በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጸሎትና የምሥጋና ሥርዓትና ትውፊት መሠረት ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን ሁሉ በላይ ለሆነችው ለወላዲተ አምላክ ለቅድስት ድንግል ማርያም የሰላምታ፣ የምስጋናና የምልጃ ተማጽኖ ይቀርባል። በአማላጅነቷም ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ እንድታማልደን እንማጸናታለን። ይህም ጥንት ሰማያውያን መላእክትና ቅዱሳን ሰዎች ባቀረቡት ሰላምታ፣ ምስጋናና የምልጃ ተማጽኖ ላይ የተመሠረተ ነው። ለእመቤታችን ከሚቀርቡ የሰላምታ፣ የምስጋናና የምልጃ ተማጽኖዎች መካከል በዘወትር ጸሎት “አባታችን ሆይ” ብለን ከምናቀርበው ጌታችን ካስተማረው ጸሎት ቀጥሎ የሚጸለየው “በሰላም ቅዱስ ገብርኤል” የሚለው የዘወትር ጸሎት ክፍል ነው። በዚህች የአስተምህሮ ትምህርታዊ ጽሑፍ ይህንን እንዳስሳለን።

በሰላመ ቅዱስ ገብርኤል መልአክ/በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ
“በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ” ስንል ይህ የምናቀርበው ሰላምታ የሰው ልጆች የደረሱት ሳይሆን አስቀድሞ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ያቀረበው ሰላምታ መሆኑን እየመሰከርን ነው። አዎን ይህ ሰላምታ በሁሉ ጌታ በእግዚአብሔር ፊት ከሚቆሙት በደል ክፋት ከሌለባቸው ንጹሐን መላእክት አንዱ ቅዱስ ገብርኤል (ገብርኤል መልአክ እመላእክት ንጹሐን ዘአልቦ ሙስና፥ እመላእክት ቀደምት ዘይቀውም ቅድመ እግዚአ ኩሉ) ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ያቀረበላት ሰላምታ ነው። ቅዱስ ገብርኤል ‘መልአክ’ ስለሆነ ያቀረበው ሰላምታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከውን (በአንደበቱ ያኖረለትን) ነው። ይህ ማለት እርሱ ያቀረበው ሰላምታ ጥንተ ምንጩ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው ማለት ነው። ስለዚህ “በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ” ስንል እግዚአብሔር አምላክ በቅዱስ ገብርኤል በኩል በላከውና ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ባቀረበው ሰላምታ ማለታችን መሆኑን ልብ ይሏል። አዎን! እርሷን ሰላም የምንልበትን ሰላምታ፣ የምናቀርበው ምስጋና ምንጩ ከሰማይ እንጂ ከምድር አይደለም። እኛ ሰዎች (ምድራውያን) ስንሆን በመላእክት (በሰማያውያን) ሰላምታ የምናመሰግንበት ሰላምታ ነው።
ይህ ሰላምታ በዋናነት ጌታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም እንደሚወለድ የተበሠረበት ታላቅ ሰላምታ ነው። ይህ ለድንግል ማርያም የተበሠረው ብሥራት በእርስዋ በኩል ለሰው ልጅ ሁሉ መዳን የተደረገ እንጂ ለእርስዋ ብቻ አለመሆኑን ልብ ይሏል። እመቤታችንም “እንደ ቃልህ ይደረግልኝ” ባለች ጊዜ መለኮትና ሥጋ ተዋሕደዋል። ስለዚህ ይህ ሰላምታ ጌታችን ተወልዶ የማዳኑ ሥራ መጀመሪያ (በር)፣ የመዳናችን አንድ አካል ነው። ዕለቱም ለሰው ልጅም ሁሉ ታላቅ የምሥራች ዜና በመልአኩ የተበሠረበት ዕለት (Annunciation) ስለሆነ ከጌታችን ንዑሳን በዓላት አንዱ ነው። አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም “እግዚአብሔር አብ በሰማይ ሆኖ ምሥራቅንና ምዕራብን ሰሜንና ደቡብን ዳርቻዎችንም ሁሉ በእውነት ተመለከተ ተነፈሰ አሻተተም እንደ አንቺ ያለ አላገኘም። የአንቺን መዓዛ ወደደ ደም ግባትሽንም ወደደ። የሚወደውን ልጁን ወደ አንቺ ሰደደ” እንዳለው ወልድ ከእርስዋ እንደሚወለድ ቅዱስ ገብርኤል ያበሰረበት ሰላምታ ነው። እንዲሁም “የቀደሙ አባቶች ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገሩብሽ ድልድይ ሆይ ከምድር እስከ ሰማይ የምትደርሽ መሰላል ሆይ የፍጥረት ሁሉ መጀመሪያ ባንቺ ታደሰ” በማለት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንባት ድልድይ መሆኗ የተበሠረበት ሰላምታ ነው።
ኦ እግዝእትየ(ነ)ማርያም ሰላም ለኪ/እመቤቴ(ታችን) ማርያም ሆይ ሰላም እልሻለሁ/እንልሻለን
ከዚያ ቀጥለን (በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ) “እመቤቴ(ታችን) ማርያም ሆይ ሰላም እልሻለሁ/እንልሻለን” እንላለን። የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን እናት “እመቤቴ ወይም እመቤታችን” ብንላት የሚያንሳት እንጂ የሚበዛባት አይደለም። ቅድስት ኤልሳቤጥ “የጌታዬ እናት” እንዳለቻት፣ እርስዋም “ትውልድ ሁሉ ብፅዕት” ይሉኛል እንዳለች እኛም “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም” እንላታለን። ማርያም የሚለውም ስሟ አባቷ ኢያቄምና እናቷ ሐና ያውጡላት ስም ነው። ማርያም የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ማሪሃም (ሚርያም) ሲሆን ትርጉሙም አብርሃም ማለት አበ ብዙኃን (የብዙዎች አባት ) ማለት እንደሆነ እመ ብዙኃን (የብዙዎች እናት) ማለት ነው (ዘፍ 17:5) ፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም መርሕ ለመንግስተ ሰማያት (ወደ መንግስተ ሰመማያት መርታ የምታስገባ)፣ ጸጋ ወሀብት፣ ፍጽምተ ሥጋ ወነፍስ፣ መልዕልተ ፍጡራን መትህተ ፈጣሪ፣ እግዝእተ ብዙኃን በማለት በምስጢራዊ ዘይቤ ተርጉመውታል።
እርሷ ፀሐይን የተጎናጸፈች፣ ጨረቃን የተጫማች፣ አሥራ ሁለት የክዋክብት አክሊል ያላት፣ የቤተክርስቲያን ፍጹም መልክ ማሳያ፣ እሙ ለፀሐየ ጸድቅ ናት (ራዕይ 12:1)። ስለዚህም ነው ቅዱስ ኤፍሬም “ኮንኪ ተንከተመ ለዕርገት ዉስተ ሰማይ፡ ብርሃንኪ የዐቢ እምብርሃነ ፀሐይ፡ አንቲ ዉእቱ ምሥራቅ ዘወፅአ እምኔኪ ኮከብ ብሩህ ዘነፀርዎ ቅዱሳን በፍሥሓ ወበሐሤት/ከምድር ወደሰማይ ለማረግ መሰላል ሆንሽ ብርሃንሽ ከፀሐይ ብርሃን ይበልጣል። ቅዱሳን በፍጹም ደስታ ያዩት ኮከብ ካንቺ የተወልደ ምሥራቅ አንቺ ነሽ” በማለት ያመሰገናት። ቅዱስ ያሬድም “እንተ በምድር ሥረዊሃ ወበሰማይ አዕጹቂሃ/ሥሮቿ በምድር ጫፎቿም በሰማይ ያሉ” በማለት አመስግኗታል። ስለዚህም ከተለዩ የተለየች፣ ከተቀደሱ የተቀደሰች ናትና ቅድስት እንላታለን። እንኳን የፈጣሪያችንን እናት ይቅርና ሌሎችንም እመቤት፣ ቅድስት የምንል አይደለንምን? ወንጌላዊ ዮሐንስ በመልእክቱ “ለእመቤቴና ለተመረጠች” በማለት ለሮምላ የጻፈውን መመልከት ለዚህ በቂ አይደለምን?
ድንግል በኅሊናኪ ወድንግል በሥጋኪ/በሀሳብሽ ድንግል ነሽ፣ በሥጋሽም ድንግል ነሽ
የእመቤታችን ዘላለማዊ ድንግልና (Perpetual Virginity) አስቀድሞ በነቢያት “ድንግል (በድንግልና) ትጸንሳለች፣ ወንድ ልጅም (በድንግልና) ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ይሉታል” ተብሎ የተነገረ (ኢሳ 7:14 )፣ በጊዜውም የተፈጸመ ነው (ማቴ 1:23 ሉቃ 1:34-35)። ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስም “በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል … ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ” (ሉቃ 1:26-27) በማለት ሁለት ጊዜ “ድንግል” ብሎ እንደገለጸው ነው። ነቢዩ ሕዝቅኤል “የተዘጋች ደጅ” ብሎ የተናገረውም ዘላለማዊ ድንግልናዋን ነው (ሕዝ 44:2)። የታጠረች ተክል፤ የተዘጋች የውሃ ጒድጓድ እርሷ ናት። እርስዋ ከመውለድዋ አስቀድሞ፣ ከወለደችም በኋላ ድንግል ናት። በኅሊናሽ/በሀሳብሽ ድንግል (ንጽሕት) ነሽ የምንላትም “ወንድ ስለማላውቅ” ያለችውን (ንጽሕና) እንዲሁም “እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይደረግልኝ” ያለችውን (ፍጹም መታዘዝና ትህትና) የሚያጠይቅ ነው (ሉቃ 1:34-35 1:38)። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “የማይወሰን እንዴት በማኅፀን ተወሰነ? ድንግልስ እንደምን በድንግልና ወለደች? ከወለደች በኋላስ እንደምን ድንግል ሆና ኖረች?” በማለት ስለእርስዋ ዘላለማዊ ድንግልና በአንክሮ ተናግሯል። ቅዱስ አትናቴዎስም “ድንግል ሆይ ከታላላቆች ሁሉ ታላቅ ነሽ፣ የእግዚአብሔር ማደሪያው ሆይ ከአንቺ ጋር ማን ይተካከላል?” በማለት መስክሮላታል።
በሥርዓተ ቅዳሴም ዲያቆኑ የጳውሎስን መልእክት ከማንበቡ በፊት “ኩሎ ዘኢያፈቅሮ ለእግዚእነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወዘኢየአምን ልደቶ እማርያም እምቅድስት ድንግል በክልኤ ታቦተ መንፈስ ቅዱስ እስከ ምጽአቱ ሐዳስ በከመ ይቤ ጳውሎስ ውጉዘ ለይኩን/ጌታችንንና መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወደው የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ በሁለት ወገን ድንግል ከምትሆን ከቅድስት ማርያም መወለዱንም የማያምን ሰው ሁሉ እንግዳ እስከሚሆን ምጽአቱ ድረስ ጳውሎስ እንደ ተናገረ የተለየ ይሁን” በማለት የእርሷን በሁለት ወገን ድንግል መሆን ያውጃል። እንዲሁም ሠራኢው ካህን በጸሎተ በቅዳሴ የጌታን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በተመለከተ እምነቱን በሚያውጅበት የመፈተት ጸሎት “አምናለሁ አምናለሁ አምናለሁ። እስከ መጨረሻዪቱም እስትንፋስ እታመናለሁ፤ በሁለት ወገን ድንግል ከምትሆን ከሁላችን እመቤት ከቅድስት ድንግል ማርያም የነሣው የጌታችንና የመድኃኒታችንም የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋው ደሙ ይህ እንደሆነ ያለ መቀላቀል ያለትድምርት ያለመለዋወጥና ያለመለየት ከመለኮት ጋራ አንድ ያደረገው፤ በጰንጤናዊ በጲላጦስም ዘመን ባማረ ምስክርነት ምስክር የሆነ፤ ስለ እኛና ስለ ሁላችንም ሕይወት አሳልፎ የሰጠው” የሚለው ይህንኑ ያረጋግጥልናል።
እመ እግዚአብሔር ጸባዖት ሰለም ለኪ/የአሸናፊ እግዚአብሔር እናት ሆይ ላንቺ ሰላምታ ይገባሻል
አዎን ቅድስት ድንግል ማርያም እመ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር እናት)፣ ወላዲተ አምላክ (የአምላክ እናት – Mother of God (Theotokos)) ናት። ይህም አስቀድሞ ቅዱስ ገብርኤል “እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም …መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” በማለት የተናገረውን የሚያጠይቅ ነው (ሉቃ 1:31-35)። አዎን ልጅዋን አምላክ ነው ብሎ የሚያምን እርስዋን ወላዲተ አምላክ ማለት የተገባ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው ብሎ የሚያምን የወለደችው እርስዋን እመ እግዚአብሔር ሊላት የተገባ ነው፣ ከሰው ዘር እንዳልጸነሰች መልአኩ ምስክር ሆኗልና። ስለዚህ ነው ቅዱስ ቄርሎስ “አማኑኤልን እውነተኛ አምላክ ነው ብሎ የማያምን፣ ቅድስት ድንግልንም ወላዲተ አምላክ (Theotokos) የማይል የተወገዘ ይሁን” በማለት የጻፈልን። ይህ “ሰላምታ ይገባሻል” የሚለው የገብርኤል ሰላምታ እጅግ ልዩ የሆነ ሰላምታ ነው። ለሰው ልጅ እውነተኛ ሰላም፣ የሰላም ንጉሥ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም እንደሚወለድ የተበሠረበት ታላቅ ሰላምታ ነው።
ቡርክት አንቲ እምአንስት ወቡሩክ ፍሬ ከርሥኪ/ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ። የማኅፀንሽም ፍሬ ቡሩክ ነው
ይህ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ” (ሉቃ 1:28) በማለት፣ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን የተመላችው ቅድስት ኤልሳቤጥ በታላቅ ድምፅም ጮኻ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ ቡሩክ ነው” በማለት ቅዱስ ገብርኤል ሰማያውያን መላእክትን፣ ቅድስት ኤልሳቤጥ ደግሞ ቅዱሳን ሰዎችን ወክለው ካቀረቡላት ምስጋና በቀጥታ የተወሰደ ነው። ቅዱስ ዮሐንስም በቅድስት ኤልሳቤጥ ማኅፀን ሆኖ በድንግል ማርያም ማኅፀን ላለው ጌታ የአምልኮ፣ ለድንግል ማርያም ደግሞ የጸጋ ስግደትን ሰግዷል። እመቤታችን ከሴቶች ሁሉ ለአምላክ እናትነት የተለየች፣ የተመረጠች ናትና “ቡርክት” እንላታለን። በንጽሕናዋ፣ በቅድስናዋ፣ በክብሯ፣ በፍጹም መታዘዟ የተለየች (በጸጋ) ቡርክት ናት። ሌሎች ቅዱሳን ቢባሉ በእምነት፣ በምግባር ጸንተው ነው። የእርስዋ ቅድስና ግን ከዚህ ሁሉ በላይ ነው። የቅድስና ምንጭ የሆነውን አምላክን ወልዳለችና። ስለዚህ ቅድስተ ቅዱሳን እንላታለን። ቅዱስ ኤፍሬምም “ተሰመይኪ ፍቅርተ ኦ ቡርክት እምአንስት አንቲ ዉእቱ ዳግሚት ቀመር እንተ ትሰመይ ቅድስተ ቅዱሳን ወዉስቴታ ጽላተ ኪዳን/ከሴቶች ይልቅ ተለይተሽ የተባረክሽ ሆይ የተወደድሽ ተባልሽ ከተለዩ የተለየች በውስጧም የኪዳን የህግጽላት ያለባት የምትባይ ሁለተኛ ክፍል አንቺ ነሽ/” በማለት ያመሰገናት ለዚህ ነው። በማኅፀንዋ ያደረው ደግሞ በባህርይው ቡሩክ አምላክ ነውና ይህንን እንመሰክራለን።
ተፈስሒ ፍስሕት ኦ ምልዕተ ጸጋ/ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ
እመቤታችንን በመጀመሪያ “ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ” ብሎ ያመሰገናት ቅዱስ ገብርኤል ነው (ሉቃ 1:28)። ቅዱስ ገብርኤል ከምንም በፊት አስቀድሞ ለእመቤታችን የተናገረው ይህንን ነው። ስሟን ሳይጠራ “ጸጋ የሞላብሽ ሆይ” ማለቱ ተለይታ የምትጠራበት ይህ “ምልዕተ ጸጋ” መሆኑን ያስረዳል። ይህም አንድም የጎደለባት ጸጋ እንደሌለ ያሳያል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን (ሮሜ 12:6)፣ የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው (1ኛ ቆሮ 12:4)፣ እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን” (ኤፌ 4:7) በማለት እንዳስተማረው ለቅዱሳን የተሰጠው ጸጋ የተለያየ ነው። እመቤታችን ግን ምልዕተ ጸጋ ናት። ቤተ ክርስቲያናችን በጸሎተ ቅዳሴ የእመቤታችንን ምልዕተ ጸጋ መሆን ከከበሩ ሊቃነ መላእክት በማነጻጸር ስትገልጽ የሚከተለውን ትጸልያለች “ተውህቦ ምህረት ለሚካኤል ወብስራት ለገብርኤል ወሀብተ ሰማያት ለማርያም ድንግል/ለሚካኤል ምህረት ተሰጠው ለገብርኤልም ማብሠር ለድንግል ማርያምም ሰማያዊ ሀብት” (ሥርዓተ ቅዳሴ)። ለሌሎች ቅዱሳን ከጸጋ እግዚአብሔር እየተከፈለ በልዩ ሁኔታ የሚገለጽ ጸጋ ሲሰጣቸው (ለምሳሌ: ለሚካኤል ምህረት፣ ለገብርኤል ብስራት) ለእመቤታችን ግን የተሰጣት ፍጹም የሆነ “ሀብተ ሰማያት” ነውና በልዩ ሁኔታ ምልዕተ ጸጋ፣ ምልዕተ ክብር (ጸጋ ሁሉ የተሰጠሽ፣ ከክብርም ሁሉ የሚጎድልሽ የሌለ) እያልን እናመሰግናታለን።
መልአኩ እንደተናገረው በእግዚአብሔር ፊት ምሉዕ የሆነ ጸጋ፣ ክብር፣ ባለሟልነትን አግኝታለች። ይህንን አብነት በማድረግም ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በውዳሴ ማርያም “ያለ ርኩሰት ድንግል የሆንሽ ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ። የዓለም ሁሉ መክበሪያ ንጽሕት ጽዋዕ ነሽ ፤ የማትጠፊ ፋና ነሽ ፤ የማትፈርሺ መቅደስ ነሽ ፤ የቅዱሳን መጠጊያቸው የማትለወጪ የሃይማኖት በትር ነሽ” በማለት አመስግኗታል። በተጨማሪም “የመላእክት ተድላ ደስታቸው አምላክን የወለድሽ ደስ ይበልሽ፤ የመላእክት ዜና ትንቢታቸው ንፅሕት ሆይ ደስ ይበልሽ፤ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ የዓለሙን ሁሉ ተድላ ደስታ የሆነውን የመልአኩን ቃል ተቀብለሽዋልና ደስ ይበልሽ” ብሎ አመስግኗታል። የእርስዋን ምልዕተ ጸጋነት ለመግለጽም ቢቸገር “ስለ እርሷ ድንቅ ሆኖ የሚነገረውን ይህንን ምሥጢር ማወቅ የሚቻለው ምን ልብ ነው መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው መስማትስ የሚቻለው ምን ጆሮ ነው” በማለት በአድናቆት ገልጾታል። ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም “ኦ ምልዕተ ጸጋ ኦ ሙኀዘ ፍሥሐ (ጸጋን የተመላሽ የተድላ የደስታ መፍሰሻ)” ብሎ አመስግኗታል። እኛም እነርሱን አብነት አድርገን “ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ” እያልን እናመሰግናታለን። መልአኩ ደስ ይበልሽ እንዳላት እርሷም “መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤ የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና” (ሉቃ 1:47-48) በማለት የባርያይቱን (የሔዋንን) ውርደት(ውድቀት) በእርሷ በኩል ባደረገው የማዳኑ ሥራ ማስቀረቱ የደስታችን ምንጭ መሆኑን በጸሎቷ ተናግራለች።
እግዚአብሔር ምስሌኪ/እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና
እመቤታችንን “እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና” በማለትም ያመሰገናት ቅዱስ ገብርኤል ነው። ከእርስዋ ሰው ሆኖ የተወለደው አምላክም ስሙ አማኑኤል (እግዚአብሔር ከእኛ ጋር) ነው። እግዚአብሔር ከእርስዋ ጋር በመሆን ከሰው ዘር ሁሉ ጋር ሆኗልና። ቅዱስ አትናቴዎስ ይህንን አብነት አድርጎ ድንግል ማርያም “የቃል ማደሪያው፣ ንጽሕት የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ናት” በማለት አስተምሯል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው የሚለውን “የድንግል ማኅፀን የመለኮት መቅደሱ ሆነ” በማለት አስተምሯል። ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያም “እግዚአብሔር ከድንግል ማርያም ጋር ነው፣ ምክንያቱም ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ (በተዋሕዶ) ሰው ሆኗልና” በማለት ጽፎልናል። ይህም የንጽሕናዋ፣ በኅቱም ድንግልና ጸንሳ በኅቱም ድንግልና የመውለዷ ሌላው ማረጋገጫ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና በተለየ አካሉ የሚያድረውም ንጹሕና ቅዱስ በሆነ አካል ብቻ ነው። ስለዚህም ነው ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም “ከኪሩቤልና ከሱራፌል ግርማ የበለጠ የመወደድ ግርማ አለሽ” በማለት ያመሰገናት። ኪሩቤልና ሱራፌል መንበረ ክብሩን ሲያገለግሉ ሊያዩትም፣ ሊነኩትም አይቻላቸውም። እመቤታችን ግን “ሰማይ ወምድር ዘኢያገምሮ” የተባለለትን ሰማይና ምድር የማይችሉትን ጌታ በተለየ አካሉ መንበር ሆናዋለችና ክብሯ፣ ግርማዋ ከኪሩቤልና ከሱራፌል በላይ ነው። ስለሆነም ቃል ከእርሷ ሥጋ መሆኑ ዘላለማዊ ነውና ዛሬም እኛ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው እያልን እናመሰግናታለን። ሐዋርያው “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?” (ሮሜ 8:31) እንዳለው እግዚአብሔር ከእርሷ ጋር ስለሆነ የሚያመሰግናት እንጂ የሚቃወማት የለም።
ሰአሊ ወጸልዪ ምሕረተ ኀበ ፍቁር ወልድኪ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ይሥረይ ለነ ኃጣውኢነ/ከተወደደው ልጅሽ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ይቅርታን ለምኝልን ኃጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ
እኛ ኦርቶዶክሳዊያን ጸሎታችንን የምናቀርበው ወደ አምላካችን እግዚአብሔር ነው። ለእመቤታችን የምናቀርበው ሰላምታ፣ ምስጋናና (የጸጋ) የምልጃ ተማፅኖ ነው። የእኛ የኃጢአተኞች ዋናው ልመናችን ኃጢአታችን ይሰረይለን ዘንድ እንጂ ሌላ አይደለም። ስለዚህም አስቀድመን በአቡነ ዘበሰማያት ጸሎታችን “በደላችንን (ኃጢአታችንን) ይቅር በለን” ብለን ወደ ፈጣሪያችን ጸሎትን አቅርበናል። እዚህ ደግሞ “ከተወደደው ልጅሽ ከጌታችን ይቅርታንና ምሕረትን ለምኝልን ኃጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ” ብለን የምልጃ ተማጽኖን እናቀርባለን። ኃጢአት ለሞት የምታደርስ ክፉ ናትና እኛ በደለኞቹ ኃጢአታችንን ያስተሰርይልን ዘንድ ወደ ፈጣሪያችን ልመናን አቅርበናል፣ የአምላክ እናቱ ሆይ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና አንቺም ኃጢአታችንን ያስተሰርይልን ዘንድ ለምኝልን (ጸልዪልን) ማለታችን ነው።
አንድ ኃጢአተኝነቱን ለሚያምንና ኃጢአቱም ለሞት ሳታበቃው በአስቸኳይ ምሕረትን ለሚሻ ሰው ጸሎቱን ወደ ፈጣሪው ማቅረቡና፣ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምም እንድታማልደው መጠየቁ የተገባ ነው። ቅድስት ድንግል ማርያም ለአብ መርዓቱ፣ ለወልድ ወላዲቱ፣ ለመንፈስቅዱስ ጽርሃ ቤቱ (የአብ ሙሽራው፣ የወልድ እናቱ፣ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ቤቱ) ስትሆን ለእኛ ለክርስቲያኖች ደግሞ “እነኋት እናታችሁ” ተብላ በዮሐንስ በኩል የተሰጠችን እናታችን ናት። እኛም “እነሆ ልጆችሽ” ተብለን በመስቀል ላይ የተሰጠናት ልጆቿ ነን (ዮሐ 19:26)። እንግዲህ ለሕይወታችን ዕረፍትን እናገኝ ዘንድ ምልጃን ለመጠየቅ ለእኛ ከእናታችን የቀረበ፣ ለእርሱም ከእናቱ የቀረበ የለም። ለእርሱ ለሥጋዌ ልደቱ እናት በመሆን፣ ለእኛም በጸጋ እናት በመሆን ፈጣሪንና ፍጡርን ያገናኘች መሰላል እርሷ ናት። ስለዚህም ዘወትር “ከተወደደው ልጅሽ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ይቅርታን ለምኝልን ኃጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ” እያልን እንማጸናታለን።
በመጨረሻም፥
ሁሉም የኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ይህንን ሰላምታ፣ ምስጋናና የምልጃ ተማጽኖ ለቅድስት ድንግል ማርያም ያቀርባሉ። የኢትዮጵያና የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ከአቡነ ዘበሰማያት ቀጥሎ “በሰላም ቅዱስ ገብርኤልን” ሲጸልዩ ሌሎቹ ግን በሌሎች የጸሎት ክፍሎች ይህንኑ ሰላምታ፣ ምስጋናና የምልጃ ተማጽኖ ያቀርባሉ። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ጌታችን ያስተማረው ጸሎት (አቡነ ዘበሰማያት) ምሉዕ ስለሆነና ኃይል፣ ክብር፣ ምስጋና ለዘላለሙ ተብሎ ስለሚደመደም ከዚያ በኋላ ሌላ ጸሎት መጨመር ተገቢ አይደለም ሲሉ ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ግን ከጌታ ጸሎት ቀጥሎ የእመቤታችንን ምልጃ መጠየቅ ተጨማሪ ጸሎት ሳይሆን ከዚያው ጸሎት ጋር አብሮ የሚሄድ (‘Complementary’) ነው ይላሉ። ሆኖም በዋናው ጉዳይ (የጸሎቱ አስፈላጊነት) ላይ ልዩነት የለም። መቼ ይጸለይ የሚለው ቅደም ተከተል (የጸሎት ሥርዓት) ላይ ግን መጠነኛ የሥርዓት ልዩነት አላቸው። ይህንን ሳያስተውሉ ሌሎች የኦሪየንታል አብያተ ክርስቲያናት “በሰላም ቅዱስ ገብርኤልን” አይጸልዩትም ብሎ ማለት ግን ትክክል አይደለም። የእመቤታችን አማላጅነት፣ የልጅዋም ቸርነት አይለየን። አሜን!