሔር አምላክ እንደሚፈልግ መዘንጋት የለብንም (ሐዋ ፬:፴፬):: ይህም እግዚአብሔር አምላክ ፊቱን ወደኛ እንዲመልስ የሚያደርግ ጸጋንም የሚያሰጥ ነው (፩ጴጥ ፭:፭):: በግርግር በሁከት በመገፋፋት በመለያየት በድፍረት በራስ ሃሳብ/ፈቃድ በመወሰድ ጸጋ አይገኝም (ዕብ ፲፪:፳፰-፳፱ ፪ቆሮ ፲፫:፭ ሚክ ፮:፮-፰ ሮሜ ፮:፩):: “ለአንዱ ተስፋችሁ እንደ መጠራታችሁ መጠን አንድ አካልና አንድ መንፈስ ትሆኑ ዘንድ እማልዳችኃለሁ” (ኤፌ ፬:፬):: ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሰውነታችንን በአገልግሎታችን ወቅት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርገን ልናቀርብ በዝማሬያችንም ወቅት መዘመራችንን ብቻ ሳይሆን የእኛን ልብ የሚመረምር አምላክ ፊት እንደቆምን በማስተዋል ሊሆን እንዲገባ ያሰተምረናል (ሮሜ ፩፪:፩-፭)::

መዝሙር እግዚአብሔር የሚወደው ንጹህ መስዋዕት ሁኖ ሳለ አንዳንድ መዝሙር ተብለው በሚዘመሩት ዝማሬዎች ፉከራ ያለባቸው የራሳችንን ድካም ኃጢአት የምንመለከትበት ሳይሆን ሌሎችን ብቻ የምንኮንንበት ወይም “የእኛ ይሻላል ከሌላ” የሚል ስሜት ባለበት ሲቀርብ በልዑል አምላክ ፊት መቆማችንን የዘነጋን ያደርገናል:: ክርስትና የራስን በደል እያሰቡ ለሌላውም መልካምን የምንመኝበት ልቡናን ከፍ ከፍ በማድረግ (በመንፈሳዊ ዝግጅት)  የምንኖረው ሕይወት እንጂ በሕይወታችን ስንዝል በሚሰማን ጊዜያዊ ስሜት ወድቀን ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መስዋዕትን ሳይሆን ስሜታችንን ብናንጎራጉር ራሳችንን እናታልላለን:: ቅዱሳት መጻሕፍት የሚያስተምሩን ‘እዘምራለሁ ንጹሕ መንገዱንም አስተውላለሁ” (መዝ ፻:፪) “በስፍራ ሁሉ ያለቍጣና ያለክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሱ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ” (፩ጢሞ ፪:፰) የሚለውን ነው:: ስለሆነም መዝሙራችን ከተነሳሂ ልቡና የሚወጣ፣ ተናጋሪውንም አድማጩንም ወደ ንስሃ የሚመራ መሆን አለበት፡፡

በአንዳንዶች ዘንድ ልማድ እንደሆነው በክርስቶስ ጸጋ ያገኘነውን የመዳን ሕይወት በራሳችን የተለየ ችሎታ ያገኘነው አስመስለን በመዝሙራችን ሌሎችን ማቃለል አይገባም፡፡ ይልቁንስ እንደ አባቶቻችን በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የየራሳችንን መዳን እንፈጽም ዘንድ በምስጋናና ራስን ዝቅ በማድረግ እግዚአብሔርን ልናመሰግን፣ ትምህርተ ሃይማኖትን ልንመሰክር ይገባል፡፡ ትህትናችን ግን ባለማወቅ መጻሕፍትን የሚተረጉሙ ሰዎች እንደሚመስላቸው ክርስቶስን የሚቃወሙትን፣ ቤተክርስቲያንን የሚያቃልሉትን፣ የሚዘርፉትን የሚያበረታታ ወይም “የማይሞቀው፣ የማይበርደው” መሆን የለበትም፡፡ መዝሙራችን ትምህርት ነውና ሰውን በሚያንጽ መልኩ፣ በፍቅር አንድ በሆነ መንፈስ በንጽህና የሚገባውን ክብር እየሰጠን ከተመላለስን በመካከላችን እንዲገኝ አምላካችን ለቃሉ የታመነ አምላክ ነው።

ዘማርያን (መዘምራን) የሚባሉት እነማን ናቸው?

በቤተክርስቲያናችን በቀዳሚነት በዝማሬ የሚታወቁት ቅዱሳን መላእክት ናቸው፡፡ እነርሱ ያለማቋረጥ “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” እያሉ በማይሰለች ልሳን፣ በማይጠገብ ዜማ አምላካችንን በሰማያት እንደሚያመሰግኑ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክሩልናል (ኢሳ ፮:፩-፬)፡፡ በሰማያዊ ልሳን ከቅዱሳን መላእክት ጋር እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት የሰማይ መንግስት ምሳሌ በሆነች ምድራዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን ሁሉ ዘማርያን፣ አመስጋኞች ናቸው፡፡ በተለየ ሁኔታ የቤተክርስቲያንን ዜማና አዘማመር የተማሩ ሊቃውንት መዘምራን ይባላሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሰንበት ት/ቤትና በልዩ ልዩ መንፈሳውያን ማኅበራት መዝሙር የሚዘምሩ ምዕመናን በሰንበት ት/ቤት ወጣት መዘምራን ይባላሉ፡፡ እንደዚሁም ኦርቶዶክሳዊ ዝማሬን በካሴትና በሲዲ እያዘጋጁ ለመንፈሳዊ ዓላማ የሚያውሉ ምዕመናንም እንዲሁ እየተለመደ ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊ ዘማሪነት ቀሚስ ከመልበስ፣ ፖስተር ከማሰራት፣ ድምጽን በካሴትና በሲዲ ከማስቀረጽ፣ ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ እነዚህ እንግዳ መገለጫዎች አንዳንድ አገልጋዮች ዘማሪነትን የገንዘብ ማግኛ ሙያ በማድረጋቸው ምክንያት ራሳቸውን ከሌላው ማኅበረ ምዕመናን ለመለየት የሚጠቀሙባቸው የንግድ ምልክቶች (trade marks) እንጅ ኦርቶዶክሳዊ ውርስ ያላቸው አይደሉም፡፡ በተለይም ዘማሪ በመባል ታዋቂነትን በማትረፍ (celebrity culture) ኦርቶዶክሳዊ መዝሙርን ብቻ ሳይሆን ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮንም ለሚቆሙለት ልዩ ልዩ ጥቅም፣ ክህደትና ምንፍቅና ሲሉ በመበረዝ ምዕመናንን ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች ከቤተክርስቲያን ማኅበር እየለዩ የሚያስኮበልሉ በበዙበት በዚህ ዘመን የዘማሪነት ግብር ትክክለኛ መገለጫዎችን መለየት ካልቻልን ለምዕመናንም በተገቢው መልኩ ካላስረዳን ታሪኩን የማያውቅ ትውልድ እንደማፍራት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ገንዘብን መውደድ የኃጢአት ሁሉ ስር እንደሆነና ይህንን የተመኙ ከሃይማኖት እንደወጡና ራሳቸውን በብዙ ስቃይ እንደወጉ ይመክረናል (፩ጢሞ ፮:፲ ቆላ ፫:፩-፫)::

ስለሆነም ዘማሪነትን ከንግድና ከታዋቂነት ገጽታ ግንባታ (celebrity culture) በእውቀትና በብልሃት መለየትና የሰይጣንን ተንኮል ማፍረስ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ከሚረዱን አሰራሮች መካከል አንዱ መዝሙራት በግለሰብ ባለቤትነት ከሚወጡ ይልቅ በሰንበት ት/ቤቶችና በማኅበራት እንዲወጡ በማድረግ ማንም የእኔነት ይዞ እንዳይመካባቸውና መውደቂያ እንቅፋትም እንዳይሆኑበት ማገዝ ይቻላል፡፡ እንደሚታወቀው ቅዱሳን መላእክትም ሆኑ አባቶቻችን መዘምራን መዝሙርን ለአምልኮና ለምስጋና በማኅበር ይዘምራሉ እንጂ አንድን ሰው በሚያገን ወይም ተከታዩን በሚያሰናክል መልኩ አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን አገልጋይ ዘማርያን በግል መዘመራቸው በራሱ ችግር ነው ማለት እንዳልሆነ ማስተዋል ይገባል፡፡ ዓላማውን ተረድተው፣ የቤተክርስቲያንን ትምህርትና ሥርዓት ጠብቀው፣ ለግል እውቅናና ጥቅም ሳይሆን ለቤተክርስቲያን ልዕልና የሚዘምሩትን በህሊና ዳኝነት እየተመራን ልናግዛቸው፣ ልናበረታታቸው ይገባል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በመዝሙር የሚያገለግሉ ሁሉ የቤተክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት አክብረው የሚያስከብሩ በሕይወታቸውም አርአያነት ያላቸው ሊሆኑ ይገባል:: አገልግሎቱን የሚሰጡ ለጸሎት የሚተጉ በሥርዓተ ቅዳሴ የሚሳተፉ ሕይወታቸው የሚያስተምር አለባበሳቸውና በሰውነታቸው ላይ የሚያኖሩት ጌጣ ጌጦች ግራ የሚያጋባ መሆን የለበትም:: ዛሬ ላይ እንደልማድ ተወስዶ በተለያየ ማህበራዊ ዝግጅቶች ላይ ዘማርያን ለሰማያዊው ዝማሬ ለታላቁ አገልግሎት ከተጠራን በኋላ ቀድመን ስንመላለስበት በነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደመከረን እንደክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ቤተ ክርስቲያንን በሚያስነቅፍ ሕይወት በዘፈኑ በስካሩ በጸብ በማይጠቅም የክርክር ሕይወት ልንታይ አይገባም (ቆላ ፪:፰ ያዕ ፫:፩ ሮሜ ፪:፳፩):: ሰይጣን ከመውደቁ በፊት አገልግሎቱ ምስጋና ነበር:: የሰው ልጅም እርሱ በለቀቀው አገልግሎት እንዳይሰማራ ሰማያዊ ከሆነው መዝሙር ይልቅ ሥጋዊ ስሜትን በሚጋብዝ ከስጦታችን ውጭ እንድንመላለስ ያለበረከት ያለዋጋ እንድንቀር በልቡናችን እንክርዳድን ይዘራል:: “አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን በኋላም የካዱትን እንደገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው” (ሮሜ ፮:፬-፮)::

አዘማመራችን የሚያስነቅፍ መሆን የለበትም

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎትን ያለሥርዓት መፈጸም እንደማይገባ ታስተምራለች፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓት ማለት በመጻህፍት የተጻፈ ብቻ ማለት አይደለም፡፡ በጽሑፍ ከተቀመጡ ሥርዓቶች ባሻገር በልማድ የዳበሩ ሕግጋት አሉ፡፡ ከአዘማመር እንቅስቃሴያችን ጋር የተያያዙ ችግሮች የሚፈጸሙት መዘምራን በግል ወይም በጋራ በሚዘምሩበት ወቅት ነው፡፡ ለምሳሌ ዓይን ጨፍኖ መዘመር፣ ያለ ልክ መጮህ፣ ከመጠን በላይ መዝለል፣ ከሚገባ በላይ እንቅስቃሴን ያካትታል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለፍጥረታት ሥርዓትን እንደሰራላቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የቆሮንቶስ ሰዎችን ያለሥርዓት በመሄዳቸው እንደገሰጻቸው እኛም እግዚአብሔር የሥርዓት አምላክ እንደሆነና በቤተክርስቲያን የሚከናወኑ አምልኮታዊ ሥርዓቶች አሰላለፋችንና እንቅስቃሴያችን እግዚአብሔር የሥርዓት አምላክ መሆኑን በመረዳት ወንጌልን የሚሰብክ በአገባብና በሥርዓት ሊሆን ይገባል (፩ቆሮ ፲፬:፵ መዝ ፻፵፪:፮ መዝ ፭:፫ ፩ቆሮ ፲፬:፵)::

በቤተክርስቲያናችን ልማድ በማኅሌትና በመዝሙር ወቅት ስሜታዊ የሚሆኑ አገልጋዮች ቢኖሩ እንኳ የቤተክርስቲያን አባቶች ጸናጽሉን በመጠቀም ምልክት እየሰጡ ያስቆሟቸዋል እንጅ ለነቀፋ አሳልፈው አይሰጧቸውም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያለአውዳቸው የሚጠቅሱ የሚቆነጻጽሉ ሰዎች ክቡር ዳዊት በታቦተ ጽዮን ፊት ራስን በመናቅ ከዘመረው መዝሙር ጋር በማስመሰል የዋሃንን ለማሳት ይሞክራሉ፡፡ ሰይጣን ሁልጊዜም ስህተቱን በቃለ እግዚአብሔር የተደገፈ ለማስመሰል እንደሚጥር ይታወቃል፡፡ እኛ ግን እናስተውል፣ ተመስጦና ራስን መናቅ ከስሜታዊነት ጋር አይገናኙም፡፡ ይልቁንም ተመስጦና ስሜታዊነት ተቃራኒዎች ናቸው፡፡ ክቡር ዳዊት በተመስጦ፣ ራስን ዝቅ በማድረግ ዘመረ እንጅ ስሜታዊ አልነበረም፡፡ መዝሙር ስንዘምር ሊኖረን የሚገባው ተመስጦ ብንችል አባታችን ቅዱስ ያሬድ በንጉሡ በአጼ ገብረመስቀል ፊት ሲዘምር በጦር መወጋትን እንኳ እስከማይሰማው ድረስ የተመሰጠውን ተመስጦ ሊመስል ይገባል፡፡

ስንዘምር ሰዎች ምን ይሉናል ብለን ለራሳችን ክብር ከተጨነቅን ለክቡር ዳዊት የተሰጠ ቡራኬ ይቀርብናል፡፡ በዝማሬያችን እግዚአብሔር አምላክ የብርሃን አምላክ ነው ስንል ዓይናችንን ወደ እርሱ በማቅናት (በመጨፈን ሳይሆን መዝ ፻፵፪:፮) በእንቅስቃሰያችንም መገፋቱን መከራ መቀበሉን ስንመሰክር መንፈሳዊ ዋጋም አለን:: ምድራዊ ሥርዓት ልዩ አሰላለፍና ክብር ካለው ለሰማይና ምድር ፈጣሪ የሚቀርበው መላው እንቅስቃሴያችን የድምጽ አወጣጣችን እንደአንድ ልብ መካሪ አንድ ሃሳብ ተናጋሪ ተጨንቀን ተጠበን ሊሆን ይገባል:: በዚህም እግዚአብሔር አምላክ የአቤልን መስዋዕት እንደተመለከተ የእኛንም በመዝሙር የምስጋና መስዋዕት ይቀበልልናል::

በመዝሙር ወቅት የዜማ መሣርያዎች አጠቃቀማችንና አያያዛችን እንዲሁም መዝሙሩን ከጨረስን በኋላ ስናስቀምጣቸው እንዲሁ በሥርዓቱ መሆን አለበት፡፡ በካህናት የማህሌት ዝማሬን ስንመለከት ካህናቱ ከበሮውን ሲመቱ እንዲሁ በዘፈቀደ ሳይሆን ምስጢርን ጠብቀው ሲጀምር በእርጋታ ምሳሌነቱም አይሁድ ጌታችንን እያፌዙ ለመምታታቸው ዝማሬው ተሸጋግሮ  በፍጥነት ሲመታም ሰንበት እንዳይገባባቸው በዚህም ጲላጦስም ምክንያትን አግኝቶ እንዳያድነው በማለት ያንገላቱበት ምሳሌ ነው:: “በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ። በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ” እንዲል (ቆላ ፫:፲፮)። የከበሮ ሰፊው አፍ (ገጽ)  የመለኮት ምሳሌ ነው ስላልን  ስናስቀምጥም አስተማሪነት እንዲኖረው ወደ ላይ መሆን አለበት:: ይህም ለሚመለከተው እንቅስቃሴያችን ድርጊታችን በመላው ሥርዓታችን ወንጌል የክርስቶስ መስቀል ሁኖ የተዋህዶን ምስጢር አስረጅ ለእኛም ለእግዚአብሔር ተብሎ የተለየን የዜማ መሳርያ የሚገባውን ክብር መስጠታችን ዋጋን የሚያሰጠን ነው::

በአጠቃላይ በዝማሬያችን የሌላውን ተመስጦ በማይነካ አንድ ወጥ በሆነ የእንቅስቃሴ ስልት በሙሉ ስሜታችን ይህን ታላቅ ምስጢር እያስተዋልን የመዝሙሩን ባለቤት ልዑል እግዚአብሔር መዝሙሩን በአንደበታችን እንዳኖረልን ተገንዝበን ልንዘምር ይገባል (ያዕ ፩:፰):: ሌላው በመዝሙር አገልግሎት ልናስተውል የሚገባን የምንዘምረው መዝሙር ወቅቱን የጠበቀ መሆኑን ነው:: ቤተክርስቲያን ሁሉ ነገሯ ሥርዓት ነውና ዓመቱን በዘመናት ከፍላ ለምስጋናም የሚስማማውን ሰርታ አዘጋጅታለች:: በሃይማኖት ጸሎታችን አንዲት ቤተክርስቲያን ብለን እንደመሰከርን ወቅቱን ጠብቀን ከዕለቱ ጋር የሚስማማውን ብንዘምር የአባታችንን ቤት ያወቅን ለእናታችን ቤተ ክርስቲያንም ታዛዦች ነን::

ማጠቃለያ

ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መስዋዕት እንጂ ለሰዎች የሚቀርብ ‘ዝግጀት’ አይደለም፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አምላክ የሥርዓት አምላክ ነውና ለእርሱም የሚቀርብ መዝሙር በሥርዓት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ቤተክርስቲያንም በሁሉ አገልግሎታችን እና ተሳትፎአችን መንፈሳዊ ዋጋ እንዲያሰጠን ዓመቱን በዘመናት ከፍላ በዝማሬያችንም ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት ባደረገና የቅዱሳን አባቶችን አሰረ ፍኖት በተከተለ አካሄድ ሰማያዊውን የዜማ ስልት ተከትለን አስተማሪነት ባለው ምስጋና እንድናመሰግን ሥርዓትን ሠርታልናለች:: እኛም በሁለንተናችን ትምህርቷን መስለን ለቤተክርስቲያንም ሥርዓት የመገዛት መንፈሳዊ ግዴታ አለብን:: በግልም ሆነ በማኅበር ስንዘምር ልናስተውላቸው የሚገቡንን እያስተዋልን፤ ዝማሬያችንም ፍጹም ለልዑል እግዚአብሔር የሚቀርብ ስለሆነ ‘መታዘዝ ከመስዋዕት ይበልጣልና’ በፍጹም ትህትናና በእምነት፤ ለቤተ ክርስቲያንም ሥርዓት በመታዘዝና ዋጋ የሚያሰጠን እንደሚሆን በማሰብ ሊሆን ይገባል:: የመዝሙሩ የምስጢር፣ ቅንብር እና የእንቅስቃሴ ስልት ምስጢሩን የጠነቀቀና ወቅቱን የጠበቀ ሆኖ የዝማሬም ሥርዓታችን ከቤተክርስቲያን ሥርዓት አንጻር በጾም በበዓላት በዘመናት መደብ ሰጥታ እንዳቆየችልን ሁሉ ሊዘመሩ የሚገባቸውን ዝማሬዎች እንደሥርዓቱ ልንከተላቸው ይገባል:: ለዚህም ሰንበት ትምህርት ቤቶች ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን  የተከተለ  የመዝሙር ሥርዓት እንዲኖር ትልቁን አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ::

ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን!