መግቢያ
አስተምህሮ ዘተዋሕዶ በአዘጋጆቿ እይታ የቤተክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና የሚገዳደሩ ስሁት አስተምህሮዎችን ትሞግታለች። እንዲሁም ቤተክርስቲያንና ልዩ ልዩ አካላቷ ባላቸው መንፈሳዊና ማኅበራዊ መስተጋብር የሚፈጠሩ የአስተምህሮ፣ የልማድና የባሕል ጉዳዮችን በመዳሰስ ተራራው ዝቅ እንዲል፣ የጠመመው እንዲቃና፣ የጎደለው እንዲሞላ ለማድረግ ትሞክራለች። እንደየጦማሮቿ ትኩረትም የተለያዩ ታሳቢ አንባብያን (target audience) አላት። የዚህች ጦማር ትኩረት “ሰባክያን” ተብለው የሚጠሩ የቤተክርስቲያን መምህራን ናቸው። “መምህር (Teacher)” ከሚለው ቃል ይልቅ “ሰባኪ (Preacher)” የሚለውን መጠቀም መርጠናል። ይህን ያደረግነው ሰባኪ የሚለው ቃል በቅርብ ጊዜ የቤተክርስቲያናችን ልማድ መምህር ከሚለው ቃል የተለየ መገለጫ (connotation) እየያዘ መምጣቱን በመገንዘባችንና የጦማሩን ትኩረት የተሻለ ስለሚገልጽ ነው። በጦማሩ የተመለከቱት የሰባክያን ድክመቶች ሁሉ የሁሉም ሰባክያን መገለጫዎች እንዳልሆኑ ብናውቅም ሁሉም የየድርሻውን ያነሳ ዘንድ ቀርበዋል። ታሳቢ አንባብያንም የየድርሻቸውን ያነሳሉ ብለን እናምናለን።
ይድረስ ለሰባኪው:-
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ በሰዎች ዘንድ የታወቁ ሰባኪ ነዎት። መድረክ ላይ ቆመው ይሰብካሉ እንጂ አይጠየቁም። ዛሬ ግን ልንጠይቅዎ ተነስተናል። ለመሆኑ ከስብከትዎ ጋር በተያያዘ ከምዕመናንና ከሌሎች አገልጋዮች ከፍተኛ አድናቆትን ሲያገኙ ያስደስትዎታል? አንጋፋው፣ ብርቅዬው፣ ዕንቁው፣ ትሑቱ፣ አንደበተ ርቱዑ፣ ትንታጉ ሰባኪ ሲባሉ ልብዎ በሐሴት ትሞላለች? ሰዎች ‘ስብከትዎ ለውጦናል’ ሲሉዎት የእርስዎ ተፈላጊነት እንደጨመረ ያስባሉ? አዎን ይህ ስሜት የሚሰማዎት ከሆነ (በግልፅ በዐውደ ምህረት እስካልተቃወሙት ድረስ እንደተስማማዎት ይቆጠራል) ቁርጥዎን ይወቁ። ይህ ሁሉ ጠቢቡ ሰሎሞን እንደተናገረው “ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ ነፋስንም እንደመከተል ነው።” (መጽሐፈ መክብብ 1:1-14) ከንቱነትም ይርቅልዎ ዘንድ ተግተው ይጸልዩ።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ የወንጌል መምህር ነዎት። በስብከትዎ ምክንያት ተሰባኪዎች “በስብከትዎ እጅግ ደስ ብሎናል” ብለው ሲያመሰግኑዎት፣ መርሀ-ግብር መሪዎች ውዳሴን ሲያጎርፉልዎት፣ በእርስዎ ምክንያት ብዙ ሰው በመምጣቱ፣ በርከት ያለ ገቢም በመገኘቱ፣ የደብር አለቆችም ቅኔ ሲቀኙልዎት፣ ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ተብሎ ሽልማት ሲበረከትልዎት እውነት በዚያን ሰዓት ልብዎ በደስታ (እርስዎ በግልፅ ተዉ ብለው እስካላስቆሙት ድረስ እንዳስደሰቶት ይቆጠራልና) ትሞላለችን? እንግዲህ የሚያውቁትን እውነት እንነግርዎታለን። ይህ ከንቱ ነው። ይህም ከንቱነት ይርቅልዎ ዘንድ ፈጣሪን ይማጸኑት።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ ወጣት የመድረክ ሰው ነዎት። አድናቂዎችዎ ከሆኑ ቆነጃጅት ጋር መታየትም ያዘወትራሉ? ለአገልግሎት ከመሄድዎ በፊት ለብዙ ሰዓታት በውበት ሳሎን፣ በመስታወት ፊት፣ እንዲሁም ከግልዎ የፕሮቶኮል ባለሙያ ጋር ይቆያሉ? “መድረክ ላይ ስወጣ ምን እመስላለሁ?” የሚለው በጣም ያስጨንቅዎታል? በአለባበስዎ፣ በጸጉርና በጺም አቆራረጥዎ የሆነ ታዋቂ ሰውን መምሰል ያስደስትዎታል? በልብስዎ ላይ ያሉት የባንዲራ ቀለማት ወይም በደረትዎ ላይ ያለው ትልቅ መስቀል ደምቆ እንዲታይ ይፈልጋሉ? ጭራሽ ራስዎ በፈጠሩት አሸንክታብ ተጀቡነው ፎቶና ቪዲዮ እየቀረፁ “አጌጥንበት ስምህን” እያሉ ይምነሸነሻሉ? እንግዲህ እውነቱን ይወቁት። ይህ ሁሉ ከንቱ ነው። ክርስቶስ የመሠረተው ዐውደ ምሕረት እርሱ ሊሰበክበት እንጂ እርስዎ ሊታዩበት አልተዘጋጀምና ይህንን ከንቱነት አስወግደው ትሕትናን ይልበሱ።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ የክርስቶስን ወንጌል ሰባኪ ነዎት። በተዋበ አነጋገርዎና በተቀመሙ ቃላትዎ መታወቅ ወይም ታዋቂ መሆን ይፈልጋሉ? ታዋቂም ሆነው በየዓለማቱ እየዞሩ በማስተማር “ዓለም አቀፍ ሰባኪ” መሆን ይፈልጋሉ? ስምዎም በዓለም ዳርቻ ሁሉ ናኝቶ ከታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ዝርዝር እንዲገቡ ይሻሉ? በተግባር የሚያደርጓቸው ነገሮች ይህንን ያሳብቃሉና እንግዲህ የሚያውቁትን ነገር ግን የማያስደስትዎትን እውነት እንነግርዎታለን። ፍላጎትዎ ከንቱ ነው። ክርስቶስን ሊያሳውቁ እንጂ ራስዎ ሊታወቁ አልተጠሩምና ወደ ሕሊናዎ ይመለሱ።
ሰባኪ ሆይ፥ በእርግጥ እርስዎ ምርጥ ሰባኪ ነዎት ይባላል። ግን የእርስዎ ብቻ የሆነ፣ እርስዎም የሚታወቁበት የተለየ የስብከት ስልት እንዲኖርዎ ይሻሉ? ሌሎች ወጣት ሰባክያንም እርስዎን ጥሩ ምሳሌ አድርገው እንዲጠቅሱ ይፈልጋሉ? ግን ይህም ከንቱ ነው። ወንጌል እንዲሰብኩ እንጂ የራስዎ የታወቀ መለያ (Brand) እንዲገነቡ አልተጠሩምና። የሰባክያን ፍፁም አርአያ (perfect example) ኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ እርስዎ አይደሉምና። መጽሐፍም፥ “ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃል አትስሙ፤ ከንቱነትን ያስተምሩአችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ” (ትንቢተ ኤርምያስ 23:16) ያለውን ያስተውሉ።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ አንደበተ ርቱዕ ሰባኪ ነዎት። በስብከትዎ መካከል ሰውን የሚያነቃቁ፣ ፈገግ የሚያሰኙ ከዓለም የተገኙ ወይም ራስዎ የፈጠሯቸውን ቀልዶችን ጣል ያደርጋሉ። እንደ ኮሜዲያን መሆንም ይቃጣዎታል። በዚህም ታዳሚዎችዎ ሲስቁልዎት ደስ ይልዎታል። ይህ የስብከት ዘዴዎ በሰው ዘንድ ተወዳጅነትን አፍርቶልዎታል። እኛ ግን የሚያውቁትን እውነት እንነግርዎታለን። ይህም ከንቱ ነው። የእግዚአብሔር ዐውደ ምህረት መቀለጃ አይደለም፣ ሕይወት የሆነው ቅዱስ ቃሉ የሚሰበክበት እንጂ። መጽሐፍም፥ “ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል” (ማቴ 12:36) ይላልና።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ ሰዎች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲለወጡ ይሰብካሉ። የሚሰብኩትን ወንጌል ሙሉ በሙሉ ራስዎ በሕይወት እንዲኖሩት አንጠብቅም። ነገር ግን የሚችሉትን ያህል በቃል የሚሰብኩትን በሕይወት ለመኖር ይጥራሉ? ወይስ ሰው በሙያው በመሥሪያ ቤት ተቀጥሮ ሥጋዊ ሕይወቱን ለመምራት ብሎ እንደሚሠራው አይነት ያለ ስሜት ይሰማዎታል? ይህ ከሆነ ከንቱነት እየቀረበችዎ ናትና ፈጥነው ያርቋት ወይም ይራቋት።
ሰባኪ ሆይ፥ በእርስዎ ዘመን ብዙ ሰባኪዎች አሉ። በስብከትዎ ከብዙዎቹ ሰባኪዎች በልጠውና ልቀው መታየት ይፈልጋሉ? እስኪ የሰባኪዎች ደረጃ ወጣ እንበልና እርስዎ በልህቀትዎ አንደኛ ደረጃ ላይ መሆን ያስደስትዎታል? መቼስ ‘አንደኛ መሆን ማን ይጠላል!’ ብለው ያስቡ ይሆናል። ግን ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። መንፈሳዊ አገልግሎት እርስ በእርሳችን የምንወዳደርበት እንዳልሆነ አይጠፋብዎትም ብለን እናስባለን።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ ‘የመንፈሳዊ ቢዝነስ’ ሰው የነበሩ ቢሆንም ግን ጥሩ ይሰብኩ ነበር። በቢዝነስም ይሁን በተሰሚነት ይገዳደረኛል ብለው የሚያስቧቸውን አገልጋዮች ግን የተሃድሶና የመናፍቅ እንዲሁም የዝሙት ርኩሰትን ታርጋ በእውነትም ሆነ በውሸት በመለጠፍና፣ እንደ መንጋ የሚነዷቸውን ጀሌዎችዎን በመጠቀም በማኅበራዊ ሚዲያ ስም በማጠልሸት የሚተካከልዎ የለም። በዚህም ብዙዎችን ከቤተ ክርስቲያን አሳደው የሌሎች ቤተ እምነቶች ሲሳይ አድርገዋቸዋል። አንዳንዶችም እርስዎን በመፍራት ሁሉን ትተው ከቤታቸው ተቀምጠዋል። ይህም ከንቱ ነው። አገልጋዮች ድክመቶች እንኳን ቢኖርባቸው በትምህርት፣ በምክርና በተግሳፅ እንጂ በማሳደድ ሊያቀኗቸው አይችሉም።
ሰባኪ ሆይ፥ አሁን ደግሞ በመጽሐፍ ሊገለጡ እንደሆነ ሰምተናል። በጣምም ደስ ብሎናል፣ መጽሐፍዎንም እንገዛለን። ነገር ግን ለየት ለማድረግ ለመጽሐፍዎ ርዕስ የማናውቀው በውጭ አገር ቋንቋ ውስጥ የሚገኝ ቃልን ሰጥተውታልን? በመጽሐፍዎ ጀርባ ላይ አስተያየት የሰጡ ሰዎች መጽሐፍዎን በሚገባ አንብበዋልን? ወይስ እርስዎ ነዎት አስተያየቱን የፃፉላቸው? በመጽሐፍዎ የምርቃት ቀን ዳሰሳ የሚያቀርቡልዎት ሰዎችስ መጽሐፍዎን ዘልቀውታልን? ለመሆኑ ይህ ስንተኛ መጽሐፍዎ ነው? ስለመጽሐፍዎ ቃለ መጠይቅ ሲደረግልዎ ‘መጽሐፌ’ የምትለውን ቃል አርባ ጊዜ ደጋግመው ይሏታልን? እንግዲህ ይህም ከንቱ ነው ንፋስንም እንደመከተል ነው። የቀደሙ ሊቃውንትን ጥበብ ይሰጥዎ ዘንድ ይጸልዩ።
ሰባኪ ሆይ፥ በእርግጥ እርስዎ ልምድ ያለዎት ሰባኪ ነዎት። በዐውደ ምሕረትም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይም ብዙ ተከታዮች (subscribers) አፍርተዋል። የእርስዎ ስብከቶችም በሚሊዮኖች ታይተዋል። ነገር ግን ተከታዮችዎ ሙሉ ትኩረታቸው ሁሉ እርስዎ ላይ እንጂ ቤተክርስቲያን ወይም ክርስትናቸው ላይ አይደለም። የእርስዎን ነገሮች ሁሉ ሲያወድሱ ይውላሉ። በእውነት ይህም ከንቱ ነው። እርስዎ ለክርስቶስ ተከታዮችን ያፈሩ ዘንድ እንጂ እራስዎን በመስበክ ለራስዎ ተከታዮችን ሊያበዙ አልተላኩምና።
ሰባኪ ሆይ፥ ባለፈው ኢየሩሳሌም (ወይም ከሌሎች ቅዱሳት መካናት በአንዱ) ሄደው የተነሱት ፎቶ ላይ የርስዎ ፎቶ የራስ ዳሽንን ተራራ ሲያክል ከጀርባዎ ያለው የደብረ ዘይት ተራራ ደግሞ የየረር ኮረብታን ያክላል። ይህንን ፎቶም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለጥፈውት ብዙ ላይክ በማግኘትዎ ሐሴት አድርገዋል። ነገር ግን የሚያውቁትንና የሚያስተምሩትን እውነት እንነግርዎታለን። ይህም ከንቱ ነው። ራስን ማስመለክ ነውር ነውና ንስሐ ይግቡ።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ ዝነኛ ሰባኪ ነዎት። ልክ አርቲስቶች “የአርቲስት እገሌ አድናቂዎች ገጽ” ብለው ለራሳቸው ገጽ እንደሚፈጥሩት እርስዎም በስምዎ ከተከፈተ የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንት በተጨማሪ ‘የሰባኪ እገሌ ድንቅ ስብከቶች’ የሚል ገጽ የራስዎ ገጽ እንደሆነ መረጃ አለን። እየዋሹን ከሆነ ይህም ከንቱ ነው። እርስዎ ራስዎን ድንቅ ብለው ሊያደንቁ አይገባም ነበር።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ በሺዎች ዘንድ ‘ትንታግ ሰባኪ’ ይባላሉ። በሚዲያ ላይም ትንታኔ በመስጠት የሚቀድምዎ የለም። ነገር ግን ከመንፈሳዊነት ይልቅ አርቲስተነትዎ ያመዝናል። ይህ ሊያስቡበት የሚገባዎ የእርስዎ ጉዳይ ነው። እኛ ግን እንኳን ከሰባኪ ከማንኛውም የሰው ልጅ የማይጠበቅ ተግባርዎን እንነግርዎታለን። “ወንድሙን ደንቆሮ የሚለው የገሃነም እሳት ፍርድ ይገባዋል” (ማቴ 5: 22) የሚለውን የወንጌል ቃል እየሰበኩ ከእርስዎ ለየት ያለ ሀሳብ ወይም አመለካከት ያላቸውን ሰዎችን (ብፁዓን አበውን ጭምር)፣ ማኅበራትን እንዲሁም ማኅበረሰብን በዱር አራዊት፣ በዕፅዋት (ለምሳሌ እንክርዳድ፣ አረም ወዘተ እያሉ)፣ በበሽታ (ለምሳሌ ካንሰር፣ እባጭ ወዘተ እያሉ) እና በሌሎችም ሰውን ከሰውነት በሚያሳንሱ (dehumanize በሚያድረጉ) ቃላት ይሰድባሉ። የእርስዎ ወገን የሆኑት ክህደትን ሲያስተምሩ ግን ሰምቶ እንዳልሰማ ትንፍሽ እንኳን አይሉም። በዚህም ጥላቻን ይተክላሉ። በእርስዎ ምክንያትም ቤተ ክርስቲያን እንድትጠላ ያደርጋሉ። እኛ ግን እንልዎታለን፥ ከዚህ አይነት መሠሪ ድርጊትዎ ይቆጠቡ፣ የፍርድ ቀን ሳይመጣ ንስሐ ይግቡ፣ የበደሉትንም ሁሉ ይቅርታ ይጠይቁ።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ ሌላው እንዲሻሻል እንደሚሰብኩ እናውቃለን። ነገር ግን እርስዎን የሚያደንቅ አስተያየት ሲያዩ ይደሰታሉ፣ ላይክም ያደርጋሉ። ላይክን ራሱ ላይክ ማድረግ ቢቻል ኖሮ ያደርጉ ነበር ይባላል። እርስዎን የሚገስፅ አስተያየት ሲያዩ ግን በጣም ይበሳጫሉ፣ ጥሩ ያልሆነ ምላሽም ይሰጣሉ፣ ወይም ተሽቀዳድመው ያጠፉታል። እንዲሁም አስተያየት የሰጠዎትን ሰው Unfriend ወይም Block ያደርጋሉ። ይህም ከንቱ ነው። ሊያስደስትዎ በሚገባው ተበሳጭተዋልና ራስዎን ይመርምሩ።
ሰባኪ ሆይ፥ አንድ አንዴ ወደ እርስዎ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ጎራ ስንል እርስዎ “በእገሌ ታላቅ ደብር የነበረን አገልግሎት እንዲህ ያማረ ነበር” ብለው ጽፈው ከሥሩ ከሁለት ልብሰ ተክህኖ ከለበሱ ካህናት መካከል ተቀምጠው፣ እንዲሁም “ስሰብክ ለፌስቡክ የሚሆን ፎቶ አንሳኝ” ብለው የተነሱትን ማይክ አፍዎ ላይ ደቅነው የተነሱትን ፎቶ አጋርተዋል። ከሥር እርስዎን የሚያደንቁ አስተያየቶችን በሙሉ ላይክ አድርገዋል። ይህም ከንቱ ነው። ውዳሴ ከንቱን ላይክ በሚያደርጉበት ጊዜ በጸሎት ቢተጉ ይሻላል።
ሰባኪ ሆይ፥ የመዓርግ ስምዎትን እንደሚወዱት እናውቃለን። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስምዎን ራሱ ሲጽፉ ሁሉንም የመዓርግ ስሞችዎን አስቀድመው ነው። ሌላም ስም ለመጨመር እያፈላለጉ እንደሆነ ሰምተናል። ሰው ያለመዓርግ ስምዎ ሲጠራዎት እንደሚበሳጩ ሰማን። ባለፊው እኛ ጋር መጥተው ሳለ በተጸውኦ ስምዎ ብቻ የጠራዎትን ወንድም አስታወሱት አይደል? በእርስዎ ግልምጫ ደንግጦ እንደጠፋ ነው። እስካሁን አልተገኘም። እንግዲህ እውነቱን እንንገርዎት። ስምን ማግተልተልም ከንቱ ነው። ንፋስንም እንደመከተል ነው።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ አይነኬ ሰባኪ ነዎት። በደብራችን የነበረውንና እርስዎ የተወሰኑ ነገሮችን እንዲያስተካክሉ የነገረዎትን ወጣት ያስታውሱታል አይደል? እንዴታ እርሱንማ አይረሱትም! ገና በስብከት አገልግሎት ብቅ ከማለቱ ለንግሥናዎ ስለሰጉ በተሃድሶነትና በዝሙት ስሙን የሚያጠፉ ሠራዊትዎን እንዳሰማሩበት መረጃው አፈትልኮ ደርሶናል። ይህም የቤተክርስቲያንን አገልግሎት ተተኪ አልባ የሚያደርግ ከንቱ ንግሥና ነው። እንግዲህ ከወዴት እንደወደቁ ያስተውሉ፥ ፈጥነውም ንስሐ ይግቡ።
ሰባኪ ሆይ፥ መቼም እርስዎ በጥልቀት የማያውቁት የጥናት (የሙያ ዘርፍ) እንደሌለ አድናቂዎችዎ ያወራሉ። ምንም እንኳን የተማሩት መንፈሳዊ ትምህርት ቢሆንም ባለፈው ስለሦስተኛው የዓለም ጦርነት ትንታኔ ሲሰጡ ሰምተናል። ስለመሬት መንቀጥቀጥም የሰጡትን ሙያዊ ትንታኔ ተከታትለናል። ስለሕዋ ሳይንስም የምርምር መጽሐፍዎን ሊያሳትሙ እንደሆነ አውቀናል። በአጠቃላይ ሁሉን ያውቃሉ ይባላል። እኛ ግን እንልዎታለን። ይህ ሁሉ ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ ነው። ሰው ሁሉን ሊያውቅ አይችልምና የተማሩትን ብቻ አጥብቀው ይያዙ።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎን እንወድዎታለን። መቸኮልዎን ግን አንወድልዎትም። ማንኛውም አይነት መልስ የሚሻ አጀንዳ ሲፈጠር ተሽቀዳድመው መልስ ይሰጣሉ። መልስዎችዎ ግን የተጣደፉና አጥጋቢ ያልሆኑ እንደሆኑ ታዝበናል። መጣደፍም መሽቀዳደምም ከንቱ ነው። ሌሎች ሊቃውንት መልስ ይሰጡ ዘንድ ተውላቸው። ወይ በሚገባ መልሱ፣ አለዚያም ሌሎች በሚገባ እንዲመልሱ ዕድል ይስጧቸው።
ሰባኪ ሆይ፥ ጂም ይሠራሉ? ዋናስ ይዋኛሉ? ለጤናዎ ትንሽ የወይን ጠጅስ ይቀምሳሉ? እነዚህን ማድረግዎ ምንም አያስዎቅስዎትም። ግን ባለፈው ለጉባዔ ተጋብዘው በነበረ ጊዜ ከእነዚህ በአንዱ ምክንያት እሁድ ጠዋት ቅዳሴ አልተገኙም ነበር። ይህም ከንቱ ነው። ተማሪዎች ተገኝተው መምህሩ ሲቀር ምን እንደሚመስል አስበውታል?!
ሰባኪ ሆይ፥ መቼም ጉባዔ ሲጠሩ ባልተጻፈ ሕግ ገቢ ማስገባትም እንደሚጠበቅብዎ እናውቃለን። ወንጌልና ገቢ ስብሰባ (fund raising) መቀላቀሉ ቢያሳዝንም የእርስዎ ድርሻ ስብከት እንጂ ገቢ ማሰባሰብ እንዳልሆነም አሳምረን እንረዳለን። እርስዎም ለሥጋዊ ኑሮዎ የሚሆን ገንዘብ እንደሚያስፈልግዎ እንገነዘባለን። ነገር ግን እርስዎ ካስገቡት ገቢ ተመጣጣኝ ድርሻ (Commission) እንደሚጠይቁም ይወራል። ይህ እውነት ከሆነ ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ ንፋስንም እንደመከተል ነው።
ሰባኪ ሆይ፥ በየሄዱባቸው የውጭ ሀገራት ማኅበራትን እንደሚያደራጁም ይታወቃል። ዓላማው ቤተ ክርስቲያንን ተደራጅተው እንዲያገለግሉ ከሆነ ያስመሰግንዎታል። ነገር ግን አንዳንዶቹ ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ለእርስዎ ጥብቅና ይቆማሉ። ከአጥቢያቸው ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ይልቅ የእርስዎን መጽሐፍ ማሳተም ያስቀድማሉ። በግልጽ ቋንቋ የእርስዎ Promoter ሆነዋል። ይህም ከንቱ ነው። ቤተ ክርስቲያን የእርስዎ ግዛት (Empire) ማስፋፊያ አይደለችምና ይመከሩልን።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ ታላቅ መምህር ነዎት። በእርስዎ ትምህርት ከሌላ ሃይማኖት ተመለስን፣ ከተለያዩ ሱሶች ተላቀቅን ያሉ ሰዎች በእርስዎ ጉባዔ ላይ የሰጡትን ምስክርነት ሰምተናል። ቆይቶ ግን አንዳንዶቹ ገንዘብና ስልጠና ተሰጥቷቸው ይህንን ድራማ እንደተወኑ ተናግረዋል ይባላል። ይህም እውነት ከሆነ ከንቱ ነው። የድራማ ደራሲ መሆን ከፈለጉ ግን ወደ ትክክለኛ ቦታው ማምራት መብትዎ ነው።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ አንደበተ ርቱዕ መምህር ነዎት። የብሔርዎን ነፅሮተ ዓለም የማጥናት ጥልቅ ፍቅር እንዳለዎም እናውቃለን። ይህን ማድረግ ይችላሉ። ነገር ግን የራስዎን ነፅሮተ ዓለምና የክርስቶስ ወንጌልን አዳቅለው አይስበኩን። ይህም ከንቱ ነውና። ሁለቱን ለይተው በሚገባቸው መድረክ መስበክ ግን መብትዎ ነው እንላለን።
ሰባኪ ሆይ፥ ከማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋት በፊት መልካም ሰባኪ ነበሩ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ራስዎን አደገኛ የማኅበረሰብ አንቂ (Nefarious Activist) አድርገዋል። በማኅበራዊ ሚዲያም በማኅበረሰብ መካከል ጥላቻን፣ ግጭትን፣ ጦርነትን፣ መጠፋፋትን የሚያጋግሉ መልእክቶችን ይጽፋሉ። እነዚህም ለሚታየው የሕይወት መጥፋት፣ አካል ጉዳት፣ ንብረት ወድመት፣ የስነልቦና ስብራትና የሕይወት መመሰቃቀል ታላቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። እርስዎ በይፋ ባይናገሩትም በርቀት የአንዱ ቡድን የጦር መሪ ሆነዋል። ነገር ግን ዕድሉ ሲገኝ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምህረት ላይ ቆመው ላስጠቋቸው ሰዎች ወንጌል ሊሰብኩ ይሞክራሉ። በዚህም ቤተ ክርስቲያንንና ክርስትናን ያሰድባሉ። ይህ ከንቱ ነው። ይህ የጥፋት መንገድ ይብቃዎ፣ የፍርድ ቀን ሳይመጣ ንስሐ ይግቡ እንልዎታለን።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ ታዋቂ ሰባኪ ነዎት። ነገር ግን ራስዎ ለራስዎ ጉባዔ የፖስተርም የቪዲዮም ማስታወቂያ ይሠራሉ፣ ያሠራሉም። የራስዎን ማስታወቂያም ራስዎ ያጋራሉ። ይህም ሳይበቃ በማስታወቂያው ላይ ‘አጋንንት ይደነግጣሉ፣ ሽባዎች ይተረተራሉ’ ይላሉ። እኛ ግን የሚጮህ የእርስዎን ድምጽ እንጂ የደነገጠ አጋንንት ወይም የተተረተረ ሽባ አላየንም፣ አልሰማንም። ይህ ሁሉ ራስዎን ለማስተዋወቅ የሚደክሙት ከንቱ ነው። ከዚህ ራስን የማምለክ አባዜ ይወጡ ዘንድ ይጸልዩ።
ሰባኪ ሆይ፥ በምሽት “የጧፍ ማብራት” ጉባዔዎ ምዕመናን ጥቃቅን ጧፍ እያበሩ የሰማይ ክዋክብትን፣ እርስዎ ደግሞ መድረክ ላይ ቆመው አጣና የሚያክል ጧፍ እያበሩና ከበሮም እየመቱ ፀሐይን (the biggest star) መስለው ባጠቃላይ Universe መስላችሁ ስትታዩ “ያምራል” ብለው ያስባሉ አይደል? ግን ይህም ከንቱ ነው። መቼም “ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” የተባለው ይህንን እንዳልሆነ እርስዎም ያውቁታል።
ሰባኪ ሆይ፥ መቼም እንዳለመታደል ሆኖ እኛን በየዘመናቱ ግጭትና ጦርነት አያጣንም። ያለፈውን ጦርነት ያስታውሳሉ አይደል? አንዴ እርስዎ የሚደግፉትን ርዕዮተ ዓለም የሚያራምደውን ቡድን “ግፋ በለው!” ሲሉ ነበር። ሌላ ጊዜ ደግሞ አንዱን ወገን ሀገር ታዳጊ መልአክ ሌላውን ሀገር አፍራሽ ሰይጣን አድርገው ሲሰብኩ ነበር። ሰው “እንዴ! ምን ነካዎት?” ሲልዎ ደግሞ ጎጂንም ተጎጂንም፣ ገዳይንም ሟችንም አጃምለው ሲኮንኑ ነበር። ይህንን ሁሉ አልፈነዋል። ግን ዛሬ ላይ በአደባባይ ወጥተው “ያንን ጦርነት በመቃወም የቀደመኝ የለም” ብለው ዋሹን። አዎን! ይህ ከንቱ ነው። ያየነውንና የሰማነውን ከዋሹን ስላላየነው ቢሰብኩ እንዴት ይታመናሉ? ደግሞም በሕግና በእግዚአብሔር ፊት አንድ ቀን ይጠየቃሉ።
ሰባኪ ሆይ፥ አንድ ሰባኪ ስብከቱን ከነባራዊ ሁኔታው (context) ጋር አለመነጠል፣ በዐውደ ምሕረት ሲቆም የምዕመናንን ስሜት ማዳመጥና ማንጸባረቅ፣ እንዲሁም በስብከቱ ዋልታ-ረገጥነትን (Polarization) መገሰፅ እንዳለበት አይስቱትም። እርስዎ ግን ሐዘን በነገሠበት ስለ ደስታ ይሰብካሉ። መጽሐፍ ‘ያዘነ ቢኖር ይጸልይ’ እያለ እርስዎ ያዘኑ ምዕመናን ማጽናናት ሲገባዎ በከበሮ (እልል በሉ እያሉ ጭምር) እንዲዘምር ያደርጋሉ። ዋልታ-ረገጥ ድርጊቶችንም በግልፅ አይገስፁም፣ በኅቡዕ የሚያበረታቱም ይመስለናል። ይህ ሁሉ ከንቱ ነው። በእሳትም እንደመጫወት ነውና ንስሐ ይግቡ።
ሰባኪ ሆይ፥ ከስብከትዎ በተጨማሪ የግል የምክር አገልግሎት (counseling services) እንደሚሰጡም ሰምተናል። የምክር አገልግሎት መስጠት ብዙ የሙያ ዝግጅት ይጠይቃል። እርስዎ ግን ምንም ሙያዊ ዝግጅት ሳይኖርዎ ስብከት ስለቻሉ ብቻ በድፍረት የምክር አገልግሎት ውስጥ መግባትዎ የድፍረት ከንቱነት ነውና ተመልሰው ሙያውን ይማሩ እንልዎታለን። ያለበለዚያ ሰው ባልተማረው ሙያ መሥራትን እንዲደፍር መጥፎ አርአያ ይሆናሉ። እንዲሁም ብዙ የትምህርትና ስልጠና ዝግጅት የሚፈልገውን ሙያ ያስንቃሉ። በዓለማዊ መስፈርት ጭምር ከደረጃ በታች የሆነ አገልግሎት በመስጠትም በሰው ላይ ጉዳትን ያደርሳሉ፣ የቤተ ክርስቲያንን ስምም ያጎድፋሉ። በመጨረሻም ይጠየቁበታል።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ ገና ወጣት ነዎት፣ ትዳርም አልመሠረቱም፣ ወይም መነኮስ ነዎት። ነገር ግን ጎልማሶችን ሰብስበው ስለትዳር ሕይወት፣ ስለልጆችም አስተዳደግ በድፍረት ያስተምራሉ። በዝርወት ዓለም የተወለዱ ልጆችንም ሰብስበው እርስዎ በማይችሉት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሊያስተምሩ ይደፍራሉ። ይህ ሁሉን አውቃለሁ፣ ሁሉን እችላለሁ ማለትዎና የሰዎችን ምክር ከመጤፍ አለመቁጠርዎ ከንቱ ነው። በተሰጥዎ መክሊት ላይ ብቻ ቢያተኩሩ መልካም ነው እንላለን።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ ስለመልካምነት ስለበጎ አድራጎት አብዝተው ይሰብካሉ። መልካም ነው። ነገር ግን እርስዎ ከሕግ ውጭ ወልደው የካዷቸው ልጆችዎ እና እናታቸው አደባባይ ወጥተው እንደ በደሏቸው እየተናገሩ ነው። የሚሰብኩት መልካምነትና በጎ አድራጎት ለእርስዎ ካልሠራ ከንቱ ነው። መጽሐፍ ቤተሰቡን የካደ ከማያምን የከፋ ነው ይላልና። (1ኛ ጢሞቴዎስ 5:8)
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ ዕውቅ ሰባኪ ነዎት። በዐውደ ምሕረትም፣ በማኅበራዊ ሚዲያም ይሰብካሉ። የስብከት ርዕስ ሲመርጡ ግን ሰው የሚፈልገውንና የሚወደውን ብቻ ነው። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እይታን ለማግኘት ብቻ ሲሉ በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተመለሰን ጥያቄ (መልሱን እያወቁት) ዛሬ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደ አዲስ ጠይቀው ውዝግብ ያስነሳሉ። አንዳንዴም የራስዎን ቪዲዮም ለማያውቁት ሰው ጭምር ኢንቦክስ (Inbox) ያደርጋሉ። ይህም ብዙ View፣ Like እና share ለማግኘት እንደሆነ ህሊናዎ ያውቀዋል። እርስዎ እንደሚሉት ግን ይህም ከንቱ ነው። ሰው የሚፈልገውን ብቻ ሳይሆን ለሰው የሚያስፈልገውንም ይስበኩ።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ ጥሩ ሰባኪ ነበሩ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የለየለት የፖለቲካ ተንታኝ ሆነዋል። “በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ጥሩ አይደለም፤ እባክዎ አንዱን ይያዙ” ሲባሉ ‘ስብከቱን በካባና በመስቀል፣ ፖለቲካውን በኮትና በከረባት ስለሆነ የምናገረው አይጋጭብኝም፣ ሁለቱንም ጎን ለጎን ማስኬድ እችላለሁ’ ይላሉ። ይህም ከንቱ ነው። ለእርስዎ ጎን ለጎን የሚመስልዎ ለአድማጭ ግን የተደባለቀ ወተትና ቡና (ማኪያቶ) ነው። ስለዚህ እኛም አንዱን ይያዙ እንልዎታለን።
ሰባኪ ሆይ፥ በአጠገብዎ ያሉ ጓደኛችዎ ‘ጥሩ ይሰብካሉ!’ ይሉዎታል አይደል? እንደውም ባለፈው ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ሰኔ 3 ቀን የተገዛው ቦታ አድራሻው 24 XXX Road መሆኑ 3 የሥላሴ፣ 24 ደግሞ የ24ቱ ካህናተ ሰማይ ምሳሌ ነው ሲሉ ብዙ ሰው አጨብጭቦልዎታልና የሚረሱት አይመስለንም። ይህን አይነት ስብከት እየሰበኩም ከእውነተኞቹ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ጋር ትከሻ ሊለካኩ ይቃጣዎታል። እኛ ግን እንልዎታለን! ለተገኘው ቁጥር ሁሉ ምስጢርና ምሳሌ መፍጠርን እንደ ጥበብ የሚቆጥር ‘አማተር ሰባኪነት’ ከንቱ ነውና አስቀድመው ከሊቃውንቱ ይማሩ።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ በጣም ደፋር ሰባኪ ነዎት። ነገር ግን በየትኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ቤቶች ገብተው አልተማሩም። በቤተ ክርስቲያንም ከአባቶች እግር ሥር እየተማሩም አላደጉም። ስለ ስብከት ዘዴም አጭር ስልጠናም እንኳን አልወሰዱም። ቅዱሳት መጻሕፍትንም በሚገባ አንብበው የተረዱ አይመስሉም። በእኛ መረዳት ከማኅበራዊ ሚዲያና ከሌሎች ተባራሪ ምንጮች ከቃረሟቸው መረጃዎች ብቻ ተነስተው የሚሰብኩ ይመስለናል። “ይመስለናል” የምንልዎ እርስዎም ብዙ ጊዜ “ይመስለኛል” እያሉ ስለሰበኩን ነው። ብዙዎቹ ስብከቶችዎ (ቀልዶችዎ ጭምር) ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አስቀድመን ያየናቸው ናቸው። በእውነቱ ራስዎ ያላወቁትን ለእኛ ሊያሳውቁ፣ ራስዎ ያልተማሩትን ለእኛ ሊያስተምሩ መድፈርዎ ከንቱ ነው። በመጀመሪያ የቤተ ክርስቲያንዎን አስተምህሮ በሚገባ ለይተው ይወቁ፣ ያላወቁትን ይጠይቁ፣ ራስዎንም ያስተምሩ። የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ ሲጠነቅቁ ያኔ ሊያስተምሩን ይችሉ ይሆናል።
ሰባኪ ሆይ፥ በሚጣፍጥ ስብከትዎ የቤተ ክህነት አስተዳደር በችግር የተተበተበና ብልሹ አሠራር የተንሰራፋበት እንደሆነ ተናግረዋል። እርሱን ከእኛ በተሻለ እርስዎ ያውቁታል። ግን እርስዎ እዚህ ሊሰብኩን ሲመጡ በትውውቅ እንጂ በቤተ ክህነት ስምሪት አይደለም። የእርስዎን አጥቢያ ለማስፈቀድ ፈልገንም ልናውቀው አልቻልንም። በእውነት እርስዎ ራስዎ በማይፈጽሙት አሠራር ቤተ ክህነቱን መውቀስዎ ከንቱ ነው። መሻሻል ከእርስዎ ቢጀምርስ ምን ይመስልዎታል?
ሰባኪ ሆይ፥ ባለፈው እንደቀልድ ስናወራ ጥሩ ሰባኪ ማን ነው? በምንስ ይገለጻል? ሲባሉ ጥሩ ሰባኪ ደብተር አይዝም (ሞባይልም አያይም) በቃሉ ብቻ ያስተምራል ብለውን ነበር። እርስዎም ባለፈው ስብከትዎ ማስታወሻ ባለመያዝዎ ይናገሩት የነበረው ከተነሱበት ርዕስ ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ ነበር። በእውኑ ስብከት ሰው ካላዳመጠው፣ መልእክቱ ካልገባው ከንቱ መለፍለፍ አይደለምን? መጽሐፍስ ሰባኪ ይዘጋጅ ዘንድ ‘የልብ ዝግጅት ከሰው ነው’ ይል የለምን?
ሰባኪ ሆይ፥ መቼም እርስዎ ታዋቂ ሰባኪ በመሆንዎ እርስዎ ባሉበት ብዙ ሰው ስለሚገኝ ጥቂት ሰው ባለበት መስበክ አያስደስትዎትም። እንደውም ያስታውሱ ከሆነ ባለፈው እኛ ጋር መጥተው ሳለ ወጣቶችን እንዲያስተምሩ ሲጋበዙ “ስንት ይሆናሉ?” ብለው የጠየቁትን። የተላከውም ልጅ “አንድ ሰላሳ ይሆናሉ” ሲልዎት ‘እኔ ራሴን አሞኛል፣ ራስህ አስተምራቸው በለው’ ያሉትን። መምህር ሆይ፥ በሰው ቁጥር ብቻ ማመንዎ ከንቱ ነው። እንዲዚያ ቢሆንማ ኖሮ ክርስቶስ ዘጠና ዘጠኙን ትቶ አንዱን ለመፈለግ ባልመጣም ነበር።
ሰባኪ ሆይ፥ በአንድ ወቅት አብረን ሳለን “እርስዎ በእድሜ ትልቅ ነዎት፤ ለምን ትዳር አይመሠርቱም?” ተብለው ሲጠየቁ “ትዳር መመሥረት እኮ በጣም ቀላል ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ከሚመጡት አንዷን ጎተት አድርጎ ተክሊል መፈጸም ይቻላል” ያሉትን ያስታውሳሉ? ክርስቶስ ያከበረውን ትዳር እንደዚህ አቅለው ማሰብዎ ከንቱነት ነው። ለእኅቶችም ያለዎት ንቀት አሳፋሪ ነው። በእውኑ ለሌላው የሚያስተምሩት ለእርስዎስ አይሠራምን? ትዳርስ ታላቅ ተቋም ስለሆነ አመሠራረቱም በጾምና በጸሎት እንጂ አንዷን ጎተት በማድረግ አይደለም።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ ብዙ ተከታይ ያለዎት ሰባኪ ነዎት። ነገር ግን በብዙ ስብከቶችዎ ውስጥ የፈጠራ ተረቶችን ፍጹም መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታዎች አስመስለው ያቀርባሉ። ይህም ከንቱ ነው። መጽሐፍ “ለዚህ ዓለም ከሚመችና የአሮጊቶችን ሴቶች ጨዋታ ከሚመስለው ተረት ራቅ።” (1ኛ ጢሞቴዎስ 4:7) ይላልና ተረቶችን ከስብከትዎ ያርቁ ስንል እንማጸናለን።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሊቅ ነዎት። ነገር ግን የጠልሰም ዕውቀት የጥንታውያን ሊቃውንት ድንቅ ጥበብ እንደሆነ እና ከክርስትና አስተምህሮ ጋር የሚስማማ እንደሆነ ይሰብካሉ። እኛ ግን እንልዎታለን፥ የክርስትናችን አብነት የሆነን ክርስቶስ ይህንን አላስተማረንም። ስለዚህ ይህም ከንቱ ነው። የቀደመ መልካምነትዎን ቢያሳዩን ይሻለናል።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ ጥሩ ሰባኪ ነዎት። ነገር ግን ብዙ ጊዜ የሌላ ቤተ እምነት ሰዎች የሚያስተምሩትን እንጂ የእኛ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረውን አያስተምሩንም። ስለሌሎች ሲያስተምሩም የሚሉትን እንደማይሉ፣ የማይሉትን እንደሚሉ አድርገው በስማ በለው የሰሙትን ሲናገሩ ሰምተናል። ቢጠነቀቁ ራስዎንም ሰሚዎችዎንም ይጠብቃሉ። አንዳንዴ ደግሞ “አውሬው ሊመጣ ቀርቧል!” እያሉ ያሸብሩናል። ይህም ከንቱ ነው። ይልቁንስ የበሰለውን የሊቃውንቱን ትምህርት ቢመግቡን እኛም እርስዎም እናተርፋለን።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ ጠለቅ ያለ መንፈሳዊ ትምህርትን የሚያስተምሩ ሰባኪ ነዎት። ዳጎስ ያሉ መጻሕፍትንም አበርክተውልናል። በዚህም እናከብርዎታለን። ነገር ግን ሌሎች አገልጋዮችን በጣም ይንቃሉ፣ አሳንሰው ያያሉ፣ አንዳንዴም ያንኳስሳሉ። በራስዎ ዕውቀት እየታበዩ አንዳንዶቹንም ከማበርታት ይልቅ “በቃ ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት ለእናንተ አይሆንም፣ ሌላ ሥራ ብትሞክሩ ይሻላችኋል” እያሉ ተስፋ ያስቆርጧቸዋል። ትንሽ ጠንከር ባሉት አገልጋዮች ላይ ደግሞ ያለዎት ምልከታ የቅናት ይመስላል። በአጠቃላይ ከእርስዎ በቀር ያለው አገልግሎት አያስደስትዎትም። ይህም ከንቱ ነው። ቤተ ክርስቲያን የሁሉም እንጂ የእርስዎ ብቻ አይደለችምና በትሕትና ያገልግሉን።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ በብዙ መድረኮች ላይ የሚሰብኩ ነዎት። ነገር ግን ስብከትዎችዎ በአብዛኛው ሁለት ነገሮች ላይ ያጠነጥናሉ። አንደኛው ስድብ (መሳደብ) ነው። በዚህም እርስዎ የማይወዷቸውን ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ተቋማት ስም እየጠቀሱም ሳይጠቅሱም ዐውደ ምሕረት ላይ ቆመው ሲሳደቡ ይውላሉ። ሁለተኛው ስብከትዎ ደግሞ ፉከራ (መደንፋት) ነው። በዚህም እኛ ጥንታውያን ነን፣ በቁጥር ብዙ ነን፣ ሁሉን ያስተማርን እኛ ነን፣ የሚችለን የለም እና የመሳሰሉትን እያሉ በመደንፋት የስብከት ጊዜዎን ይጨርሳሉ። ከቅርብ ሰዎችዎ እንደምንሰማው ደግሞ ይህንን ስብከትዎን “እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ ያለ ተግሳጽ ነው” ብለው እንደሚያስቡ ተረድተናል። እኛ ግን እንልዎታለን። ስድብና ድንፋታ ተግሳጽ ሳይሆን ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ ነው። ስለዚህ ወደ ሕሊናዎ ተመልሰው ትሕትናና ፍቅርን ይስበኩ።
ሰባኪ ሆይ፥ እርጋታና ጠለቅ ያለ መልእክት ያላቸው ብዙ ስብከትዎችዎን እየሰማን ስላደግን እንደ አባት እናከብርዎ ነበር። ነገር ግን በቅርብ ጊዜ በነበረው ጦርነት ድንገት ተለውጠውብን በማኅበራዎ ትስስር ገፅዎ ላይ ፍፁም አረመኔነት የተሞሉ ብዙ ጽሑፎችን የሃይማኖት ስብከት አስመስለው ሲጽፉና ሲለጥፉ አስተውለናል። በዚህ ድርጊትዎም እጅግ አዝነን፣ አልቅሰንም ነበር። ግን ደግሞ አንድ ቀን ተነስተው ሁሉንም ጦረኛ ጽሑፎችዎን አጥፍተው ምንም እንዳልተፈጠረ ቆጥረው ወደ ቀደመው ልማድዎ ተመለሱ። በእርግጥ ባደረጉት ከልብ ተጸጽተው፣ ንስሐ ገብተውና የበደሉትን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀው ከሆነ መልካም ነው። የተደበቀ ማንነትዎ በነዚያ ክፉ ወራት ገንፍሎ ወጥቶ እንደገና መልሰው ደብቀውት ከሆነ ግን ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ ነው። ሰው (ሊያውም ሰባኪ) ክፋቱን ደብቆ መንፈሳዊ መስሎ በመኖር አይድንምና ከልብዎ ተጸጽተው ንስሐ ይግቡ እንልዎታለን።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ የተዋጣልዎት ሰባኪ ነበሩ። በስብከትዎም የቤተ ክህነትም ይሁን የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አሠራር ምን መሆን እንዳለበት አብራርተው ያስተምሩን ነበር። ጊዜው ደርሶ እርስዎም በዚያ ቦታ ሲቀመጡ ያስተማሩትን በተግባር ያሳዩናል ብለን ስንጠብቅ እርስዎ ግን በተቃራኒው ሲተቿቸው ከነበሩት ከበፊቶቹ ይልቅ ከፉብን። የሽማግሌዎችን ሳይሆን የአብሮ አደጎቹን ምክር እንደሰማው ሮብዓም ሆኑብን፣ በቀንበራችን ላይ ጨመሩብን፣ በጊንጥም ገረፉን (1ኛ ነገ 12:1-17)። አዎን፥ ይህም ከንቱ ነው። ስልጣንም አላፊ ነውና ከጭካኔዎ ተመልሰው ንስሐ ይግቡ እንልዎታለን።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ ትጉኅ ሰባኪ ነበሩ። ባለዎት ተደማጭነትም ለመንግሥት ስልጣን በቅተዋል። በዚህም የቤተ ክርስቲያን ስደት፣ የክርስቲያኖችም ሞት ያበቃ ዘንድ ወገኖቿ እስራኤልን እንደታደገችው እንደ አስቴር የበኩልዎን ይወጣሉ ብለው ተስፋ ያደረጉ የዋሐንን ቤት ይቁጠራቸው። እርስዎ ግን አስቴርን ሳይሆን ሐማን አብነት አድርገው የቤተ ክርስቲያን ስደት፣ የክርስቲያኖችም ሞት ከቀደመው ይልቅ እጅግ እንዲከፋ ተግተው ሠሩ። ነገርዎት ሁሉ እንደ ባለ አእምሮ ሳይሆን አንዳች ክፉ መርዝ እንደቀመሰ ለማዳ የቤት እንስሳ እንደ ጤዛ ለሆነ የማሸርገድ ስልጣንዎ ስጋት የሆነውን ሁሉ ያለ መታከት መንከስ መሆኑን ታዝበናል። ቀድሞ ያቀነቅኗቸው የነበሩ የቤተ ክርስቲያን እና የክርስቲያኖችን “አጀንዳዎች” ጭቃ መቀባት ዋና ተግባርዎ የሆነ ይመስላል። ይህም ከንቱ ነው። የቤተ ክርስቲያን እና የክርስቲያኖች መዳን ከሌላ ስፍራ ይሆን ይሆናል። እርስዎ ግን አንድ ቀን በሕግና በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ ይቀርባሉና ፈጥነው ንስሐ ይግቡ።
ሰባኪ ሆይ፥ እርስዎ በስብከት ያገኙትን ታዋቂነት ተጠቅመው በቤስት ኔት፣ በኩዌስት ኔት፣ በቲያንስና በመሳሰሉት የnetwork marketing ስልቶች (ንግድ) አቅልዎን ስተው ስናይዎት አዘንን። በእርስዎና በመሰሎችዎ የማጭበርበርና የማምታታት አሠራር (business model) በርካታ የዋሐን ምዕመናን ገንዘባቸውን ተበሉ። ከዚያም ባሻገር መንፈሳዊ አገልግሎትንና በብዙዎች ኪሳራ ጥቂት በፒራሚድ አናት ላይ የተቆናጠጡ ጬልሌዎች ያለአግባብ በሚበለጽጉበት የማጭበርበር ንግድን ከመቀላቀልዎት የተነሳ የከሰሩ ብዙዎች “ማን የሚታመን አለ?” እያሉ ከንግዱም፣ ንግዱን ካሳለጠው “አገልግሎትም” ሲሸሹ ታዝበናል። እርስዎ ግን ተጠቃሚ ስለሆኑ ዓይኔን ግንባር ያድርገው ብለው “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” የሚል የቅዱስ ጳውሎስን ቃል ለክፋትዎ መሸፈኛ እየጠቀሱ ቀጥለዋል። አሁንማ እርስዎና መሰሎችዎ የተለመደ ወለፈንዲ የቢዝነስ አሰራራችሁን (business model) አሳድጋችሁ ባንኩንም፣ ሚዲያውንም፣ ሱቁንም፣ ሆስፒታሉንም ለመምራት እየተጠቀማችሁበት እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነው። ይህ ሁሉ ከንቱ ነው። መንፈሳዊ አገልግሎት ያስገኘውን ታዋቂነት ለሥጋዊ ጥቅም ማካበቻ ማዋል እንኳን እግዚአብሔር ፍትሐዊ የምድር ባለስልጣናትም የሚጸየፉት መሆኑን ለእርስዎ ለማስረዳት ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከቀደምት ሊቃውንት ትምህርት መጥቀሱን “ለቀባሪው መረዳት” ይሆናል በማለትና መልእክቱን ላለማስረዘም ትተነዋል።
ሰባኪ ሆይ፥ ለመሆኑ ታላቅ የቢዝነስ ሰው ወይም ታዋቂ የሚዲያ ባለቤት (Media mogul) ወይም ከፍተኛ ባለስልጣን የመሆን ሕልም አለዎት? በስብከት አገልግሎት ያገኙትን ታዋቂነት ለዚህ ሕልምዎ የማኅበራዊ መሠረት መደላድል ካደረጉት በእውነት ከንቱ ነው። እኛ በትሕትናና በፍቅር ቢያገለግሉ እንወዳለን። ይህ ሕልም ካለዎት ግን በጊዜ ይፋቱንና ወደዚያው ያምሩ። መልካምም ዕድል ይሁንልዎ!
ሰባኪ ሆይ፥ እስካሁን ድረስ እድሜህን ታሳቢ ሳናደርግ “እርስዎ” እያልን የጠራንህ ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? በዘመናችን የበቀላችሁ ሰባክያን አስገዳጅ ሃይማኖታዊ መሰረት የሌለው ቢሆንም፣ ባሕልን ለራስ በሚመች ሁኔታ ቆልምማችሁ ድክመታችሁን በአንቱታ መሸፈን እንደምትፈልጉ ስለምናውቅ፣ የእድሜ ታላላቆቻችሁን ሳይቀር በአንቱታ አልጠራኝም ብላችሁ እንደምታኮርፉ ስለምናውቅ “አንተ” ብለን ጦማሩን ብንጀምር እንደ ተራ “የስም አጠራር ባሕል” ከማየት ይልቅ ምስጢረ ሥላሴን ካፋለሰ መናፍቅ በበለጠ እንደምትጸየፈንና በዚያም የተነሳ ጦማሩን ከማንበብ እንዳትናጠብብን ብለን ነው። ነገር ግን መከራ ልትቀበልበት ቃል ኪዳን ገብተህ የጀመርከውን የስብከት አገልግሎት የአንቱታ መሸመቻ ማድረግህ ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ ድካም መሆኑን ልናስታውስህ እንወዳለን። አምላካችን እግዚአብሔር እድሜ ከሰጠን ይህን “የአንቱታ አምልኮ” ሃይማኖታዊ አስተምህሮን ከባሕላዊ ልማድ መለየት ለማይሳንህ ለአንተ ሳይሆን ያን መረዳት ለሚከብዳቸው የዋሐን ምዕመናን በሚስማማ መልኩ በሌላ ጦማር እንመለስበታለን። ለማንኛውም አንተም ሆነ እርስዎ ብትባል ለመስማት የተዘጋጀ ልብና ቀልብ ይኑርህ።
አቤቱ ጌታ ሆይ፥ የሰባኪውን ከንቱነት መዘርዘርም ራሱ ከንቱነት ነው። እኛ ይህንን የጻፍነው አንተ በፍጹም ትሕትናና ፍቅር ባገለገልህባት ዐውደ ምሕረት ከንቱነት ነግሦ ብናይ ልባችን ተቃጥሎብን እንጂ እኛ ከሰባኪው እግር ስር ተቀምጠን መማር እንኳን የማይገባን ደካሞች ልጆችህ ነን። አቤቱ እንደ ቸርነትህ ብዛት ማረን።