የዘወትር ጸሎት፣ ውዳሴ ማርያም፣ አንቀጸ ብርሃንና ይዌድስዋ መላእክት
ከዚህ በታች የዘወትር ጸሎትን፣ ውዳሴ ማርያምን፣ አንቀጸ ብርሃንንና ይዌድስዋ መላእክትን በአማርኛ ቋንቋ ያገኛሉ። ጸሎቱን ለመክፈት ከታች ያሉትን መስፈንጠርያዎች (ሊንኮች) ይጫኑ (click ያድርጉ)። ለመዝጋት እንደገና ይጫኑት። Below are the Introductory Prayers, the daily Theotokia, The Gate of Light, and The Angels Praise Her in Amharic language. Click on the links below to open the prayers and praises, and click again to collapse
የዘወትር ጸሎት
በጌታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ትዕምርተ መስቀል ፊቴንና መላ ሰውነቴን ሦስት ጊዜ አማትባለሁ፡ አንድ አምላክ በሆኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ንጹሕ ልዩ ክቡር ጽሩይ በሆኑ በሦስትነት ወይም በሥላሴ እያመንኩና እየተማጸንኩ ጠላቴ ሰይጣንን እክድሃለሁ፤ በዚህች በእናቴ በቤተ ክርስቲያን ፊት ቁሜ እክድሃለሁ ለዚህም ምስክሬ ማርያም ናት። በዚህም ዓለም በወዲያኛውም ዓለም እርሷን አምባ መጠጊያ አድርጌ እክድሃለሁ።
አቤቱ እናመሰግንሃለን፤ አቤቱ እናከብርሃለን፤ አቤቱ እንገዛልሃለን፤ አቤቱ ቅዱስ ስምህን እናመሰግናለን። ጉልበት ሁሉ የሚሰግድልህ አቤቱ እንሰግድልሃለን፤ አንደበትም ሁሉ ለአንተ ይገዛል፤ የአምላኮች አምላክ፣ የጌቶች ጌታ፣ የንጉሦችም ንጉሥ አንተ ነህ፤ የሥጋም የነፍስም ፈጣሪ አንተ ነህ። እናንተስ በምትጸልዩበት ጊዜ እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ ብሎ ቅዱስ ልጅህ እንዳስተማረን እንጠራሃለን።
አባታችን ሆይ፤ በሰማያት የምትኖር፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን፤ የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ፤ በደላችንንም ይቅር በለን፤ እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል። አቤቱ ወደ ፈተናም አታግባን፤ ከክፉ ሁሉ አድነን እንጂ፤ መንግሥት የአንተ ናትና ኃይል ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ አሜን።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ፤ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እንልሻለን። በሀሳብሽ ድንግል ነሽ፤ በሥጋሽም ድንግል ነሽ። የአሸናፊ የእግዚአብሔር እናት ሆይ ለአንቺ ሰላምታ ይገባሻል፤ ከሴቶቹ ሁሉ ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ፤ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና ከተወደደው ልጅሽ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ይቅርታንና ምሕረትን ለምኝልን ኃጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ ለዘለዓለሙ አሜን።
ሁሉን የፈጠረ አንድ አምላክ በሚሆን በእግዚአብሔር አብ እናምናለን። ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የሚታየውንና የማይታየውን። ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ አንድ የአብ ልጅ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን። ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ። የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ በባሕርዩ ከአብ ጋር የሚተካከል ሁሉ በእርሱ የሆነ በሰማይም ካለው በምድርም ካለው ያለ እርሱ ምንም ምን የሆነ የለም። ስለእኛ ስለ ሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ ወረደ፤ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ሆነ። ደግሞም ስለእኛ ተሰቀለ፤ በጰንጤናዊ በጲላጦስ ዘመን እርሱ መከራን ተቀበለ፣ ሞተ፣ ተቀበረ፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሳ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈ በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ፤ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ላይ ለመፍረድ በምስጋና ይመጣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም። በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን፤ እርሱም ጌታ ሕይወትን የሚሰጥ ከአብ የሠረፀ ከአብና ከወልድ ጋራ በአንድነት እንሰግድለታለን፤ እናመሰግነዋለን፤ እርሱም በነቢያት አድሮ የተናገረ ነው። ከሁሉም በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሠሯት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን። ኃጢአት በሚሠረይባት በአንዲት ጥምቀትም እናምናለን። የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን። የሚመጣውንም ሕይወት ለዘለዓለሙ አሜን።
አሸናፊ እግዚአብሔር ሆይ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብለህ ትመሰገናለህ። ምስጋናህም በሰማይና በምድር የመላ ነው። ክርስቶስ ለአንተ እንሰግድልሃለን ከሰማያዊ ከቸር አባትህ ጋራ አዳኝ ከሆነ ከመንፈስ ቅዱስም ጋራ እንሰግድልሃለን። ወደዚህ ዓለም መጥተህ አድነኸናልና።
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አንዲት ስግደት እሰግዳለሁ (ሦስት ጊዜ በል)። አንድ ሲሆን ሦስት፤ ሦስት ሲሆኑ አንድ፤ በአካል ሦስት ሲሆኑ በመለኮት አንድ ለሚሆኑ እሰግዳለሁ። አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም እሰግዳለሁ፤ ዓለምን ሁሉ ለማዳን ሲል ኢየሱስ ክርስቶስ ለተሰቀለበት መስቀልም እሰግዳለሁ። መስቀል ኃይላችን ነው፤ ኃይላችን መስቀል ነው፤ የሚያጸናን መስቀል ነው፤ መስቀል ቤዛችን ነው፤ መስቀል የነፍሳችን መዳኛ ነው። አይሁድ ይክዱታል እኛ ግን እናምነዋል ያመነውም እኛ በመስቀሉ እንድናለን ድነናልም።
ለአብ ምስጋና ይገባል ለወልድም ምስጋና ይገባል ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል (ሦስት ጊዜ በል)። አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም ምስጋና ይገባል፤ ለኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልም ምስጋና ይገባል። ክርስቶስ በቸርነቱ ያስበን ዘንድ፤ ዳግመኛም በመጣ ጊዜ እንዳያሳፍረን፤ ስሙን ለማመስገን ያነቃን ዘንድ፤ እርሱንም በማምለክ ያፀናን ዘንድ። እመቤታችን ጸሎታችንን አሳርጊልን፤ ኃጢአታችንንም አስተሥርዪልን፤ በጌታችን መንበር ፊት ጸሎታችንን አሳርጊልን። ይህንን ኅብስት ላበላን፤ ይህንንም ጽዋ ላጠጣን፤ ምግባችንንና ልብሳችንንም ላዘጋጀልን፤ ኃጢአታችንንም ሁሉ ለታገሰልን፤ ክቡር ደሙን ቅዱስ ሥጋውን ለሰጠን፤ እስከዚህችም ሰዓት ላደረሰን፤ ለእርሱ ለልዑል እግዚአብሔር ፍጹም ምስጋና ይገባል፤ ለወለደችው ለድንግልም ምስጋና ይገባል፤ ለክቡር መስቀሉም ምስጋና ይገባል። የእግዚአብሔር ስሙ ፈጽሞ ይመሰገን ዘንድ ዘወትር በየጊዜያቱና በየሰዓቱ ምስጋና ይገባል።
እናታችን ማርያም ሆይ ሰላም ለአንቺ ይሁን እያልን እንሰግድልሻለን እንማልድሻለን። ከአዳኝ አውሬ ታድኝን ዘንድ ተማጽነንብሻል። ስለ እናትሽ ስለ ሐና ብለሽ ስለ አባትሽ ስለ ኢያቄም ብለሽ ድንግል ማኅበራችንን ዛሬ ባርኪልን።
አምላክን በድንግልና የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ጸሎት። ማርያምም አለች ነፍሴ እግዚአብሔርን ታላቅ ታደርገዋለች፤ መንፈሴም በመድኃኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ይላታል፤ የባሪያዪቱን መዋረድ አይቷልና። እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ እርሱ ብርቱ የሚሆን ታላቅ ሥራን ለእኔ አድርጓልና። ስሙም ቅዱስ ነው፤ ለሚፈሩትም ምሕረቱ ለልጅ ልጅ ነው፤ ኃይልን በክንዱ አደረገ። በልባቸው አሳብ የሚኮሩ ትዕቢተኞችን በታተናቸው፤ ብርቱዎችንም ከዙፋናቸው አዋረዳቸው፤ የተዋረዱትንም ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ የተራቡትንም በቸርነቱ አጠገባቸው፤ ባለጠጎችንም ባዶ እጃቸውን ሰደዳቸው። ምሕረቱን እንዲያስብ እስራኤል ባርያውን ተቀበለ። ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለዘሩም እስከ ዘላለሙ ድረስ እንደተናገረ።
የሰኞ ውዳሴ ማርያም
ሰኞ የሚጸለይ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ምስጋና
ጌታ ልቡ ያዘነና የተከዘ አዳምን ነጻ ያወጣውና ወደ ቀድሞ ቦታው ይመልሰው ዘንድ ወደደ ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን ።
ከድንግል ያለ ወንድ ዘር በሥጋ ተወለደና አዳነን። ከይሲ ዲያቢሎስ ያሳታት ሔዋንን እግዚአብሔር ምጥሽንና ጻርሽን አበዛዋለሁ ብሎ ፈረደባት። ሰውን ወደደና ነፃ አደረጋት። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ሰው የሆነና በኛ ያደረ ቃል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ክብሩንም ለአባቱ አንድ እንደመሆኑ ክብር አየን። ይቅር ይለን ዘንድ ወደደ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈስ ቅዱስ የዐማኑኤልን ምስጠር አየ። ስለዚህም ሕፃን ተወለደልን፤ ወልድም ተሰጠልን ብሎ አሰምቶ ተናገረ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ሰው ሆይ ፈጽመህ ደስ ይበልህ፤ እግዚአብሔር ዓለሙን ወዶታልና፤ አንድ ልጁንም የሚያምንበት ሁሉ እስከ ዘለዓለም ፈጽሞ ይድን ዘንድ አሳልፎ ሰጥቷልና። ልዑል ክንዱን ሰደደልን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የነበረው የሚኖረው፤ የመጣው ዳግመኛ የሚመጣውም ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ያለመለወጥ ፍጹም ሰው ሆነ። አንዱ ወልድ በሥራው ሁሉ አልተለየም፣ የእግዚአብሔር መለኮት አንድ ነው እንጂ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የነቢያት ሀገራቸው ቤተ ልሔም ሆይ ደስ ይበልሽ። ሁለተኛው አዳም ክርስቶስ በአንቺ ዘንድ ተወልዷልና፤ የቀድሞውን ሰው አዳምን ከምድር (ከሲኦል) ወደ ገነት ይመልሰው ዘንድ። አዳም ሆይ መሬት ነበርህና ወደ መሬት ትመለሳለህ ብሎ የፈረደበትንም የሞት ፍርድ ያጠፋለት ዘንድ። ብዙ ኃጢአት ባለችበት የእግዚአብሔር ጸጋ ትበዛለች። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የሰው ሁሉ ሰውነት ደስ ይላታል። በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም ለሰውም እርሱ በሚፈቅደው እያሉ አሰምተው ንጉሥ ክርስቶስን ከመላእክት ጋራ ያመሰግኑታል፤ የቀድሞውን እርግማን አጥፍቷልና። የጠላትን ምክሩን አፈረሰበት። ለአዳምና ለሔዋን የዕዳ ደብዳቤያቸውን ቀደደላቸው፥ በዳዊት ሀገር የተወለደ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና ሔዋንን ነፃ አደረጋቸው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
በዚህ ዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሃን ስለ ሰው ፍቅር ወደ ዓለም የመጣህ። ፍጥረት ሁሉ በመምጣትህ ደስ አለው፥ አዳምን ከስሕተት አድነኸዋልና ሔዋንንም ከሞት ጻዕረኝነት ነፃ አድርገኻታልና። የምንወለድበትን መንፈስ (ረቂቁን ልደት) ሰጠኸን፥ ከመላእክት ጋርም አመሰገንህ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የማክሰኞ ውዳሴ ማርያም
ማክሰኞ የሚጸለይ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ምስጋና
የመመኪያችን ዘውድ የድኀነታችን መጀመሪያ የንጽሕናችንም መሠረት እኛን ስለማዳን ሰው የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል በወለደችልን ሰድንግል ማርያም ተገኘልን። ሰው ከሆነ በኋላም ፍጹም አምላክ ነው። ስለዚህም በድንግልና ወለደችው። ድንቅ የሆነ የመውለድዋ ምስጢር የማይመረመር ሊነገር የማይቻል ነው:: ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
በእርሱ ፈቃድ በአባቱ ፈቃድ ሰመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መጥቶ አዳነን። በድንግልና ፍጽምት የሆንሽ ማርያም ሆይ የድንግልናሽ ምስጋናና ክብር ታላቅ ነው። እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ሲሆን ባለሟልነትን አግኝተሻልና። ያዕቆብ ከምድር እስከ ሰማይ ደርሳ የእግዚአብሔር መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት ያያት መሰላል አንቺ ነሽ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ሙሴ በነደ እሳት ሳትቃጠል ያያት ዕፅ አንቺ ነሽ። ይኸውም መጥቶ በማኀፀንሽ ያደረው የእግዚአብሔር ልጅ ነው። የመስኮቱ እሳትነት ሥጋሽን አላቃጠለውም። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ዘር ያልተዘራባት እርሻ አንቺ ነሽ። የሕይወት ፍሬ ከአንቺ ወጣ። ዮሴፍ የዋጃትና የከበረ ዕንቁን ያገኘባት ሣጥን አንቺ ነሽ። ይኸውም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በማኀፀንሽ አደረ፤ በዚህ ዓለምም ወስድሽው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የመላእክት ደስታቸው የሆነ ጌታን የወለድሽ ሆይ ደስ ይበልሽ። የነቢያት ዜናቸው ንጽሕት ሆይ ደስ ይበልሽ። እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ሲሆን ባለሟልነትን አግኝተሻልና ደስ ይበልሽ:: የዓለም የሰው ሁሉ ደስታ የሆነ የመልአኩን ቃል ተቀብለሻልና ደስ ይበልሽ:: ዓለምን ሁሉ የፈጠረ ጌታን የወለድሽ ሆይ ደስ ይበልሽ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
በሚገባ የአምላክ እናት ተብለሻልና ደስ ይበልሽ። የሔዋን መድኃኒት ሆይ ደስ ይበልሽ። ፍጥረቱን ሁሉ የሚመግበውን እሱን ጡትሽን አጥብተሽዋልና ደስ ይበልሽ። የሕያዋን የጻድቃን ሁሉ እናታቸው ሆይ ደስ ይበልሽ። ትለምኝልን ዘንድ ወደ አንቺ እናንጋጥጣለን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ድንግል ሆይ ቅድስት ሆይ ጌታን የወለድሽ ሆይ እኛን ለማዳን ድንቅ ምሥጢር (ተዋህዶ) በአንቺ ሲደረግ ንጉሥን ወልደሽልናልና ፍጥረታትን በልዩ ልዩ መልክ የፈጠረ የርሱን የገናንነቱን ነገር ፈጽመን መናገር አይቻለንምና ዝም እንበል። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ወደ ደብረሲና የወረደ ለሙሴ ሕግን የሰጠ የተራራውን እራስ በጽጋግ በጢስ በጨለማና በነፋስ የሸፈነ ፈርተው የቆሙትንም በነጋሪቶች ደምጽ የገሠፀ የአብ አካላዊ ቃል ነው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
በትሕትና የተናገርሽ ተራራ ሆይ ይኸውም ወደ አንቺ የወረደው ነው። ሰውን የወደደ እርሱ ያለመለወጥ ባንቺ ሰው ሆነ። እንደ እኛ በሚናገር ሥጋ ፍጹም ሆኖ አምላክ በመንፈስ ቅዱስ በማኅፀኗ አደረና ፍጹም ሰው ሆነ። አዳምን ያድነው ዘንድ ኀጢአቱንም ያስተሠርይለት ዘንድ በሰማያት በሰማያዊ መዓረግ ያኖረው ዘንድ በቸርነቱና በይቅርታው ብዛት ወደ ቀደመ ቦታው ይመልሰው ዘንድ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የድንግልን ገናንነቷን ሊናገሩት አይቻልም። ጌታ መርጧታልና። የሚቀርበው የሌለ ብርሃን ውስጥ የሚኖር እርሱ መጥቶ አደረባት። ዘጠኝ ወር በማኀፀንዋ አደረ። የማይታይና የማይመረመር ታይቶ የማይታወቅ እርሱን በድንግልና ወለደችው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ነቢዩ ዳንኤል ያየው ያለ እጅ ከረጅም ተራራ የተፈነቀለው ያ ደንጊያ ከአብ ዘንድ የወጣው ቃል ነውና መጥቶ ያለ ወንድ ዘር ከድንግል ተወልዶ አዳነን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
እንደ ንጹሕ ጫፍ ሆንሽ፤ የሃይማኖትም መገኛ ነሽ፤ የቀናች የቅዱሳን አባቶቻችን ሃይማኖታቸው ነሽ። አምላክን የወለድሽና በድንግልና የታተምሽ ንጽሕት ሆይ የአብን ቃል ወለድሽልን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን መጣ። ቅድስት ለምኝልን።
የከበርሽ ጌታን የወለድሽ ሆይ የማይታይ ቃልን የተሸከምሽው የብርሃን እናቱ አንቺ ነሽ። እሱን ከወለደሽው በኋላ በድንግልና ኖረሻልና። በፍጹም ምስጋና ያገኑሻል። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የአብ ቃል እናቱ ንጽሕት ድንግል ሆይ፥ ስለአንቺ የሚነገረውን ነገር መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው? ኪሩቤል ለሚሸከሙት ንጉሥ ዙፋኑ (ማደሪያው) ሆንሽ። የተከበርሽ ሆይ እናመሰግንሻለን። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ መልካሟ እርግብ ሆይ ስምሽን ለልጅ ልጅ እንጠራለን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
እናትና ገረድ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ። የታቀፍሽውን መላእክት ያመሰግኑታልና። ኪሩቤልም በፍርሃት ይሰግዱለታል። ሱራፌልም ያለማቋረጥ ክንፋቸውን ዘርግተው የሚያመስግኑት ንጉሥ የክብር ባለቤት ይህ ነው። በይቅርታው ብዛት የዓለምን ኃጢአት ያስተሠርይ ዘንድ የመጣው ይህ ነው ይላሉ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የረቡዕ ውዳሴ ማርያም
ረቡዕ የሚጸለይ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ምስጋና
የምድር ሁለተኛ የሆንሽ ሰማይ ሆይ የሰማያት ሠራዊት (መላእክት) ንዕድ ነሽ ይላሉ። ድንግል ማርያም የምሥራቅ ደጅ ናት:: ሙሽራዋ ንጹሕ የሆነ ንጹሕት የሠርግ ቤት ናት:: አብ በሰማይ አይቶ አንድ ልጁን ላከው በአንችም ሰው ሆነ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ ትውልድ ሁሉ አንቺን ያመሰግኑሻል። የእግዚአብሔር ሀገር (ከተማ) ሆይ ነቢያት ድንቅ ድንቅ ነገርን ተናገሩልሽ። ደስ የተሰኙ የጻድቃን ማደሪያ ሆነሻልና። የምድር ነገሥታት ሁሉ በብርሃንሽ ይሄዳሉ። ሕዝቡም (ሠራዊቶቻቸውም) በብርሃንሽ ይሄዳሉ፣ ማርያም ሆይ ትውልድ ሁሉ ያመሰግኑሻል። ካንቺ ለተወለደውም ይሰግዱለታል፣ ያገኑታልም። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የዝናብ ውሃ የታየብሽ የእውነት ደመና አንቺ ነሽ። አብ የልጁ ምልክት አደረገሽ፣ መንፈስ ቅዱስ አደረብሽ፣ የልዑል ኃይል ጋረደሽ፣ ማርያም ሆይ ለዘለዓለም የሚኖር የአብን ልጅ ቃልን የወለድሽልን፣ መጥቶም ከኃጢአት አዳነን። ደስ የተሰኘህ ሆነህ ምሥራችን የተናገርክ መልአኩ ገብርኤል ሆይ የተሰጠህ ክብር ታላቅ ነው። ወደእኛ የመጣ የጌታን ልደት ነገርከን። ለድንግል ማርያም ጸጋን የተመሳሽ ሆይ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ ብለህ አበሠርካት። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ጸጋን አገኘሽ፤ መንፈስ ቅዱስ አደረብሽ፤ የልዑል ኃይልም ጋረደሽ (ጸለለብሽ)፤ ማርያም ሆይ በእውነት ቅዱሱን ወለድሽ፤ ዓለምን ሁሉ የሚያድን መጥቶ አዳነን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
አንደበታችን የድንግልን ሥራ ያመሰግናል። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዳዊት አገር ከእርስዋ ስለተወለደ አምላክን የወለደች ማርያምን ዛሬ እናመስግናት። አሕዛብ ኑ ማርያምን እናመስግናት። እናትና ድንግል ሁለቱንም ሆናለችና። ርኩሰት የሌስብሽና የአብ ቃል መጥቶ ካንቺ ሰው የሆነ ንጽሕት ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ። ነውር የሌለብሽ ፍጽምትና ጉድፍ የሌለብሽ ሙዳይ ሆይ ደስ ይበልሽ። ስለቀደመ ሰው አዳም ሁለተኛ አዳም የሆነ የክርስቶስ ማደሪያው የምትናገሪው ገነት ሆይ ደስ ይበልሽ። ከአባቱ ያልተለየ አንድ የተሸከምሽ ሆይ ደስ ይበልሽ። በክቡር ጌጥ ሁሉ ያጌጠ እርሱ መጥቶ ሰው የሆነብሽ ንጽሕት የሠርግ ቤት ሆይ ደስ ይበልሽ። የመለኮት እሳት (ባሕርይ) ያላቃጠለሽ ጳጦስ ሆይ ደስ ይበልሽ። በኪሩቤል የሚቀመጠውን ሰማያዊ መለኮትን በሥጋ የተሸከምሽ የተሸከምሽ ገረድና እናት ድንግልና ሰማይ ሆይ ደስ ይበልሽ። ስለዚህ ንጹሐን ከሆኑ መላእክት ጋር በፍጹም ደስታ ተሰኝተን እናመስግን። በሰማይም ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ዕርቅ ይሁን እንበል። ክብርና ምስጋና ጌትነት ያለው እርሱ አንቺን ወድዋልና። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ከቅዱሳን ክብር የማርያም ክብር ይበልጣል፣ የአብን ቃል ለመቀበል በተገባ ተገኝታለችና። መላእክት የሚፈሩትን ትጉሆች በሰማያት የሚያመሰግኑትን ድንግል ማርያም በማኀፀንዋ ተሸከመችው። ይህች ከኪሩቤል ትበልጣለች፣ ከሱራፌልም ትበልጣለች፣ ከሦስቱ አካል ለአንዱ ማደሪያ ሆናለችና። የነቢያት ሀገራቸው ኢየሩሳሌም ይህች ናት። ለቅዱሳን ሁሉ የደስታቸው ማደሪያ ናት። በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው። በቅዱሳን ላይ የሚያድር እግዚአብሔር እኛን ለማዳኝ ልዩ ከሆነች ከድንግል ሰው ሆኗልና። ኑ ይህን ድንቅ እዩ። ስለ ተገለጠልን ምሥጢር ምስጋና አቅርቡ። ሰው የማይሆን ሰው ሆኖዋልና፣ ቃል ተዋህዷልና። ጥንት የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊ ሆነ፣ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት። የማይታወቅ ተገለጠ፣ የማይታይ ታየ፣ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ በርግጥ ሰው ሆነ። ትላንት የነበረው ዛሬም ያለው መቼም የሚኖረው ኢየሱስ ክርስቶስ እንሰግድለትና እናመሰግነው ዘንድ አንድ ባሕርይ ነው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ነቢዩ ሕዝቅኤል ስለ እርስዋ መሰከረ፣ ድንቅ በሆነ ታላቅ ቁልፍ የተዘጋች ደጅ ከምሥራቅ አየሁ አለ:: ከኃያላን ጌታ በቀር ወደ እርስዋ ገብቶ የወጣ የለም:: ቅድስት ሆይ ለምኝልን::
ኆኀትም ደጅም መድኃኒታችንን የወለደች ድንግል ናት። እርሱን ከወለደች በኋላ እንደ ቀድሞ በድንግልና ኖራለችና። መጥቶ ምሕረት ከሌለው ጠላት እጅ ያዳነን ጌታን የወለድሽ ሆይ የማኅፀንሽ ፍሬ የተባረከ ነው፣ አንቺ ፍጽምትና የተባረክሽ ነሽ። የእውነት አምላክ በሆነ በክብር ባለቤት ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና:: በምድር ላይ ከሚኖር ሁሉ ይልቅ ገናንነትና ክብር ለአንቺ ይገባል። የአብ ቃል መጥቶ በአንቺ ሰው ሆነ። ከሰው ጋርም ተመሳስሰ። መሐሪ ይቅር ባይ ሰውን ወደጅ ነውና በልዩ አመጣጡ አዳነን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የሐሙስ ውዳሴ ማርያም
ሐሙስ የሚጸለይ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ምስጋና
ርኵሰት የሌለባት ድንግል ማርያም ሙሴ በበረሃ በነደ እሳት ጫፎቿ ሳይቃጠሉ ያያት ዕፅን ትመስላለች፤ የአብ ቃል በርስዋ ሰው ሆኗልና፣ እሳተ መለኮቱ (የመለኮቱ ባሕርይ) አላቃጠላትምና፤ ከወለደችውም በኋላ ድንግልናዋ አልተለወጠምና፤ ሰውም ቢሆን መለኮቱ አልተለወጠም በእውነት አምላክ ነውና፤ በእውነት አምላክ የሆነ እርሱ መጥቶ አዳነን። ቅድስት ሆይ ልምኝልን።
አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ ሁላችን እናገንሻልን። ይቅርታሽ ለሁላችን ይሆን ዘንድ ነውና። ሔዋን እንጨት በልታ ባደረገችው ዓመፅ በባሕርያችን ያደረ የቀድሞው እርግማን በእርስዋ የጠፋልን አምላክን የወለደች ድንግል ማርያም የሁላችን መመኪያ ናት። ስለ ሔዋን የገነት ደጅ ተዘጋ፤ ዳግመኛም ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን። ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን። ይኸውም እኛን ስለመውደድ መጥቶ ያዳነን የክርስቶስ ክቡር ሥጋው ክቡር ደሙ ነው። ስለ እርሷ ድንቅ ሆኖ የሚነገረውን ይህን ምሥጢር ማወቅ የሚቻለው ምን ልቡና ነው? መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው? መስማት የሚቻለው ምን ጆሮ ነው? ሰውን የሚወድ እግዚአብሔር አንድ ብቻ የሆነ አምላክነቱ ሳይለወጥ ከዓለም በፊት የነበረ የአብ ቃል ከአብ ዘንድ መጥቶ ልዩ ከሆነች እናቱ ሰው ሆነ። ከወለደችውም በኋላ ድንግልናዋ አልተለወጠም። ስለዚህ አምላክን የወለደች እንደሆነች ታወቀች። የእግዚአብሔር የጥበቡ ስፋት ምን ይጠልቅ? በጻእር በምጥ በልብ ጋር ትወልድ ዘንድ የፈረደባት ማኅፀን የሕይወት መገኛ ሆነች። ከባሕርያችን እርግማንን የሚያጠፋልንን ያለ ወንድ ዘር ወለደችልን። ስለዚህም ሰውን የምትወድ ሆይ ክብር ላንተ ይገባል፤ ቸርና የሰውነታችን መድኃኒትም ነህ እያልን እናመስግነው። ቅድስት ሆይ ልምኝልን።
ያለ ወንድ ዘር አምላክን የወለደች ድንግል የማኅፀንዋ ሥራ ምን ይደንቅ? ለዮሴፍ የታየው መልአኩ ከእርሷ በመንፈስ ቅዱስ የሚወለደው ያለ መለወጥ ሰው የሚሆነው የእግዚአብሔር ቃል ነው ብሎ መስክሯልና። ማርያም የዚህ ደስታ ዕፅፍ የሆነ እርሱን ወለደችው። መልአኩ ልጅ ትወልጃለሽ ስሙም ዐማኑኤል ይባላል አላት። ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ ማለት ነው። ዳግመኛ ወገኖቹን ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው ኢየሱስ ይባላል። በችሎታው (በኃይሉ) ያድነን ዘንድ ኃጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ ለዘለዓለም ክብር ይግባውና ሰው የሆነ እርሱን አምላክ እንደሆነ በተረዳ ነገር አውቀነዋልና። ልዩ ከሆነች ድንግል ማርያም ይህ የአምላክ መወለድ ምን ይደንቅ ቃልን ወሰነችው። ልደቱንም ዘር አልቀደመውም። በመወልዱም ድንግልናዋን አልለወጠውም። ቃል ከአብ ያለ ድካም ወጣ። ከድንግልም ያለ ሕማም ተወለደ። ሰብአ ስገል ሰገዱለት። አምላክ ነውና ዕጣን አመጡለት። ንጉሰም ነውና ወርቅ አመጡለት። ስለእኛ በፈቃዱ ለተቀበለው መዳኛችን ለሆነ ሞቱም ከርቤ አመጡለት። ቸር ሰውን ወዳጅ የሆነ አንድ እርሱ ብቻ ነው ። ቅድስት ሆይ ልምኝልን።
ከአዳም ጎን አንዲት ዐፅም ማንሣት ምን ይደንቅ? ከእርሱ ሴትን ፈጠረ፤ የሰው ፍጥረትንም ሁሉ ፈጠረ። ጌታ የአብ ቃል ተሰጠ። ከልዩ ድንግልም ሰው ሆነና ዐማኑኤል ተባለ፤ ስለዚህ ሁል ጊዜ እርስዋን እንለምን፣ ከተወደደ ልጅዋ ታማልደን ዘንድ። በቅዱሳንና በሊቃነ ጳጳሳት ዘንድ ቸር ናት፤ ደጅ የሚጠኑትን ወልዳላቸዋልችና፤ ለነቢትም ትንቢት የተናገሩለትን ወልዳላቸዋለችና፤ ለሐዋርያትም እስከ ዓለም ዳርቻ በስሙ ያስተማሩለትን ወልዳላቸዋለችና፤ ሰማዕታትና ምዕመናንም የተጋደሉለትን የጥበቡ ጸጋ ብዛት የማይታወቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርስዋ ተወልዷልና፤ የይቅርታውን ብዛት መርምረን እንወቅ (እንገፈልግ) መጥቶ አድኖናልና። ቅድስት ሆይ ልምኝልን።
እግዚአብሔር የባሕርይህን ፍሬ በዙፋንህ አኖራለው ብሎ ለዳዊት በእውነት ማለ አይጸጸትም። ጻድቅ እርሱ ዳዊት ክርስቶስ በሥጋ ከእርሱ እንዲወለድ ባመነ ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ማደሪያ ፈልጎ ያገኝ ዘንድ ወደደ፤ ይህንንም በታላቅ ትጋት ፈጸመ። ከዚህም በኋላ እነሆ በኤፍራታ ሰማነው ብሎ በመንፈስ ቅዱስ አሰምቶ ተናገረ። ይህቺውም ዐማኑኤል እኛን ለማዳን በሥጋ ይወልድባት ዘንድ የመረጣት የያዕቆብ አምላክ ማደሪያ ናት። ዳግመኛም ከነቢያት አንዱ ሚክያስ አንቺ የኤፍራታ ክፍል የሆንሽ ቤተልሔም ከይሁዳ ነገሥታት መሳፍንት አገር አታንሺም ወገኖቼ እስራኤልን የሚጠብቃቸው ንጉሥ ካንቺ ይወጣልና፤ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ ከቸር አባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ምስጋና ስለተገባው ስለ ክርስቶስ ባንድ መንፈስ ቅዱስ ትንቢት የተናገሩት የነዚህ የሚክያስና የዳዊት ነገር ምን ይረቅ? ቅድስት ሆይ ልምኝልን።
ለእስራኤል የነገሠ ዳዊት ጠላቶቹ በተነሡበት ጊዜ ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ ይጠጣ ዘንድ ወደደ። የጭፍሮቹ አለቆች ፈጥነው ተነሡና በጠላቶቹ ከተማ ተዋግተው ሊጠጣ የወደደውን አመጡለት። ጻድቅ ዳዊት ግን ጨክነው ሰውነታቸውን ስለ እርሱ ለጦርነት ለሞት አሳልፈው እንደ ሰጡ ባየ ጊዜ ያን ውኃ አፈሰሰ። ከእርሱም አልጠጣም። ከዚህ በኋላ ለዘለዓለም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። ሰማዕታት የዚችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ። ደማቸውንም ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ። ስለ መንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሱ። እንደ ይቅርታህ ብዛት ይቅር በለን። ቅድስት ሆይ ልምኝልን።
ከቅድስት ሥላሴ አንዱ ወልድ መዋረዳችንን አይቶ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ባሕርዩን ዝቅ አደረገና መጥቶ በድንግል ማኅፀን አደረ። ከብቻዋ ከኃጢአት በቀርም አንደኛ ሰው ሆነ፤ ነቢያት ትንቢት እንደተናገሩለት በቤተልሔም ተወለደ። ፈጽሞ አዳነን ወገኖቹም አደረገን። ቅድስት ሆይ ልምኝልን።
የዓርብ ውዳሴ ማርያም
ዓርብ የሚጸለይ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ምስጋና
ከሴቶሽ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ። የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረክ ነው። ያለርኵሰት አምላክን የወለድሽ ድንግል ማርያም ሆይ እውነተኛ ፀሐይ ከአንቺ ወጣልን (ጌታ ተወለደልን)። በክንፈ ረድኤቱም አቀረበን። እርሱ ፈጥሮናልና። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ፥ የብርሃን እናት ነሽና አንችን ብቻሽን በክብር በምስጋና እናገንሻለን። የተባረክሽ አንቺ ከመላእክት ትበልጫለሽ፤ ከደቂቀ አዳምም ትበልጫልሽ። ከአሳቦች ሁሉ ትበልጫልሽ፤ ገናንነትሽን መናገር የሚቻለው ማነው? አንቺን የሚመስል የለምና። ማርያም ሆይ መላእክት ያገኑሻል ሱራፌልም ያመሰግኑሻል። በኪሩቤልና በሱራፌል ላይ አድሮ የሚኖር ጌታ መጥቶ በማኅፀንሽ አድሮአልና። ሰውን የሚወድ ወደ እርሱ አቀረበን፣ ክብር ምስጋና ያለው እርሱ የእኛን ሞት ተቀብሎ የእርሱን ሕይወት ለእኛ ሰጠን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የደናግል መመኪያቸው አምላክን የወለድሽ ድንግል ማርያም ሆይ የተባረክሽ ነሽ። የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። ከዓለም በፊት የነበረ እርሱ ሰው ሆኖዋልና። ከአንቺ ተወለደ ሥጋችንን ነሣ (ተዋሐደ)። መንፈስ ቅዱስንም ሰጠን። በቸርነቱ ብዛት መሳዮቹ አደረገን። ጸጋንና ክብርን ከተቀበሉ ብዙ ሴቶች አንቺ ትበልጫልሽ። አምላክን የወለድሽ ማርያም ሆይ ልዑል እግዚአብሔር ያደረብሽ (የከተመበሽ) ረቂቅ ከተማ ነሽ። በኪሩቤልና በሱራፌል ላይ የሚኖረውን ጌታን በመኻል እጅሽ ይዘሸዋልና። በቸርነቱ ብዛት ሥጋዊ ፍጥረትን ሁሉ የሚመግብ እርሱ ጡትሽን ይዞ ጠባ። ይኸውም ሁሉን የሚያድን አምላካችን ነው። ለዘለዓለሙ ይጠብቀናል። እንሰግድለትን እናመስግነው ዘንድ እርሱ ፈጥሮናልና። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ድንግል ማርያም የሽቱ መኖሪያና የሕይወት ውኃ ምንጭ ናት። የማኅፀንዋ ፍሬ ሰውን ሁሉ አድኖአልና። ከእኛም እርግማንን አጠፋልን። በመካከለችንም ሆኖ በመስቀሉ አስታረቀን። በልዩ ትንሣኤውም ሰውን ዳንመኛ ወደ ገነት መለሰው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ንጽሕት ድንግል ማርያም የታመነች አምላክን የወለደች ናትሽ። ለሰዎች ልጆችም የምሕረት አማላጅ ናት። ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ልጅሽ ወደ ክርስቶስ ለምኝልን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ድንግል ማርያም በቤተመቅደስ አሰምታ ትናገር ነበር። መልአኩ ቅድስት ድንግል ሆይ ሰላምታ ይገባሻል ብሎ አክብሮ ከነገረኝ ነገር በቀር ምንም ምን ሌላ የማውቀው እንደሌለኝ እግዚአብሔር ያውቃል አለች። የማይቻለውን ቻልሽ የማይወሰነውንና ምንም ምን የሚወስነው የሌለውን ወሰንሽ። በክብር ሁሉ ላይ ጸጋን የተመላሽ ሆይ ምስጋናሽ ይበዛል ክብርሽ ፍጹም ነው። የአብ ቃል ማደሪያ ሆነሻልና የክርስቲያን ወገኖች ምእመናንን የምትሰበስቢያቸውና ማኅየዊ የሚያድኑን ለሆኑ ለሥላሴ ሰጊድን (መሰገድን) የምያስተምሪላቸው ሰፊ መጋረጃ ሙሴ ያየውን የእሳት ዓምድ የተሸከምሽ አንቺ ነሽ። ይኸውም መጥቶ በማኅፀንሽ ያደረው የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ሰማይና ምድር ለማይወስኑት የታመንሽ አንቺ ነሽ። ከምድር ወደሰማይ ለማረግ መሰላል ሆንሽ። ብርሃንሽ ከፀሐይ ብርሃን ይበልጣል። ቅዱሳን በፍጹም ደስታ ያዩት ኮከብ ካንቺ የተወለደ ምሥራቅ አንቺ ነሽ። አንቺ ማርያም ግን ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ የሚል ቃልን ሰማሽና መጥቶ ያዳነን የፍጥረት ሁሉ ገዥ የሆነ ንጉሥን ወለድሽልን። መሐሪ ነው፣ ሰውንም ወዳጅ ነው። ስለዚህ ማርያም ሆይ የተባረክሽ ነሽ፣ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። ጸጋን የተመላሽ ሆይ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ እያልን መልአኩ ገብርኤል እንዳመሰገነሽ እናመሰግንሻለን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የቅዳሜ ውዳሴ ማርያም
ቅዳሜ የሚጸለይ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ምስጋና
ንጽሕት ነሽ ብርህትም ነሽ። ጌታን በመኻል እጅሽ የያዝሽው ሆይ በሁሉ የተቀደሽ ነሽ። ፍጥረት ሁሉ ቅድስት ሆይ ለምኝልም ብለው እየጮኹ ካንቺ ጋር ደስ ይላቸዋል። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ። ባለሟነትን አግኝተሻልና ደስ ይበልሽ። እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ። ግርማ ያለሽ ድንግል ሆይ ገናነትሽን እናመሰግናለን እናደንቃለን። እንደ መልአኩ ገብርኤልም ምስጋና እናቀርብልሻለን። የባሕርያችን መዳን በማኅፀንሽ ፍሬ ተገኝቷልና። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
እንደ ሠርግ ቤት ጉድፍ የሌለብሽ ነሽ። መንፈስ ቅዱስ አድሮብሻልና። የልዑል ኃይልም ጸልሎሻልና። ማርያም ሆይ ለዘለዓለም የሚኖር መጥቶ ከኃጢአት ያዳነን የአብ ልጅ ቃልን በእውነት ወለድሽ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ከዳዊት ሥር የተገኘሽ ባሕርይ (ዘር) አንቺ ነሽ። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ ወልደሽልናልና። ከአብ የተወለደ ከዓለም በፊት የነበረ አንዱ ቃል ራሱን (ባሕርዩን) ሰወረ። ካንቺም የተገዥን (ሰውን) አርአያ ነሣ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
አምላክን ያለርኵሰት የወለድሽው ሆይ፥ የምድር ሁለተኛ ሰማይን ሆንሽ፣ እውነተኛ ፀሐይ ካንቺ ወጥቶልናልና። እንደነቢያት ትንቢትም ያለዘርና ያለመለወጥ ወደልሽው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ከተለዩ የተለየች የተባልሽ የኪዳን ጽላት ያለብሽ የተሰወረ መና ያለበት የወርቅ መሶብ ያለብሽ ደብተራ ድንኳን አንቺ ነሽ። ይኸውም መና የተባለው መጥቶ በድንግል ማርያም ማኅፀን ያደረው የእግዚአብሔር ልጅ ነው። የአብ ቃል በእርስዋ ሰው ሆነ። መጥቶ ያዳነን የባሕርይ ንጉሥን በዓለም ውስጥ የወለደችው የሚናገር በግ የክርስቶስ እናቱ ገነት ደስ ይላታል። ለዘለዓለም የሚኖር የአብ ልጅ እርሱ መጥቶ ከኃጢአት አድኖናልና። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የንጉሥ ክርስቶስ እናቱን ተባልሽ። እርሱን ከወለድሽ በኋላም በድንግልና ኖርሽ። ድንቅ በሆነ ምሥጢርም (ተዋህዶ) ዐማኑኤልን ወለድሽው። ስለዚህም ባለመለወጥ አጸናሽ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
እግዚአብሔር በላይዋ ተቀምጦባት ያዕቆብ ያያት መሰላል አንቺ ነሽ። በሁሉ በኩል የማይመረመር እርሱን ተፈትሖ በሌለበት ማኅፀንሽ ተሸክመሽዋልና። እኛን ስለማዳን ካንቺ ሰው በሆነ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ አማላጅ ሆንሽን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የተባረክሽና ንጽሕት የሆንሽ አዳራሽ ሆይ፥ እነሆ ጌታ የፈጠረውን ዓለም ሁሉ በይቅርታው ብዛት ያድን ዘንድ ካንቺ ወጣ (ተወለደ)። ፈጽመን እናመስግነው። ቸርና ሰውን ወዳጅ ነውና። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ያለርኩሰት ድንግል የሆንሽ ጸጋን የተመላሽ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ፤ የዓለም ሁሉ መክበሪያ ንጽሕት ጽዋ ነሽ። የማትጠፊ ፋና ነሽ። የማትፈርሽ መቅደስ ነሽ። የቅዱሳን መደገፊያቸው (መጠጊያቸው) የማትለወጪ የሃይማኖት በትር ነሽ። ቸር አዳኛችን ወደ ሆነ ልጅሽ ለምኝልን። ፈጽሞ ይቅር ይለንና ይምረን ዘንድ፤ ኃጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የእሑድ ውዳሴ ማርያም
በሰንበተ ክርስቲያን እሑድ የሚጸለይ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ምስጋና
ከሴቶሽ ይልቅ ተለይተሽ የተባረክሽ ሆይ የተወደድሽ ተባልሽ። ከተለዩ የተለየች በውስጧም የኪዳን የሕግ ጽላት ያለባት የምትባይ ሁሉተኛ ክፍል አንቺ ነሽ። ኪዳንም በእግዚአብሔር ጣቶሽ የተጻፉ ዓሥሩ ቃላት ናቸው። ያለመለወጥ ካንቺ ሰው የሆነ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደገኛ ስሙን (መጀመሪያ ስሙን) አስቀድሞ በየውጣ ነገረን፣ ለአዲስ ኪዳንም አስታራቂ ሆነ። በከበረ ደሙ ፈሳሽነት ወይም መፍሰስ ያመኑትንና ንጹሐን የሆኑትን ወገኖች አነጻቸው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ሁል ጊዜ ንጽሕት የሆንሽ አምላክን የወለድሽ እምቤታችን ሆይ፥ ሁላችን ስለዚህ እናገንሻለን። ሰውን በሚወድ በጌታ ዘንድ ይቅርታን እናገኝ ዘንድ እንለምንሻለን ወዳንቺም እናንጋጥጣልን። ከማይነቅዝ እንጨት የተቀረፀ በውስጥና በውጭ በወርቅ የተለበጠ ታቦት ያለመለየትና ያለመለወጥ ሰው የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይመስልልናል። ይኸውም መለወጥ የሌለበት ንጹሕ መለኮት ነው። ከአብ ጋር የተካከለ ነው። ለንጽሕት በራሱ አበሠራት። በልዩ ጥበብ ያለ ወንድ ዘር እንደ እኛ ሆነ። መለኮቱን አዋሕዶ ያለ ርኵሰት ባንቺ ሰው ሆነ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
በእግዚአብሔር ሥዕል የተሣሉ ኪሩቤል የሚጋርዱሽ መቅደስ አንቺ ነሽ። ንጽሕት ሆይ ያለመለወጥ ካንቺ ሰው የሆነው ቃል ኃጢአታችንን የሚያስተሠርይልንና አበሳችንን የሚደመስስልን ሆነ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የተሠወረ መና ያለብሽ የንጹሕ ወርቅ መሶብ አንቺ ነሽ። መናም ከሰማይ የወረደውና ለዓለም ሁሉ ሕይወትን የሚያድለው ኅብስት ነው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ሁል ጊዜ ብርሃንነት ያለውን ፋና የተሸከምሽ የወርቅ መቅረዝ አንቺ ነሽ። ይኸውም ፋና የዓለም ብርሃን ነው። ጥንት ከሌለው ብርሃን የተገኘ ብርሃን ነው። ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ እውነተኛ አምላክ ነው። ያለ መለወጥ ከአንቺ ሰው የሆነው ነው። በመምጣቱም (ሰው በመሆኑም) በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለምንኖር ለእኛ አበራን። በልዩ የጥበቡ ምሥጢር በሥጋዌ የልቦናችንን እግር ወደ ሰላም መንገድ አቀናልን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ቡሩክ ከቤተ መቅደስ ይዞሽ የወጣ እሳትነት ያለውን ፍሕም የተሸከምሽ የወርቅ ማዕጠንት አንቺ ነሽ። ፍሕም የተባለውም ኃጢአትን የሚያስተሠርይና በደልን የሚደመስስ ነው። ይኸውም ካንቺ ሰው የሆነና ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያሳረገ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የእግዚአብሔርን ቃል የወለድሽልን መልካሟ ርግብ ማርያም ሆይ፥ ደሽ ይበልሽ። ከዕሴይ ሥር የወጣሽ መዐዛሽ ያማረ አበባ አንቺ ነሽ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ሳይተክሏትና ውሃ ሳያጠጧት የለመለመች የአሮን በትር ነበረች። ያለ ወንድ ዘር ሰው ሆኖ ያዳነን እውነተኛ አምላክችንን ክርስቶስን የወለድሽልን ሆይ፥ አንቺ እንደርሷ ነሽ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ጸጋን የተመላሽ ሆይ፥ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ትለምኝልን ዘንድ ላንቺ ይገባል። አንቺ ከሊቃነ ጳጳሳት ትበልጫለሽ። ከነቢያትም ከመምህራንም ትበልጫለሽ። ከሱራፌልና ከኪሩቤል ግርማ የሚበልጥ የመወደድ ግርማ አለሽ። በእውነቱ የባሕርያችን መመኪያ አንቺ ነሽ። ለሰውነታችንም ሕይወትን የምትለምኝ ነሽ። ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምኝልን፤ እርሱን በማመን በቀናች ሃይማኖት ያጸናን ዘንድ ይቅርታውንና ምሕረቱን ይሰጠን ዘንድ በቸርነቱ ብዛት ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
አንቀጸ ብርሃን
ቅድስት ሆይ ብፅዕት ነሽ። የተመሰገንሽና የተባረክሽ ነሽ። የከበርሽና ከፍ ከፍ ያልሽ ነሽ። የብርሃን መውጫ የሕይወት መሰላል ነሽ። አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ድንግል ማርያም ሆይ ከተለዩ የተለየሽ የመለኮት ማደሪያ ነሽ። ከፍጥረት ሁሉ ይልቅ የተከበርሽ ሆይ አብ የወደደሽ ወልድ ያደረብሽ መንፈስ ቅዱስ ያረፈብሽ ተባልሽ። በምድር ላይ ከፍተኛ አርያምን የሆንሽ ከሰማያት በላይ ያለ የአርያም የልዑል ስፍራ ምትክ አንቺ ነሽ። ቅዱሳን ነቢያት ካህናትና ነገሥታት ያንቺ ምሳሌ አድርገው በውስጧ የኪዳን የሕግ ጽላት ያለባት ቅድስተ ቅዱሳን ከተለዩ የተለየችውን ሠሩ። ቅድስት ሆይ፣ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።
የአምላክ ልጅ ካንቺ ሰው ስለመሆኑ ስላንቺም ከምድር ወደ አርያም ወደ መንግሥተ ሰማያት የቀረብን ሆን። በአንቺና በልጅሽ ስም የቀረብን ሆንን። ዐሥሩ ቃላት በጣቶቹ የተጻፉ የፍጥረት ሁሉ ጌታ ይኸውም የአምላክ ልጅ በማኅፀንሽ አደረ። አብ በሥልጣኑ አጸናሽ። መንፈስ ቅዱስም ጸለለብሽ። የልዑል ኃይልም አጸናሽ። ኢየሱስም ያንችን ሥጋ ለበሶ በታላቅ ቃል ጮኸ። መጽሐፍ “የሕይወት ውኃ ምንጭ ከሆዱ ይፈልቃል” እንዳለ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደኔ መጥቶ ይጠጣ” አለ። ቅድስት ሆይ፣ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።
አብ አስቀድሞ በየውጣ ነገረን የውጣ የተባሉ በእግዚአብሔር ጣቶች የተጻፉ ዐሥሩ ቃላት ናቸው። ልጅህ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንተ ብቻ አባቱ እንደ ሆንክ እርሱም ብቻ ልጅህ እንደሆነ አስተማረን። እንዲሁም በሰማይ እናት በምድር አባት የለም ብለን እናምናለን። መምጣቱን ከአባቱና ከእውነት መንፈስ ከጰራቅሊጦስ በቀር የሚያውቅ ሳይኖር ከሰማይ ወረደ ብለን እናምናለን። በማኅፀንሽ አደረና ዘጠኝ ወር ተሸከምሽው። ሰማያት ደስ ተሰኙ ምድርም ደስ ተሰኘች። በልጅሽ መወለድ መልአክ ምሥራች ተናገረ። የሰማይ ጭፍሮችም መላእክትም ምስጋና በሰማይ ለእግዚአብሔር ይሁን በምድርም ላይ ሰላም በሰውም እርሱ በሚፈቅደው እያሉ አመሰገኑ። እረኞችም በቤተልሔም ካዩትና ከሰሙት የተነሣ አደነቁ የጥበብ ሰዎች ለልጅሽ ሊሰግዱና አንቺን ሊያገለግሉ ኮከብን አይተው ከሩቅ አገር መጡ። ከምሥራቅ ጀምሮ መርቶ እስከ ቤተልሔም ያደረሳቸው ያ ኮከብ አንቺ ከሕፃንሽ ጋር ባለሽበት ቦታ ላይ ቆመ። እነዚያ ብልሆች ሰዎች አይተው በታላቅ ደስታ ደስ ተሰኙ። ወደ እርሱ ወደ ሕፃንሽ ገቡና በፊቱ ቆሙ። በምድር ላይ ወድቀው ሰገዱለት። ሣጥናቸውንም ከፈቱና ወርቅ ዕጣን ከርቤን እጅ መንሻ አድርገው አገቡለት። የወገኖችህን ልመናቸውንና መስዋዕታቸውን ትቀበል ዘንድ ኃጢአታቸውንም ታስተሠርይላቸው ዘንድ የመጣህ አምላካችን ሆይ፣ እጅ መንሻ አገባንልህ ለከበረ ስምህም ካንተ የተገኘውን ዕጣን አቀረብንልህ አሉት። ቅድስት ሆይ፣ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።
ከንጹሐን ይልቅ ንጽሕት የሆንሽ አንቺ ነሽ። ከማይነቅዝ እንጨት እንደተሠራ በወርቅ እንደተጌጠና ዋጋው ብዙ በሆነ በሚያበራ ዕንቁ እንደተለበጠ ታቦት በቤት መቅደስ ውስጥ የኖርሽ የተመረጥሽ ድንግል ነሽ። እንዲህ ሆነሽ በቤተ መቅደስ ኖርሽ። መላእክትም ዘወትር ምግብሽን ያመጡ ነበር። መላእክት እየጐበኙሽ እንዲህ አሥራ ሁለት ዓመት ኖርሽ። መጠጥሽም የሕይወት መጠጥ ነበር። ምግብሽም የሰማይ ኅብስት ነበር። አባትሽ ዳዊት በመሰንቆ አመሰገነ፤ በትንቢት መንፈስም በመንፈስ ቅዱስም በገና እየደረደረ እንዲህ ብሎ ዘመረ “ልጄ ሆይ፣ ስሚ እዪም ጆሮሽንም አዘንብዪ ሕዝብሽንና የአባትሽን ቤት እርሺ ንጉሡም ውበትሽን ይወዳል እርሱ ጌታሽ ነውና ለእርሱም ትሰግጃለሽ።” ቅድስት ሆይ፣ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።
ካልበደሉ መላእክት ወገን የሆነና በደል የሌለበት በሁሉ ጌታ ፊት የሚቆም ከደጋጐቹ መላእክት ወገን የሆነ መልአኩ ገብርኤል አበሠረሽ። እንዲህም አለሽ፥ ጸጋን ያገኘሽ ሆይ፣ ደስ ይበልሽ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው። ከሴቶች ይልቅ የተባረክሽ ነሽ። የሁሉ ገዥ በሆነ እግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አገኘሽ። እነሆ ትፀንሻለሽ፣ ልጅም ትወልጃለሽ። ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ። እርሱ ታላቅ ነው የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል። ለዘላለሙ የያዕቆብን ወገን ይገዛል። ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም። መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል የልዑል ኃይልም ይጸልልሻል። ካንቺ የሚወለደውም ቅዱስ ነው። ቅድስት ሆይ፣ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።
የንጽሕና አዳራሽና ከተለዩ የተለየሽ መቅደስ አንቺ ነሽ። የብርሃን መጋረጃና የማይመረመር የክብር ዙፋን አንቺ ነሽ። ቅድስት ማርያም ሆይ፣ መንፈስ ቅዱስ መጥቶ ስላደረብሽና የልዑል ኃይል ስለጸለለብሽ ቅድስተ ቅዱሳን በሆነች መቅደስ መሰልንሽ። የብርሃን መጋረጃ ነሽ ማለታችን ግን የአብ ቃል የሆነ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማኅፀንሽ ስለተሠወረ ነው። ይኸውም በላይ ያለ የሁሉ ጌታ ነው መላእክትና የመላእክት አለቆች መናብርትና ሥልጣናት አጋዕዝትና ኃይላት ሊቃናትና መኳንንት የሚያመሰግኑት ነው። ልጅሽንም በዚህ ዓለም በወለድሽው ጊዜ ዓይኖቻቸው ብዙዎች የሆኑ ኪሩቤልና ክንፎቻቸው ስድስት የሆኑ ሱራፌል በበረት ውስጥ ጋረዱልሽ። የብርሃን ደመናዎችም ከበቡሽ የመላእክት አለቆች የመላእክት ሠራዊትና የሰማይ ጭፍሮች በመፍራትና በመንቀጥቀጥ በፊትሽ ቆሙ። በዚህም ዓለም ኪሩቤልና ሱራፌል በሰማያት ካለው ምስጋናቸው ወይም ከቀድሞ ምስጋናቸው ወገን ባልሆነ በሌላ በአዲስ ምስጋና አመሰገኑሽ። ፍጥረትን ሁሉ ሰብስቦ የያዘና ፍጥረቱን ሁሉ የሚመግብ ጌታቸው በክንድሽ ተቀምጦ ጡትሽን እንደ ሕፃን ሲጠባ ባዩ ጊዜ በአርያም ፈለጉና በዚያ እንደ ቀድሞው ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አገኙት። የጌታ ትህትናውን ባዩ ጊዜም ዓይኖቻቸውን ወደ ላይ ወደ አርያም ከፍ ከፍ አደረጉ። ክንፋቸውንም ዘርግተው ለሁሉ ጌታ ላንተ በሰማይ ምስጋና ይገባሃል እያሉ ጌታቸውን አመሰገኑ። ዳግመኛም በዋሻ በጎል ውስጥ አንቺን ከሕፃንሽ ጋር አይተው በምድር ላይ ሰላም ሆነ አሉ። ካንቺ የነሳውን የኛን ሥጋ ለብሶ ባዩት ጊዜም ሰውን ምንኛ ወደደው ብለው ሰገዱለት። ነቢዩ ዳዊትም እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ። እግዚአብሔር በሰማይና በማደሪያው ቦታ ሆኖ በምድር ወደሚኖሩት ሁሉ ተመለከተ የሰውንም ልጆች ሁሉ አየ። ንጉሥ ውበትሽን ወደደ። ዘለዓለም ማረፊያዬ ይህች ናት መርጫታለሁና በእርሷ አድራለሁ አለ። ቅድስት ሆይ፣ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።
የተለየሽና ደግ የሆንሽ የተመሰገንሽና የተባረክሽ የከበርሸና ከፍ ከፍ ያልሽ ሆይ፣ የሕይወት ኅብስት ባለበት በወርቅ መሶብ መሰልንሽ። የሕይወት ኅብስትም ይኸውም በቀኙ ካሉ ጻድቃን ጋር እርሱን ለሚያምን በሃይማኖትም ፈቃደኛ በሆነ ልብ ከእርሱ ለሚበላም ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ ከሰማይ የወረደ ነው። ቅድስት ሆይ፣ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።
የብልሃተኛ እጅ ያልሠራት በውስጧም መብራት የማያበሩባት የወርቅ መቅረዝ አንቺ ነሽ። ራሱ የአብ ብርሃን ያበራባታል እንጂ። ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ወደ አንቺ መጥቶ አደረ በአምላክነቱም በዓለም ሁሉ አበራ። ጨለማን ከሰዎች ላይ አራቀ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ በብርሃኔ እመኑ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ ብሎ በሚያድን ቃሉ አዳነን። ቅድስት ሆይ፣ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።
ከሁሉ ጌታ የተገኘ የሁሉ ጌታ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን በእውነት የሁሉ ጌታ የባሕርይ አምላክ ከሆነ የተገኘ እውነተኛው የሁሉ ጌታ የተወለደ እንጂ የተፈጠረ ያይደለ በህልውና በአኗኗር ከአባቱ ጋር የተካከለ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ በእርሱ የተፈጠረ እኛን ሰዎችን ስለማዳን የወረደው ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ፈጽሞ ሰው ሆነ። በመምጣቱም አበራልን፤ ፍጹም ደስታንም አበሠረን፤ ወደ አባቱም አቀረበን ወደ ሕይወት ጎዳናም መራን፤ የዘለዓለም ሕይወትንም ሰጠን። ነቢዩ ኢሳይያስ እርሱን በማመን ከሕጉ የተነሣ በትንቢት እያደነቀ “ሕግህ በምድር ላይ ብርሃን” ነው አለ። አረጋዊ ካህንና የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የጠበቀ ጻድቅና ንጹሕ ዘካርያስ ፈጽሞ አደነቀ መናገርም ጀመረና እንዲህ አለ “አምላካችን በይቅርታውና በምሕረቱ በአርያም ሆኖ ጐበኘን።” በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩትም ብርሃኑን ይገልጥላቸው ዘንድ ተወለደ ይቅር ይለን ይምረንም ዘንድ እግሮቻችንን ወደ ሰላም መንገድ አቀናልን። ቅድስት ሆይ፣ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።
እመቤታችን ሆይ፣ የቅዱሳንና የምእመናንን ሁሉ ጸሎት በማዕጠንታቸው ከምድር ወደ ሰማይ በሚያሳርጉ በሰማያውያን የካህናት አለቆች እጆች ውስጥ ባለ የወርቅ ማዕጠንት እንመስልሻለን። እንዲሁም ስምሽን በመጥራት የሰው ልጆችን ልመና ወደ ልዩ ሦስት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ያሳርጋሉ። የወገኖችሽንም ኃጢአት ታስተሠርይ ዘንድ ከአብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ተፈቅዶልሻል፤ ለሰዎች ልጆች የዘለዓለም ሕይወት ድልድይ ትሆኝ ዘንድ። የዓለም ሁሉ መድኃኒት ሆይ፣ ለምእመናን ወገኖችሽ መድኃኒታቸው ልትባይ ይገባሻል። ቅድስት ሆይ፣ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።
አንቺ የተባረክሽ ዕፅ ነሽ። የሕይወትና የድኅነት ዕፅ ነሽ። በገነት ውስጥ ባለ ዕፀ ሕይወት ፈንታ በዚህ ዓለም የሕይወት ዕፅ ሆንሽ። ፍሬሽም የሕይወት ፍሬ ነው። በሚወዱት በሚያውቁት በዓለም ሰዎች ዘንድ የሚሸት መልካም መዓዛ ያለው አበባ ካንቺ ታየ። ይኸውም ከርቤ ሚዓ ሰሊክ የተባሉ ሽቱዎች በልብሶችስ ላይ አሉ ብሎ በበገና ነቢዩ ዳዊት ትንቢት የተናገረልሽ ነው። አባትሽ ስሎሞንም ያፍንጫሽ መዓዛ እንደ ነጭ ዕጣን መዓዛ ነው አለ እኅቴ መርዓት ሙሽራዬ ሆይ፣ የታጠርሽ ተክል ነሽ። መንገድሽ የታጠረች ተክል የታተመች ጉድጓድ ናት። ከሽቱ ቅመም ጋር ሽቱ አለሽ። ቆዕ የሚባል ሽቱ ናርዶስ ከሚባል ሽቱ ጋር አለሽ። ናርዶስ የሚባል ሽቱ መጽርይ (ቀጋ) ከሚባል ሽቱ ጋራ አለሽ። ቀጽመታት ቀናንሞስ የተባሉ ሽቱዎች ከደጋ ሽቱዎች ጋራ አሉሽ። ከሽቱዎች ሁሉ የሚበልጡ ከርቤና አልው የሚባሉ ሽቱዎች ከነዚህ ሁሉ ሽቱዎች ጋራ አሉሽ። የገነት ፈሳሽ ሆይ፣ ከደጋ የሚፈስ የሕይወት ውኃ መገኛ ነሽ። ቅድስት ሆይ፣ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።
ሳይተክሏትና ውሃ ሳያጠጧት የለመለመች የአሮን በትር በቤተ መቅደስ ነበረች። ለካህናት ዝግጁ ያደረጋት ነበረች። አንቺም በቅድስናና በንጽሕና ጸንተሽ እንደ እርሷ በቤተ መቅደስ ኖርሽ። ከቤተ መቅደስም በክብር በታላቅ ደስታ ወጣሽ። በእውነት የሕይወት ፍሬ የሆነ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ካንቺ ተገኘ። ቅድስት ሆይ፣ መልአኩ መንፈስ ቅዱስ መጥቶ ያድርብሻል የልዑል ኃይልም ይጸልልብሻል ብሎ ነግሮሽ ነበርና። ቅድስት ሆይ፣ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።
ጸጋን የተመላሽና የደስታ መገኛ ሆይ፣ በልጅሽ ስም ላመንን ለእኛ ለወንዶችና ለሴቶች አገልጋዮችስ ትለምኝልን ዘንድ ይገባሻል። ይልቁንም ዐይኖቻቸው ብዙዎች ከሆኑ ከኪሩቤልና ክንፎቻቸው ስድስት ከሆኑ ከሱራፌል ግርማ የሚበልጥ የመወደድ ግርማ አለሽ። እነዚያ ፊታቸውን ይሸፍናሉ። እግሮቻቸውንም የትምእርተ መስቀል አምሳያዎች ናቸው። ከልጅሽ መለኮት ከሚወጣው እሳት ይድኑ ዘንድ። አንቺ ግን ለመለኮት ማደርያ ሆንሽ። የመለኮት ባሕርይም አላቃጠለሽም። ሙሴ እንጨትነቷ በእሳት ሳይቃጠል ያያት ዕፀ ጳጦስን መሰልሽ። ሁለተናው ፍጹም እሳት የሆነ የኃያላት ጌታ እንደ ዕፀ ጳጦስ አላቃጠለሽም። ለክርስቲያን ወገኖች በእውነት መመኪያ የሆንሽ አንቺ ነሽ። የአምላክ ልጅ ካንቺ ሰው ስለመሆኑም ባንቺ ከምድር ወደ አርያም የቀረብን ሆንን። በጸሎትሽ ለሚያምኑ ምሕረትን የምታሰጪ ሆይ! ለነፍሳችን ሕይወትን የምትለምኚ ነሽ። ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምኝልን። እርሱን አባቱን መንፈስ ቅዱስን በማመን በቀናች ሃይማኖት ያጸናን ዘንድ ይቅርታውንና ምሕረቱን ይሰጠን ዘንድ በምሕረቱ ብዛት ኃጢአታችንን ያሰሠርይልን ዘንድ የሁሉን ጌታ የወለድሽው ሆይ፣ ምስጋና ይገባሻል። ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለምም ምስጋና ክብር ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ይገባል አሜን።
ይዌድስዋ መላእክት
መላእክት ማርያምን በመንጦላዕት ውስጥ ያመሰግኗታል፤ ሐዳስ ጣዕዋ ላንቺ ምስጋና ይገባሻል እያሉ። መልአክ ማርያምን ቃልን ተቀበይው አላት ካንቺ ዘንድ ይመጣልና በማኅፀንሽም ያድራል። እንዴት ከድሀ ቤት አደረ? እንደ ምስኪን ከሰማያት ወርዶ የእርሷን ባሕርይ ባሕርዩ አድርጎ ተወለደ።
በስድስተኛው ወር ገብርኤል መልአክ ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ ተላክ። ካንዲት አገር ናዝሬት ገሊላ ከምትባል ለዮሴፍ እጮኛ ከሆነች ከድንግል ዘንድ። የዚች የድንግል ስሟ ማርያም ነው። መልአኩ ወደ እርስዋ ገብቶ እንዲህ አላት ደስታ ይገባሻል። እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ካንቺ ሰው ሆኗልና። ከሴቶች ይልቅ አንቺ ቡርክት ነሽ። ከቃሉ አነጋገር አይታ ደነገጠች። እንዲህም አለች እንዲህ ያለ የምስጋና እጅ መንሻ ይደረግልኛል? መልአክ እንዲህ አላት፥ ማርያም ሆይ አትፍሪ። ከእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና። እነሆ ትፀንሻለሽ ትወልጃልሽ። ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ። እርሱም ታላቅ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እግዚአብሔር አምላክም የዳዊት ያባቱን ዙፋን ይሰጠዋል። እርሱም በያዕቆብ ወገን ለዘላለሙ ይነግሣል። መንግሥቱም አያልፍም። ማርያምም መልአኩን እንዲህ አለችው፥ ይህ ነገር እንደምን ይሆንልኛል? እንዘ ኢየአምር ብእሴ። መልአኩም እንዲህ አላት፥ መንፈስ ቅዱስ ይጠብቅሻል። የልዑል ኃይልም ያድርብሻል። ይህ የሚወለደው ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ነው። እነሆ ኤልሳቤጥ ካንቺ ወገን የምትሆን ከሸመገለች ካረጀች በኋላ ፀነሰች። ልጅም አገኘች። እነሆ ይህ ስድስት ወር ሆነ። መካን ሲሏት ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። ማርያምም መልአኩን እንደ ቃልህ ይደረግልኝ እኔ ለእግዚአብሔር ባሪያው ነኝ አለቸው።
መልአኩ ገብርኤል ማርያም ድንግል ላንቺ ክብር ምስጋና ይገባሻል አላት። ወላዲተ አምላክ ምስጋና ይገባሻል፣ ቅድስት ነሽና ምስጋና ይገባሻል፣ የመለኮት ማደሪያ ነሽና ምስጋና ይገባሻል፣ የተሸለምሽ ድንኳን ነሽና ምስጋና ይገባሻል፣ የመላእክት እኅት የሕዝቡ ሁሉ እናት ነሽና ምስጋና ይገባሻል፣ የሁሉ እመቤት ማርያም ምስጋና ይገባሻል፣ የሁሉ ሰላም ማርያም ምስጋና ይገባሻል፣ ልዑል ማደሪያው ትሆኝ ዘንድ መርጦሻልና ምስጋና ይገባሻል፣ በወርቅ የተሸለምሽ የርግብ ክንፍ በብር ያጌጥሽ ምስጋና ይገባሻል፣ ጎኖችሽ በወርቅ አመልማሎ የተሸለሙ ላንቺ ምስጋና ይገባሻል፣ የምሥራቅ ደጃፍ የብርሃን እናቱ ላንቺ ምስጋና ይገባሻል፣ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበሪ ክብርሽ ከአድባራቱ ሁሉ ከፍ ከፍ ያለ ላንቺ ምስጋና ይገባሻል፣ ማርያም ሆይ ከተመረጡ የተመረጥሽ ከተከበሩ የተከበርሽ ላንቺ ምስጋና ይገባሻል።
ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ለምኝልን ያድነን ዘንድ ከአባቱ ምስጋና ከቅዱሳን መላእክቶቹ ጋር በመጣ ጊዜ ጻድቅንን በቀኙ ኃጥአንን በግራው ባቆመ ጊዜ እኛን ከሰማዕቱ እንጢፋኖስ ከመጥምቁ ዮሐንስ ከሁሉ ቅዱሳን ከሰማዕታትም ጋር ያቆመን ዘንድ ለምኝልን ለዓለመ ዓለም አሜን፤ ለዘለዓለሙ ይቅር ይበለን።
የአስተምህሮ ትምህርታዊ ጽሑፎች
ጸሎተ እግዝእትነ ማርያም: የእመቤታችን የማርያም ጸሎት
ጸሎተ ሃይማኖት: እንዲህ እናምናለን፤ እንዲህም እንታመናለን!
በሰላመ ቅዱስ ገብርኤል: በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እንልሻለን!
አቡነ ዘበሰማያት: አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር
አንቀጸ ብፁዓን ፲ – እግዚአብሔርን መምሰል : ይህን ብታውቁ፥ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ።
አንቀጸ ብፁዓን ፱ – በክርስቶስ መከራ መካፈል: ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።
አንቀጸ ብፁዓን ፰ – የጽድቅ ምስክርነት: ስለጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
አንቀጸ ብፁዓን ፯ – ፍጹም ሰላም: ሰላምን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።
አንቀጸ ብፁዓን ፮ – ንጹሕ ልቡና: ልበ ንጹሐን ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና።
አንቀጸ ብፁዓን ፭ – ምሕረትን ማድረግ: ምሕረትን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፥ ምሕረትን ያገኛሉና።
አንቀጸ ብፁዓን ፬- ለጽድቅ መትጋት: ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና።
አንቀጸ ብፁዓን ፫ – መንፈሳዊ የዋህነት: የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና።
አንቀጸ ብፁዓን ፪- እውነተኛ ንስሐ: የሚያዝኑ (የሚያለቅሱ) ብፁዓን ናቸው።
አንቀጸ ብፁዓን ፩ – ልባዊ ትህትና: በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው።
አንቀጸ ብፁዓን – የመንፈሳዊ ሕይወት መሠረቶች: መግቢያ
ሙዚቃና ዘፈን: የጽድቅ ሥራ ያልሆነ ሁሉ የኃጢአት ሥራ ነውን?
አሠርቱ ትዕዛዛት: በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያላቸውና ሊኖራቸው የሚገባው ተፈጻሚነት
ማኅበራዊ ሚዲያዎች በቤተ ክርስቲያን: የተለበጠ ስማቸውና የተገለጠ ግብራቸው
ደብረ ጽዮን ሀገረ እግዚአብሔር: የእግዚአብሔር ሀገሩ ወዴት ነው?
ዘመናዊ ጣዖታትና የጣዖት አምልኮ በቤተ ክርስቲያን
ልብ ወለዳዊ ስብከት: ውሸተኛ ከንፈር በእግዚአብሔር ዘንድ አጸያፊ ነው!
እውነተኛው የቤተ ክርስቲያን ድምፅ የትኛው ነው?
የመጽሐፍ ቅዱሷ ኢትዮጵያ: የተጠቀሰችባቸው ዐውዶች
ቅዱስ መስቀል: እግዚአብሔር ያገለገለባት መቅደስ ወዮ እንደምን ያለች ናት?!
ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መሥራት: ትኩረት የሚሹ ዐበይት ጉዳዮች
ምክሐ ዘመድነ: በእውነት የባሕርያችን መመኪያ አንቺ ነሽ!
መባ ስለሚያገቡ ሰዎች ጸልዩ: ጸሎት በገንዘብ አይሸጥም!
ራሳችንን አናታልል: ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም!
ክርስቲያናዊ አንድነትና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት
በየቋንቋው ማ(መ)ገልገል: ሐዋርያዊነትን ከብሔርተኝነት እንለይ!
ገንዘብና ክርስትና: አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን!
ዕቅበተ እምነት፡ ምዕመናንን በማንቃት ወይስ ሐሰተኞችን በማጥቃት?
ክርስቲያናዊ አንድነት: ማኅበራዊ ብዙኅነትንና ዘረኝነትን ማምታታት አይገባም!
ሴቶች በቤተ ክርስቲያን (ክፍል ፮): ክህነት ለምን ለሴቶች አይሰጥም?
ጾመ ኢየሱስ (ዐቢይ ጾም): በገዳመ ቆሮንቶስ በዲያብሎስ ተፈተነ
ሴቶች በቤተ ክርስቲያን (ክፍል ፭): የማስተማር ሚናቸው እንዴት ይታያል?
ሴቶች በቤተ ክርስቲያን (ክፍል ፬): በወር አበባ ጊዜና ከወሊድ በኋላ
ሴቶች በቤተ ክርስቲያን (ክፍል ፪): የፆታ እኩልነት
ሴቶች በቤተ ክርስቲያን (ክፍል ፩): የቅዱሳት አንስት (ሴቶች) አገልግሎት
በመንፈሳዊ አገልግሎት ካባ ግለሰባዊ ታዋቂነትና ዝነኝነት ሲገነባ
መንፈሳዊ አገልግሎትና የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም
ጾመ ነቢያት: አስተምህሮ፣ ስብከት፣ ብርሃንና ኖላዊ
ንግሥ እና ንግድ: የተቀደሰውን የማርከስ ክፉ ልማድ
ወርኃ ጽጌ፡ ክርስቶሳውያን ስለጽድቅ ይሰደዳሉ፣ ሄሮድሳውያን ጽድቅን ያሳድዳሉ!
“ቤተ ክርስቲያን መመሥረት”: ስሁትና ከፋፋይ ልማዶች ይታረሙ!
የክልል ቤተክህነት: ለዘላቂ መንፈሳዊ አንድነት ወይስ ለፖለቲካዊ ልዩነት?
ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና: አዕምሮውን ለብዎውን ሳይብን አሳድሪብን!
ዘማሪ ማስመጣት፡ በሐዋርያዊ ጉዞ ላይ የዘማርያን ሚና
የሐዋርያዊ ጉዞ መርሆች: ሰባኪ በመምጣቱ ምን ለውጥ መጣ?
ሰባኪ ማስመጣት: የዘመናችን ሐዋርያዊ ጉዞና ዓለማዊ ጓዙ
በልጆች መንፈሳዊ ትምህርት ‘የሰበካ ጉባዔ’ ኃላፊነት
ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት የማስተማሪያ ስልቶችና ዘዴዎች
በልጆች መንፈሳዊ ትምህርት የሚሳተፉ መምህራን ሊያሟሏቸው የሚገቡ መስፈርቶች ምንድን ናቸው?
ለልጆች መንፈሳዊ ትምህርት መሳካት ከወላጆች ምን ይጠበቃል?
ልጆቻችን መንፈሳዊ ትምህርትን በቋንቋቸው ወይስ በቋንቋችን ይማሩ?
ኑ ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠበቃ እንሁናት!
ኪዳነ ምህረት: የድኅነት ምክንያት ቃል ኪዳንሽ ባይኖር ኖሮ የጥፋት እሳት ባጠፋን ነበር!
የካህናት፣ የሰባክያንና የዘማርያን አለባበስ፡ ሁሉን በአግባብና በሥርዓት አድርጉ!
ስብከትና ፖለቲካ፡ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን!
ሰንደቅ ዓላማና ቤተክርስቲያን፡ የቄሳርን ለቄሳር!
ኖላዊ፡ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ
ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን፡ የሙታንን መነሣት ተስፋ እናደርጋለን የሚመጣውንም ሕይወት ለዘለዓለሙ!
ምስጢረ ቁርባን፡ የቤተክርስቲያን ምስጢራት አክሊል (ክፍል 2)
ምስጢረ ቁርባን፡ የቤተክርስቲያን ምስጢራት አክሊል (ክፍል 1)
በምስጢረ ሥጋዌ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችና ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ
ምስጢረ ሥጋዌ: ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው!
ምስጢረ ሥላሴ፡ የእግዚአብሔርን ፍጹም አንድነትና ልዩ ሦስትነት ማመን ከሁሉ ይቀድማል
ቅዱስ መስቀል፡ እግዚአብሔርን ለሚፈሩ የተሰጠ ምልክት!
መዳንም በሌላ በማንም የለም: ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ
ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር፡ ርስታችንን አጥብቀን እንያዝ (ክፍል ፬)
ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር፡ ርስታችንን አጥብቀን እንያዝ (ክፍል ፫)
ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር፡ ርስታችንን አጥብቀን እንያዝ (ክፍል ፪)
ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር: ርስታችንን አጥብቀን እንያዝ (ክፍል ፩)
ጾመ ሐዋርያት: የሐዋርያት ጾም የእኛም ጾም ነው!
ሰማዕታትና ሰማዕትነት: የሰማዕታት ደም የክርስትና ዘር ነው!
ትንሣኤ፡ በሦስተኛውም ቀን ነፍሱን ከሥጋው ጋር አዋሐዳት!
ስቅለት፡ ሕይወትን የሠራውን ከበደለኞች ጋር ሰቀሉት!
ኒቆዲሞስ (የዐቢይ ጾም ሰባተኛ ሳምንት)፡ የትህትና፣ የትጋትና የጽናት አብነት
ገብር ኄር (የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት)፡ ካህናት ብቻቸውን ወደ ገነት አይገቡም!
ደብረ ዘይት (የዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት)፡ ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንጠብቃለን!
መጻጉዕ (የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት): የዳነው ያዳነውን አላወቀውም!
ምኩራብ (የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት): የእግዚአብሔርን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ!
ቅድስት (የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት)፡ እግዚአብሔር ለቅድስና እንጂ ለርኲሰት አልጠራንም
ዘወረደ (የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት)፡ ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም
የሕይወት ውኃ እና ሳምራዊቷ ሴት: እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ለዘላለም አይጠማም።
አስተርእዮ ማርያም: ዕረፍትሽን እያሰብን ሰላም እንልሻለን!
ጾመ ሰብአ ነነዌ (‘ጾመ ዮናስ’): በፍርድ ቀን የነነዌ ሰዎች እንዳይፈርዱብን ምን እናድርግ?
ጥምቀተ ክርስቶስ: የፈጠረውን ሥጋ የተዋሐደ ጌታ በፈጠረው ውኃ ተጠመቀ
ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ወይስ ታደርሳለች?