የደሴተ ቆጵሮስ ኤጲስ ቆጶስ የነበረው ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በቅዳሴው “እግዚአብሔር በገናናነቱ ገናና ነው። በቅድስናው የተቀደሰ ነው። በምስጋናው የተመሰገነ ነው። በክብሩም የከበረ ነው።” በማለት እግዚአብሔር ቅድስና የባህርይው እንደሆነ ተናግሯል (ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ)። ቅዱሳን መላእክቱም ዘወትር “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” እያሉ የሚያመሰግኑት አምላክ እርሱ ለዘላለም ቅዱስ ነው። (ኢሳ 6: 3 ራዕ 4:8) እግዚአብሔር በዘመናትም ሁሉ በቅዱሳን እንዲሁ ሲቀደስ፣ ሲመሰገን፣ ሲወደስ ይኖራል። እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ አምላክ ነው። ሕገ እግዚአብሔርን በማፍረሱ ከገነት የተባረረው የሰው ልጅም ዳግመኛ ወደ ጽድቅ ይደርስ ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ በሕገ ልቡና፣ ከዚያም በሕገ ኦሪት፣ ኋላም በሕገ ትሩፋት ሲመራው ኖሯል፣ ይኖራልም። በእነዚህ ዘመናትም ሕግጋተ እግዚአብሔርን በመጠበቅ ብዙዎች ክብር፣ ብፅዕና፣ ቅድስና አግኝተዋል።
ብፅዕና በሕገ ርትዕ
በሕገ ርትዕ (በብሉይ ኪዳን ሕግ) የሰው ልጆች በረከትን የሚያገኙት ሕግን በመጠበቅ ነበር። እነዚህም በሊቀ ነቢያት ሙሴ በኩል እግዚአብሔር የሰጣቸው ሕግጋት ናቸው። ስለዚህም አሠርቱ ትዕዛዛትንና ሌሎች የኦሪትን ሕግጋት የሚጠብቁ የተመሰገኑ (የተባረኩ) ይባሉ ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘም ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ በእርሱ የታመኑ (መዝ 2:12 34:8 40:4 84:12)፣ በቤቱ የሚኖሩ(መዝ 84:4)፣ ምስጋናን የሚያውቁ (መዝ 89:5)፣ ፍርድን የሚጠብቁ፥ ጽድቅንም ሁልጊዜ የሚያደርጉ (መዝ 106:3)፣ በመንገዳቸው ንጹሐን የሆኑ፥ በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ(መዝ 119:1) ፣ ምስክሩን የሚፈልጉ፥ በፍጹም ልብ የሚሹት(መዝ 119:2) ሁሉ የተመሰገኑ/ምስጉኖች ናቸው በማለት ዘምሯል።
በተጨማሪም በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ (መዝ 1:1)፣ መተላለፉ የቀረችለት ኃጢአቱም የተከደነችለት (መዝ 32:1)፣ እግዚአብሔር በደልን የማይቈጥርበት በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት (መዝ 32:2)፣ እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው (መዝ 33:12)፣ ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ (መዝ 41:1)፣ አንተ የመረጥኸው በአደባባዮችህም ለማደር የተቀበልኸው(መዝ 65:4)፣ እርዳታው ከአንተ ዘንድ የሆነለት፥ በልቡም የላይኛውን መንገድ የሚያስብ (መዝ 84:5)፣ አንተ የገሠጽኸው ሕግህንም ያስተማርኸው (መዝ 94:12)፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ፥ ትእዛዙንም እጅግ የሚወድድ (መዝ 112:1)፣ በመንገዶቹም የሚሄድ (መዝ 128:1) ምስጉን ነው በማለት ለእግዚአብሔር ተቀኝቷል።
በመጽሐፈ ምሳሌና በትንቢት መጻሕፍት እንደተጻፈው የእግዚአብሔርን መንገድ (ሕጉን) የሚጠብቁ (ምሳ 8:32)፣ ቃሉን ሰምተው ዕለት ዕለት በጸሎት እየተጉ ምሕረቱን የሚጠባበቁ (ምሳ 8:34)፣ እርሱን በመተማመን ምሕረቱን በትዕግስት የሚጠባበቁ (ኢሳ 30:18)፣ ሰንበትንም የሚጠብቁ፣ እጆቻቸውንም ክፋት ከማድረግ የሚጠብቁ (ኢሳ 56:2)፣ የእግዚአብሔርን በረከት በመተማመን በላባቸው ሠርተው ለማግኘት የሚጥሩ (ኢሳ 32:20)፣ በእግዚአብሔር የታመኑ እምነታቸውም እግዚአብሔር የሆነ (ኤር 17:7)፣ የመከራን ዘመን በመታገሥ የሚያሳልፉ (ዳን 12:12) ብፁዓን ናቸው ተብሎ በቅዱሳት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ተጽፏል።
ብፅዕና በሕገ ትሩፋት
በሕገ ትሩፋት (በሕገ ወንጌል) ግን ብፅዕና የሚገኘው ኃጢአትን ባለማድረግ ብቻ ሳይሆን የጽድቅ (የትሩፋት) ሥራን በመሥራትም ጭምር ነው። ከሁሉ አስቀድሞ ከሰው ልጆች ሁሉ እርሱ መርጦ ማደሪያው ያደረጋት፣ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ በተዋሕዶ ሰው የሆነባት ቅድስት ድንግል ማርያም በሰማይ ቅዱሳን መላእክት፣ በምድር የሰው ልጆች (ትውልድ) ሁሉ ብፅዕት እያሉ ያመሰግኗታል። ይህንንም መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ (ሉቃ 1:28)” በማለት፣ ቅድስት ኤልሳቤጥ ደግሞ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው (ሉቃ 1:42)” በማለት፣ እንዲሁም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል (ሉቃ 1:48)” በማለት አረጋግጠውልናል። በእውነትም ቅድስት ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ መነጽር እምነቷን አይታ “ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት (ሉቃ 1:45)” ያለቻት ቅድስት ድንግል ማርያም ብፅዕት በአፈ ኩሉ (በፈጣሪዋም፣ በመንፈስ ቅዱስ በተቃኙ ቅዱሳንና ቅዱሳት ሰዎችም፣ በቅዱሳን መላእክትም የተመሰገነ) ናት።
ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም ጌታችን በፊሊጶስ ቂሳርያ ሐዋርያቱን “እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ ሲመልስ ጌታችን “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ (ማቴ 16:16-17)” በማለት “ብፁዕ” ብሎታል። በእውነትም ረቂቅ የሆነው ምስጢረ ሥጋዌ ተገልጦለት ሥጋን የተዋሐደውን ክርስቶስን አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ ብሎ የተዋሕዶን ምስጢር የመሰከረ ቅዱስ ጴጥሮስ ምንኛ ብፁዕ ነው! በዚህች እምነቱ “አንተ ጴጥሮስ (አለት) ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም” የሚል ታላቅ ቃል ኪዳን ተሰጥቶታልና። እንዲሁም “የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል” የሚል ታላቅ ስልጣነ ክህነት ተሰጥቶታልና።
አንቀጸ ብፁዓን – የመንፈሳዊ ሕይወት መሠረቶች
“ብፁዕ” ማለት የተባረከ፣ የተመሰገነ፣ ለብቃት የደረሰ ማለት ሲሆን በክብር እና በቅድስና መካከል ላለ ሰው ይነገራል። ለብዙ ሰው ሲሆንም ብፁዓን ይባላል። ብፅዕና የሚለው ቃል በውስጡ በረከትን (Blessing) እና ደስታን (Happiness) በአንድነት የያዘ ቃል ነው። በዚህም በረከትን ማግኘትንና በዚያም የሚገኝ ደስታን በአንድነት ይገልፃል። ጌታችንም ስለብፅዕና መንገድ ያስተማረው ጥልቅ ትምህርት “አንቀጸ ብፁዓን” ይባላል። አንቀጸ ብፁዓን ማለት የብፁዓን በር፣ ደጃፍ፣ መግቢያ ማለት ሲሆን ለብፅዕና የሚያበቁ የክርስቲያናዊ ስነ-ምግባር መሠረቶችንና የመንፈሳዊ ሕይወት ምሰሶዎችን ጌታችን በተራራው ስብከቱ ያስተማረበት ነው። አንቀጸ ብፁዓን የሚባሉት በቁጥር አሥር ናቸው። ዘጠኙ በማቴዎስ ወንጌል የሚገኙ ሲሆኑ አሥረኛው በዮሐንስ ወንጌል ይገኛል። እነዚህም እያንዳንዳቸው ለብፅዕና የሚያበቁ ሕገ ትሩፋትንና እነዚህንም ለፈጸሙ የሰጠውን ተስፋ ያጠቃልላሉ።
አንቀጸ ብፁዓን አስቀድሞ ከተሰጡት አሠርቱ ትዕዛዛት ጋር የሚስማሙና የሚመጋገቡ ናቸው። አሠርቱ ትዕዛዛት ሰውን ከኃጢአት ይጠብቃሉ። ነገር ግን ኃጢአትን አለማድረግ ብቻውን ለጽድቅ፣ ለብጽዕና አያበቃም። የጽድቅ ሥራንም መሥራት ያስፈልጋልና። አንቀጸ ብፁዓን ይህንን የጽድቅ ሥራን በማካተት ሰውን ወደ ቅድስናና ፍጹምነት የሚያደርሱ የትሩፋት ሕግጋት ናቸው። በዚህም አንቀጸ ብፁዓን አሠርቱ ትዕዛዛትን ፍጹም ያደርጓቸዋል። አምስቱ አዕማደ ምስጢራት የእምነት ምሰሶዎች እንደሆኑት ሁሉ አንቀጸ ብፁዓን ብፁዓን ደግሞ የምግባር ምሰሶዎች (“አእማደ ምግባር”) ናቸው። ነገር ግን የክርስቲያናዊ ስነ-ምግባር መሠረቶች መሆናቸው ቢታወቅም እያንዳንዳቸውን በጥልቀት የሚዳስስ ትምህርት በሚፈለገው መጠን አይገኝም። አልፎ አልፎም አንቀጽ ብፁዓንን እንደሚመቻቸው የሚተረጉሙም አጋጥሞናል። ይህንን መነሻ በማድረግ ከዚህ ቀጥሎ በተከታታይ በምናቀርባቸው የአስተምህሮ ጽሑፎች እያንዳንዱን አንቀጽ (beatitude) እናብራራለን፣ አስረጂ ምሳሌዎችንም እናቀርባለን። ለጽሑፎቹ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሽኖዳን Contemplations on the Sermon On The Mount (1997) መጽሐፍ እንደ መነሻ ተጠቅመናል።
ድካም ጉስቁልና የሚስማማው ስጋን የለበሱ ቅዱሳንን በቸርነቱ ፣ በመሐሪነቱ ወደ ጽድቅ፣ ወደ ቅድስና፣ ወደ ብፅዕና የሚመራ፣ በድካማችን የሚራራልን፣ የሚያግዘን የደጋግ አባቶቻችንና እናቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ ፣ እግዚአብሔር መንፈስቅዱስ ለሁላችንም አንቀፀ ብፁዓንን በመንፈስ የምንረዳበትን ጥበብ መንፈሳዊ እንዲያድለን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን ። አሜን።