ሙዚቃና ዘፈን: የጽድቅ ሥራ ያልሆነ ሁሉ የኃጢአት ሥራ ነውን?

ምክንያተ ጽሕፈት

የዚህች ጦማር አዘጋጅ በአንድ ወቅት ከሙዚቃ ተመልሳ መዝሙር ያወጣችን እኅት የቪዲዮ መዝሙር እየተመለከተ ነበር። የቀድሞዋ ሙዚቀኛ የአሁኗ ዘማሪት በምትዘምረው መዝሙር ውስጥ የትናንት የሙዚቃ ሕይወቷ ከሁሉ የተለየ ፍጹም የኃጢአት፣ የክህደትና የሞት መንገድ እንደነበር አድርጎ ይኮንናል። ከዚያ ሕይወት ወጥታ ወደ ዘማሪነት መሸጋገሯ ደግሞ ከሲኦል አምልጦ ወደ ገነት የመግባት ያህል ተደርጎ ተስሏል። እኅታችንም በአደባባይ ከሰው ሁሉ የበለጠ፣ ከኃጢአት ሁሉ የከፋውን እንደፈጸመች ተደርጋ ቀርባለች። በወቅቱም ብዙ ሰው ”ሙዚቃ ተወች፣ መዝሙር አወጣች” የሚለውን በሰፊው ያወራ ነበር።

ይህ ክስተትና ከዚህ በፊትም የነበሩ ተመሳሳይ ክስተቶች በውስጣችን የሚፈጥሯቸው ብዙ ጥያቄዎች አሉ። የመጀመሪያው ሙዚቃ ሁሉ በእውነት ኃጢአት ነውን? ኃጢአትስ ቢሆን ከሌሎች ኃጢአቶች እንደዚህ ከፍቶ እንዲታይ ያደረገው ምንድን ነው? የሚለው ነው። ሁለተኛው ሙዚቀኞች በሙያቸው ስለሠሩ ስለምን እንደዚህ ርዕሰ ኃጢአትን የፈጸሙ ተደርገው እንዲሳሉ ይደረጋሉ? የሚለው ነው። ሦስተኛው ሙዚቀኞች ‘ሙዚቃ አቁመናል’ ባሉ ማግሥት አቻኩሎ በመዝሙር ወደ ዐውደ ምሕረትና ወደ ሚዲያ ማምጣቱ ለምን አስፈለገ? የሚለው ነው። አራተኛውና የመጨረሻው ሙዚቃ ትተው፣ ከንስሐ አባታቸው ዘንድ ንስሐቸውን ጨርሰው የሚዘምሩ ወንድሞችና እኅቶች ለምን እንደገና በሕዝብ ፊት በመዝሙር ሰበብ እንዲጸጸቱና እንዲያለቅሱ ይገደዳሉ? የሚለው ነው። በዚህች የአስተምህሮ ጦማር እነዚህን ነጥቦች እንዳስሳለን።

ሙዚቃ የሚለው ቃል በቀጥታ ትርጉም የመዝሙርና የአምልኮ ዜማን ሊጨምር ይችላል። ይሁንና በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ትውፊትና አስተምህሮ ለመንፈሳዊ ዓላማ የሚቀርቡ መዝሙራትና ልዩ ልዩ የአምልኮ ዜማዎች እንደየሀገራቱ ባሕል እና ልማድ አቀራረባቸው ቢለያይም እንደ ንጹሕ ዕጣን በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርቡ ልዩ መስዋዕቶች ናቸው። ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በአስተምህሮዋ ዓለማዊ ሙዚቃን (በተለይም ዘፈንን) ከመዝሙር ጋር አታምታታም። ስለሆነም በዚህች ጦማር ስለ ሙዚቃና ዘፈን የተጻፈው ዓለማዊ ይዘት ያላቸውን ብቻ የተመለከተ መሆኑን እንገልጻለን። በድፍረትም ሆነ ባለማወቅ መንፈሳዊ መዝሙርን ከዓለማዊ ሙዚቃና ዘፈን ጋር የሚያምታቱ ሰዎች ቅሰጣ ከጦማሩ ትኩረት ውጭ በመሆኑ በጥልቀት አልተዳሰሰም።

ሙዚቃ ሁሉ የኃጢአት ሥራ ነውን?

ይህንን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ስለሙዚቃ ጥቂት ማለት ያስፈልጋል። ሙዚቃ (Music) በመዝናኛ ዘርፍ ካሉ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች አንዱ ሲሆን፣ ማኅበረሰብ የራሱን ማንነት ከሚገልጥባቸው ማኅበራዊ እሴቶችም አንዱ ነው። ሙዚቃ ማኅበረሰቡ በሠርግ፣ በልደት፣ በንግሥ፣ በድል ቀን ወዘተ ደስታውን የሚገልጥበት፣ የታመቀ ስሜቱን እንዲሁም ብሶቱን የሚያንጸባርቅበት፣ የቆየ ትዝታውን የሚያስታውስበት፣ የሚገረምበት፣ የሚቆዝምበትና የተለያዩ ስሜቶቹን የሚገልፅበት ነው። ሙዚቃ ግጥም (መልእክት)፣ ዜማ (ድምፅ) እና መሣሪያ ያለው ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ ስልት ያለው እንቅስቃሴንም ሊያጠቃልል ይችላል። በሙዚቃ ሥራ ውስጥም የግጥም ደራሲዎች፣ የዜማ ደራሲዎች፣ ድምፃውያን፣ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች፣ የቀረፃና የቅንብር ባለሙያዎችና ሌሎችም እንደሚሳተፉበት ይታወቃል።

ሙዚቃው ከታተመ በኋላም ብዙ አካላት በሥርጭትም፣ በአድማጭነትም፣ መልሶ በማዜምም ይሳተፉበታል። ሙዚቃ በይዘቱም ብዙ ነገሮችን ይዳስሳል። ለምሳሌ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ማኅበራዊ ሕይወትን፣ ሀገርን፣ መልክአምድርን፣ ወዘተ ይገልጻል። ሙዚቃ በድምፅ እና ወይም በምስል ተቀርፆ ሰዎች በሚዲያ ወይም በራሳቸው ጊዜ እንደሚያዳምጡት እና ወይም እንደሚመለከቱት ይታወቃል። ከቅርብ ዘመናት ወዲህ ደግሞ ከሩቅም ሆነው በቀጥታ ለሙዚቃ ዝግጅት የሚታደሙ አሉ። እንዲሁም ብዙ የተለመደው የሙዚቃ ዝግጅቱ የሚቀርብበት ቦታ በአካል ተገኝቶ ማድመጥ፣ መመልከት፣ እንዲሁም መሳተፍ ነው። ሙዚቃን በሆቴሎች፣ በሱቆች፣ በትራንፖርትና በተለያየ ቦታ ልንሰማው እንችላለን። በዚህም ሙዚቃ ከማኅበረሰብ ባሕል ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑ የታወቀ ነው።

በመሠረታዊነት ሙዚቃ የኪነ-ጥበብ ሥራ እንጂ የጽድቅ ሥራ ነው የሚል አስተምህሮ አላጋጠመንም። ነገር ግን የጽድቅ ሥራ ያልሆነ ሁሉ የኃጢአት ሥራ ነው ማለት አይደለም። ለምሳሌ ስፖርት የጽድቅ ሥራ አይደለም፣ የኃጢአት ሥራም አይደለም። ሙዚቃም እንዲሁ ነው። ነገር ግን ይህ ማለት ሙዚቃ የኃጢአት ሥራ ሊሆን አይችልም ማለት አይደለም። መታየት ያለባቸው ሦስት መስፈርቶች ሊኖሩ ይገባል። የመጀመሪያው መልእክቱ (Lyrics/Themes) ነው። የሙዚቃው ግጥሞችና እንቅስቃሴዎች የሚያስተላልፉት መልእክት ምንድን ነው የሚለውን ማጤን ያስፈልጋል። ሁለተኛው ዓላማው (Intention) ነው። ሙዚቃው የሚቀርብበት (የምንሰማበት) ዓላማ ምንድን ነው የሚለውን መጠየቅ ያስፈልጋል። ሦስተኛው ሙዚቃው የሚቀርብበት ዐውድ (context) ነው። ሙዚቃውን የምንሰማበት ዐውድ ወደ ኃጢአት ሊመራን ይችላልና ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል። እነዚህ ነጥቦች ከመንፈሳዊ አስተምህሮም ይሁን ከማኅበረሰቡ እሴቶች አንጻር ታይተው እያንዳንዱ ሰው የራሱን ውሳኔ ሊወስን ይችላል።

በሚገባ ባልተለየ ብያኔ ሙዚቃና ዘፈንን እያምታታን የምንረዳው ከሆነ ከቅዱሳት መጻሕፍት የዘፈን ክልከላ ዓላማም ሆነ ከአመዛዛኝ አእምሮ ከሚጠበቅ ሚዛናዊ እይታ ይጋርደናል። ለምሳሌ አንድ ማሲንቆ ወይም ዋሽንት የሚጫወትን ምዕመን እንመልከት። ሙያውን ለመንፈሳዊ ዓላማ ሲያውለው ጽድቅ፣ ላልተቀደሰ ዓላማ ሲጠቀምበት ግን በደል ሊሆንበት ይችላል። ይህ መመዘኛ ለጥበቃ ሰራተኛውም፣ ለጽዳት ሰራተኛውም፣ ለኤዲቲንግ ባለሙያውም፣ ለሌላውም የሚሰራ እንጂ በተለየ ሁኔታ ለማሲንቆ ተጫዋቹ ወይም ለድምጻዊው ብቻ የሚሰራ ከመሰለን የሰዎችን ጽድቅም ሆነ ኃጢአት የምንመዝንበት መለኪያ የተሳሳተ ሳይሆን አይቀርም። በሙዚቃ ውስጥ ግጥም አለ። ግጥም የሌለው ሙዚቃ የለም። አንባቢ ሆይ ገጣሚን በገጣሚነቱ የኃጢአት ወይም የጽድቅ ስራ እንደሰራ መቁጠር ተገቢ ነው ብለህ/ሽ ታስባለህ/ታስቢያለሽ? ሙዚቃም እንዲሁ ነው። ሙዚቃን ጽድቅም ሆነ ኃጢአት የሚያደርገው ከላይ የተብራሩት መመዘኛዎች እንጅ ሙያው ራሱ አይደለም።

በዚህም መነሻነት ስለ ሰላምና ፍቅር፣ ሀገርና መልክዓምድር፣ ሥራና ክብር፣ እንዲሁም ስለተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች የሚያወሱና የማኅበረሰብን ባሕል የሚገልጡ፣ ማኅበረሰቡ ደስታውን (በሠርግ፣ በልደት፣ በዓመት በዓል ቀን፣ በንግሥ ቀን ወዘተ) ለመግለጥ የሚጠቀምባቸው ሙዚቃዎች ማኅበራዊ እሴቶች ናቸው። በራሳቸው ጽድቅም ኃጢአትም ናቸው ማለት አይቻልም። ለምሳሌ የእናት ውለታዋ፣ እንቁጣጣሽ እንኳን መጣሽ፣ ቢማማር ቢረዳዳ፣ ሀገሬ ኢትዮጵያ፣ ማን እንዳገር፣ በይ እንሂድ ሐረር እና የመሳሰሉት የሙዚቃ ሥራዎች ጥሩ ማኅበራዊ እሴቶች ናቸው። እነዚህም ማንንም ወደ ኃጢአት ሥራ እስካልገፉ ድረስ ይልቁንም ለማኅበራዊ አብሮነትና ለሥራ እስካነሳሱን ድረስ ታላቅ ማኅበራዊ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል። የሙዚቃ ሥራዎች ማኅበራዊ እሴት የሚሆኑት ግን ከማኅበረሰቡ ባሕል እስካላፈነገጡ ድረስ ብቻ መሆኑን ማስተዋል ይገባል።

ይልቁንም አንዳንድ በቅርብ ጊዜ የሚወጡ የአማርኛ መዝሙራት የግጥም ይዘታቸው ከሙዚቃ ብዙም ያልራቀ ነው። ወጥቼ ወርጄ፣ ወድቄ ተነስቼ፣ ደህይቼ ከብሬ፣ ነጥቼ ጠቁሬ፣ ከስቼ ወፍሬ ወዘተ የሚል መልዕክት ያላቸው ግጥሞች ከብዙ የሙዚቃ ግጥሞች ሲወዳደሩ በመልዕክትም በኪነ-ጥበባዊ ጥራታቸውም ያልተሻሉ ናቸው። በቪዲዮ የሚያሳዩትም የዘማሪውን አለባበስና ተክለ ሰውነት፣ አዲስ ቤት፣ ዘመናዊ የቤት ዕቃዎች፣ መኪና ወዘተ ናቸው። ከዜማ አንጻርም ከታየ ጥቂት የማይባሉ መዝሙራት ዜማቸው ከሙዚቃ ብዙም የራቀ አይደለም። አንዳንዶቹም ከሙዚቃ የተወሰዱ መሆናቸው የታወቀ ነው። ብዙ የሙዚቃ መሣሪያዎችም ለመዝሙርም ይውላሉ። ይህ በሆነበት ሁኔታ ሙዚቃ የሚመስሉ ‘መዝሙራት’ እንደ ጽድቅ አገልግሎት ተቆጥረው ብዙ ማኅበራዊ እሴት ያላቸው የጥበብ ሥራዎች ‘ኃጢአት ናቸው’ ተብለው የሚወገዙበት ምክንያት አሳማኝ አይመስለንም።

የቅዱሳት መጻሕፍትን የዘፈን ክልከላ ያለ ዐውዱ በመረዳት እንዲሁም ሙዚቃና ዘፈንን በማምታታት ሁሉንም ሙዚቃና ሙዚቀኞችን በተለየ ሁኔታ በኃጢአተኝነት የሚፈርጁ ሰዎችና ስብስቦቻቸው ኃጢአት ብለው የፈረጁትን ሙዚቃ በመኮረጅ ቀባብተው እያቀረቡ “አሁን የተቀደሰ መዝሙር ሆነ” ዓይነት የግብዝነት ትንተና ሲሰጡ መስማት የተለመደ ነው። ለዚህም ማሳያ የሚሆኑን በአስተምህሮ ደረጃ ዘፈንን ከመዝሙር የሚለይበት ቀመርም ትውፊትም የተምታታበት የፕሮቴስታንት ስብስብና የተወሰነ ባሕልና ሃይማኖታዊ ስርዓትን የሚቀላቅለው የኢትዮጵያ ከተማ ቀመስ አዲስ “ኦርቶዶክስ ነኝ ባይ” ልማድ ናቸው። የፕሮቴስታንታዊ ልማዱ የአስተምህሮ ዘተዋሕዶ ትኩረት ስላልሆነና መጨበጫም ስለሌለው ለአንባብያን ህሊና አልፈነዋል። በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ የአንድ አካባቢ ባሕላዊ ሙዚቃዎችን በመጠነኛ ኩረጃ በመሸቃቀጥ “መዝሙር” ሆነዋል የሚባልበትን ልማድ ማስታወስ አንባብያን የዚህን ጦማር መልእክት በቀላሉ እንዲረዱት ሊያደርግ ይችላል። አንባቢ ሆይ አበባየሆሽ እና ሆያ ሆየ የሰፈር ህጻናት ወይም ወጣቶች በተከበረ ባሕላቸው ሲጫወቱት “ኃጢአት”፣ የመዘምራን ልብስ የለበሱ ሰዎች “remix” አድርገው ሲያቀርቡት “የተቀደሰ መዝሙር” ነው ብሎ መቀበል የሚችል አእምሮ አለዎት ወይስ ፍረጃውን የቅዱሳት መጻሕፍትን መሰረታዊ ጭብጥ በተረዳ አመክንዮ ለመመርመር ዝግጁ ነዎት?

አንባቢ ሆይ! በአማርኛ ቋንቋ የተግባቦት ልማድ ለጠቃሚ ማኅበራዊ ዓላማ የሚውሉ ሙዚቃዊ ሥራዎችን “መዝሙር” እያሉ የመጥራትን ልማድ አስተውለው ይሆን? ለምሳሌ የሀገራት ብሔራዊ መዝሙርን፣ የህጻናት መጫወቻ መዝሙርን፣ የትራፊክ አደጋና ልዩ ልዩ በሽታዎችን በተመለከተ ማኅበረሰባዊ ግንዛቤን ለማሻሻል የሚቀርቡ መዝሙራትን መጥቀስ እንችላለን። መዝሙር ማለት ምስጋና ማለት ነውና እነዚህ ሙዚቃዎች “መዝሙር” እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። ታዲያ ለምን “መዝሙር” እያልን እናዋድዳቸዋለን? በእኛ ምክንያታዊ ግምት (reasonable guess) የዚህ ልማድ መነሻ ሙዚቃና ዘፈንን ቀላቅሎ ኃጢአት ያልሆነውን እንደ ዋና ኃጢአት እንዲቆጠር ካደረገው አዳፍኔ ፍረጃ (hasty generalisation) ለማምለጥ በነሲብ (unconsciously) የተፈጠረ ይመስላል።

ይህንን ስንል ግን የሙዚቃ ሥራ እንደማንኛውም የጥበብ ሥራ ለኃጢአት ሥራ አይውልም እያልን አይደለም። አንዳንድ የፊልም (ልቅ ፊልሞች አሉ)፣ የተውኔት (ብልግና ያለባቸው አሉ)፣ የኮሜዲ (ለማሳቅ ብለው ዝሙት ነክ ቀልድ፣ ማኅበረሰብን የሚያሳንስ ቀልድ የሚቀልዱ አሉ)፣ የስዕል (ሰውን አራቁተው የሚስሉ አሉ) ወዘተ ሥራዎች ወደ ኃጢአት ሊገፉ እንደሚችሉ ሁሉ አንዳንድ የሙዚቃ ሥራዎችም እንዲሁ ያደርጋሉ። ብዙ ለመዝናኛነት የሚውሉ የጥበብ ሥራዎች የሰውን በሥራ የደከመ አእምሮ እያዝናኑ የማነቃቃት አቅምም አላቸው። በአንጻሩም የሰውን አእምሮ ለዝሙትና ለሌሎች ኃጢአቶች የሚያነሳሱም አሉ። የሚበጀውን የጥበብ ሥራ መሥራት የባለሙያዎቹ፣ የሚበጀውን መርጦ ማድመጥ ወይም መመልከት ወይም ጭራሹንም አለመመልከት የእያንዳንዱ ግለሰብ ውሳኔ ነው። ከዚህ ውጭ ከብዙ የጥበብ ሥራዎች ሙዚቃን ብቻ ለይቶ በጅምላ ኃጢአት ነው ብሎ ለመበየን፣ ወይም ሙዚቀኞችን ብቻ ነጥሎ ኃጢአተኞች ናቸው ብሎ ለመፍረድ አንችልም። የሙዚቃን መልእክት፣ ዜማ፣ ዓላማና ዐውድ መንፈሳዊ ሕይወትን የሚጎዳ ከሆነ ልንተወው ይገባል። ይህ ማለት ግን ሌላው ሙዚቃ ለመንፈሳዊ ሕይወት ይጠቅማል ማለት አይደለም ለሥጋዊ ሕይወት እንጂ።

ዘፈን የኃጢአት ሥራ ነውን?

ዘፈን (Orgies/revelries) እንደ አንድ የሙዚቃ አካል ቢታይም የራሱ የተለየ ባሕርይ አለው። ዘፈን በርከት ያሉ ሰዎች ተሰባስበው እየበሉና እየጠጡ በሙዚቃ አውራጅ እየተመሩ የሚጨፍሩበት ሁኔታ ነው። ስለዚህም ጭፈራን፣ ስካርን እና ሌሎች የሥጋ ምኞቶችን (ለምሳሌ መዳራትን) ያካትታል። በጥንት ዘመን የጣኦት አምልኮንም ያካትት ነበር። ይህም የሄሮድያዳ ልጅ በሄሮድስ ፊት ዘፍና የዮሐንስን አንገት እንዳስቆረጠችው ነው። “ነገር ግን ሄሮድስ የተወለደበት ቀን በሆነ ጊዜ፥ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ዘፈነች ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤ ስለዚህም የምትለምነውን ሁሉ እንዲሰጣት በመሐላ ተስፋ አደረገላት። እርስዋም በእናትዋ ተመክራ። የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ በወጭት ስጠኝ አለችው። ንጉሡም አዘነ፥ ነገር ግን ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ተቀምጠው ስላሉት ሰዎች እንዲሰጡአት አዘዘ” (ማቴ 14:1-12)። በዘመናችንም ዘፈኖችን በምሽት ክለቦች የዝሙት መንደርደሪያ፣ የአሥረሽ ምችው ማጀቢያ ይደረጋሉ። በጦርነትም ወቅት ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማነሳሳትና ለማጋጨት ሲውሉ ይስተዋላል። ሙዚቃን ለእነዚህ እኩይ ዓላማዎች መሥራት ወይም መጠቀም ኃጢአትንና ሞትን እንደሚያስከትል ማንም ሊስተው አይገባም።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በገላትያ መልዕክቱ (ገላ 5:19) ከሥጋ ሥራዎች መካከል “ዘፋኝነት” (አሥረሽ ምቺው) ብሎ የገለጸው ለዚህ ነው። እዚህ ላይ ማስተዋል የሚያስፈልገው ሐዋርያው የገለጠው ዘፋኝነት በምሽት/በክለብ/በwild Parties ከመጠጥ/ከስካር ጋር ሰው አእምሮውን ስቶ በኃጢአት የሚወድቅበትን በጋራ የሚደረገውን ሥርዓት የለሽ ጭፈራ (አሥረሽ ምቺው) መሆኑን ልብ ይሏል። በዚህ መሠረት በግል (በቤት ውስጥ) የሚዜመው፣ በመርኃግብሮች መካከል በመድረክ የሚቀርበው፣ በካሴት የተቀረጸው፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የሚተላለፈው፣ በአንተርኔት የሚጫነው ሙዚቃ ለዘፈን ዓላማ እስካልዋለና ሰውን ወደ ሥጋ ፈቃድ (በተለይም ዝሙትና ጣኦት አምልኮ) እስካልመራ ድረስ ማኅበራዊ እሴት እንጂ ኃጢአት ሊባል ይችላል የሚል ቀላልና ቀጥተኛ ድምዳሜ መድረስ ፍርደ ገምድልነት ይመስላል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና (1ኛ ጴጥ 4:3)” ሲል የተናገረው ሰውን ወደ ኃጢአት በመምራት ከእግዚአብሔር መንግስት የሚለየውን ዘፈን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ዘፈንን ሲጠቅስ አብሮ ስካርንና መዳራትን ያስቀምጣል። ይህም በግልጽ ዘፈን ከሙዚቃ እንደሚለይ ያሳያል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ “በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን (ሮሜ 13:13)” በማለት ከዘፈን መራቅ እንዳለባቸው አስተምሯል።

ታዲያ ሙዚቀኞች ለምን እንደዚህ ኃጢአተኞች ተደርገው ተሳሉ?

እውነት እንነጋገር ከተባለ ማንኛውንም የጥበብ ሥራ የሚሠሩ ወገኖቻችን የሙያውን ስነ-ምግባር ጠብቀውና የማኅበረሰቡን እሴቶች አክብረው እስከሠሩ ድረስ ከማንም የተለየ ኃጢአተኞች ተደርገው ሊቆጠሩ አይገባም። ምናልባትም የተሻሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ሌሎች ሰዎች የእነርሱን መልካም ሥራዎች ላልተገባ ነገር ከተጠቀሙም እነርሱ ዕዳ የለባቸውም። ተጠያቂ መሆን ያለበት ያለ አግባብ የተጠቀመው አካል ነው። ብዙ ሰው ሙዚቃቸውን እያዳመጠ ሲያሰኘውም እያንጎራጎረ ዝም ተብሎ ሙዚቀኞቹን ብቻ መኮነንም ጤነኝነት አይመስለንም። እንዲሁም ጭፈራ ቤት የሚሄደውን፣ በሱስ የሚጠመደውን፣ በዝሙት የሚወድቀውን ማስተማር ትተን ሙዚቀኞችን መኮነን አግባብ አይሆንም።

ታዲያ ለምን ድምፃውያኑ ዒላማ ተደረጉ የሚል ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል። ይህ በአብዛኛው የሙዚቃንና የዘፈንን ልዩነት አጥርቶ ካለማወቅ የሚመነጭ ነው። የትኛው ሙዚቃ ማንን እንዳሰናከለ፣ ምን ያህል ሰው እንዳሰናከለ፣ እንዴት እንዳሰናከለ ባልታወቀበት ሁኔታ ድምፃውያንን ዒላማ ማድረግ የተተነተነ አመክንዮ የማይቀርብለት ግርፍ ድምዳሜ ነው። ቤተ ክርስቲያንም በግልፅ “ሙዚቃ ሁሉ ኃጢአት ነው” ብላ ባልደነገገችበት ሁኔታ ዝም ብሎ በስሜት ተነስቶ ሙዚቀኞችን መኮነን አሳማኝ አይደለም። ደግሞስ ሙዚቃ ኃጢአት ነው ቢባል እንኳን ታላላቅ ሙዚቀኞች እንደ ንጉሥ/ንግሥት እየተከበሩ የተወሰኑ (ተጋላጭ – vulnerable) ሙዚቀኞች ብቻ ተለይተው የሚኮነኑበት አግባብ መኖር የለበትም። ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር ሙዚቀኞችን ለይቶ ለመኮነን የሚያስችል ውኃ የሚያነሳ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክንያት እንደሌለ ነው።

እኛ ለሙዚቀኞች ጥብቅና የመቆም ፍላጎትም ዓላማም የለንም፣ ኖሮንም አያውቅም። በእኛ መረዳት ግን የዚህ ችግር መንሥዔዎች ሦስት ናቸው። አንደኛው ምንም ትንታኔ የማያስፈልገው የሙዚቃንና የዘፈንን ልዩነት አለማወቅ ነው። ሁለተኛውና ዋነኛው ሙዚቃ ለጭፈራ፣ ለስካርና ከመዳራት መንደርደሪያ ወይም ማጀቢያ መደረጉ ነው። ሦስተኛው ግን ሙዚቃ የምዕመናንን ትኩረት፣ ጊዜና ገንዘብ ከመሻማቱ የተነሳ ይመስለናል። የአንዳንዶች ምክንያት ግን ሰውን ከቤተ ክርስቲያን ያስቀራል (ያርቃል) የሚል ነው። እውነት እንነጋገር ከተባለ በሙዚቃ ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን ከራቀው ይልቅ ከሚሰብኩት ተቃራኒ በሚሠሩ ግብዝ ‘አገልጋዮች’ ተሰናክሎ ከቤተ ክርስቲያን የጠፋው ይበልጣል። በሙዚቃ ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን የቀረው ነገ ከነገ ወዲያ ይመጣል። በአገልጋዮች ግብዝነት ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን የወጣ ግን በሕይወት ዘመኑ ያለመመለስ ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ይህ በሆነበት ሁኔታ ሙዚቀኞች ላይ ጣት ከመቀሰር ይልቅ ራሳችንን ብናርም ይሻላል።

ሙዚቃ በተዉ ማግሥት ወደ ዘማሪነት

መጽሐፍ ‘ደስ የሚለው ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር’ እንዳለ (ያዕ 5:13) ድምፃውያን ሙዚቃ ትተው መዘመራቸው በጣም ያስደስታል። ነገር ግን ሙዚቃ በተዉ ማግሥት ወደ መዝሙር ማውጣት መሸጋገር ትርጉም የለሽና መዝሙር መስዋዕተ እግዚአብሔር መሆኑን የዘነጋ ይመስላል። የቀድሞ ሙዚቀኞች ወይም ዘፋኞች በቀጥታ መዝሙር ወደ ማውጣት መሄድም የራሳቸው ፍላጎት ብቻ አይመስልም። የእነርሱ ፍላጎት በመንፈሳዊ ሕይወት ማደግ ሊሆን ይገባል። ነገር ግን መግፍኤ የሚሆኑት ሁለት ምክንያቶች አሉ። አንደኛውና ዋነኛው ምክንያት የእነርሱን ክህሎትና ታዋቂነት ለመጠቀም የመሽቀዳደም ነገር ነው። ለዚህም ነው ሙዚቃ መተዋቸውን እንኳን ሳንሰማ (መስማት ባይጠበቅብንም) ቀድመን መዝሙር ማውጣታቸውን የምንሰማው። በመንፈሳዊ አገልግሎት ሰበብ ስጋዊ ጥቅም ለማግኘት ሲባል በሙዚቃቸው የታወቁ ሰዎችን መጠቀም “ቀድሞ ሙዚቀኞች ነበሩ” ተብለው በኃጢአተኝነት ከተፈረጁ ሰዎች እጅግ የከፋ በደል ነው። በመዝሙር ስም የሚነግዱት ሌቦች ግን በአስመሳይ መንፈሳዊነት ተሸሽገው የቀድሞ ሙዚቀኞችን “ሙዚቃ መተዋቸው ታላቅ ተአምር ነው” ተብሎ በየሚዲያው ቃለ መጠይቅ እንዲደረግላቸው በማድረግ ብዙ ችግሮችን ይፈጥራሉ። በመጀመሪያ ይህ አካሄድ ብዝበዛ (exploitation) ነው። ሁለተኛ መዝሙራቱም የሙዚቃ ቅላጼን ይዘው እንዲወጡ ያደርጋል። ሦስተኛ ለግለሰቦቹም ከመድረክ ወደ ዐውደ ምሕረት ቀጥታ መሸጋገር ራሳቸውን የሚያዩበትና መንፈሳዊ ሕይወታቸውን የሚያቃኑበት ጊዜ እንዳይኖራቸው ያደርጋል። ይልቁንም ዘማሪ ባልጠፋበት ትናንት ሙዚቀኞች የነበሩትን አቻኩሎ ወደ ዐውደ ምሕረት የማምጣቱ ነገር ምክንያቱ ከላይ የጠቀስነው መሆኑን ያጠናክርልናል።

ሌላው ምክንያት ድምፃውያኑ ሙዚቃ ከተው በኋላ ሌላ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩበት፣ ለራሳቸው የአእምሮ ዕረፍትም የሚሠሩት ሥራ ላይኖራቸው ይችላል። በዚህ ምክንያት በተቻኮለ መንገድ መዝሙር ወደ ማውጣት ሊገፉ ይችላሉ። ይህንን ችግር ሁላችን ልንረዳላቸው ይገባል። ብዙዎቻችን እነርሱን ሙዚቃ ለማስተው እንጂ ከተውስ በኋላ የሚለው የሚያሳሰበን አይመስልም። በመጀመሪያ ሙዚቃ ለመተው ሲወስኑ ያለጫና በራሳቸው በነጻነት (informed decision) ሊሆን ይገባዋል። ሙያቸውን፣ ሥራቸውና ኑሯቸውን ትተው ሲመጡም ቀጣይ ሥራቸው ምን ሊሆን እንደሚገባ መዘጋጀት አለባቸው። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ሰውን ለባሰ ችግር መዳረግ ግን የከፋ ኃጢአት ነው።

ስለምን በሕዝብ ፊት እንዲያለቅሱና እንዲጸጸቱ ይደረጋል?

እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ኃጢኣትን ያደረገ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ተጸጽቶ፣ በንስሐ አባቱ ፊት ቀርቦ ኃጢኣቱን ተናዞ፣ ንስሐውን መቀበልና ያንን ኃጢኣትን ደግሞ ላለመፈጸምም መወሰን ይኖርበታል። ከዚህ በተጨማሪ ሰውን በግል የበደለ በግል ይቅርታ መጠየቅና መካስ ይገባዋል። በአደባባይ የበደለም በአደባባይ ይቅርታ መጠየቅና መካስ ይገባዋል (ማቴ 3:5-6 ያዕ 5:14-16 ሐዋ 8:22-24 1ኛ ዮሐ 1:9)። ከላይ እንደ ተብራራው ሙዚቀኞች የሙያቸውን ስነ-ምግባር አክብረው እስከሠሩ ድረስ በአደባባይ በድለዋል አያስብላቸውም። ስለዚህ በአደባባይ ይቅርታ መጠየቅ አይጠበቅባቸውም። የግል ጉዳያቸውን እንደማንኛውም ክርስቲያን ከንስሐ አባታቸው ጋር መጨረስ ይኖርባቸዋል።

ከዚህ በተቃራኒ ግን በመዝሙር ሰበብ በአዳባባይ እንዲጸጸቱና እንዲያለቅሱ ማስገደድ ራሱ ታላቅ ግፍና በደል ነው እንላለን። ይህ ስነ-አእምሯዊ ማሰቃየት (Psychological/mental torture) ስለሆነ በምድርም በሰማይም ያስጠይቃል። ከማንም የተለየ ኃጢኣት ባልሠሩበትና ከማንም የተለየ በደል ባልበደሉበት ሁኔታ ለዚህ አይነት የአደባባይ ጸጸት መዳረግ ስሁት ድርጊት ስለሆነ መቆም ይኖርበታል። መዘመር ካለባቸውም እንደማንኛውም ዘማሪ ሥርዓቱን ጠብቀው ሊዘምሩና ሊያመሰግኑ ይችላሉ። በአደባባይ በመጸጸታቸው ሰው ሙዚቃቸውን ማዳመጥ ይተዋል ብለን የምናስብ ከሆነ ግን መታወቅ ያለበት ጉዳይ ምንም እንኳን ድምጻውያኑ ሙዚቃ ቢተውም፣ በአደባባይ ቢጸጸቱም ሙዚቃቸው መደመጡን አያቆምም። የሙያቸው ፍሬም ስለሆነ በማኅበረሰቡ ዘንድ ባህላዊ እሴት ሆኖ ይቀጥላል።

ማጠቃለያ

እግዚአብሔር ኃጢአት ነው ያላለውን ማንም ኃጢኣት ሊያደርገው አይችልም። እግዚአብሔር ኃጢኣት ነው ያለውንም ማንም ከኃጢአትነት ሊሰርዘው አይችልም። ሙዚቃ ሁሉ ኃጢአት፣ ሙዚቀኛ ሁሉ ኃጢአተኛ፣ ዘማሪ ሁሉ ጻድቅ አይደለም። ሙዚቃንና ዘፈንን ለይተን ማየት ይኖርብናል። የኪነ-ጥበብ ሙያ እንደማንኛውም ሙያ የተከበረና ባሕላዊ እሴት ነው። ማንኛውም ሙያ በአግባቡ ሥራ ላይ ከዋለ እንደሚጠቅመው፣ ካላግባብ ከተተገበረ ደግሞ እንደሚጎዳው የኪነ-ጥበብ ሙያም እንዲሁ ነው። ሙዚቀኞችም ሆኑ ሌሎች የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የሙያቸው ዘርፍ በተለየ ሁኔታ ከኃጢኣት ጋር ብቻ መያያዝ የለበትም፣ ከጽድቅም ጋር እንዲሁ። መታየት ያለበት እንደ አንድ የሙያ ዘርፍና ባሕላዊ እሴት ነው። ይህ በሆነበት ሁኔታ ሙዚቀኞች ከሌላው ሰው ተለይተው ኃጢአተኛ ተደርገው መታየት የለባቸውም። ሰው ሙዚቃ የሚተወው መዝሙር ለማውጣት አልሞ መሆን የለበትም። አገልጋዮችም ሙዚቃ የተወ ክርስቲያን ወደ መዝሙር ማውጣት በግድ መግፋት የለባቸውም። ሙዚቃ ትተውም ለመዘመር ከወሰኑም አገልግሎታቸውን በቤተ ከክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ሊፈጽሙ ይገባል እንጂ በተለየ መልኩ በመዝሙር ሰበብ በአደባባይ እንዲያለቅሱ መደረግ የለባቸውም። ይህ አካሄድ ሁሉንም የሚጎዳ እንጂ ማንንም የሚጠቅም አይደለምና።